በመሐመድ ሐሰን
(ኢትዮ-ምህዳር ላይ የወጣ)
ግዴላችሁም እመኑኝ ይህ ህዝብ
የተዋጣለት ቀልደኛ ሆኗል፤ "አያውቅም" በሚል ጥቅል ፍረጃ ስናጣጥለው የከረምነው የኢትዮጵያ ህዝብ በብዙ ርቀት
ጥሎን ሄዷል፤… ቀልደኛ በማድረጉ በኩልም አንድ ለሀገሪቱ የሆነው ብቸኛው እና ዝነኛው ቴሌቪዥን ጣቢያችን ቀዳሚውን ስፍራ ይወስዳል፡፡
የኢ.ቴ.ቪ
"ጋዜጠኞች" እና በነሱ አማካኝነት ወደ ቴሌቪዥን መስኮቱ የሚመጡ ባለስልጣናት ያልተሳካ ፖለቲካዊ ተውኔት
አልጥም (አልዋጥ) ያላቸው የጣቢያው ተመልካች የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ከሚተላለፍ አንድ ፕሮግራም ጀርባ የራሳቸውን
ተውኔት፣ትንታኔ፣ቀልድ፣ፍተላ፣… ማቅረብ ከጀመሩ ሰነበተ፡፡… ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2006 ዓ፣ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን
ከሙስና ጋር በተያያዘ "የነቀዙ ህሊናዎች" በሚል "ዶክመንተሪ"ውን ያቀረበ እለትም ያስተዋልኩት
ይህንኑ እውነት ነበር፤ እኔም ዛሬ ያስተዋልኩትን እውነት ላካፍላችሁ መርጫለው፡፡
ሐሙስ ምሽት እኔ የሙያ ነገር
ሆኖብኝ፣ ወዳጆቼና ቤተሰቦቼ ደግሞ የኔ ፍላጎት ተጭኖባቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደ ልማዱ በከፍተኛ ትጋት ሲያስተዋውቀው
የከረመውን "ዶክመንተሪ" ለመታደም ቁጭ ብለናል፤ ዛሬ እንዳጋጣሚ በቤቱ ውስጥ ያለው ሰው ብዛት ቤታችንን ዲሽ
(ቪዲዮ) ቤት እስመስሎታል፤ ከወዳጆቼ አንዱ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በጣቢያው እና በርዕሱ ላይ ትችቱን መሰንዘር ጀመረ፡-
"እኔ የምለው? አንድ የነቀዘ
ጣቢያ እንዴት ስለ ንቅዘት ማውራት ይቻለዋል?... አረ በናታችሁ እኛንም በፕሮፖጋንዳቸው ከማንቀዛቸው በፊት ጣቢያ ቀይሩልን!…"
ሲል ምሬት ያየለበት አስተያየቱን ሰነዘረ፤ ሌላው ተከተለ፤
"ጋዜጠኞቹ እራሱ እኮ ይሄኔ
ይህንን ፕሮግራም ለመስራት በቅድሚያ ሙስና በልተው ይሆናል፤… "… የውይይት አቅጣጫው መልኩን ቀይሮ ከፕሮግራሙ ይልቅ ፕሮግራሙን
በትዕዛዝ የሰሩት የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰራተኞች ናዳ ይወርድባቸው ጀመር፤… ለተወሰነ ጊዜ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅቶች ውስጥ
ይሰራ የነበረው ወዳጃችን እውነተኛ ያለውን ገጠመኝ ያካፍለን ጀመር፡-
"ጋዜጠኖቹ ሙሰኛ መሆናቸውን
ትጠራጠራለህ እንዴ?... ህዝብ ከፍሎ በሚያስተዳድረው ጣቢያ ውስጥ ደሞዝ ተከፍሏቸው እየሰሩ፣ የህዝብን ጉዳይ እንዲዘግቡ
ስንጠራቸው በስንት ልምምጥ መሰላቹ የምናሰራቸው?... ከካሜራ ማኑ ጀምሮ እስከ ሪፖርተሮቹ ድረስ ከሌላው ሚዲያ የተለየ ተጨማሪ
አበል እንዲከፈላቸው ይፈልጋሉ፣ የተለየ እንክብካቤ ለምን አልተደረገልንም ብለው ይንጫነጫሉ፣ አበል እንደሌለው ካወቁ
አይመጡልህም፣…ስንቱን ዘርዝሬ ልንገራችሁ? በቃ ባለስልጣን በሏቸው!"
የወዳጄ ንግግር እኔም በግል
የታዘብኳቸውን እውነቶች አስታወሰኝ፤ እውነት ለመናገር የጣቢያው ሰራተኞች ካለባቸው ችግር ጥቂት ትዝብቱን ብቻ ነው ያጋራን፤…
ኢ.ቴ.ቪ ካልተገኘ በሚል የተሰረዙ ስብሰባዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፤… በጣቢያው ውስጥ ቁጭ ብለው ፓርቲው በሚሰፍርላቸው ቀለብ ታግዘው፣ የፓርቲውን ውዳሴ እና ጥቅማጥቅም ለማግኘት
ምስል እየቆራረጡ "ዶክመንተሪ?" ብለው የሚያቀርቡ ሰዎችንም ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡… በዩፕሮግራሞች ላይ
ግንባር እንዲያስመቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸውም በገዢው ፓርቲ ጸበል የተጠመቁት ናቸው፡፡…ከጣቢያው ጋር የተያያዙ ጉዶች ድርሳን ሊወጣቸው
የሚችል ቢሆንም ወዳጆቼ አሁንም ውይይታቸውን ስላላቆሙ ላስቀድማቸው፤
"በደንብ ይግረማቹና ጋዜጠኞቹ
ለፕሮግራሙ የሚሆናቸውን ሰው የመረጡት በምንም መመዘኛ ሳይሆን፣ በተለያየ የሙስና መንገድ ነው፤…" አለ ብዙ ጊዜ
ከኢ.ቴ.ቪ ጋዜጠኞች ጋር እንደሚዝናና የሚያወራው ሌላኛው የቤታችን ታዳሚ፡፡
አሁን ፕሮግራሙ ሊጀመር ነው፤…
የፈረንጅ ፊልም ለማየት መጥቶ፣ ክርክራችን ፕሮግራሙን የማየት መጠነኛ ጉጉት የፈጠረበት ቀልደኛው ጎረቤታችን፣ ፀጥታ ለማስፈን
ሲል፡-
"እባካችሁ ዝም በሉ፤
ፕሮግራሙ ከጀመረ ቦሃላ፣ አይደለም እንደናንተ አይነት ፀረ-ልማት አስተያየት፣ ተራ ወሬ እንኳን ከሙሰኞቹ ተርታ ሊያሰልፈን
ይችላል፤…አልያም የኢ.ቴ.ቪን ፕሮግራም ለማሰናከል የሞከሩ አሸባሪዎች የሚል ክስ ሊያስቀርብብን ይችላልና ፀጥ በሉ! ፌዴራል
ፖሊስ በቆመጡ ፀጥ ከሚያሰኛቹ እኔ በምክሬ ብገስፃቹ ይሻላል፤" ብሎ ፕሮግራሙን ለማየት ወደ ቲቪው ከመዞሩ ማስታወቂያ
ሲለቀቅ ተመለከተ፤ "ዶክመንተሪው" በስፖንሰር መታገዙ ነው እንግዲህ፤… ጎረቤታችን ተግሳፁን ሳይጨርስ ለሌላ
ውይይት የሚጋብዝ አግራሞቱን ሰነዘረ፡-
"በለው! ላንቺም ‘ስፖንሰር?!
ይህ ነው እንጂ የተዓማኒነት እመርታ!"… አንዱ አንዱን እየተከተለ ቀጠሉ፡፡
"አንተ ደግሞ፣ የሚከታተለው
ቢጠፋ እንኳን እንደነ "ገመና" ምናምን በማስታወቂያ ሞቅ ደመቅ! ይበል እንጂ፤" አለ መንግስታዊ
ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ይሰራ የነበረው ጓዴ፤
"ግን ድርጅቶቹ ምን ለማትረፍ
ነው እንዲህ ያለውን ደረቅ ፕሮግራም የሚያስተዋዉቁት?" ጎረቤቴ ጠየቀ፡፡
"እንዴ ምን ነካህ ጣቢያው
እራሱ እኮ መንግስት ሆኗል፤ በመጀመሪያ በትህትና አጋርነትህን እንድታሳይ ይጠይቅሀል፤ ካንገራገርክ በሙስና ክስ ማስፈራራት
ነው፤… ለነገሩ ያን ያህል መድከም አስፈላጊም ላይሆን ይችላል፤ የየተቋማት ሀላፊዎች እራሳቸው እንዲህ ያለውን የእጅ መንሻ
ትብበር በማድረግ ከተጠያቂነት ማፈግፈግን እንደ አማራጭ ይጠቀሙበትም ይሆናል" በመጀመሪያ ትችት መሰንዘር የጀመረው
ወዳጄ ነበር፡፡
አሁን ከ‘ስፖንሰሮቹ ማስታወቂያ
ተመልሰናል! ፕሮግራሙም የምር ጀምሯል፤… በየፕሮግራሙ መሀል ማስታወቂያ እየገባ ባይረብሸኝም፣ በዙሪያዬ ያሉ ወዳጆቼ ግን
በሰሙት እና ነገር ላይ ሁሉ ትንታኔ በመስጠት ከተመስጦዬ እያናጠቡኝ ነው፡፡…
በፕሮግራሙ የሆነ ደቂቃ ላይ ህይወት
በአድሎዋ ሙስና የሰራችባቸው ጎልማሳ ብቅ ብለው ሙሰኞችን "...ጸረ-ልማት ናቸው፤…እኔ በልቼ የቀረው ይሙት የሚሉ…
የውጪ ጠላት ይሻላል!..." ዓይነት አስተያየታቸውን ሲሰነዝሩ፣ የፍልስፍና መምህር የሆነው ወዳጄ አድናቆቱን መሰንዘር
ጀመረ፤
"እውነትም እኮ ይህ ህዝብ ቅኔ
ነው! አያችሁልኝ ባገኘው አጋጣሚ ባለስልጣናቱን ልክልካቸውን ሲነግራቸው?..." ጎረቤቴ በአስተያየቱ ግራ ተጋብቶ፡-
"የታሰረን ባለስልጣን ልክ
ልኩን መንገር ምን ያስገርማል?" ሲል ጠየቀ፤ ለተናጋሪው አድናቆት የቸረው መምህሩ ወዳጄም፡
"ምን የታሰሩትን ብቻ አሁን
ስልጣን ላይ ያሉትንም ሰዎች ልክ ልካቸውን እየነገራቸው ነው እንጂ!... ሙስና እኮ የስርዓቱ መገለጫ ነው፤ የደም ስር!
ልትለው ትችላለህ፤ አሁን የሚያወሩትን ድራማ እንዳትሰማ፤ ሙስናን እንደሚሉት አከሰሙት ማለት አብረው ስርዓቱን ወደ መቃብር
አወረዱት ማለት ነው፤… እንደውም አንድ ነገር ልንገርህ፤ እኔ እንደሚመስለኝ እንደውም፣ ከገዢው ፓርቲ ይፋ ያልሆኑ አስርቱ
ትዕዛዛት አንዱ፣ ‹ሙሰኞቹን አትንኳቸው! መንግስቴ የፀናችው
በነሱ ነውና!› የሚል ይመስለኛል፡፡"
ፕሮግራሙን በትጋት ለመከታተል
የማደርገው ጥረት በሁለት መንገድ እየተሳካ አይደለም፤ አንድም ጓደኞቼ እያናጠቡ ሲያስቸግሩኝ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከፕሮግራሙ
ይልቅ ጆሮዬ ወደ ወዳጆቼ ትንተና እየተሳበ አስቸግሮኛል፤ ህግ በመማር ላይ ያለው ወዳጄ የበኩሉን ማለት ቀጠለ፡-
"የፕሮግራሙ አዘጋጆችም ሆኑ
ተሳታፊዎቹ ለመንግስት በመወገን በህጉም ላይ ጭምር ሙስና እየሰሩ ነው፤ እንዲህ ያለውን ያለፍርድ ቤት ውሳኔ የፍርድ ቤትን ስራ
መስራት ለኢ.ቴ.ቪ ከተሰጠው ቆየ፤ ይህ ሁኔታ ከዚህ ቀደም በጋዜጠኞች፣ በፖለቲከኞች፣ በሙስሊሞች፣ እና ሌሎች ክሶችም ላይ የታየ ነው፤…"
አማርኛ እና ትያትርን አጥንቶ
የተመረቀው ወዳጄም፣ የህግ ተማሪው ወዳጄን ትንተና ተከትሎ ያስተዋለውን አከለ፡
"በነገራችን ላይ እኚህ
ለምስክርነት የቀረቡት ሰዎች እራሱ የሙስና ክስ ያለባቸው ነው የሚመስሉት፤ በድንጋጤ ውስጥ ከመሆናቸው የተነሳ ቋንቋቸው
የተሰናሰለ አይደለም፤ ሙስና የሚለውን ቃል በጥራት ለመጥራት የቸገራቸውን አስተውያለው፤ ንግግራቸው ሁሉ ባልተሳካ ቃለ ተውኔት
የታጀበ ነው፤ ስለዚህ በቋንቋችን እና በተውኔት ላይ ጭምር ሙስና እየሰሩ ነው፡፡…"
ሟቹ ጠ/ሚኒስትር በ‘ስክሪኑ ላይ ገጭ
ሲሉ፣ ውይይታችንን ይሰሙ ይመስል ሁሉም ፀጥ አለ፤ እሳቸውም አሉ፡ "...መንግስት አንድ እጁን ታስሮ ነው የሚታገለው፤
እጁም እግሩም ያልታሰረው ተራው ህዝብ ነው፤…" የሳቸውን ንግግር ተከትሎ ዳግም ፀጥታውን ጎረቤቴ አደፈረሰው፡
"የትኛውን ህዝብ ነው
የሚሉት? ህዝቡ ነው እንጂ ካለሙስና አላሰራ ባሉት የስራ ሀላፊዎች እግር ከወርች የታሰረው እና በግድ የሙስና ተሳታፊ እንዲሆን
የተገደደው፤… እዩት ደግሞ ይሄኛው መተባበር አለብን ይላል፤ ገዢዎቻችንን ለማጋለጥ መተባበር መጨረሻው ቃሊቲ ገብቶ መሰባበር
መሆኑ አልገባውመ፤…"
ቲቪውንም ወዳጆቼንም ለመከታተል
የማደርገው ጥረት እንደቀጠለ ነው፤…የጠ/ሚኒስትሩን አዳኝነት ሲመሰክሩ የነበሩ ሰዎች በአንድ ዶክመንተሪ ላይ አብረው በመሳተፍ
ህልማቸውን አሳክተዋል፤ በጠ/ሚኒስትሩ ምጡቅነት ለናወዙ ልጆቻቸውም ይህ አጋጣሚ እንደ ጥሩ የምስራች የሚቆጠር ሳይሆን
አይቀርም፤…
በዙሪያዬ የከበቡኝ ተንተኞች
እየተዳከሙ ነው፤ የኢ.ቴ.ቪ ማጫወቻም ፕሮግራሙ ቋቅ ብሎት ይሁን ወይም ደግሞ መሀይም ነው ምንም አያውቅም ብለው የሚንቁት
የኢትዮጵያ ህዝብ እርግማን ደርሶ ይሁን አላውቅም ፕሮግራሙ መቆራረጥ ጀመረ፤ ታዲያ በዚህ መሀል ተዳከሙ ካልኳቸው ጓደኞቼ
አንደኛው "ደግሞ ከሰሞኑ ማን ላይ እርምጃ ሊወስዱ ይሆን?... እኔ ግን ሳስበው ሳስበው ከመብራት ሀይል ሰዎች ጋር
ሳይቃቃሩ የቀሩ አይመስለኝም፤…" አለ፤ እሱን ተከትሎም ከመጠን በላይ የተለቀቀ ሀይል ቴሌቪዥኑን አቃጥሎበት፣በኛ ቤት
ቴሌቪዥን ላይ ጥገኛ የሆነው ጎረቤታችን የረሳው ንዴቱ ብልጭ ብሎበት፡ "እነሱንማ ይበሏቸው! እነሱ በሙስና ብቻ
ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ በማሳቀቅ የሽብር!፣ የጥፋት!፣ የውድመት!...!! ወንጀል ነው መጠየቅ ያለባቸው፤
የሀገሪቱን ህዝብ ጨለማ ውስጥ እንዳኖሩት ሁሉ ጨለማ ክፍል ውስጥ ማሰር ነው!..." እያለ ብሶቱን አሰማ፡፡ ሁሉም
እሱን ተከትለው ብሶታቸውን ሲግተለትሉ መብራት ሀይል እርግማኑን ለማብረድ በማሰብ ይመስላል መብራቱን አጠፋው፤ እኛም በያዝነው
ወሬ ተመስጠን ፕሮግራሙ ይለቅ አይለቅ ሳናውቅ የመብራቱ መጥፋት ከትንታኔያችን ገታን፤ አንደኛውም እንዲህ ሲል አከለ፡
"አረ እናንተ ሰዎች ግዴላችሁም እኚ ሰዎች ሁሉ ነገራችንን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው እየሰሙን ሳይሆን
አይቀርም፤"… በጨለማው ላይ የወዳጃችን የመጨረሻ ንግግር ስጋትን አክሎበት ተለያየን፡፡
እኔ ግን ፕሮግራሙንም፣ መብራቱንም፣
ወዳጆቼንም ሸኝቼ የፍልስፍና መምህሩ ወዳጄ "ሙሰኞቹን
አትንኳቸው! መንግስቴ የፀናችው በነሱ ነውና!" ሲል ከሰነዘረው ሐሳብ ጋር ቀርቼ ሰሞኘኛውን የ
"ኢትዮ-ምህዳር" ጉዳይ ከኢህአዴግ የሙስና እርምጃ ጋር ማሰላሰል ጀመርኩኝ፡፡
የ"ኢትዮ-ምህዳር"
ጋዜጠኞች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ የደረሱባቸውን ክሶች፣ አደጋዎች፣ መጉላላቶች፣ እስር፣… ስንመለከት ምንጩ ይኽው የስርዓቱ
ሙሰኞችን አይነኬነት ማሳያ ነው፤ በሙስና ላይ የምር ዘመቻ ማካሄድ አደጋ እንዳለው እና ሙሰኞችም ሀይ ባይ እንደሌላቸው፣ ከህግ
በላይ እንደሆኑ እና እርስ በርሳቸውም እንደሚፈራሩም ጭምር በግልጽ
የታየበት ነው፡፡
በጋዜጣዋ ላይ ክስ ሊቀርብ ይችላል-
ግድ የለም፤ ከህግ አግባብ ውጪ ከከተማ ከተማ እያዟዟሩ ማጉላላትን ምን ይሉታል?.. ይህንንም ይሁን ብለን እንለፍ፤ የአንድ
ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና ስራ አስኪያጅ ያለምንም ክስ በባለስልጣን ትዕዛዝ ጆሯቸው ተይዞ እንደ በግ ተወስደው ሁለትና ሶስት
ቀናት እስር ቤት የሚታጎሩበት አካሄድ ምን ይነግረናል? ሀይ ባይ እንዴት አጡ? ማንስ ነው የሚናገራቸው? ከህግ ውጪ ያለውን
እርምጃቸውንስ ማነው ያወገዘው? የማውገዝ ሞራል ያለው አካልስ ይኖር ይሆን? በሙስና ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃስ ምን ያህል
እውነተኛ ነው?... የሚሉ በርካታ መሰል ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፤ ዞሮ ዞሮ ግን ሁኔታዎች ሁሉ የመምህሩን አባባል
የሚያስረግጡ ይመስላሉ፤ "ሙሰኞቹን አትንኳቸው!
መንግስቴ የፀናችው በነሱ ነውና!" … ከተነኩ እንግዲህ ከሰሞኑ እንዳስተዋልነው እንደ በግ በማንኛውም
ተቆጣጣሪ በሌለው ባለስልጣን ትዕዛዝ እንደ በግ ተጎትቶ ከከተማ ከተማ መንከራተት፣ አልያም ያለጥያቄ መታጎር ነው፡፡
"ሙሰኞቹን አትንኳቸው! መንግስቴ የፀናችው በነሱ ነውና!"
ሀገሪቱ ላይ የተንሰራፋው የሙስና
ስርዓት ህጋዊነትን የተላበሰ ይመስላል፤ ስርዓቱም ከላይ እስከ ታች በጉዳዬ ስለተዘፈቀ፣ "ዙፋኔን እስካልነቀነቅክ ድረስ
ደሀ ሀብታም ሳትል ዝም ብለህ ጋጥ!" የሚል ውስጠ ደንብ እንዳለው ያስጠረጥራል፡፡…
ሀገሪቱ ላይ ከሙስና የጸዳ ሀብታም
ማግኘት ህልም እየሆነ ነው፤ ከስርዓቱ ጋር እስከተስማሙ ድረስ ህጋዊነታቸው ይታወጅላቸዋል፤ የተኳረፉ ቀን ደግሞ የወንጀል
መዝገባቸው ገለጥና ወደ ወህኒ ይወርዳሉ፤ ሁሉም እንዲህ ያለውን ማኖ እንዲነካ ይበረታታል፤ በስርዓቱ ላይ ፋውል የሰራ ቀን
ወይም ሊሰራ ያሰበ ቀን ብዥሙ አንገቱ ላይ የገባው ገመድ ይጎተታል፡፡…
በቀደመው ስርዓት የሀብት መጠን ከፍ
ባለ ቁጥር ስጋቱ የመወረስ ነበር፤ አሁን ግን ከታች እስከ ላይ ባሉ የስራ ሀላፊዎች የመጋጥ ስጋት ተቀይሯል፡፡…
አንድ ምርር ያለው ነጋዴ ከሰሞኑ
እንዳለኝ ብዙ ሀላፊዎች ወንበር ላይ በተቀመጡ በወር እና በሁለት ወራቸው ከአናታቸው ላይ ቂቤ ይፈሳል፤ በአባዛኛው ዜጋ አናት
ላይ ደግሞ እሳት ይንበለበላል፡፡
የኢህአዴግ መንግስት በሙስና ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ከመቀረፍ
አቅም በላይ እንደሆነና ችግሩም ከግለሰቦች ይልቅ ስርዓታዊ እንደሆነ የሚያምኑ ምሁራን ቁጥር በርካታ ነው፤ ባለፈው አዋራ
ያስነሳው የጉምሩክ ከፍተኛ ሀላፊዎች እስር ወቅት ከተጻፉ ድንቅ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ የዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ፅሁፍ ነው፤
ዶክተር "ከሕዝባዊ ታጋይነት
ወደ ግለሰባዊ ሙሰኝነት" በሚል በ"አዲስ
ጉዳይ" ላይ ባቀረበው ትንታኔ ላይ ይህንኑ እውነት የሚያረጋግጥ ነው፤ ዶክተር ዳኛቸው "አገሪቱ ላይ የሚስተዋለው ሙስና ሥርዐታዊ ነው ወይስ
ከግለሰቦች የሞራል ግድፈት የመነጨ?" በሚል በሚሰነዝረው የመጀመሪያ ጥያቄው ላይ፡ "…ሙስና የግለሰብ የሞራል
ድክመትንም የሚያሳይ ቢሆንም መነሻው ከሥርዐት ጋር በጣም የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡" ይላል፡፡ ሶስት መሰረታዊ
ጥያቄዎችን አንስቶ ሰፋ ያለ ትንታኔ በሚሰጠው የዳኛቸው ጽሁፍ ውስጥ በርካታ እውነቶችን ግልጽ ብለው እናገኛል፤ እስኪ እኔ
ለተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ማጠናከሪያ የሚሆኑኝን ነጥቦች ከጽሁፉ ውስጥ አለፍ አለፍ እያልኩ ልጥቀስ፡-
…አሁን በአገራችን ያለውን ሁኔታ ስናይ “ሠርተህ ብላ” ሳይሆን “ተደራጅተህ ብላ” መሆኑን እንረዳለን፡፡
…ሀብት ለማፍራት ወደ ንግድ ዓለም መግባት አስፈላጊ
መሆኑ ይቀርና ሰፊ የሀገር ሀብት ወደ ሚያስተዳድረው የመንግሥት መዋቅር መግባት አትራፊና የሀብት መንገድ ይሆናል፡፡
…መንግሥት እንደ ፊውዳል ሥርዐቱ የመሬት ባለቤትነቱን
ካልተገፈፈ ሙስና ይጸዳል ብሎ መገመት ትልቅ የዋሕነት ይመስለናል፡፡
…በየትኛውም ዓለም እንደታየው ከፍ ያለ ንብረት
አስተዳዳሪ የሆነ መንግሥት ከፍ ወዳለ ሙስና መውደቁ አይቀሬ መሆኑን እናስታውሳለን፡፡
…ማንኛውም ሥርዐት ሙስና ተንሰራፍቶበት ረዘም ላለ ጊዜ
እያደገ በሚሔድበት ጊዜ ሥርዐቱ ፍጹማዊ እክልና ውድቀት እንዳይገጥመው አንዳንድ የእርማት እርምጃዎችን መውሰዱ አይቀሬ ነው፡፡
…ሙስና በአገራችን የፖለቲካ ሕይወት በራሱ የቆመ ነገር
ሳይሆን ከሥርዐቱ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው፡፡ የኢህአዴግ አሁን የተጀመረው የ“ፀረ-ሙስና” እንቅስቃሴ መሠረታዊ ከሆነ
የሥርዐት ለውጥ ውጪ የሚካሔድ ስለሆነ የምዝበራ ሂደቱን ትንሽ ሊያስታግሰው ይችል እንደሆነ ነው እንጂ በምንም መልኩ ሊቆጣጠረው
አይችልም፡፡
…ኢህአዴግ በብዙኃኑ ስም ከመሬት ነጠቃ፣ ከቤት
ማፍረስ፣ ከደመወዝ መቁረጥ፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ በፖሊስነት እንዲያገለግል በማድረግ፣ በቂ ካርታ የሌላቸው ወጣቶች ወደ ንግድ
ዓለም ለመግባት ሲያስቡ በድርጅቱ እንዲታቀፉ ማስገደድ፣ ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው የሚወጡ ሥራ እንዲያገኙ የፓርቲ አባልነትን
በመስፈርትነት ማስቀመጡ ከላይ ለጠቀስነው የግለሰብ መብት ረገጣ እንደማሳያ የሚቀርብ ሲሆን፣ በሌላም ሥርዐቱ በመንግሥትና
በፓርቲ መሐል ልዩነት የማያውቅ ጠቅላይና አካታች (Totalize የሚያደርግ) መሆኑን ያሳየናል፡፡
…አንዳንድ የፖለቲካ ፈላስፎች እንዳሳሰቡት “ሥልጣን
ያማስናል፤ ፍጹማዊ ሥልጣን ደግሞ ፍጹም ያማስናል” (Power Corrupts, Absolute power corrupts
absolutely) ይህም የሥልጣን ብልግና በሙስና፣ በአድልዎ፣ በሞራል ዝቅጠት፣ በምዝበራ፣ በንዝህላልነትና በማንአለብኝነት
ይገለፃል፡፡
ዳኛቸው ያነሳትን አንድ ምሳሌ እኔም የዘመኑን ሙሰኞች በደንብ የምትገልጽ ስለመሰለኝ፣ አስፍሪያት እንሰነባበት፤
….በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩ ዳኛ የመንግሥት ገንዘብ አጉድሎ የተከሰሰና በእርሳቸው ችሎት ቀርቦ
ጥፋተኛነቱ ለተረጋገጠ ሰው የሠጡትን ተግሣጽ ልናጋራ እንወዳለን፡፡
ዳኛው ለተከሳሹ— “ሰማህ ወይ? የመንግሥት ገንዘብ ሲያዝ ልክ ለቡጢ እንደተዘጋጀ ሰው እጅህን ጭብጥ አድርገህ ትይዘዋለህ፡፡ ከዚያም እጅን ‘ጠበቅ ጠበቅ’ ስታደርገው ጨብጠህ ከያዝከው ነገር ‘ፊጪጭ ፊጪጭ’ እያለ የሚወጣውን ላስ ላስ ታደርጋለህ እንጂ እንደው በመንግሥት አገር እጅህን ከፍተህ ትገምጠዋለህ?” አሉት፡፡
አሁን የሚካሔደውን ምዝበራ በምናይበት ጊዜ የዳኛው ምክር ሕጋዊ ጥያቄ ሊያስነሣ ቢችልም ሲሆን የምየው ግን እርሳቸው እንዳሉት “በጠብታ የሚላስ” ሳይሆን “እጅ ተከፍቶ” የአገሪቱ ንብረት እየተገመጠ መሆኑን ነው፡፡
ዳኛው ለተከሳሹ— “ሰማህ ወይ? የመንግሥት ገንዘብ ሲያዝ ልክ ለቡጢ እንደተዘጋጀ ሰው እጅህን ጭብጥ አድርገህ ትይዘዋለህ፡፡ ከዚያም እጅን ‘ጠበቅ ጠበቅ’ ስታደርገው ጨብጠህ ከያዝከው ነገር ‘ፊጪጭ ፊጪጭ’ እያለ የሚወጣውን ላስ ላስ ታደርጋለህ እንጂ እንደው በመንግሥት አገር እጅህን ከፍተህ ትገምጠዋለህ?” አሉት፡፡
አሁን የሚካሔደውን ምዝበራ በምናይበት ጊዜ የዳኛው ምክር ሕጋዊ ጥያቄ ሊያስነሣ ቢችልም ሲሆን የምየው ግን እርሳቸው እንዳሉት “በጠብታ የሚላስ” ሳይሆን “እጅ ተከፍቶ” የአገሪቱ ንብረት እየተገመጠ መሆኑን ነው፡፡
ኀሰሳ ስጋ
እልፍ ከሲታዎች ቀጥነው
የሞገጉ
"ስጋችን የት
ሄደ?" ብለው ሲፈልጉ
በየሸንተረሩ፣ በየጥጋጥጉ
አሥሠው አሥሠው በምድር
በሰማይ
አገኙት ቦርጭ ሆኖ ባ‘ንድ
ሰው ገላ ላይ፡፡
(በዕውቀቱ ስዩም- ኗሪ
አልባ ጎጆዎች)
