Saturday, June 22, 2013

የትኛው አማራጭ ለአሜሪካ?

 
 
“ኢህአዴግን ምን እናድርገው? ንገሩን!”
hearing3
አሜሪካ ከመቼውም ጊዜ በላይ ደንግጣለች። ኦባንግ እንዳሉት ለህዝባቸው “ሬት” ለምዕራባውያንና “ማር” (የቤት ቀጋ፤ የውጭ አልጋ) የነበሩት አምባገነን በድንገት እንደ ተነቀለ ቡሽ ተስፈንጥረው ከሲስተም መውጣታቸው አሜሪካንን አስጨንቋታል። በተለይም እሳቸው አፍነው የያዙት የስርዓቱ “ክፉ ጠረን” አሁን እነርሱ (አሜሪካውያኑ) ደጅ የደረሰ ያህል መፍትሄ ለመፈለግ የወሰኑ ይመስላሉ። አውቀውና ፈቅደው ሲታለሉ የቆዩበትን ጊዜ አስልተው መንገዳቸውን የማስተካከል ስራ የጀመሩት ዛሬ አይደለም። አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት ከመለስ ሞት በኋላ አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ላይ ሚዛኗን ሊያስታት የሚችል ውድቀት የሚደርስባት ኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም ማስተካከል ሲያቅታት ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ።
“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮት ዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” የዛሬ 22ዓመት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ከተናገሩት፡፡
“አሜሪካኖች ነጻ እንድታወጡን አንጠይቃችሁም። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ነጻ እንደሚወጣ ያውቃል። እናንተ ግን በነጻነት መንገዳችን ላይ ዕንቅፋት አትሁኑብን፤ (የነጻነት መንገዱን አትዝጉብን)። ከመንገዱ ላይ ገለል በሉ … እስካሁን ያልተሞከረ መንገድ አለ … እሱም እርቅ ነው … ከመንግሥትም ሆነ ከተቃዋሚው በኩል ዓመኔታ የሚጣልባቸው አሉ … ” አቶ ኦባንግ ሜቶ፡፡
“የሚታየኝ ጦርነት ነው፣ የርስ በርስ ግጭት ነው። የርስ በርስ ግጭት በኢትዮጵያ የመነሳቱ ጉዳይ የማይቀር ነው። አገሪቱ ላለፉት 21 ዓመታት በተጓዘችበት መንገድ አትቀጥልም። … ሕዝብ በጭቆና አገዛዝ እየተገዛ ዝም ብሎ የማይኖርበት ደረጃ ላይ ደርሷል … ዝም ብሎ ግን አይቀመጥም … ይፈነዳል … ይህን እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ” ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፡፡
አቶ መለስ “አሮጋንት /እብሪተኛ/፤ የፈለገውን ነገር በፈለገው ጊዜ የሚያደርግ ሰው … እንደነበር አዲስ አበባ ሄጄ ባነጋገርኩበት ወቅት አረጋግጫለሁ” ክሪስ ስሚዝ፡፡
“እድሜ ልካችሁን አትገዙም ብለን መክረናቸዋል” ዶናልድ ያማሞቶ፡፡
 hearing1የምክክሩ መድረክ
“ኢትዮጵያ ድኅረ መለስ፤ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች የወደፊት ዕጣ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ፤ ከኢትዮጵያ ሁለት ተናጋሪዎች ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ጸሐፊ ዶናልድ ያማሞቶ፣ የአሜሪካ የዓለምአቀፍ የልማት ተራድዖ የአፍሪካ ቢሮ ረዳት አስተዳዳሪ ኤሪል ጋስት፤ የማይክል አንሳሪ የአፍሪካ ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ፒተር ፓሃም እንዲሁም በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመንግሥት ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አዶቴ አክዌ የተጋበዙበት የምክክር ሸንጎ ላይ የቀረቡት ሃሳቦች በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሱ ነበሩ። ሰብሳቢው በአሜሪካ የተወካዮች ምክርቤት በአፍሪካ፣ በዓለምአቀፍ ጤናና ሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች ንዑስኮሚቴ ሰብሳቢ ክሪስቶፈር ስሚዝ ደግሞ ኢህአዴግ ከፍተኛ ገንዘብ አፍስሶ ያኮላሽው ኤችአር2003 የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ረቂቅ ህግ ከሟቹ ዶናልድ ፔይን ጋር በማዘጋጀት በምክርቤት ለማስወሰን ያስቻሉ ነበሩ።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ እንዲሁም በበክኔል ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት የግንቦት 7 ሊቀ መንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እንደ እምነታቸው ንግግር አድርገዋል። ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። በምክክር ሸንጎው ላይ ከተጋበዙት መካካል ኢህአዴግ በቀጥታ ባለመወከሉ “ያለመመጣጠን (ያለመወከል)” ችግር አልነበረም፡፡ ኢህአዴግም ተገኝቶ ቢሆን ኖር ሊናገረው ከሚችለው በላይ ተናጋሪና ተከራካሪ ስለነበረው የኢህአዴግ መኖር አስፈላጊ አልነበረም የሚል አስተያየት ስብሰባውን በአካል ተገኝተው ከታዘቡና በቀጥታ ስርጭት ከተከታተሉ ወገኖች  ተደምጧል።
ያም ሆኖ ግን ምክክሩ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የበላይ ሰው ክሪስ ስሚዝ ቢሮ በመገኘት አሉ የሚሏቸውን መከራከሪያዎች አቅርበው ነበር። የጎልጉል ምንጮች ለማረጋገጥ እንደቻሉት ኢህአዴግ ምክክሩን ተከትሎ ኤች አር 2003 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ የተጠቀመበትን መንገድ ገና ካሁኑ በድጋሚ ጀምሯል።
ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እያደር የእግር እሳት ሆኖ ያለፈውን የ1997 ምርጫ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ በማምራት ከኢህአዴግ መሪ አቶ መለስ ጋር በርካታ ዲፕሎማቶች ተነጋግረዋል። አንዱ ከኒውጀርሲ ጠቅላይግዛት የአሜሪካ ም/ቤት ተወካይ ክሪስ ስሚዝ ነበሩ። “ኢትዮጵያ ከመለስ በኋላ” በሚል የተዘጋጀውን የምክክር ሸንጎ በመሪነታቸው ሲከፍቱ አቶ መለስን “አሮጋንት /እብሪተኛ/፤ የፈለገውን ነገር በፈለገው ጊዜ የሚያደርግ ሰው …” በማለት ነበር የገለጹዋቸው። የርሳቸው ገለጻ ታዲያ ከሁለት ዓስርተ ዓመታት በፊት ኢህአዴግ እንዲነግስ ሲወሰን ከቃል በላይ እሳት እየተፉ ንግግር ያደረጉትን ኢትዮጵያዊ አስታወሰ – የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ!
“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮት ዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የትንቢት ያህል፤ ሳግ እየተናነቃቸው የኢትዮጵያን ተላልፎ መሰጠት በዚሁ በሰኔ ወር ከ22ዓመት በፊት አስረግጠው በማስረጃና በማስጠንቀቂያ በመቃወመ፣ በማሳሰብ፣ እንደማይሆን በመምከር፣ አድሮ እንደሚያቃጥል በማስጠንቀቅ፣ ላቀረቡት ንግግር የክሪስ ስሚዝ ገለጻ በማረጋገጫነት የሚቆም እውነት ይሆናል።
አሜሪካ ራስዋ ቀብታና ባርካ በትረ ሹመት የሰጠቻቸውን ሰዎች ከ22ዓመት በኋላ መልሳ “ገምግሙልኝ” ማለቷ አስገራሚ የሚሆንባቸው ጥቂት አይደሉም። ሰብሳቢው በመግቢያቸው የተናገሩት የኢትዮጵያ መንግስት ወቅታዊ መገለጫ፣ ቀደም ሲል ሚ/ር ያማሞቶን በመጥቀስ ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸውን መረጃዎች ለተከታተሉ “አሜሪካኖቹ ምን የማያውቁት ነገር አለና ነው የሚጠይቁት ያሰኛል” በሚል የሚገረሙ በርካታዎች ናቸው።
obang at hearingለዚህ ይመስላል የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ታሪካዊውን የኮሎኔል ጎሹ “ትንቢትና የኢትዮጵያ ህዝብን የሚወክል የምልጃ መቃተት” በማስታወስ ቀዳሚ የሆኑት። አስከትለውም “አሜሪካኖች ነጻ እንድታወጡን አንጠይቃችሁም። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ነጻ እንደሚወጣ ያውቃል። እናንተ ግን በነጻነት መንገዱን ላይ ዕንቅፋት አትሁኑበት። (ከመንገዱ ላይ ገለል በሉ)” የሚል መልክት አስተላለፉ።
የጋራ ንቅናቄው መሪ በድርጅታቸው መርህ ላይ ተመሥርተው በሰጡት የምስክርነት ቃል “ህወሓት እስካሁን በነጻአውጪ ስም አገር እየመራ እንደሆነ፤ መለስ ለህዝባቸው “ሬት” ለምዕራባውያንና “ማር” (የቤት ቀጋ፤ የውጭ አልጋ) ዓይነት መሪ እንደነበሩና የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 22ዓመታት በመከራ ውስጥ ያለና የዛሬ 8ዓመት በዚሁ ቦታ ላይ ያማሞቶ ኢትዮጵያ በአቋራጭ መንገድ (ክሮስሮድ) ላይ እንደምትገኝ” መናገሩ አቶ ኦባንግ ካስታወሱ በኋላ “መቼ ነው መንገዱን የምናቋርጠው? ከስምንት ዓመት በኋላ አሁም አንሻገርም ወይ፤ አናቋርጠውም ወይ” በማለት ተሰብሳቢውን ያስደመመ ለሰብሳቢዎቹ ግልጽ ጥያቄ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ኦባንግ ሲቀጥሉም “ኢትዮጵያውያን የምንጠይቀው በጣም ቀላል ጥያቄ ነው፤ አሜሪካኖች የሚመኩበትን ሰብዓዊ መብት እኛ ተነፍገናል፤ የራሳችን ክሪስ ስሚዝ ይኑሩን ብቻ ነው የምንለው” ካሉ በኋላ በኃይለሥላሴም ሆነ በመንግሥቱ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ዕድላቸውን እንደተነፈጉ አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱም በዚሁ ም/ቤት የዛሬ 22ዓመት በወርሃ ሰኔ ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ የዛሬዋን ኢትዮጵያን መተንበያቸውን አቶ ኦባንግ በንግግራቸው አስታውሰዋል፡፡ አሁንም የኢትዮጵያውያንን ቁርጠኛ አቋም ምን እንደሆነ ለአሜሪካውያኑ ግልጽ አድርገዋል “አሜሪካ እንድታድነን አይደለም የምንጠይቀው፤ ራሳችንን ማዳን እንችላለን፤ በነጻነት መንገዳችን ላይ ግን ዕንቅፋት አትሁኑብን፤ ራሳችንን ነጻ እናወጣለን፤ ኦባማ ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደር በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሚያገኙት ጥቂት ደመወዝ ለምርጫው ዘመቻ ረድተው ነበር፤ ከኦባማ ግን የሰማነው ነገር እስካሁን ምንም የለም፤ ነጻነታችንን እየለመንን አይደለም፤ ራሳችንን ነጻ እናወጣለን” በማለት የበርካታ ኢትዮጵያውያንን የነጻነት መንፈስ የቀሰቀሰ ንግግር አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ ለውጥ 300 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ሰጥቻለሁ እንደሚል ከጠቀሱ በኋላ “ይህ ሁሉ ገንዘብ የት ነው የገባው፤ የት ነው የሄደው” በማለት ኢህአዴግ ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይ ሥልጣኑን እንደተቆጣጠረ፤ ሙስሊሙ መሪውን እንምረጥ ሲል አሸባሪ ተብሎ እንደሚፈረጅ ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር አገርና መሬት ብቻ ሳይሆን የምንጋራው በደም የተሳሰርን መሆናችን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ አንድ ጊዜም እንኳን ጦርነት ሰብከውም ሆነ መሳሪያ አንስተው የማያውቁ መሆናቸውን የተናገሩት ኦባንግ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት “አሸባሪ” መባላቸውን በመናገር የኢህአዴግን አሸባሪነት አጋልጠዋል፡፡ እስካሁን በአገራችን ላይ የፈሰሰው ደም በቂ እንደሆነ የጠቆሙት የጋራ ንቅናቄው መሪ፤ በኤድስና ምግብ በማጣት የረደሰብን ዕልቂት በቂ እንደሆነና ከእንግዲህ ወዲህ መጋደል እንደሌለብን ሆኖም ከኢህዴግም ሆነ ከተቃዋሚ በኩል አመኔታ የሚጣልባቸው ሰዎች ስላሉ እስካሁን ያልተሞከረውን የዕርቅ መንገድ (ሥራ) በኢትዮጵያ መከናወን እንዳለበት አቶ ኦባንግ ሜቶ በሚመሩት ድርጅት መርህና በሚታገሉለት የማዕዘን ሃሳብ ላይ ተተርሰው ሃሳባቸውን አጠቃልለዋል፡፡
በምክክር ሸንጎው ላይ የተገኙት የግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው የንግግራቸውና የማሳሰቢያቸው ማሳረጊያ ሊባል የሚችል መልዕክት አስተላልፈዋል። ዶ/ር ብርሃኑ “አስተውሉ፣ ልብ ብላችሁ ተገንዘቡ” በማለት ያሳሰቡት ዛሬ ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ የሚጠበቡበት፣ እንዲከሰት የማይፈልጉትን የመጨረሻው ስጋት ነው።nega
በምክሩ ላይ በቀዳሚነት ምልከታቸውን ያብራሩት ዶ/ር ብርሀኑ ኢህአዴግ የዘረጋው የአፈና ስርዓት ያስመረረው ህዝብ፣ ኢህአዴግ ሆን ብሎ የሚያንኮታኩታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሆን ብሎ የሚተናኮለው ህዝብ፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ ብረት ማንሳት ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል። በቅርቡ የኢህአዴግ የአፈና ስርዓት ፈተና እንደሚገጥመው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ቀጣናውን በሙሉ እንደሚረብሽና የአሜሪካንን ጥቅም በእጅጉ እንደሚጎዳ ዶ/ር ብርሃኑ በግልጽ በማስረዳት አሜሪካ ገንዘቧን በተገቢው ቦታ ላይ ማዋል እንዳለባት ምክር ሰጥተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተቃዋሚ ኃይሎች አማራጭ ከማጣት የተነሳ ብረት ማንሳታቸውን የጠቆሙት የግንቦት 7 ሊቀመንበር፤ ሕዝብ ዝም ብሎ በአስከፊ አገዛዝ ሥር እየኖረ እንደማይቀጥል አስጠንቅቀዋል፡፡ በመሆኑም አማራጭ ሲጠፋ ባገኘው መንገድ ሁሉ መብቱን ወደማስጠበቅ እንደሚገፋና በአሁኑ ወቅትም የተቃዋሚ ኃይሎች በመተባበር በኢህአዴግ ላይ ጥቃት መሰንዘር የሚስችላቸውን ብቃትና ኅብረት እንደፈጠሩ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም ኢህአዴግ በምንም መልኩ የማይሰማና በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን ለማስረከብ የማይችል መሆኑን በተለይ በ1997 ምርጫ ካስታወቀ ወዲህ በግልጽ የሚከተለው መርህ በራሱ ማስረጃ እንደሆነ ዶ/ር ብርሃኑ በጥያቄ መልክ ለቀረበላቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኢህአዴግ የደምሥር የውጭ ዕርዳታ እንሆነ የተናገሩት የግንቦት 7 መሪ አሜሪካ ከአውሮጳውያን ጋር በመተባበርና ለእያንዳንዱ የተሃድሶ ዕርምጃ ቀነ ገደብ በመሥጠት በተሰጠው ገደብ ውስጥ እስረኞች ካልተፈቱ፤ የምርጫ ኮሚሽን ካልተቀየረ፤ ወዘተ በማለት ዕርዳታው እንደሚቆም በማስጠንቀቅ አሜሪካውያኑ ለኢህአዴግ መመሪያ ቢሰጡ ለገንዘብ ሲል ኢህአዴግ ሊታዘዝ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም በድጋሚ የሰብሳቢውን ስም በመጥራት ትኩረት የጠየቁት ዶ/ር ብርሃኑ “የሚታየኝ ጦርነት ነው፣ የርስ በርስ ግጭት ነው። የርስ በርስ ግጭት በኢትዮጵያ የመነሳቱ ጉዳይ ነው። አገሪቱ ላለፉት 21 ዓመታት በተጓዘችበት መንገድ አትቀጥልም። ይህን እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ከክሪስ አንደበት
ሰብሳቢው ክሪስ ስሚዝ በምክርቤት ስብሰባ ላይ ድምጽ መስጠት በሚገባቸው ረቂቅ ህጎች ላይ ሲሳተፉ ስለነበር ምክከሩ የጀመረው ከታቀደው ሰዓት 1፡30 ያህል ዘግይቶ በመሆኑ ይቅርታ በመጠየቅ ነበር መንበራቸው ላይ ተሰይመው ንግግር ጀመሩት። የምክክሩ ሊቀመንበር አቶ መለስ የዘረጉት አገዛዝ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ልዩ ባህሪው እንደሆነ የተለያዩ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ምክከሩን ከፈቱ። ምክክሩ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶችና የዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩርና የአሜሪካ መንግሥት ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያመላከት ምክር የሚካሄድበት እንደሆነ አስገነዘቡ።
ኢትዮጵያ እስላማዊ አሸባሪነትን በቀጣናው በመዋጋት የአሜሪካ ደጋፊ አገር ሆና መቆየቷን፣ ሆኖም ግን በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚፈጽመው ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት ተጠያቂ ማድረግ እስካሁን አለመቻሉን ሳይሸሽጉ ተናገሩ።smith3
የፖለቲካ ድርጅቶች በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን፣ መንግስታዊ ባልሆኑ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች (መያዶች) ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ፣ ጋዘጠኞች እንደሚታሰሩ፣ በርካታ ዜጎች ከመሬታቸው እንደሚፈናቀሉ ወዘተ በመዘርዘር አስረዱ።
የአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅት – ዩኤስኤይድ እንደሚለው ከሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ግልጽ ግንኙነት ማድረግ ወደፊት የዴሞክራሲና የለውጥ ሂደቶችን ለማሳካት ይረዳል ተብሎ ቢታሰብም፣ በክሪስ ስሚዝ አመለካከት ግን እምነቱ ሊተገበር የሚችል ቢመስልም እስካሁን ምንም ፍሬ እንዳላመጣ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ስልታዊ አፈናና የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ለሌሎች አገራት መጥፎ ምሳሌ እየሆነ መሄዱን ሊቀመንበር ስሚዝ ጠቅሰዋል፡፡ ንጹሃን ዜጎች ስቃይ፣ ድብደባ እንደሚደርስባቸው፣ በኤሌክትሪክ እንደሚጠበሱና የግዳጅ ወሲብ እንደሚፈጸምባቸው፣ የአምነስቲ ሪፖርት መዘገቡን ክሪስ ስሚዝ በእማኝነት ተናግረዋል፡፡
ራሳቸው ክሪስ ስሚዝ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ረቂቅ ህግ አዘጋጅተው እንደነበርና በወቅቱ የነበረው የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ግን ኢትዮጵያን በአሸባሪነት ላይ ወዳጅ በማድረጉ ምክንያት በነበረው ቸልተኝነት የተነሳ ተፈጻሚ ሳይሆን መቅረቱን አስታውቀዋል። ሚ/ር ስሚዝ እነዚህን ጉልህ ህጸጾች በመጠቆም ምክክሩ ላይ ተናጋሪ እንዲሆኑ የተጋበዙትን ክፍሎች በየተራ በማስተዋወቅ ጋብዘዋል። ከንግግሩ በኋላም ጥያቄዎችን ጠይቀዋል። ሌሎች ተሳታፊዎችም ጥያቄ በመሰንዘር ማብራሪያ እንዲወስዱ ተደርጓል።
ያማማቶ ምን አሉ?
ያማሞቶ በመግቢያ ንግግራቸው መለስን አወድሰዋል። አፍሪካን በዓለም መድረክ ከፍ እንድትል ያደረጉ መሪ በማለት አመስግነው ኢትዮጵያ ተሰሚነቷ እንዲጨምር ያደረጉ፣ ተሟጋችና ጎበዝ ተናጋሪ እንደነበሩ መስክረዋል። ኢኮኖሚውን አሳድገዋል፣ ኢትዮጵያን በቀጣናውና በዓለም ታዋቂ አድርገዋል፣ በሶማሊያ ተሟጋች፣ በሱዳን አስታራቂ፣ በአፍሪካ የአየርንብረት ጉዳይ ደግሞ አንደበተ ርዕቱ አፈቀላጤ ነበሩ በማለት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ከሚደረድረው በላይ ቃል አከማችተው ምስጋና ቸረዋቸዋል።
ያማማቶ በማያያዝ እንደ አምባሳደርነታቸው በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ አስመልክቶ አቶ መለስን ማነጋገራቸውን ጠቁመዋል። በሰብዓዊ መብቱን መጓደል ዙሪያም በተመሳሳይ መነጋገራቸውን  አክለዋል።
ካሊፎርኒያ ሎሳንጅለስ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ወረዳ ተወካይ የምክርቤት አባል ሚስዝ ባስ፤ ያማሞቶን መስቀለኛ ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር። ጠያቂዋ “የኢህአዴግ መንግሥት ዋናው ችግር ምንድነው? ለምንድነው ይህንን ሁሉ መከራና አፈና የሚያካሂደው” በማለት የመገረም የሚመስል ጥያቄ ጠይቀዋል። ያማሞቶ እንደ መንተባተብ ሲሉ “ችግሩ ምንድ ነው?” በማለት ባስ በድጋሚ ጥያቄያቸውን ወረወሩ። “ችግሩ እንዳለ ነው” ሲሉ ደግመው መልስ የሰጡት ያማሞቶ “ጠቅላይ ሚ/ር ሃይለማርያም አፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ እንዳሉት ነው፣ የዴሞክራሲ እሴቶች አስፈላጊ ናቸው፣ መጥፎ ህጎች መወገድ አለባቸው፣ እንስራ፣ እንሞክር ብለዋል” አሉና መለሱ።
ኮንግሬስማን ሜዶውስ በኢትዮጵያ ኢህአዴግ ሁሉን ተቆጣጥሮዋል፤ እኛ አሜሪካኖች ምን ልናደርግ እንችላለን? እንዴት ነው ልናስተካክለው የምንችለው? የሚል ጥያቄ ለያማሞቶ ወረወሩ። ያማሞቶም  “ከምርጫው በኋላ ደስተኞች አለመሆናችንን ተናግረናል፡፡ ከበስተጀርባና በፊትለፊት እየሰራን ያለነው ነገር አለ፡፡ ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ ለምሳሌ በሴቶች ላይ የሚደረግ የመብት ጉዳይ አለ እናም ይህንን ከዩስኤድ ጋር እየሰራን ነው” አሉ፡፡
ሜዶውስ የረኩ አይመስልም “እና ያለው ፍርሃት ምንድርነው?” ሲሉ በድጋሚ መልስ መፈለጋቸውን አመለከቱ። “ነግረናቸዋል ፣ ለዘላለም ልትገዙ አትችሉም። ስለዚህ የተቃዋሚውን ተሳትፎ ማበረታታት አለባችሁ ። እነዚህ ተቃዋሚዎች አንድ ቀን መንግሥት ይሆናሉ። ስለዚህ ዝግጅት መደረግ አለበት ብለናቸዋል” የሚል የደፈና መልስ ከያማሞቶ ተሰጠ።
ጋንት፤ የዩኤስ ኤይድ ረዳት ዳይሬክተር
የሴፍቲኔት ፕሮግራም እየተካሄደ መሆኑንና በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ እየተረጋጋች እንደሆነ፣ ከዚህም ጋር በማከል ኢኮኖሚው እያደገ እንደሆነ ልክ የኢህአዴግ ወኪል መስለው ተናገሩ። ሰብሳቢው ስሚዝ “ቶርቸር በየቦታው አለ እና ይህንን እንዴት ነው ለማስታረቅ ወይም ለማቆም የሚቻለው?” ሲሉ ማብራሪያ ጠየቁ። ሚ/ር ጋንት “አስቸጋሪ ነገር ነው። ቶርቸር እንዳለ እናውቃለን ግን ዋናው ሥራችን መልካም ነገሮችን ለማበረታታት ነው የምንሞክረው” የሚል ምላሽ ሰጡ።
በሚ/ር ጋንት ንግግር ላይ ተንተርሰው ተጨማሪ ጥያቄ ያቀረቡት ክሪስ ስሚዝ፣ ኢትዮጵያ ትምህርትን አስመልክቶ የሚሊኒየም ጎል ተሳክቷል ማለታቸውን ጠቅሰው “ጋንት ግን እኮ ጥራቱ በጣም የዘቀጠ እንደሆነ ነው ሪፖርቱ የሚያሳየው” ሲሉ ሞገቱዋቸው። የዩኤስ አይዲው ዳይሬክተር ጋንት “አዎ ችግር አለ ግን በርካታ መምህራን ተሰማርተዋል በትምህርቱ በኩል ዕድገት አለ” የሚል መልስ መመለሳቸው ለግንዛቤ ያህል የሚጠቀስ ሆኖ አግኝተነዋል።
ያማሞቶና ጋንት ያቀረቡትን ንግግርና ምስጋና ያደመጡ፣ በአካል ተገኝተው የተከታቱተሉ እንዳሉት በምክክሩ ላይ ኢህአዴግ ቢገኝም የሚጨምረው ምንም ነገር ሊኖር እንደማይችል አመልክተዋል።
ዳግም HR2003
የዛሬ አስር ዓመት፤ ኤች አር 2003 በምክር ቤት ደረጃ ከፍተኛ የሸንጎ (ኮንግሬስ) አባላትን ድጋፍ ካገኘ በኋላ የሕግ መወሰኛ ም/ቤት (ሴኔት) አጽድቆት በፕሬዚዳንቱ ተፈርሞ ፖሊሲ ሆኖ እንዲጸድቅ ባለመደረጉ ተቋማዊና አስተዳደራዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮች መከኑ። የህጉ መርቀቅና እንዲጸድቅ የተጀመረው እንቅስቃሴ ያስበረገገው ኢህአዴግ ጡረተኛ የሴኔት አባላት ከሚመሩት ዲኤልኤ ፓይፐር ከተባለ የጎትጓች (ሎቢ) ቡድን ጋር ከፍተኛ በጀት በጅቶ ታገለ። ባፈሰሰላቸው መጠን ጎትጓቾቹ ባልደረቦቻቸውን ጠመዘዙና ህጉ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው አዲስ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ህግ እንዳይሆን ተደረገ። ይህንኑ ህግ በማዘጋጀት ከሟቹ የምክርቤት አባል ዶናልድ ፔይን ጋር በወቅቱ ብዙ ደከሙት ክሪስ ስሚዝ የወቅቱን የቡሽ አስተዳደርን በንዝላልነት መድበው አሁን ይሀንኑ ህግ ተግባራዊ የሚደረግበትን አግባብ እንደሚገፉበት አመልክተዋል።
እንዴት እዚህ ተደረሰ?
የኢህአዴግን የአገዛዝ ዘመን ተቃዋሚዎችን አጃቢ አድረጎ የህግ ሽፋን በመስጠት የሚያራዝመው ዋና ተቋም ምርጫ ቦርድ፣ የፕሬስ ነጻነት፣ የመናገርና የመሰብሰብ ነጻነት፣ የህግ የበላይነት፣ ሕግን የማክበርና የማስከበር ሃላፊነት፤ ወዘተ በኢትዮጵያ ነጻ ከሆኑ ኢህአዴግ ከፊትለፊቱ ካለው ምርጫ የመዝለል አቅም እንደሌለው ይታመናል። ስለዚህም ለድርድር አያቀርባቸውም። ኢህአዴግ ከጅምሩ በህዝብ የማይታመነውና እውቅና የሚነፈገው ራሱን በነጻ አውጪ (ህወሓት) የሰየመ መንግስት ስለሆነ ነው። ነጻ አውጪ እየተባለ አገር መምራቱ አቅዶ፤ ተልሞና መድረሻውን አስልቶ የሚጓዝ ስለመሆኑ ያሳብቅበታል። ለዚህም ይመስላል ስርዓቱ በሙስና የሸተተ፣ በግፍ የገለማ፣ የሚመራውን ህዝብ የሚገል፣ የሚያስር፣ የሚያሰቃ፣ መንግስት ሆኖ  የሚሰርቅ፣ ብሔራዊ ክብርን የሚጠላ፣ ህብረትንና አንድነትን የሚጠየፍ፣ ጎሳና ጠባብ አመለካከት ላይ የተቀረጸ፣ በተራና በወረደ ተግባሩ ለመንግስትነት የማይመጥን መሆኑን የተረዱት አጋሮቹ አሁን ያመረሩበት ደረጃ ስለመዳረሳቸው ምልክቶች እንዳሉ አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል ተናግረዋል።
ይህ የምክክር ሸንጎ እንዴት ሊዘጋጅ ቻለ ለሚለው ጥያቄ በርካታ ጥረቶች መካሄዳቸውን በመግለጽ ዝርዝር ያላቀረቡት አቶ ኦባንግ ሐሙስ በተካሄደው ምክክር በመካከል ላይ ሚ/ር ስሚዝና ሌሎቹ ተወካዮች በምክርቤት ድምጽ መስጠት ስለነበረባቸው ምክክሩ ተቋርጦ እንደገና ሲጀመር ያልታዩበትን ምክንያት ተናግረዋል። ምክክሩ በተባለው ሰዓት ተጀምሮ ያልቃል የሚል እምነት ስለነበራቸው ሌላ ተደራራቢ የጉዞ መርሃግብር አመቻችተው እንደነበር አመልክተዋል።
“አሁን ስራ ላይ ነኝ” ያሉት አቶ ኦባንግ “እስራኤል አገር ለሁለት ከፍተኛ ጉዳዮች መጓዝ ነበረብኝ። አንዱ የወገኖቻችን ጉዳይ ነው። ሌላኛው ደግሞ የአገራችን ጉዳይ ነው። ከጉዞዬ በኋላ ማብራሪያ ለመስጠት እችላለሁ” በማለት ሁለተኛው ስብሰባ ሲካሄድ እርሳቸው ወደ እስራኤል ለሥራ እየተጓዙ እንደነበር አስታውቀዋል።

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በተያያዘ በቅርቡ የተፈጠረውን ቀውስ ምክንያት በማድረግ የሀገሪቷ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካሎች ያካተተ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የፊታችን ሰኞ (ሰኔ 17, 2005) ቀን በጊዮን ሆቴል ጠራ።
በአለፈው እሁድ አዲስ አበባ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የደቡብ አፍሪካ አቻውን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በብራዚል አስተናጋጅነት በቀጣዩ አመት በሚካሄደው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በ13 ነጥቦች ማለፉን ቢያረጋግጥም፣ ከጨዋታው ጥቂት ሰአታት ቆይታ በኋላ የአለም አቀፉ እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፊፋ ኢትዮጵያ ከ ቦትስዋና ጋር ከሁለት ሳምንት በፊት ስትጫወት በሁለት ቢጫ ቅጣት መጫወት ያልነበረበት ተጨዋች አሰልፋለች በሚል ምርመራ በመክፈቱ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ጥፋቱን በማመኑ ኢትዮጵያ ቦትስዋናን 2 ለ 1 በማሸነፍ ያገኘችው ሶስት ነጥብ ቅነሳ እና የ 6 ሺህ የስዊዝ ፍራንክ ቅጣትን ለመጋፈጥ ተገዳለች።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን አስመልክቶ በአለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ለክስተቱ ጥፋተኛ ናቸው ያላቸውን ግለሰቦች ስም ዝርዝር ከማቅረቡ በተጨማሪ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በጥፋተኞቹ ላይ በቅርቡ ተገቢውን ቅጣት በመውሰድ የቅጣት ውሳኔውን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር።
የፊታችን ሰኞ የሚካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የተጠራው “የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከስልጣን ሊለቅ ስለሆነ ነው” የሚለውን አስተያየት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ውድቅ ቢያደርጉትም የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚገልጹት ግን ሁሉም የስራ  አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ባይሆንም የሚለቁ ግለሰቦች እንደሚኖሩ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ስብሰባ የጠራበት ደብዳቤ
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ስብሰባ የጠራበት ደብዳቤ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የፊታችን ጳጉሜ ወር ከመሀከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር በጥሎ ማለፍ መልክ ወደሚካሄደው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ለማለፍ የምድቡ የመጨረሻውን እና ወሳኙን ጨዋታ ያደርጋል።

Friday, June 21, 2013

ሁለት የመከራና የድል ዓመታት (ስለሺ ሐጎስ)



ጸሀዩ(ጠራራው) መንግስታችን ማብረጃውን ይላክለትና ይኸው፡-

ሀገር አልባ ካረገኝ ሀያ ሁለት ዓመቱ
ወደብ አልባ ካረገኝ ሀያ  ዓመቱ
ፕሬስ አልባ ካረገኝ ሰባት ዓመቱ
ሚስት አልባ ካረገኝ ደግሞ ዛሬ ሁለት ዓመት ሞላው፡፡

ግን አለሁ፤ ያውም በተስፋ፤ ከማለዳ ጸሀይ እጅጉን በፈካ ተስፋ እየኖርኩ ነው፡፡

አንድ ቀን ባለ ሀገር እሆናለሁ እያልኩ ስደትን እርም ብያለሁ፤
አንድ ቀን ኤርትራ ወደ እናት ሀገሯ መመለሷን እያለምኩ የወደብ አልባነት ቁዘማዬን ትቼዋለሁ፤
አንድ ቀን ሀገሬ የነጻነት አምባ እንደምትሆን በፍጹም ልቤ በማመን ልሳናቸው ስለተዘጉ ሚዲያዎቻችን መብሰልሰሌን አቁሚያለሁ፤
አንድ ቀን ርዕዮትን እውነት ነጻ እንደምታወጣት ስለማውቅ ከብቸኝነቴ ጋር እንዲህ እዘምራለሁ፡-

Dear my love,
Our vision prevails over their fear…
Our passion prevails over their power…
Our love prevails over their hate…
Celebrate our vision for freedom, passion for justice, love for humanity and፡
I do celebrate your vision for freedom, passion for justice and love for humanity.
Dear Reeyot, …. I love you!

አባይ ሲያግበሰብሰን (መሀመድ ሀሰን)



 አባይ ሰሞኑ ሀይሉን ጨምሯል፡፡ ሁሉንም አግበስብሶ እወሰደ ነው፡፡ ጥግ ቆሞ ክፉና ደጉን የሚያስተውል የጠፋ እስኪመስል አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ ከወንዙ ውስጥ ሰጥመዋል፡፡ መድረሻቸውን ቢጠየቁ ግን አንዳቸውም በእርግጠኝነት አይናገሩም፡፡ ገዢው ፓርቲ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ወጣቱ፣ ሽማግሌው፣ አሮጊቷ፣ ተማሪው፣ ሰራተኛው፣ ተማረው፣ ያልተማረው፣….አብዛኞቹ ያልተተኮሰው ባሩድ እየሸተታቸው ጦርነትን እያበሰሩን ነው፡፡ ከተቃዋሚው ወገን ያየን እንደሆነ የሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ ቀዳሚው ነው፡፡ በአንድ በኩል ኢህአዴግን በሌላ በኩል ደግሞ ግብጽን ተንኮስ የሚያደርገው የሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ፣ ተንኳሽነቱ የሚጀምረው ከርዕሱ ነው፡፡ ርዕሱ ‹‹እነሱ ከአባቶቻቸው አይበልጡም እኛም ከአባቶቻችን አናንስም!!!›› ይላል፡፡ ይህ ርዕስ ምናልባትም የበርካታ ሰሞነኞችን ስሜት ይገልጽ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው መግለጫ ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የሚሰጥ እንደመሆኑ በርካታ ትችቶችን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ የተሻሉ አማራጮችን መጠቆም ያልቻለው ይህ መግለጫ፣ በዘመናት ውስጥ የመጡ ተለዋዋጮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ባለመቻሉ ሩቅና የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን ጦርነት በመናፈቅ ሙቀቱን ለመቀላቀል የቸኮለ ይመስላል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ቀደም ብለው ስለ አባይና ወቅታዊው ጉዳይ ባተቱበት ጽሁፋቸው ላይ ያሰቀመጧት ሀሳብ፣ ለሰማያዊ ፓርቲ መግለጫና በዛ ስሜት ውስጥ ላለን ኢትዮጵያውያን ጥሩ ምላሽ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ፕሮ በጽሁፋቸው ላይ ‹‹…ለፍቅር መተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለጠብም መተዋወቅ ያስፈልጋል፤ የተሟላ መረጃ ቢኖረን የጥንት ታሪክ እየጠቀስን ሰዎችን ለጦርነት አንቀሰቅስም ብዬ አምናለሁ፤…›› ይሉና ከግብጽ የጦር ሀይል አቅም ጋር የተያያዙ እውነታዎችን ማስቀመጣቸውን ይቀጥላሉ፡፡
የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የመገናኛ ብዙሀንንም መረጃዎች የተመለከትን እንደሆነ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ ጦርነትን የናፈቁ ዘገባዎችን ይዘው በመውጣት ጦርነቱን ለማብሰር የቸኮሉ ይመስላሉ፡፡ በእርግጥ ጥቂቶች በተቃራኒው ሌሎች ጥርጣሬዎችን በማንሳት ሌላኛውን ጎን መመልከታቸው አልቀረም፡፡ በዚህኛው ምድብ ውስጥ ያሉት ሰዎች የሰሞኑን ሽኩቻ ለፖለቲካዊ ትርፍ ሲባል ሆን ተብሎ የታቀደ ነው ሲሉ ይጠረጥራሉ፡፡ የግብጽ ፖለቲከኞችም ሆኑ ኢትዮጵያውያኑ ፖለቲከኞች የውስጥ ውጥረታቸውን ለማርገብ የሰሞኑን ሙቀት አልተጠቀሙበትም ማለት እንደማይቻል ነው በዚህኛው ምድብ ውስጥ ያሉት ጠርጣሪዎች ስጋታቸውን የሚገልጹት፡፡ ገና በጽንስ ላይ ላለው አባይ ነጋሪት መጎሰማችን እና በአደባባይ ወንዙን አስቀየስን ብሎ መደንፋቱ ግብጾችን በቶሎ እንዲበሳጩ አድርጓቸዋል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ከነዚህኞቹ ውስጥ እጅግ በጣም ጠርጣራዎቹ ደግሞ ‹‹የተሰበሰበው ገንዘብ ከ10 በመቶ የማይበልጥ መሆኑና ቀረውን ገንዘብ መሰብሰብ ስለሚያዳግት፣ ባለስልታናቱ ሆን ብለው ወደ ጦርነት እንድንገባ ፈልገዋል፡፡›› ይላሉ፡፡ አሁን ላይ ቆመን የትኛው ሀሳብ ትክክል እንደሆነ ለመናገር ቢከብድም በሀገር ጉዳይ ላይ የተለያየ ሀሳብ ተነስቶ መንሸራሸሩ፣ የተሻለውን አማራጭ ለማየት ሚረዳ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡


የምን ጦርነት? ማንስ ሊያተርፍ?

የጦርነቱ መዓዛ ባየለበት በዚህ ወቅት ሰከን ያለ ጽሁፍ ካቀረቡት ውስጥ አንዱ የዞን ዘጠኙ ዘላለም ክብረት ነው፡፡ ዘላለም ክብረት ‹‹ኢትዮጵያ-አባይ-ግብጽ›› በሚለው ጽሁፉ ላይ ካነሳቸው በርካታ ነጥቦች ውስጥ አንዱ የተፋሰሱ ሀገራት ከወንዙ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በዘላቂነት ችግሮቻቸውን ሊፈቱባቸው የሚችሉት አራት አማራጮች ይዘረዝራሉ፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ ተባብሮ መስራት ሲሆን፣ ሁለተኛው አማራጭ ተበደልኩ የሚለው አካል ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ወስዶ ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት ነው፡፡ በሶስተኛነት የተቀመጠው ሌላው አማራጭ ከዚህ በፊት ተሞክሮ ያልተሳካው የላይኞቹን ተፋሰስ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ማሳመጽ እና ኢትዮጵያን አሁን ያለው አጠቃቀም ሳይሳካ አስገዳጅ ውል ውስጥ መክተት ነው፡፡  በአቶ ዘላለም ጽሁፍ ላይ እንደተገለጸው፣ ጦርነት አራተኛውና የመጨረሻው አማራጭ ነው፡፡ በዘሂሁ አማራጭ ውስጥ ቃል በቃል ‹‹… በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ጦርነት ማስነሳት ለህልም የቀረበ አማራጭ ነው፤…›› ይለናል፡፡
ግብጽ በአሁን ወቅት በውሀው የመጠቀም መብታችንን መገደብ ባትችልም፣ ወደ ጦርነት መግቢያ እድሉ  ጠባብ በሆነበት ጦርነትን መናፈቅ ምን ይሉታል? መሪዎቻችንም በህዝቡ ስሜት ተነሳስተው ከጦርነቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ጥቅምን ለመሻት አይነሳሱም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ገና ባልጠነከረውና ጽንስ በሆነው ኢኮኖሚያችን ላይ ጦርነትን መመኘትም ጽንሱን ለማጨናገፍ መሯሯጥም ጭምር ነው፡፡ ህዝቡ በልቶ በማደር ችግር ውስጥ ባለበት ሰዓት የዳቦና የዘይትን በጀት ወደ ጦርነቱ ስለማዞር ማሰብ እብደትም ጭምር ነው፡፡ በጦርነቱ ኢትዮጵያ ክፉኛ እንደምትጎዳ ለማሰብ ጠንቋይም፣ ወልይም መሆን አያስፈልግም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ከላይ በተጠቀሰው ጽሁፋቸው መግቢያ ላይ ‹‹ ጦርነት እንኳን በልቶ ላልጠገበ ህዝባና ለጥጋበኞችም አይመችም፤ የተራበ ህዝብ በጠገቡ መሪዎች ሲነዳ ግን ጦርነት ለአጉል ጀብደኛነት ዝና የሚጠቅም መስሎ ይታያቸዋል፡፡›› ይላሉ፡፡
እንደ ሰሞኑ ያለ እሰጥ አገባ ከዚህ ቀደም በፍጹም ተስተውሎ የማያውቅ አይደለም፡፡ በደርግ ግዜ ኢትዮጵያ እና ግብጽ፣ እንዲሁም ሱዳንና ግብጽ (በአልቱራቢ እና በሆስኒ ሙባረክ ግዜ) ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ፣ ከአሁኑ በባሰ ከፍተኛ የሆነ የቃላት ጦርነት ይለዋወጡ ነበር፡፡ ስለዚህ ትላንትን በመርሳት በቃላት ጦርነቱ ብቻ ተሸብሮ ለሀገራዊ ሽብር መቻኮሉ ቀውሱን ያፋጥነዋል፡፡
ሱዳን በግብጽ ላይ ፊቷን አዙራለች የሚለው ዜና ለኢትዮጵያውያን ጦርነት ናፋቂዎች የልብልብ ሳትሰጠን አልቀረችም፡፡ በሱዳን ላይ ተስፋ መቁረጥ ባይገባም ሙሉ በሙሉ እምነት መጣሉ ግን ስህተት ውስጥ ሊጥለን ይችላል፡፡ ፕሮ እነዳሉት ሱዳንን ጨምሮ አብዛኞቹ ጎረቤቶቻችን ከግብጽ ጋር አብረው የአረብ ማህበርተኞች ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ከእኛና ከግብጽ ማን ያዋጣታል ብሎ መጠየቁ ፌዝ ሊሆን ይችላል፡፡ ሱዳኖች ከኢጥዮጵያ ጋር ባላቸው የሀይል አቅርቦት ንግድ የተነሳ ወደኛ ያደላሉ የሚሉ ትንታኔዎችም ብቅብቅ ሲሉ ይስተዋላል፡፡ ሆኖም ግን እኛ አብዛኛው የነዳጅ ፍጆታችን ከሱዳኖች መሆኑና በተሻለ ዋጋም እያገኘን እንደሆነ ይዘነጋል፡፡ በዚህ በኩል ካየነው ሱዳን ለኛ በኢኮኖሚው በኩል በጣም አስፈላጊዋ ሀገር እንደሆነች ይገለጥልናል፡፡
በሱዳን ላይ ሙሉ እምነት የማያስጥል የቅርብ ግዜ ክስተትም አለ፡፡ ‹‹የናይል ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ስምምነት›› ውል በግንቦት ወር 2002 ዓ.ም ሲፈረም፣ ‹‹አሁን ያለውን የአጠቃቀም ኮታ በማይነካ መልኩ›› የሚል ሀረግ ካልገባበት አንፈርምም ያሉት ግብጽና ሱዳን ነበሩ፡፡ በዚህ የተነሳም ለተፋሰሱ ሀገራት  የተሻለ እልባት ያመጣል የተባለው ህግ ሳይጸድቅ ቆይቷል፡፡ባለፈው ሀምስ ግን ኢጥዮጵያ የቅኝ ግዛት ውሉን ውድቅ በማድረግ የናይል ትብብር መዕቀፍን አጽድቃለች፡፡
ፎርብስ መጽሄት የግብጽ ጦር በኢትዮጵያ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አማራጮች ለማሳየት ሞክሯል፡፡ ከፎርብስ ትንታኔ ብንነሳም ጦርነቱ ተመራጭ የሆነው አማራጭ ሆኖ አናገኘውም፡፡ የግብጾች እቅድ ግድቡን ማውደም እንደሆነ የሚያትተው ፎርብስ ይህንን ለማድረግ ግን መሰናክሎች እንዳሉ ይዘረዝራል፡፡ ለግብጽ ሀይል ዋነኛው ፈተና የሚሆንበት ከግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ያለው ርቀት ነው፡፡ አሁን ካለችበት ርቀት አንጻር ለአየር ላይ ጥቃት እንኳን አመቺ አይደለም፡፡ ግብጽ ሊኖራት የሚችለው ብቸኛው አማራጭ ለግድቡ ቅርብ የሆነችው የሱዳንን የአየር ክልል መጠቀም ነው፡፡ እንደ ፎርብስ ትንተና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ካላት ቅርበት አንጻር ቀጥተኛ የጦር ፍጥጫ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡
በፎርብስ የተቀመጠው ሌላኛው አማራጭ ግብጽ ልዩ ሀይልና ታጣቂዎችን በመላክ ኦፕሬሽን ማካሄድ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ የግድቡን ፕሮጀክት ማዘግየት ወይም ማስተጓጎል ትችላለች፡፡ ሱዳን በዚህ ግዜ ልዩ ሀይሉ ሰርጎ ስለመግባቱ ምንም አይነት ግንዛቤ እንደሌላት ትናገራለች፡፡ በዚህ ሁኔታ ታጣቂዎችን መላኳ ግድቡን ለማውደም ዋስትና ሊሆን አይችልም ላል ፎርብስ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እነዲህ ያሉ ግድቦች በልዩ ወታደራዊ ሀይል የሚጠበቁ መሆናቸው ነው፡፡ የግብጽ ወታደሮች የፈለገ የሰለጠኑ ቢሆንም ቁጥራቸው አነስተኛ ሆኖ መግባታቸው እቅዳቸውን እንዳያሳኩ ያደርጋቸዋል ይላል የፎርብስ ትንታኔ፡፡ በማጠቃለያው ላይም ግብጽ የፈለገው ሀይል ቢኖራት ርቀት ስለሚገድባት ሙሉ የቶር ሀይሏን መጠቀም አትችልም፡፡ የትኛውንም አማራጭ መጠቀም ለግብጽ ዋጋ ያስከፍላታል፤ ይለናልፎርብስ መጽሄት፡፡
ስለዚህ፡ በየትኛውም መንገድ ብንሄድ ጦርነቱ ሩቅ ያለ፡ ብዙ አማራጮች ያልተሟጠጡበትና እንደ መጨረሻ አማራጭ ልናየው የሚገባ እንጂ፡ እንዲሁ ዝም ብሎ ሳያመዛዝኑ ዘው ብለው የሚገቡበት አይደለም፡፡ ጽሁፌን አንድ በላይ ከተባለ ወዳጄ በሰማኋት ተረት ልቋጫት፡፡
ባልና ሚስት ናቸው አሉ፤ አንድ ቀን ይጣሉና ሚስት ረዘም ያለ መንገድ አቆራርጣ ከአባቷ ዘንድ ትሄዳለች፡፡ አባትም የልጃቸው ያለወትሮ መምጣት ስገርማቸውና ‹‹ልጄ ምን ሆነሽ መጣሽ?›› ይሏታል፤ ልጅትም ‹‹ከባሌ ጋር ተጣልቼ›› ትላቸዋለች፡፡ አባት ‹‹በምን ምክንያት ተጣላችሁ?›› ብለው ጥያቄ አከሉ፤ ልጃቸውም ‹‹እየበላን ሳለ አጉርሺኝ አለኝ አላጎርስም አልኩት፡ተጣላንና መጣሁ፡›› ብላ መለሰች፡፡ አባት ይሄኔ ‹‹ከባልሽ አፍና ከአባትሽ ቤት የቱ ይቀርብሻል?›› ሲሉ ጥያቄ አከል ምላሽ ሰጧት፡፡   

Thursday, June 20, 2013

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ሕዝባዊ ንቅናቄ በይፋ ጀመረ


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ሕዝባዊ ንቅናቄ በይፋ ጀመረ

ዛሬ (ሰኔ 13/2005) በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሳወቀው ለ3 ወራት የሚዘልቅ "ሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት" የተሰኘ ሕዝባዊ ንቅናቄ አውጇል።

ሕዝባዊ ንቅናቄው የአዳራሽ ስብሰባ፣ የተቃውሞ ሰልፍ እና የፀረሽብር ሕጉ እንዲሰረዝ የሚጠይቅ ፊርማ (ፒቲሽን) ይሰበሰባል። በዚህም በአዲስ አበባ 6 እና በክልል ደግሞ ለመጀመሪያ ዙር ዐሥር ስብሰባዎች ይካሄዳሉ።

የንቅናቄው ዓላማ የፀረሽብር ሕጉ እንዲሰረዝ፣ የዜጎች መፈናቀል እና የመሬት መቀራመት እንዲቆም፣ የሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት እንዲቀረፍ እና የንግዱ ማኅበረሰብ ውስጥ ፍትሐዊ ውድድር እንዲሰፍን መሆኑ በመግለጫው ተጠቁሟል።

የፓርቲው ተወካዮች "ሌላ ፓርቲ ሲያደርግ አይታችሁ ነው ወይ?" በሚል ለቀረበው ጥያቄ ሲመልሱ "ከሌላ መማር ለአንድነት ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም ሆኖም ስር እስክንሰድ ጊዜ ወስደን ነው እንጂ ዓመታዊ ዕቅዳችን ላይ ነበር። ፓርቲያችን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንጂ በግብታዊነት አይሠራም" ብለዋል። የፀረ ሽብሩን ሕግ እንዲሰረዝ ስለሚያስፈልግበት ምክንያት ሲናገሩ ደግሞ የፀረ ሽብር ሕጉ ከአሸባሪዎች ይልቅ ዜጎችን ለማጥቃት የተዘጋጀ ነው በማለት ንቅናቄው ለሕዝብ ጥቅም መሆኑን "አሁን እየጠየቅን ያለነው ስለአንዱዓለም ወይም ስለአንድነት አይደለም። ስለኢትዮጵያውያን ነው" በሚል ገልጸውታል።

"ፀረ ሽብር ሕጉ እንዲሻር ነው ወይስ እንዲሻሻል የምትጠይቁት?" በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ተወካዮቹ "አንድ አዋጅ ሕገ መንግሥቱን አንዴ ከጣሰ ይሰረዛል። ይህ አዋጅ ግን እስከ15 ጊዜ ሕገ መንግሥቱን ስለሚጥስ መሰረዝ አለበት" ብለው መልሰዋል። "ኢትዮጵያ የውጭ ሽብር ስጋት ቢኖርባትም አዋጁ ዜጎችን ለማፈን የወጣ ነው። ማሰብም ሳይቀር ይከለክላል" ብለውታል።

"የሰልፍ ፈቃድ ብትከለከሉስ?" ለሚለው ጥያቄ ደግሞ "ሕግ ማሳወቅ እንጂ ፈቃድ መጠየቅ አይጠይቀንም። ትግላችን ሰላማዊ ነው፣ አይቆምም" ብለዋል።

Sunday, June 16, 2013

Ethiopia coach warns Bafana Bafana

Collins Okinyo

SuperSport.com

Ethiopia coach Sewnet Bishaw has warned South Africa's Bafana Bafana not to expect an easy time when the two sides clash on Sunday in a crucial World Cup qualifier in Addis Ababa.

Bishaw reiterated that their aim was to get all the three points and further castigated Bafana Bafana coach Gordon Igesund for questioning the suitability of the National Stadium in Addis Ababa.

"Our expectations are to beat South Africa and qualify for the third round. We expect to win just the way as we did against Botswana last week. Playing at home is an added advantage since the whole country will be behind us."

"Our secret of success has been the unity and understanding in the team and this has helped us to go past our opponents easily," Sewnet Bishaw told supersport.com.

"I really fail to understand why the South African coach should be complaining about the pitch. Those are clear signs of fear and I dismiss his opinion and urge him to let the game be decided on the pitch."

On whether his players had improved in their disciplinary issues witnessed during the Afcon hosted by South Africa in January, Bishaw was categorical.

"The players are now more disciplined and more experienced. Most of them were playing Afcon for the first time and that made them very nervous but we have since improved a lot and we have brought in the referees committees to enlighten them on the rules of the game.”

ያችን ልጅ ጠጣናት፡፡

 
በሀብታሙ ስዩም

በአዲስ ጉዳይ መጽሄት ላይ እንደወጣው

ደቡብ አፍሪካ በሚባል ሃገር...በዛች ልጅ ደቡባዊ ክፍል በኩል ጉድ ተሰራን፡፡ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከሚለው ቃል በመቀጠል የሚያስጠራት live sex የሚለው እንደሆነም ታወቀ፡፡መጀመሪያ ጉድ ተባለ በኃላ very good የሚሉ መጡ፡፡ያች ልጅ ከሴራሊዮናዊ ጋር አንሶላ ተጋፈፈች ዘጠኝ ወር ሳይሞላው በመላ ኢትዮጵያዊያ ክርክር ወለደች፡፡
ከክርክሮች ሁሉ ግን የጦፈው በዚህ ድራፍት ቤት በዚህ ጠረጴዛ ላይ እየተደረገ ያለው ሳይሆን አይቀርም፡፡እልኸኛው ሞገሴ፣ስሜት አልባኛው ይጋረድ፣ሙዚቀኛው ቀረሮ እና እኔ ባለንበት ጥግ ላይ፡፡
በሰላም እየጠጣን ነበር ፡፡እንደምታውቁት ወዝ አልባ ሙዚቀኛ ጭር ሲል አይወድም፡፡ሙዚቃው የነሳን ሰላም ሳያንስ ቀረሮ እራሱ ብጥብጥ አስነስቶ ቁጭ አለ፡፡
‹‹በነገራችን ላይ ልጂቱን በማሰመልከት ነጠላ ዜማ እየጨረስኩ ነው፡፡››አለ አንደፓርቲ አባል እየተኩራራ፡፡
ልማዱ ነው ፡፡ ምንም ነገር ይፈጠር ነጠላ ዜማ ሰርቶ ወደ ኢቲቪ ይሮጣል፡፡በብዙ ነገሮች ላይ ነጠላ ዜማ ሰርቷል፡፡የእናቱ ነጠላ ጫማ የጠፋለት ሁሉ ነጠላ ዜማ ሰርቷል፡፡ለብዙ ጊዜያት ሙዚቃ አትችልም እያለን ልናተርፈው ሞከርን ስልችት ሲለን ግን ‹‹በነጥላሁን ዘመን ተፈጥረህ ቢሆን ኑሮ የጥላሁንን ጥላ ትሆን ነበር፡፡››እያለን በጫጫታ አልመለስ ያለንን በጭብጨባ ልንገድለው ወሰን፡፡ ሞገሴ ብቻ ነው የማታገሰው፡፡
‹‹ዜማው ከሙሉቀን መለሰ ሰውነቷ የተወሰደ ነው፡፡››
ሁለታችን ከንፈራችንን በመጠጫው ላይ መርገን ዝም አልነው፡፡
ዝምታችንን ከይሁንታ እኩል አድርጎ በሙሉቀን ዜማ ላይ በጎደሎ ቀን የመጡለትን ግጥሞች ጨምሮ ያንቋርር ጀመር፡፡
‹‹ጣይቱን እያሰብኩ እኮራ ነበረ፡፡
ተዋቡ እያሰብኩ እኮራ ነበረ፡፡
እሷ እፈጠር ብላ አንጀቴ አረረ፡፡
አይ ሰውነቷ…
ቲቸር ነኝ ማለቷ፡፡››
‹‹ዝጋ!››ሞገሴ አምባረቀ፡፡
‹‹እንዴት ነው?››አለን ቀረሮ በጉጉት ተሞልቶ፡፡‹‹ምኑ?››አለው ሞገሴ ንዴቱን ለመደበቅ እየታገለ፡፡
‹‹ግጥሙ…››
ሞገሴ አልራራለትም፡፡
‹‹ግጥሙ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ግጥምህ ሰምቶ በቦክስ ሊገጥምህ የሚመጣ ብዙ ሰው ሊኖር ስለሚችል-እኔ ምመክርህ የጸጋየን ግጥሞች እያነበብክ በጸጋ ብትኖር ነው፡፡አወይ መቃጠል በእውነቱ ለመናገር እኮ በዚች ልጅ የተነሳ ሀገራችን ተደፍራለች፡፡›› ሞገሴ በድራፍት ጥዋ ጠረጴዛውን ወቀረ፡፡
በሞገሴ አነጋገር መሰረት ኢትዮጵያ የምትገኘው ከምድር ወገብ በላይ ሳይሆን ከዛች ልጅ ወገብ በታች ነው፡፡
ሞገሴ ንግግሩን ከመቀጠሉ በፊት በላዩ ላይ የወደቀውን የጉም ቁራሽ የመሰለ ጋቢ አስተካከለ፡፡ድራፍት ቤቱ ሞቃት ነው ስለምን ሞገሴ ጋቢ ደረበ? ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ሞገሴ ጋቢ የሚለብሰው ጋቢ የኢትዮጵያዊነት ምልክት ነው ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡እንደ ሞገሴ ከሆነ ዝሆን በኩምቢው ኢትዮጵያዊ በጋቢው ይታወቃል፡፡ይህ ጋቢ የሞገሴ ሻኛ ይመስል ከሞገሴ ትክሻ ላይ ወርዶ አያውቅም፡፡ እንደሞገሴ ዜጎች ባህላቸውን ሚስቶች ባሎቻቸውን ቢያከብሩ ኑሮ የት በደረስን ነበር፡፡ሞገሴ የሀገሩን ወግ ለመጠበቅ ባለው ቁርጠኝነት መሰረት ድራፍት እንኳ የሚጠጣው ፈረንጅ በሰራው መጠጫ ሳይሆን አንጥረኛ በሰራው ዋንጫ ነው፡፡በዋንጫው ውሰጥ ያለው መጠጥ ኮማሪት የጠመቀችው ጠላ ሳይሆን ፈረንጅ የበረዘውን አተላ መሆኑ ግን ታስቦት አያውቅም፡፡
‹‹እንደው ለምን ብላ ግን ይሄን አጠያፊ ነገር ፈጸመች ?››
‹‹ምክንያቱ ከሁለት አይዘልም…››አለ ነገር ከላባ ማቅለል የሚሆንለት ይጋረድ፡፡‹‹ልጅቱ ከዛ አፍሪካዊ ጋር በግላጭ ለመገናኘት ያሰበችው በሁለት ምክንያት ነው፡፡የመጀመሪያው ከአፍሪካዊያን ጋር ያለንን ግንኙነት ከሀሳባዊ አንድነት ወደስጋዊ አንድነት ለማምጣት አስባ ነው የሚለው ነው፡፡ሁለተኛውን ግን እስካሁን ደረስ አላወኩትም፡፡››
‹‹አሳፍራናለች !››
‹‹አዎ አሳፍራናለች፡፡ሰማኒያ ሚሊየን ህዝብ የተፈጠረበትን ሚስጢር በአደባባይ አሳይታ ጉድ ሰርታናለች፡፡››
‹‹ትናንት መንገድ ላይ ያገኘሁት ጎብኝ… አለባበሴን አይቶ ብዙ ነገር ጠየቀኝ፡፡አጠያየቁ ባህል ሚኒስተር በአዋጅ ፈርሶ እኔ ባህል ሚኒስተር እንደሆንኩ አይነት ነው፡፡ኢትዮጵያዊያን የምታዘወትሩት ባህላዊ ምግብ አይነት ምንድነው አለኝ?የምናዘወትረው ባህላዊ ምግብ ጾም የተባለው ነው አልኩት፡፡የምታዘወትሩት ባህላዊ ሙዚቃ ምንድን ነው?አለኝ፡፡ምናዘወትረው ባህላዊ ሙዚቃ ልመደው ሆዴ የሚለው ነው አልኩት፡፡በስተመጨረሻ ስለባህላዊ እስፖርታችን ሲጠይቀኝ ተፋረሰን፡፡ተወዳጁ ባህላዊ ስፖርታችሁ ምንድነው አለኝ፡፡ትግል ነው አለኩት፡፡‹ትግል ማለት እንዲህ ቢግ ብራዘር አልጋ የምትታገሉት ነው ወይስ ሌላ አይነት ትግል አላችሁ አለኝ፡፡በጣም አናደደኝ፡፡በበሃላችን ላይ በመሳለቁ ምክንያት ከባህላዊ የመደብደቢያ መንገዱች መከካል አንዱን ልተገብርበት አስመርጠው ጀመር፡፡
‹‹በክርን ሰብቄ ልጣልህ ይሆን?
ወይስ በአይበሉባ ላዋልቅህ ይሆን ?
ወይስ በስካልቹ ላንሳህ ይሆን?››እያልኩ ብዙ ካሰብኩ በኃላ ይሄን የኢትዮጰያ ባህላዊ ልብስ ለብሸ ይሄን ባደርግ ኢትዮጵያ ትሰደባለች ብየ በመስጋት የህንዶችን ባህላዊ ልብስ እስክዋስ ድረስ ብየ ሳልነካው ላኩት፡፡ነገሩ አይፈረድበትም አለም ትንሽ ናሙና አይታ ብዙ ደምዳሚ ነች…በቢላደን ሰበብ ጺማም ሰው ትፈራለች፤በደብሊው ቡሽ ሰበብ የነዳጅ ጄሪካኗንን ሳይቀር ትደብቃለች..በዚያች ልጅ ሰበብ የplay boy ሀገር ኢትዮጵያ ሆናለች፡፡››
‹‹እኔ ግን የሃገሬውም የአንተም ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት በፍጹም አልተዋጠልኝም፡፡››አለ ይጋረድ የድራፍቱን አረፋ ከአፉ ላይ
በአይበሉባው እየጠረገ ፡፡
‹‹አንተ እንኳን ነገር እህል እራሱ መች ይዋጥልሃል…ውሃውን ያኑርልህ አንጂ..››
‹‹ይች ልጅ አውቃም ይሁን ሳታውቅ ይሄን ነገር አደረገች፡፡ሆኖም ግን ሃገራችን ኢትዮጰያ በዚች ልጅ ጭን ውሥጥ ትገኝ ይመስል በሷ ሰበብ ሃገራችን ተደፍራለች ማለት አግባብ አይደለም፡፡
በርግጥ ያደረገችው ነገር ውግዘት ሊያስፈልገው ይችል ይሆናል ፡፡ሃገሬውን ላየ ግን ጉዳዩ ከውግዘት አልፎ ውግረት ሊያመጣ እንደሚችል ያስጠረጥራል፡፡
ወጣት ናት የወጣት የቅርብ ጓደኛው ሰይጣን ነው፡፡አሁን እያደረግን ያለነው እሷን ከማሳቀቅ አልፎ ሰይጣንን እንዲያስፈነድቅ መሆን የለበትም፡፡
እንግዲህ ምን ይደረግ ፈርዶበታል፡፡ያደረገችው ነገር በርግጥ አሳፋሪ ነው አዎ አሳፋሪ ነው፡፡የቺቺንያ ሰዎች ፈጣሪ እያያቸው የሚያደርጉትን እሷ ካሜራ እያያት አድርገዋለችና አሳፋሪ ነው፡፡ከዚህ በተረፈ ግን ፍልጥ ይዘን አንጠብቃትም መቸም፡፡››
ይኸኔ ቀረሮ ጣልቃ ገባ፡፡
‹‹አሁን በተነጋገራችሁት ላይ አዲስ የነጠላ ዜማ ሃሳብ መጦልኛል፡፡››
ፈቃደኝነታችንን ሣይጠይቅ የቴወድሮስ አፍሮን ጃ ያስተሰርያል ዜማ ክፉኛ ተዳፍሮ ማቀንቀን ጀመረ፡፡
‹‹ግርማዊነታቸው ቢኖሩልን ኖሮ
ስቅላት ነበረ ቦሌ ላይ ዘንድሮ፡፡››
‹‹ዝጋ!››ሞገሴ አንባረቀ፡፡
‹‹ምነው ግጥሙን አልወደዳችሁትም?››
‹‹ሞት ይሻልሃል እኔ አንተን ብሆን ኑሮ ይሄን የመሰለ ግጥም ከመግጠም ይልቅ በርና መስኮት መግጠም እማር ነበር፡፡››
ቀረሮ ወደኛ ዞረ፤
‹‹አሪፍ አይደለም አንዴ?››አለን በማሪያም አሪፍ ነው በሉኝ በሚል ቅላጼ፡፡
‹‹አሪፍ ነው …አሪፍ ነው ፡፡ለሌላ ሙዚቀኛ ግን እንዳታሳየው የዘንድሮ ሙዚቀኛ የሰው ግጥም ባቻ ሳይሆን የሰው ገጠመኝም ይሰርቃል፡፡
ሞገሴ አምስተኛውን ድራፍት በዘመራ ጠላ ወግ እፍ አፍ ብሎ ከተጎነጨ በኃላ ወደ ቁጭቱ ተመለሰ፡፡
‹‹ቪዲዮውን ሳስተውለው ግን ልጂቱ ሰይጣን ያሳሳታት አትመስልም፡፡ምናልባት ሰይጣኑን አሰስታው እንደሆነ ለማጣራት እሞክራለሁ፡፡ቪዲዮው ምን ያህል በምራባዊያኑ ስውር ድንዛዜ ውስጥ መሆናችን አመላካች ነው፡፡
ይሄን ለማለት የቻልኩት ልጂቱ ስትንቀሳቀስ የነበረው እንደ ኢትዮጵያዊ አለመሆኑን ካስተዋልኩ በኃላ ነው፡፡ኢትዮጵያዊ ሴቶች አውልቂ አታውልቂ የሚገቡትን እሰጣ አገባ ታውቁታለችሁ…አንድን ኢትዮጵያዊ ሴት መቀነት ከማስፈታት አንድን ወታደር ትጥቅ ማስፈታት ይቀላል፡፡
የምረባዊያኑ ተጽእኖ ግን ነውርን ስልጡንነት ፤ ክልከላን መጣስ ዘመናዊነት እያስመሰለው ብዙ ነገራችንን አበላሽቶት ቁጭ አለ፡፡እነሱ ሁሉን ግልጽልጽ አድርገው የገቡበትን ጦስ እኛም እንድንቀላለቀለው እየሣቡን ነው፡፡ወትሮም ክፉ ወዳጅ ጠባዩ ይሄው ነው…አብረን እንጠውልግ አንጂ አብረን እንጽደቅ አያውቅም፡፡
ግርም ሚለኝ ግኝ ይጋረድን የመሰሉት ፈረንጆቹ ሲጎትቱን እነሱ ሲገፉን ማየቴ ነው፡፡በአደባባይ ሲታይ የሚያምርና በአደባባይ ሲታይ የሚያስመርር ነገር አለ፡፡ልጂቱ ይሄን የምታውቅ ይመስለኛል…ግን ምን ይደረጋል ባዕድ ስናይ ብዙ ነገራችን ይረሳናል፡፡ያደረግነው አንገታችንን የሚያስደፋን ሃገር ቤት ተመልሰን የሰው አይን ሲዳፋን ነውና እሷም ለማየት ያብቃት፡፡የልጂቱ ግን አርባ መገረፍ በቀረበት ዘመን በመፈጠሯ ፈጣሪን ታመሰግነው፡፡››
ይጋረድ ጥብቅናውን ቀጠለ፡፡
‹‹በልጂቱ መፍረድ ትክክል አይደለም ፡፡ሁላችንም የውስልትና ልጆች ነን፡፡ያች ልጅ ያደረገችው ከሽህ አመታት በፊት ማክዳና ሰለሞን ያደረጉትን ነው፡፡ለየት የሚያደርገው ንጉስ ሰለሞን ጠቢብ ሲሆን ቦልት ግን ጠርብ መሆኑ ነው፡፡››
‹‹እዚህ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አለኝ፡፡››ሞገሴ አመር ብሎ ተነሳ ፡፡
‹‹አኔም እዚህ ላይ አዲስ ነጠላ ዜማ አለኝ፡፡››ቀረሮ በቆረጣ ገባ፡፡
ሁላችንም ጮህንበት ፤
‹‹ዝጋ…››
ሞገሴ የኢትዮጵያዊያንን ታሪክ ይጋረድ የኢትዮጵያዊያንን ግምጃ እየገለጠ ክርክሩ ቀጠለ፡፡ከብዙ ድራፍት ከብዙ ክርክር ጋር…እየመረረችን እየጣመችን እየረገምናት እያዘንልላት ያችን ልጅ ጠጣናት፡፡