በእናቶች ላይ ያስጨከኑ የመደራጀት ሴራዎች
በመሐመድ
ሐሰን
በአራት ኪሎ ቤተ-መንግስት አፍንጫ ስር የሚፈጸሙ ግፎች አይነታቸውና ብዛታቸው
ለጉድ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ላደግንበት ኢትዮጵያዊ ባህል እጅግ በጣም እንግዳ ከመሆናቸው የተነሳ፣ ጭንቅላት አስይዘው፣ ደረት እያስደቁ
ኡኡኡ…!! የሚያስብሉ ናቸው፡፡ ስርዓቱ ምን ያህል ማንነታችንን እንደሸረሸረው፣ እንዳጨካከነን፣ ሆዳም እንዳደረገን፣ ሰብአዊነታችንን
እንደገፈፈው፣… ማሳያ የሚሆኑ ግፎች በአራት ኪሎ በሽ ናቸው፡፡
ለዛሬ የምናነሳቸው ግፎች ዋነኛ ማስፈጸሚያ የሆነው ቡድን ‹‹መደራጀት››
የሚል ህቡዕ ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ይህን ቡድን ማቋቋም ያስፈለገው፣ አንድም ግፍ የበዛበት አላማቸውን በግዚያዊ ጥቅም
በመደለል በፍጥነት ማስፈጸም እና ግፋቸውን ቢያንስ በጥቅም ለደለሏቸው ቡድኖች ትክክለኛ ተግባር እንደሆነ ማሳመን ሲሆን፣ በሌላ
በኩል ደግሞ ይህንን ቡድን በግፋቸው ውስጥ ተካፋይ በማድረግ ከምንም በላይ የበደላቸውን ሴራ ያጦዙታል፡፡ ከራሱ ከህብረተሰቡ የወጡ
ወጣቶች በአከባቢያቸው፣ በአሳጋጊዎቻቸው፣ በጎረቤቶቻቸው፣ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው ላይ ግፍ በመፈጸም፣ የስርዓቱን ወንጀል ይጋራሉ፤
እጃቸውን ያጨቀያሉ፡፡
ስለዚህም የአራት ኪሎን ወጣት ‹‹መደራጀት›› የሚል ህቡዕ ስያሜ
በተሰጠው ቡድን ውስጥ አካተው የሰፈሩን፣ የዘመዱን፣ የጎረቤቱን፣ ከፍ ሲልም የእናቱን ቤት አፍራሽ አድርገውት ቁጭ አሉ፡፡ ከዚህ
ግዜ ጀምሮ እንግዲህ በግዚያዊነት ወደ ኪሳቸው የሚገባውን ገንዘብ ብቻ በማሰብ ታውረው፣ እህት ወንድሞቻቸው የዓመቱን ትምህርታቸውን
እያገባደዱበት የነበረውን ትምህርት ቤት ከማፍረስ ጀምሮ፣ በአከባቢው ላይ ያገኙትን የቧንቧ ብረት እና ለመተላለፊያ መንገድነት የዋሉትን
ፌሮ ብረቶች መነቃቀል፣ መሰባበራቸውን ተያያዙት፡፡ የየቀኑ ጉጉታቸውና
ወሬያቸውም፣ ‹‹ ለኛ ቡድን የሚደርሰው የማን ቤት ይሆን? የስ! ብራቮ! አራት ኪሎ ሆቴል ለኛ ደረሰን፤…›› በሚሉ የአፍራሽነት
ሱሶች ውስጥ ተጠመዱ፡፡ ቶሎ ቶሎ ቤቶች እንዲፈርሱ ጎትጓችም ጭምር ሆነው ተገኙ፡፡
ቡድኑ በአደገኛ የአፍራሽነት ሱስ ውስጥ ከመውደቁ የተነሳ፣ ቅንጣት ታህል
ርህራሄ ራቀው፡፡ እናም ኢትዮጵያዊ ብቻ ሆነን ሳይሆን እንደ ሰውም ጭምር ስንሰማቸው የሚሰቀጥጡ የማፊያ ታሪኮች በአራት ኪሎ ለመፈጸም
በቁ፡፡ ብዙዎች የሚሰሙት እና የሚያዩት ነገር የምድር ፍጻሜ (ሰምንተኛው ሺህ) ማሳያ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ጀመሩ፡፡
እምባቸውን አፈሰሱ፤ በአከባቢያቸው ወዳሉ የእምነት ተቋማት በመሄድም ፈጣሪያቸውን ተማጸኑ፡፡ የልጆቻቸውን እና የገዢዎቻቸውን ጤናም
ጥፋትም አንድ እንዲል የመጨረሻውን ማመልከቻ፣ የመጨረሻው ቅሬታ ሰሚያችን ነው ለሚሉት ፈጣሪ አስገብተው ወደየቤታቸው ተመልሰው ሚሆነውን
ዘግናኝ ግፍ ሁሉ ማየት ጀመሩ፡፡
እነሆ ቆጥረን ከማንዘልቃቸው የግፍ ታሪኮች ውስጥ አንድ ሁለቱን እንካፈላቸው፡፡
ልብ አድርጉ! እነዚህ ታሪኮች አንዳችም ፈጠራ ያልታከለባቸው እውነቶች ናቸው፡፡ ምናልባትም እኔ የታዘብኩትን ስለማቀርብላችሁ እንጂ፣
ከነዚህ የከፉ ችግሮችም (ካሉ ማለቴ ነው) ስላለመፈጸማቸው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ የኔን ግን ቀጠልኩኝ፡፡
፩
‹‹ ልጄ አንተም ጅብ ነበርክ፣
ጅብ በላህ››
ልጅ የእናቱ ቤት በእጣ ደርሶታል፡፡
ሊኖርበት እንዳይመስላችሁ፣ ሊያፈርሰው እንጂ፡፡ ለተደራጁት ቡድኖች እጣ በሚወጣበት ወቅት፣ ይህ ባለታሪካችን ወጣት ያለበት ቡድን፣
የእራሳቸውን ቤት እንዲያፈርሱ እጣው ይወጣላቸዋል፡፡ ታዲያ የዚህ ቡድን አባላት ሳይውሉ ሳያድሩ ወደ ወጣቱ እናት ቤት ይገሰግሳሉ፡፡
እናት በልጃቸው እየተመሩ የመጡትን የሰፈር ልጆች ሲያዩ፣ አመጣጣቸው ከቤታቸው ጎራ በማለት እንደቀደመው ግዜ ሁሉ ሊጫወቱ እንደሆነ
እርግጠኛ ሆነዋል፡፡
ብዙም ሳቆይ ግን እናት ግምታቸው
የተሳሳተ መሆኑን ወጣቶቹ ያረዷቸዋል፡፡ ‹‹የመጣነው ቤቱን እንድናፈርስ ታዘን ነው፤›› አሏቸው፡፡ እናት በሁኔታው እጅግ በጣም
ቢደነግጡም፣ የተላኩት ወጣቶች ማንነት ዳግም ሌላ የተስፋ ጭላንጭ ዘራባቸው፡፡ ከአፍራሽ ወጣቶች ውስጥ አብዛኞቹ የሳቸውን እንጀራ
በሚጥሚጣ እየበሉ፣ ውሃ እና ጠላቸውን እየጠጡ ያደጉ ሲሆኑ፣ አንደኛው ደግሞ አምጠው የወለዱት የገዛ ልጃቸው ነው፡፡ ስለዚህ ቤታቸው
ከመፍረስ እንደማይተርፍ ቢገባቸውም፣ ቢያንስ እንኳን ምንም ሳይስተካከል በጀሞ አከባቢ የተሰጣቸውን ቤት እስከሚያስተካክሉ እንደሚታገሷቸው
እርግጠኛ ሆነዋል፡፡
በድጋሚ ሌላ የተሳሳተ ተስፋ፡፡ ወጣቶቹ
‹‹…አንዴ መጥተናል፣ ሳናፈርስ አንመለስም!›› በሚል ተዘገጃጁ፡፡ እናትን ጨምሮ ጎረቤት እና በአከባቢው የነበረው ሰው በሙሉ የሚሆነውን
ማመን ከብዶታል፡፡ የልጅ ክንድ ከመከታነት፣ ወደ አፍራሽነት ተቀይሮ ማየቱ በፍጹም ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ በሁኔታው ያዘነ ጎረቤት
በሙሉ በየተራ ወጥቶ ከመለመን አልፎ፣ እንደፈጣሪ ተንበርክኮ ተማጸናቸው፡፡ በፍጹም ሚሰማቸው ጠፋ፤ ልጅ ከወጣቶቹ ሁሉ ብሶ ተገኘ፡፡
እናት በልጃቸው እግር ስር ተደፍተው፣ የመጨረሻ ያሉትን የአንድ ቀን እድሜ ብቻ እንዲሰጣቸው አልቅሰው ተማፀኑት፡፡ ማንም ግን ቤቱን
በእለቱ ከመፍረስ ሊታደገው አልቻለም፡፡ እናት በገዛ ልጆቻቸው ጭካኔ እና ግፍ ከቤታቸው ተገፍትረው ወጥተው ከነ እቃቸው ዝናብ ላይ
ተወረወሩ፡፡ በነጋታው የአከባቢው ነዋሪ ተረባርቦ፣ ለአቅመ መኖሪያነት ወዳልበቃው የጀሞ ማረፊያቸው አደረሳቸው፡፡
ልጅ በተመሳሳይ መልኩ ከሚያፈርሳቸው
ቤቶች በሚያገኘው ገንዘብ ደንዝዞ፣ የመረጠውን እየበላ፣ ያሻውን እየጠጣ፣ ከፈለጋት ጋር እየተቃበጠ አለሙን መቅጨቱን ተያያዘው፡፡
ህይወት አሁን በጀመራት ‹‹ጣፋጭ›› መንገድ እንድትቀጥልለት፣ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ፈራሽ እንድትሆንለት አጥብቆ ሳይመኝ አልቀረም፡፡
ነገር ግን ምኞቱ፣ ተራ ምኞት ብቻ በመሆኑ፣ ብዙ መስለው የታዩት የአከባቢው ቤቶች ለየቡድኖቹ እየተከፋፈሉ ፈርሰው አለቁ፡፡ እሱም
እንዳሻው ሲረጨው የከረመው የግፍ ገንዘብ ያልቃል፡፡ ይሄኔ ልጅ አይኑን በጨው ያጥብና በስካር ሞቅታ ውስት ሆኖ ወደ እናቱ ቤት
ያመራል፡፡ እናት በልጃቸው አይን ያወጣ ድፍረት ቢገረሙም፣ እንደሱ
ግፍ ግን ፊት ለመንሳት አልቸኮሉም፡፡ በዚህ ግዜ ሁኔታውን የሚያውቁ ጎረቤቶቻቸው ኬቤታቸው ይወጡና፡
‹‹ደግሞ ምን ቀረኝ ብሎ መጣ?! ይህ አረመኔ!.. ታስገቢውና እንተያያለን፡፡
አንቺ ዝም ብትዪ እንኳን እኛው እንገለዋለን፡፡…›› የሚሉ የተለያዩ ዛቻዎችን ሁሉም በየበኩሉ ይሰነዝርና ያባርሩታል፡፡ እናትም
ለልጃቸውን እርማቸው ቀድመው አውጥተዋልና፣ አሁን ጎረቤት የሚያደርገውን ነገር ምንም አልተቃወሙም፡፡ ልጅም አንገቱን ደፍቶ እግሩ
ወደመራው ይሄዳል፡፡
በጨለማው የተባረረው ልጅ፣ እግሩ
በአቅራቢያው ወደነበረ አንድ ጉራንጉር ውስጥ ይመራውና እዛው ጋደም ባለበት ጅብ በልቶት ያድራል፡፡ በመጨረሻም የልጃቸውን ሞት የሰሙት
እናት፡
‹‹ ልጄ፣ልጄ፣…
አንተም ጅብ ነበርክ፤ ጅብ በላህ፡፡›› ብለው አልቅሰው ልጃቸውን በድጋሚ ለሁለተኛ ግዜ ቀበሩት፡፡
፪
አሮጊቷን በአምቡላንስ፣ ቤታቸውን
በአፍራሽ
በአራት ኪሎ አከባቢ ይኖሩ የነበሩ
አንድ እናት (አሮጊት ናቸው)፣ ቤታቸው አይናቸው ስር ባደጉ ወጣቶች ሊፈርስባቸው ሲል፣ ‹‹እንዴት ሲደረግ!›› በሚል ይከላከላሉ፡፡
ከቆይታ ቦሃላ፣ አፍራሾቹ ፖሊስ አስከትለው ተመለሱ፡፡ በአከባቢው በተፈጠረው ወከባ እና ግርግር አሮጊቷ እናት ህመማቸው ይነሳና
እራሳቸውን ስተው ይዘረራሉ፡፡ ከቆይታ ቦሃላም አምቡላንስ ይመጣና ይዟቸው ወደ ሆስፒታል ይከንፋል፡፡ ይሄኔ አፍራሾቹ ምን የሚያደርጉ
ይመስላቹሀል? ተደናግጠው ወደመጡበት የሚመለሱ ከመሰላቹ ተሳስታቹሀል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ወደዚህ የአፍራሽነት ስራ ውስጥ ገና ሲገቡ
ይሉኝታ፣ ባህል፣ወግ፣እንዲሁም ህሊናቸውንም ጭምር ከጫማቸው በታች በማዋል ጨፍልቀዋልና አምቡላንሱ መኪና ገና ከአይን ሳይርቅ ነበር
ወዲያው ቤቱን ማፍረስ የጀመሩት፡፡
ለአብነት ያህል ከላይ ያነሳናቸውን
ዓይነት ግፎች፣ በአራት ኪሎና በሌሎችም ‹‹ልማት›› የሚባል ጸረ-ደሃ እንቅስቃሴ በጎበኛቸው አከባቢዎች ላይ ማስተዋል ቀላል ነው፡፡
ጥቂት ሀብታሞች ብቻ በሚኖሩባት ሀገራችን ውስጥ የአብዛኞቹ ድሆች የየዕለት ስጋትም ‹‹መቼ ይሆን እኔስ ከቤቴ የምፈናቀለው?››
የሚል ከሆነ ሰነበተ፡፡
ከሁሉ በላይ ግን፣ እኔ በዚህ ታሪክ
ውስጥ ጎልቶ የሚታየኝ እውነታ፣ ስርዓቱ በዘረጋቸው ሴራዎች ውስጥ ለመጠለፍ ያለን ዝግጁነት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ነው፡፡
እራሳችንን ለዚህ ሴራ ክፉኛ አመቻችተናል፡፡ ስርዓቱ ከሀገራችን አልፎ በከተማችን፣ በአከባቢያችን፣ በጎረቤታችን፣ ብሎም በራሳችን
ላይ እንኳን ሲመጣ ተባባሪዎች ሆነናል፡፡ የማይነኩ ህልውናዎቻችንን የትኞቹ እንደሆኑ እንኳን መለየት እስኪሳነን ድረስ ማንነታችንን
አሳልፈን ሰጥተናል፡፡ ‹‹እምቢ! አይቻልም፣ ይህንን አላደርገውም፣›› የምንልበትን ሞራል እንኳን አጥተነዋል፡፡ እና ታዲያ ይሄኔ
በስርዓቱ መሰሪነት ላይ ብቻ ጣታችንን መቀሰሩ ተገቢ ይመስላቹሀል? ስርዓቱ ለመሰሪነቱ የልብ ልብ እንዲሰማው እኛስ አላገዝነው ይሆን?
ምናልባት ወደ እኛ የተቀሰሩትን ጣቶች እየዘነጋናቸውም እንዳይሆን እሰጋለው፡፡
የጅቡ ታሪክ
በአራት ኪሎ አከባቢ ቤት ከፈረሰባቸው
አንዱ የሆነው ብሩክ (ትክክለኛ ስሙ አይደለም) በነሱ አከባቢ ቤቶች የሚፈርሱት ከሌላው አከባቢ በተለየ አራት ኪሎ ላይ የካድሬዎችን
ክፍለ ከተማ ለመገንባት ታስቦ እንደሆነ ያምናል፡፡ በተጨማሪም ብሩክ እራሱን እና የአከባቢውንም ሰው ጭምር ተጠያቂነት ለማሳየት
ሁሌ የሚያነሳት አንድ ተረት አለችው፡፡ እኔ እንደተረዳኋት በራሴ መንገድ ላቅርባት፡፡
ሁለት ጓደኛሞች አብረው ተኝተው ሳለ
ጅብ ይመጣል፡፡ ጓደኛሞቹ ጸጥ ብለው ተኙ፡፡ ኋላም አንደኛው ‹‹ቀርጨጭ፣ ቀርጨጭ፣…›› የሚል ድምጽ ይሰማና ጓደኛውን ‹‹ምንድነው
የምሰማው ድምጽ?›› ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛውም ‹‹ዝም በል! ጅቡ እኮ ነው፤ እግሬን እየበላው ነው፡፡›› ሲል ይመልስለታል፡፡
እግሩን ሲጨርስ ወደ ጭንቅላቱ መምጣቱን ዘንግቶት ዝምታን መምረጡ ነው፡፡
ብሩክ ይህቺን ተረት የሚያነሳት
‹‹ይበለን! የእጃችንን ነው ያገኘነው፤›› ለማለት ፈልጎ ነው፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዳም፣ ቀደም ብሎ ከኛ በቅርብ ርቀት ላይ ይኖሩ
የነበሩ ነዋሪዎች ቤታቸው በግፍ ሲፈርስ፣ ከነሱ ጋር ከመወገን ይልቅ፣ ጥጋችንን ይዘን ታዛቢ ሆነን ነበር፤ ዛሬ ያ ግፍ በኛም ላይ
እንደሚደርስ ዘንግተን፤ በሚል ያንን ግዜ በቁጭት ያስታውሳል፡፡ ይህ የጁቡ ታሪክ በስንቶቻችን የህይወት ክፍል ውስጥ ስንቴ ገጥሞን
ይሆን?
በአራት ኪሎ ቤተ- መንግስቱ አፍንጫ
ስር የሚፈጸሙ ግፎችን ያጋራሁት አንድ ወዳጄ፡ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ቦታ (ቤተ-መንግስቱን) እያስታወሰ፣ ‹‹ታዲያ ይሄ ምኑን ቤተ-መንግስት
ነው ቤተ- ሽፍታ እንጂ›› ሲል ነበር የገለጸው፡፡

