Sunday, June 16, 2013

ያችን ልጅ ጠጣናት፡፡

 
በሀብታሙ ስዩም

በአዲስ ጉዳይ መጽሄት ላይ እንደወጣው

ደቡብ አፍሪካ በሚባል ሃገር...በዛች ልጅ ደቡባዊ ክፍል በኩል ጉድ ተሰራን፡፡ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከሚለው ቃል በመቀጠል የሚያስጠራት live sex የሚለው እንደሆነም ታወቀ፡፡መጀመሪያ ጉድ ተባለ በኃላ very good የሚሉ መጡ፡፡ያች ልጅ ከሴራሊዮናዊ ጋር አንሶላ ተጋፈፈች ዘጠኝ ወር ሳይሞላው በመላ ኢትዮጵያዊያ ክርክር ወለደች፡፡
ከክርክሮች ሁሉ ግን የጦፈው በዚህ ድራፍት ቤት በዚህ ጠረጴዛ ላይ እየተደረገ ያለው ሳይሆን አይቀርም፡፡እልኸኛው ሞገሴ፣ስሜት አልባኛው ይጋረድ፣ሙዚቀኛው ቀረሮ እና እኔ ባለንበት ጥግ ላይ፡፡
በሰላም እየጠጣን ነበር ፡፡እንደምታውቁት ወዝ አልባ ሙዚቀኛ ጭር ሲል አይወድም፡፡ሙዚቃው የነሳን ሰላም ሳያንስ ቀረሮ እራሱ ብጥብጥ አስነስቶ ቁጭ አለ፡፡
‹‹በነገራችን ላይ ልጂቱን በማሰመልከት ነጠላ ዜማ እየጨረስኩ ነው፡፡››አለ አንደፓርቲ አባል እየተኩራራ፡፡
ልማዱ ነው ፡፡ ምንም ነገር ይፈጠር ነጠላ ዜማ ሰርቶ ወደ ኢቲቪ ይሮጣል፡፡በብዙ ነገሮች ላይ ነጠላ ዜማ ሰርቷል፡፡የእናቱ ነጠላ ጫማ የጠፋለት ሁሉ ነጠላ ዜማ ሰርቷል፡፡ለብዙ ጊዜያት ሙዚቃ አትችልም እያለን ልናተርፈው ሞከርን ስልችት ሲለን ግን ‹‹በነጥላሁን ዘመን ተፈጥረህ ቢሆን ኑሮ የጥላሁንን ጥላ ትሆን ነበር፡፡››እያለን በጫጫታ አልመለስ ያለንን በጭብጨባ ልንገድለው ወሰን፡፡ ሞገሴ ብቻ ነው የማታገሰው፡፡
‹‹ዜማው ከሙሉቀን መለሰ ሰውነቷ የተወሰደ ነው፡፡››
ሁለታችን ከንፈራችንን በመጠጫው ላይ መርገን ዝም አልነው፡፡
ዝምታችንን ከይሁንታ እኩል አድርጎ በሙሉቀን ዜማ ላይ በጎደሎ ቀን የመጡለትን ግጥሞች ጨምሮ ያንቋርር ጀመር፡፡
‹‹ጣይቱን እያሰብኩ እኮራ ነበረ፡፡
ተዋቡ እያሰብኩ እኮራ ነበረ፡፡
እሷ እፈጠር ብላ አንጀቴ አረረ፡፡
አይ ሰውነቷ…
ቲቸር ነኝ ማለቷ፡፡››
‹‹ዝጋ!››ሞገሴ አምባረቀ፡፡
‹‹እንዴት ነው?››አለን ቀረሮ በጉጉት ተሞልቶ፡፡‹‹ምኑ?››አለው ሞገሴ ንዴቱን ለመደበቅ እየታገለ፡፡
‹‹ግጥሙ…››
ሞገሴ አልራራለትም፡፡
‹‹ግጥሙ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ግጥምህ ሰምቶ በቦክስ ሊገጥምህ የሚመጣ ብዙ ሰው ሊኖር ስለሚችል-እኔ ምመክርህ የጸጋየን ግጥሞች እያነበብክ በጸጋ ብትኖር ነው፡፡አወይ መቃጠል በእውነቱ ለመናገር እኮ በዚች ልጅ የተነሳ ሀገራችን ተደፍራለች፡፡›› ሞገሴ በድራፍት ጥዋ ጠረጴዛውን ወቀረ፡፡
በሞገሴ አነጋገር መሰረት ኢትዮጵያ የምትገኘው ከምድር ወገብ በላይ ሳይሆን ከዛች ልጅ ወገብ በታች ነው፡፡
ሞገሴ ንግግሩን ከመቀጠሉ በፊት በላዩ ላይ የወደቀውን የጉም ቁራሽ የመሰለ ጋቢ አስተካከለ፡፡ድራፍት ቤቱ ሞቃት ነው ስለምን ሞገሴ ጋቢ ደረበ? ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ሞገሴ ጋቢ የሚለብሰው ጋቢ የኢትዮጵያዊነት ምልክት ነው ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡እንደ ሞገሴ ከሆነ ዝሆን በኩምቢው ኢትዮጵያዊ በጋቢው ይታወቃል፡፡ይህ ጋቢ የሞገሴ ሻኛ ይመስል ከሞገሴ ትክሻ ላይ ወርዶ አያውቅም፡፡ እንደሞገሴ ዜጎች ባህላቸውን ሚስቶች ባሎቻቸውን ቢያከብሩ ኑሮ የት በደረስን ነበር፡፡ሞገሴ የሀገሩን ወግ ለመጠበቅ ባለው ቁርጠኝነት መሰረት ድራፍት እንኳ የሚጠጣው ፈረንጅ በሰራው መጠጫ ሳይሆን አንጥረኛ በሰራው ዋንጫ ነው፡፡በዋንጫው ውሰጥ ያለው መጠጥ ኮማሪት የጠመቀችው ጠላ ሳይሆን ፈረንጅ የበረዘውን አተላ መሆኑ ግን ታስቦት አያውቅም፡፡
‹‹እንደው ለምን ብላ ግን ይሄን አጠያፊ ነገር ፈጸመች ?››
‹‹ምክንያቱ ከሁለት አይዘልም…››አለ ነገር ከላባ ማቅለል የሚሆንለት ይጋረድ፡፡‹‹ልጅቱ ከዛ አፍሪካዊ ጋር በግላጭ ለመገናኘት ያሰበችው በሁለት ምክንያት ነው፡፡የመጀመሪያው ከአፍሪካዊያን ጋር ያለንን ግንኙነት ከሀሳባዊ አንድነት ወደስጋዊ አንድነት ለማምጣት አስባ ነው የሚለው ነው፡፡ሁለተኛውን ግን እስካሁን ደረስ አላወኩትም፡፡››
‹‹አሳፍራናለች !››
‹‹አዎ አሳፍራናለች፡፡ሰማኒያ ሚሊየን ህዝብ የተፈጠረበትን ሚስጢር በአደባባይ አሳይታ ጉድ ሰርታናለች፡፡››
‹‹ትናንት መንገድ ላይ ያገኘሁት ጎብኝ… አለባበሴን አይቶ ብዙ ነገር ጠየቀኝ፡፡አጠያየቁ ባህል ሚኒስተር በአዋጅ ፈርሶ እኔ ባህል ሚኒስተር እንደሆንኩ አይነት ነው፡፡ኢትዮጵያዊያን የምታዘወትሩት ባህላዊ ምግብ አይነት ምንድነው አለኝ?የምናዘወትረው ባህላዊ ምግብ ጾም የተባለው ነው አልኩት፡፡የምታዘወትሩት ባህላዊ ሙዚቃ ምንድን ነው?አለኝ፡፡ምናዘወትረው ባህላዊ ሙዚቃ ልመደው ሆዴ የሚለው ነው አልኩት፡፡በስተመጨረሻ ስለባህላዊ እስፖርታችን ሲጠይቀኝ ተፋረሰን፡፡ተወዳጁ ባህላዊ ስፖርታችሁ ምንድነው አለኝ፡፡ትግል ነው አለኩት፡፡‹ትግል ማለት እንዲህ ቢግ ብራዘር አልጋ የምትታገሉት ነው ወይስ ሌላ አይነት ትግል አላችሁ አለኝ፡፡በጣም አናደደኝ፡፡በበሃላችን ላይ በመሳለቁ ምክንያት ከባህላዊ የመደብደቢያ መንገዱች መከካል አንዱን ልተገብርበት አስመርጠው ጀመር፡፡
‹‹በክርን ሰብቄ ልጣልህ ይሆን?
ወይስ በአይበሉባ ላዋልቅህ ይሆን ?
ወይስ በስካልቹ ላንሳህ ይሆን?››እያልኩ ብዙ ካሰብኩ በኃላ ይሄን የኢትዮጰያ ባህላዊ ልብስ ለብሸ ይሄን ባደርግ ኢትዮጵያ ትሰደባለች ብየ በመስጋት የህንዶችን ባህላዊ ልብስ እስክዋስ ድረስ ብየ ሳልነካው ላኩት፡፡ነገሩ አይፈረድበትም አለም ትንሽ ናሙና አይታ ብዙ ደምዳሚ ነች…በቢላደን ሰበብ ጺማም ሰው ትፈራለች፤በደብሊው ቡሽ ሰበብ የነዳጅ ጄሪካኗንን ሳይቀር ትደብቃለች..በዚያች ልጅ ሰበብ የplay boy ሀገር ኢትዮጵያ ሆናለች፡፡››
‹‹እኔ ግን የሃገሬውም የአንተም ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት በፍጹም አልተዋጠልኝም፡፡››አለ ይጋረድ የድራፍቱን አረፋ ከአፉ ላይ
በአይበሉባው እየጠረገ ፡፡
‹‹አንተ እንኳን ነገር እህል እራሱ መች ይዋጥልሃል…ውሃውን ያኑርልህ አንጂ..››
‹‹ይች ልጅ አውቃም ይሁን ሳታውቅ ይሄን ነገር አደረገች፡፡ሆኖም ግን ሃገራችን ኢትዮጰያ በዚች ልጅ ጭን ውሥጥ ትገኝ ይመስል በሷ ሰበብ ሃገራችን ተደፍራለች ማለት አግባብ አይደለም፡፡
በርግጥ ያደረገችው ነገር ውግዘት ሊያስፈልገው ይችል ይሆናል ፡፡ሃገሬውን ላየ ግን ጉዳዩ ከውግዘት አልፎ ውግረት ሊያመጣ እንደሚችል ያስጠረጥራል፡፡
ወጣት ናት የወጣት የቅርብ ጓደኛው ሰይጣን ነው፡፡አሁን እያደረግን ያለነው እሷን ከማሳቀቅ አልፎ ሰይጣንን እንዲያስፈነድቅ መሆን የለበትም፡፡
እንግዲህ ምን ይደረግ ፈርዶበታል፡፡ያደረገችው ነገር በርግጥ አሳፋሪ ነው አዎ አሳፋሪ ነው፡፡የቺቺንያ ሰዎች ፈጣሪ እያያቸው የሚያደርጉትን እሷ ካሜራ እያያት አድርገዋለችና አሳፋሪ ነው፡፡ከዚህ በተረፈ ግን ፍልጥ ይዘን አንጠብቃትም መቸም፡፡››
ይኸኔ ቀረሮ ጣልቃ ገባ፡፡
‹‹አሁን በተነጋገራችሁት ላይ አዲስ የነጠላ ዜማ ሃሳብ መጦልኛል፡፡››
ፈቃደኝነታችንን ሣይጠይቅ የቴወድሮስ አፍሮን ጃ ያስተሰርያል ዜማ ክፉኛ ተዳፍሮ ማቀንቀን ጀመረ፡፡
‹‹ግርማዊነታቸው ቢኖሩልን ኖሮ
ስቅላት ነበረ ቦሌ ላይ ዘንድሮ፡፡››
‹‹ዝጋ!››ሞገሴ አንባረቀ፡፡
‹‹ምነው ግጥሙን አልወደዳችሁትም?››
‹‹ሞት ይሻልሃል እኔ አንተን ብሆን ኑሮ ይሄን የመሰለ ግጥም ከመግጠም ይልቅ በርና መስኮት መግጠም እማር ነበር፡፡››
ቀረሮ ወደኛ ዞረ፤
‹‹አሪፍ አይደለም አንዴ?››አለን በማሪያም አሪፍ ነው በሉኝ በሚል ቅላጼ፡፡
‹‹አሪፍ ነው …አሪፍ ነው ፡፡ለሌላ ሙዚቀኛ ግን እንዳታሳየው የዘንድሮ ሙዚቀኛ የሰው ግጥም ባቻ ሳይሆን የሰው ገጠመኝም ይሰርቃል፡፡
ሞገሴ አምስተኛውን ድራፍት በዘመራ ጠላ ወግ እፍ አፍ ብሎ ከተጎነጨ በኃላ ወደ ቁጭቱ ተመለሰ፡፡
‹‹ቪዲዮውን ሳስተውለው ግን ልጂቱ ሰይጣን ያሳሳታት አትመስልም፡፡ምናልባት ሰይጣኑን አሰስታው እንደሆነ ለማጣራት እሞክራለሁ፡፡ቪዲዮው ምን ያህል በምራባዊያኑ ስውር ድንዛዜ ውስጥ መሆናችን አመላካች ነው፡፡
ይሄን ለማለት የቻልኩት ልጂቱ ስትንቀሳቀስ የነበረው እንደ ኢትዮጵያዊ አለመሆኑን ካስተዋልኩ በኃላ ነው፡፡ኢትዮጵያዊ ሴቶች አውልቂ አታውልቂ የሚገቡትን እሰጣ አገባ ታውቁታለችሁ…አንድን ኢትዮጵያዊ ሴት መቀነት ከማስፈታት አንድን ወታደር ትጥቅ ማስፈታት ይቀላል፡፡
የምረባዊያኑ ተጽእኖ ግን ነውርን ስልጡንነት ፤ ክልከላን መጣስ ዘመናዊነት እያስመሰለው ብዙ ነገራችንን አበላሽቶት ቁጭ አለ፡፡እነሱ ሁሉን ግልጽልጽ አድርገው የገቡበትን ጦስ እኛም እንድንቀላለቀለው እየሣቡን ነው፡፡ወትሮም ክፉ ወዳጅ ጠባዩ ይሄው ነው…አብረን እንጠውልግ አንጂ አብረን እንጽደቅ አያውቅም፡፡
ግርም ሚለኝ ግኝ ይጋረድን የመሰሉት ፈረንጆቹ ሲጎትቱን እነሱ ሲገፉን ማየቴ ነው፡፡በአደባባይ ሲታይ የሚያምርና በአደባባይ ሲታይ የሚያስመርር ነገር አለ፡፡ልጂቱ ይሄን የምታውቅ ይመስለኛል…ግን ምን ይደረጋል ባዕድ ስናይ ብዙ ነገራችን ይረሳናል፡፡ያደረግነው አንገታችንን የሚያስደፋን ሃገር ቤት ተመልሰን የሰው አይን ሲዳፋን ነውና እሷም ለማየት ያብቃት፡፡የልጂቱ ግን አርባ መገረፍ በቀረበት ዘመን በመፈጠሯ ፈጣሪን ታመሰግነው፡፡››
ይጋረድ ጥብቅናውን ቀጠለ፡፡
‹‹በልጂቱ መፍረድ ትክክል አይደለም ፡፡ሁላችንም የውስልትና ልጆች ነን፡፡ያች ልጅ ያደረገችው ከሽህ አመታት በፊት ማክዳና ሰለሞን ያደረጉትን ነው፡፡ለየት የሚያደርገው ንጉስ ሰለሞን ጠቢብ ሲሆን ቦልት ግን ጠርብ መሆኑ ነው፡፡››
‹‹እዚህ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አለኝ፡፡››ሞገሴ አመር ብሎ ተነሳ ፡፡
‹‹አኔም እዚህ ላይ አዲስ ነጠላ ዜማ አለኝ፡፡››ቀረሮ በቆረጣ ገባ፡፡
ሁላችንም ጮህንበት ፤
‹‹ዝጋ…››
ሞገሴ የኢትዮጵያዊያንን ታሪክ ይጋረድ የኢትዮጵያዊያንን ግምጃ እየገለጠ ክርክሩ ቀጠለ፡፡ከብዙ ድራፍት ከብዙ ክርክር ጋር…እየመረረችን እየጣመችን እየረገምናት እያዘንልላት ያችን ልጅ ጠጣናት፡፡

No comments:

Post a Comment