ርዕዮታዊው መንፈስ እንደ ‹‹ቻይኒዝ ባምቡ›› ፪
በመሐመድ
ሐሰን (ኢትዮ-ምህዳር ላይ የወጣ)
እኔ እዚህ ብዕሬን ተጠቅሜ ርዕዮታዊውን መንፈስ መመርመሬን ስንቀጥል፣ በሌላ
በኩል ደግሞ የኢህአዴግ ባለስልጣናት እና በቃሊቲ ያስቀመጧቸው ቅጥረኞቻቸው የሀገሪቱን ህግ ያለአግባብ በመጠቀም፣ ርዕዮትን (ቤተሰቦቿን)
መወንጀላቸውን እና ማሰቃየታቸውን አጠናክረው ገፍተውበታል፡፡ እንግዲህ ‹‹ከሳሽ ዳኛ ሆኖ…›› ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ቀድሞ በተጠነሰሰ
ሴራ ከሰሞኑ በመገናኛ ብዙሀኑ ስንሰማ እንደነበረው፣ የሚፈልጉትን እርምጃ ወስደው በወዳጅ ዘመድ እንዳትጠየቅ ካደረጓት ቦሃላም ቢሆን
የበቀል ግልቢያቸውን አላቆሙም፡፡ ማንም ሰው እንዳያወራት አድርገዋል፤
የህግ መሰረት የሌለውን ትዕዛዝ አልቀበልም ብላ እያወራቻት እና አጋርነቷን እያሳየቻት የነበረችውን፣ ሌላኛዋን ጠንካራ ሴት ፈትያ
መሐመድን ከርዕዮት ነጥለው ሌላ ቦታ አዛውረዋታል፤ ከሷ ጋር መልዕክት ይለዋወጣሉ ብለው የጠረጠሯቸውን እጅግ በጣም አሳፋሪ
በሆነ መልኩ የማሸማቀቅ ተግባር እየፈጸሙባቸው ነው፤…ሌላም ሌላም በርካታ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ያሉት ህግ አለ በሚባልበት
ቃሊቲ ግቢ ውስጥ ነው፡፡
በተለይ ርዕዮት ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ስታገኝ እና ስትታጭ፣ ወንጀላቸውን
በመላው ዓለም ይበልጥ ስለሚያስተጋባው፣ እርምጃቸውን ጠንከር ያደርጉታል፡፡ ከሰሞኑ የሚወስዱት እርምጃዎች የጠበቀበት አንዱ ምክንያትም
ይሄው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ርዕዮት ለ2013ቱ የሳካሮቭ ሽልማት ታጭታለች፡፡
ዓለምዓቀፍ እውቅናው ላቅ ያለው ይህ ሽልማት ለሐሳብ ነጻነት ለታገሉና ለሚታገሉ የሚሰጥ የአውሮፓ ፓርላማ የዓመታዊ ክንዋኔው አንድ
አካል ሲሆን፣ ዘንድሮ ለመጨረሻው ሽልማት ከቀረቡ ሰባት እጩዎች ውስጥ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን እስክንድር ነጋ እና ርዕዮት ዓለሙ ናቸው፡፡
ሁለቱም በቃሊቲው መንግስት ስቃይ ስር ቢሆኑም፣ ዓለም ግን በጀግንነታቸው ሊሸልማቸው አጭቷቸዋል፡፡
እንግዲህ መካሪ ያጣው ኢህአዴግ ኪሎው የሚወርድብን ይሄኔ ነው፡፡ ማንንም
ማሸነፍ በማይችልበት ደረጃ መሽመድመዱን ማሳያ ነች በእድሜ ትንሿ ርዕዮት፡፡ ‹‹የሞኝ ለቅሶ…›› እንዲሉ ከዚህ በፊት ከዚህ በከፋ
መልኩ ሞክረው ያልተሳካላቸውን ሙከራ ነው በከንቱ እየተገበሩት ያሉት፡፡ አሁን ርዕዮት ላይ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ዋነኛ ዓላማ
የመንፈስ ጥንካሬዋን (ርዕዮታዊውን መንፈስ) ለመንጠቅ ነው፡፡ ግን አልቻሉም፤ አይችሉምም! ምክንያቱም በባለፈው ጽሁፌ ላይ በተወሰነ
መልኩ ለመግለጽ እንደሞከርኩትና ቦሃላም በደንብ እንደምገልጸው፣ ርዕዮታዊው መንፈስ ዝም ብሎ በእስሯ የመጣና በቀላሉ የሚከሽፍ አይደለም፡፡
ለማንኛውም እነሱ የተካኑበትን የህገ ወጥነት ተግባር ይቀጥሉበት፣ እኔ ደግሞ የርዕዮታዊውን መንፈስ ምርመራ በመቀጠል ዓላማቸው እንዴት
እንደማይሳካ ለማሳየት እሞክራለው፡፡
ርዕዮት ለምን ታሰረች?
ባለፈው ሳምንት ጽሁፌ ላይ ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት የርዕዮት እስር ምንም
ዓይነት ህጋዊ መሰረት የሌለው፣ እንዲሁም የፍርድ ሒደቱ አንዳችም ተጨባጭ ማስረጃ ያልቀረበበት እና ቀሽም ፖለቲከኞች የደረሱት ፖለቲካዊ ድራማ ነበር፡፡ ከዚህ ቦሃላ ወደ አንባቢዎች
ህሊና ሊመጣ የሚችለው አንደኛው ጥያቄ ‹‹እና ታዲያ ለምን ታሰረች?›› የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ጥያቄ አይደለም እኔ አሳሪዎቿ
እንኳን ቁርጥ ያለ አንድና ብቸኛ መልስ የላቸውም፡፡ አረ እንደውም ጭራሽ መልስ የላቸውም! ብቻ አንድ ዕለት የኢህአዴግ ካድሬዎች ከእንቅልፋቸው ሲነቁ፣ ርዕዮት የምትባል በሳል ጋዜጠኛ ውል አለችባቸው፡፡
ከዛ ቦሃላ የተወሰኑ ግብዞች ይነሳሱና ከምታስተምርበት መንግስታዊ ትምህርት ቤት ስብሰባ ጨርሳ ስትወጣ አፈፍ አድርገው ከመኪናቸው
ላይ ዶሏት፡፡
በወቅቱ ርዕዮት እውነታው (የነሱ እውነት) እስኪገለጥላት ሊፍት ያገኘች
ሳይመስላት እንዳልቀረ እገምታለው፡፡ እውነታቸው ሲገለጥላት ርዕዮት ከመደንገጥ ይልቅ መገረሟ ቅድሚያ እንደሚኖረውም እጠረጥራለው፡፡
ከወዳጇቿ እና ከቤተሰቧ ውጪ ሌላ ሰው ያውቀኛል ብላ ያልገመተችው ርዕዮት፣ ለካ ኢህአዴጋውያኑ ክፉ ቀልባቸው አርፎባት ኖሯል፡፡
እሷም የታሰረች ሰሞን ‹‹ኢህአዴግ መውረዱ የገባኝ እኔ ጋር ሲደርስ ነው?›› ዓይነት ንግግሯን ሹክ ብላናለች፡፡ እዚህች ጋ
‹‹ኢህአዴግ ወርዶ ወርዶ…›› ዓይነት ማጀቢያ ሙዚቃ ብንሞዝቅ አሪፍ ሳሆን አይቀርም፡፡ ለማነኛውም እኔ ለርዕዮት እስር ምክንያት
ናቸው ያልኳቸውን ነጥቦች ልዘርዝር፡፡
አንደኛ፡-
የርዕዮት እስር አሳሪዎቿ (የኢህአዴግ ባለስልጣናት) ለግለሰብ ያላቸውን ፍራቻ እና ከግለሰቦች ጋር የተጋቧቸው እልሆች ማሳያ ነው፡፡
ብዙ ነገሮችን ማስተዋል ከቻልን፣ መሪዎቻችን ሀገሪቱን የሚጎዱ በርካታ ውሳኔዎችን ከግለሰቦች ጋር ካላቸው ግንኙነት በመነሳት ውሳኔ
ያሳልፋሉ፡፡ በዚህ መንገድ ካየነው፣ የርዕዮት እስር ለዳያስፖራ ፖለቲከኞች (ተቀናቃኞቻቸው) ያላቸውን ፍራቻ አልያም ጥላቻ የምንመለከትበት
ነው፡፡ ምክንያቱም ርዕዮት የኢትዮጵያን መንግስት አቋም አጥብቆ ለሚተቸው ኢትዮጵያንሪቪው (ethiopianreview) ድረ-ገጽ
በሪፖርተርነት መስራት እንደጀመረች ነው ብዙም ሳይቆይ ለእስር የተዳረገችው፡፡
ከታሰረች ቦሃላ በፍርድ ቤት የነበረው ሂደት ላይም እንደተከታተልነው፣ የከሳሾቹ
ዋነኛ ትኩረት የነበረው ኤልያስ ክፍሌ የተባለው የ ethiopianreview ድረ-ገጽ ባለቤት ነው፡፡ ይህንን ሰው ደግሞ ደጋግመው
ከነ ግንቦት ሰባት እና መሰል አካላት ጋር እያያያዙ ያነሱታል፡፡ ርዕዮትን ደግሞ ‹‹ከዚህ ሰው የሽብር ተልዕኮ ስትቀበይ ነበር››
ይሏታል፡፡ ምን ዓይነት ተልዕኮ እንደተቀበለች ግን አንድም ማስረጃ አላቀረቡም፡፡ እውነታውን ማወቅ ስለማይሹ እንጂ፣ ርዕዮት በጽሁፏ
ጭምር የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝነቷን በተደጋጋሚ ከመግለጽ ባለፈ በተቃራኒው የቆሙትንም ደህና አድርጋ መሸነንቆጥ ችላለች፡፡
የሷን ጉዳይ እንኳን ትተን ኤልያስ በሚሉት ሰው ላይ እንኳን ሲያቀርቡት
የነበረው ማስረጃ በግልጽ ለ ኢሳት ቴሌቪዥን ጣቢያ የሰጠውን ቃለ-ምልልስ ነበር፡፡ ልብ ማለት የሚገባው ሌላኛው ጉዳይ እነ ርዕዮት
ዋነኛ ጥፋታቸው ተደርጎ የቀረበው ከኤልያስ ጋር መገናኘታቸው ሲሆን፣ እስከዚህ ግዜ ድረስ ግን ኤልያስም ሆነ
ethiopianreview በሽብርተኝነት አልተፈረጁም፤ በፍርድ ቤት የተላለፈባቸው ውሳኔም አልነበረም፡፡
እንግዲህ እንዲህ ባለው ሁኔታ ርዕዮት ለድረ-ገጹ በሪፖርተርነት እንደምትሰራ
ደጋግማ አረጋገጠች፡፡ እነሱ ግን እውነታውን ሳይሆን ያሰቡትን ብቻ ነበር የሚናገሩት፡፡ በየክፍለሃገሩ መሰረተ ልማቶች ላይ ሊደረግ
ለታሰበው ጥቃት እየተሰናዱ ካሉት ውስጥ አንዷ እንደሆነች እና ስልጠናም እንደወሰደች ከሳሾቿ ወተወቱ፡፡ አይደርስ የለ ‹‹ማስረጃ››
የሚሰማበት ቀን ደረሰና ‹‹ማረጃችሁን›› ተባሉ፡፡ ያቀረቡት ማስረጃ ምን መሰላችሁ? ከኤልያስ ክፍሌ ጋር ያደረገችው የስልክ ልውውጥ፡፡
በስልኩ ያስተላለፈላት መልዕክት ምን ነበር? ‹‹አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ‹‹መለስ በቃ›› የሚል ጽሁፍ ተለጥፏልና
ፎቶ አንስተሸ ላኪልኝ›› ይላታል፡፡ የስልክ ልውውጣቸው እነሱ በፈለጉት መልኩ ተቆራርጦ ቢቀርብም፣ በንግግራቸው ወቅት በግልጽ እንደሰማነው፣
ርዕዮት ተጽፏል ያላት ቃልም ሆነ ተጽፎባቸዋል የተባሉት ቦታዎችን ስላላወቀቻቸው ደጋግማ ስትጠይቀው ነበር የሰማነው፡፡…
በመጨረሻም ግን አቃቤ ህጉ የደረደራቸውን አብዛኞቹ ክሶች ‹‹ዳኞቹ›› ውድቅ
ቢያደርጉትም፣ ‹‹በቃ›› በሚለው ጽሁፍ ግን ተጠያቂ መሆኗን በመግለጽ ነበር የፈረዱባት፡፡ ሲፈርዱ ምን አሉ፣ ከሰማነው ድምጽ ጋር
አብሮ የማይሄድ ‹‹…ጽሁፉ ሲጻፍ እየተከተልሽ ፎቶ ታነሺና መረጃ ታቀብዪ ነበር…›› ሲሉ ጥፋተኛ አደረጓት፡፡ ይህ ሁሉ ድራማ ነው፤
እውነታው የእሷ ከኤሊያስ ጋር ማውራት ስለበርካታ ‹‹ባላንጣዎቻቸው›› በማሰብ የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል፡፡ እንጂማ
እንደተላለፈው ውሳኔስ ቢሆን ግድግዳ ላይ የተጻፈን ጽሁፍ ፎቶ ማንሳት አይደለም ለጋዜጠኛ፣ ለሌላውስ ማን ነው የከለከለው? ቀደም
ብዬ እንደጠቀስኩት ለዚህ መሰል ጥያቄ እነሱ መልስ የላቸውም፡፡
ከዚሁ ነጥብ ጋር በተያያዘ አንድ ነገር ላክል፡፡ ርዕዮት ጉዳይዋ ገና በፍርድ ቤት ታይቶ ሳያልቅ፣
በኤልያስ ላይ መስክራ እንድትወጣ እድል ሰጥተዋት ነበር፡፡ ይህ በአንድ በኩል ጉዳያቸው ከኤልያስ ጋር መሆኑን ሲያሳየን፣ በሌላ
በኩል ደግሞ የርዕዮታዊውን መንፈስ ማንነት በደንብ ይነግረናል፡፡ ኤልያስ የሚኖረው አሜሪካን ሀገር ነው፤ ርዕዮት እና ኢህአዴግ
ደግሞ ያሉት እዚሁ ኢትዮጵያ፤ ርዕዮት መስክራበት ልትወጣ ትችል ነበር፤ ከየትም አምጥተው አያስሩትም፤ ትውውቃቸውም ቢሆን ከ ሶስት
እና አራት ወራት በላይ ያልዘለቀና እሱም ቢሆን የስራና የስራ ብቻ ነበር፡፡ ለርዕዮት ግን ቁም ነገሩ እሱ አይደለም፤ እውነት ነው፡፡ የማታውቀውን፣ የማታምንበትን፣…ነገር ከማድረግ ልቅ፣
አሁን ያለችበትን መራራ! ጽዋ መቀበልን ትመርጣለች፡፡
ሁለተኛ፡-
የርዕዮት እስር ለካድሬዎቹ ግላዊ ጥቅም መረማመጃነት ውሏል፡፡ ለዚህ ጥሩ
ማሳያ የሚሆነን በሷም በእጮኛዋም በኩል ወዳጅ መስለው ይቀርቧቸው የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ የእነዚህን ሰዎች ስም አሁን ላይ ማንሳት
ተገቢ ባይሆንም፣ በደንብ የሚያውቁትን እውነታ አንሻፈው በማቀበል ፣ከፓርቲያቸው ተጨማሪ ሹመት ለማግኘት ሲሉ እነ ርዕዮትን በመስዋዕትነት
አቅርበዋቸዋል፡፡
ሶስተኛ፡-
የርዕዮት እስር በስህተት የተፈጸመ ነው ለማለት የሚያስችሉ ምክንያቶችም አሉ፡፡ ካድሬዎቹ እና ባለስልጣናቱ ርዕዮትን ተረባርበው
ካስያዟት ቦሃላ፣ የተወሰኑ መርማሪዎቿ ጋር የነበረው መረጃ ፍጹም የተሳሳተ ነበር፡፡ በመጀመሪያ የተያዘች ሰሞን ‹‹ኤርትራ ድረስ
በመሄድ የአሰልጣኝነት ስልጠና ወስዳለች…›› የሚል የ‹‹በሬ ወለደ›› ክስ ቀርቦባት ስለነበር፣ ለበርካታ ግዜ መርማሪዎቿ ጋር ስትቀርብ
እጇን በሰንሰለት ታስራ ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ወሰደች ባሉት ስልጠና እንዳትዘርራቸው በመፍራት ነበር፡፡ ታዲያ እውነታው የተገለጸላቸው
አንድ ቀን እንደታሰረች የታሸገ ዉሃ መክፈት ሲሳናት በማየታቸው ነበር፡፡ ይሄኔ መንግስትም መርማሪዎችም በቀሽም ካድሬዎቻቸው እንደተሸወዱ
መጠርጠር ስህተት አይሆንም፡፡
አራተኛ፡-
የርዕዮት እስር ከስራዋ ጥንካሬ የመጣ እንደሆነም መገመት ይቻላል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ብዙ ግዜ ፕሬሶች ላይ የሚወስደው እርምጃ
ከጥንካሬያቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሀሳብ አላቸው ብሎ የሚያስባቸው ፕሬሶች እና ጋዜጠኞች ላይ በተለያየ መንገድ ጠንከር ያሉ እርምጃን
የሚወስድ ሲሆን፣ ብዙም የማያሰጉትን ግን በተለሳለሱ አካሄዶች ያዝ ለቀቅ እያደረገ ያንገዳግዳቸዋል፡፡ የርዕዮትን ስራዎች በምናይበት
ግዜም፣ ጽሁፎቿ ሀሳብ ያላቸው እና በጠንካራ ምክንያታዊነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ለዚህም ማሳያው ከጽሁፎቿ ጋር በተያያዘ (በተለይ
‹‹አዲስ ፕሬስ›› ጋዜጣ ላይ ስትሰራ) በየግዜው ከመንግስት አካላትም ጭምር ምላሾች እየመጡ በጋዜጣው ላይ ወጥተዋል፡፡ በግልም
ቢሆን ስልኮች የሚደወሉላት ሲሆን፣ ከተለያዩ ቦታዎች ዛቻና ስድብ ያዘሉ በርካታ ገጽ ያላቸው ደብዳቤዎች ደርሰዋት ያውቃሉ፡፡ ነገር
ግን ፋይዳ ስላልነበራቸው ለፍጆታነት አውላቸው አታውቅም፡፡
ስለዚህ በየትኛውም መንገድ ብንሄድ የርዕዮት እስር ምንም ዓይነት ህጋዊ
መሰረት የሌለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ‹‹እና ታዲያ ለምን አየረፈቷትም?›› የሚለው የበርካቶች ጥያቄ የሚመጣው ይህንን ተከትሎ ነው፡፡
አርግጥ ነው መንግስት ርዕዮትን ሊፈታት የፈለገው ቀደም ብሎ ነው፡፡ ነገር ግን ርዕዮትን መፍታት የእስሩን ያህል ቀላል አልነበረም፡፡
እንደፈለጉት ልትንበረከክላቸው አልቻለችም፤ የሀሰት ምስክርነቱንም አላገኙም፡፡ ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው እና የበላይነቱን ስለነጠቀቻቸውም
ጭምር ነው ሰሞነኛውን ኢህአዴጋዊ አጉል መንፈራገጥ እያስተዋልን ያለነው፡፡ ነገር ግን የሚቻላቸው አይደለም፤ ምክንያቱም የርዕዮታዊው
መንፈስ ጥንካሬ እስከ አሁን ድረስ ሊገባቸው አልቻለም፡፡
የርዕዮታዊው መንፈስ ጥንካሬ ማሳያዎች እና ፈተናዎቹ
በቀደሙት ጽሁፎቼ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የርዕዮት ጥንካሬ መሰረት
ያለው እና በሁኔታዎች መመቸት እና አለመመቸት የሚቀያየር አይደለም፡፡ ጥንካሬው እና እምነቱ የሚጀምረው ከቤት ነው፡፡ ከዚህ ጋር
በተያያዘ ብዙ ምሳሌዎችን ማንሳት ቢቻልም፣ ከቅርቡ አንድ ብቻ ልጥቀስ፡፡
አሁን ማንም እንዳይጠይቃት በተከለከለችበት እና አባቷ እና እናቷ ብቻ ጠያቂ እንዲሆኑ ሲፈቀድላቸው አባቷ የሰጡት ምላሽ
በምን አይነት የሞራል ክበብ ውስጥ እንዳደገች አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ‹‹ሌላ ሰው እየተከለከለ እኔ እንዴት እገባለው? ይህ ህገወጥነት
ነው፤ ከህገ ወጦች ጋር ደግሞ አልተባበርም!›› ነው ያሉት፡፡ ይህ ውሳኔ እንዴት ያለ ክብደት እንዳለው ለማወቅ የግድ አባት ሆኖ
ማየትን የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡
ከዚህ ባለፈ ርዕዮት ከንባብ እና በዙሪያዋ ካሉ ሰዎች ያገኘችው እውቀት
የማንነቷ መሰረቶች ሲሆኑ፣ ‹‹አማን›› የተሰኘው የምክክር ቡድናቸው ደግሞ ከጥንካሬዋ
ጋር ብቻ ሳይሆን፣ መንፈሱን በመጋራት በኩልም ቢሆን ቀዳሚው ነው፡፡ ሌላው ርዕዮት በእስር ላይ እንኳን እያለች ለአደባባይ ማብቃት
የቻለቻቸው ጥቂት ጽሁፎቿ የአቋም ለውጥ የማይታይባቸው እና የጥንካሬዋ ማሳያዎች ናቸው፡፡
አስታውሳለው ከርዕዮት ጋር ከፍተኛ ሙግት ካደረግንባቸው ግዚያቶች አንዱ
የ‹‹አዲስ ነገር›› ባልደረቦች ሀገር ለቀው የወጡበት ወቅት ነበር፡፡ በዛን ግዜ ርዕዮት በፍጹም መውጣት እንዳልነበረባቸው አጥብቃ
ሞገተችኝ፡፡ እኔ ደግሞ የራሳቸው ዓላማ እና አሳማኝ ምክንያት ቢኖራቸው ነው ዓይነት ሙግት አነሳው፡፡ የሆነው ሆኖ አዲስ ነገሮች
ከሀገር ከወጡ ቦሃላ ባልጠበቅነው መልኩ ከመጥፋታቸው ባለፈ አንዳንዶቹ መውጣት እንዳልነበረባቸው ሲገልጹ (ለምሳሌ ታምራት ነገራ
‹‹ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ ክሽፈቱን…›› በተሰኘው ጽሁፉ ላይ ገልጾታል፤) ወዲያው የርዕዮት ሙግት ነበር ትዝ ያለኝ፡፡
ርዕዮት ይህን ውጪ የነበረው አቋሟ ዛሬ እስር ቤት በመሆኗ አልተለወጠም፡፡
ርዕዮት እስከ አሁን የጠቀስኳቸው እና ሌሎችም የጥንካሬዋ ማሳያዎች በተደጋጋሚ
አደገኛ ፈተናዎች ገጥሟቸዋል፡፡ ፈተናዎቹ ከአሳሪዎቿ እና ከራሷ ወገን ጭምር የመጡ ቢሆኑም፣ እሷ ግን በብቃት አልፋቸዋለች፡፡ ከአቋሟም
ንቅንቅ ሊያደርጓት አልቻሉም፡፡ በማዕከላዊ 13 ቀን ምግብ ከልክለው
ለብቻዋ ጨለማ ክፍል ውስጥ አስረው ከማሰቃየት ጀምሮ ምትወደው እጮኛዋን አስሮ እስከማሰቃየት ተደጋጋሚ በደል ተፈጽሞባታል፡፡ ርዕዮት ግን ከዚህም በላይ
ህይወቷን መስጠት ካለባት በፍጹም ወደ ኋላ የማትል መንፈሰ ጠንካራ እና ለዓላማዋ ስትል ሟች ናት፡፡
ሐላፊነት ካለመውሰድ ጋር በተያያዘ ርዕዮት በዙሪያዋ ባሉ ሰዎች እንኳን
ተከድታ እምነቷ ቅንጣት ታህል አልተሸራረፈም፡፡ ከርዕዮት በተጨማሪ ቤተሰቧ እና እጮኛዋ የርዕዮትን መታሰር ተከትሎ በብዙ ወዳጆቻቸው
ተከድተዋል፡፡ በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ የቅርብ ዘመዷ እንኳን ሳይቀሩ ርዕትን ለመጠየቅ አይደፍሩም፡፡ በችግራቸው ግዜ ይደርሱላቸው
የነበሩ ወዳጆቻቸው ከእስሯ ቦሃላ ሸሿቸው፡፡ በስራው ዓለም የረዳቻቸው ሳይቀሩ ከሷ ጋር ለተያያዙ ጉደዮች ቸልተኛ ሆኑ፡፡ እጮኛዋን
ጨምሮ እህቷም የስራ ዋስትናቸውን አጡ፡፡… ሰማይ ምድሩ እስኪጨልምባቸው ድረስ ለከፍተኛ ችግር ተዳረጉ፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ሁሉ
ስቃዮች አሁንም የርዕዮትን አቋም እና እምነት የሚያስቀይሩ አልነበሩም፡፡ ዓላማዋ እሰከ መቃብርም ድረስ አብሯት የሚወርድ ለመሆኑ
እሷም ጭምር አስረግጣ ትናገራለች፡፡ ሞት ለርዕዮት አስፈሪ ነገር እንዳልሆነ የሚያውቋት ሁሉ የሚያውቁት ሀቅ ነው፡፡ ይህን ዓላማዋን
እንደማትቀይር ስትናገር፣‹‹ርዕዮት የአቋም ለውጥ ታደርጋለች ብላችሁ ስጋት አይግባችሁ!›› ትላለች፡፡
ከእስር ቤት ውጪ ያለነውንም ቢሆን ነጻ ነን ብላ አታስብም፤ ለዚህም ነው ‹‹በርቺ›› ስንላት፣ ‹‹እናንተም በርቱ፤ በዘጠነኛው ዞን ውስጥ ነውና ያላችሁት፡፡›› የሚል ምላሽ ነበር የምትሰጠን፡፡
ታዲያ ይህ ርዕዮታዊው መንፈስ አሳሪዎቿ እንዳሰቡት የማይረታ ከመሆኑ ባለፈም፣ የራሱን
ተከታዮች እና የመንፈሱ ተቋዳሾችን ማፍራቱ አልቀረም፡፡ ወደፊትም እውነት ቦታዋን ስትይዝ የበላይነቱን እንደያዘ ይበልጥ ይጎመራል፡፡
እስከዛው ድረስ ግን የእውነት ቦታዋ ቃሊቲ ይሆናል፡፡ ሀገሪቱም ምንም ባልሰሩ እና ብዙ ባወሩ እራሳቸውን የዘመኑ ታጋይ እያደረጉ
በሚያቀርቡ ትምክህተኞች እንደተወረረች ትቆያለች፡፡ ይህ ነው የአሁኗ ኢትዮጵያ እውነት፡፡ ኢህአዴግም እስከዛው መቼም ከፍሎ የማይጨርሳቸውን
ግፎች በመቀፍቀፍ ባለ እዳነቱን አጠናክሮ ይቀጥልበታል፡፡
ለዛሬ የመረጥኳት ግጥም የሰለሞን ሞገስ (ፋሲል) ናት፤ ‹‹እውነትን ስቀሏት!››
ከተሰኘው ድንቅ የግጥም መድብሉ ውስጥ ያገኘኋት ናት፡፡ ርእሷ‹‹ስንቅ የሚያቀብሉኝ እስረኞቹ ናቸው›› ትላለች፤ ይህቺን ግጥም ዶክተር
ዳኛቸው በመጽሀፍ ምርቃቷ ወቅት አሪፍ አድርጎ እንደተነተነው አስታውሳለው፡፡ በሱው እንሰነባበት፡፡ በነገራችን ላይ ርዕዮት የማንበብ መብቷን ጭምር የተነፈገች እስረኛ ናት፡፡
ስንቅ የሚያቀብሉኝ እስረኞቹ
ናቸው
እስረኛ ነኝ እኔ መብቱ የጎደለ፣
ነጻ እርግብ ለመሆን ከቶም ያልታደለ፡፡
በአጥር- በጠመንጃ- በዘብ ተጠብቄ፣
በአንዲት ጠባብ ክፍል ምኞቴን አምቄ፣
ታስሬ እኖራለሁ፣
በመጽሀፍ ቅጠል ዓለምን እያየሁ፡፡
የለም ነጻ ሰው ነኝ! እስረኛ አይደለሁም!
ጭንቅና ሰቀቀን ከእኔ ጋራ የሉም፡፡
‹‹እታሰር ይሆን ወይ?›› ብዬ መች ልፈራ?
ታስሬያለሁና ከራሴ እውነት ጋራ፡፡
የሚዳቋ ስጋት፣ ጭንቅ የሞላባቸው፣
የታሰሩትማ በደጅ ያሉ ናቸው፡፡
እኔ ነጻ ሰው ነኝ!
ያሻኝን ሰርቼ፣
የልቤን አውርቼ፤
ይኽው እዚህ አለሁ ነጻነት አግኝቼ፡፡
የታሰሩትማ በውጭ ያሉ ናቸው!
የልብን ለማውራት-
የልብን ለመስራት ወኔ የከዳቸው፣
የሚደናበሩ በገዛ ጥላቸው፣
እኔ ነጻ ሰው ነኝ! የታሰሩትማ ያልታሰሩት ናቸው፡፡


