Wednesday, August 21, 2013

የአሚር ልደት እና የመለስ ሙት ዓመት

በመሐመድ ሐሰን

ይህ ጽሁፍ በትላንትናው (ነሀሴ 14ቀን 2005) ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ላይ የወጣ ስለሆነ፡ ትናንትን ታሳቢ እያደረጋችህ አንብቡት፤

                                                            ፩

እንደመንደርደሪያ

የመለስ ሞት ወይስ የሀገር ሞት?

አሚር የሚለው የአረብኛ ቃል ንጉስ (መሪ) የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል፤ ያኔ በንጉሱ የልደት በዓል ላይ ተደረገ ሲባል የምንሰማው ነገር እጅግ በጣም አስገራሚ ነበር፤ የኬኩ ርዝመት፣ የሻምፓኙ እንዲሁም የታዳሚያኑ አይነትና ብዛት፣ ለልብስ የወጣው ወጪ፣ የድግሱ ስፋት፣ ለውሻዋ ለብቻዋ የተጋገረው ኬክ፣… ምን ያልተባለ ነገር አለ? ከሁሉ በላይ ደግሞ የልደት አከባበሩን አነጋጋሪ እንዲሆን ያደረገው፣ በወቅቱ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን አስከፊ በተባለ የረሀብ ሁኔታ ላይ ስለነበሩ ነው፤ እናም ንጉሱ ሆዬ የሀገሪቱን ረሀብ ደብቀው፣ ደማቁን ልደታቸውን ለዓለም አወጁ አሉ፡፡

ከዚህ በ‹‹አሉ›› ከሰማነው ታሪክ የከፋውን እውነት ግን ዛሬ እውን ሆኖ እያየነው ነው፤ ያኔ ንጉሱ ያከበሩት ልደታቸውን በመሆኑ፣ የተነሳባቸውን ቅሬታ የመስማት፣ የማስተባበል፣ ምክንያት የመስጠት፣ ብሎም ‹‹ስህተቱን›› አምነው ከተቀበሉ በህይወት ስለነበሩ ሰርቶ የመካስ እድል ሁሉ ነበራቸው፤ በሌላኛው ጎኑ ካየነውም ንጉሶች እራሳቸውን የሀገሪቱ ምስል እድርገው ስለሚያዩ ያከበሩት የሀገሪቱን ልደትም ጭምር ነበር ብለን ልንል እንችላለን፤ በብዙዎች መራብ ውስጥ የተከበረ ልደት፤ ዛሬ ግን እየተከበረ ያለው ብቻ ሳይሆን ሁላችንም በግድ እንድናከብረው እየተገደድን ያለነው ‹‹የሀገሪቱን›› ሙት ዓመት ነው፤ ያውም በ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› መንገድ ተመረጠ ከሚሉን አንድ መሪ ጋር አብራ ‹‹የተቀበረችን›› ሀገር ሙት ዓመት፡፡

በአሁን ሰዓት የመንግስትን ስልጣን የሙጥኝ ብሎ ሀገሪቱን እያስተዳደረ (እያሳረረ ቢባል ይቀላል) ያለው ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ (ህ.ወ.ሐ.ት) እለን ያለው፣ ‹‹ሀገሪቱ ላይ የነበረው አንድ ሰው ነው፣ እሳቸውም ሞተዋል፣ ስለዚህ ከአሁን ቦሃላ መመራት ያለብን በሳቸው ሙት መንፈስ ነው፤›› እያለን ነው ያለው፡፡ ንጉሱ ‹‹ሀገሪቷም ህዝቧም ተጠቅልለው የተሰጡኝ ለኔ ነው›› በሚል ጠቅልለው ሲገዙን ነበር፤ የአሁኖቹ ደግሞ በባሰ ሁኔታ ከተገዛንም ቦሃላ ‹‹ጠቅልለው መቃብሩ ድረስ እንክተታችሁ!›› ነው እያሉን ያሉት፤ ባለስልጣናቱና ልሳኖቻቸው ዓመቱን ሙሉ ለቅሶ ድረሱ እያሉ መከራችንን ሲያሳዩን ነው የከረሙት፤ ስራ ፈትተው የከረሙ ካድሬዎችም የፈረደበትን ህዝብ እያሰባሰቡ አደራጅተው ከማስለቀሳቸው ባለፈ፣ ወትሮም ቁምነገር ያልነበረው ወሬያቸው ማድመቂያ ሆኖ የዘለቀው የአቶ መለስ ‹‹ራዕይ›› እና ፎቶግራፍ ነበር፤ የሀገሪቱ ሀብት፣ የመስሪያ ቤቶች ንብረትና ሰራተኞች፣ እንዲሁም መልከዓ ምድሩን ጨምሮ ሁሉም የአቶ መለስ ሙት መንፈስ ተከታይ እንዲሆኑ የተገደዱ ናቸው፤ ‹‹ያደለው›› መሪ ከመቃብር በታች ሆኖ ሀገር ይመራል፤ ጓዶቹም ከሱ ውጪ ምንም አቅም የሌላቸው ሙቶችና በሙት ራዕይ የሚመሩ እነደሆኑ በአደባባይ ይመሰክራሉ፡፡

ንጉሱ ሀገሪቱ በምግብ ረሃብ ላይ በነበረችበት ወቅት ስላስጋገሩት ኬክ ስናወግዛቸው ኖርን፤ ከምግብ ረሀብ ባሻገር ለመልካም አስተዳደር ረሀብ፣ ለፍትህ ረሀብ፣ ለዴሞክራሲ ረሀብ፣ ለፕሬስ ረሀብ፣ ለንግግር ነጻነት ረሀብ፣ ለሀገር ረሀብ፣ ለወደብ ረሀብቨ… ተቆጥረው ለማያልቁ ህልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ረሀቦች ዳርገው፣ የሀገራችንን ሞት ሊያበስሩን ለሚሞክሩ መለስ ሰራሾች (Made in Meles) የሚመጥን የግፍ ገላጭ ቃል ይኖር ይሆን?! እኔ ግን ለግዜው ግፈኞች!! ብያቸዋለሁኝ፡፡

                                                                        ፪

የግፈኞቹ ግፍ ውልብ ብሎብኝ በመንደርደሪያዬ ውስጥ ሰጥሜ ቀረሁኝ እንጂ፣ ዛሬስ በዋነኝነት ላወጋችሁ የፈለግኩትኝ ልክ የዛሬ ዓመት ስለተወለደው አሚር እና በዛው እለት ስለሞቱት አቶ መለስ ነው፤ አሚር የሚለው ቃል ንጉስ የሚለውን፣ ንጉስ የሚለው ቃል ደግሞ ንጉስ ኀይለስላሴን እና ልደታቸውን ስላስታወሰኝ ሌላ ነገር ውስጥ ገብቼ ስዘባርቅ ቆየሁ፤ ለማንኛውም ይቅርታችሁን ጠይቄ (በተለይ ‹‹የራዕዩ›› ተከታይ ለሆናችሁ የኢህአዴግ ካድሬዎች) ቀጥ ለጥ ብዬ ወደ ጉዳዬ እገባለሁኝ፡፡

በህጋዊ መንገድ እነደተመዘገበው፣ ነሀሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ረፋዱ ላይ አሚር መሀመድ ወደዚህች ምድር መጣ፤ አምርሮም አለቀሰ፤ በወቅቱ አለቃቀሱን የታዘበውና ሁሉንም ነገር በፖለቲካ አይኑ የሚቃኘው ሀይሌ፣ ‹‹በመለስ ኢትዮጵያ ላይ ተወልዶ እንዲህ ያለውን የምሬት ለቅሶ ባያለቅስ ነበር የሚገርመኝ!›› ሲል ፖተሊካውን ፖተለከ፤ ኢህአዴግ የሚዘውራቸው ሚዲያዎች ደግሞ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሲያወዛግብ የቆየው የአቶ መለስ ሞት እውን የሆነው በዚሁ ቀን ምሽት ላይ እንደሆነ ነሩን፤ ለቅሶም ድረሱ ተባለ፤ የአሚር እናትም ለልጇ አሚር የሚለውን ስያሜ ሰጠችው፤ ምክንያቷንም በኩራት ስትናገር ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሞቱት በንጉሱ ልጄ ወደዚህ ምድር መምጣት ደንግጠው ስለሆነ፣ ልጄን አሚር አልኩት፤›› ትላለች፤ አሚርን ሊያዩ የመጡ አንድ ሽማግሌ በጨቅላዎቹ ክፍል ተወልደው የተኙ ልጆች በሙሉ ወንድ መሆናቸውን አስተውለው፣ ‹‹ምነው የመለስን ሞት ተከትሎ የተወለዱት ሁሉ ወንድ ሆኑ?›› ሲሉ ጠየቁ- መሪነትን ከወንዶች ጋር ብቻ ሲያቆራኙት፤ ከፈለጋችሁ ከመለስ የባሱ ጨቋኝ በሏቸው፡፡

የሆነው ሆኖ ህጻን አሚር እና ሟቹ ጠቅላይ አቶ መለስ የዛሬዋን ቀን ይጋሯታል፤ የአንደኛው ልደት ሲከበር፣ የሌላኛው ሙት ዓመት ይከበራል፤ ታዲያ ሁለቱ በሚጋሯት ይህቺ ቀን ላይ፣ በህይወት እና በሞት መካከል ያለውን ልዩነት ያህል ታስቦ የሚውልበት መንገድም የዛኑ ያህል ሰፊ ልዩነት የሚታይበት ነው፤ ታዲያ ይሄኔ ያለውን ትውልድ (ያውም ጨቅላውን) በሚወክለው አሚር እና ሙታንን እንዲሁም ሙት ፓርቲያቸውን የሚወክሉትን አቶ መለስን በሚመለከት በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ለሁለቱም ምናቸው ነች? ታሪክስ እንዴት ያስታውሳቸዋል? የሁለቱ ነገ ምን ይመስላል? ዛሬ ላይስ የሚያመለክቱን ምን ይሆን? እውነቱ የቱጋ ነው ያለው? ምኞታቸውስ ምንድነው? ህያውነት የሚወርሰው ማነው? አድበስባሽነቱና አግበስባሽነቱስ ይቀጥላል? ከሁለቱ ልደት እና ሞት ተጠቃሚው ማነው?...??? ከዚህ የበለጡ በርካታ ጥያቄዎችን በየበኩላችን መሰንዘር እንችላለን፡፡

ኢህአዴጋውያኑ እና ልሳኖቻቸው ኢትዮጵያ በብቸኝነት ያበቀለችው መሪ አቶ መለስን ብቻ መሆኑን፣ እሳቸው በመሞታቸውም ሀገሪቱ አብራቸው መቃብር ወርዳ በሳቸው ለመተዳደር እንደመረጠች ነጋ ጠባ ሲወተውቱን ይኅው አንድ ዓመት አለፈ፤ ዛሬ ደግሞ መቃብር ወርዳለች ብለው ሊያሳምኑን የሞከሩትን የሀገራችንን ሙት ዓመት እናክብር እያሉን ነው፤ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያ የጋራችን የሆነች ሰፊ ሀገር እንጂ፣ የአንድ ፓርቲን መሪ በመከተል መቃብር እንዳልወረደች ማረጋገጥ ይኖርብናል፤ በዕለቱም ሞት ብቻ ሳይሆን ልደትም ጭምር መከበሩ ለነገዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ እንደ አንድ ማሳያ ሊወሰድ ይችላል፤ አሚርን ጨምሮ የእያንዳንዶቻችን ልደቶች የኢትዮጵያን ህያውነት ይመሰክራሉ፤ እርግጥ ነው ዛሬ የአሚር ልደት የሚከበረው ቤተሰቦቹ በተገኘንበት በፎቶ ፕሮግራምና ቁራሽ ዳቦ ነው፤ የአቶ መለስ ሙት ዓመት ደግሞ በተቃራኒው ሀገር እራሷ ስራ ፈትታ ነጠላዋን አደግድጋ ከነልጆቿ እንድታከብር ተገዳለች፤ ነገር ግን የአከባበሩ መድመቅና መፍዘዝ እውነታውን አይለውጠውም፤ አሚር በህይወት ኖሮ ልደቱን እያከበረ ያለ የኢትዮጵያ ተስፋ ነው፤ አቶ መለስ ደግሞ ዳግም ከመቃብር ፈንቅለው መነሳት የማይችሉ ሲሆን፣ ፓርቲያቸው ብቻ በሙት መንፈሳቸው እየነገደ አብሯቸው ቀብር ወርዷል፡፡

ኢትዮጵያ ለሁለቱም እኩል መሆኗን ለግዜው ባለስልጣናቱ ሊቀበሉት ባይፈልጉም፣ ነገ ግን ስለሁለቱም እውነቱን የመመስከር አቅም አላት፤ አባቶቻችን የተነፈጉትን እድል እኛ ልጆቻቸው ካልሆነም ደግሞ የኛ ልጆች እነ አሚር (በእርግጥ እዛ ድረስ አይርቅም) ማግኘታችን ስለማይቀር፣ እውነታው በታሪክ ላይ ስለመስፈሩ ቅንጣት ታህል ልንጠራጠር አይገባም፤ ያኔ በፈጠራ የሽብር ክስ ንጹሀን ዜጎችን፣ ጋዤጠኞችን፣ ፖለቲከኞችን፣ የሀይማኖት አባቶችንና ምሁራንን፣… በእስር ቤት ስላጎሩት፣ ተቃናቃኞቻቸውን በሴራ ስላስወገዱት፣ ምሁራንን ከሀገር ስላባረሩት፣ ሀገሪቱን ወደብ አልባ ስላደረጓት፣ በዘርና በሀይማኖት ስለከፋፈሉን፣ ዴሞክራሲን አንቀው ስለገደሉት፣ ነጻውን ፕሬስ ስላሽመደመዱት፣ ሙስናን ስላንሰራፉት፣ የፈጠራን ክስ ስላስፋፉት፣ ፓርቲ የሀገርን ኢኮኖሚ ጠቅልሎ እንዲቆጣጠር ስላደረጉት፣ ደካሞችን ብቻ ሰብስበው መሪ ስላሳጡን፣ ህዝቡን ካድሬ በሚባል የደካሞች ስብስብ መተንፈሻ ስላሳጡት፣ ኢትዮጵያዊነትን ስለገደሉት፣… አቶ መለስ እና ስርዓታቸው ሁሉም ነገር ይፋ ይወጣል፡፡

የአቶ መለስን የህያውነት ውክልና የወሰደው ፎቷቸውም ሆነ የፎቶው ተከታዮች እያመላከቱን ያሉት የተሻለ ነገን ሳይሆን መቃብራቸውን ይመስለኛል፤ አንድ ወዳጄ በየቦታው የተሰቀለውን እና የሆነ ነገር እያመለከቱ የተነሱትን ፎቶ ባየ ግዜ ‹‹እኚህ ሰው ሞታቸውን ነው እንዴ እያመላከቱን ያሉት?›› ያለው አባባል ይበልጥ ሁኔታውን ይገልጸዋል፡፡ በአሚር ልደት የነገዋን ኢትዮጵያ ከማሳየት፣ በመለስ ሙት ዓመት የዛሬዋን ስልጣናቸውን ማረጋገጥ ይሻሉ፤ ህያውነትን የሚወርሰው ልደቱ ይሁን ሞቱ ቆመው ማሰብ የተሳናቸው ባለስልጣናቱ፣ በአድበስባሽነት ጉዟቸው እነ አሚርም የሞታቸው አግበስባሽ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡

ከአቶ መለስ የሞት ድግስ በቀጥታ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች እና ተቋማት የሉም ማለት አይቻልም፤ በተለይ የአብዛኞቹ ካድሬዎች ህልውና ከአቶ መለስ ሞትና የሞት ወሬ ጋር ከተያያዘ ቆየ፤ ትጋታቸው እየታየ ሹመት የተሰጣቸው ጥቂት አይደሉም፤ የባለስልጣናቱም ታማኝነት በቅድሚያ የሚረጋገጠው የሳቸውን ቃላት እና ድርጊት እንደ ዳዊት በመድገም ነው፤ በየመስሪያ ቤቱ ምስጋና እና የደሞዝ ጭማሪም የሚሰፈረው በየግዜው የሳቸውን ስም በማንሳት፣ የሳቸው ምስል ያረፈበት ካናቴራ በመልበስ እንዲሁም እንደዛሬው የሳቸውን ሙት ዓመት በማስተባበርም ጭምር ነው፡፡

ልማታዊ ጋዜጠኞቻችንም ቢሆን በአቶ መለስ ዙሪያ ፕሮግራም መስራት የመጀመሪያ ተመራጭ ስራቸው ነው፤ ጥቅም አለዋ! ከጋዜጠኝነት መርህ ይልቅ የአቶ መለስን ንግግር ቆራርጦና አጣፍጦ ማቅረብ፣ በየክፍለ ከተማው እየዞሩ የካቢኔዎችን እና አባላትን ለቅሶ የተቀላቀለበት ውዳሴ ማሰባሰብ ተቀዳሚው መስፈርት ነው፤ የሳቸውን መታሰቢያ ፕሮግራም ሀዘን በተቀላቀለበት ድምጽ መስራትማ አማራጭ የማይገኝለት አቋራጭ ነው፡፡ ከዝክረ መለስ ማንኛውም ዝግጅት ጀርባ ያሉ ሌሎቹ ዋነኛ ተጠቃሚዎች ቢልቦርድና ባነር የሚሰሩ የማስታወቂያ ባለሙያዎች ናቸው፤ እያንዳንዱን መስሪያ ቤትና ድርጅት ይሉኝታ በማስያዝ የሚያፎካክሩበት ሁኔታም አለ፤ ተቋማትም ተለቅ ያለውን ባነር (ቢልቦርድ) በማሰራት አጋርነታቸውን ለማሳየት ይሽቀዳደማሉ፤ ታዲያ በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ተጠቃሚ የሆኑት ነጋዴዎች በየቀኑ ሞታቸውን እየዘከርን ብንኖር አይጠሉም ሊባል ይችላል፤ የትኞቹንም ተጠቃሚዎች ብንመለከት ጥቅሙ የጥቂቶች እንጂ የሀገር ነው ሊባል አይችልም፡፡ የነአሚር ልደት ግን ከተሰራበት ጥቅሙ ሀራዊ ከመሆኑ ባሻገር የኢትዮጵያን ትንሳኤ የምናበስርበትም ጭምር ነው፤ ሞትን በማጀገን ተስፋችንን የሚያጨልሙት ሰዎች የልደቱን መኖር ለማየት የማይፈልጉና ያልታደሉ በመሆናቸው፣ የልደቱን መኖር ሊክዱት አይችሉም፤ ለሁላችንም ልደቱን የምናይበት ቅን ልቦና እንዲሰጠን እመኛለሁ፤ በመጨረሻም ይህንን ሁሉ እንድዘባርቅ ምክንያት ለሆነኝ አሚሬ እንኳን ተወለድክ መልካም ልደት ማለት እፈልጋለሁኝ፡፡