Thursday, September 26, 2013

ኢህአዴግ እዳ አለበት! ፪ ርዕዮታዊው መንፈስ እንደ ‹‹ቻይኒዝ ባምቡ›› ፩



በቅድሚያ፡-  ይህ ጽሁፍ በትላንትናው (መስከረም 14 ቀን 2006 ዓ.ም) በ ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ ላይ ርዕሱ እና ጥቂት ነጥቦች በአዘጋጆቹ ግላዊ ፍላጎት ተነካክተው የወጣ ሲሆን፣ ትክክለኛው እና እኔ የጻፍኩት ግን ይህ ነው፡፡ ያለፈውን ሳምንትም ሆነ ይህንን ጽሁፍ በ ‹‹ብሎጌ››  www.yemohagets.blogspot.com or www.yemohagets.wordpress.com ላይ በመግባት መጎብኘት እስከ አሁን ድረስ በኢህአዴግ ያልተገደበ መብታችሁ ነው፡፡ 








 በአገዛዝ ከሄድን እኔ የኢህአዴግ ልጅ ነኝ፤ ከኢህአዴግ በፊት ስለነበረው የትኛውም ስርዓት ከንባብ ያለፈ ምንም ዓይነት ትውስታ የለኝም፤ ትምህርቴም፣ንባቤም፣ግንዛቤዬም፣የስራ ህይወቴም፣… በኢህአዴግ ዘመን ተጠንስሶ በኢህአዴግ ዘመን ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በአንድ ስርአት ውስጥ ከትምህርት ዘመን እስከ ስራ ህይወት! ኢህአዴግ እና ኢህአዴግ ብቻ! ሀያ ምናምን አመት  ሙሉ ኢህአዴግ! አይደለም እንደ ኢህአዴግ ካለው ስርዓት ጋር ከማንም ጋር ቢሆን ይሰለቻል! ያንገፈግፋል!... አንዳንድ ሰዎች ‹‹ያለፈውን ስርዓት ስለማታውቅ እኮ ነው የምታማርረው፤…›› ይሉኛል፤ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ያለፉትን ስርዓቶች ከንባብም ሆነ ከሰዎች ምስክርነት ልረዳው እችላለው፤ ነገር ግን የአሁኑን ስርዓት ለመተቸት ቀደምቶቹን ማወቅ ግዴታም አስፈላጊም አይደለም፤ ስርዓቱም ይህቺን ምክንያት በማቅረብ ነው እድሜውን ሊያራዝም የሚፈልገው፡፡
 ኢህአዴግ መመዘንና መለካት ያለበት በራሱ ዘመን እና እኩያ ስርዓቶች ነው፡፡ ስለዚህ እኔም የደረስኩበት የነጻነትና የዴሞክራሲ ዘመን ከኢህአዴግ ጋር አልገጥም ቢሉኝ ኢህአዴግን እየተቸሁት ነው፤ የስርዓቱ ጭካኔ ከፍ ሲልም ‹‹ኢህአዴግ እዳ አለበት›› በማለት እዳዎቹን፣ፍዳዎቹን፣ግፎቹን፣…እዘረዝራለው፡፡ ታዲያ ዝም ብዬ ከመሬት በመነሳት ሳይሆን እድሜዬ በአይኔ ያሳየኝን ግፎች ነው የምዘረዝረው፤ እነሱ ግን ዘወትር ሁሉንም ሰው ለመፈረጅ የሚያጠልቁት መነጽር አንድ በመሆኑ፣ እኔንም ታላላቆቼንም ‹‹የደርግ (ያለፈው ስርዓት) ርዝራዥ›› በማለት ጅምላዊ ፍረጃ ያካሂዳሉ፡፡ የተለየ ድምጽ ማስተናገድ ስለማይፈልጉም ሲብስባቸው ወደ ቃሊቲ ይወረውሩናል፤ እኔም ሳምንት በርዕዮት መነሻነት የቃሊቲ ግፎችን ነበር በተወሰነ መልኩ ለማሳየት የሞከርኩት፤ ታዲያ በቃሊቲ ደርሶ መልሴ ገና ብዙ የማወጋችሁ ኢህአዴጋዊ ግፎች ይኖሩኛል፡፡ ዛሬ ግን የርዕዮትን ጉዳይ በማንሳት እሷንና በሷ ውስጥ መቼም ተከፍሎ የማያልቀውን የኢህአዴግን እዳዎች በተግባር እንቆጥራለን፡፡ በቅድሚያ ግን ርዕሴን በመጠኑ ላብራራ፡፡      
  መስከረም 25 ቀን 2002 ዓ.ም ለንባብ በበቃችው ‹‹አዲስ ፕሬስ›› ጋዜጣ ላይ፣ እኔና ርዕዮት ዓለሙ ከታላቁ የአደባባይ ምሁር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ጋር ቆይታ አድርገን ነበር፡፡ ወቅቱ ከወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ዳግም እስራት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ትኩሳት የነበረበት ነው፤ ለዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ደግሞ ትክክለኛው ሰው ዶክተር ዳኛቸው ሆኖ ስላገኘነው ከሱ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ ለማድረግ ወደድን፡፡ ታዲያ በመጀመሪያ የሰነዘርንለት ጥያቄ፡-
 ‹‹በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የእስር ጉዳይ ላይ ጠንካራ ጽሁፎችን ከጻፉ ሰዎች መካከል አንዱ አንተ መሆንህ ይታወቃል፤ ይህን እንድታደርግ ምክንያት የሆነህ ምንድነው? የመታሰሯን ምክንያትና የአያያዟን ሁኔታስ እንዴት ትገልጸዋህ?›› የሚል ነበር፡፡ እሱም የሚከተለውን ምላሽ ነበር የሰጠን፡-
  ከሁሉ አስቀድሞ የብርቱካን እስራት የህግ ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ የብርቱካን እስራት ከሞራልና ከፖለቲካ የመነጨ የአይበገሬነት ጥያቄ ነው፡፡ እኔ አሜሪካን ሀገር እያለሁኝ የሁለተኛው የኢራቅ ወረራ ጊዜ የፈረንሳይ መሪ ፕሬዝዳንት ዣክ ሺራክ ነበሩ ይመስለኛል፤ እና ፕሬዝዳንት ቡሽ ወረራውን እንዲደግፉ ለማግባባት ሲሞክሩ ፣ ‹‹ይሄ የኢንተርናሽናል ህግን የሚጋፋ ስለሆነ አልተባበርም፤›› ብለው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ፣ ፓሪስ ያሉ ዘፋኞች (የኪነት ሰዎች) አንድ የሚገርም ዘፈን ያወጣሉ፡፡ ‹‹The man who said no!›› (እምቢ ያለው ሰውዬ) የሚል ዘፈን በማቀንቀን የአድናቆት ስያሜ ሰጧቸው፡፡
ብርቱካንን ከተለያየ አንጻር መፈረጅ ይቻላል፤ ሆኖም ግን ከሞራል አንጻር ያለችበትን ሁኔታ ስናየው፣ እሷ ደግሞ የኛዋ እምቢ ያለችው ሴት (she is a woman who said no!) ናት፡፡ ብርቱካንን… ይሄ ትልቅ የሞራል አይበገሬነት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የፖለቲካል እምቢተኝነትን ያመጣል፡፡
እንግዲህ እስራቷ በአንድ በኩል የዜጎች እምቢተኝነትን፣ በሌላ በኩል መንግስት የዜጎችን እሺታና ተቀባይነትን ለማስፈን የሚደረግ ፍልሚያ ነው፡፡ እስራቷ አንገት በማስደፋትና አንገት ቀና በማድረግ ፍልሚያ መካከል በመሆኑ፣ ከብርቱካን ባሻገር እምቢተኝነትን እና አይበገሬነትን ለመስበር የተካሄደ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ኢህአዴግ ‹‹ሁሉንም አንገት አስደፍቻለው ቀና ያለ አንገት ‹‹ክሪሚናል›› አደርጋለሁኝ›› ከሚል ‹‹ኢምፐልስ›› የተነሳ ነው፤ ‹‹እኔ እምቢ አልባልም›› ከሚል የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል እምቢተኝነት ነው፤ አንድም ድምጽ ቶለሬት አለማድረግ ነው፡፡…
ለመደምደም፣ ከጀርባው ከፖለቲካ አንጻር የመጠየቅን፣ እምቢ የማለትን፣ የመተቻቸትን፣ እና የእምቢተኝነትን መንፈስ ሰብሮ፣ የተቀባይነትን፣ የተሸካሚነትን፣ እና የይሁን ባይነትን መንፈስ ለማስረጽ የተወሰደ እርምጃ ነው፡፡
ዶክተር ዳኛቸው ከእስሯ ጋር በተያያዘ ሌሎች በርካታ ሰፋ ያሉ ትንታኔዎችን ከሰጠን ቦሃላ፣ በመጨረሻም ከእስር ቤቱ አያያዝ ጋር በተገናኘ ላነሳንለት ጥያቄ የሰጠንን ምላሽ እንመልከተው፡-
  በኔ አመለካከት የብርቱካን የእስር ቤት አያያዝ ከላይ የጠቀስነውን የሞራል እና የፖለቲካ አይበገሬነት መንፈስ ለመስበር የሚወሰድ እርምጃ ነው፤ የብርቱካን የእስር ቤት አያያዝ ከላይ የጠቀስነውን ሞራል እና የፖለቲካ አይበገሬነት መንፈስ ለመስበር የሚወሰድ እርምጃ ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ብርቱካን መሰረታዊ የሆነ ለእስረኞች የሚሰጥ መብት የተነፈጋት እስረኛ ናት፡፡… ወዳጅ ዘመድ ሊጠይቃት በማይችልበት ሁኔታ … መብቷን ተነጥቃለች፡፡ በሀገራችን የረዥም ዚጌ ታሪክ ነገስታቱ ተቀናቃኝ የሚሏቸውን ልኡላን፣ መሳፍንት፣ እውቅ የሆኑ የጦር አበጋዞችን ራቅ ያለና የተገለለ አምባ ላይ እንደሚያስሯቸው ሁሉ፣ ብርቱካንንም በትልቁ እስር ቤት ውስጥ ትንሽ አምባ ፈጥረው ከእናቷ እና ከጨቅላዋ ልጇ በቀር ማንም ሰው እንዳይጠይቃት አድርገዋል፡፡ አምባ ስላላገኙ እንጂ እሷንም አምባ ላይ ወስደው ቢያስሯት ይመርጡ ነበር፡፡ ይህ አይነት ድርጊት በመጀመሪያ ብርቱካንን በስነ ልቦና ለመስበር መሆኑን ለማወቅ ስነ-ልቦና ተመራማሪ መሆን አያስፈልገንም፡፡ ይህ የስነ-ልቦና ጦርነት (psychological war) ከጀርባው የእምቢተኝነት እና የአይበገሬነት መንፈስ ከሷ ላይ ሲጠፋ፣ የተቀረው ማህበረሰብ ጋር ያለውንም የመቋቋም መንፈስ አብሮ ለመጨፍለቅ ነው፡፡ በመሆኑም አላማቸው ብርቱካንን እንደ ግለሰብ ሳይሆን ብርቱካናዊውን መንፈስ ለመጨፍለቅ ነው፡፡
ለዶክተሩ ምጡቅ ሀሳብ እጅ ነስቻለው! ሀሳቡ በወቅቱ የነበረውን መንፈስ በመግለጽ ብቻ የማይገደብ ከመሆኑ ባሻገር፣ ዛሬንም ጭምር የመግለጽ አቅም ያለው ትንቢት ነው! ዛሬ ላይ ስላለው ስርዓትም ይነግረናል፤ በድጋሚ ለዶክተሩ ምጥቀት እጅ ነስቻለው፡፡ ይህ የዶክተር ዳኛቸው ንግግር በርዕዮት ልክ የተሰፋ መሆኑን ለማወቅ፣ ማስረጃዎቹን ከጽሁፌ ውስጥ በሂደት ታገኙታላችሁ፡፡ በተለይ እኔው አጽንኦት የሰጠሁባቸውን ነጥቦች ልብ እንድትሏቸው እፈልጋለሁኝ፡፡ ስለዚህም ርዕዮታዊ መንፈስ የሚለውን ስያሜ ከዶክተር ዳኛቸው ሀሳብ ላይ ተውሻለሁኝ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንኑ ርዕዮታዊ መንፈስ በ‹‹ቻይኒዝ ባምቡ›› መስዬዋለሁኝ፤ ፓውሎ ኮሊሆ (Paulo coelho) የተባለው ታላቁ ብራዚላዊ ጸሀፊ (በተለይ ዘ አልኬሚስት በሚለው የ1988 ስራው ይታወቃል)፣ ‹‹አሌፍ›› ሲል በሰየመው ሌላኛው ድንቅ መጽሀፉ ውስጥ ‹‹ቻይኒዝ ባምቡ›› (Chinese bamboo) የሚባል ዛፍ አለ፤ ይህ ዛፍ አምስት ዓመት ሙሉ ምንም ሳይታይ ውስጥ ለውስጥ ነው የሚያድገው፤ ልክ በአምስተኛ ዓመቱ ላይ 25 ሜትር ወደ ላይ ተምዘግዝጎ ከሁሉም ዛፎች ልቆ ይታያል፡፡ አሁን ላይ እያወራሁላት ያለችው ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ የፈጠረችው ርዕዮታዊው መንፈስም ዝም ብሎ ወፍ (ኢህአዴግ) ዘራሽ ሳይሆን፣ እንደ ‹‹ቻይኒዝ ባምቡ›› ለዘመናት ውስጥ ለውስጥ ሲገነባ ቆይቶ ነው አደባባይ የወጣው፡፡ ‹‹እንዴት?›› ለሚለው ጥያቄ፣ አሁንም ምላሹ የሚገኘው ዘለግ ብሎ ከሚቀጥለው ጽሁፍ ውስጥ ነው፡፡
ርዕዮት ማናት?
  በቀጥታ ርዕዮት አሁን ያለችበትን ጉዳይ ከማንሳቴ በፊት፣ በተወሰነ መልኩ ርዕዮትን መግለጹ ስለሷ የሚነግረን ብዙ ነገር ይኖራል፡፡ ርዕዮትን ለመረዳትና ስለርዕዮት ማንነት ለማወቅ ዘለግ ያለ ትውውቅ እንዲሁም ጥብቅ ወዳጅነት ግዴታ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ርዕዮት ግልጽ ከመሆኗ ባለፈ ተግባሯ ማንነቷን በደንብ እንድንረዳው ያደርገናል፡፡ ለምሳሌ የርዕዮት እና የኔ ትውውቅ የሚጀምረው ሐምሌ 2001 ዓ.ም ‹‹አዲስ ፕሬስ›› ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት ተቀጥረን መስራት ከጀመርን ቦሃላ ሲሆን፣ በደንብ ለመግባባት ብዙም ግዜ አልፈጀብንም፡፡ የስራዋ ጥንሬ ከርዕዮት ዝምታና እርጋታ ውስጥ የሚፈልቅ አይመስልም፤ ሁሌም በጨዋታ መሀል አድማጭ ነች፤ የማወቅና ከሰዎች ሀሳብ ለመጋራት ያላት ጉጉት አስገራሚ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ስትሰራ ያላየ በፍጹም ስራው የሷ መሆኑን መረዳት ይከብደዋል፡፡ አንድ ጽሁፍ ለመጻፍ ሶስትና አራት ቀናትን የምታባክነው በየቤተ መጽሀፍቶች እዞረች መረጃ በማሰባሰብ እና ስለጉዳዩ ያላትን እውቀት በማዳበር ነበር፡፡ ርዕዮት ካላት የተልፈሰፈሰ አካሏ በተቃራኒ ከአለት የጠነከረ አቋምና ስብዕና አላት፡፡
  የርዕዮት ምግባር እና ስራ ስለዘመኑ ጋዘየጠኞችም ጭምር ብዙ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ የሷ ትኩረት ዘወትር የስራዋን ጥራት ማስጠበቅ እንጂ አጉል ዝና እና ገንዘብ ፈላጊ አልነበረችም፡፡ በንባብ የዳበረች የሀሳብ ባለቤት መሆኗንና ለንባብ ያላትን ጥልቅ ፍቅር የሚያዉቁ ሁሉ ‹‹ከርዕሰ አንቀጽ እስከ ስፖርት›› የሚለው ስያሜዋን ያስታውሳሉ፡፡ ዛሬ ላይ ከሀሳብ ይልቅ ግለሰብ ማጥቂያ፣ ማንነትን መገንቢያ፣ ተራ ፕሮፋይል መዘክዘኪያ፣ ገንዘብ መሰብሰቢያ፣…እየሆነ የመጣውን ‹‹ጋዜጠኝነት›› ሳስብ ርዕዮትን አጥብቄ እናፍቃታለሁ፡፡
  ርዕዮት ምንም ዓይነት የግል ጥቅሟን እያሰበች የምትሰራ ጋዜጠኛ አይደለችም፡፡ መነሻዋም መድረሻዋም እውነት እና ሀገር ነው፡፡ ስለ ርዕዮት እየጻፍኩት ያለው ነገር አንዳችም ግነትና አጨብጫቢነት የማይታይበት እውነት ነው፡፡ በምድር ላይ ከማንም በላይ በእርግጠኝነት የማወራላት ሰው ነች ርዕዮት ዓለሙ ማለት፡፡ የሚያውቋት ሁሉ ክፋት ካልጠለፋቸው ይህንን መሰክራሉ፡፡ በእርግጥ ርዕዮት እንደ ብዞዎቹ የስራዋን ያህል አልተራገበላትም፡፡ እኔንም ጨምሮ ብዙዎቻችን ልናወራላት አልፈቀድንም፡፡ ርዕዮትን ከአራጋቢዎችም ከእስሩም በላይ እውነቱ ነው በሂደት እያደር ዋጋ የከፈላት፡፡ አሁንም ግን ቢሆን ስራዋንና ጽናቷን በማየት ትክክለኛው ዋጋ ተሰጥቷታል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ርዕዮት ክፍያ ትቀበል የነበረው አብዛኛውን ስራዋን ካቀረበችበት ‹‹አዲስ ፕሬስ›› ጋዜጣ ብቻ ሲሆን፣ ለሌሎቹ በሙሉ ግን ትሰራ የነበረው ያለምንም ክፍያ ነበር፡፡ ርዕዮት ይህን ታደርግ የነበረው ብር ኖሯት አይደለም፤ ይልቅስ ርዕዮት ደሞዟ ላለባት ቤተሰባዊና ማህበራዊ ሀላፊነት አልበቃ ብሏት፣ አንዳንዴ ካስተማረች ቦሃላ በእግሯ ትመላለስ ነበር፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ አልፋም ቢሆን፣ በማስጠናት የምታገኘውን ገንዘብ  በትምህርት ቤቱ ውስጥ ችግረኛ ልጆችን እየረዳች ታስተምርበት ነበር፡፡
ርዕዮት በፍጹም ለገንዘብ ብላ በህሊናዋ ተደራድራ አታውቅም፤ ብዙ ጋዜጠኞች አንድ ስልጠና ላይ ከተገኙና አበል ከተከፈላቸው፣ በማግስቱ የሚሰሩትን ዘገባ አስተውላችሁ ከሆነ ከአበሉ ጋር የተመጣጠነ ሙገሳ ወይም ትችት ነው፡፡ ርዕዮትን በተመለከተ አንዱን ብቻ ላስታውሳችሁ፤ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ተቋም ናዝሬት ላይ የሁለት ቀን ስልጠና ያዘጋጅና ርዕዮት እንድትሳተፍ ትላካለች፤ እንደተመለሰች የጻፈችው ጽሁፍ ‹‹እምባ ጠባቂ ኢትዮጵያን እምባዋን ሊያብስላት ወይስ ሊያላቅሳት??›› ስትል ነበር ሞጋች ብዕሯን ያነሳችው፤ ስራዋን ያነበባችሁ ታስታውሱታላቹ፡፡ ታዲያ ጽሁፉ በወቅቱ ከመንግስት ወገን ብዙዎችን ያስቆጣና ምላሽም ጭምር ለጋዜጣችን ተልኮ የወጣበት ወቅት ነበር፡፡              
  ከሁሉ በላይ ደግሞ ርዕዮት አዛኝ እና ቅን ናት፡፡ ርዕዮት የአራዊቶች ውጪ ማደር ሀዘንና ብርድ የሚያጋባባት፣ ከብቶች ሲታረዱ ማየት የማትችል ብሎም ስጋቸውን እንኳን ለረዥም ግዜ ላለመብላት ወስና የቆየች፣… ሰዋዊ ባህሪ ከሚባለው በላይ ጎልቶ የሚታይባት ቡቡ ፍጡር ናት፡፡ ከቤተሰቧ እና ከአከባቢዋ የወረሰችው ማንነትም ቢሆን ለእውቀቷ እና ለስብዕናዋ ያደረገው አስተዋጽኦ እጅግ በጣም ጠንካራ የሚባል ነው፡፡ ስለ ርዕዮት ከዚህም በላይ ብዙ ብዘ!... ነገር ማለት ቢቻልም እሷን ሚገልጽልንን አንድ ጥሩ ማሳያ ከእጮኛዋ ስለሺ ሀጎስ ጽሁፍ ውስጥ አንድ ነጥብ ልጥቀስ እና ወደ ቀጣይ ነጥቦች ልለፍ፡፡
ስለሺ ሀጎስ ነሀሴ 29 ቀን 2005 ዓ.ም ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ ላይ ‹‹የፀረ-ሽብር ዐዋጁ ለምን ይሰረዝ?›› በሚል የጻፈው ጽሁፍ ላይ ርዕዮትን ሲገልጻት ‹‹ርዕዮት ዛሬ በእስር ላይ የምትገኝ ጋዜጠኛ ናት፡፡ ሁለት ሰዎች ተጯጩኽው ሲነጋገሩ ቆማ ማድመጥ የማትችል ፍጹም ሰላማዊ ሰው ነበረች፡፡›› ነው ያለው፤ ይሄ ንግግር ለማሳመር ሰፈረ ሀሳብ አይደለም፤ እውነቱ ይሄው ነው፤ ርዕዮት ማለት ይህቺው ናት በቃ! እንደተባለው የርዕዮት ጣቶች ‹‹ከእንጀራ እና እስክሪብቶ›› ውጪ ይዘው አያውቁም፤ የማማስያ ዱላም ቢሆን!      
የርዕዮት እስርና የኢህአዴግ ኪሎ
  እኔ በግሌ አንድም ቀን ቢሆን የኢህአዴን የሽብር ክስ (በተለይ የጋዜጠኖችን እና ፖለቲከኞችን) ሙሉ በሙሉ አምኜበት አላውቅም፡፡ ዘወትር ክሶች በተፈበረኩ ቁጥር በርካታ ጥያቄዎችን አነሳለው፡፡ ‹‹እንዴት›› ስልም በርከት ያሉ ጥያቄዎችን እጠይቃለው፡፡ ክሱ ርዕዮት ጋር ሲደርስ ደግሞ በእርግጠኝነት ሙሉ በሙሉ የኢህአዴግን ልክ ነበር የነገረኝ፡፡ በጣም ቀለለብኝ! ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለታሰሩት ከምንግዜውም በላይ አዘንኩ፡፡ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ይበልጥ ስለኢህአዴግ ማንነት ነገረኝ፡፡ እውነትም በኢህአዴግ ስርዓት ‹‹ማሰብ ያስቀጣል!›› የመባሉ እውነታ ተገለጠልኝ፡፡
የመከላከያ ምስክር ጭምር በመሆን የፍርድ ሂደቷን ተከታትዬው ስለነበር፣ የዳኝነት ስርዓቱም ቀለለብኝ፤ በጥይት ምትክ ‹‹በህግ የመቁላቱ›› ሚስጥርም ይበልጥ ገባኝ፡፡ ምንም ዓይነት አሳማኝ ማስረጃ ሳይቀርብ፣ ምስክርም ሳይደመጥ፣ ፍትሀዊ ክርክር ሳይካሄድ፣ መብቷ ሳይከበርላት፣ የሀገሪቱ ሚዲያዎችና መሪዎች ከሚያወሩት የተለየ ክስ ተደምጦ፣ወዘተ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈባት፡፡ አሁንም ከቀደመው የስለሺ ጽሁፍ ላይ በዕለቱ የተነበበውን አስገራሚ ፍርድ ልጥቀስ፡-                                                                   በአዲስ አበባ አንዳንድ የአደባባይ ቦታዎች ላይ በቀይ ቀለም ‹‹መለስ በቃ›› ሚል አመጽ የሚያነሳሳ ጽሁፍ ሲጻፍ፣ ቦታው የት እንደሆነ ተከታትላ በማንሳት መረጃ አስተላልፋለች፡፡ ታዛቢዎች ባሉበት ከእርሷ ኢሜይል ፕሪንት ተደርጎ የወጣ ‹‹ሶሊዳሪቲ ሙቭመንት ፎር ኒው ኢትዮጵያ›› የሚል ጽሁፍ የተገኘ ሲሆን ይህ ደግሞ ከህግ ውጪ የሚንቀሳቀሰው ሀይል የሚያራምደው አቋም ስለሆነ፣ በመረጃ ማስተላለፍ ላይ ይህ ሲታከልበት ይግባኝ ባይ የፈጸመችው የጋዜጠኝነት ሥራ ነው የሚል ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡
የቀረቡ ማስረጃዎች ይግባኝ ባይ የሽብርተኛ ድርጅት አባል ናት ለማለት የሚያስችል ባይሆንም፣ ለሽብርተኛ ድርጅት የሚደርሱ መረጃዎችን በማቀበል፣ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ የተሳተፈች ስለመሆኑ የሚያሳዩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡…››
  እንግዲህ የራሳችሁን ትዝብት ከውሳኔው መውሰድ ነው፡፡ ሌላው የኢህአዴግን ኪሎ ያቀለለብኝ ጉዳይ ከርዕዮት ጋር በተያያዘ የሚሰጧቸው እርስ በርስ የተምታቱና በቅጥፈት የተሞሉ ሸፋፋ  ሀሳቦች ናቸው፡፡ ‹‹ማረሚያ›› ቤቱ ከሰሞኑ እየወሰደ ያለው እርምጃ እና ባለስልጣናቱም የሚያስተጋቡት ሴራ ቀደም ብሎ የተጠነሰሰ ነበር፡፡ ማረሚያ ቤቱ በሚያዚያ ወር 2005 ዓ.ም ለሪፖርተር ጋዜጣ ጽፎ እንዳነበብነው፣ ርዕዮትን ‹‹ያለምንም ጥረት እና ልፋት ዝናን ለማግኘት ከታራሚዎችና ከጥበቃ ሀይሎች ጋር›› እንደምትጋጭና እነሱም ‹‹የዲሲፕሊን እርምጃ ›› ለመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ ሌሎች ሚስጥሮችንም አሾልኮልን አንብበናል፡፡ መቼም እንዲህ ያለው ተቋማዊ ቅጥፈት አይን ያወጣ ብቻ በመባል የሚታለፍ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለውን ፍረጃ እንግዲህ ከርዕዮት ስብዕና ጋር አዛምዶ ማየቱ ምላሹን ይሰጠናል፡፡ ርዕዮት ባለፈው ሳምንትም በተወሰነ መልኩ ለማንሳት እንደሞከርኩት ጠባቂዎቹ እንደትንኝ አፏ ላይ ተለጥፈው ‹‹ አንቺን ማሰር ሳይሆን መግደል ነበር! አንቺ አትንቀሳቀሺ! ጠያቂዎችሽ ይንቀሳቀሱ1…›› በሚል ከሰው ልጅ የመቻል አቅም በላይ ሲተናኮሷት እንኳን፣ ያ ቀይ ፊቷ ብስል ቲማቲም መስሎ እራሷን ከመጉዳት ባለፈ አንድም ቀን ስትናገራቸው ተስተውሎ አያውቅም፡፡ ታዲያ እምነቷን እንዲነኩባት ትፈቅዳለች ማለት አይደለም፤ እሱን ማድረግ ስላልቻሉም ነው ስቃዩዋን የሚያበዙትና ባልተገባ መንገድ የሚፈርጇት፡፡
  ከዚህ በተረፈ ርዕዮትን ከከንቱ ዝና ፈላጊነት ጋር ማቆራኘቱ እንደማይሰራ ሌላ ማሳያ ሊሆነን የሚችለው፣ በእስር ቤቱ ውስጥ የሚደርሱባትን እጅግ በጣም አስቀያሚ የሚባሉ በደሎቿን፣ አይደለም ለዜና ፍጆታነት ለቤተሰባዊ ወግ እንኳን አታቀርበውም፤ ብዙ የሚታዩ በደሎችን እንኳን በተደጋጋሚ ትደብቅ ነበር፡፡ ሌላው ርዕዮት ዋነኛውን የመከራ ግዜ ስታልፍ ከእጮኛዋ እና ቤተሰቦቿ በቀር ብዙዎቹ ከጎኗ አልነበሩም፡፡ በፍርድ ቤት ይፋ ያወጣችውን ስቃይዋን እንኳን የሚዘግበው ሚዲያ እንዳልነበር ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ከዚህ ቦሃላም ቢሆን እያደር መከራቸው ቢያበረታት እንጂ አላልፈሰፈሳትም፡፡
  የባለስልጣናቱ ጉድ ብዙ ነው፤ የጸረ-ሽብር ህጉን ከነ አሜሪካ እንደቀዱት በተደጋጋሚ ይነግሩናል፡፡ እርምጃቸውን የሚኮንኑት እና እነሱ አሸባሪ ብለው ያሰሯቸውን ‹‹ጀግና›› ብለው የሚሸልሙትም እነ አሜሪካ ናቸው፤፤ ስለተሸላሚዎቹና ሸላሚዎቹ ሲጠየቁ ደግሞ ሰበብ የማያልቅባቸው ጎበዞች፣ አይናቸውን በጨው አጥበው ‹‹መጀመሪያ ተልዕኮ ሰጥተው ያሰማሯቸዋል፣ ሲነቃባቸው እና ሲታሰሩ ደግሞ ይሸልሟቸዋል፡፡›› ይላሉ፡፡ እኔ የምለው አሜሪካ ነች እንዴ ‹‹መለስ በቃ›› የሚል ፎቶ ያስነሷት? እኚህ ሰውዬ መቼም በእውቀታቸው የማይቀናባቸው የለም¡¡
  መች በዚህ ይበቃና እነ ‹‹ሼም›› የለሽ ደግሞ በየግዜው የአቋም አክሮባት ሲሰሩ አይጣል ነው! በእውነት እንዲህ ባለው የመዋሸት ብቃታቸው አለመጎዳት ብቃታቸውን ያሳያል፡፡ ‹‹ርዕዮት የታሰረችው መሰረተ ልማት ልታወድም ስላሴረች ነው1›› ልብ አድርጉ ፍርድ ቤታቸው እንኳን ይህንን ክስ አልጠቀሰባትም፡፡ ቀጥለው ደግሞ ‹‹ ርዕዮት አምደኛ እንጂ ጋዜጠኛ አይደለችም፡፡›› አሉ፡፡ ልብ አድርጉ እንግዲህ፣ እኚህ ሰው የህግ ባለሙያም ነበሩ አሉ! እንዲሁም መንግሰትን የሚያብጠለጥል ጋዜጣ ባለቤትም ጭምር ነበሩ! አሉ፣ነበር፣… ነው እንግዲህ! አሁን ደግሞ ከሰሞኑ እየተወሰደባት ያለውን እርምጃ ቀደም ብሎ በማረሚያ ቤቱ እንዲጠነሰስ ካደረጉት የዲሲፕሊን እርምጃ ጋር በማያያዝ ሌላ ፋውል ሰሩ፡፡ ፋውል! ፋውል! ፋውል !.... ነሱ፡፡ ሳምንት የሚገነቡት እስር ቤቶች ደርሰው ካልገባን ርዕዮታዊውን መንፈስ መፈተሸችንን እንቀጥላለን፡፡
የበረሃ ጩኽት
ሰርቶ ካላሳየ     
ሀቁን ካላወጋ
ሰምቶ ካልፈረደ
እያየ ካልዳኘ
‘ራርቶ ካልገራ
አስቦ ካልመራ
አልሆነም ፈጣሪ አልሆነም አለቃ
ለስሙም አልበቃ¡¡
አልሆኑም ፍጡራን፣አልሆኑም አማኞች፣
ሁላቸው-ሁላቸው የውሀ ኩበቶች፤
በባዶ አንጀታቸው፣ ሰሚ በሌለበት፣ ጸሎት ፈብራኪዎች፡፡
(ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ  ሚያዚያ 1981)

                         

Wednesday, September 25, 2013

አንድነቶች እና ፖሊሶች በጋራ ያሰሩት ወዳጄ

በመሐመድ ሐሰን


መቼም ርዕሱን ቀድማችሁ ያያችሁ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ! ሲጀመር ኢትዮጵያ ውስጥ ፖሊስ ከተቃዋሚዎች ጋር መች ተባብሮ ያውቅና ነው?...›› አይነት ጥያቄ ትጠይቁ ይሆናል፡፡ እናንተ ልክ ናችሁ፤ የኔም ርዕስ ግን ትክክል ነው፡፡ አንድነቶች እና ፖሊስ በጋራ ባደረጉት የየራሳቸው ርብርብ የልብ ወዳጄን አስረውታል፡፡ ‹‹እንዴታ?›› ካላችሁ ነገሩ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
ሳንዶካን ደበበ የተባለው ወዳጄ ትላንት (መስከረም 14 ቀን 2006 ዓ.ም) እግሩ ዘወትር ከማይጠፋበት አራት ኪሎ ጥሎታል፡፡ ታዲያ ወዳጄ በተገኘበት አራት ኪሎ አንድነት ፓርቲ ለመስከረም 19 ለጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ እያደረገባቸው ካሉ አከባቢዎች አንዱ በመሆኑ ቅስቀሳቸውን አጧጡፈውታል፡፡ ይሄኔ በህዝብ አገልጋይነት ስም የኢህአዴግ አገልጋይ ሆነው የቀሩት የአራት ኪሎ ፖሊሶች፣ የአንድነት አባላትን እና የቅስቀሳ ቡድኑን ለማደናቀፍ እስከ መስከረም 19 መታገስ አልሆነላቸውም፡፡ ከቀስቃሾቹ የሚወጣው ድምጽም ሚያገለግሉትን ፓርቲ ክፉኛ ‹‹ያስቀይምብናል›› ብለው የሰጉም ይመስላሉ፤ ስለዚህ አላስቻላቸውምና ዘው ብለው የለበሱትን ልብስ በማይመጥን ፍጥነት እና አኳሀን ቅስቀሳውን አገቱት፡፡
በአከባቢውም ውዝግብ ተፈጠረ፤ መንገደኛውም ‹‹እንዴት ነው ነገሩ ፖሊስ እንዲህ ያለውን ተግባር መፈጸም አለበት እንዴ?›› ሲሉ ጠየቁ፤ ለራሳቸውም ‹‹ሼም! ነው!›› የሚል ምላሽ መስጠት ጀመሩ፡፡ ፖሊሶች ግን ‹‹መስሚያችን ድፍን ነው! ከኢህአዴግዬ ውጪ አይሰማንም፤ አናዳምጣችሁም!›› ያሉ ይመስላል የአንድነት አባላትን ሰብስበው ለእስር አዘጋጇቸው፡፡ ወደ እስር ቤት ከማምራታቸው በፊት ግን በዙሪያቸው ከተኮለኮለው አላፊ አግዳሚ ውስጥ የተወሰነውን ሰው ለአንድነቶች መመልመል ፈልገዋል፤ እነማን? አሳሪዎቹ- ፖሊሶች፡፡ ይሄኔ ነው ታዲያ ከጥግ ቆሞ ትዕይንቱ መስጦት በሞባይል ካሜራው ሲያስቀር የነበረው ወዳጄ በፖሊሶቹ የዓይን ካሜራ ውስጥ የገባውና በአባልነት የተመለመለው፡፡ እሱ በትዕይንቱ ሲመሰጥ እነሱ ደግሞ በሱ ቀድመው ተመስጠው ኖሮ ቀላቀሉት፡፡ ‹‹ምነው?!›› ቢል ማን ሊሰማው? ‹‹መስሚያ የለንም! አንድነት ነህ ብለናል አንድነት ነህ በቃ!›› ብለው ቀላቀሉት፡፡ ካሉ እኮ አሉ ነው፤ በዛ ላይ ደግሞ በእለቱ ሌላ ሰው በማሰር ሀራራቸው አልወጣላቸው ይሆናል፣ ቁጥሩን በርከት አድርገው ወደ እስር ቤት ይዘዋቸው ላፅ አሉ፡፡
የአንድነት ፓርቲ ቢሮ በየትኛው አቅጣጫ እንደሆነ እንኳን በውል የማያውቀው ጓዴ በፖሊሶቹ ምልመላ ለዕለቱ ሀያ ምናምን ደቂቃ አባል እንዲሆን ተገዷል፡፡ አዚህ አገር እኮ መሆንም አለመሆንም ችግር ነው፤ ሁሉም ነገር የሚወሰነው በነሱው ነው፤ ‹‹አሸባሪ፣ አክራሪ፣ ወዳጅ፣ጠላት፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ሙሰኛ፣…›› እያሉ የሚፈርጁትስ በራሳቸው ተነሳሽነት አይደል! ወዳጄ ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለህም!›› ሊሉህ ሁሉ ይችሉ ነበር፤ ለመለስተኛው ደግነታቸው ምስጋና ማቅረብ ይገባሀል¡¡
እናላችሁ ይህ ቅጭጭ ያለው ወዳጄ (ታዲያ ልቧ ተራራ ነው፤ ዋ! ብዙ ካማረራችሁት ያው ነው…ሰው በስጋ፣ በሀብት፣ በጎሳ፣… አትመዝኑ፤) አብረውት በታፈሱ የአንድነት አባላት ከፍተኛ እና የተጠናከረ ርብርብ (እሱ እንደውም ተጠናከረ ሂበርተ ነው ያለው) ከነሱ ጋር እንዳልሆነ ለፖሊሶቹ ነግረዋቸው ሞባይሉ ከተፈተሸና ጉዳዩ ከተጣራ ቦሃላ ሊለቀቅ ችሏል፡፡
እዚህ ሀገር እስር ቀላልና በየትኛውም ሰዓት የፈለገው ነገር ጠለጥፎብን ልንታሰር የምንችልበት ድራማ ብዙዎቹ ሳይገባቸው አልቀረም፡፡ ከዚህ ወዳጄ የእስር ቤት ቆይታ ቦሃላ በ ‹‹ፌስ ቡክ›› ገጹ ላይ ብዙዎች ያሰፈሩት የስላቅ ምላሽም ይህንኑ ነው ያረጋገጠልኝ፡፡ እኔ ግን ሁኔታውን እንደነገረኝ ‹‹የሚጣራም የሚያጣራም በሌለበት ሀገር ላይ ይህቺን ታህል ደቂቃ ብቻ ታስረህ መፈታትህ እድለኝነትህን ያሳያልና በፍጥነት ሎተሪ ሞክር፡፡›› ነበር ያልኩት፡፡ እውነቴን እኮ ነው የፈለጉትን ነገር ሊሉት ይችሉ ነበር፤ መረጃ ቢያጡ እንኳን ፣‹‹ወደፊት አሸባሪ መሆኑ ስለማይቀር ከወዲሁ በቁጥጥር ስር አውለነዋል፤›› ብለው ለዛ ማነው ኢቴቪ ውስጥ ቁጭ ብሎ ፊልም የሚቆራርጠው? አዎ! ለሱ ሰጥተው ዶክመንተሪ ሊሰሩብህ ይችሉ ነበር፡፡
በመጨረሻ ላይ ያካፈለኝ ሀሳብ ግን ለኔ በጣም ወሳኝ መስሎ ታይቶኛል፡፡ ቃል በቃል ያለኝን ሳሰፍረው ‹‹… እኔ ግን አንድነቶች በፍቅራቸው አስቀንተውኝ፣ በአንድነታቸው አስረውኝ፣ ከእስር ቤት አስፈትተውኛል፤›› የሚል ነው፡፡ ከዚህ አባባል ውስጥ ወዳጄ በፖሊሶች የተሳሳተ ድርጊት አማካይነት ለአንድነቶች ሁለቴ መመልመሉን እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ በስህተት ቦሃላ ግን ለማያውቀው ነገር በማጋለጥ፡፡ እኔ ግን አሁንም ይበልጥ ማስረገጥ የምፈልገው ‹‹…አንድነቶች በፍቅራቸው አስቀንተውኝ፣ በአንድነታቸው አስረውኝ፤…›› ሲል የገለጻት ነጥብ ላይ ነው፡፡ ወዳጄ ለምስክርነት ያስቀመጣት ነገር የምር ሙሉ ለሙሉ በፓርቲው ውስጥ የሚታይ ከሆነ እሰየው ነው፤ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበትም እንዲህ ለምስክርነት የሚበቃው እንደስማቸው አንድነታቸው እና ፍቅራቸው ነው፡፡ የምር ሀገር የምትለወጠውም በሁሉም ፓርቲ ውስጥ ወዳጄ የገለጸው አንደነት እና ፍቅር ሲኖር ነው፤ አለበለዚያ ግን ‹‹ሁሉም ነገር ከንቱ ነው! የከንቱ ከንቱ…›› ወዳጄ አንተው ጨርሰው፡፡
በመጨረሻ ግን በወቅቱ እስር ቤት ለነበራችሁት እና ወዳጄ ምስክርነቱን የሰጠላችሁ እንዲሁም ወዳጄን በፍቅራችሁ እና አንድነታችሁ ላሰራችሁት የአንድነት አባላት ትክክለኛውን ነገር ስለያዛችሁት ቪቫ! ብያለው፡፡
የመጨረሻ መጨረሻ ህሊናዬ እንዲህ ሲል ሞገተኝ ‹‹ አንድነት እና ፍቅር የሚጠነክረው በእስር ግዜ ብቻ ይሆን እንዴ?›› እኔ እንጃ እያሰላሰልኩት ነው፡፡ እናንተ ግን መልስ ካላችሁ ወዲህ በሉን፡፡              
            

Wednesday, September 18, 2013

ኢህአዴግ እዳ አለበት! (ቃሊቲ ደርሶ መልሶች) ፩ ርዕዮትና ርዕዮታዊው መንፈስ በቃሊቲ



ቃሊቲ ግቢ ብቻ ሳይሆን ሀገር ነው፤ የአንድ ሀገር እውነታዎችና ሰዎቿ ሁሉ በዚህ ይገኛሉ፤ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ብቻ አይደለም ቃሊቲ ማሰቃያ፣ ማመናጨቂያ፣ ማጉላያ፣ ማዋከቢያ፣ መበቀያ፣ … ጭምር ነው፤ ግቢው በጣም ሰፊ ነው፤ በስፋቱ ልክ ብዙ እውነታዎችን ታጭቋል፡፡ በአንድ ወቅት ርዕዮት ዓለሙንና ፈትያ መሀመድን ጠይቀን ስንወጣ፣ አንድ ሰው (የፈትያ ጠያቂ ይመስለኛል) ‹‹አንተ ይህ ግቢ እኮ በጣም ሰፊ ነው፤ ከእስር ቤትም በላይ ነው፤ ለምን ሌላ ነገር አይሰሩበትም? ወይ ደግሞ በተካኑበት የመሬት ችብቸባ በሊዝ ይሽጡት፤›› አለኝ፤ እኔም ‹‹ምን ይሰሩበታል! የሚሰራን ሰው እያመጡ ያኮላሹበት እንጂ!›› ስል መለስኩለት፡፡ ቃሊቲ እርግጥ ነው ሰፊ ነው፤ በስፋቱ ልክ ከክፋት ባሻገር አንዳንድ ደግነቶችንም በዙሪያው አቅፏል፡፡ በክፋቶቹ ውስጥ ደግሞ ኢህአዴግ ከፍሎ የማይጨርሳቸው እዳዎች እዚህም እዛም  አፍጠው ይታያሉ፡፡ እኔ እውነታዎቹን ባየሁና በሰማሁ ቁጥር ‹‹ኢህአዴግ እዳ አለበት!›› እንድል የሚያስገድዱኝ ናቸው፡፡ ርዕሱ እንዳይንዛዛብኝ ብዬ እንጂ ‹‹ ኢህአዴግ እዳ! ፣ፍዳ!፣ ግፍ!፣ ጡር!፣… አለበት!!›› ብል ምንኛ ሀሳቤን በገለጸልኝ!  ለማኝኛውም እነዚህን የኢህአዴግ ግፎች፣ ፍዳዎች፣ እዳዎች፣ጡሮች፣… ከዛሬ ጀምሮ፣ ‹‹ኢህአዴግ እዳ አለበት!›› በሚል አብይ ርዕስ ስር የተለያዩ ንዑስ ርዕሶችን እየሰጠን የቃሊቲውን እውነት እንጨዋወተዋለን፡፡
ዛሬ ግን ላስቀድመው የነበረውን ክፍል በአግባቡ ማስኬድ ተስኖኛል፡፡ ከሰሞኑ በቃሊቲ እነ ርዕዮት ዓለሙ፣ ፈትያ መሀመድ፣እማዋይሽ፣… ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍና እነሱም እየወሰዱት ያለው እርምጃ፣ እጅግ በጣም ቀደም ብዬ ልጽፍበት ያሰብኩትን ‹‹ርዕዮታዊ መንፈስ…›› በተረጋጋ ሁኔታ እንዳሰፍረው የሚያደርግ አይደለም፡፡ ሰሞነኛው ቃሊቲ ከርዕዮታዊው መንፈስ ጽሁፌ አናጥቦኛል፡፡ በዛሬው ጽሁፌ ትንሽ (ኽረ በጣም!) ልዘባርቅ እችላለው፤ ሲፈጸም የከረመው ጉዳይ ያልተለመደ ባይሆንም፣ መረን ለቀቀ! በዛ! ከአንድ መንግስት አይደለም መንግስት ባለበት ሀገር ላይ እንኳን ሊፈጽሙት የሚከብድ ውንብድና ነው!
መቼም እኔ ዛሬ ስዘባርቅ የምንደው የጽሁፍ ህግ እንደነሱ ሁሉን ገዥ የሆነውን የሀገር ህግ ከመናድ አይከፋም፤ ግፋ ቢል ጽሁፌ ስነ ጽሁፋዊ ውበቱን ቢያጣ ነው፤ ግፋ ቢል በቋንቋ ምሁራኑ ቢተች ነው፤… ምንም ቢሆን ለዛሬ ግድ የለኝም፤ ዛሬ የምዘባርቀው ብዙ እውነት በመኖሩ፣ እሱኑ ማስተላለፉ ላይ አተኩራለው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ወቅቱ እኮ በደምፍላት ጭምር የሚያጽፍ ነው!›› ሲሉኝ፣ አይገባኝም ነበር፤ አሁን ግን እኔ እራሱ ደምፍላት ውስጥ እንዳለው ይሰማኛል፤ ታዲያ ምክንያታዊነት ገደል ገብቶ ወገቤን ይዤ እሞጣሞጣለው ማለት አይደለም፤ እንዲያማ ከሆነ፣ ከነሱ በምኑ ተሻልኩት? ለማንኛውም ቀጠልኩኝ፡፡
የነ ርዕዮትን የእስር ቤት አያያዝ ሳስብ አሜሪካዊው ሻለቃ ናዲል ሀሰን ድንገት ትዝ አለኝ፡፡ ይህ አሜሪካዊ ወታደር የሰራው ወንጀል እጅግ በጣም ሰቅጣጭ የሚባል ነው፤ አይደለም ሲፈጽሙት ሲሰሙትም ያማል፡፡ ይህ ወታደር በፈረንጆቹ ህዳር ወር 2009 ዓ.ም ላይ አብረውት የሚሰሩ 13 ወታደሮችን ተኩሶ ይገላል፤ በተቀሩት 32 ወታደሮች ላይ ደግሞ የግድያ ሙከራ ይፈጽማል፡፡ ታዲያ በእስር ላይ የሚገኘው ናዲል፣ ከተያዘበት 2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም ያለፈው ወር ድረስ፣ ከ 300.000 የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚጠጋ ደሞዙ ሲከፈለው ነበር፤ ህክምናን ጨምሮ በእስር ቤት ውስጥ ያሉ መብቶቹን በሙሉ ይጠቀማል፡፡ እንዲህ ያለው እውነት ለኛ ኢትዮጵያውያኑ አጃኢብ ነው!
መቼም ‹‹እኛ ጋርስ እንዴት ይሆን?›› ብሎ መጠየቅ በራሱ በብዙሀኑ ስነ ልቦና ላይ እንደመጫወት ይቆጠራል፡፡ አስታውሳለው ርዕዮት አይደለም ከታሰረች ቦሃላ ሊከፈላት፣ መታሰሯ እንደተሰማ ነው ቀድማ የሰራችበትን ደሞዝ እንኳን የከለከሏት፡፡ አስታውሳለው ‹‹ፍርድ ቤት›› ጉዳይዋን ከሰዓት ልንከታተል፣ ጠዋት ላይ ሟቹ ጠቅላያችን ፓርላማ ተገኝተው ‹‹አሸባሪ›› እያሉ ሲጠሯቸው ነበር፡፡ አስታውሳለው ርዕዮት በህመም በምትሰቃይበት ወቅት ወደ ህክምና እንኳን ሊወስዷት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ርዕዮት ትምህርቷን እንዳትማር ሰበብ ሲያመርቱና እርስ በርሱ የሚጋጭ አስተያየት ሲሰጡባት ነበር፤ ቀደም ብሎም እዛው ማረሚያ ቤቱ ውስጥ እራሳቸው ከሳሽ እራሳቸው መስካሪ በነበሩበት ሁኔታ ከሰዋት ነበር፤  ሌላም ሌላም…፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ ይኽው እንደሰማነው መብቱን ብቻ በአግባቡ ከሚጠቀመው አሜሪካዊው ሻለቃ በተቃራኒ፣ የኛዋ ኮ/ል በከባድ ወንጀል ተይዘውም ስልጣናቸውን እንደተሸከሙት ከአጥሩ ውስጥ ሆነው የነ ርዕዮትንም መብት በመንጠቅ ጭምር ተጨማሪ ግዙፍ ወንጀሎችን ይሰራሉ፤ ወይስ እነዚህ ሰዎች ወደ ወህኒ የሚወርዱት በተቀያሪነት ለማሰቃየት ነው? ያደለው ከነ ስልጣኑ ይታሰራል! ለነገሩ እዚህች ሀገር ላይ ሞት እንኳን መች ከስልጣን ይለያል?!
እኔ የምለው? እነዚህ ባለስልጣኖች መቼ ነው ቆይ መፈራራታቸውን የሚያቆሙት? ከውጪ እሰከ እስር ቤት ድረስ በጉያቸው እንደሸሸጓቸው ነው፡፡ ታሳሪ ባለስልጣናቱም የፓርቲያቸውን ስስ ብልት ስለሚያውቁ ይመስላል ዛሬም በማሽቃበጥ ምህረትን ይሻሉ፤ ፍርድ ቤት በቆሙበት አጋጣሚ ለፓርቲያቸው ከንቱ ውዳሴ በማቅረብ አፈጻጸምን ያማርራሉ፤ ደግሞ እኮ ኮሎኔሏ ‹‹አንቺን ብሎ ጋዜጠኛ!...›› አሏት አሉ፤ የፓርቲያቸው ልሳኖች ‹‹ወንጀለኛ›› ብለው ሲሏቸው ያጠየቁትና ጉዳዩን በሚገባ የዘገቡላቸው የርዕዮች የስራ አጋሮች መሆናቸውን ማን በነገራቸው!
እነ ርዕዮት በሴትየዋ፣ በእስር ቤቱ ጠባቂዎች፣ በታሳሪ ሰላዮች፣ በእስር ቤቱ ቢሮክራሲ፣… መብታቸው ተነፍጎ መሰቃየታቸው ሳይበቃ፣ ርዕዮት ጭራሽ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ እንዳይጠይቃት ተከለከለች፡፡ ይሄኔ ነው እንግዲህ የተከማቹት ስቃዮች ጫፍ የደረሱትና እሷንም ለረሀብ አድማ እርምጃው ያበቃት፡፡ ታዲያ ስቃዩ ከርዕዮት ባሻገር በሌሎችም ላይ ይፈጸም ነበርና ርዕዮታዊውን መንፈስ በመከተል፣ ሌሎች የተወሰኑ ሴቶችም የረሀብ አድማውን ከአዲሱ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ ይህን ጽሁፍ እስካስገባሁበት መስከረም 4 ምሽት ድረስ ተቀላቅለው ምግብ አልበሉም ነበር፡፡
ከነዚህ ውስጥ አንዷ የአወሊያዋ ተማሪ ፈትያ መሀመድ ናት፡፡ በሴቶች ዞን ብዙ አስገራሚ ህይወት ያላቸው ጠንካራ ሴቶች ቢኖሩም፣ ርዕዮታዊውን መንፈስ በመጋራት በኩል የምትጀግንብኝ ሌላኛዋ እስረኛ ብዙም ያልተወራላት ፈትያ መሀመድ ናት፡፡ የታናናሾቿ ሀላፊነት ያለባት የ22 ዓመቷ ፈትያ ለእስር የተዳረገችው የእናቷን ሀዘን እንኳን በወጉ ሳትጨርስ ነበር፡፡ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከበርካታ ሴቶች ጋር በማዕከላዊ ከ ሶስት ወር በላይ የታሰረችው ፈትያ፣ ወደ ቃሊቲ ያመራችው ግን ብቸኛዋን ነበር፤ አሳሪዎቿ ሌሎችን በሚፈልጉት መንገድ ሲፈቱ ፈትያ ግን የራሷን መንገድ በመምረጧና የአይበገሬነት መንፈሷ አብሯት በመኖሩ ሳትፈታ ቀርታለች፤ እስከ አሁንም የፍርድ ሂደቱን በመከታተል ላይ ናት፡፡
ፈትያ በመጠየቂያ ሰዓቷ ላይ የሚታይባት በራስ የመተማመን መንፈስ የሚገርም ነው፤ ‹‹በልኬ ጉድጓድ ቆፍረው እንኳን ቢቀብሩኝ ከአላማዬ ንቅንቅ አልልም፤ የማደርገው ነገር ሁሉ የማምንበትን ነው፤›› ትላለች፡፡ ጠያቂዎቿ በመጡ ግዜም ሀዲስ በማውራት የምታበረታቸውና የምታጠነክራቸው ከሽቦው ውስጥ ያለችዋ ፈትያ ናት፡፡ እንደ ርዕዮት ሁሉ የንባብ ማዕቀብ የተጣለባት በመሆኑና በሁኔታው እጅግ ከመቆጨቷ የተነሳ፣ ‹‹እዚህ ያለ ንባብ ከምታሰር፣ንባብ ተፈቅዶልኝ ማዕከላዊ እንደፈለጉ ቢያሰቃዩኝ ይሻላል፤›› ስትል አድምጫለሁኝ፡፡ ታዲያ ፈትያ የምታደርገውን ነገር ሁሉ አምናበት የምታደርገው እንጂ ማንም እንዲያወራላት እንደማትፈልግ የሰሞኑ የረሀብ አድማዋ አንዱ ማሳያ ነው፤ በፍጹም እንዲወራ እንዳልፈለገች አውቃለሁኝ፤ ሆኖም ግን ‹‹መወራት ያለበት ሁሉ መወራት አለበት›› በሚለው ስለማምን ለማውራት ተገድጃለው፡፡
ታዲያ እንደ ርዕዮት፣ፈትያ፣እማዋይሽ፣ሂሩት፣ጫልቱ፣… ያሉት ሴት እስረኞች፣ ከሌላው እስረኛ ሁሉ በተለየ ሁኔታ ልዩ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን፣ የሚጠየቁበት ሰዓትም እንዲሁ በጣም አስቀያሚ የሚባል አጭርና አድልዎው ያፈጠጠበት ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች (በተለይ ርዕዮትና ፈትያ) እያንዳንዳቸው በሁለት ጠባቂዎች ግራና ቀኝ የሚጠበቁ ሲሆን፣ ከጠያቂዎቻቸው ጋር በሚጨዋወቱበት ግዜም የጠባቂዎቹ ጆሮ አፋቸው ስር ይለጠፍና አንዳንድ ግዜ እስረኞቹ አፋቸው ስር ተጨማሪ ሁለት ጆሮ ያላቸው ሊመስለን ይችላል፡፡ ፖሊሶቹ ምን ማውራት እንዳለብህ እንኳን ሊወስኑልህ ይሞክራሉ፤ ያልጣማቸውን ወሬ ሁሉ ‹‹አይቻልም!›› በማለት ያስቆማሉ፤ ሳቅ ጨዋታችን ያበግናቸዋል፤ በራሳቸው የማይተማመኑ ስለሆኑም እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ከራሳቸው ጋር ያያይዙታል፤ ስለዚህ ሁሉ ነገራቸው ነቅቶ አፋችን ላይ ያርፋል፤ እንግዲህ የአፍ ትራፊክ መሆናቸው ነው፡፡
እንዲህ ባለው ሁኔታ ብዙ ግዜ በጠባቂዎቹና በጠያቂዎቹ መካከል ግጭቶች ሲፈጠሩ አስተውያለው፡፡  ከነ ርዕዮት ጋር በተመሳሳይ ክስ የታሰሩት ወንወዶች እንኳን ያለጠባቂዎች አጀብ በየትኛውም ሰዓት ሰፋ ላለ ግዜ እንዲጠየቁ ሲፈቀድላቸው፣ እነ ርዕዮት ግን ዛሬም ከሰኞ እስከ አርብ ከ6 ሰዓት ጀምሮ ለ አስር ደቂቃ፣ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድን በተመሳሳይ ሰዓት ለ30 ደቂቃ ይጠየቃሉ፡፡ በዚህች ደቂቃ ውስጥም ‹‹ፖለቲካ ታወራላችሁ›› በሚል ይፈርጃሉ፤ ቃሊቲ ውስጥ ፖለቲካ ማውራትም እንግዲህ ወንጀል ነው፡፡  ‹‹የአስር ደቂቃ ፖለቲካ›› ነው ያለችው እህቷ እስከዳር? ታዲያ ይህቺው ሰዓት በር ላይ ባሉ ቢሮክራሲዎችና ትንኮሳዎች መሽራረፏንም ጭምር ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡         
በነገራችን ላይ በቃሊቲ ያሉ የነ ርዕዮት ጠባቂዎች (ሁሉንም አይመለከትም) ትዕዛዝ ፈጻሚዎች ስለሆኑ፣ እንደ አለቆቻቸው በእስረኞቻቸው መካከል ያለው አንድነትና የሚያሳዩት ጥንካሬ ያርዳቸዋል፡፡ የጠያቂዎቻቸው ማንነትና ብርታት ያበሳጫቸዋል፤ እንደ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም፣ ዶ/ር ሽመልስ ተ/ጻድቅ፣ ዶ/ር ያዕቆብ ሀ/ማሪያም፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣… ላሉ ታላላቅ ጠያቂዎች እንኳን ክብር የላቸውም፡፡ ለታሳሪ ቤተሰቦችም ቢሆን ትንሽ ትልቅ ሳይሉ፣ ከሰው እንዳልተፈጠሩ ሁሉ ምግባራቸው የሚያስቀይም ነው፡፡ ታዲያ አንዳንድ የተባረኩ ፖሊሶች ቢኖሩም፣ መልካምነታቸው ስለማይፈለግ ለቅጣት ይዳርጋቸዋል፤ አልያም በቅርቡ እንዳደረጉት ከቦታ ቦታ ያዘዋውሯቸዋል፡፡ በቃሊቲ ያሉ የስርዓቱ አገልጋይ ፖሊሶች ዘወትር በማበሳጨትና በማሰላቸት ጠያቂ እንዳይኖር ለማድረግ ብዙ ይጥራሉ፤ የሚሸነፍላቸው አጥተው ሲብስባቸው፣ በፖሊስ ልብስ የተሸፈነው ትክክለኛው ማንነታቸው ይወጣና መተናኮስ ይጀምራሉ፡፡ መቼም እንዲህ ያለውን አስቀያሚ ሁኔታ ወደ ቃሊቲ ጎራ ያለ (በተለይ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችን እና ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቆ ጋር በተያያዘ የታሰሩትን ጠያቂ) ሁሉ ያውቀዋል፡፡
ትንኮሳው ገና ከመግቢያው በር ላይ ነው የሚጀምረው፤ ስድስት ሰዓት ሆኖ ‹‹ልዩ›› ጠያቂዎች በር ላይ ተኮልኩለን በምንጠብቅበት ሰዓት የዕለቱ ተረኛ ይመጣና ጮክ ብሎ! ‹‹እ! ግንቦት ሰባቶች ናችሁ?!...እናንተ ሁሉ ግንቦት ሰባት ናችሁ?...›› ይልና እያጉረመረመ ወደ ውስጥ ይዞን ይዘልቃል፡፡ መቼም አንባቢዎቼ ‹‹እና የናንተ ምላሽ ምንድነው?›› የሚል በሰላማዊ ሀገር ላይ የሚጠየቅ የዋህ ጥያቄ ትሰነዝሩ ይሆናል፤ በቃ ቃሊቲ እነሱ ከሚፈልጉት ውጪ ያንተ ምላሽ ቦታ የለውም፤ እዚህ የፈለጉትን ነህም አይደለህምም፤ እንደፍላጎታቸው ይወሰናል፤ ገና በር ላይ ሲጠራ ‹‹አይደለሁም!›› ብለህ ሙግትህን ልትጀምር ስታስብ እንዳትገባ ይከለክልሀል፡፡ እነሱ እንዲህ ያለውን ስያሜ የሚለጥፉብንና ጮክ ብለውም የሚጠሩን እንድንሸማቀቅና የአከባቢው ሰውም ጭምር እንዲፈርጀን ነው፤ እውነታው ግን ከዚህ በተቃራኒ ቃሉ ለቀልድ ጭምር ውሎ፣ በስድስት ሰዓት የምንሄድ ጠያቂዎችን፣ ‹‹ እ!..አንቺ ደግሞ ስንት ቁጥር ነሽ? መቼም ዘንድሮ ጨዋታው በቁጥር ሆኗል፤…›› በሚል ያስፈግጉናል፡፡
አንድ ግዜ እንዲህ ባለው ሁኔታ ወደ ውስጥ ከዘለቅን ቦሃላ እየተጨዋወትን እና እየተሳሳቅን እነ ርዕዮት ጋር ከደረስን ቦሃላ፣ ‹‹እሺ እንዴት ነሽ ግንቦት ሰባት?…›› እየተባባልን ሰላምታ ተለዋወጥን፤ ይሄኔ በዕለቱ የርዕዮት ጠባቂ የነበረችው እሳት ጎርሳ እሳት ልሳ ‹‹ለምንድነው ስርዓት የማትይዙት?...›› በሚል ያልሰማናቸውን እና ልገልጻቸው የሚከብዱኝን አስቀያሚ ቃላት ደረደረች፤ እኛም ጥፋታችን ምን እንደሆነ ጠየቅናት፤ ‹‹ በቃ! ምንድነው ግንቦት ሰባት ነን ምናምን እያላችሁ የምትሉት?...›› አለችን፡፡ ‹‹የኔ እህት አትበሳጪ ይህንን ስያሜ የሰጡን በር ላይ የቆሙት ያንቺው ጓደኞች ናቸው፤›› አልኋት፡፡ መግባባት ግን አልቻልንም፤ እሷም ይበልጥ ተበሳጭታ ተጨማሪ ነገሮችን ቀባጠረች፡፡ በሌላኛው ቀን ስንመጣ በዚህ ጉዳይ ርዕዮትም እኛም ላይ በማረሚያ ቤቱ ክስ እንደመሰረተችብን ሰማሁ፡፡
በሌላኛው ቀን እንዲሁ አባት አቶ ዓለሙ፣እስከዳር፣ስለሺና እኔ ሆነን ርዕዮትን ልንጠይቃት ሄድን፡፡ ያለችውን አጭር የመጠየቂያ ሰዓት መሻማት ስላለብን እኔና ስለሺ ቀድመን ትንሽ አወራናትና ቦታውን ለሁለቱ ለቀቅን፤ ከዛም እነሱ እስኪያወሯት እኔና ስለሺ አጠገባችን ባገኘነው እንጨት ላይ ቁጭ አልን፤ ወዲያውም አንዲት ፖሊስ ከውስጥ ወጥታ ወደ አጠገባችን መጣችና ስለሺን ‹‹አሁን እዚህ ተዘፍዝፈህ ሰዓትህን ግደልና ቦሃላ ሰዓት አለቀ ብለህ አፍህን ትከፍታለህ!›› ብላ እሷው አፏን ከፈተችው፡፡ ለካ ይህቺው ሴት ሌላ ግዜም ታስቸግረው ኖሯል፣ ‹‹አንቺ ሴትዮ ለምንድነው የማትተዪኝ?›› ሲል አጭር ምላሽ በጥያቄ አቀረበላት፤ ከዚህ ቦሃላ እስክንወጣ ድረስ ያለማቋረጥ ትለፈልፍ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ተናዳፊዎች ያሉበት ነው ቃሊቲ፡፡ ቃሊቲ ከዚህም በላይ ነው፡፡ 
ስለሺ ሀጎስ (የርዕዮት እጮኛ) የቃሊቲውን ግፍ በመቅመሱ በኩል ግንባር ቀደሙ ነው፤ የትንኮሳ ሰለባ ከሆነባቸው ይልቅ ያልሆነባቸውን ግዚያቶች መቁጠሩ ይቀላል፤ ከ አራት ኪሎ እስከ ቃሊቲ ያለውን አስቀያሚ መንገድ ያለማቋረጥ ለሁለት ዓመታት ያህል መመላለስ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ የሚያውቀው፣ ለአንድም ቀን ቢሆን ቃሊቲ ደርሶ የተመለሰ ሰው ነው፡፡ በአጭሩ ለመግለጽ፣ የአንድ ቀን የቃሊቲ ደርሶ መልስ አንድን ሙሉ ቀን ያበላሻል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ስለሺ ርዕዮት ቃሊቲ ከገባችበት ግዜ አንስቶ፣ ለሁለት ዓመታት ያህል በየቀኑ ቀኑን ሲያጣ ነበር ማለት ነው፡፡አባት እና እናትም ቢሆኑ በማረፊያ ግዚያቸው የዚሁ ስቃይ ሌሎቹ ሰለባዎች ናቸው፤ እህቷ እስከዳር ዓለሙም በተለይ ስራዋን ካጣችበት ግዜ አንስቶ ቀኖቿን እየገበረች ትገኛለች፡፡ በጥቅሉ እሷ ከታሰረችበት ግዜ አንስቶ ያለውን እድሜውንና ህይወቱን ለቃሊቲው መንግስት ገብሯል፡፡ ግን ታዲያ ሁኔታዎች እንዲህ ሆነው ለዘላለም አይቀጥሉም፡፡ 
ስቃያቸው በመመላለስ ብቻ ቢያበቃ ጥሩ ነው፤ ግን እውነታው እንደዛ አይደለም፤ በየግዜው ለሰው ልጅ ከመቻል አቅም በላይ የሆኑ ትንኮሳዎች፣ ግልምጫዎች፣ጉንተላዎችና ስቃዮች አሉ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ጓንታናሞ በሆነው ማዕከላዊም ለሁለት ወራት ያህል አሰቃዩት፡፡  በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ግን ለፍቅሩ ያለውን የመቻል ጥግ ማንም ሊደርስበት አልቻለም፤ ወደፊትም እንደማይሳካ በልበ ሙሉነት ለመናገር እደፍራለው፡፡ እንዲህም ሆኖ ስለሌሎች ስቃይና መብት መቆርቆሩን ያልተወ ቅን አሳቢነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ልጅ ነው ስለሺ ሀጎስ ማለት፡፡ አሳሪዎቻቸውም የርዕዮትና የስለሺ ነፍስ ምን ያህል እንደተቆራኘች ስለሚያውቁም ነው ብዙ ግዜ በፍቅሯ ስቃይ የሚመጡባት፤ አሰሩት፣ገረፉት፣አጎሳቆሉት፣… ለመናገር የሚከብዱ ብዙ ነገሮችን ፈጸሙበት፤ ግን ታዲያ የጋራ እምነታቸውን በማስቀየር ሊያንበረክኳት አልቻሉም፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ ዋነኛ መነጋገሪያ የነበረው የርዕዮት የረሀብ አድማ ማድረግ ነው፤ አድማው ሌሎች በርካታ ስቃዮች ከጀርባው ቢኖሩትም፣ ለመጨረሻው ውሳኔ ያበቃት ግን እንደቀደመው ግዜ እንዳትጠየቅ መደረጉ ነበር፤ የረሀብ አድማዋን አጠናክራ ከገፋችበትና ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን ሲበቃ ግን፣ ሌላ ሰበብ ተፈጠረ፤ ‹‹እኛ እንዳትጠየቅ ያልነው በእህቷ እስከዳርና በእጮኛዋ ስለሺ ነው›› ሲሉ ሌላ የለመዱትን የውሸት አክሮባት ሰሩ፡፡ እኔ ግን ይህቺም ሰበብ ብትሆን በመበለጣቸው ለሌላ ተጨማሪ በቀል ሲሉ እንደፈጠሯት አስባለው፤ የማይሆን ክስ በመፍጠር የሚዋደዱ ነፍሶችን ነጥለው ለተጨማሪ ሰቀቀን መዳረግ፡፡ ለስለሺም ሆነ ለእስከዳር አሁን ባለው ሁኔታ ርዕዮትን ጨርሶ አለማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ለአንድም ቀን ቢሆን አለመተያየታቸው ከባድ ሰቀቀን ነው፤ ለርዕዮትም እንዲሁ፤ ነገር ግን ይሄ እስከ አሁን ካለፉት መከራ የማይብስ በመሆኑ፣ እምነታቸውን አይቀይረውም፤ የበላይነታቸውንም አይነጥቀውም፡፡
በዚህ ጨካኝ ውሳኔያቸው ባለመርካታቸውም፣ አርብ መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም ህግ ያውቃሉ፣የህግ ሰዎች ናቸው በሚል ወደ ቃሊቲ ጥያቄ ሊያቀርብ የሄደውን ስለሺ ከ ስምንት ሰዓት እስከ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ድረስ በእስር አቆይተው የተለመደውን ህገ ወጥ ተግባራቸውን ሲፈጽሙበት ውለዋል፡፡ እንዲህ ያለው እገታ በስለሺ ላይ ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ ለምዶታል፤ ቃሊቲ የሚስቱ ብቻ ሳይሆን የስቃዩም ጭምር መኖሪያ ከሆነ ከራረመ፡፡
ለኔ ግን የሰሞኑ እርምጃቸው ስርዓቱ ምን ያህል እንደዘቀጠና የግፋቸው ጉዞ ምን ያህ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው የሚነግረኝ፡፡ የቃሊቲ አዛዥ ናዛዦችም ከህግ በላይ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ባስተውልም፣ አሁን ግን የራሳቸውን አምባገነናዊ ስርአት በቃሊቲ እንዳቋቋሙ ይሰማኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች እራሳቸውን ከህግ በላይ አድርገው በሚቆጥሩበት ሀገር ላይ እንዴት የታሳሪዎችን ህግ ሊጠብቁ ይቻላቸዋል? አንድ ማሳያ ልጥቀስ፤
በአንድ ወቅት የርዕዮትን ችሎት ልንከታተል በልደታ ‹‹ፍርድ ቤት›› ተገኝተናል፤ ችሎቱ እንዳለቀም እነ ርዕዮትን የሚወስዳቸው መኪና እሰኪመጣ እንዲሁም ሌሎች እስረኞች እስኪሟሉ በግቢው ውስጥ ወዳለ ማረፊያ ቦታ ይወሰዳሉ፤ ይሄኔ እንደ ሁልግዜውና እንደ ግቢው ልማድ፣ ቤተሰቦቿ ራቅ ብለው ቆመው ይሰናበቷታል፤ ሁኔታውን ያስተዋለው አንድ የፖሊሶቹ ሀላፊ (ቃሊቲም ቢሆን ቤተሰቡን በደንብ ያውቀዋል፤ጥላቻውንም በተደጋጋሚ ይገልጻል፤) ፊቱን አጨማዶና ድምጹን ጠንከር አድርጎ ‹‹ዞር በሉ ከዚህ!... እናንተንም ሰብስቤ ነው የማስገባችሁ!›› ይላቸዋል፤ እነሱም ያሉበትን ግቢ ስም አምነው በነጻነት ፈታ ብለው እየሳቁ ‹‹አረ ባክህ?!›› ይሉታል፤ እሱም በእርግጠኝነት ኮራ ብሎ ‹‹ማሪያምን አስገባቹሀለው!›› ብሏቸው አረፈው፡፡ በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ሆኖ እንዲህ የሚል አንድ የፖሊሶች ሀላፊ ሀላፊ፣ ቃሊቲ ውስጥ ደግሞ ከበታቹ የሚያዛቸውን ጨምሮ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመቱ አይከብድም፡፡
ያም ሆነ ይህ፣ ርዕዮትን ከያዘችው የበላይነት መንገድ ማንም ሊመልሳት አይችልም፤ ምክንያቱ ደግሞ ርዕዮታዊው መንፈስ ማንም እንደፈለገ ሊጠመዝዘው በማይችለው ደረጃ ጠንካራ መሰረት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ርዕዮት የስርዓቱ ጭካኔ፣ ኢ ፍትሀዊነት፣ ኢ ዴሞክራሲያዊነት፣ኢ ሰብዓዊነት፣… በጥቅሉ ርዕዮት የስርዓቱ ሚዛን ማሳያ ናት፤ ሳምንት ርዕዮታዊው መንፈስ እንዴት ያለ ነው?፣ ጥንካሬው ምን ይመስላል?፣ከየት መጣ?፣ እንዴት?፣… የሚሉ ሌሎችም በርካታ መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ርዕዮታዊ ወጋችንን ‹‹ ርዕዮታዊው መንፈስ እንደ ቻይኒዝ ባምቡ›› በሚል ርዕስ ስር  እንቀጥለዋለን፡፡ እስከዛው ግን በቃሊቲው መንግስት ስቃይ ስር ላሉ ወገኖቼ ብርታቱን እመኛለው፤ በመጨረሻም ከሰው ልጅ፣ ከህግ፣ ከፍትህ፣ ከዴሞክራሲ… ይልቅ ህንጻና መንገድ የተሻለ ዋጋ በሚሰጣቸው ኢህአዴጋዊ አገዛዝ ውስጥ እንዳለን ሳስበው፣ በበዓሉ ግርማ ‹‹ኦሮማይ›› ውስጥ ያለ አንድ ግጥም መሰነባበቻችን እንዲሆን ተመኘው፡፡

‹‹ከጎራው ዘልቄ እስኪ ልነጋገር
ካለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር?
የኔ ውብ ከተማ-
ህንጻ መች ሆነና የድንጋይ ክምር፤
የኔ ውብ ከተማ-
መንገድ መች ሆነና የድንጋይ አጥር፤
የኔ ውብ ከተማ የኔ ውብ አገር
የሰው ልጅ ልብ ነው
የሌለው ዳርቻ የሌለው ድንበር፡፡
ሕንጻው ምን ቢረዝም፡ ምን ቢጸዳ ቤቱ
መንገዱ ቢሰፋ ቢንጣለል አስፋልቱ
ሰው ሰው ካልሸተተ ምንድነው ውበቱ?
እኔ ውብ የምለው
የሰውን ልብ ነው፡፡
ምን ቢነድ ከተማው ተንቦግቡጎ ቢጦፍ
ቢሞላ መንገዱ በሺ  ብርሀን ኩሬ
በሺ ብርሃን ጎርፍ
ምን ያደርጋል?
ምን ያሳያል?
ካለሰው ልብ ብርሃን
ያ ዘላለማዊ ነበልባል ያ ተስፋ ሻማ
ጨለማ ነው
ሁሉም ጨለማ፡፡..›› (ገጽ 250-251)
ህንጻዎቹም የጨቋኞቹ መኖሪያና ገንዘብ ማግበስበሻ፣ መንገዱም የነሱው መመላለሻ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም!