በመሐመድ
ሐሰን
(ኢትዮ-ምህዳር
ላይ የወጣ)
እለተ ሐሙስ ጥቅምት ሰባት ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው የኢትዮጵያ ፓርላማ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ
አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ አንደኛው እኔን በጣም ነበር ያስገረመኝ፤ አንድ እናት የመሰሉና ስጋቸው ሞላ ያለ
ሴትዮ የመጠየቅ እድሉ ሲሰጣቸው የተለመደውን ውዳሴ ካቀረቡ ቦሃላ ‹‹ነጻውን›› ፕሬስ የሚኮንነውን ንግግራቸውን አዥጎደጎዱት፤ በማጠቃለያቸው
ላይም ‹‹አንዳንድ አላስፈላጊ አሉባልታ በሚነዙ ነጻ ፕሬሶች ላይ ከህገ ወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ምን ታስቧል?›› ዓይነት ጥያቄ
ሰነዘሩ፡፡ ይህ ጥያቄ በዘንድሮው ፓርላማ ውስጥ ስለመሰንዘሩ አብዝቼ ተጠራጠርኩ፤ ምናልባት እንዲህ ያለው ጥያቄ ከ97 ምርጫ ቀደም
ብሎ በነበረው ፓርላማ ውስጥ ተነስቶ ቢሆን ኖሮ ለተጨማሪ ውይይት ሊጋብዘን ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ ላይ ነጻ ፕሬስ
የሚባለው ነገር ክፉኛ ተደቁሶ ወደ ግብዓተ መሬቱ ባመራበት፣ አፍን ሞልቶ ‹‹አለ›› ማለት በማይቻልበት፣ መሰናክሎች እንደ አሸን
በሚፈለፈሉበት፣ ወዘተርፈ እንዴት ጣት ይጠቆማል? በሌለ ነገር ላይ እንዲህ ያለውን መርዛማ አስተያየት እና ጥያቄ መሰንዘርስ በራሳቸው
ዘንድ እንኳን ግምት ውስጥ አይከታቸው ይሆን? የፓርቲያቸው እምነት ከሆነስ ዓላማው ምንድን ነው? ምንስ ይነግረናል? በሞተ አካል
ላይ ዱላን ማመቻቸት በእናት ላይም ሆነ በማንኛውም የሰው ፍጡር ላይ የሚፈጥረው ስሜት ምን ይሆን? ነጻ ፕሬስ የሚለው ሀሳብ እውነት
ገብቷቸው ይሆን? ገብቷቸው ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነጻነት ሊያሳዩን ይችላሉ? ምናለ እግረ መንገዳቸውን የነጻ ፕሬሶችን
ዝርዝር ቢያስታውሱን?...?...
ከእኚህ የፓርላማ ተወካይ ንግግር ቦሃላ ደግሞ ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 11ቀን 2006 ዓ.ም የ‹‹ኢትዮ-ምህዳር››
ጋዜጣ አዘጋጆች እና ባለቤቶች የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባቀረበባቸው ክስ የተነሳ ሐዋሳ ድረስ በመሄድ ሊጉላሉና ስራቸው ሊስተጓጎል ችሏል፤
ጉዳዩ አሁንም ለዛሬ በተሰጠ ተለዋጭ ቀጠሮ ምክንያት መፍትሄ አላገኘም፤ ዳግም
ወደ ሐዋሳ በመጓዝ ተጨማሪ የስቃይ ጽዋን ለመጎንጨት ተገደዋል፡፡ በቀደመው ግዜም የ‹‹ሪፖርተር›› ጋዜጣ ስራ አስኪያጅ አማረ አረጋዊ
ጎንደር ድረስ ተወስዶ በመታሰሩ ተመሳሳይ እንግልት የደረሰበት ሲሆን፣ የዚሁ ጋዜጣ ሌላኛው ባልደረባ ጋዜጠኛ መላኩ ደምሴም ባለፈው
ወር ከአዲስ አበባ ወደ ሐዋሳ በመወሰድ ለእስር ተዳርጎ ነበር፡፡ ጋዜጦቹ ምንም ዓይነት አቋም ይኑራቸው፣ እንዲህ ያለው አካሄድ
ግን እጅግ በጣም አደገኛና ‹‹በሌለው?›› ነጻ ፕሬስ ላይ የሚወሰድ ሌላኛው አስገራሚ ነጥብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ዘመቻው እተካሄደ ያለው በየትኛው ነጻ ፕሬስ ላይ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፣ የጥቃቱ ዓይነት
እና አካሄድ ግን ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ማስተባበያውን እንዲወጣለት ፈልጎ ላከ፤ ማስተባበያ ያለውም ጽሁፍ
ወጣለት፤ ታዲያ መክሰስ ለምን አስፈለገ? በፌዴራል ደረጃ ፍቃድ አውጥቶ የሚንቀሳቀስን ድርጅት ሐዋሳ ድረስ በመውሰድ ማንከራተት
እና ስራ ማስፈታትስ ምን ያህል ተገቢ ነው?... ይሄም ብቻ አይደለም፤ ዋናው ነጥብ ከጠየቁት የሞራል ካሳ 300.000 ብር በተጨማሪ፣
ከሳሽ ሆኖ የቀረበው አካል ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ የጋዜጣው ፈቃድ እንዲታገድ አልያም እንዲሰረዝ የሚጠይቅ ነው፡፡
እንግዲህ እዚህች ጋር ሰፋ አድርጎ ማየት እና መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
ከህትመት እና ወረቀት ዋጋ እንዲሁም ከማተሚያ ቤት ጋር የተያያዘው ችግር እያፈጠጠ የመጣ ሌላኛው
ችግር ሲሆን፣ ማንበብን በግልጽ የመቃወም ያህል አደገኛ እርምጃዎች ናቸው፡፡ …እነ ‹‹አዲስ ዘመን›› በገጽ ሶስት ላይ የተያያዙት
እርምጃ፣ እስከአሁንም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዞ የሚመላለሱ ጋዜጠኞች ጉዳይ፣ በቅርቡ ከነጻው ፕሬስ ጋር በተያያዘ ሌላ አዋጅ
ይወጣል የሚል ጭምጭምታ መሰማቱ፣…ስለ ነጻው ፕሬስ ጣር አብዝተን እንድንጨነቅ የሚጋብዙ ናቸው፡፡ አሁንም ደግሜ መጠየቅ የምፈልገው
"በሌለ" ነገር ላይ ይህ ሁሉ ሽረባ ለምን አስፈለገ? የሚል ነው፡፡
ለዚህ ብዙዎች አንድ ፈጣን መልስ አላቸው፤ ይኽውም ምንድነው- ስርዓቱ የፕሬስን ሐይል ጠንቅቆ
ስለሚያውቀው ዘወትር ነጻውን ፕሬስ በጥንቃቄ ከማየት ባለፈ ፍራቻም ጭምር አለባቸው የሚል ነው፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ
ለደረሰበት ሽንፈት ዋነኛው የተቃዋሚው ሐይል አድርጎ የሚቆጥራቸው በወቅቱ የነበሩ ነጻ የህትመት ውጤቶችን ነው፤ ስለዚህ አሁንም
ለቀጣዩ ምርጫ 2007 ቀደም ብለው ለመጠንቀቅ በመፈለጋቸው ሜዳውን እንደቆሙበት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ሳይፈልጉ አልቀረም፡፡ ሆኖም
ግን በዚህ አማራጭ በበዛበት ዘመን፣ ስሌቱ ብዙ ርቀት ሊያስጉዝ የሚችል አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ከነሱ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ሌሎች
አማራጮች አሉና፡፡
የኢትዮጵያ
ፕሬስ አዘቅት!
በኢትዮጵያ የኢህአዴግ መንግስት መግባትን ተከትሎ እስከ ምርጫ 97 ድረስ የነበረው የነጻው
ፕሬስ እንቅስቃሴ ጥሩ ሊባል የሚችል ነበር፡፡ በወቅቱም በርካታ የህትመት ውጤት አማራጮች የነበሩ በአንጻራዊነት የተሸለ የሚባል
አንባቢ የነበረበት ጊዜም ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በዚህ በነጻነት ጊዜ የነበረው የአንባቢ ቁጥርም ቢሆን ደረት የሚያስነፋ አልነበረም፡፡
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1998 UIS (Unesco Institute of Statistics) ባወጣው መረጃ መሰረት ከ1000 ሰው ውስጥ
0.375 የሚሆነው ሲሆን የሚያነበው፣ በኬንያ ግን በተቀራራቢ ዓመት በ1999 ከ1000 ሰው 8.33 የሆነው ያነብ ነበር፡፡
97 ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የአንባቢ (የህትመት) ቁጥር የተመዘገበበት ሲሆን፣ የምርጫውን
ውጤት ተከትሎ ሁሉም ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ አብዛኞቹ ጋዜጦች ከህትመት ውጪ ሆነዋል፡፡ ከዛ ቦሃላ ወደ 2008 ዓ.ም ላይ ከ64
የማያንሱ ጋዜጦች ይታተሙ እንደነበር መረጃዎች ሲያሳዩ፣ በወቅቱ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበራት እና በኢትዮጵያ ፕሬስ ውስጥ ጉልህ
አሻራዋን ያሳረፈችው ‹‹አዲስ ነገር›› ሳምንታዊ ህትመቷ ወደ 30.000 ኮፒ ገብቶ ነበር፡፡
‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ ከተዘጋች እና ከተሰደደች ከዓመታት ቦሃላም ቢሆን፣ ቀደም ብሎ ከላይ
በተጠቀሱት እና ሌሎች ምክንያቶች የህትመት ፈቃድ ማግኘት እየከበደ ከመምጣቱ ባለፈ ‹‹አሉ›› የሚባሉት ፕሬሶች የስርጭት መጠንም
በጣም አስደንጋጭ የሚባልበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ በእርግጥ በቅርቡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህመም እና ህልፈት ጋር
በተያያዘ፣ ከህትመት ውጪ የሆኑትን ጋዜጦች ጨምሮ አሁንም በህትመት ላይ ያሉት የግል ፕሬሶች የህትመት ቁጥራቸው በግዚያዊነት ከፍ
ብሎ ነበር፡፡
በመስከረም ወር 2006ዓ.ም የወጣው የብሮድካስት ባለስልጣን መረጃ እንደሚያሳየው፣ በአሁን
ሰዓት በሀገሪቱ ላይ ‘ስፖርትን፣ ፖለቲካን፣ ጤናን፣ ስነ-ልቦናን፣ መዝናኛን፣ ቢዝነስን፣… ጨምሮ በሁሉም ቋንቋዎች በመታተም ስርጭት
ላይ ያሉት ጋዜጦች ቁጥር 16 ሲሆን፣ መጽሄቶች ደግሞ 27 ናቸው፡፡ ከሪፖርተር ውጪ ሁሉም ጋዜጦች ሳምንታዊ ሲሆኑ፣ መጽሔቶቹም
አብዛኞቹ ወርሀዊ እና በየ15 ቀኑ የሚወጡ ናቸው፤ በሳምንታዊነት ደግሞ የ‹‹አዲስ ጉዳይ››ን መንገድ በመከተል 4 መጽሔቶች (ሎሚ፣ፋክት፣አዲስ ጉዳይ እና ሰፋ) ለህትመት ይበቃሉ፡፡
የስርጭት መጠናቸውን በምናይበት ጊዜም በጋዜጦቹ በኩል ከፍተኛ የሚባለው ሳምንታዊ ህትመት "ሪፖርተር"
(የእሁዱ) ሲሆን፣ አማካይ ቁጥሩ 10.720 ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚባሉት ሳምንታዊ ህትመታቸው በአማካይ
ከአምስት ሺህ እስከ ስምንት ሺህ የሚደርሱት ናቸው፤ በቅርቡ ገበያውን የተቀላቀለችው ‹‹ኢትዮ-ምዳር››ም ምድቧ እዚህ ከሁለተኛው
ጎራ ውስጥ ነው፤ ሳምንታዊ ህትመቷ በአማካይ ከ 5000 በላይ ነው፡፡… ዝቅተኛ የሚባለውን ቁጥር ስንመለከት ደግሞ "ፕሬስ
ዳይጀስት" 185፣ "ቢዝነስ ታይምስ" 1000፣ "ሜዲካል" 1633፣ "ሊግ ስፖርት"
1750፣ "ሰንደቅ" 1833፣ "ኢትዮ ቻናል" 2000፣… ሳምንታዊ የስርጭት መጠናቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ
የ16ቱም ጋዜጦች ሳምንታዊ የስርጭት መጠን በአማካይ 80446 እንደሆነ በመረጃው ላይ ሰፍሯል፡፡
የመጽሔቶቹን ስርጭት በምንመለከትበት ጊዜም ከጋዜጦቹ በብዙ የራቀ አይደለም፤ ከፍተኛ ወርሀዊ
የስርጭት መጠን አላቸው የሚባሉት ሶስቱ (ሎሚ፣ አዲስ ጉዳይ እና ፋክት) ሳምንታዊ መጽሄቶች ሲሆኑ፣ እንደ ቅደም ተከተላቸው በአማካይ
65.000፣59.000፣55.975 ወርሀዊ የስርጭት መጠን አላቸው፤
ይህ ማለት ከፍተኛ የሚባለው የአንድ መጽሄት ሳምንታዊ የስርጭት መጠን 17.000 እንኳን አይሞላም ማለት ነው፡፡ ይህ
ቁጥር እንኳን በራሱ ቋሚነት ያለው ሳይሆን በየጊዜው የሚዋዥቅ ነው፡፡… እንግዲህ እንዲህ "ባለው?" ፕሬስ ላይ
ነው ተመጣጣኝ ያልሆነ ቡጢ እተሰነዘረ ያለው፡፡
ጎረቤት
ኬንያን እንደማሳያ
የኢትዮጵያ ነጻው ፕሬስ ‹‹የለም›› የሚባልበት ደረጃ ላይ እንደሆነ ለማሳየት ብዙ ርቀት ሳንጓዝ
ጎረቤት ሀገር ኬንያን መመልከቱ ጥሩ ማሳያ ይሆነናል፤ ማሳያዎቹ ምናልባትም የማንበብ ልምዳችንን፣ የፕሬስ እድገቱን፣ የአሰራራችንን
ልዩነት፣ የፕሬሶቻችንን አቅም፣… የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1952 አካባቢ ወደ 50 የሚጠጉ ነጻነትን ሰባኪ ጋዜጦች እንደነበሯት
የሚነገርላት ኬንያ፣ ዛሬም የቀደምት ጋዜጦቿ ዱካ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም፡፡… ዛሬ ላይ ከ100 በላይ እለታዊ እና ሳምንታዊ ጋዘየጦች፣
እንዲሁም ወርሃዊ እና ሳምንታዊ መጽሄቶች ያሏት ኬንያ፣ በየእለቱ የሚታተሙ አራት ሀገር አቀፍ
ጋዜጦች አሏት፡፡ የእነዚህ አራት እለታዊ ጋዜጦች የአንድ ቀን ስርጭት ከ400.000 በላይ ነው፡፡ የኛን 16 ጋዜጦች
(80446) ሳምንታዊ እና 27 መጽሄቶች ወርሃዊ ስርጭት
(273.500) አንድ ላይ ቢደመር እንኳን የኬንያን 4 ጋዜጦች የአንድ ቀን ስርጭት አያክልም፡፡ የኛ አጠቃላይ ድምር 353946
ነው፡፡
ከጠቅላላው የጋዜጦች ስርጭት ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚጋሩት "ዴይሊ ኔሽን"
እና "ዘ ‘ስታንዳርድ" የተባሉት ሁለቱ የኬንያ ጋዜጦች ሲሆኑ፣ ብዙ የሚወራለት ታሪክ ያካበቱ የሚዲ ተቋማት ናቸው፡፡
በ1958 የተመሰረተው የአሁኑ የኬንያ ዝነኛ ጋዜጣ "ዴይሊ ኔሽን"፣ ብቻውን በቀን ከ205.000 በላይ ኮፒ ያሳትማል፡፡
ይህ ማለት፣ "ዴይሊ ኔሽን" በአንድ ቀን ብቻ የሚያሳትመው የጋዜጣ ቁጥር፣ በሀገራችን ውስጥ በአንድ ወር ከሚታተሙ
የ16 ጋዜጦች ድምር ቁጥር የበለጠ ነው ማለት ነው፡፡
በናይሮቢ በባለ 17 ፎቁ ነጩ መንትያ ህንጻው ላይ የሚገኘው የ"ዴይሊ ኔሽን"
(nation media group) ዋና ቢሮ እህት ጋዜጣው "ሰንደይ ኔሽን"ን፣NTV ቴሌቪዥንን፣ የሬድዮ ጣቢያ፣
Easy FMን፣…ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሚዲያዎችን በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ በባለቤትነት ያስተዳድራል፡፡ በድረገጽ በኩል ያለው
እንቅስቃሴም ከኛ ጋር ስናነጻጽረው አስገራሚ የሚባል ሲሆን፣ ድረገጻቸውን በቀን ከሶስት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ይጎበኙታል፡፡ እነ
"ዴይሊ ኔሽን" በቁጥር የበዛ ሚዲያ ባለቤት የመሆናቸውን እውነታ ከኛው ሀገር አሳሪ ህግ ጋር በፍጹም የሚነጻጸር
አይደለም፤ በኛ ሀገር የአንድ ሚዲያ ፈቃድ ማግኘት በመርፌ ቀዳዳ የመሹለክ ያህል የከበደ ከመሆኑም ባለፈ፣ ከአንድ በላይ ፕሬስ
(ሚዲያ) ባለቤት መሆን በህግ (አዋጅ) ጭምር የተወገዘ ነው፡፡
ጠንካራ አቅም ያለውን እና ለረዥም ጊዜ የቆየ ሚዲያም ቢሆን አለን ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፤
በኢትዮጵያ ውስጥ 20 ዓመት እንኳን ያስቆጠረ ነጻ ፕሬስ የለንም፡፡… በኬንያ ከ"ዴይሊ ኔሽን" በመቀጠል በቀን
በ54.000 ኮፒ ገበያውን በሁለተኛ ደረጃ የሚከተለው እና ወደ 30 ከመቶ የሚሆነውን የገበያ ድርሻ የሚይዘው "ዘ ስታንዳርድ"
(The Standard) ጋዜጣ እ.አ.አ በ1902 ዓ.ም ነው የተቋቋመው፤ ከመቶ ዓመት በላይ መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ እንደ
"ዴይሊ ኔሽን" ሁሉ "ዘ ስታንዳርድ"ም የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን፣ እንዲሁም በርካታ የህትመት
ውጤቶችን በበላይነት ያስተዳድራል፡፡ ታዲያ ይህ ጋዜጣ (The standard Group) በተለያየ ጊዜ ለተለያዩ ሰዎች የባለቤትነት
ድርሻው ሲሸጋገር ነው ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው፡፡
ከጎረቤታችን ኬንያ የግል ፕሬሶች እውነታ ላይ ተቀንጭቦ በቁንጽል የቀረበው ነጥብ የኛን ቦታ
በደንብ አድርገው የሚጠቁሙ እና ልዩነቶቹም የሚያሸማቅቁ (የሚሸማቀቅ ካለ) አይነት ናቸው፡፡ …ያለ ፕሬስ የሚደረገው ሐገራዊ ጉዞ
መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ሐላፊነት ያለባቸው አካላት ቢያስቡበት መልካም ነው፡፡ ጎረቤታችንን ዞር ብሎ መቃኘቱም የማንነታችንን
ልክ በደንብ ይነግረናል፤ ጎረቤቶቻችንን ብቻ ሳይሆን የራሳችንን ትላንት ብንመለከትም ዛሬ ያለንበት ደረጃ ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ
ይገለጽልናል፡፡ ሐገራችን የኋልዮሽ ከተያያዘቻቸው ጎዳናዎች አንዱ እና ዋነኛው ይህ የፕሬስ ጉዳይ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር
ይቻላል፡፡ የስርዐቱ ዘዋሪዎች ግን አሁንም ነጻነትን እንዳጎናጸፉን እና በዴሞክራሲ ጠበል እየተጠመቅን እንደሆነ ሌት ከቀን ይሰብኩናል፡፡
መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን የሚሉትን አያሳይም፡፡… ለማንኛውም ቀጣዩ የሰለሞን ሞገስ ግጥም ያሰነባብተን፡-
ውረዱ
ከመስቀሉ ላይ!
እስቲ ትንሽ ፋታ ስጡን፣
ምን ሁኑ ነው የምትሉን?
እስቲ ትንሽ ገለል በሉ-
ኧረ ሂዱልን ወ‘ደዛ!
"ለእናንተ ስል በመስቀል ላይ
ተሰቀልኩ" የሚለን በዛ
ለማንም! አዎ ለማንም!
እኛኮ ለእኛ ብላችሁ ተሰቀሉልን አላልንም !!
እኛው እንሸከማለን-
የእኛኑ መከራ ስቃይ
የት ነው የተሰቀላችሁ?
ውረዱ ከመስቀሉ ላይ!!
ማናችሁ? ማን ነን አላችሁ?
ስንተኛ "ክርስቶስ" ናችሁ?
(ተጻፈ፡-2000ዓ.ም - ምንጭ ፡-"እውነትን
ስቀሏት")
No comments:
Post a Comment