በመሀመድ
ሐሰን
‹‹በአለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ እስላም ኢትዮጵያውያን ማካሄድ የጀመሩት ትግል በዓይነቱም፣ በስፋቱም፣ በአስተሳሰቡም፣ በስሜቱም፣ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአገዛዙ ጋር ከተደረጉ ትግሎች በጣም የተለየ ነው፤ በመጀመሪያ ደረጃ ትግሉ ለሀይማኖት ነጻነት ነው፤ ስለዚህም በአገዛዙ በኩል የፖለቲካ ዓላማና የፖለቲካ መልክ እየተሰጠው ሲሆን በእስልምና ምእመኖቹ በኩል ግን ትግሉን ከፖለቲካ የፀዳ ለማድረግ ግሩም የሆነና የተሳካ ጥረት እያደረጉ ነው፤ ሁለተኛ የትግሉ ስልት ፍጹም ሰላማዊ በመሆኑ የአገዛዙን የጉልበት ስልት እያከሸፈ ያጋለጠው ይመስላል፤ አንዱና ዋነኛው ትግሉ ሰላማዊነት መገለጫ በቤተ መስጊድ መወሰኑ ነው፤…፡፡››
ይህንን የመግቢያ አንቀጽ የወሰድኩት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ህዳር ወር 2005 ዓ.ም
‹‹ የእስላም ኢትዮጵያውያን የትግል ስልት›› በሚል ከጻፉት ጽሁፍ ላይ ነው፤ በአሁን ወቅት ከዓመት በላይ ባስቆጠረው የሙስሊሞች
ሰላማዊ ትግል ላይ በርካታ ምሁራንና መገናኛ ብዙሀን ዝምታን ሲመርጡ፣ የሀገራቸውን የየዕለቱ እስትንፋስ በንቃትና በጥንቃቄ የሚከታተሉት
ፕሮፍ ግን፣ ከላይ የጠቀስኩትን ጽሁፍ ጨምሮ በርካታ ጽሁፎችን በጉዳዩ ላይ ጽፈዋል፤ እስላም አይደለሁም በሚል ዝምታን አልመረጡም፤
የተሰማቸውን ሁሉ በየግዜው አስነብበውናል፡፡
በግለሰብ ደረጃ ሙስሊም ያልሆኑ ጸሀፍት እጅግ በጣም ረዘም ላለ ግዜ ጉዳዩን ከጥግ ቆመው ለመታዘብ
መርጠዋል፤ እርግጥ ነው እንደ አናንያ ሶሪ ያሉ ጋዜጠኞች በጉዳዩ ላይ ከመጀመሪያ ጀምሮ ሀሳባቸውን መሰንዘር የጀመሩ ሲሆን እስካሁንም
ድረስ የሙስሊሞችን ጥቃትና ጥያቄ እንደራሱ በመቁጠር፣ በንቃት እየተከታተሉ ከሚጽፉት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ በሌላ በኩል ከሀገር ውጪ
ያሉ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች በተሻለ መንገድ ለትግሉ ትኩረት ለመስጠት የሞከሩበት ሁኔታ አለ፡፡ እኔን ጨምሮ ግን ሌሎች ጋዜጠኞች
በጉዳዩ ላይ የመረጥነው ዝምታ አሳፋሪ ሊባል የሚችል ነው፤ ጉዳዩን አጣመው ለማቅረብ የሞከሩ አንዳንድ ጋዜጠኞች ደግሞ ይበልጥ ተወቃሾቹ
ናቸው፡፡ እኔም ብሆን ዛሬ የምጽፈው ስሜ መሐመድ ስለሆነ አይደለም፤ ምናልባት የተሸከምኩት ግዙፍ ስም ሀይማኖተኛ አስመስሎኝ ይሆናል፤
በእርግጥ በተሰቦቼ ጥሩ ሙስሊሞች ናቸው፤ የእኔን እውነታ ግን በቅርበት ለሚያውቁኝ ብተወው ይሻላል፡፡
በተቋም ደረጃም ካየነው፣ እንቅስቃሴው በተጀመረበት ወቅት ሁሉም ዝምታን ሲመርጡ፣ ቦሃላ ላይ
ግን ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት የሰጠው ቀዳሚው መጽሄት ‹‹አዲስ ጉዳይ›› ነበር፡፡ መጽሄቱ የሀምሌ ወር እትሙን የፊት ሽፋን ያዋለው
‹‹ኮሚቴው-መጅሊሱ-መንግስት›› ለሚለው አብይ ርዕስ ነበር፡፡ ይህ መጽሄት ከዛ ቦሃላም ቢሆን ለሙስሊሞች ጥያቄ ተደጋጋሚ ሽፋን
ለመስጠት ሞክሯል፤ በተረፈ በወቅቱ ከነበሩት ጋዜጦች አንዳንዶቹ በወቅቱ ከነበረው የአወሊያ ተኩስ ይልቅ የአንድ ደብር አስተዳዳሪ
ውዝግብ ውስጥ መግባት ነበር ቀልባቸውን ሲስበው የነበረው፡፡
አሁን ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት በወቅቱ አብዛኞቹ መገናኛ ብሁሃን ለምን ቸልተኛ ሆኑ? ምክንያታቸውስ
ምን ነበር? የሚለው ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ጥያቄ ከሚዲያው ሰዎች ባሻገር፣ የሙስሊሙን ጥያቄ በአሉታዊ ጎኑ የሚመለከቱ ሰዎችንም
ይጨምራል፡፡ ብዙ ግዜ ፊትለፊት የቀረበውን ጥያቄ ከመመርመር ይልቅ በዘልማድ ስንሰማቸው ላደግናባቸው የተዛቡ አስተሳሰቦች የምንሰጠው
ግምት ፣ ለስጋት ሰለባነት ሳይዳርጉን አልቀሩም፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሙስሊሞች ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ይጠራጠራሉ፤ እንዲህ ያለውን
አስተሳሰብ የሚያጠናክር ተረትም ጭምር በሀገራችን ውስጥ አለ፤ መተማመን ያለብን ግን መሬት ላይ ባለው እውነታ ነው፤ መንግስት ያስቀመጠውን
ቁጥር እንኳን ብናይ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከአጠቃላዩ ህዝብ ውስጥ ወደ 35 በመቶ የሚሆነውን ቁትር ይሸፍናሉ፤ ስለዚህም እንደ
መንግስት በጭፍን ይህንን ሁሉ ህዝብ ‹‹ጥቂቶች›› በማለት ከማለፍ ጥያቄያቸውን ማድመጥና የየራሳችንን መፍትሄ መፈለጉ ፋይዳው ሀገራዊ
ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አሳማኝ የሆኑና ግልጽልጽ ያሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፤ መንግሰት ግን በጉዳዩ
ላይ እስከ አንገቱ ድረስ ጣልቃ በመግባት ስህተት ፈጸመ፡፡ ጥያቄውን በአግባቡ ካለመመለስ አልፎ፣ ፊትለፊት የሚታዩ እውነታዎችን
መካድ ጀመረ፡፡ ዩአህባሽ ሰዎችን ወደ ኢትዮጵያ ጋብዞ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ከየቦታው በማሰባሰብ ማሰልጠን ጀመረ፤ ለኢትዮጵያ
ሙስሊሞች የሚበጅ እስልምና በሚል ፈሊጥም ‹‹ሀይማኖታችሁን ልምረጥላችሁ›› ሲል በአደባባይ ተሰማ፡፡ ዙሩንም አካሮት በማን አለብኝነት
ከ 500.000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ ሙስሊም የወከላቸውን ኮሚቶዎች ‹‹ጥቂቶች›› ሲል አሰራቸው፡፡ ከዚህ ቦሃላ ነበር ፍጹም
ሰላማዊ የሆነው የህዝበ ሙስሊሙ ትግል እጅግ በተጠናከረና በተቀናጀ መልኩ የቀጠለው፡፡
አስገራሚው
ትግልና ስልቶቹ
እኔን ጨምሮ በርካቶቻችን ለሙስሊም ኢትዮጵያውያኑ የነበረንን ግምት ገደል የከተተና ያስደመመንን
ትግል ነበር ሙስሊሞቹ ሲያካሂዱ የነበሩት፡፡ ብዙዎቻችን ሙስሊሙን ማህበረሰብ ከንግዱ ጋር ብቻ እናቆራኘዋለን፤ ከዚህ ውጪ ለሀገራዊ
ጉዳይ እና ለመብታቸው ይህን ያህል ርቀት ተጉዘው መሄዳቸውን የገመቱ ብዙዎች አልነበሩም፡፡ ከዚህ በፊት ከነበረው ልምድ በመነሳትም
አብዛኛው ሙስሊም ለኢህአዴግ ድምጽ የሚሰጥበት ሁኔታ ስለነበር፣ በዚህ ደረጃ ይገዳደሩታል ተብሎ አልታሰበም፡፡ ሌላው ቀርቶ በምርጫ
97 ወቅት እንኳን ህዝቡ ኢህአዴግን ‹‹አይንህን ለአፈር›› ሲለው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሙስሊሞች ድምጻቸውን አልነፈጉትም፡፡
ነገር ግን በሚገርም ሁኔታ ነገሮች ሁሉ ተለዋውጠው፣ ሙስሊሙ በአንድነት ተነሳ፤ ቴክኖሎጂውን ከማናችንም በተሻለ ፍጥነት ተጠቅመው፣
በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ሙስሊሞች አንድ አይነት መረጃ ይለዋወጡበት ጀመር፤ ለዚህም ደግሞ በእንቅስቃሴው ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ከሚወስዱት
ውስጥ አንደኛው ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› የተሰኘውና በማህበረሰብ ድረ ገጾች ላይ በትጋት፣ በፍጥነትና በሀላፊነት እየሰራ ያለው ቡድን
ነው፡፡
የሙስሊሞቹን ትግል እጅግ በጣም ስኬታማ ካደረጉት ነገሮች ውስጥ በዋነኛነት ሳይጠቀስ የማይታለፈው
መሪና ተመሪው በግልጽ የተቀናጁበት መሆኑ ነው፤ መሪው የትኛውንም ሀላፊነት ወስዶ ለመስራት ዝግጁ ሲሆን፣ ተመሪውም አለቆቹን ለመከተልና
ማንኛውንም መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው፤ ለዚህም ነው መሪዎቹ እስከመታሰር የደረሱት፤ ምዕመኑም ታዲያ ጥሎ አልጣላቸውም፤ በሚገባ
ነበር ቃሉን የጠበቀው፤ ትግሉን ከማስቀጠል ባለፈ የታሰሩበት ድረስ በመሄድ ተዓምር ሊባል የሚችል ጥየቃ አድርጎላቸዋል፤ በየግዜውም
ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እየሄዱ መጠየቃቸውን አላቋረጡም፡፡ መረዳዳቱ አስገራሚ በሚባል መልኩ ጠንካራ ነው፡፡ የታሳሪዎቹ የመንፈስ
ጥንካሬም ቢሆን ፍጹም የበላይነታቸውን ያሳያል፤ እስከተከለከልኩበት ድረስ ወንዶቹን አንድ ሁለቴ፣ ፈትያ መሐመድን ደግሞ በተደጋጋሚ
የመጠየቅ እድሉ ገጥሞኛል፤ የእውነት ያስቀናሉ፡፡ ይሄኔ ታዲያ በተገቢው
ሰው እንኳን ለማይጠየቁ ጋዜጠኛ ወዳጆቼ ማዘኔ አልቀረም፡፡ ይህ ሌሎች ትግሎች ውስጥ አለን የምንል ሰዎችም ልንቀስመው ከሚገባው
ትምህርት አንደኛው ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሁኔታው በየግዜው ይቀያየር የነበረው የትግል ስልት (ተቃውሟቸውን
የሚገልጹባቸው መንገዶች) እስደማሚ ሊባል የሚችል ነው፤ የሚይዙት መፈክር፣ የሚጠቀሙት ምልክት፣ የሚገናቹባቸው መስጊዶችና ግዚያት፣
ውሳኔ የሚያስተላልፉበት መንገድ፣… በሙሉ ተለዋዋጭና ከግዜው ጋር የሚሄድ ከመሆኑም ባሻገር ከምናውቃቸው ኢትዮጵያዊ የተቃውሞ ስልቶች
ሁሉ የላቁና ወደፊት ብዙ ርቀት የተራመዱ ናቸው፡፡ መስጊዶችን ባዶ ማድረግ፣ ምርጫቸውን ዋጋ ማሳጣት፣ መፈክሮችን በጥንቃቄ በመጻፍ፣
የሌሎችን መብት ባለመንካት፣… ቆጥረን የማንጨርሳቸው ስልቶችን ተጋባራዊ በማድረግ ፍጹም የተሳካ ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ትግሉ
ሰላማዊና ሰላማዊ ብቻ መሆኑ ነው፤ ለዚህ ሰላማዊነት ደግሞ ሁሉም ሀላፊነት ወስዶ ሲሰራ ነበር፤ የኢህአዴግም ሴራ ያልተሳካው ትግሉን
ሰላማዊ ለማድረግ ሁሉም ሙስሊም ተሳታፊ በመሆኑ ነበር፡፡ በተቃውሞው ላይ የተገኘ ሁሉ አከባቢው ያለው ሰው ምንም አይነት ሰላምን
የሚያውክ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ የመቆጣጠር ሀላፊነት ነበረበት፤ ከቻለም በካሜራ ጭምር ይቀርጸዋል፤ እንዲህ ያሉትን አዋኪዎች
‹‹አሳልፈን እንስጥ›› የሚል ትዕዛዝ ሁሉ ከላይ ለምዕመናኑ ተላልፏል፤ በኢህአዴግ በኩል አንዳንድ ሙከራዎች ቢደረጉም፣ ሰላማዊነቱን
ግን ማስቀጠል ተችሏል፡፡ ይህም ብዙ ሊያስተምረን የሚችል እውነታን የተሸከመ ሌላኛው ነጥብ ነው፡፡
እውነቱን መነጋገር ካለብን የሙስሊሞቹ ትግል በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥም ሆነ በገዢው በኩል ከሚካሄደው
ትግል በብዙ እጥፍ ልቆ ሄዷል፤ ምናልባት እንዲህ ያለውን ምስክርነት ለመስጠትና ባርኔጣችንን ለማንሳት የሚተናነቀን ሌላ ዘልማዳዊ
አስተሳሰብ ከሌለ በስተቀር እውነታውን የግድ አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡ ከምንም በላይ ያስገረመኝን የቅርቡን የኢድ ተቃውሞ ማንሳት
እፈልጋለሁኝ፤ በየትኛውም ኢትዮጵያዊ ተሞክሮ በማያውቅ ድፍረት ባንዲራችንን ‹‹ጨርቅ›› ያለው ደፋሩ የአቶ መለስ ኢህአዴግ፣ አጀንዳ
ቢያልቅበት ሙስሊሙን ወስዶ ከባንዲራ ጋር ሊያላትም ሞከረ፤ ጆሯችን እስኪደማ እሱ የባንዲራ ተቆርቋሪ ሆኖ ሙስሊሙን ‹‹ባንዲራ ያቃጠሉ››
ሲል መወንጀሉን ተያያዘው፡፡ ታዲያ እኚህ ብልህ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች፣ ኢህአዴግ በመጨረሻ አለኝ የሚለውን ቀለሃ አከሸፉበት፤ በኢድ
ሰላት ላይ ‹‹ለሀገራችን ባንዲራ ያለን ፍቅርማ በአንተ ሚዛን አይሰፈርም፤›› በሚል አብዛኛው ሙስሊም ባንዲራ ይዞ በመምጣት ለሀገሩ
ባንዲራ ያለውን ክብር ገለጸ፤ ኢህአዴግም ቀለሃውን በመጨረሱና ፍጹም በመበለጡ እውነተኛ ማንነቱ ወጣ፤ ቀድሞም የማያከብረውን ባንዲራ
መንጠቅ ጀመረ፣ የሚችልበትን የጫካ ጨዋታም ጀመረው፤ መስገጃ ለያዙ ሰላማዊያን ጥይትና ቆመጥ አደላቸው፤ ድሮም ሃብ የሌለው ሰው
ከዚህ የተሻለ ማድረግ አይቻለውም፡፡
ለኢህአዴግ
የጎሳ ፌዴራሊዝም የማይመቸው እስልምና
ማንም እንደሚያውቀው የኢህአዴግ መንግስት አደገኛው አካሄድና እድሜ ማራዘሚያው ብሄር /ጎሳን
መሰረት ያደረገ አካሄዱ ነው፤ ሀገሪቱን በሙሉ ብሄር በብሄር ያደራጅና እነሱ እርስ በእርሳቸው ሲፋጠጡና ሲፋለሙ፣ እሱ ጥግ ቆሞ
የሴራውን ግጥሚያ እያየ የዙፋኑን ዘለቄታ ለማረጋገጥ ይሞክራል፤ በዚህ መንገድ ሀገሪቱን ሁሉ ሊዳርስ የሚያደርገው ጥረት ግን አንድ
ቦታ ላይ እክል ይገጥመዋል፡፡ ይህን እክል የፈጠረው ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ የማይናቅ ቁጥርና የኢኮኖሚ ድርሻ ያለው ሙስሊሙ ማህበረሰብ
ነው፤ ኢህአዴግ እስከዛሬ ሲያደርግ እንደነበረው ከሙስሊሙ ጋር መጋጨት የፈለገውና ወደ ፍልሚያው የገባው ይህችኑ ከፋፋይ የጎሳ ፌዴራሊዝሙን
ተማምኖ ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለው አካሄድ በእስልምና ውስጥ ፈጽሞ አይሰራምና፣ በማይችለው ግጥሚያ ውስጥ ገብቶ እንዳይሆን
ስለመሆኑ ለማረጋገጥ እንደ ኢ.ቴ.ቪ እና ሬድዮ ፋና ያሉትን ወያኔ እንደፈለገ የሚጋልባቸውን የመገናኛ ብዙሃን ከንቱ ድራማዎች መመልከቱ
ከበቂ በላይ ማሳያ ሊሆነን ይችላል፡፡ በእስልምና ውስጥ ከሁሉ በላይ ቀድሞ የሚመጣው ወንድማማችነቱ ነው፤ ኦሮሞውና ትግሬው ያለ
ልዩነት የእውነት ወንድማማችነታቸውን አምነው የሚቀበሉበት ነው እስልምና ማለት፤ ለዚህም ነው መረዳዳቱና መተዛዘኑ እስር ቤት ድረስ
አብሮ የሚዘልቀው፤ ለዚህ ነው መንግስት የሾማቸው የሀይማኖት አባቶች እንኳን ሳይቀሩ በየግዜው በበመስጊዱ ለታሰሩት ወንድምና እህቶች
አላህ ምህረቱን እንዲልክላቸው የሚጸልዩት፤ ለዚህ ነው ሰሞኑን በረመዳን እንደታዘብኩት ምንም የሌለው ደሃው መስጊድ ውስጥ ልብሱን
እያወለቀ፣ ሴቷም ወርቋን እያወለቀች ለታሰሩት እንዲጸለይላቸው ሲማጸኑ መመልከት የቻልነው፤ ለዚህ ነው… ለዚህ ነው ሆዳቸውን ከሚያመልኩ
በቴሌቪዥን መስኮት ከሚቀርቡትና በመጅሊሱ ዙሪያ ከመሸጉ ጥቂቶች በቀር ሁሉም ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የትግሉ ደጋፊ የሆኑት፤ ጥቂት
የሆኑት ኢህአዴጋውያኑ ግን ሁሉም እንደነሱ የጥቂቶች ስብስብ ስለሚመስላቸው ወደ 30 ሚሊየን የሚጠጋውን የሙስሊም ማህበረሰብ ‹‹ጥቂቶች››
ሲሉ የሚያሳንሱት፡፡
ከላይ በመግቢያዬ ላይ በጠቀስኩት የፕ/ር መስፍን ጽሁፍ ላይ ትልልቅ የሚባሉት ጎሳዎችን ያቀፈው
እስልምና በጎሳ የታጠረ ባለመሆኑ ለኢህአዴ አገዛዝ እንዳልተመቸ ጽፈዋል፤ በዘሂሁ ጽሁፍ ላይ ‹‹…ከብዙ ዓመታት በፊት በተደረገ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ‹‹እስላሞች
በጎሳ አይከፋፈሉም›› በማለት የገለጹትን ቁም-ነገር አገዛዙ የረሳው ወይም እስላሞቹ ረስተውታል ብሎ ያሰበ ይመስላል፤…››
የሚል ሀሳባቸውን ያሰፈሩት ፕሮፍ በሌሎች የክርስቲያን ቤተ እምነቶች ውስጥ የተፈጠሩ የጎሳ መከፋፈሎች የሚያሳፍር ደረጃ ላይ መድረሳቸውንም
አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡ ወደ ቤተ መስጊዶች እና የኢህአዴግ መሰሪነት ሲመጡ ደግሞ ‹‹…ቤተ መስጊዶች ኢዚህ ደረጃ አልወረዱም፤ እስልምና በጎሳ አይቀደድም፤ እስላሞች ሁሉ የአላህ ልጆች ናቸው፤ በቤተ
መስጊድ የሚሰበሰበው ሁሉ በአላህ ልጅነቱ ነው፤ ስለዚህም በመሀከላቸው ልዩነት የለም፤ ይህ የእስላሞች አቅዋም ሃያ ዓመት ተፈተነ፤
የማይበገር ሆነ፤ ስለዚህ ከጎሳ አስተሳሰብ ወጥቶ ሌላ ቀዳዳ መፈለግ ግዴታ ሆነ፤ አል- ሀበሽ አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው፤››
በሚል ስሱን ብልት ያጋልጡታል፡፡
አሁንም ከሙስሊሙ ትግል መቅሰም ያለብንን ቁምነገር እዚህች ጋር ነው ቆም ብለን ማሰብ ያለብን፤
ስንተባበር፣ አንድ ስንሆን፣ ኢትዮጵያ የምትለዋ ትልቋ ምስል በቅድሚያ ሁላችንንም ማስተሳሰር ስትችል፣… ያኔ አሁን በሙስሊሞቹ ላይ
እየታየ ያለው ድል በሀገሪቱ ላይ ስለመታየቱ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤ አለበለዚያ ግን፣ በጎጥ ከፋፋይ ለሆነው ስርዓት የሚመቸውን
የመቧደን ጨዋታ ማናችንንም ፈቀቅ አያደርገንም፤ ምናልባት የኢህአዴግን ፍላጎት በማሟላት ሀገሪቱን እንበጣጥሳት ካልሆነ በስተቀር፡፡
የተኳሹና ተንኳሹ ኢህአዴግ አደገኛ አካሄዶች
ያኔ እስልምና በተገቢው መንገድ አልተስተናገደም በሚል በሚወቀሰው በአጼው ስርዓት እንኳን እስላሞች
ዋና ዋና በሚባሉ የአዲስ አበባ አከባቢዎች በመዞር በነጻነት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፤ አንድም ጥይት እልተተኮሰባቸውም፤ በወቅቱ
አዲስ ዘመንም ለጉዳዩ ሽፋን ሰጥቶታል፤ አስቡት እንግዲህ ከዛ ቦሃላ
የንጉሱ ስርዓት ወርዶ፣ ደርግ ተተክቶ፣ እሱም ተገርስሶ፣ ኢህአዴግ ከ20 ዓመት በላይ ሀገሪቱ አናት ላይ በብቸኝነት ፊጥ ብሎም
የንጉሱን ያህል እንኳን መሰልጠን አልቻለም፤ አይደለም ከተማዋን በመዞር በመስጊድ ዙሪያ እንኳን መሰባሰብ ወንወጀል እየሆነ ነው፤
ያውም የወነወጀሎች ሁሉ ጌታ የሆነው የሽብር ወንወጀል፡፡
አሁን አሁንማ ይበልጥ ስርዓቱ የአውሬነት በሀሪው ጎልቶ በመውጣቱ አይደለም ተቃውሞ፣ መዕመናኑ
ወደ ቤተ መስጊድ ሄደው እንኳን ሄደው እንዳያመልኩ እየተከለከሉ ነው፤ በጾም ሰሞን ለሊት ሰባት ሰዓት የሚፈጸመውን ስግደት (ለይል)
ይሰግዱ የነበሩ በርካታ መእመናን በየአከባቢው መንገላታት ሲደርስባቸው መታዘብ ችያለው፤ አንዳንድ ቦታ ላይ እንደውም ‹‹በዚህ ሰዓት
የሚካሄድ ስግደት የለም፤ እናንተ የምትገናኙት ለአመጽ ልትማማሉ ነው፤›› በሚል የወንበዴ ፍረጃ እተደበደቡ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ
ተደርገዋል፡፡ በዚህኛው አርብ በነበረው የጁምዓ ስግደት እለትም፣ ለሆዳቸው ያደሩና ሀላፊነት የጎደላቸው የጸጥታ ሀይሎች (በጥባጭ
ሀይሎች ቢባሉ ይቀላል) በሴት እህቶች፣ እናቶች እና ህጻናት ላይ የፈጸሙት ድብደባ የስርአቱን አረመኔያዊ አካሄድ በይፋ ያሳየ ነበር፤
ቀላል የማባል ቁጥር የነበራቸው ሰጋጆችም መንገድ ላ እንዳይሰግዱ ተከልክለው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
በየትኛውም መንገድ ቢሄድ ሙስሊሙን መርታት የማይቻል እንደሆነ ኢህአዴግ የተረዳ አይመስልም፤
ሁሌ እንደ መፍትሄ በሚወስደው አፈሙዝ ለመርታት ማሰቡ እዚህ የሚሰራ አይደለም፤ ለሀይማኖት ሲባል ሞት በእስልምና ውስጥ ትልቅ ክብር
የሚሰጠውና የማይገኝ እድል ነው፤ ኮሚቴዎቹ ይህን በተደጋጋሚ ሲሉት ተደምጧል፤ ግርግር እንደሚኖር እያወቀች የ8 ወር ልጇን ለኢድ
ስግደት ወደ ስቴድየም ይዛ የምትሄድ እናት አጋጥማኛለች፤ በሀይማኖቷ ለመጣው አደጋ ልጇ ቢሰዋ ግድ እንደሌላትም አጫውታኛለች፤ እንዲህ
ያለው ጥንካሬ ነው ኢህአዴግ ያልገባው፤ ለግዜው እንጂ ለዘላለሙ የማይዳፈን ትግል፡፡
አሁን አሁንማ ሙስሊም መሆን ወንጀል ይመስል በበርካታ መንግስታዊ ተቋማትና መንገድ ላይም ጭምር
የተለየ ውክቢያ ማካሄድ ተጀምሯል፤ አንዳንድ ተቋማት አከባቢ እንደውም ‹‹ሙስሊሞች ለምን በዙ?›› የሚል ውይይት ሁሉ መካሄድ መጀመሩን
እየታዘብን ነው፤ በአሳፋሪ ሁኔታ መድረሳዎችን ጨምሮ በርካታ እስላማዊ ተቋማት በመዘጋት ላይ ናቸው፤ ለችግሮቹ የማይረቡና የተለመዱ
ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን በመስጠት፣ መንግስት ጉዳዩን ወደ አደገኛ መንገድ ለመምራት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው፤ እንደውም ኢትዮጵያዊው
ማንነታችን ባይገታን ኖሮ፣ እንደነሱ ፍላጎት ተጨራርሰን ባለቅን ነበር፤ እቅዳቸው ግን ዛሬም ነገም እንደማይሳካ በእርግጠኝነት መናገር
ይቻላል፤ በነ ኢ.ቴ.ቪ የሚነፋው የፕሮፖጋንዳ ጡሩምባም ህዝቡን ታክቶታል፤ እድሜ የነ ኢ.ቴ.ቪ ብሶት ለወለደው ዲሽ ይግባውና ከኛ
ከጋዜጠኞች ውጪ ሰው ሁሉ ኢቴቪ ትዝ የሚለው ለድራማ ብቻ ሆኗል፡፡
ከጅምሩም ቢሆን ኢህአዴግ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ትንኮሳ ያካሄደው አንድነትን በመጥላት ነበር፤
በወቅቱ ሙስሊሙ ሰደቃውን ያሰናዳ የነበረው ‹‹አንድነት ሰደቃ›› የሚል ስያሜ በመስጠት ሙስሊሙንም ክርስቲያኑንም ያካተተ ነበር፤
ባቲ ላይ ለክርስቲያኑ ታርዷል፤ አዲስ አበባ ላይም ሸጎሌ ክርስቲያኑ 5000 እንጀራ ጋግሮ ለሙስሊሙ በመስጠት ‹‹አንድ ነን››
የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፤ ሆኖም ግን አንድነት የሚለው ቃል የሚያስበረግገው ኢህአዴግ እንደፈለገ የሚነዳቸው ሀይሎችን
ልኮ ለሰደቃው የተዘጋጁ ምግቦችን ሲያስደፋ ከብቶቹንም አስነድቷቸዋል፤ ከዛ ትንኮሳው ተጠናክሮ ቀጠለ፣ ተኩሱም ተከተለ፡፡ ሄኔ ነው
እንግዲህ ‹‹አሸባሪው ማነው?!›› ብሎ መጠየቅ የሚገባው፤ ሙስሊሙ ነው ወይስ ኢህአዱግ ብሎ ምርጫ ማቅረብና ለማነጻጸር መሞከሩ
በራሱ ስህተት ነው፡፡
ያልተረዳነው
እምነትና ያልተረዳናቸው ምእመናኖች
እስልምና ሲባል ሀይማኖቱን ከሽብር፣ ከግድያ፣ከጭካኔ፣… ጋር የሚያያይዙት አሉ፤ ኢህአዴግም
ይህ የተዛባ አመለካከት በተወሰነ የህብረተሰቡ ክፍል ውስጥ እንደነበረ ስለሚያውቅ ሊጠቀምበት ሲጣጣር እየተመለከትነው ነው፤ ይህ
ግን ከሀይማኖቱ ህግጋቶች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፤ ሀይማኖቱ እንደውም በቅዱስ ቁርአኑ ላይ እነዚህን ሰይጣናዊ ተግባሮች
አጥብቆ እንደሚያወግዝ በግልጽ ተቀምጧል፤ ለምሳሌ በሱረቱል አል ማኢዳ ላይ ‹‹ አንዲትን ነፍስ የገደለ ሰው ሰዎችን ሁሉ እንደገደለ
ነው፤ ህያው ያደረጋት ደግሞ የሰው ልጆችን ሁሉ ህያው እንዳደረገ ይቆጠርለታል፤›› የሚል ሀቅ ተቀምጦ እናገኛለን፤ ስለዚህ አንድ
ሰው መሰል ተግባራትን የሚፈጽመው እስልምና ስለሚያዘው ነው ማለት አይቻልም፤ እንደውም እስልመና ከሚያዘው ውጪ በመፈጸሙ እስላም
ነው ሊባል ሁሉ አይችልም፡፡
በእስልምና ሀይማኖት መጽሀፍ ውስጥ አንድ እስላም በሶስት ነገሮች ላይ እንደማይደራደር በአንድ
ወቅት የሙስሊሞቹ ጠበቃ ከሆኑት ጠንራው ሰው አቶ ተማም አባቡልጉ ቃለምልልስ አንብቢያለው፤ ጠበቃው በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም
ለወጣው ‹‹ላይፍ›› እንዲህ ብለውት ነበር፡ ‹‹ በእምነት መጽሀፋችን
ላይ በሶስት ነገሮች በሀይማኖታችን፣ በሚስቶቻችንና በአገራችን ጉዳይ እንደማንደራደር ተጠቅሷል፡፡ ደምበኞቼ አገራቸውን የሚወዱት
የዜግነት ግዴታ ስለሆነባቸው ብቻ አይደለም፤ የሀይማኖትም ትዕዛዝ አለባቸው፡፡››
ጠበቃው በተከታዮቹ ንግግራቸውም የኮሚቴዎቹን ነጻነት በተደጋጋሚ ለማስረዳት ሞክረዋል፤ ደንበኞቻቸው
መብት ጠያቂ እንደሆኑና በሻማም ጭምር ተፈልገው የመጡ ጀግኖች እንደሆኑ አስረግጠው ተናግረዋል፤ የነ አቡበከርን ጉዳይ የያዙት ለሶስት
ነገሮች(ሙያ፣ ሀይማኖትና የሚከፈላቸው ገንዘብ) ሲሉ እንደሆነ በግልጽነት የሚናገሩት አቶ ተማም ጉዳዩን በመያዛቸው ይፈሩ እንደሆነ
ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ትልቅ የሞራል ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ነው፤ ጠበቃው የሚከተለውን ነበር ያሉት፡ ‹‹… እኔ የምፈራው ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ጉዳዩን በትክክል ሳልሄድበት
ቀርቼ አምላኬን እንዳላሳዝነው ብቻ ነው፤ ህይወቴ በፈጣሪ እጅ እንዳለች የማምን ሰው በመሆኔ ከእርሱ ውጭ የምፈራው ነገር የለም፡፡››
ከአቶ ተማም በተቃራኒው በእስልምና ስር የተጠለሉ ጥቂት አጎብዳጆችም እንዳሉ መካድ ግን አይቻልም፤
በስመ ‹‹ሙስሊም ነን›› የሚነግዱ ባለስልጣናት፣ ካድሬዎች፣ በመጅሊሱ ስር የተሰባሰቡ፣ጋዜጠኖች፣… በገዛ ወገናቸው ላይ በትር የሚያሰነዝሩ
ሆድ አምላኪዎች ናቸው፤ ለምስክርነት የማይበቁ ከንቱዎች ናቸው እንጂ የማይዘባርቁት ነገር የላቸውም፤ አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩት
ነገር ይሰቀጥጣል፤ ‹‹አርብ አርብ አንዋር እየተሰበሰቡ በመረበሽ መልስ አይገኝም… አንድም ቀን መንግስት ጣልቃ ገብቶ አያውቅም፣…
እኛም መንግስት እንዲገባ እድሉን አንሰጥም፣…›› አቤት!! ከወገናቸው የተለየ ምን ያህ እንጀራ ቢበሉ ነው እንዲህ ያለውን ንግግር
የሚናገሩት? የእውነት ሆዳምነታቸውን ለማረጋገጥ ከዚህ የተሸለ ማስረጃ የለም፤ ዘንድሮ መቼም የሀይማኖቱም የትምህርቱም ቆብ ዋጋ
አጥቷል፤ እነዚህ ሰዎች ህሊናቸውን አራት ኪሎ ላለው ጌታቸው አስረክበዋል፤ ደግሞ ህሊናቸውን አስረክበው አሻንጉሊትነታቸውን አምነው
ከተቀበሉ ቦሃላ ‹‹ማንንም ጣልቃ አናስገባም›› ብሎ ፈሊጥ ምን ይሉታል? የነሱ የነዋይ ጥያቄ በመመለሱም የሚሊዮን ሙስሊሞች ጥያቄ
‹‹ተመልሷል›› በሚል አፋቸውን ሞልተው ይከራከራሉ፤ ደግነቱ ሀይማኖቱንም ሰውነትንም የማይወክሉት እነዚህኞቹ የእውነት ጥቂቶች ስለሆኑ
በብዙሀኑ እውነት ፈላጊዎች እንጽናናለን፤ ደግሞም እውነት ስለማሸነፏ ጥርጣሬ እንዳይገባን፡፡ በመጨረሻም ጨካኙንና ይህንን ሁሉ ሰብዓዊ
መብታችንን የነፈገንን ኢህአዴግን ከእንግዲህ ሐራም!! ብናደርገው ስህተት ይሆን? ለማንኛውም በቀጣዩ የፕ/ር መስፍ ‹‹ነጻነት››
የተሰኘች ግጥም እንሰነባበት፡፡
ሰው የሚፋጅበት ምንድነው ነጻነት?
ሰነጻነት ሰው መሆን ነው፤
ሌላ ትርጉምም የለው፤
ዕፀ በለስን ቅርጥፍ አርጎ መብላት፤
ከገነት
ወጥቶ መንከራተት፤
ወይም ሌላ ገነት መስራት፣
በኻልዮ፣ በነቢብ በገቢር ሰው የሚልቅበት
ይኽው
ነው ነጻነት፤
ነጻነት
በሌለበት ማን ነው አስተማሪ?
ማንስ ነው ተማሪ፣መርማሪ፣አበጣሪ?
ነጻነት በሌለበት ማን ነው ሚቀመጥ ለዳኝነት?
ማንስ ነው የህጉ ባለቤት?
የማያምኑትን፣ የማይቀበሉትን እምቢ ማለት፤
ይህ ነው
ነጻነት ቅጣት ሌለበት፤
የሚያውቁትን፤የሚያምኑትን
መናገር፤
እስቲያንገሸግሸው ደስ የማይለውም ቢኖር!
ለጉልበተኛ
አለመገበር፤አለመንበርከክ፤
ነጻነትን
አውቆ እስቲረዳው የራሱን ልክ፤
ማንም
ከማንም አይበልጥም በነጻነት፤
ባሕርዩ ነው የሰውነት፡፡
ሰው በባሕርዩ ባርነትን አይመርጥም፤
ክብርን
በውርደት አይለውጥም፤
ባሪያ ሆኖ ከመክበር፣
ይሻላል በነጻነት መቸገር፤
ያልመረጡት ባርነት ይብሳል ከባርነት፤
ከታች
አዘቅት፣ ከላይ ዳገት፤
ሰው አያቆለቁልም ወዳዘቅቱ፡
ምንም ቢከፋ ዳገቱ ይጋልበዋል ለነጻነቱ፡፡
ወደግራ
ብሄድ ወደቀኝ፣
ማን ነው የሚከለክለኝ?
ነጻነት
ካለኝ!
ሰማዩን ብቧጥጥ፣ መሬቱን ብቆፍር፣
ማን ሊያግደኝ፣ ማን ሊደፍር!
ነፍሴ እያለች በዚች ምድር!
ሰው የመሆኔን ምልክት፣ ነጻነት፣
ማንም አውሬ አይነሳኝ ሳልፈቅድለት፣
ሰው መሆኔን ሳልክድለት፡፡
(ምንጭ፡
ዛሬም እንጉርጉሮ መጽሀፍ፣ ገጽ 122-123)

No comments:
Post a Comment