በመሐመድ ሐሰን
መንደርደሪያ፡-
ረቡዕ ታህሳስ 9 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው "ሰንደቅ" ጋዜጣ ላይ ዘሪሁን ሙሉጌታ የተባለው
የጋዜጣዋ ባልደረባ "መለዮ አልባው፤ “ምሁር” " ሲል በዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ላይ ጽፎ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም ጸሀፊውን ክፉኛ በማውገዝ የፃፉ በርካቶች
ናቸው፡፡ እንደ "ፌስ ቡክ" ያሉ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ያለፈው ሳምንት ዋነኛ መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ይኽው ፅሁፍ ነበር፡፡
የዚህን ጽሁፍ ይዘት ተከትሎ ግመሾቹ አስተያየት ሰጪዎች ዘሪሁንን (ፀሀፊውን)
በወያኔነት ሲፈርጁት፣ አንዳንዶቹ ከተስፋዬ ገብረ አብ ጋር አመሳስለውታል፤ አብዛኞቹ ደግሞ ዳኛቸው ለምን ተነካ በሚል ስሜት የተጫነውን
ሀሳብ ሰንዝረዋል፤ የተቀሩት ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲን ነፃ ለማውጣት ሲሉ ዳኛቸውን በአደባባይ ለመስቀል ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን እኔ
ካየኋቸው ፅሁፎች ውስጥ አንዳቸውም ዘሪሁን ባነሳው ሀሳብ ላይ በመንተራስ ያቀረቡት ጠብ የሚል ሀሳብ የለም፡፡…
እኔ እንደማምነው ዘሪሁንን በወያኔነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የፈረጁት
ሰዎች ዳኛቸውን በመውደድ ብቻ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ ዘሪሁን የመጻፍ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡… እኔ በበኩሌ ዳኛቸው ፍፁም አይነኬ
(የማይፃፍበት) ሰው ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን ሲጀመር ሀሳብ ይዘን መነሳት አለብን፡፡… የዚህ ጽሁፍና ጸሀፊ ዓላማም
ዘሪሁንን በመተው ያቀረበውን ሀሳብ መሞገት ነው፡፡
የነገሩ መነሻ፡-
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ያረፉበትን 100ኛ ዓመት ለመዘከር በሚል እሁድ ታህሳስ 6 ቀን 2006
ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ የውይይት መድረክ ያዘጋጃል።በውይይቱ ላይ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ከተጋበዙት እንግዶች ውስጥ አንዱ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ነው። እናም ዶክተሩ "የሰንደቅ ጋዜጣ መቅረፀ ድምፅ ይነሳልኝ…”
ይላል፡፡ በቃ የዘሪሁን ጽሁፍ መነሾ ይህ ነው፡፡ እኔም በዚህ መነሻነት የተጸፈውን የዘሪሁንን ጽሁፍ ነው መፈተሸ የፈለኩት፡፡
ሚዛናዊነት
እና ምክንያታዊነት
ጸሀፊው ዘሪሁን በጽሁፉ ውስጥ ይበልጥ የተቆጨውና የተብሰለሰለው ዳኛቸው ከሚዛናዊነት እና
ምክንያታዊነት አፈንጧል ብሎ ስላሰበና የኢትዮጵያ ፕሬስን መፃኢ እድል በዛች ክስተት ማየቱ ነው፡፡… ኢዚህች ጋር ሌላውን ትተን
ጸሀፊው እራሱ ባነሳው ሚዛናዊነት እና ምክንያታዊነት የራሱን ጽሁፍ እንገምግመው፡-
ዘሪሁን ጽሁፉን ሲጽፍ ከፊትለፊቱ የስድብ ዝርዝር (ሜኑ)
ያስቀመጠ ነው የሚመስለው፡፡ ወገቡን ይዞ ስድቦቹን ያዥጎደጉዳቸዋል፡፡… ሲቅበዘበዙ፣ የሚዲያ ቂመኛ፣ መሸታ
ቤት ካልሆነ…፣ እብሪተኞች፣ በቀለኝነት፣ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለታቸው፣ ተለዋዋጭ
ባህሪ፣ ቃርመው የሚያመጡትን “ኀሳብ”፣ ዘመቻ ማካሄዳቸው፣ ቂም፣ በቀል፣ በትር..፣ ምሁር ተብዬው፣ በቂም በቀለኝነት የታወረ
ምሁር፣ ሆደ ሰፊነት የሌላቸው፣ ማመዛዘን የማይችሉ “ፊደላዊ ምሁር”፣ “የአደባባይ ምሁር” ብለው ራስዎትን እንደሾሙ፣ በቲፎዞ
ጭብጨባ ስካር ውስጥ ከገባ “ምሁር”፣ የእርስዎን ትንሽነት መድገም፣ እንደሳቸው ትንሽ ላለመሆን፣…"
ጸሀፊው ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ጉተታ የበዛበት፣… ሀሳቡን በመያዝ ዳኛቸውን
ወደታች ለመጎተት ይዳክራል፡፡ ዳኛቸው ላይ ከየትም ያገኘውን ጭቃ ይወረውራል፡፡ ይሄኔም የተነሳበትን የምክንያታዊነትና የሚዛናዊነት
ነጥብ ገደል ይሰደዋል፡፡ የተወሰኑ ማሳያዎችን እንምዘዝ፡-
1.
በጽሁፉ አምስተኛ አንቀጽ ላይ "… ይህን ያደረኩት እንደሳቸው
ትንሽ ለመሆን ባለመፈለግ ነበር።…" የሚል ሀሳብ ሰፍሯል፡፡ ዘሪሁን ምክንያታዊነቱን እንዲያረጋግጥልን የተወሰኑ ጥያቄዎችን
እንሰንዝር፡- እውን ዶክተር ዳኛቸው ትንሽ ነው?
ከሆነስ የአሁኑን ጨምሮ በሌሎችም እትሞቻችሁ ላይ ቀዳሚና ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው ለምንድነው? ትንሽ ከሆነ መቅረጸ-ድምጹን ቀድሞውኑ ለምን
ማስቀመጥ አስፈለገ? ትንሽ ሰው ፍለጋ መቅረጸ ድምጽ አዝሎ ያለበት ድረስ መሄድ ምን ይሉታል? ጸሀፊውስ ለትንሽ ሰው ይህን ያህል
መብሰልሰል ለምን አስፈለገው? ...
2.
ወረድ ብሎ በሰባተኛው አንቀጽ
ላይ የሰፈረውን ሀሳብ ደግሞ እንየው፡- " ….. “ያለፉት ሃያ አንድ ዓመታት
ፖለቲካ” በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ሰፊ ሐተታ በብቸኝነት ዘግባ የነበረችው ሰንደቅ ጋዜጣ ነበረች። በዛን ወቅት ለጋዜጣውም ሆነ
ንግግራቸውን በፅሁፍ መልክ አደራጅቼ ያቀረብኩት እኔ በመሆኔ በግል ስልኬ በመደወል ጭምር “እንዲህ ነው ጋዜጠኝነት” ሲሉ
አድናቆት አዥጎድጉደውልኝ ነበር።…. ያዙኝ ልቀቁኝ ማለታቸው የሰውየውን
ተለዋዋጭ ባህሪ ያጋለጠ ክስተት ነበር።"
እዚች ጋር ትንሽ ሰፋ ያለ ሀሳብ
እናነሳለን፤ በቅድሚያ ግን አሁንም ጥያቄ እንሰንዝር፡- ዘሪሁን ይህንን አንቀጽ ያነሳው የዳኛቸውን ተለዋዋጭ ባህሪ ያሳይልኛል
በሚል ነው፡፡ "አድናቆት ገለጹልኝ…" ያለው ነገር እውነት ቢሆን
እንኳን፣ እሱ የጠቀሰው ነገር እንዴት የዳኛቸውን ተለዋዋጭ ባህሪ ያሳያል? በአንድ ወቅት ዘሪሁንን አደነቀ፣ አሁን ደግሞ ሰንደቅን ተቸ፤ ዘሪሁንና ሰንደቅ ምን አገናኛቸው? በአንድ ወቅት ጥሩ ሲሰራ የተደነቀ ሰው
ሲያጠፋም እንዲሞገስ ይሻል?...
ሌላው በሰባተኛው አንቀጽ ውስጥ
ከሰፈረው ነጥብ ጋር በተያያዘ ላነሳው የምፈልገው፣ “ያለፉት ሃያ
አንድ ዓመታት ፖለቲካ” በሚል ርዕስ ሰንደቅ ላይ የወጣው ጽሁፍ "ጥሩ ነው" የተባለበትን ምክንያት ነው፡፡ በወቅቱ ጽሁፉ ከመውጣቱ ቀደም
ብሎ ዳኛቸው ከቀደመ ተሞክሮው በመነሳትና ሀሳቡ እንዳይዛባበት ሲል ሊረዳቸው እንደፈለገ ይነግራቸዋል፡፡ ከተወሰኑ የስልክ
ልውውጦች በኋላ ይስማሙና ዘሪሁን ጽሁፉን አመጣው፡፡ ዳኛቸውም ከአሉላ ጥላሁን ጋር በመሆን ጽሁፉን ያስተካክሉትና ባነበብነው
መልኩ ጥሩ ሆኖ ሊቀርብ ችሏል፡፡ ይህ ሲሆን እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔም ስምምነት ላይ እስኪደርሱ በቦታው ላይ ነበርኩኝ፡፡
3.
"…. እኔም ዶ/ሩ ከላይ በተቀመጠው የተጋነነ ገለፃ መጠን በየዋህ ልቦና አደንቃቸው ነበር። ዳሩ
ግን ይህ ሁሉ የተባለላቸው ሰው ማመዛዘን የማይችሉ “ፊደላዊ ምሁር” ሆኑብኝ።…" ይህ የጸሀፊው ሀሳብ በተለያዩ አንቀጾች ላይ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡
ለገጽ ቁጠባ ሲባል ሁለት ነገሮችን ብቻ አንስተን እንለፍ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የጸሀፊው አድናቆትና የዳኛቸው ምሁርነት የሚጸናው
ዳኛቸው ከዘሪሁን ጋር እስከተስማማ ድረስ ብቻ ነው፡፡ መመዘኛው ከሱ ጋር ያላቸው ግንኙነት መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ ሌላውና
ዋነኛው የምንረዳው ጉዳይ ቢኖር ዘሪሁን በሚቃረም ሀሳብ የሚመረቅን መሆኑን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዝቅ የሚያደርገው ጸሀፊውን እንጂ
ዳኛቸውን አይደለም፡፡
4.
የዶክተሩን ምሁርነት ጸሀፊው መካድ ወይም መጠራጠር የሚጀምረው ከርዕሱ ነው፡፡ ምክንያት ግን የለውም፡፡
የዳኛቸውን ትልቅነት ለማሳየት ከሱ አይጠበቅም በሚል እምነት በርካታ ምክንያቶችን ሲዘረዝር፣ አውርዶ ሲጥለው ግን ምንም ማሳያ ሳያቀርብ
አላዋቂ ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳል፡፡… አንድ ቦታ ላይ የጠቀሰውን ጽሁፍ ለማሳያነት እናንሳው፡-
“ዶ/ር ዳኛቸው ተነቦ የማያልቅ መጽሐፍ ነው። ለብዙ ተዋስኦች
ጤናማ ገዢ ኀሳቦች አሉት። የኢትዮጵያን ታሪክንም አብጠርጥሮ
ያውቃል። ፍልስፍና ለእርሱ ክህሎት ነው። ልክ እንደፈረንሳዊ ፈላስፋ በሀገርኛ የሥነ-ጽሁፍ ውጤቶች አጅቦ ታላላቅ የፍልስፍና
ቲዎሪዎች ለብዙዎች በሚገባና በሚማርክ መልኩ ያቀርባል”
ይህንን ጽሁፍ ሲሰነቅር ምንም አይነት ማብራሪያ አይሰጠንም፡፡ ይልቅስ በደፈናው በሰፈረው ሀሳብ
ላይ በመሳለቅ ለማለፍ ይሞክራል፡፡ እኔ በመግቢያዬ ላይ ጭምር እንደገለጽኩት አንድ ሰው ሀሳብ ይዞ ከተነሳ ማንንም ሊተች ይችላል፡፡
ዝም ብሎ በደፈናው ሳይመረምሩ ግን ማድነቅም ሆነ ማጣጣል ተገቢ አይደለም፡፡
እኔ በግሌ ዳኛቸው ተነቦ የማያልቅ መጽሀፍ ነው፣ በሀሳቦቹ ውስጥም የኢትዮጵያን ችግሮች ማየትና
መመርመር ይቻላል፣ ታሪክንም ሆነ ፍልስፍናን ጠንቅቆ ያውቃል፣…ከሚል እምነት ባለፈ በግል ተነሳሽነት ሀሳቦቹን መርምሬ በመጽሀፍ
መልክ እያዘጋጀኋቸው እገኛለው፡፡ ሌላው ወገን ደግሞ ከፈለገ ተቃራኒውን ሀሳብ አንስቶ በምክንያት መሞገት ይችላል፡፡ ችግር
የሚሆነው በስሜት እና በንዴት ውስጥ ሆኖ ብዕር መጨበጥ ነው፡፡
5.
ቂምና በቀል የሚለው አገላለጽ በጽሁፉ ውስጥ አብዛኛው ቦታ ላይ ተጠቅሷል፡፡… ዘሪሁን ዳኛቸው እርምጃውን
የወሰደው በቂም በቀል ነው ብሎ ያምናል፡፡ ከዚህ የምንረዳው እነ ዘሪሁን ቂም የሚያሲዝ አንዳች ነገር ሰርተዋል እንደማለት ነው፡፡
ከሰሩ ደግሞ አንድም ቦታ አልተጠቀሰም፡፡
በሌላ ቦታ ላይ እንዲሁ "የግል ቂም በቀል ግን የለንም…" ይላል፡፡ አንድ
ሰው እንዲህ የሚያደርገው በቂም በቀል ነው ብሎ ካመነ በኋላ ነው የሚገረመው፡፡ ስለዚህ የሚገረመው ስለሌላቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡ በጽሁፉ ቀደም ያለው አንቀጽ ላይ ደግሞ "በኛ ላይ ዘመቻ ከፈቱብን…"
የሚል ነገር ሰፍሯል፡፡ ዘሪሁንን እዚህች ጋር እንይዘዋለን፡፡ እራሱን ከሰንደቅ ጋር ሰፍቷል፡፡ ሌላውን ችግር ማየት አልፈለገም፡፡
ስለ ሰንደቅ ሌላ ሚዲያ ላይ ማውራት ዘመቻ ሲሆን እነሱ ግን ስለ ዳኛቸው የፈለጉትን ሲሉ መብት ይሆናል፡፡
6.
በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ለዳኛቸው ማስተባበያ ተሰራለት የተባለበት መንገድ በጣም አስገራሚ ሊባል
የሚችል ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡- "… በኋላም መስከን ሲጀምሩ አማላጅ በመላክ ጭምር በዘገባው ላይ ሌላ ሰው በምንጭነት ተጠቅሶ
“የብአዴን አባል ናቸው” የሚለው አገላለፅ ተገቢ ባለመሆኑ፣ ለጊዜውም ማረጋገጫ ያልተገኘለት በመሆኑና በቀጣይም ከእሳቸው ጋር
ሊኖር የሚገባውን ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር ሲባል ማረሚያው ወጥቶላቸዋል።"
እንግዲህ ከዘሪሁን ገለጻ
እንደምንረዳው ሰንደቆች ማስተባበያ የሚያወጡት የሙያ ግዴታ ሆኖባቸው ሳይሆን መስከን ለጀመረ፣ አማላጅ ለላከ፣… ነው፡፡ በዚህ
አንቀጽ ውስጥ ሌሎች በርካታ ችግሮች ያሉ ሲሆን፣ በገደምዳሜም ቢሆን ዳኛቸውን ከብአዴን ጋር በግድ የማጣበቁ ሂደት አሁንም
ተጠናክሮ የቀጠለ ይመስላል፡፡
ከምክንያታዊነት ባለፈ በዘሪሁን ጽሁፍ ውስጥ የምናገኛቸው የተዛቡ እውነታዎች
ብዙ ናቸው፡፡ ዳኛቸው የ"ፌስ ቡክ" ገጽ እንዳለው ተደርጎ የቀረበው መረጃና እራሱን የአደባባይ ምሁር እያለ ይጠራል የሚሉትን ስህተቶች
ለአብነት ያህል መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዳኛቸው ከኮምፒተር ጋር ብዙም ግንኙነት የሌለው ሲሆን፣ የአደባባይ ተዋስኦና የአደባባይ ምሁር
የሚሉትን ሀሳቦች እነ ዘሪሁን በአግባቡ አልተጠቀሙባቸውም፡፡
ዘሪሁን እዚህ ሁሉ ስህተት ውስጥ ከመግባቱ በፊት ግን ዶክተሩን እዛው
መድረክ ላይ "ለምን ድምጼን አትቅዳኝ አልክ?" ብሎ ቢጠይቀው ምን ነበረበት?
ምናልባት ይህንን አድርጎ ቢሆን ኖሮ በፈለጉ ጊዜ የሰጡትን መለዮ በፈለጉ ጊዜ ከማንሳት ዳግም ስህተት ይታደጋቸው ነበር፡፡ ከመለዮዋ
ጋር በተያያዘ አንድ ወዳጄ ያለውን ላስታውስ፡-
"እነኚህ ልጆች
መለዮ የሚወዱ ከሆነ መተቸት ያለባቸው መለዮ በአደባባይ የሚያውለበልብን መሪ ነው እንጂ ዳኛቸውማ ባርኔጣውን የሚያውለበልብብበት
አደባባይ ከየት አምጥቶ?!"
ከመብት አኳያ፡
እንደ አሜሪካ ባሉ ያደጉ ሀገራት ውስጥ አንድ ሰው ንግግር በሚያደርግበት
ወቅት በግልጽ የሚሰራ ህግ አለ፤ ማንኛውም ተናጋሪ ሲጋበዝ አብሮ concent form (የይሁንታ ቅጽ) ይቀርብለታል፡፡ ድምጹ እንዲቀረጽ፣
ፎቶ እንዲነሳ፣… ፈቃደኛ መሆኑን የሚጠይቁ ዝርዝር መረጃዎች በፎሩሙ ላይ አሉ፡፡ እንደ ግለሰብ የመወሰን መብት የግለሰቡ ነው፡፡
ከዚህ ተነስተን የዳኛቸው እና የሰንደቅ ጉዳይ ላይ ጥያቄዎች መሰንዘር
እንችላለን፡፡ አንድ ግለሰብ አንድን ሚዲያ "ድምጼን አትቅረጸኝ" ሲል መብቱ ነው ወይስ የፕሬስ አፈና እየፈጸመ? ድምጹን መቅረጽ ሰውዬ የሚሰጥው
ወይስ የሀገሪቱ ህገ-መንግስት የሚሰጠው መብት?... ዘሪሁን መልሱን ካገኘው እስኪነግረን
መጠበቅ ነው፡፡
መደምደሚያ
ዘሪሁን በጋዜጣዋ ውስጥ የተለያዩ ጉዳዮችን በመድፈር የተሻለ ጋዜጠኛ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ምናልባት ግን ከኋላው ያሉ
ግፊቶች አንዳንዴ ትክክለኛውን መንገድ እንዲስት እያደረጉት ይሆናል፡፡ ስለ ፕሬስ ነጻነት የመቆርቆር ስሜቱን ብጋራም የምር የምንታገል
ከሆነ ግን በነጻው ፕሬስ ስም ተቋቁመው ያሉትንም ጭምር ነው መቃወም አለብን፡፡ ስራው መጀመር ያለበት ከቤታችን ነው፡፡ ሰንደቅም
እራሷን ትመርምር፡፡ የፕሬስ አፈናውን ከሚያግዙት አንዱ በነጻው ፕሬስ ስም የሚንቀሳቀሱ አስመሳይ ጋዜጦችም ጭምር መሆናቸውን ማመን
ይኖርብናል፡፡ ምናልባት በዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ እመለስበት ይሆናል፡፡ ለማንኛውም ግን የዘሪሁንን መዝጊያ ተውሼ ልሰናበት፡፡ ረጅም ዕድሜ፣ ጥንካሬና ኃላፊነት
ለኢትዮጵያ ፕሬስ!

