Sunday, August 11, 2013

የ‹‹ፌስቡክ›› ካድሬዎች እና እኛ





በመሐመድ ሐሰን          


እኛ ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ስሜቶቻችንን ሰብሰብ ብለን የምንገልጽበትን፣ የምንጮህበትን መስቀል አደባባያችንን ከተነፈግን ድፍን ስምንት ዓመት አለፈን፡፡ እርግጥ ነው ባለፈው በሰማያዊ ፓርቲ አዲስ አበባ ላይ፣ ሀምሌ ስምንት ደግሞ በአንድነት ፓርቲ ጎንደር እና ደሴ ላይ የተደረጉትን ሰልፎች አልዘነጋኋቸውም፡፡ በእኔ እምነት እነዚህ ሰልፎች የተካሄዱት በገዢው ፓርቲ ፈቃደኝነት ሳይሆን፣ ፓርቲዎቹ በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠላቸውን መብት በአግባቡ ለመጠቀም አንድ እርምጃ ለመራመድ በመድፈራቸው ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ፈቃደኛ ባይሆን እንኳን፣ በማሳወቅ ብቻ ሰልፉን ለማካሄድ ደፍረዋል፡፡ ከቅርብ ግዚያት ወዲህ በህዝቡ ላይ የሚታየው ስሜትም እንዲሁ፣ ኢህአዴግ እንደፈለገ የሚጠመዝዘው አይመስልም፡፡ በመሆኑም ሙከራዎችን እያየን ነው፡፡
በትክክል የገዢውን ፓርቲ አካሄድ ከተመለከትነው ግን፣ ከምርጫ 97 ቦሃላ አይደለም የአደባባይ ስብሰባና ዱለታ፣ በአንድ ሆቴል ጠረጴዛ ዙሪያ እንኳን የሚካሄድ ውይይት ለ‹‹አውራው›› ፓርቲ የአውሬ ያህል አስበርጋጊ ነው፡፡ እናም ከዚሁ ግዜ ቦሃላ ከእያንዳንዱ የእድር፡ የቢሮ፡ የሀየማኖት፡ የሴቶች፡ የወንዶች፡ የቀበሌ፡ የአሮጊቶች፡ የሽማግሌዎች፡ የነጋዴዎች፡… ብሎም ከቤተሰብ ጉባዔ ጀርባ ሳይቀር፣ የካድሬዎች (ጆሮ ጠቢዎች) መኖር ግድ ሆነ፡፡ ታዲያ እነዚህ ካድሬዎች ትጉህ ከመሆናቸው የተነሳ ሰብሰብ ባሉ ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ሰብሰብ ብለው በቆሙ እንስሳትና ዛፎች ላይም ሳይቀር ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ ትጋቱ ከፍ ያለና ይሄውም ትጋቱ ከፍ ተደርጎ እንዲጻፍለት የፈለገ ካድሬ ደግሞ ከሰዎቸ አልፎ፣ ሰብሰብ ያሉትን እንስሳት ከመበተን፣ እጅብ ብለው የበቀሉ  ዛፎችንም ከማስመንጠር ወደኋላ አይልም፡፡
ይህ ሁሉ ክልከላ እንዳለ ሆኖ፣ ዛሬ ላይ ህዝቡ የራሱን መስቀል አደባባይ አልያም አብዮት አደባባዮች ‹‹ፌስቡክ›› በተባለው የማህበረሰብ ድረ ገጽ ላይ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በዚህ የ‹‹ፌስቡክ›› አደባባይ ላይ የሚሰማቸውን ይገልጻሉ፣በባለስልጣናቱ ላይ ያንጓጥጣሉ፣ይሳደባሉ፣ ያሞግሳሉ፣ ያቅራራሉ፣ ይጠራራሉ፣ ይቀጣጠራሉ፣ ያሻቸውን ሀሳብ ያነሳሉ፣ ያልፈለጉትን ይጥላሉ፣ ሌላም ሌላም፡፡ ታዲያ ሰብበሰብ ያለ ነገር እዚህች ሀገር ላይ የሚታየው በመቃብሬ ላይ ነው የሚለው ኢህአዴግ፣ ካድሬዎቹን ወደ ፌስቡክ አደባባይም ጭምር አሰማርቷል፣መድቧል፡፡ ኢህአዴግ ካድሬዎቹን በሌላኛው የፌስቡክ አደባባይ ያሰማራቸው ሁሉንም ነገር በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ከመፈለጉ ባሻገር፣ ለታማኝ ካድሬዎቹ የሌለውን የስራ እድል ለመፍጠር ሲል የተወሰኑትን ወደዚህ የፌስቡክ አደባባይ ለመመደብ የተገደደ ይመስለኛል፡፡ ክፍት የስራ መደብ መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡
ዛሬ በዋናነት ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ፣ እኛ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ስለካድሬዎቹ ያለን ግምትና አመለካከት ቢሆንም፣ እግረ መንገዴን የፌስቡክ ካድሬዎቹንም ጉዳይ ማንሳት ፈልጊያለው፡፡ በነሱው ግዜ ላይ ቁጭ ብሎ ስለነሱ ሳያነሱ ማለፍ በጸረ-ሽብር ህጉ ሊያስከስስ ይችላል፡፡ እንደውም ለምን ለነሱ ቅድሚያውን አልሰጣቸውም? አዎ ከባለግዜ ጋር ከመጋፋት ይቅደሙ፡፡

እነሱ
የፌስቡክ ካድሬዎቹ ስራቸው፡አይነታቸው፡ እና ተግባራቸወ መልከ ብዙ ነው፡፡ ወደዚሁ አደባባይ የተመደቡ ካድሬዎች ከፌስቡክ ውጪ ያለውን ሌላ ዓለም በፍጹም እንዳያዩ የሚከለከሉ ይመስለኛል፡፡ ከፌስቡክ ውጪ ያለን ጽሁፍ አያነቡም፡አይመለከቱም፡አይሰሙም፡፤ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው አንድን በጋዜጣ ወይም መጽሄት ላይ የወጣን ጽሁፍ በፌስቡክ ላይ ካዩት፣ ያ ለነሱ ትልቅ ግኝት ነው፡፡ ከርዕሱ በዘለለ ሌላውን ዝርዝር መረጃ በደንብ የማየት ግዜና ትዕግስቱ የላቸውም፡፡ በሩጫ እየተክለፈለፉ ሄደው ለአለቆቻቸው ትኩስ ያሉትን ወሬ ያቀብላሉ፡፡ ያለአንዳች ጥያቄም ነጥብ ያስመዘግባሉ፡፡ ከዛም ወደ ፌስቡክ አደባባይ ይመለሱና ተኩስ ይጀምራሉ፤ በቃላት ማለቴ ነው፡፡ ታዲያ የሚጽፉት ነገር እጅግ በጣም በደምፍላት የተሞላ ከመሆኑ የተነሳ፡ መሳሪያ ደቅነው የሚልኩልን ሊመስለን ይችላል፡፡ ቢችሉ እንደውም የያዙትን መሳሪያ ላጥ አድርገው፡ በቅጡ ያልተረዱትን ቴክኖሎጂ ግንባሩን (ግንባሩን እንግዲህ እነሱው ያውቁታል) ብለው ፌስቡክ አደባባይን ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ቢያወድሙት ይመርጣሉ፡፡ እነዚህ የፌስቡክ ካድሬዎች በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚሰለፉ ናቸው፡፡
የማስደንበር ተልዕኮ ብቻ ተሰጥቷቸው ወደ ፌስቡክ አደባባይ የሚላኩ ካድሬዎች ቁጥርም ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ እነዚህኞቹ በቅድሚያ ማንን መከተል እንዳለባቸው ስለሚነገራቸው፣ ያንን ሰው በማስደንበር መንግስት ከሚጠላው ተግባሩ ሊያርቁት ይሞክራሉ፡፡ የደነበረ ከተገኘማ ሁኔታውን የተረዱ ሌሎች እጩ የፌስቡክ ካድሬዎችም ትዕይንቱን ለመቀላቀል እራሳቸውን ካድሬ አድርገው ብቅ ይላሉ፡፡
እንደውም በአንድ ወቅት ላይ ምን ገጠመኝ መሰላችሁ? ፌስቡክ ከፍቼ እየተጠቀምኩ፣ አንድ ሰው በመሀል በቀጥታ ያወራኝ (ቻት) ያደርገኝ ጀመር፡፡ እናም የካድሬነቱን ልዩ ምልክቶች ያንጸባርቅ ጀመር፡፡ ለካስ ይህ ወጣት ጌታ ፓርቲውን በመቃወም የጻፍኩት ጽሁፍ አናዶት ኖሯል፡፡ ጭቅጨቃውና ጉንተላው ሲበረታብኝ እና አልተው ሲለኝ፣ ፎቶውን ከፍቼ ማንነቱን በደንብ አየሁት፡፡ ፎቶውን የተነሳው አንድ የግንብ አጥር ተደግፎ አደባባይ ላይ ነው፡፡ ከዛማ እኔም የሰው ልጅ አይደለሁ? ብስጭት! አልኩና ‹‹ እኔ እንዳንተ በአደባባይ ፎቶ መነሳት ብቻ ሳይሆን፡ በአደባባ ሀሳቤንም እገልጻለሁ፤ ያነበብካቸው እና የሚያናድዱህ ጽሁፎች በሙሉ ጋዜጣ ላይ የወጡ ናቸው፤ነጃሳ!›› ልለው አሰብኩና እንዳይነጅሰኝ ስለፈራው ሸሸሁት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ሽሮሜዳ ቁጭ ብሎ ሽሮ እየበላ አሜሪካ ነዋሪ ነኝ ከሚለው፣ ስሙን፣ጾታውን እና ፎቶውን ቀይሮ እሰከሚጨቀጭቀን ድረስ በርካቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ያለችኝን ይህችኑ ስልጣን ተጠቅሜ፣ ሀገሬ ላይ እንደልቤ እንዳልንቀሳቀስ የገደባችሁኝን የናንተን ጉዳይ እዚህች ጋር ቋጭቼ፣ የቀረችውን ቦታ ለኛው ለጭቁኖቹ አውላታለው፡፡ ከፈለኩ ህገመንግስታዊ መብቴ ነው፣ አንቀጽ 30 ይከበር! ምናምን እያልኩኝ እጮሀለው፤ መስቀል አደባባይ እስካልወጣው ድረስ፡፡ ብወጣስ  ደግሞ?!....

እኛ
እኛ የፌስቡክ አደባባዩ እድምተኞች፣ ለፌስቡክ ካድሬዎቹ ያለን ቦታ ትንሽ የተጋነነና የተዛባ ነገር ያለው ይመስላል፡፡ አንዲት እውነትነት ያላትም ትሁን የሌላትን ፍንጭ ስናገኝ፣ እንደ ታላቅ ግኝት እሷኑ ወሬ ይዘን እናራግባታለን፡፡ መፈክሯንም ይዘን ወደ ፌስቡክ አደባባይ እንወጣለን፡፡እየተቀባበልንም እናስተጋባለን፡፡
   ‹‹ይህ ሰው የወያኔ ካድሬ (ቡችላ) ነው፤ መልኩን በደንብ ያጥኑት፤ እራስዎን ይከላከሉ፡፡››
ይህንና እነደዚህ አይነት ይዘት ያላቸውን መፈክሮች ማስተጋባቱ አሁን አሁን በቋሚነት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ በተያያዥነት አብሮ የሚያስነሳቸው ጥያቄዎች ይኖሩታል፡፡
እነዚህ ሰዎች የወያኔ ቡችላ የሆኑ እንደሆነስ ምን ይጠበስ?! ከማንስ ነው እራሳችንን የምንከላከለው? ከስራ ባልደረቦቻችን? ከጎረቤቶቻችን? ከጓደኛችን? ከወንድማችን? ወይስ ከማን? ማነው በአሁን ግዜ ካድሬ እንዲሆን ያልተገደደና ያልሆነው? ወይም ደግሞ በካድሬዎች ያልተጠረነፈው? ደግሞስ ምንም አይነት ሚስጥር ከማይደበቅበት የፌስቡክ አደባባይ ላይ ወጥቶ ‹‹ እራስዎን ከነዚህ ቡችሎች ይከላከሉ፤…›› ማለት ምን ማለት ነው? በፌስቡክ አደባባይ ላይ የምንለቀው ሀገራዊ መረጃ ካድሬዎቹን ያበሳጫል፤ መሪዎቻችንን ያስቆጣል፡፡ ይህ ደግሞ እኔን ያስፈራኛል የምንል ከሆነ ቀድሞውኑ መረጃውን አለመልቀቅ ነው፡፡ አምነን ከለቀቅን ደግሞ ስለማንም ግድ ሊኖረን አይገባም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ፌስቡክ›› ከሚባለው አደባባይ ላይ የተለቀቀው ነገር የአደባባይ ሚስጥር ነውና ነው፡፡  
ሁሉንም ሰው ለመጠርጠር የተጠናወተን አባዜ አንዳንዴ ይጦዝና፣ የተለየ ሀሳብ በማንሳት መንግስትን በመሞገት በዙሪያቸው በርካቶችን መሰብሰብ ለቻሉ ሰዎች ‹‹ማር›› የሚል መጠሪያ በመስጠት ለመንግስት የሚሰሩ ሰዎች አድርገን እንፈርጃቸዋለን፡፡
በእርግጥ እነዚህ ስዎች እንደምናስበው ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እኛ የምንከተለው ግለስቡን ሳይሆን የሚያነሳውን እና የተስማማንን ሀሳብ ነው፡፡ ያ ግለሰብ ነገ ቢሄድ፣ አምነን የተቀበልነውን ሀሳብ እውነትነት አያፈርሰውም፡፡ እንደሚባለው እውነትም ያ ሰው ያነሳውን ሀሳብ ምን ያህል ሕዝብ ይደግፈዋል በሚል የመለየት ስራ ለመሰራት እንኳን ቢሆን፣ የዛ ሀሳብ ደጋፊ ቁጥር ሊያስደነግጣቸውና ቆም ብለው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ከመቻሉም ባሻገር፣ ያንን ሁሉ ስው ስብስቦ ማጎር የሚቻላቸው እንዳልሆነም ጭምር ይረዱታል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው፣ አሁንም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በፌስቡክ እያደረጉት ያለው እንቅሰቃሴ ነው፡፡ሁሉም ማለት በሚያሰደፍር መልኩ መንግሰትን  የማያስደስቱ መብቶቻቸውን ያስተጋባሉ፣ በግልጽም ያቀነቅናሉ ፡፡ አሁንም እያቀነቀኑ ነው፡፡ ሀሳባችውም የፌሰቡክ ካድሬዎችን ጨምሮ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ታዲያ መንግሰት ይህንን ሁሉ ሙስሊም ሰብስቦ ማሰር የሚቻለው ይመሰላቹሀል?!... እኔ እንደሚሰማኝ እውነትነት ያለውን ሀሳብ በብዛት በማቀንቀን ከእስር በላይ ብዙ እንደሆንን ማሳየቱ ከምንም በላይ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡
በካድሬነት የምንፈርጃቸው ሰዎች ላይ ያለን እርግጠኝነት ውሸት ሆኖ መገኘቱ በራሱ ሊያሳጣን የሚችለው አንድን ግለሰብ ብቻ አይደለም፤ እሱን የመሰሉ በርካቶችን ከፖለቲካው መድረክ እንዲያፈገፍጉ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ በእርግጥም ደግሞ ማድረጉ አይቀርም፡፡
በተቃራኒው ደግሞ አንድን ሰው የፓርቲ አባል በመሆኑ ብቻ እየፈረጁ መግፋትና በመፈክሩ ላይ ማንጠልጠሉ ውለታ እንደመስራትም ጭምር ነው፡፡ እጩ ታማኝ ካድሬ ለመሆን የነበረውን ከፍተኛ ጉጉት በአቋራጭ እናሳካለታለን፡፡ ምንም ሀሳብ የሌለው፣ ነገር ግን የኢህአዴግ ደጋፊነታቸውን የሚያሳብቅ ጽሁፍ ይዘው በመምጣታቸው ብቻ ያገዘፍናቸው ካድሬዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ምንም አይነት ብርሀን የማይፈነጥቅ ተራ ጽሁፍ በብርሀኖቻችን ላይ (ከሰሞኑ እንደ በዕውቀቱ ስዩም ባሉ ድንቅ ጸሀፊዎቻችን ላይ የተጀመረውን ዘመቻ እንደ ማሳያነት ማንሳት ይቻላል) የሚቸከችኩ ካድሬ ‹‹ጸሀፊዎችን›› ያገነናቸው እኛው ነን፡፡ ነጋ ጠባ አጀንዳችን አድርገናቸው፡፡
ስለዚህ ፌስቡክ የአደባባይ መድረክ እንደመሆኑ በምክንያታዊነት ብንጠቀምበት፣ እነሱም የማይረባ ነገር እየለጠፉ አያሰልቹን እንጂ ሀሳብ ነው ያሉትን ነገር እንዲያንጸባርቁ፣ ጓደኞቻችንም እንዲሆኑ እየፈቀድን፣ አደባባዩን እነሱም በአግባቡ እንዲለማመዱት ብናደርግ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ባይሆን ብሽቆች ሲገጥሙን ‹‹እኛ በአደባባይ ፎቶ መነሳት ብቻ ሳይሆን በአደባባ ሀሳብንም መግለጽ እንችልበታለን›› ብንላቸው ሳይሻል አይቀርም፡፡
በመጨረሻም፣ ቴክኖሎጂው ለፈጠረልን አደባባይ በድጋሚ ቪቫ ላ ቴክኖሎጄ፣ ቪቫ ላ ፌስቡክ፣ ቪቫ ላ ዙከንበርግ፣… ብለን ብናሳርግስ? ማን ያውቃል፣ ነገ ደግሞ የሀሳብ ልዩነታችንን የሚያከብር የ‹‹ፌስቡክ›› ካድሬ ይገጥመንና ‹‹ቪቫ ላ ካድሬው›› እንለው ይሆናል፡፡   
  

No comments:

Post a Comment