በ መሀመድ
ሀሰን
በርዕሴ ላይ የደነቀርኩትን ‹‹ምርጫ›› የሚለውን ቃል ስታዩ ‹‹ምንድነው ደግሞ እኚህ የዘመኑ
ጸሀፊዎች ምርጫ በሌለበት ምርጫ ምርጫ እያሉ የሚያደነቁሩን?! ደግሞስ ለዚህ ለዚህ የብቸኛውና የዝነኛው ቴሌቪዥንና የመሰሎቹ የቁራ
ጩሕት አይበቃንም? የት ብንሄድ ነው ይህን ቃል የማንሰማው? አረ ተቃጠልን ተውን!ኡኡ..!!››የምትሉ ጥቂቶች እንዳይደላችሁ እገምታለው፤አስተውላለሁ፡፡
የኔም ስሜት ከናንተው ቢብስ እንጂ አያንስም፡፡ ምርጫው ምን አይነት ምርጫ ነበር? ምርጫ ለመባልስ ይበቃል ወይ? …የሚሉትን ጥያቄዎች
ለግዜው እንተዋቸውና፡ብቻ የሆነ ‹‹ምርጫ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የራስ በራስ ውድድር በዚህ ወቅት በሀገራችን ላይ ተካሂዷል በሚለው
እንግባባ፡፡ይህንን መካድ አይቻልምና፡፡ ባይሆን ምርጫ የሚለውን ቃል በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ እናስቀምጠው፡፡ለምርጫ ቦርድ ሰዎችና
ለባለስልጣናቱ አፍ የቀለሉትን ፍትሀዊ፡ ነጻ፡ ገለልተኛ፡ ዴሞክራሲያዊ፡ ምናምን የሚሉትን የቃላት ጨዋታ እንተዋቸውና፡
‹‹ምርጫው;;›› የተወልንን ትዝብቶች አንድ ሁለትእያልን እንጨዋወታቸው፡፡ ትዝብቶቼ ሙሉ በሙሉ በምስቅ የሀገሪቱ ክፍል ባለኝ ቆይታ
የታዘብኳቸው ናቸው፡፡
ድንኳኑ
የምርጫ የሚመቸው ለበርጫ
‹‹ምርጫው›› ምርጫ አልመስል ያለው ገዢው ፓርቲ ፡‹‹ጭር ሲል አልወድም ይደብረኛል!!››
በሚል እራሱን ለመሸወድ ሲል የተለያዩ ድምቀት የሚፈጥሩለትን ዝግጅቶች ሲያደርግ ሰንብቷል፡፡ ከዝግጅቶቹም ውስጥ በተለያዩ መኪኖች
ላይ ሞንታርቦ ስፒከሮችነ ገጥሞ፡ ጩኅት ብቻ የበዛባቸውን ሙዚቃዎች በመልቀቅ ፡ከማዝናናት ይልቅ ህዝቡን ሲያሸብረው ነበር የከረመው፡፡ይህንን
ሙዚቃዊ-ሽበራ የታዘበ አንድ ወዳጄ ‹‹ምርጫው ምንም አይነት ሁከትም ድምቀትም ስለአልታየበት፡በአሸባሪ ሙዚቃዎቻቸው ብቻ 97ን ማስታወስ
የፈለጉ ይመስለኛል፡፡››ነበር ያለው፡፡
በዋዜማው ላይ ከታዘብኩትና ካስተዋልኩት ሌላኛው የድምቀት መፍጠሪያ እና ማሸበሪያ ዘዴዎች መሀከል
ደግሞ እንደ ተዝካር-ሰደቃ በየጎዳናው ላይ ድንኳኖችን መትከላቸውና ሰዎችን ቡና ጠጡ እያሉ ማሸበራቸው ነው፡፡ ለነገሩ ምርጫ የሚባለው
ነገር ሞቶ ተዝካሩ እየወጣ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ታዲያ እኔ በደረስኩባቸው ሁለት ድንኳኖች ውስጥ ያስተዋልኩት ነገር ግርምትን ፈጥሮብኛል፡፡
በእለተ ቅዳሜ ከሰዓት ቦሀላ ድንኳኖቹ በሚቅሙ ሰዎች ተሞልቶ ነበር፡፡ ሁሉም ከየቀበሌያቸው የተሰጣቸውን ግዳጅ ለመወጣት ይመስላል፡
በሌለው ምርጫ ላይ ይሟገታሉ፡ ይሞጋገሳሉ፡ አንዳንዶቹም በአሽሙር ይጎሻሸማሉ፡ በየድርጅታቸው እየተቧደኑ ቁጭት ብጤ ያሳያሉ፡፡ በየንግግራቸው መሀልም ‹‹ባለራዕይ›› የሚሉትን ጌታቸውን እያነሱ ቡራኬ ያሰማሉ፡፡
በቂማው መርቀን ያሉት ደግሞ በድንኳኑ ውስጥ የተሰቀለውን የጌታቸው የአቶ መለስን ፎቶ አጠገባቸው ያለ ያህል በስስት እያዩትና ስለሱ
እያወሩ፡ አንዳንዶቹም የአዞ እንባቸውን እያወረዱ(መለስ ለአንድ አፍታ
ቀና ቢል ‹‹ወራዶች!!›› የሚላቸው ይመስለኛል) ከፍተኛውን የካድሬነት ነጥብ ለማስቆጠር ይጣጣራሉ፡፡ ጫታቸውን በጉያቸው የሸጎጡና
መንገዳቸው ላይ ድንኳን በቅሎ የጠበቃቸው መንገደኞችም ‹‹ምርጫ ይመቻል ለበርጫ!!›› በሚል እዛው ጫታቸውን ይፈቷታል፡፡ በካድሬዎች
ጥርስ ውስት እንዳይገቡ የሰጉ አንዳንድ የአከባቢው ነዋሪዎችም፡ በዚህች እለት ጫትን በቤታቸው ከመቃም ይልቅ በድንኳኗ ውስጥ መቃምን
መርጠዋል፡፡ እርግጥ ነው እቤት ውስጥ በሙቀት እየተቃጠሉ ከመቃም በድንኳኗ ውስጥ ነፋስ እያገኙ ዘና ብሎ መቃሙ ሳይሻል አይቀርም፡፡
እንደውም እነዚህ ሰዎች በየቀኑ ‹‹ምርጫ›› እንዲኖር ሳይመኙ አልቀረም፡፡‹‹ምርጫው›› ለበርጫ ይመቻላ!!
አንድ
እጩው ጅብ
‹‹በምርጫው›› ዕለት በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች እና አንዳንድ ቦታዎች ላይ ስዟዟር የገጠሙኝ
ነገሮች እጅግ በጣም በርከት ይላሉ፡፡ ‹‹ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል›› ነውና እኔም ከትዝብቶቼ የተወሰኑትን ላውጋችሁ፡፡
ገና በጠዋቱ ከቤት ወጥቼ አንድ ካፌ በረንዳ ላይ ለትዝብት ተሰየምኩኝ (ካፌውን በርካታ ጆሮ ጠቢዎች እንደሚያዘወትሩት ይነገራል)፡፡
ከኔ ትይዩ ባለው ወንበር ላይ የተቀመጡ ሁለት ሰዎች ‹‹የምርጫ›› ወግ ይዘዋል፡፡ አንደኛው ይጠይቃል ሌላኛው ይመልሳል፡፡
‹‹መረጥክ?››
‹‹ማንን ነው የምመርጠው?ኢህአዴግን?ለምን ሲባል?ምን ስላገኘው?››
‹‹ኢሶዴፓ የሚባለው አለ አይደል እንዴ?››
‹‹እሱን ከኢህአዴግ ምን ይለየዋል?››
‹‹እ…ሌላም እኮ በግል የቀረበ አለ ተብሏል፡፡››
‹‹ህህ..!! እሱን ከምመርጥ ገደል ብገባ እመርጣለው፡፡››
‹‹እንዴ! ለምን?››
‹‹ልጅ መሰለህ የተረገመ እኮ ነው፡፡ ውሎ አዳሩ እኛው ቀበሌ ነው፡፡ ባለፈው አንድ ጉዳይ
ላስጨርስ ሄጄ 200 ብር ነው ጉቦ የተቀበለኝ፡፡ከኔ ከደሀው 200 ብር የተቀበለ ጅብ መርጬ ሀገር ሊበላ ነው?!››
ሁለት
የቦምቦሊኖው ስትራቴጂ
ከካፌው የሁለቱ ጓደኛሞች ወግ በመቀጠል በአቅራቢያዬ ወደሚገኙት ‹‹የምርጫ›› ጣቢያዎች ዘወር-
ወር ማለት ጀመርኩኝ፡፡ እነደ አጋጣሚ ልማታዊ ጋዜጠኞቻችንስ ምን እያሉ ይሆን? በሚል የሀገሪቱን ክልሎች በሙሉ ካልተቆጣጠርኩኝ
እያለ ያለውንና የኢህአዴግ ቴርሞ ሜትር የሆነውን የሬድዮ ጣቢያ ከፈትኩትኝ፡፡ በመሀል ነበርና የከፈትኩትኝ ስቱዲዮ የነበረው ‹‹ጋዜጠኛ››
በምርጫ ዘገባ ላይ ለነበረችው ጋዜጠኛ ድንቅ ጥያቄ ሲሰነዝርላት ሰማሁ፡፡
‹‹እስኪ አንቺ ባለሽበት ጣቢያ እየተወዳደሩ ስላሉት አዲስና አሮጌ ተወዳዳሪዎች የምትዪን ነገር
ካለ?..››
ሲላትና እኔም ቀጣዩን ትዝብቴን ካስተዋልኩበት ጣቢያ ስደርስ አንድ ሆነ፡፡
ጣቢያው ለሰው ልጆች አደገኛ የተባለ ስፍራ ይመስል አንድም ሰው ደፍሮ ሲጠጋው ማየት አልቻልኩም፡፡
እኔ የሚታየኝ መራጭ ሳይሆን ቦምቦሊኖ ገማጭ ብቻ ነው፡፡ በዞርኩባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እንደታዘብኩት ከሆነ፡ በዚህ ምርጫ ከመንግስት
ይልቅ መንግስት በፈጠረላት ምቹ የስራ እድል ተጠቅማ ቦምቦሊኖ የምትጠብሰው ካድሬዋ ወይዘሮ ይበልጥ አትራፊ ትመስለኛለች፡፡ በጣቢያዎቹ
የሚታዩኝ የምርጫ አስፈጻሚዎችና የጥበቃ ዘቦች በሙሉ በመራጭ ድርቅ የተመታውን ጣቢያ፡ ውድድር በሚመስል መልኩ በቦምቦሊኖ ገመጣ
ሊያደምቁት ሞክረዋል፡፡ ምናልባትም ሳት ብሏቸው ከፉ ክፉውን እንዳይዶልቱ ኢህአዴግ የቀየሰው የቦምቦሊኖ ስትራቴጂ ሳይሆን እንዳልቀረ
ገምቻለው፡፡ በዚሁ የቦምቦሊኖ ገመጣ አብዮት ውስጥ የተካተተው ልማታዊው ጋዜጠኛም ቦምቦሊኖ እየገመጠ ይጠይቃል፡እየተገመጠ ይመለስለታል፡፡
በእለቱ ምራቅ መዋጥ ያበዛ፡ ትን ያለውና ያሳለው ‹‹ጋዜጠኛ›› ሰምታችሁ ከሆነ እርግጠኛ ሁኑ እሱ ቦምቦሊኖ እየበላ ሳይጨርስ አየር
ላይ የወጣ ነው፡፡ የቦምቦሊኖው ቃለ መጠይቅ ተጀመረ፡፡
‹‹ምርጫው እንዴት ነው?››
‹‹እንደምታየው እንግዲህ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ፡ፍትሀዊና፡ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡››
‹‹ጋዜጠኛው›› ምንም በሌለበት ይጠይቃል፡ሀላፊውም ምንም በማይታይበት እንደምታየው እያለ ይመልሳል፡፡
ጠያቂው አሁንም በድጋሚ ሌላ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡
‹‹አጠቃላይ ምርጫውን እንዴት ይገልጹታል;››
‹‹በእውነቱ በጣም የተሳካ ምርጫ ነው፡፡ከአስር በላይ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት ነው የሚመስው፡፡…››
ሐላፊው እንዲህ ባለው አስደንጋጭ ኩሸት ያበለፀገው ቦርጩን እያያሻሸ
ተቀደደ፡፡ ጋዜጠኛውም ካሜራ ለማሳመር ያለአንዳች ጥያቄና መገረም በአዎንታ ጭንቅላቱን ከላይ ታች ይወዘውዛል፡፡ ይህ ሙያው ሳይሆን
እንጀራው ነውና፡ ከዚህ ውጭ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ አንዳንዱ ተንኮለኛ ግን ‹‹አስር የበላው የቦምቦሊኖ ቁጥር ሳይሆን አይቀርም!››
በሚል ሊሳለቅ ይችላል፡፡
ሶስት
የተወጠረ ጉንጭና የተራበ ኮሮጆ
ከሰዓት ቦሃላ ከነበርኩበት ሰፈር ትንሽ ራቅ ብዬ ሄድኩኝ፡፡በሄድኩበት ሰፈር ካለ አንድ ሰፊ
ግቢ ውስጥ ሌላ የምርጫ ጣቢያ ገጠመኝ፡፡በዚህኛው ግቢ ውስጥም አስመራጭ ኮሚቴ ተብዬዎች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ከአጠገባቸው ካርድ
የራበው ከሲታ ኮሮጆ ሆዱ ተጣብቆ ይታየኛል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ከኮሮጆው አጠገብ የተሰባሰቡት አስመራጭ ኮሚቴዎች የምሳ ሰዓት በመድረሱ
ይመስላል፡ ጉንጫቸውን በምግብ ወጥረዋል፡፡ ይሄኔ ኮሮጆው አፍ ቢኖረው ‹‹እኔስ መች ይሆን በዚህች ሀገር ላይ ምርጫ ተካሂዶ ሆዴ
እንደናንተ ጉንጭ የሚቆነዘረው?›› የሚል ይመስለኛል፡፡ በጠረጴዛው ላይ የተከመረው ምግብ ለአስመራጭ ኮሚቴዎች ብቻ ሳይሆን፡ ተመራጩ
ወደፊትም መረጡኝ ለሚላቸው ዜጎች ጭምር የቋጠረው ስንቅ ነበር የሚመስለው፡፡ ከምግቡ አጠገብ ደግሞ ሊቃም የተዘጋጀ ጫት ቁጭ ብሏል፡፡
እዚህም እንግዲህ ምርጫን በበርጫ መሆኑ ነው፡፡
በዚሁ ጣቢያ አካባቢ ሆኜ ትዝብቴን ስኮመኩም፡ እንደ አጋጣሚ አንዲት አብራኝ የተማረችና፡ በአሁን
ሰዓት በአንድ ሚዲያ ውስጥ የምትሰራ ልማታዊ ወዳጄን አገኘኋት፡፡ ተነፋፍቀን ነበረና ቶሎ መላቀቅ አልሆነልንም፡፡ስለዚህ ትንሽ ታግሻት
ወደምትሄድበት አብረን ልንሄድ ተስማማን፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ አንድ የምርጫ ቦርድ ተወካይ ማናገር ነበረባትና ወደሱው አመራን፡፡
ሰውየው በከተማዋ ውስጥ ያሉ ጣቢያዎች ምክትል ሀላፊ ነገር ነው፡፡ ወዳጄ የመራጮቹ ቁጥር ምን ያህል አንደደረሰ ጠየቀችው፡፡ እሱም
በወቅቱ አሳማኝ በመሰለኝ መልኩ አንዲት ነጥብ አንኳን ሳያጎድል በርግጠኝነት ድምጸት 76.8 ከመቶ ማለትም 42876 /ቁጥሩ ላይ
እርግጠኛ አይደለሁም/ የሚሆኑ መራጮች ድምጽ ሰጥተዋል፡፡ አስከ 12 ሰዓት ወዳ 96.9 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ
ይገመታል ፡፡……..›› አላት፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ፡ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ወዳገኘችው የአንድ ነጠላ ጣቢያ ተወካይ ደውላ የመራጩ ቁጥር ምን ያህል አንደሆነ ትጠይቀዋለች፤
ሰውየውም ‹‹እስከ አሁን ቆጥረን ስላልጨረስን ትክክለኛውን ቁጥር አላውቀውም፡፡›› ብሏት አረፈው፡፡ እና ሀላፊው አጠቃላዩን ድምር
ከየት አመጣው; ብሎ መጠየቅ ነውር ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ለኢህአዴጋውያኑ ብቻ የሚገለጥ ጥበብ ነውና፡፡
የኢህአዴግና የኢሶዴፓ ግብግብ
የዛሬዋን ሰኞ (ይህ ትዝብቴ በምርጫው ማግስት ሰኞ የታዘብኩት በመሆኑ ነው) ከቀደሙት ሰኞዎች
ምንም የሚለያት ነገር የለም፡፡‹‹ከምርጫው›› ቀደም ብሎ ሲያሽቃብጡ የነበሩት ሚዲያዎች በባዶ ሜዳ ሲጮሁ እንደነበር የገባቸው በዚህ
ቀን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ‹‹ከምርጫው›› ውጤት ጋር በተያያዘ ምንም የሚያወሩት ነገር አልነበራቸውም፡፡ ትኩረታቸውን ወደቀደመው
ህብረተሰቡን የማደናቆር ስራቸው ላይ አድርገዋል፡፡ ምናልባት ይህንን ሰኞ ለየት የሚያደርገው ነገር እንፈልግ ከተባለ፡ የቀበሌና
የምርጫ ቦርድ ሰዎች የእረፍት ቀናቸውን የሚጀምሩበት ቀን መሆኑ ነው፡፡ የቀደሙትን ሁለትና ሶስት ወራት በምርጫው ሰበብ ደሞዝ የሚከፍላቸውን
ህብረተሰብ ሲያጉላሉ የከረሙት ሰራተኞች፡ አሁን ደግሞ ለምርጫው ደክመናል በሚል ለተጨማሪ ቀናቶች(ምናልባትም ወራቶች) ህዝቡን ሊያጉላሉት
ነው፡፡ በዚህ ቀን ያገኘሁት አንድ ወጣትም( እንደነገረኝ የምርጫው አስፈጻሚ ነበር፡፡) ያረጋገጠልኝ ይህንኑ ነው፡፡ ‹‹..ሰሞኑን
ደከምን አይደለም እንዴ;…አሁንማ ስራ መግባት የለም፡፡›› ነበር ያለኝ፤ የእረፍት ቀኑ መጀመሩን ሲናገር፡፡ ምን ችግር አለው!?
ቢጉላላ ህዝብ ነው! ከፓርቲ በላይ ነፋስ ነው ነገሩ፡፡ ታዲያ ይህ ትጉህ ወጣት የእረፍት ግዜውን በምን የሚያሳልፍ ይመስላቹሀል?
ጉያው ስር በኩራት ሸጉጦት በሚሄደው ጫት፡፡
እናላችሁ ይህ ‹‹ትጉህ›› ወጣት፡የፓርቲውን ልምላሜ ለማንጸባረቅ ይመስላል ከአረንጓዴው ጫት
በተጨማሪ ደማቅ አረንጓዴ ካናቴራ ለብሷል፡፡ በአረንጓዴው መደብ ላይ ደግሞ በቢጫ ቀለም ‹‹ኦህዴድ/ኢህአዴግ እና ኢሶዴፓን ይምረጡ››
የሚል ዓረፍተ ነገር ሰፍሮበታል፡፡ እንዲህ ነው እንጂ ዴሞክራሲያዊ እመርታ! ኢህአዴግን እና ኢሶዴፓን በአንድ ካናቴራ ግብግብ ሲገጥሙ፡፡
አሁንም ወጣቱን ስንት ራዕይ የሚያይበትን የበርጫ ሰዓት እየተሻማሁት ነው፡፡ ዝም ብዬ እንደቀልድ፡ ‹‹ኢሶዴፓ የሚለው ቃል ትርጉሙ
ምንድነው?›› አልኩት፡፡ እሱም ‹‹ያው የሶማሌ ምናምን ስለሆነ ነው…›› በሚል ለኔም ለሱም ብዙ ግልጽ ያልሆነ ምላሽ ሰጠኝ፡፡
እኔም አፌ አያርፍም ‹‹ኢ ምንድናት፡ምንን ትወክላለች?›› ስል ጥያቄዬን አስከተልኩኝ፡፡ ‹‹ያው ኢህአዴግና ኢሶዴፓ አንድ አይደለም?
እነደዛ ማለት ነው፡፡›› ብሎኝ አረፈው፡፡ እመኑኝ ተረት አይደለም የማወራው፡፡ ካላመናችሁኝ፡ወደ ቀበሌ ጎራ በሉና አንድ ሁለት
የኢህአዴግ አባላትን መሰል ጥያቄ ሰንዝሩላቸወ፡፡
ይሄኔ ነው እንጂ እሪሪ….!! በይ ሀገሬ ማለት፡፡ ስምሽን እንኳን በቅጡ የማያውቅ ዜጋሽ፡
ላንቺ ይበጃል የሚለውን ሰው ሊመርጥልሽ ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡ ያውም የጫቱ ከራማ ሁሉ ተደማምሮ፡፡
ከወጣቱ ጋር ተለያየን፤ እሱ እቤቱ ገብቶ ከዋዜማው የተረፈውን የድንኳን ውስጥ ጨዋታ እያኘከ፡
አለቆቹ በቀጣዩ ‹‹ምርጫ›› በምርቃና የሚነድፉለትን ስትራቴጂና አፈጻጸም ይጠብቃል፡፡ የኛም ምርቃና የእነሱ ደረጃ ላይ ሲደርስ
ለሀገር የሚበጅ ምርጫ ምን አይነት እንደሆነ ይገለጥልን ይሆናል፡፡ እስከዛው ግን ለኛም ለእነሱም የሚበጅ ምርቃና ይስጠን ብለን
ብንመራረቅስ? አሜን!!
No comments:
Post a Comment