መሐመድ
ሐሰን

በቀደሙት ግዚያት የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን
ስናስብ በርካታ ጠንካራ ጐኖቻቸው ወደ እዝነ ህሊናችን ይመጣሉ፡፡ በተለይ ከንባብ እና የሙግት ባህላቸው ጋር በተያያዘ፣ ከወቅት
እማኞች የምንሰማው እውነታ አስገራሚ ሊባል የሚችል ነው፡፡ በየጥጋጥጉ፣ በየመማሪያ ክፍሉ፣ ወዘተ የሚደረገው ውይይት መነሻው መፅሐፍ
ሲሆን፣ ታላላቅ ፀሐፊዎችም እንደጉድ ይጠቃቀሳሉ:
ውጤቱ ላይ ሰፊ ክርክሮች የሚስተጋቡ ቢሆንም እነዚህ የቀደሙት የዩኒቨርሲቲ
ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ይበጃል ባሉት ሀሳብ ላይ ተሳትፈዋል፤ ተሟግተዋል፣ ታግለዋል፡፡ የሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ
ጉዳይ ያገባናል ይመለከተናል በሚል ያመኑበትን ሀሳብ አቀንቅነዋል፡፡
ብዙም ወደኋላ ርቀን ሳንሄድ የታላላቆቻችንን
የቅርብ ግዜ ትዝታዎችን ለማስታወስ ብንሞክር እንኳን ብዙ እውነታዎች ይገለጡልናል፡፡ የርዕስ ጉዳያቸው ማጠንጠኛ ሀገራዊ ፖለቲካ፣
ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ሲሆኑ ምክንያቶቻቸውም ልፍስፍስ የሚባሉ አልነበሩም፡፡
ዛሬስ
?
ዛሬ ዛሬ በዩኒቨርስቲዎቻችን ውስጥ ያለው ሁኔታ
ከቀደሙት ግዚያት የተለየና ሌላ አሳፋሪ መልክ እየያዘ ከመጣ ሰንበትበት አለ፡፡ ለሚነሱት ግጭቶች መንስኤው ብሔር ነው፡፡ በብዛት
ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በአካዳሚያዊ ነፃነቶች ላይ ተሟግቶና ተከራክሮ በሀሳብ ፍጭቶች ከመተማመን ይልቅ፣ ብሔሬ ተነካ በሚል ሰበብ ብቻ
መበጣበጥ፣ የዚህ ዘመን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሳፋሪው መገለጫ ሆኗል፡፡ ከዚህ ውጪ በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ግጭቶች ከተነሱ
መነሻቸው “ወጥ ቀጠነ፣ እንጀራው ሳሳ፣ ዳቦው ጠቆረ፣ ወዘተ” የሚሉ ሆድ ተኮር ተልካሻ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችንም
ሀገራዊ ጉዳይ ግድ የማይሠጣቸው “ምሁራንን?” ማምረታቸውን አጠንከረው የቀጠሉበት ይመስላሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ተመራቂዎች ነገ በከፍተኛ
የሀላፊነት ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ሀገራዊ ቀውስ ማሰቡ ብዙም ከባድ አይሆንም፡፡
በዚህ ዘመን በዩኒቨርሲዎቻችን ውስጥ ለሚስተዋሉ
ዝቅጠቶች የትምህርት ፖሊሲው እና ፅንፈኝነት እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የሚሰጠው ትምህርት በጥናትና ምርምር
ላይ ያልተመሰረተ መሆኑ፣ ለተማሪው የሚሰጠው ድጋፍ እና የተማሪዎቹ ውጤት ዝቅተኝነት፣ የትምህርት ጥራቱን የሚያረጋግጥ ተቋም አለመኖር፡
የአስተማሪዎቹ ብቃት ማነስ እና ሌሎችም ተያያዥ ነጥቦች ለዩኒቨርሲቲዎቻችን ውድቀት እንደማሳያነት የሚቀርቡ ናቸው፡፡
አንድ የትምህርት ተቋም በተማሪዎቹ መካከል
የሀገራዊ ማንነትን ስሜት፣ ባህላዊ መከባበርን፣ መረዳዳትን፣… መፍጠር እንዳለበት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ የኛ ሀገር የትምህርት
ስርዓት ግን ከዚህ በተቃራኒ፣ በተማሪዎች መካከል መራራቅን፣ መጠላላትን፣ ስጋትን እና ጥርጣሬን በተማሪዎች መካከል እያነገሰ እንደሆነ
ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በየትምህርት ተቋማቱ ያሉ የአስተዳደር አካላትም ጉዳዩን ችላ በማለት ተማሪው ሲደናቀፍ ከጥግ ቆመው መታዘብን
የመረጡ ይመስላሉ፡፡
ሰሞነኛ
ምርቃቶች
ይህ ወቅት ከምርቃት ፕሮግራሞችጋር በተያያዘ
ዩኒቨርሲቲዎችና ተመራቂ ተማሪዎቻቸው ሽር ጉድ የሚሉበት ነው፡፡ አንዳንዶችም ማስመረቅ ጀምረዋል፡፡ ሆኖም ግን በተማሪዎቹ ላይ በርከት
ያሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡ እውን እነዚህ ተማሪዎች ብቁ ሆነው ነው የሚወጡት? የእውቀታቸው ልክስ እስከየት ይደርሳል?
የስራ ዋስትናቸው ምን ይመስላል? በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ ሳሉ ምን ሰሩ? ምንስ ይሰሩ ነበር? መሰረታዊ ፍላጐታቸውስ ምንድነው?
ወዘተ የሚሉ ማቆሚያ የሌላቸው ጥያቄዎች በዘመኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የሚነሱ ናቸው፡፡ ለትምህርታቸው ተጨማሪ አስረጅ የሚሆኗቸውን
መጽሀፍትን እና ከትምህርት ውጪ ያሉትን የህትመት ውጤቶች ለማንበብ ያላቸው ተነሳሽነትም ትልቅ ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡
የማይስማሙ
ተማሪዎች
ተማሪው በግቢ ውስጥ ተስማምቶ ለመኖር በወንዛዊነት፣
በፓርቲ አባልነት፣ በሀይማኖት፣ ዝቅ ሲልም በዲፓርትመንት (ትምህርት ክፍል)፣ መቧደኑ ግድ እየሆነ ለመምጣቱ በርካታ ማሳያዎችን
ማንሳት ይቻላል፡፡ ተማሪውን አንድ የሚያደርገው ጉዳይ ማግኘት የሰማይ ያህል ርቋል፡፡ የ “ቶም እና ጄሪ” ባህሪ መገለጫቸው የሆነው
ተማሪዎቹ፣ በአንድ ትምህርት ክፍል ውስጥ ሁለት ቲሸርት፣ መፅሔት፣ ጉዞ፣… ማዘጋጃ እየተለመደ መጥቷል፡፡ የአዲስ አበባና የክፍል
ሀገር ልጆች በመባባል መቧደንም የዚህ ዘመን እጩ “ምሁራን” መገለጫ ነው፡፡
የፓርቲ
“አባልነት” የስራ ዋስትና
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት ስድስት ኪሎ ካምፓስ
ውስጥ ከሚገኘው ባህል ማዕከል በርከት ያሉ ተማሪዎች በመውጣት ላይ ናቸው፡፡ “ላንተ ምን ተሰጠህ? ላንቺ ምን ተሰጠሸ?” በሚል
አፍ ለአፍ ገጥመው ሁሉም ይንሾካሾካሉ፡፡ ተማሪዎቹ በጉጉት እየተጠያየቁ ያሉት በፓቲያቸው ውስጥ ስለሚሰጣቸው “ኤ” እና “ቢ” እንዲሁም
አፈንጋጭ የተባሉት አባላት ስለሚያገኙት “ሲ” ነው፡፡ መምህሮቻቸው ከሚሰጧቸው “ኤፍ” ይልቅ፣ ከፓርቲያቸው በአባልነት የሚሰጣቸው
“ሲ” ህይወታቸውን እንደሚያጨልመው ይሰማቸዋል፡፡ በአሁን ሰዓት የፓርቲ አባልነት፣ የስራ ዋስትና የመሆን ተስፋው ተሟጦ ስለማለቁ
የሚናገሩት አባላቱ እራሳቸው ናቸው፡፡ እውነት ኢህአዴግ ለአባላቱ በሙሉ ስራ ይሰጣል? መስጠትስ ይችላል? ይህንን ሁሉ አባል የማስተናገድ
አቅሙስ ምን ያህል ነው? የአባላቱ መብዛትስ የስራ ዋስትና የመስጠት አቅሙን አልተገዳደረው ይሆን? . . ከብዙዎች የሚነሳ ጥያቄ
ነው፡፡ ብዙዎችም ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ፡፡
በግቢ (ዩኒቨርሲቲ) ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ
ከተራ አባልነት እስከ ሀላፊነት ኢህአዴግን ሲያገለግሉ የነበሩ ሰዎች በስራ ማጣት ሲንገላቱና በመጨረሻም ከተመረቁበት የትምህርት
መስክ ውጪ፡ እንደ አስተማሪነት ባሉ ስራዎች ላይ ሲሰማሩ እያየን ነው፡፡ ይህም አባልነት የስራ ዋስትና መሆኑ እያከተመ ለመምጣቱ
ጥሩ ማሳያ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ሳያምኑበት ለስራ በሚል ብቻ ህሊናቸውን ሸጠው አባል እንደሆኑ ይነገራሉ፡፡ ያም
ሆኖ ግን ስራውን ማግኘት አልተቻላቸውም፡፡ ማን ነበር “ጮማ እየበላሁ ማሰብ ከማቆም ቆሎ እየቆረጠምኩ ባስብ ይሻለኛል፡፡” ያለው?
ምን
ተይዞ ጉዞ?
ከሱፉ እና ከጋዋኑ ስር ያለው የተማሪዎቹ ማንነት
ግልፅ አይደለም፡፡ ነገር ግን ወደፊት የሚጠበቅባቸውን ህይወት እና የሚያገለግሉትን ማህበረሰብ ስናስብ ብዙ ነገር እንድንጠይቅ እና
እፍረት እንዲሰማን እንሆናለን፡፡ በቅጡ እውቀት ሳይጨብጡ የሚመረቁ ተማሪዎች ማህበረሰቡ ውስጥ ገብተው ሊያገለግሉና ሊያስተምሩ?
ወይስ በድጋሚ ለሀገር ሸክም በመሆን ማህበረሰቡ ሊያገለግላቸውና ሊያስተምራቸው?
በ2001 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት
ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪዎች በቲሸርታቸው ላይ “Never stop Asking” የሚል ፅሁፍ አስፍረው እንደነበረ አስታውሳለሁኝ፡፡
ነገር ግን የለበሱትን ተማሪዎች ጨምሮ፡ የአሁን ግዜ ተመራቂዎች (በተለይ በጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ውስጥ ያሉት) በድፍረት ጥያቄዎችን
ስለማንሳታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ስለማንበባቸው እና ስራቸውን በአግባቡ ለመወጣት ስለመፃፋቸው አፍን ሞልቶ መናገሩ ይከብዳል፡፡
በአንድ ወቅት ለሀገራዊ ጉዳች ሀገራዊ ምሳሌዎችና
ተረቶች ከማይነጥፉበት ምሁር ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋር ስንጨዋወት ያካፈለኝን ወግ እዚህች ጋር ብጠቅሰው ተገቢ መስሎ ይሰማኛል፡፡
ሰውዬ አሁን ስማቸውን በውል የማላስታውሳቸው የአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግስት ባለስልጣናት ናቸው፡፡ እናም እኚህ ባለስልጣን ከግራዝማቾችና
ቀኝ አዝማቾች ጋር በመጋጨታቸው፣ ነጋዴውን ሁሉ እያሰጠሩ የቀኝ አዝማችነት እና የግራአዝማችነት ማዕረግን በማደል ሀገሩን በሙሉ
አጥለቀለቁት፡፡ ከዛ በኋላ ማዕረጉ ረከሰ፡፡ አሁንም ኢህአዴግ ይህንኑ ስልት በመከተል ሀገሪቱን በሙሉ በድግሪ ምሩቃን፣ በዶክተሮች
እና በፕሮፌሰሮች በማጥለቅለቅ ት/ትን ዋጋ ማሳጣት የፈለገ ይመስላል፡፡ ይህ አካሄድ የስርዓቴ ተቃዋሚ ናቸው የሚላቸው ምሁራንን
ለማጥቂያነት ቢያውለውም፣ ውጤቱ ግን ለሀገራዊ ውድቀት እንደሚዳርገን ከፍንጭ በላይ የሆኑ እውነታዎችን ማየት ከጀመረን ሰነበተ፡፡
ለሁላችንም ስለ ሀገር የማሰብ ልቦናውን እንዲሰጠን መመኘቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለማንኛውም ወጉ እንዳይቀርብኝ ለተመራቂዎች እንኳን
ደስ ያላችሁ ብያለው፡፡
No comments:
Post a Comment