Friday, October 25, 2013

ከፕሬዝዳንታዊው ወግ ጀርባ


በመሐመደድ ሐሰን

ጋሽ ግርማን ለቀቅ! ኢህአዴግን እና ኤፈርትን ጠበቅ!
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጽ/ቤት የመጎብኘት አጋጣሚው የተፈጠረልኝ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ከተሰማራሁ ቦሃላ ሲሆን፣ እስከ አሁን ባለው ግዜ ውስጥም ለሶስት ግዚያት ያህል ገባ ወጣ ማለት ችያለው፤ ከሶስቱ ቀናት ሁለቱ ወደ አንድነት፣ አንደኛው ደግሞ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛው በር ፊት ለፊት አከባቢ ወደሚገኘው መድረክ ጽ/ቤት ጎራ ያልኩባቸው ናቸው፡፡ በመድረክ ጽ/ቤት የተገኘነው በ2002 ዓ.ም መጀመሪያ (ከመሐመድ አሊ ጋር) ከአቶ ገብሩ አስራት ጋር ቆይታ ለማድረግ ነበር፤ ሆኖም ግን፣ ከዛሬው ጉዳዬ ጋር ግንኙነት ያላቸው በአንድነት ጽ/ቤት ያደረግኳቸው ሁለቱ ቆይታዎች በመሆናቸው ወደዛው ልለፍ፡፡  
በ 2002 ዓ.ም መጀመሪያ ባምቢስ አከባቢ ወደነበረው የአንድነት ጽ/ቤት ባመራሁበት ወቅት፣ የመጀመሪ የመስክ ስምሪቴ እንደመሆኑ፣ ባገኘሁት ሰው እና ባየሁት ነገር መገረሜ አልቀረም፤ በወቅቱ ቀደምት የፓርቲው አመራሮች መረጃ ለመስጠ በሚያመነቱበት ወቅት አንድ ሰው ያደረገልኝ ትብብር በጣም አስገራሚ የሚባል ነበር፤ ከትብብራቸው ባለፈ የሰውዬው ማንነት በራሱ ይበልጥ ግርምት ፈጥሮብኛል፤ የምፈልገውን መረጃ ከሰጡኝ ቦሃላ ተጨማሪ የሚረዱኝን ጽሁፎች ለመስጠት ያለሁበት ድረስ በመሮጥ መጥተው አቀብለውኛል፤ ኮፒ አልቆባቸው ቢሯቸው በር ላይ የተለጠፈ ወረቀት ገንጥለው ሰጥተውኛል፤…
ትንሽ ቆየት ባልኩ ቁጥር የማስተውለው ነገር ይበልጥ ግርምቴን እያናረው ነው፤ የምሳ ሰዓት ደርሶ ነበርና እኚሁ ሰው አነስ ያለች ሰሀናቸውን ከፍተው እዛው በቢሯቸው ለመመገብ ሲሰናዱ አስተዋልኩኝ፤ የእውነት ነው የምላችሁ ልቤ ‹‹…ጉድ ነው! ጉድ! ጉድ!...›› በሚለው የጂጂ ሙዚቃ ታጅቦ ይደልቅ ጀመር፡፡ እኚህ ሰው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት እና ከ6 ዓመት በላይ የቆዩበትን የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው የለቀቁት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ናቸው፡፡

በቅርቡ አንድነት ፓርቲ በጸረ-ሽብር ህጉ ላይ እያካሄደ በነበረው ዘመቻ አዘጋጅቷቸው ከነበሩት መርሀ ግብሮች ውስጥ አንዱ ህጉን የሚቃወሙ ሰዎች ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ማድረግ ነበር፤ እኔ እና አንድ ወዳጄም በዚሁ ሀሳብ መነሻነት ለመፈረም ቀበና ወደሚገኘው አዲሱ የፓርቲው ጽ/ቤት ጎራ ብለን ነበር፤ በዚህ ግዜም እንደመጀመሪው ሁሉ አንድ ነገር መታዘቤ አልቀረም፤ ወዳጄ ‹‹መቶ አለቃ?›› ሲል ሰላምታ ያቀረበላቸው አንድ ሸምገል ያሉ ሰው ቢሯቸው ውስጥ ቁጭ ብለው፣ አነስ ባለች ሰሀን ዳቦ በወጥ እየበሉ ነበር፡፡ እናም ወዲያው ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ (እሳቸውም መቶ አለቃ መሰሉኝ?) በዛው ተመሳሳይ ሰዓት ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን የምሳ ሰዓት  እያስታወስኩ፣ ‹‹ሁለቱ መቶ አለቃዎች በምሳ ሰዓት›› ስል አሰብኩኝ፡፡
እርግጥ ነው በቤተመንግስት ውስጥ የሚኖረው የምሳ ሰዓት ቀደም ብዬ ካነሳኋቸው ሁኔታዎች በእጅጉ የተለየና ለንጽጽርም የማይቀርብ ነው፤ ምናልባትም ለአልበርት አንስታይን የአንጻራዊነት ንድፈ ሀሳብ (Reletivity Theory) ጥሩ ማሳያም ጭምር ሊሆን የሚችል ነው፡፡ በምሳ ሰዓት ቤተ-መንግስቱ በጭልፋና ማንኪያ ጩኽት፣ በምግብ አብሳዮቹ ሽር ጉድና መስተንግዶ፣ በምግብ ዓይነቶቹ ብዛትና ጥራት፣ ወዘተ እንደሚደምቅ መገመት አያዳግትም፡፡
ሁለቱም ለዚህች ሀገር ይበጃል ያሉትን በየፊናቸው የሚሰሩ ናቸው፤ ነገር ግን ልዩነታቸው ለመግለጽ እንኳን በማይመች መልኩ የሰፋ ነው፤ መንግስት በተቃዉሞ ጎራ ያሉትንም ያቀማጥል የሚል ጥያቄ ማቅረቡ የማይታለም ቢሆንም፣ ቢያንስ ግን ከስር ከስር በመከተል ስቃያቸውን እንዳያበዛባቸው መመኘት ይቻላል፡፡ ይህንን እና መሰል የዜግነት መብታቸውን ብቻ ቢያከብርላቸው እና ክብራቸውን ቢጠብቅላቸው፣ በቤተመንግስት ውስጥ በወከባ ከሚቀርብላቸው ጮማ በተሻለ፣ በጠባቧ ቢሮ ያለው ነጻነት እና ሽሮ ለእነሱ በእጅጉ የላቀ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
በተለይ የዶክተር ነጋሶ ጉዳይ ይበልጥ ይረብሻል፤ እሳቸው ሁሉንም ነገር ያደረጉት እና ጠባቧን ቢሮ ከጠባቧ ህይወት ጋር የመረጡት፣ ከምንም በላይ እንደ ሰው በነጻነት መኖር ፈልገው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፤ ሆኖም ግን እንደ አንድ ዜጋ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩ አንድ ትልቅ ሰው፣ በአንዲት ጠባብ ቢሮ ውስጥ ከመመገባቸው በተጨማሪ፣ ታክሲ ተጋፍተው ሲሳፈሩ፣ የሚኖሩበትን የኪራይ ቤቶች ለቀው እንዲወጡ ሲገደዱ፣ ጥቅማጥቅማቸውን ሲነፈጉ፣ በአንድ ተራ ፖሊስ ሲጎነተሉና ሲታሰሩ፣ በህመማቸው ጊዜ የጤና ዋስትና ሲያጡ፣… ከማየት በላይ ምን የሚረብሽ ነገር አለ?... ይህንን ጉዳይ ይበልጥ እንቆቅልሽ የሚያደርግብን ደግሞ ከሰሞኑ ለተሰናባቹ ፕሬዝዳንት በወር  የ400.000 ብር ቤት መንግስት እንደተከራየላቸው ስንሰማ ነው፡፡
ከተሰናባቹ ፕሬዝዳንት የቤት ኪራይ ጋር በተያያዘ የተነሱት ነጥቦች (እኔ ያየኋቸው)፣ በፕሬዝዳንቱ ስብዕና ላይ ያተኮሩ እና በብሩ መብዛት ግርምት የተፈጠረባቸው ናቸው፤ እኔ ግን ከቤቱ ኪራዩ ጋርም ሆነ ከፕሬዝዳንትነት ዙፋኑ ጋር በተያያዘ መነሳት ያለባቸው ነጥቦች እንዳሉ አስባለሁ፡፡
የቀደሙት ፕሬዝዳንት የስራ ዘመናቸው ወደመገባደዱ በተቃረበበት ወቅት ቀጣይ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ለመሆን እንደሚፈልጉ ይናገሩ የነበሩ እና ለፕሬዝዳንትነት በየመገናኛ ብዙሀኑ ይታጩ የነበሩ ሰዎችን ልብ ብለን ካስተዋልን፣ ቦታው ምን ያህል እንደተናቀ ይገባናል፤ አንዳንዶቹ መደበኛ ትምህርታቸውን እንኳን በአግባቡ የጨረሱ አልነበሩም፤ ህልመኞቹ ሀገር በእግር ፍጥነት አልያም ደግሞ በድምጽ ውበት የሚመራ ያህል ሳይሰማቸውም አልቀረም፤ ብዙዎች በድፍረት ቦታውን ከመመኘት አልተቆጠቡም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ያላቸውን ዓለም አቀፋዊ ክብር ከግምት ያስገቡት አይመስሉም፤ የገዢው ፓርቲ አሻንጉሊት መሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ሊወተውቱ ሁሉ ቃጥቷቸዋል፡፡… የሆነው ሆኖ ቦታው ምን ያህል እርባና ቢስ እንደሆነ ከደፋሮቹ ድፍረት የተሻለ ሌላ ማሳያ ፍለጋ መኳተን የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡… አዲስ የተሾሙትን ዶ/ርም ይህንኑ በደንብ የሚያጠናክሩልን ይመስለኛል፡፡    
ጋሽ ግርማን ለቀቅ! ኢህአዴግን እና ኤፈርትን ጠበቅ!
እኔ እንደማምነው ጋሽ ግርማ ቀደም ብሎም ቢሆን በቦታው ላይ አልነበሩም፤… ዶክተር ሙላቱም ቢሆኑ ያው ነው፤… ቦታው በኢህአዴግ ስርዓት እና አሰራር ሽባ ተደርጓል፤ ነገር ግን ግለሰቦቹ በቦታው ላይ እስካሉ ድረስ የፓርቲው ፍላጎት በስማቸው ይፈጸማል፤ አሁን ደግሞ ከወረዱም ቦሃላ ለፓርቲው ተጨማሪ ጥቅም ማግበስበሻነት እንዲውሉ እየተደረገ ነው፤ ከሰሞኑ ስንነጋገርበት የነበረው የፕሬዝዳንቱ የቤት ኪራይ ጉዳይ የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በአሁን ጊዜ በየከተሞች ውስጥ ከምናያቸው ግዙፍ ህንጻዎች በስተጀርባ የባለስልጣናቱ (በተለይ የህወሐት) ስውር እና ግልጽ እጆች አሉ፤ ገንዘቡ ደግሞ ግልጽ ነው ከየትም የመጣ ሳይሆን በተለያየ መንገድ ከሀገሪቱ ሀብት እና ከህዝቡ የተበዘበዘ ነው፡፡… እነዚህ ህንጻዎች በብዝበዛ  ተሰርተው ካለቁ ቦሃላም ለተጨማሪ የሀገሪቱን ሀብት መበዝበዣነት ይዘጋጃሉ፤ በየከተሞቹ ከሚቆሙ ህንጻዎች ጀርባ ያሉት ባለስልጣናቱ፣ ያላቸውን ሀላፊነት ተጠቅመው ህንጻዎቹ ለአንድ መንግስታዊ ተቋም ቢሮነት አልያም ከሰሞኑ ለጋሽ ግርማ እንደተደረገው ለባለስልጣናቱ መኖሪያነት በውድ ዋጋ እንዲከራይ ያደርጋሉ፡፡
በአሁን ሰዓት ብዙ መንግስታዊ ቢሮዎች በዓመት ለኪራይ የሚያወጡት ብር የራሳቸውን ህንጻ መገንባት የሚያስችላቸው ቢሆንም፣ የህወሐት /ኤፈርት/ ስውር እጆች ግን ይህ እንዲሆን የሚፈቅዱ አይደሉም፤ በህንጻ ኪራይ ስም ከመንግስት ካዝና የሚሰበሰበው ጥቅም ዳጎስ ያለ በመሆኑ አሰራሩን ይበልጥ መሰረት ይሰጡታል፤ አንድ መንግስታዊ ቢሮ በወር እስከ ሁለት ሚሊየን ብር ለህንጻ ኪራይ የሚከፍልበት ሁኔታ እየተለመደ መጥቷል፤… ከሰሞኑ እንደሰማነው ደግሞ ጋሽ ግርማ በወር እስከ 400.000 ብር የሚያወጣ ቤት ተሰናድቶላቸዋል፡፡… ይህ የተደረገው ለሰውየው አልያም ለዙፋኑ ካላቸው ክብር የተነሳ አይደለም፤ ይልቅ ከህንጻዎቹ ጀርባ የአንድ ታጋይ፣ባለስልጣን፣የፓርቲው ተቋም፣ ወዘተርፈ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስላለበት እንጂ፡፡ በቃ እውነታው ይሄ ነው!
የዛሬዋ ኢትዮጵያ መሪዎች እንዲህ ናቸው- ሁሉን ነገር በኢኮኖሚ ሚዛን ላይ ከመስፈር ጋር ፍቅር የያዛቸው፤…ሁሉንም ነገር ከፓርቲ ጥቅም አንጻር ብቻ መመዘን!... ሀገርን ባገኙት አጋጣሚ እና ቀዳዳ ሁሉ መበዝበዝ! … መሬቱን በህገወጥ መንገድ ማገኘት እና ህንጻውን በበዘበዙት ገንዘብ ማሰራቱ አልበቃ ቢላቸው በኪራይ ሰበብም ከስጋዋ አልፈው አጥንቷ ድረስ ይግጧታል!... በቃ እነሱ ይሄው ናቸው፤ ከጠሉና ለፓርቲያቸው ካልበጀህ የቀደመ ፕሬዝዳንት ብትሆንም ግድ የላቸውም፤ ዜግነትህ ሳይቀር ይገፉሀል፤… አገልጋይ/ሎሌ/ ከሆንክ ደግሞ ዳጎስ ያለ ቁሳዊ ጥቅም ይዘጋጅልሀል፤ ባንተ ሰበብም ለፓርቲው እና ሰዎቿ ሲባል ሀገራዊ ብዝበዛው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡…  
ይሄኔ ነው ታዲያ ጮክ ብሎ እንዲህ ማለት፡-     
እናት ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!
የመብላት እና የመበላት ሂደቱ መልክና አይነቱን እየቀየረ ይቀጥላል፤ ግን እስከመቼ?!....    

No comments:

Post a Comment