Tuesday, May 21, 2013

ወደ ዶክተር ዳኛቸው የተወረወሩ ጠጠሮች


መሀመድሀሰን                                          (yemohagets.blogspot.com or yemohagets.wordpress.com)


 

ከሁለት አመት በፊት የነበሩ ማክሰኞዎች ለኔና ለወቅቱ የስራ ባልበረቦቼ (ርዕዮት ዓለሙ፤ መሀመድ አሊ፤ ነብዩ ሀይሉ፤ ፍስሀ መንግቱ፤ እንዲሁም ጸሀፊያችን መሰረትን እና የሂሳብ ባለሙያዋ ኩኪ) ልዩ ትርጉም ያላት ቀን ነበረች፡፡ በወቅቱ የ‹‹አዲስ ፕሬስ›› ጋዜጣ ባልበረባ ስለነበርኩና ጋዜጣዋም ገበያ ላይ የምትውለው ማክሰኞ ስለነበር (የተወሰነ ግዜ ቅዳሜ ወጥታለች) የእረፍት ቀናችን የሚውለው ማክሰኞ ቀን ነው፡፡ ታዲያ የእረፍት ቀናችን ብሩህ ሆኖ በሰላም እንዲውል ጠዋቷ ከምንም በላይ ወሳኝ ናት፡፡ ጋዜጣችን ከማተሚያ ቤት በሰላም ወጥቶ ገበያ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለብን፡፡ አቤት ይህንን እስክናረጋግጥ ያለው ጭንቀት! እርግጠኛ ከሆንን ቦሃላ ያለው ደስታስ ቢሆን?! ከየትኛውም የደስታ አይነት ጋር የሚነጻጸር አይመስለኝም፡፡ ልጅን ወልዶ መሳም የሚሰጠው ደስታ እንኳን የታተመው ጋዜጣ ገበያ ላይ ውሎ ከማየት ጋር አይነጻጸርም፡፡  
ነሀሴ 25 ቀን 2002 ዓ.ም የዋለው ማክሰኞ ጋዜጣችን ገበያ ላይ መዋሉ በመረጋገጡ ሰላም ነው፡፡ በዚህ ጋዜጣ ላይ ደግሞ ሁለት ጽሁፎችን ጽፊያለው፡፡ ‹‹የኳስ ፍቅራችን ወደማንነት ቀውስ እንዳያመራ›› የሚለው አንዱ ሲሆን፤ ሌላኛው ጽሁፌ ደግሞ ‹‹መኢአድ ምን እየሰራ ነው?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ በቀጣዩ ቀን የምትመጣዋ እሮብ እንደ እረፍት ቀናችን ሁሉ ተናፋቂ ናት፡፡ ከጽሁፋችን ጋር በተያያዘ ገንቢ፡ አፍራሽ፡ አስደሳች፡ አስቀያሚ፡… አስተያየቶችን የምንቀበልበት ቀን በመሆኗ ነው፡፡ ምሁሩ፡ ሽማግሌው፡ ወጣቱ፡ ሴቱ፡ ወንዱ፡ ካድሬው፡ ፖለቲከኛው፡ ባለስልጣኑ፡…ሁሉም ደውለው እንደ ደረጃቸውና አቅማቸው የሚሉትን ይላሉ፡፡
ከሀሳብ ይልቅ ላብ የፈሰሰባት እሮብ
እሮብ ነሀሴ 26 ቀን 2002 ዓ.ም ጠዋት ነቃ ባለ የስራ ስሜት ወደ ቢሮ ስንገባ የተንጫረረው የመጀመሪያው የስልክ ጥሪ የኔ ነበር፡፡ ማኔጂንግ ዳይሬክተሬ ወደ ቢሮው ጠራኝና የስልኩን እጄታ አቀበለኝ፡፡ ገና ሀሎ ከማለቴ ከዛኛው ጫፍ የተቀበለኝ ድምጽ በጠዋቱ የወፎች ዜማ ሳይሆን በገጀራ የታጀበ ነበር የሚመስለው፡፡ ከጻፍኳቸው ጽሁፎች አንደኛው መዘዝ ይዞ መምጣቱ ነው እንግዲህ፡፡  ደዋ ከመኢአድ አመራሮች ውስጥ አንዱ የነበረው (ዛሬ ያኔ የተሟገተለትን ግዚያዊ እውነታ በየፍርድ ቤቱ ይዞ የሚንከራት፤ ባዳ ሊሆን) አቶ ማሙሸት አማረ ነው፡፡
ነገ ይህቺን ሀገር ዴሞክራሲያዊ በሆነ ህግ፤ ስርዓት፡ አካሄድ፡… እመራታለሁኝ፡ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማስከበር እየታገልኩኝ ነው የሚል የፓርቲ አመራር ከኔው ጋር መታገል ጀመረ፡፡ ያለማቋረጥ በስሜት ተውጦ፡ ጮክ ብሎ ያወራል (ይጮሀል ብል ይቀለኛል)፡፡
‹‹ መኢአድ ምን እየሰራ ነው ማለት ምን ማለት ነው?!፡ መኢአድ አንተ የገለጽከው አይነት ፓርቲ ነው?! ፡እኛ ከመአህድ ተገንጥለን ነው ወደዚህ የመጣነው?! ኢንጂነር ሀይሉ ሻውል ከፓርቲው ርቀዋል እያልክ የምትነዛውን አሉባልታ ከየት አመጣኽው?፡ እሳቸው አሁንም አብረውን እየሰሩ ነው፤፡መግለጫችን ምንም ፋይዳ የለውም?!፡ ቢያንስ የተጎዱ፡የሞቱ ሰዎች እንኳን አያሳዝኑህም?!፡ ለስንት ሚሊዮን ሰው ስማችንን ካጠፋህ ቦሃላ እንዴት ነው የምናስተባብለው?፡ ማንስ ነው ከፓርቲው የወጣውና የተባረረው?፡ እንከስሀለን!!....›› ፋታ የሌለው ጩኽት፤ ያስታወስኩትን እንኳን ስዘረዝር፤ አሁንም ድጋሚ መድከሜ ተሰማኝ፡፡ በእርግጠኝነት ከእኚህ ሰው አጠገብ መሀረብና ማራገቢያ ይዞ የቆመ አንድ አባል እንዳለ ገምቻለው፡፡ ታዲያ አቶ ማሙሸት ከላይ በገለጽኩት መልኩ ላባቸውን እያፈሰሱ የተሟገቱለትን ሀሳብ ዛሬ በአንድ ካፌ ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብለው ሻይ እየተጎነጩ ለጋዜጦች እንደዋዛ በሚሠጡት ቃል ሲያፈርሷት መታዘብ ቀላል ነው፡፡ ያውም ሀሜት ቀላቅለውበት፡፡
እኔ በወቅቱ በጽሁፌ ላይ ለማንሳት የሞከርኩት፡ መኢአድ ነሀሴ 18 ቀን 2002 ዓ.ም በአይቤክስ ሆቴል ከምርጫ 2002 ጋር በተያያዘ ከሰጠው መግለጫ በመነሳት፡ በሌሎች ፓርቲዎች (ኢዴፓ እና አንድነት) ከተቀደማችሁ በኋላ አሁን ላይ የዘገየውን መግለጫ መስጠት ፋይዳው ምንድነው?፡ የተጎጂ ቤተሰቦችን ተሞክሮ ከማካፈል በዘለለ ከሌሎች ፓርቲዎች የተለየ ነገር ይዛችሁ አልመጣችሁም፤ዛሬም ድረስ አቶ ማሙሸት እራሳቸው ተጠቂ ሆንኩበት የሚሉትንና ሌሎች የፓርቲውን ክፍተቶች አንስቺያለሁኝ፡፡ በተጨማሪም እንደ ኢንጂነር ሀይሉ ሻውል ያሉ አስኳል አመራሮች ከፓርቲው መራቅ መጀመራቸው ፓርቲውን በተክለ ስብዕናም በተክለ ሰውነትም እየጎዳው ነው፤ በሚል በመግለጫው ላይ የተሳተፉ ጋዜጠኞችንም አስተያየት ጭምር በማካተት ነበር ‹‹መኢአድ ምን እየሰራ ነው?›› ስል የጠየቅኩት፡፡ ያውም ግማሽ ገጽ እንኳን በቅጡ ባልሞላ ጽሁፍ፡፡ አቶ ማሙሸት ግን ምናልባት መሪ የመሆን ህልማቸውን ለረዥም ሰዓት በመናገር የጓድ ሊቀመንበርን ሪከርድ በመስበር ማካካስ የፈለጉ ይመስላል፡ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ ስልኩ ላይ ቆየን፡፡ እሳቸው ይጮሀሉ (ይዝታሉ) እኔ እሰማለው፡፡
አስቡት እስኪ አንድ ሰዓት ሙሉ ሰው ሲጮህ መስማት፤ ያውም ፖለቲካ፤ መያዣ መጨበጫ የሌለው ደረቅ የኢትዮጵያ ፖለቲካ! አንድ ሰዓት ሙሉ በስልክ ለፍቅር ወግ እንኳን የሚበዛ ይመስለኛል፡፡ ቆይታችን ከሀሳብ ይልቅ ላብ ፈልቆ የፈሰሰበት ግብግብ ነበር ቢባል ይቀላል፡፡ ደግሞ እኮ ያንን ሁሉ ውርጅብኝ የምሰማው ቆሜ መሆኑ ነው፡፡ አሁን ላይ ሳስበው አንድ ሰዓት ሙሉ ቆሞ እንዲህ ያለውን ጩኽት የመስማት ሪከርዱ የኔ ይመስለኛል፡፡ እሳቸው ግን 4 ሰዓት ጮኽው የሊቀመንበሩን ሪከርድ እንዳያሻሽሉ ቀጣዩ ንግግሬ አሰናከላቸው፡፡
   ‹‹ እንግዲህ እርሶ አንድ ሀገር እመራለው የሚል ፓርቲ አመራር ነዎት፡፡ እኔ ደግሞ
    ምናልባት አጥፍቼ እንኳን ቢሆን ልታረም የምችል ትንሽ ልጅ ነኝ፤ ምናልባትም 
    ይወልዱኝ ይሆናል፡፡ ከዘሂህ ሰዓት ቦሃላ ግን እንዲህ ባለው ሁኔታ ከእርሶ ጋር
    መነጋገር አልችልም፤ ከፈለጉ ይክሰሱኝ፡፡›› አልኳቸው የሞት ሞቴን ያገኘሁትን ፋታ ተጠቅሜ፡፡ አቤት የዛን ቀን የባከነው ላብ! እኔን እንዲያ ካላበኝ እሳቸው እንዴት ሊሆኑ ይሆን? ማለቴ አልቀረም፡፡ ለነገሩ እሳቸው ያኔ ያፈሰሷትን ላብ መተኪያ ባያገኙ ሰሞነኛዋን ጨዋታ አይጀምሯትም ነበር ብሎ መጠርጠር ይቻላል፡፡ እንደሳቸው ግን የ‹‹በሬ ወለደ››ን ሀሜት በእርግጠኝነት አደባባይ ይዤ አልወጣም፡፡ ለነገሩ ይዤ ብወጣስ ብዞዎችን ግድ ይሰጣቸው ይሆን? እኔ እንጃ፡፡
የሰሞነኛዋ  መንጠራራት
ከአቶ ማሙሸት ጋር ያደረግነውን ዘለግ ያለ ግብግብ አንስቼ ያጫወትኳቸው ወዳጄቼና ባልደረቦቼ በቀጣይ ሊያመጡብኝ እንደሚችሉ ሲነግሩኝ መገረሜ አልቀወረም፡፡ እንዲህ ያለችና መሰል ሁኔታ የገጠመቻቸው በርከት ያሉ በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች የሚለጥፏት ታርጋ አለቻቸው፡፡ እገሌ እኮ ኢህአዴግ ነው የሚል፤ ከዛ ቦሃላ ወሬውን ለማናፈስ በትጋት መስራት፡፡ ይህንን ታርጋ መለጠፍ የሚጎዳው ምናልባት በአዘጋጅነት እሰራበት የነበረውን ጋዜጣ ካልሆነ በስተቀር፡ በቤተሰቦቼና ወዳጆቼ ብቻ የምታወቀው እኔን ቅንጣት ታህል አትጎዳኝም፡፡ እናላችሁ ታዲያ ‹‹ኢህአዴግ ነው›› የምትለው ይህቺ ታርጋ ከሰሞኑ አቶ ማሙሸትን ጨምሮ በሌሎች ተፈናቃይ ፖለቲከኞችም ጭምር ስትመዘዝ እንዳስተዋላችሁ እገምታለው፡፡ እኔ ከላይ ረዘም ያለውን ሀተታ ማንሳቴ ዝም ብሎ ገጽ ለማባከን ሳይሆን ታርጋውን ከመዘዙት ውስጥ አንዱ የሆኑትን የአቶ ማሙሸት አማረን ስብዕናና ማንነትም ጭምር በማሳየት ይረዳኛል ብዬ ስላሰብኩኝም ጭምር ነው፡፡
እኔ ዛሬ ትኩረት ማድረግ የፈለክሁት ከሌሎቹ ይልቅ አቶ ማሙሸት በመዘዙት ታርጋ ላይ ነው፡፡ ታርጋውን ለመለጠፍ ያሰቡት ደግሞ በታላቁ የአደባባይ ምሁር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ላይ ነው፡፡ ዶክተር ዳኛቸው በሰጠው (አንተ የምለው ፍቃድ ስላለኝና እሱንም ስለሚያስደስተው እነጂ፤እድሜውን እንኳን ብንተወው እውቀቱ ብቻ ለአንቱታ ክብር ያበቃዋል) ምላሽ ላይ አቶ ማሙሸትን ጭራሽ እንደማያውቃቸው ነግሮናል፡፡ ምናልባት ዳኛቸው ምላሽ መስጠት የፈለገውም ስለማያውቃቸው ይሆናል እንጂ ማንነታቸውን በደንብ ቢያውቅ ምላሽ ሰጥቶ እንዲህ ባላገነናቸው ነበር፡፡ ጉዳዩ ዳኛቸውም ተሳትፎበት እንዲህ አየሩን ከተቆጣጠረ ዘንዳ እኔም የበኩሌን ስለሁለቱ ሰዎች የማውቀውንና የተሰማኝን ነው እያሰፈርኩ ያለሁት፡፡
ለመሆኑ አቶ ማሙሸት እኩዮቻቸውን (የእድሜ ሳይሆን የእውቀት ማለቴ ነው) ወዴት አድርገው ነው ታላቁ ምሁር ላይ መንጠልጠል የፈለጉት? በምንና እንዴትስ ባለው ድፍረት ይህንን አሰቡት? እውነት ዳኛቸውን ያውቁታል? አላማቸውስ ምንድነው? ስል ከፍ ባለ ትህትና እጠይቃለው፡፡
ዶክተር ዳኛቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ጠቅልሎ መኖር ከጀመረበት ግዜ አንስቶ የምር የአደባባይ ምሁር መሆኑን በተጋበዘባቸው በርካታ መድረኮች እና ሚዲያው ላይ ብቅ ባለባቸው ግዚያት አስመስክሯል፡፡ ከኪነ ጥበቡ እስከ ፖለቲካው ድረስ እውቀቱ ምሉዕ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ደግሞ እንዴት አወቀው በሚል እስክንደመም ድረስ በንባብ የተከማቸ ሁለገብ እውቀት ያከማቸ ላይብረሪ ነው፡፡ ይህንን የተከማቸ እውቀትና ተሞክሮ ፍለጋ ‹‹የጥናታዊ ጽሁፍ አቅርብልን›› ጥያቄ ከሚያቀርቡለት ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ በዚህም መሰረት በርካታ ፓርቲዎች ባዘጋጇቸው ህዝባዊ መድረክ ላይ በመገኘት ጠለቅ ያሉ ምርምሮችን አቅርቧል፡፡ ጥናቱን ከአንዴም ሁለት ግዜ ካቀረበባቸው ቦታዎች አንዱ መኢአድ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ መቀራረብን ፈጥሮ ዶክተር ከፓርቲው ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ያለውን አቅም የተረዱት የፓርቲው የተወሰኑ አመራሮችም የፓርቲያቸው አባል እንዲሆን ተመኙ፤ የልዩነት አዙሪት በተጣባው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ልዩነት እንዲያጠብ ጠየቁት፡፡ ምናልባት ዳኛቸው ወሳኝ የሚላቸው ፖለቲከኞችን ለማሸማገል ሲሯሯጥ የረሳቸው አቶ ማሙሸት ‹‹እኔም እኮ ወሳኝ ነኝ!›› በሚል አኩርፈው ይሆናል፡፡ የሆነው ሆኖ ለዳኛቸው  የቀረቡለት ሁለቱም ሀሳቦች ክፋት የላቸውም፡፡ ሁለቱም ሀሳቦች ዳኛቸው በጠቀሳቸው የተለያዩ ምክንያቶች አልተሳኩም፡፡
እስከዚህ ድረስ ያለው ሂደት ነው እንግዲህ አቶ ማሙሸትንና ግብረ አበሮቻቸውን ለሰሞነኛዋ ፈጠራ ያነሳሳቸው፡፡ እስኪ ይታያችሁ፡ አንድ ምሁር እውቀቱን ተጠቅሞ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ጥናታዊ ጽሁፍ ማቅረቡ፡ በፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ መሞከሩና ከዛ ፓርቲ አባልነት ጥያቄ ስለቀረበለት ብቻ፡ እንዴት ሆኖ ነው የዛ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሊሆን ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርሰው?! አረ ጎበዝ ምክንያታዊ ለመሆን እኮ የግድ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ሎጂክ መማር አያስፈልግም፡፡ አብሮን የተፈጠረ ማመዛዘኛ አለ እኮ፡፡ እሺ ይሁን እንበልና (እውነት አቶ ማሙሸት ለሀገር እና ለፓርቲያቸው የሚያስቡ ቢሆን እንደ ዶክተር ዳኛቸው ያለ ምሁር በመምጣቱ ደስተኛ ሊሆኑ ይገባ ነበር፡፡ እኔ ግን የሰማሁት ዜና ውሸት በመሆኑ መደሰቴን አልደብቃችሁም፡፡ምክንያቱም ዳኛቸው የሁላችንም የአደባባይ ምሁር እንደሆነ ስለሚቀጥል፡፡) አቶ ማሙሸት ይህንን ጉዳይ ያነሱት የሚያውቁትን እውነት ቀድሞ ለማውጣት ነው፤ ምንም ክፋትም የለውም እንበል፡፡ ታዲያ ተከታይዋ ‹‹የብአዴን›› አባልነት አፍራሽ ከየት፡ እንዴትና ለምን መጣች? ብለን ብንጠይቅ ፕሬዝዳንት ሊሆን ነው የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፤ እነሱ ደግሞ መኢአድ ይገባናል በሚል እየተከራከሩ ነው፡፡ ነገ መኢአድን ተረክበው የሚያስተዳድሩበት አጋጣሚ ቢፈጠርላቸው፡ ከዳኛቸው ነጥቆ ስኬት ስለማይታሰብና ስራቸውንም እጅግ በጣም ስለሚያከብደው የኢንጂነሩን መኢአድ እንዳይረከብ ከአሁኑ ስሙን የማጠልሸት ስራ መስራት መጀመራቸው ነው፡፡
ሌላ ነገር እንጠርጥር ከተባለ፡ እነ አቶ ማሙሸትን ጨምሮ አንዳንድ ጋዜጠኞች የዳኛቸው ስም ተራና ወቅታዊ ትኩረትን ለመሳብ ተጠቅመውበታል ማለት ይቻላል፡፡ እነ አቶ ማሙሸት ከፓርቲው ሲባረሩ ምንም ትኩረት የሚሰጣቸው አላገኙም፡፡ ፍርድ ቤት ሄደው ሲካሰሱም ብዙም ጉዳዬ ብሎ ያዳመጣቸው አልነበረም፤ ሌላው ቀርቶ ምርጫ ቦርድ እንኳን ችላ እንዳላቸው እራሳቸው እየነገሩን ነው፡፡ ስለዚህም በፖለቲካው ዓለም ነገ ተጠያቂነት መኖሩን ዘንግተው የዛሬን ተራ ዝና ብቻ ፍለጋ ሲሉ ‹‹የበሬ ወለደ›› ፈጠራቸውን መንዛት ጀመሩ፡፡
ጋዜጠኞቹም የጉዳዩን ባለቤት የመጠየቂያ ፋታ እንኳን መውሰድ አልፈለጉም፡፡ወሬውን አተሙት፡፡ እንደሚታወቀው በአሁን ሰዓት አንባቢው ከሚናፍቃቸው ግንባር ቀደም ሰዎች አንደኛው ዳኛቸው በመሆኑ ብዙዎቹ የሱን ጉዳይ በመያዝ ገበያው ላይ ጨው መሆንን አጥብቀው ይፈልጉታል፡፡ የተረሱት እነማሙሸትም ‹‹ይህ ሰውዬ ማን ነበር?›› እስኪባሉ ድረስ ስማቸው ተነሳ፡፡ ጋዜጦቹም ለጉድ ተነበቡ፡፡ ጨቅላዋ የኔ የጡመራ ገጼ ላይ እንኳን ሳይቀር ከወቅታዊ ጉዳዮች ሁሉ ልቆ የዳኛቸው ጉዳይ ቀዳሚውን ስፍራ ያዘ፡፡
ዶክተር ዳኛቸው በሰጠው ምላሽ ላይ እነ አቶ ማሙሸት ወሬውን የነዙት የአደባባይ ተዋስኦውን ለማጠልሸት አስበው እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ዳኛቸው ቀደም ሲልም እንዳነሳው የሰዎቹን ማንነት ስለማያውቅ እንጂ የዳኛቸው ተዋስኦ በነ አቶ ማሙሸት አቅም የሚጠለሽ የአሸዋ ላይ መሰረት ያለው አይደለም፡፡ ዳኛቸው መሀል ሜዳ ገብቶ የሚጫወት እውነተኛ ምሁር ነው፡፡ያውም የቅርብ ሰዎቹ (የቤተሰቦቹን አባላት ጨምሮ) ያሉበት የኢህአዴግ ፓርቲ ባነሳው ሀሳብ ላይ እንዳያንሰራራ አፍረክርኮ በእውነት ስለ እውነት የሚረታ ምሁር ነው፡፡ ለሱ ከቤተሰባዊነትም ከጓደኝነትም በላይ እወቀት ላቅ ያለ ቦታ አላት፡፡ እዚህች ጋር እንደማሳያ ከፍተኛ ነጥብ ያስቆጠረበትና የቅርብ ወዳጆቹ የነበሩትን የገዢው ፓርቲ ሰዎች ያሳጣበትንና  (በርግጥ እነሱ ናቸው ያጡት) በቀድሞዋ ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ ላይ ስለ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጽፎት የነበረውን ድንቅ ስራ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ኢህአዴግ መልስ ሊኖረው በማይችልበት ሁኔታ ብርቱካን እንዴት ነጻ እንደሆነችና ኢህአዴግ ደግሞ እንዴት ያለ ግዙፍ ስህተት እንደሰራ ቁልጭ አድርጎ ነበር ያሳየው፡፡ የብርቱካንንም የሞራል ልዕልና ከፍታ አሳይቶናል፡፡
እነ አቶ ማሙሸት የተጠናወታቸው የመጠላለፉ አባዜ አልለቅ ብሏቸው ካልሆነ በስተቀር፡ ዶክተር በፍጹም ከመዶለቻቸው ዙፋን ላይ የመቀመጥ ቅንጣት ታህል ፍላጎት እንደሌለው በእርግጠኝነት እናገራለሁኝ፡፡  እንደሚያወሩልንም ኢህአዴግ እንደ ዳኛቸው ያለ ምጡቅና ቅን ሰው ማስጠጋት ጀምሮ ከሆነ እየተለወጠ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲያ ከሆነማ… እረ አያድርግብን፤ አያድርግበት፡፡ ስለዳኛቸው መጻፍ ከጀመርኩኝ ማቆሚያ አይኖረኝም፡፡ እንኳን ጋዜጣ መጽሀፍም አይበቃኝም፡፡ ደግሞም አይቀርም በሚል ተስፋ ላድርግና እዚህች ጋር ላብቃ፡፡
በመጨረሻም በድጋሚ እጠይቃችኋለሁኝ፡ ምን አይነት ትግል ውስጥ ነው ያላችሁት፡ የረብሻችሁ ውጤት ምንድነው፡ ኢትዮጵያ እንደ ዳኛቸው ካሉ ምሁራን ውጪ ምን እንደሆነች፡የምትሿት ኢትዮጵያስ እንዴት ያለችውን ነው፡ የምር ታውቋታላችሁ፡ ስል፡፡ ብረት ላይ እንቁላል መወርወር ከመሰበር ውጪ ሌላ አማራጭ ይኖረው እንደሆን እኔ አላውቅም፡፡ ለማንኛውም ማቃኛውን ለነሱም ለኛም እንዲሰጠን እመኛለሁኝ፡፡ ክብር የአንድ እጅ ጣት እንኳን ለማትሞሉት የአደባባይ ምሁራን፤ ቪቫ ብያለው፡፡