Wednesday, November 6, 2013

ለፈጣሪዋ ብቻ የተተወችው ኢትዮጵያ



በመሐመድ ሐሰን
(ኢትዮ-ምህዳር ላይ የወጣ)

... እንደቀላጤ አክንባሎ ቁልቁል ባፍጢም ተተክለን
በእርኩስ አመዳይ ተበክለን
እንዲህ የትም ስንቀር እያየህ ዝም ካልክማ
እውነት… እውነት ከመንበርህ የለህማ!

(ከባለቅኔ ሙልጌታ ተስፋዬ "እውነት ከመንበርህ የለህማ!" ከተሰኘው ግጥም ላይ የተቀነጨበ፤ ምንጭ፡- የባለቅኔ ምህላ የግጥም መድብል፡፡)

ባለፈው ሳምንት ‹‹የኢትዮጵያ ፕሬስ ጣር!›› በሚል ያሰፈርኩት ጽሁፍ ላይ የ‹‹የኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ አዘጋጆች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተከፈተባቸው ክስ የተነሳ፣ ሐዋሳ ድረስ በመመላለስ ለተጨማሪ ስቃይ እና እንግልት እየተዳረጉ እንደሆነ ገልጬ ነበር፤ ጋዜጣዋ ለገበያ በቀረበች ማግስት እለተ እሮብ ጥቅምት 20 ቀን 2006 ዓ.ም፣ የ‹‹የኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ አባላት (ስራ አስኪያጁ ሚሊዮን ደግነው፣ ዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ እና ከፍተኛ አዘጋጁ ኤፍሬም በየነ) በቀጠሯቸው መሰረት ሀዋሳ ቢገኙም፣ የተሰማው ዜና ግን የፍርድ ቤት ውሏቸውን ብቻ የሚያትት አልነበረም፤ ከወደ ሐዋሳ የተሰማው አሳዛኝ ወሬ ሶስቱ የ‹‹የኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ ባልበረቦችን ይዛ ትጓዝ የነበረችው ባጃጅ የመገልበጥ አደጋ እንደደረሰባት  የሚገልጽ ነበር፡፡
በወቅቱ የደረሰው አደጋ እና ከክሱ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ብዙዎችን ያነጋገረ ከመሆኑ ባለፈ፣ በኤፍሬም ላይ የደረሰው ከፍተኛ የጉዳት መጠን ግን ይበልጥ ልብን የሚሰብር ነበር፤ ሁለቱም እግሮቹ ምንም እንደማይንቀሳቀሱ ሰማን፤ በተጨማሪም የሳንባ ችግር ገጥሞት ወደ ማገገሚያ ክፍል መግባቱ ተወራ፤ እራሱን ችሎ በእግሩ መቆም ለተሳነው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ደግሞ እንዲህ ያለው ተጨማሪ ጉዳት ይበልጥ የሚያሽመደምደው ነው፤… ከትርፍ ይልቅ የቀጣዩን ህትምት የማተሚያ ቤት ክፍያ ለማሟላት ለሚፍጨረጨሩ የግል ፕሬሶች፣ በኤፍሬም ላይ የደረሰው አይነት ጉዳት እና ለውስብስብ ህክምናው የሚያስፈልገው ወጪ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› የሚሉትን ብሂል የሚያስታውስ ነው፡፡ እንዲህ ያለው እውነት የ ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች በርካታ የሀገሪቱ ነጻ ፕሬሶችም የሚጋሩት ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ ስቃይ ቦሃላ፣ ቅዳሜ እለት ለቀጣዩ ስራቸው ወደ ቢሯቸው ጎራ ያሉት የጋዜጣዋ አዘጋጆች፣ ከወደ ለገጣፉ በመጣባቸው ሌላ ክስ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በወቅቱ ለስራ ጉዳይ ወጣ በማለቱ ከእስር የተረፈው ዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ የጋዜጣውን ስራ ከጨረሰ ቦሃላ ሰኞ እለት ቃሉን ለመስጠት ባልደረባው ሚሊዮን ደግነው ወደታሰረበት ለገጣፉ ቢያመራም ለእስር ተዳርጓል፤ እስከ ቀጣዩ አርብም (ምናልባትም ከዛ በላይ) በእስር ለመቆየት ተገደዋል፡፡…   
ለዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ መነሻ የሆነኝ የኔ የግል እምነት ሳይሆን፣ ከኤፍሬም ጉዳት ጋር በተያያዘ ከባልደረባዬ ጌታቸው አንደበት የሰማሁት ቃል እና በቃሉ ውስጥ የተጋባብኝ ጥልቅ ስሜት ነው፤ እናም ከሱ የተዋስኩትን እውነት ሳጤነው የሀገሪቱ ሀቅ ሆኖ ተሰማኝ፤ ከዛማ እንደሚከተለው ላሰፍረው ወደድኩኝ፡፡
ባለፈው አርብ ነው፤ ኤፍሬም በኮሪያ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ህክምናው ተካሂዶለታል፤ በተወሰነ መልኩም እግሩ የመንቀሳቀስ ተስፋ አሳይቷል፤ ወዳጆቹም ‹‹ወደፊት በእግሩ ቆሞ መሄዱን እንጃ›› ከሚል ቀቢጸ ተስፋ ሻል ባለ መልኩ እምነታቸውን ጥለዋል፤ ነገር ግን ማንም ስለነገው በእርግጠኝነት መናገር አይችልም፤ ኤፍሬም ለተጨማሪ ህክምና ወደ ውጪ መሄድ ሊኖርበትም ይችላል፤… ይህ ማለት ግን ሁኔታው በሙሉ እንደማወራው ቀላል ነው ማለት አይደለም፤ ቀጣዩ እርምጃ ከመታሰቡ በፊት፣ ዛሬ ላይ የ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ ባለቤቶች  ከአቅማቸው በላይ የሆነውን የህክምና ወጪ መሸፈን ይኖርባቸዋል፤… በሁኔታው እጅግ በጣም ጭንቅ ጥብብ ያለው ጌታቸው ስለ ጉዳዩ ባነሳሁበት ጊዜ ውስጥን በሀዘን በሚያላውስ ድምጸት የሰነዘረው ቃል ቢኖር አንድ ብቻ ነው- ‹‹ጸሎት! (ዱዓ!)›› የሚል፡፡
የህመሙ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ ጌታቸው የገንዘብ አቅሙንም ለፈጣሪ የተወ ይመስላል፤ እናንተ አንባቢዎቼ ‹‹የአንድ ጋዜጣ ባለቤት መሰል የገንዘብ ችግር ውስጥ መግባት አለበት ወይ?፣ መሰል ችግርንስ ለፈጣሪ ማቅረብ ተገቢ ነውን?፣ ፕሬሶቻችን ምን ያህል ችግር ውስጥ ቢኖሩ ነው…?፣…›› የሚሉ መሰል ጥያቄዎችን ትሰነዝሩ ይሆናል፤ እኔ ግን እጠይቃለው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ለፈጣሪ ያልተሰጠው ነገር ምንድነው? ለምን›› ስል፡፡
እንደኔ እምነት የሆነውንም ያልሆነውንም ነገሯን ሁሉ በፈጣሪዋ ላይ የምትጥል ሀገር የታደለች ናት ብዬ አላስብም፤…በምድር ላይ ስንኖር እኛው ልናሟላቸው (ልንወጣቸው) የሚገቡ ተግባራት ይኖራሉ፤… የታደሉ ናቸው ብዬ በምላቸው ሀገራት ላይ ፕሬሶች የህልውና ስጋት የሌለባቸው፣ ፍትህ የሰፈነባቸው፣ የሚተገበር ህግ ያላቸው፣ የመረጡት ስርዓት የሚያስተዳድራቸው፣ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው የተከበረላቸው፣ መልካም አስተዳደር ያሰፈኑ፣ ዜግነታቸው የተከበረላቸው፣…ወዘተርፈ ናቸው፡፡
ወደ ዛሬዋ ሀገራችን ኢትዮጵያ በምንመጣበት ጊዜ እያንዳንዱ ጉዳያችን ምድራዊ እልባት ተነፍጎት በ"ሪፈር" ለፈጣሪ እና ለፈጣሪ ብቻ የተላለፈ ይመስላል፤ በየቦታው የሚታዩ ችግሮች እና የሚሰሙት ምላሾችም ይህንኑ በደንብ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ለፈጣሪ ቅርብ እንደሆኑ ከሚታመነው ቤተ-እምነቶች ብንነሳ በውስጣቸው የሰፈነውን አስተዳደራዊ በደል፣ የመንግስት ጣልቃገብነት፣ የተለያዩ አካላት ጥቃቶች፣ የእምነት ነጻነት መነፈግ፣… ስንመለከት ተገቢውን ምድራዊ ፍትህ ተነፍገው የፈጣሪቸውን ሰማያዊ ፍትህ በመማጸን ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡…
አንድ ሰው ከቤቱ እንደወጣ አሸባሪ ተብሎ ያለመታሰሩ ዋስት ለፈጣሪ የተተወ ይመስላል፤ በአንደኛው ቀን ውሏችንም በፖሊሶች ቆመጥ ያለመቀጥቀጥ እድላችን በአስተማማኝ የህግ ጥላ ስር ያለ አይደለም፤…ወደ እስር ቤት ጎራ ቢባል የእስረኞች የመጠየቅ፣ በአግባቡ የመያዝ፣… ህጋዊ መብታቸው እየተሸራረፈ አቤት ባይ ምድራዊ ዳኛ ከጠፋ ሰነበተ፡፡…
በአሁን ጊዜ ሀገሪቱ ላይ ዜጎች እምነታቸውን እያጡባቸው ከመጡ ተቋማት ውስጥ ፍርድ ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው፤ እንዲህ ያለው አካሄድ ደግሞ ለአንዲት ሀገር ወደ አደጋ ማምራት ዋነኛ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው፤…ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዞ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነታቸውን ከመጣል ይልቅ ፊታቸውን ወደ ፈጣሪ ቀድመው ያዞሩ ዜጎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ ፍርድ ቤቶች እና ቤተ-እምነቶች ቦታ የተቀያየሩ ሁሉ ሊመስለን ይችላል፡፡…
በየጊዜው እሳት እየሆነ የሚመጣው የኑሮ ውድነት አልገፋ ያላቸው፣ በቀን ሁለቴና ሶስቴ በልቶ ማደር ያቃታቸው ዜጎች፣ሁሉ ነገራቸውን ለፈጣሪያቸው ተናዘው የሰቆቃ ኑሮ የሚገፉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡…
የበሽታ ወረርሽኙ መፍትሄ አጥቶ ከጤና ባለሙያዎች ይልቅ ከፈጣሪ መድሀኒቱን የሚለምኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ናቸው፤…እዚህች ጋር ባለፈው ወደ ድሬ ደዋ ጎራ ባልኩበት ወቅት የገጠመኝን ነገር ላነሳው እፈልጋለው፡፡
ድሬ ላይ እግር ጥሎት ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ጎራ ያለ ሰው በእርግጠኝነት ወዳጁ፣ ቤተሰቡ አልያም ጎረቤቱ በአንድ ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ተይዞ ያገኘዋል፤ በሽታው እስከ አሁንም ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ ሆኖ የድሬን ህዝብ እያሰቃው ይገኛል፤ የወባ አይነት ስሜት ያለው ወረርሽኝ ምንነቱን ለማወቅ ለተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራ ደሞች ወደሌላ ቦታ(ናዝሬት ይመስለኛል) እንደተላኩ አንድ ሀላፊ ከሀያ ቀን በፊት በአንድ ሬድዮ ጣቢያ ላይ ሲናገሩ ያደመጥኩኝ ቢሆንም፣ ዛሬም ግን የወረርሽኙ መድሀኒት እና ምንነት አልታወቀም፤ ሐላፊው በቆይታቸው በቂ ባለሙያ እንደተዘጋጀ ቢናገሩም፣ እውነታው ግን የተለየና ህዝቡም በየጤና ጣቢያው በስርዓት የሚያስተናግደው ባለሙያ አጥቶ በመንከራተት ላይ ይገኛል፡፡
በነገራችን ላይ የጤና ባለሙያዎች መድሐኒት እና ስያሜ ያጡለት ይህ በሽታ በድሬዎች "ሸዋንዳኝ" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፤ ምክንያታቸው ደግሞ የበሽታው (ወረርሽኙ) ዋነኛ መለያ ሰውነትን ስብርብር ማድረግ በመሆኑ፣ ከሸዋንዳኝ አዲሱ ‹‹ስብርብር አለብኝ ጉልበቴ…›› ከሚለው ዘፈን ጋር በማያያዛቸው ነው፡፡    
እንግዲህ በድሬደዋ ላይ የታየው ችግር ስለሌሎች ተደራሽነት ስለሌላቸው የገጠር አከባቢዎች የሚነግረን እውነታ ምን ያህል እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡…ግን ታዲያ ሁሉም እምነታቸውን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይልቅ በፈጣሪ ላይ መጣልን መርጠዋል፡፡         
ኢትዮጵያ ላይ የስርዓት ለውጥ እንኳን በምርጫ ካርድ ሊመጣ እንደማይችል ያመኑት ካላመኑት በብዙ ሺህ እጥፍ ይበልጣሉ፡፡… ሀገሪቱ በማን እና እንዴት እየተመራች እንደሆነ እንኳን በዜጎቿ በግልጽ ከማይታወቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ የመብራት፣ የታክሲ፣ የኔትወርክ፣ የውሀ፣…ችግሮች እንኳን በሐላፊዎቹ አቅም ከመቀረፍ በላይ የሆኑ ናቸው፡፡…
በሀገራቸው ካንገሸገሻቸው ኑሮ ይልቅ ነፍሳቸውን ሳይሞቱ ለፈጣሪ ሰጥተው በየበረሀ ወድቀው የሚቀሩ ዜጎችን የሞት ዜና መስማት ብርቃችን ከሆነ ሰነባበተ፤ ብዙዎቹ ከወንድም እህቶቻቸው ሞትና ስቃይ የመማሪያ ፋታ እንኳን የላቸውም፤ ፈጣሪን ብቻ በመተማመን አስፈሪውን የበረሀ ስደት እና ስቃይ ይገቡበታል፡፡…
በየተቋማቱ፣በየመስሪያ ቤቱ፣ በየቀበሌው፣…ያለው አሰራር ኢ-ፍትሀዊነት በሰው ሀይል አልፈታ ብሏቸው ለፈጣሪ አቤት ብለው የሚያማርሩ ኢትዮጵያውያን በሽ ናቸው፡፡… በመልካም አስተዳደር እጦት የዜግነት መብቶቻቸውን የተገፈፉ እና እንደ ዜጋ በሀገራቸው ላይ በነጻነት መኖር ያልቻሉ ዜጎች የመጨረሻ አማራጫቸው ያደረጉት ፈጣሪን ነው፡፡…
በዚህች ሀገር ላይ ከመንግስት ባሻገር ህግ የማይገዛቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም፤ ስራ ሰርተው የላባቸውን ገንዘብ የሚከለከሉ ወይም እንደሚከፈላቸው በእርግጠኝነት የማያወሩ ወገኖቻችን በየቦታው ማግኘት ከባድ አይደለም፤ ስራ ለመቀጠር ችሎታ መስፈርት የሚሆንበት ዘመን ክፉኛ እየተመናመነ የመጣ ይመስላል፤ ሁሉም ጉዳዩን ለመለኮታዊው ሀይል ብቻ አቤት ማለትን እንደብቸኛው አማራጭ ወስደውታል፡፡
እንዲህ ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ ለፈጣሪ የመስጠት አካሄዳችን ለፈጣሪ ካለን ቅርበት እና ፍራቻ ይልቅ፣ ሀገሪቱ ላይ ባለው የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣… ስርዓት ላይ ያለን እምነት ምን ያህል ተሸርሽሮ እንዳለቀ አመላካች መስሎ ይሰማኛል፡፡ እንዲህ ያለውን ስሜት የሚጋሩ ዜጎች ቁጥር ከፍ እያለ በመጣ ቁጥር ደግሞ፣ አንዲት ሐገር እንደ ሐገር መልካም አስተዳደርን እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን አስፍና የመቀጠል ህልውናዋ አጠያያቂ እንደሚሆን ለመናገር ግዴታ ነብይነትን አይጠይቅም፡፡…
ከአዲስ አበባ እስከ ሐዋሳ የተዘረጋው የ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ የክስ ሂደት እና መከራም አሁን ባለበት ሁኔታ የተቋጨ አይደለም፤ ኤፍሬም ተጨማሪ ህክምናዎች እና ወጪዎች ያስፈልጉታል፤ ክሱም በሀዋሳ መታየቱን እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱ ወስኖ ለህዳር 10 ቀጥሯቸዋል፤ ያኔ የሚመጣው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እና በሌሎች ባልደረቦቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለው ተጨማሪ ስቃይ እና እንግልትም ለፈጣሪ የሚተው ይመስላል፡፡ ለማንኛውም ለባልበረባዬ ኤፍሬምም ሆነ ለኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ የበዛ ምህረትን እናፍቃለው፤ ኤፍሬምን ለመታደግ የተጀመረው ርብርብም ከዳር እንዲደርስ ምኞቴንም ጥሪዬንም ማስተላለፍ እፈልጋለው፡፡
     አቤቱ!  
"ኃይል ያንተ ናት" ብዬ
ፀለይኩ አመሰገንኩ
አንተም በመንበርህ ቆየህ ተመለከትኩ
"ከክፉ ሰውረን" ብዬ ስጠይቅህ
ይሄው ዘመን ቆጠርኩ…
መልስህን ተነፈግኩ!
(ዓለም ፀሐይ ወዳጆ- ምንጭ የማታ እንጀራ)     

No comments:

Post a Comment