በ‹‹ላይክ›› እና ‹‹ሼር›› መቧደን
በመሐመድ
ሐሰን (ኢትዮ-ምህዳር ላይ የታተመ)
ከአራት
ኪሎ ወደሜክሲኮ በሚሄድ ታክሲ ውስጥ ነን፤ ጉዟችን ተጀምሮ ‹‹የሚታይ እንጂ የማይበላ›› ይሉትን አባባል ከሚያስታውሰኝ ሸራተን
ሆቴል አከባቢ ስንደርስ የታክሲው ረዳት ሂሳብ መሰብሰብ ጀመረ፤ ከኔ ኋላ ባለው የመጨረሻ ወንበር ላይ ከተቀመጡት አራት ተሳፋሪዎች
(አንድ ሴት ሶስት ወንድ) ውስጥ አንደኛዋ ዘመን ያቀለለውን የሀምሳ ብር ኖት አውጥታ ለረዳቱ ትሰጠዋለች፤ ረዳቱም ሂሳቡን ይቆርጥና
መልስ ይሰጣታል፤ ልጅትም የተሰጣትን መልስ ትቆጥርና፡-
‹‹ስንት ነው የመለስክልኝ?!›› ስትል ጠንከር ባለ ድምጸት ትጠይቀዋለች፤
ረዳቱም፡-
‹‹የሁለት ሰው አይደል የምቆርጠው?›› የሚል ጥያቄ ለጥያቄዋ ይሰነዝራል፤ እሷም ረዳቱ አውቆ ነው የሸወደኝ በሚል እምነት ቀልጠፍ
ብላ፡-
‹‹በል
መልሴን አምጣ! ማን የሁለት ሰው ቁረጥ አለህ? ለማንኛውም ቀልድህን ‹‹ላይክ›› አድርጌልሀለው፤›› ስትል ‹‹ፌስቡክ››ኛ ቋንቋዋን ተጠቀመች፤
አብረዋት የተቀመጡት ጎረምሶች በሙቀቷ ጋል ብለው ይሁን አልያም በልጅት ላይክ ለመደረግ ጓጉተው ባይገባኝም፣ ንግግሯን ተከትለው
ከሌላው ተሳፋሪ በተለየ ደመቅ ባለ ሳቅ ተሸቀዳድመው አጀቧት፡፡…
ከልጅት
ንግግር ውስጥ በውስጤ የቀረውና ወደሌላ ሀሳብ የመራኝ ‹‹ላይክ›› የሚለው ቃል ሲሆን፣ ‹‹ላይክ›› ደግሞ አጋሩ የሆነው ‹‹ሼር››ን
ጎትቶ ወደ ‹‹ፌስቡክ›› አደባባይ ይዘውኝ ዘለቁ፡፡
እነ ዙከንበርግ
‹‹ላይክ››ና ‹ሼር››ን ብዙ ነገር አስበው ቢጠበቡበትም፣ እኛ ግን እንበጣበጥበታለን፤ እኔም ዛሬ ማንሳት የፈለግኩት እነዚህ ሁለት
ቃላት በበርካታ የ‹‹ፌስቡክ›› ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዴት ለጥፋት እየዋሉ እንደሆነ ነው፤ እንደኔ እምነት እነዚህ ሁለት
ቃላት የተዛባ አስተሳሰባችንን የሚያባዙና ሚዛን የሚያስቱ ቫይረሶች ናቸው፡፡ ታዲያ ‹ፌስቡክ›ን በአግባቡ በሚጠቀሙ ሰዎች ዘንድ
ያለው ፋይዳ ሳይዘነጋ ማለት ነው፤ ከዓመት በፊት የፌስቡክን የላቀ ፋይዳ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ማስነበቤን አስታውሳለሁኝ፡፡ ለማነኛውም
የተጀመረው ወጋችንን እንቀጥል፡፡
ባለፈው
ጊዜ ኳሱ ሞቅ ደመቅ ያለበት ሰሞን ነው፤ አንድ ወዳጄ የኳስ ተመልካቹን ወሬና ውይይት ከታዘበ በኋላ ‹‹የሚገርም ዘመን ላይ እኮ
ነው የደረስነው! የምናገባው ጎልና የሚያገባ ተጫዋች ሲጠፋ፣ ግብ ከመሆን የተረፈችውን ኳስ ስላቀበለው ተጫዋች፣ ኳሷን ስለለጋው
በረኛ፣…በመጨረሻም ስለኳሷ መፈጠር ብቻ ውዳሴ ማዝነብ እንጀምራለን፤›› ነበር ያለኝ፡፡
የዚህ
ወዳጄ ንግግር ስለዚህ ዘመን የሚናገረው ጉድ ብዙ ነው፤ በትክክል የምናሳካውና እርግጠኛ የምንሆንበት ነገር እየጠፋ የመጣ ይመስላል፤
ግባችንን ካጣነው ከራርመናል፤ ከግባችን ጋ ያገናኘን የመሰለንን ነገር በመከተል እየጠፋን ነው፤ በትክክል የምናደንቀው በማጣታችን
የአድናቆት ፍሬያችንን እንደሰነፍ ገበሬ የትም እየዘራነው ነው፤ እውነተኛው ምስል እየጠፋብን በመሄዱ "አርቴፊሻሉ"
ላይ እየተመሰጥን ነው፤… በየትኛውም ዘርፍ ተገቢውንና ትክክለኛውን አውራ እያጣነው፣ እያከሰምነው፣ እያደበዘዝነው፣ … መጥተናል፤
አሁን የሁሉም ነገር ጨዋታ "ፌስቡክ" ወደሚሉትና ዉሉ ባልታወቀ አደባባይ ላይ ተንጠልጥሏል፡፡
ድጋፋችን፣
አድናቆታችን፣ ጥላቻችን፣ ፖለቲካችን፣ ትችታችን፣ ጸባችን፣ ሰልፋችን፣ "ሀሳባችን"፣ አብዮታችን፣ ሀይማኖታችን፣
እምነታችን፣… ሁሉም ጠቅልለው ከፌስ ቡክ አደባባይ ከትመዋል፤ ሀይማኖተኛው፣ መምህሩ፣ ጋዜጠኛው፣ ፖለቲከኛው፣ ትልቁ፣ ትንሹ፣ የተማረው፣
ያልተማረው፣ …ያለልዩነት ሁሉም በፌስቡክ ሜዳ ላይ ያሻቸውን ቁጥር አልባ ማልያ ለብሰው ይጫወታሉ፤ ጎል አግቢዎች ግን አይመስሉም፤
ግባቸው ከመረቡ ላይ ስለማረፉ ማንም በእርግጠኝነት መናገር አይችልም፤ ባልተቀናጀ ሜዳ ላይ ያልተቀናጁ ተጫዋቾች ተገናኝተው እንዴት
ጎል ሊያስቆጥሩ ይችላሉ?... ብቻ ይህንን የሚጠይቅ ያለ አይመስልም፤ ሁሉም ሜዳውን "ላይክ"ና "ሼር"
እያደረገ ይቀላቀለዋል፡፡
ከ‹ፌስቡክ› ወጣ ባለው ህይወታችንም ይኸው አባዜ ይጠናወተናል፤ የበላያችንን፣
የአለቃችንን፣ የመሪውን፣ የሀብታሙን፣ የመንጋውን፣…‹ሀሳብ› እየተቀበልን "ላይክ"ና "ሼር" በማድረግ
ተያይዘን የምክንያታዊነት ፍሬን በሌለው ቁልቁለት መፍሰስ ነው፡፡
በ"ፌስቡክ"
ላይ የሚለጠፉ አጀንዳዎች ቢረቡም ባይረቡም፣ ቢጠቅሙንም ቢጎዱንም፣ ቢያዋርዱንም፣ ባይመጥኑንም፣ ጉዳያችን ባይሆኑም፣… አብዛኛውን
ፌስቡካውያን ለሁለት መክፈላቸው አይቀሬ ነው፤ በቃ! ሆሆ..!! ከተባለ መከተል ነው፤ ዛሬ ላይ የሀገሪቱ አጀንዳ የሚነደፈውና የሚፈጸመው
እዛው የ"ፌስቡክ" አደባባይ ላይ ነው፤ ብዙ ሀሳብ ሳይሆን የበዛ "ላይክ"ና "ሼር"
ያለው የወቅቱን አጀንዳ ይገነባል፤ የሚገነባው አጀንዳም ቢሆን በየትኛው ሚዛን መሰረት የሌለው ነውና ወዲያው ይከስማል፤ ነገሩ ሁሉ
የቲፎዞ ነዋ!
ታዲያ ሌላ ተመሳሳይ አጀንዳ ወዲያው ይተካል፤ ምን ጣጣ አለው! የፌስቡክ አጀንዳ
ቁጭ ብሎ ማሰብና ማመዛዘን አያስፈልገው! በቃ! ሳይገነቡ መናድ ነው፤ በ‹ፌስቡክ›
አደባባይ የሚመረጠው አጀንዳ ሁሉ ፋሽን ተኮር በመሆኑ ለውጥ እስኪያመጣ፣ ሀሳብ እስኪሆን፣ በእግሩ እስኪቆም፣…አይጠበቅም፤ "ላይክ"ና
"ሼር" የሚያደርጉ ፋሽን ተከታዮች ቁጥር ሲቀዛቀዝ፣ አጀንዳውም በ"ላይክ"ና "ሼር"
እጦት ጠውልጎ ይሞታል፤ ሌላ ደግሞ አዘናጊ ጉዳይ ዘመነኞቹን ወክሎ ‹ከች› ይላል፡፡ በዚህ ጉዳይ የተማረረው ሌላኛው ወዳጄ “የኛ
ነገር እኮ መላ እየጠፋው መጥቷል! ከምላሳችን ከሚወጣው ይልቅ የምላሳችንና የውስጥልብሳችን ‹ማች› ሆኗል የሚያሳስበን!"
ብሎ ብስጭቱን አካፍሎኛል፡፡
ምሁሩም፣
ፖለቲከኛውም፣ ሀይማኖተኛውም፣ ጋዜጠኛውም፣ ወጣቱም፣…የተገኙትና የታደሙት በ‹ፌስቡክ› አደባባይ ላይ በመሆኑ እርቃናቸውን ናቸው፤
በአለባበስም ሆነ በአስተሳሰብ የተራቆቱ ፌስቡካውያን ናቸው፤ እኛም እርቃናቸውን "ላይክ"ና "ሼር"
እያደረግን የመራቆታቸውን ልክ እናሰፋዋለን፤ አብረንም እንራቆታለን፤ ከዛም የተራቆተ አስተሳሰባችንን እናስፋፋለን፤ እድሜ ለ"ላይክ"ና
"ሼር"! ድጋፋችንና ፉከራችን ሁሉ ሀሳብ አልባ ጥዝጥዝ!
ታዲያ
የአደባባዩ ግለት ብዙዎችን ከሚዛናቸው አውርዶ ያቀልብናል፤ ከሽፍንፍናቸው አውጥቶ ያራቁትብንል፤ መጽሀፋቸውን እንዴት ጻፉት፣ እንዴት
ጋዜጠኛ ሆኑ፣ እንዴትስ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ወጡ፣ የእውነት መምህር ናቸው!፣ ሀይማኖተኛ እንዲህ እንዲያደርግ ይፈቀድለታልን፣
የደራሲ ብዕር እንዲህ ይሻክራል፣ ፖለቲከኛ ማለት እንዲህ ራዕይ አልባ ነው እንዴ፣ እንዴትስ ፓርቲ ሲመሩ ኖሩ፣??... ማቆሚያ
የሌላቸውን መሰል ጥያቄዎች ለማግተልተል ከአደባባዩ ወጣ ብሎ ትንሽ መጠየቅ ይበቃል፡፡
ታዲያ
የፌስቡክ አደባባይ የብዙዎቻችንን ጊዜ በአልባሌ ከማባከን ባለፈ፣ በማቧደን በኩልም የተሳካለት ይመስላል፤ ከፖለቲካ፣ ጎሳ፣… ቡድንተኝነት
ወደ ‹ፌስቡክ› ቡድንተኝነት ከተሸጋገርን ከራረምን፤ የወቅቱን አጀንዳ በመፍጠር ሜዳውን የተቆጣጠረ ፌስቡከኛ በፈለገው መደብ ላይ
መድቦ ‹ላይክ›ና ‹ሼር›ን እየተጠቀመ ህሊናችንን ነጥቆ እንደ ድንችና ሽንኩርት ይመድበናል፡፡
ያደለው
በፌስቡክ ይማማራል፣ የራሱን ሀሳብ ያራምዳል፣ አጣሁት ያለውን የመናገርና የመጻፍ ነጻነት በአግባቡ ይገልጻል፤ ጠቃሚ መረጃ ይለዋወጣል፤…
እኛ ግን እንቧደናለን፣ እንዘናጋለን፣ እንዘላለፋለን፣ እንለያያለን፣ እንቀላለን፣ የሙያዊነትን ድንበር እንጥሳለን፤…
ከሁሉም
በላይ ደግሞ የፌስቡክ አደባባይን ጉዳይ አስገራሚ የሚያደርገው፣ ተግባራችንና ፍላጎታችን ሊጣጣም አለመቻሉ ነው፤ አብዛኞቻችን የፌስቡክ
ገፃችንና መለያ ፎቶዎቻችንን ላስተዋለ ከኢትዮጵያዊነትና ሰብዓዊነት ጋር የተቆራኘ ነው፤ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ጀግንነት፣ ፍቅር፣
ነፃነት፣ ሰብዓዊነት፣ ወዘተርፈ የሚያትቱ ገፆችና ምስሎች መለያችን ናቸው፤ ተመሳሳይ ጉዳዮችን “ላይክ” ና “ሼር” በማድረግም የሚወዳደረን
አይገኝም፤ በተግባር ስናየው ግን እውነታው ሌላ ነው፤ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ባዕድነት፣ ከአብዓዊነት ይልቅ ጨካኝነት፣ ከፍቅር ይልቅ
ጥላቻ፣ ከርህራሄ ይልቅ ጭቆና፣ ከነፃነት ይልቅ አፋኝነት፣… ትክክለኛው ማንነታችን ነው፡፡ ጨቋኝ ያልነውን አገዛዝ “በፌስቡክ”
አደባባይ ላይ ተገናኝተን ለማውገዝ ቀዳሚዎች ነን፤ የዘነጋነው ግን የኛን ተግባር ነው፤ ከገዥዎች ባልተናነሰ፣ አንዳንዴም በባሰ
ሁኔታ የሀገሪቱም የራሳችንም ጨቋኞች በየፌስቡክ አደባባይ ላይ ተሰግስገናል፡፡
ሜክሲኮ
ከመድረሳችን በፊት ብሄራዊ ጋ ያለው መብራት ላይ ሳለን ከጎኔ የተቀመጠችው ልጅ ስልክ ከፌስ ቡክ አደባባዩ ተውኔቴ መንጥቆ አወጣኝ፤
የሷም ንግግር ወደ ሌላ ሀሳብ ሊገፋፋኝ ሞከረ፤ “ሄሎ እንዴት ነሽ?!... አትይኝም፤ እና በላችሁ?... እዛ ቤት እኮ ሰንበት
ላይ ጥሩ አይደለምይባላል፤ ለምን እንትን አትበሉም? እና ዛሬ አንበላም ማለት ነው?... ለነገሩ ትናንት ተጋዣለሁ፤…” ምግብ ተኮሩ
የወጣቷ ወሬ እጅ እጅ ከማለቱ በፊት ታክሲው ሸበሌ ደርሶ ገላገለኝ፡፡
አሁን
ከታክሲው መውረድ ጀመርን፤ ልጅት አብረዋት የነበሩት ሶስቱም ወንዶች አይን አርፎባታል፤ ላይክ ሳያደርጓት አይቀሩም፤ ሊከተሏት እየዳዳቸው
ነው፤ እኔም ላይክ የማድረግ ፍላጎት እየከጀለኝ ነው፤ በእኔስ ከመንጋው በምን እለያለሁ?ͥÍ ነገር
ግን በ‹ሼር› እንደሚደርሰኝ ተስፋ አድርጌ ወደ ሸበሌ ሳይሆን ወደ ቤቴ ጉዞ ጀመርኩኝ፤ ከምወደውና ዘወትር ከምጠቅሰው ገጣሚ በዕውቀቱ
ስዩም መጽሀፍ ላይ ቀጣዩን ግጥም እየወረድኩት፡-
ወደ
ምንም የሚያደርሰው መንገድ
ቸኳይ የሚመስለው
ፈጣን የሚመስለው
በውልውል መኪና
በፋሽን መጫሚያ
ወይም በባዶ እግሩ
ሽው እልም የሚለው
ይሄ ሁሉ ምሁር፣ ይሄ ሁሉ ማይም
መንገዱን የሞላው ከታችም ከላይም
ሲመላለስ እንጂ ሲደርስ አይታይም፡፡
