Wednesday, April 24, 2013

ከወደብ አልባነት ወደፕሬስ አልባነት


የዛሬይቱን  ኢትዮጵያ  የሚያስተዳድረው  ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ሀገራችንን ወደብ አልባ ብቻ ሳይሆን ፕሬስ አልባ የማድረግ ህልሙም የሰመረለት ይመስላል፡፡የእኛም ዘርፈ ብዙ አስተዋጾ ተደማምሮ  ቀጣዩ ጉዞ ወደ ጋዜጠኛ አልባነት እያመራ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በአሁን ሰዓት ኢትዮጽያን land locked ብቻ ሳሆን mouth locked country ብሎ መጥራት ፍጹም ስህተት አይመስለኝም፡፡ በሀገሪቱ ላይ የነበረው የነጻው ፕሬስ ጭላንጭል ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ተዳፍኗል፡፡ ጭላንጭሉን አምነው ሲከተሉ የነበሩ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞችም እራሳቸውን ከድቅድቁና አስፈሪው ጨለማ ውስጥ እራሳቸውን አግኝተውታል፡፡ እንደ ርዕዮት ዓለሙ፡እስክንድር ነጋ፡ውብሸት ታዬ፡… ያሉት ማረፊያቸው ከዝነኛው የቃሊቲ እስር ቤት ሲሆን፤ይህ እጣ ፈንታ እንዳየደርስባቸው የሰጉት ጥቂት የማይባሉት ጋዜጠኞች ደግሞ ስደትን መርጠዋል፤ ሌሎች የቀረነው ደግሞ ብዕራችንን ተነጥቀን፡አፋችን ተለጉሞ በገዛ ሀገራችን ላይ የባዕድነት ስሜት እንዲሰማን ሆነን በየጥጋጥጋችን ተወትፈናል፡፡
ዛሬ በዋነኝነት ብዕሬን ያነሳሁት ብዙ የተባለለትና የተባለበት የኢትዮጽያ ሚዲያ ስለገባበት ውጥንቅጥ ለመጻፍ አይደለም፤ ይልቅስ ከላይ በሶስት ምድብ ከከፈልኳቸው ውስጥ በመጨረሻዎቹ ሁለቱ ጋዜጠኞች/በስደት ላይ ያሉትና ሀገርቤት ውስጥ ከስራ ውጪ ያለነው/ ላይ የተሰማኝን የአብሰልስሎቴን ውጤት ለመሞነጫጨር እንጂ፡፡ለግዜው  እስር ቤት ያሉትን ማረሚያ ቤቶቻችን እስኪዘምኑ ከስቃያቸው ጋር እንተዋቸው፡፡ በመቀጠል በሁለቱ ምድብ ውስጥ ስላካተትኳቸው ጋዜጠኞች ስጽፍ ‹‹እንዴ! እስር ቤት ያሉትስ ቢሆኑ ይህንን ከማድረግ የሚያግዳቸው ምንድነው;›› የምትሉ የዋሖች ስለማትጠፉ፡ወዳጄ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ በአንድ ወቅት በማዕከላዊ እስር ቤት ሳለች የገጠማትን እዚህች ጋር ላጫውታችሁ፡፡
 ርዕዮት የግዜ ቀጠሮ እየተጠየቀባት በማዕከላዊ እስር ቤት የነበራት ቆይታ እንዲራዘም የተደረገበት ወቅት ነበር፤ታዲያ በአንደኛው ቀን ሊጠይቋት ከመጡት ወዳጆቿ ውስጥ አንደኛው  የመጣው ከባህር ማዶ ነበር፡፡ዜግነቱም ኢትዮጽያዊ አይደለም፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ምን እነዳነሳሳው አይታወቅም/የመንግስታችን ሰዎች ቢሰሙት እስረኞችን ለሽብር በማነሳሳት ወንጀል ይከሱት ነበር፡፡/ ‹‹እስር ቤቱ ውስጥ የምትዝናኑባቸው የጌም አይነቶች ምን ምን ናቸው;›› ሲል ይጠይቃታል፡፡ ይሄኔ ሊጠይቋት የመጡት ወዳጆቿ ይሄ ሰው እየጠየቀ ያለው ጋዜጠኛዋን ርዕዮትን ነው ወይስ ቤተመንግስት ውስጥ የሚቦርቁት የባለስልጣናት ልጆች በሚል አይነት ስሜት ይመስላል ተያይዘው ይስቃሉ፡፡ ሰውዬው በሳቃቸው ግራ ተጋብቶ ሲያበቃ በኢትዮጽያ እስር ቤቶች ውስጥ እንደዛ ያለው ነገር ቅዠት መሆኑን ያስረዱታል፡፡ጠያቂዋ ግን በዚህ አላበቃም ለሌላ ክስ የሚያበቃውን ጥያቄ በድጋሚ ሰነዘረ፤ ደብዳቤዎችን በመጻፍ እንደምትዝናና እና የምትጽፋቸውን ደብዳቤዎችም ከቤተሰብ ጋር መለዋወጥ እንደምትችል ይጠይቃታል፡፡ይሄኔ ግን መንግስታችን ብቻ ሳይሆን እኔም በወዳጄ ሞራል ላይ እየተረማመደ እነደሆነ በማሰብ ቅር ተሰኘው፡፡ ትሁቷ ወዳጄ ግን እንኳን ሊጠይቃት ለመጣው ለአክበሪዋ ቀርቶ በማዕከላዊ ለሚጨቀጭቋትና ለሚያሰቃዩዋት ‹‹ደህንነቶችም›› ምላሽ ከመስጠት ቦዝና አታውቅምና ፡ለጠያቂዋ በድጋሚ እንዲህ ያለው ነገር በኛ አገር እስር ቤቶች ውስጥ የማይታሰብ እንደሆነ አስረዳችው፡፡ከዚህ ቦሃላ ጠያቂዋ በእስር ቤቱ ግቢ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱም ላይ የሚቆይ በማይመስል ሁኔታ ተደናግጦ፡ እሱም አሸባሪ ተብሎ ከመታሰሩ በፊት ግቢውን ለቆ ሄደ፡፡ ርዕዮት በማዕከላዊ እያለች የህትመት ውጤቶችንና መጽሀፍትን ማግኘት ትችል ነበር፡፡አሁን ላይ ግን በቃሊቲ ምንም አይነት የቤተመጽሀፍት አገልግሎት አታገኝም፡፡ያኔ የደነገጠው ወዳጇ ይህንን ቢሰማስ ምን ይል ይሆን;!
የሀገሬንና የወዳጄን ጉድ ከጀመርን ማቆሚያም ስለማይኖረው፤ወደ ጉዳያችን እንመለስ፡፡ በስደት ላይ ያሉትና በሀገር ውስጥ ያለነው አብዛኞቻችን፤ስንሰራበት የነበረውን ሚዲያ ስንነፈግ፤ከሙያችን በመራቅ አርፎ መቀመጥን የተያያዝነው ይመስላል፡፡ እንዲህ ያለው ከሙያችን የመራቅ ሂደት በርካታ ምክንያቶች ሊደረደሩለት ይችላል፡፡ስንፍና፤ተስፋ መቁረጥ፤አማራጮችን አለማየት ወይም አቃሎ መመልከት፤በሌላ የግል ህይወት መጠመድ፤ፍራቻ፤ክህደት፤…ዝርዝሩ ከዚህም ይሰፋል፡፡
አንድን ጋዜጠኛ ለምን ፈራህ ብሎ ግብግብ መግጠም ባይቻልም፡የተቀሩት ምክንያቶች ግን ጋዜጠኝነትን ሙያዬ ብሎ ለያዘ ስው ብዙም ውሀ የሚያነሱ አይመስለኝም፡፡ከራሴ ስጀምር፡ሌሎች በርካታ ችግሮች በዙሪያዬ ቢኖሩም ዋነኛው ግን ስንፍና ይመስለኛል፡፡በዙሪያዬ ያሉ በርካታ ጋዜጠኞችም ይህንኑ ችግር ይጋራሉ፡፡እኔም ዛሬ ብዕሬን ሳነሳ ዋነኛው ግቤ በአደባባይ ቃል በመግባት ይህንን ስንፍና ማስወገድና ያሉትን አማራጮች ለመጠቀም ቃል ለመግባት ነው፡፡
ኢትዮ-ምህዳርም የካድሬዎች ውቃቢ በፈቀደ ቀን መዘጋቷ የማይቀር በመሆኑ፡እንደኔ እምነት እንደ ፌስቡክ /ሚናውን ማቃለል ፍጹም ስህተት ነው/ያሉትን ሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾችን መጠቀሙ ሌላኛው አማራጭ ነው፡፡ በአሁን ግዜ ብዙም ልፋት የማይጠይቀውን የጡመራ መድረክ/ብሎግ/ ከፍቶ ሀሳብን ማንሸራሸርም ይቻላል፡፡ ይህንን ማድረጋችንም በርከት ያሉ ፋይዳዎች እንደሚኖሩት በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮ ትተን የራሳችንን ብቻ እንኳን ብንመለከት፡እንደ ፌስቡክ ያሉት ማህበረሰባዊ ድረ-ገጾች ያመጡት ውጤት አለ፡፡ ለዚህ እነደ ጥሩ ማሳያ ሊወሰድ የሚችለውደግሞ የኢትዮጽያ ሙስሊሞች እያካሄዱት  ያለው ሰላማዊ ትግል ነው፡፡እነዚህ ሙስሊሞች ዋነኛ የመረጃ መለዋወጫ መንገዳቸው ፌስ ቡክ ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪ በቀደመው ግዜ ጋዜጠኛ የነበሩም ያልነበሩም በርካታ ፌስ ቡከሮች በገጻቸው ላይ በሚጽፏቸው መጣጥፎች በርካታ ተከታዮችን አፍርተዋል፤አንዳንዶቹም ወደ ጋዜጠኝነቱ ጎራ እየተቀላቀሉ ይመስላል፡፡ ከኔ ጋር የፌስቡክ ጓደኛ ከሆኑትን ትጉ ጻሀፊዎች ውስጥ የተወሰኑት ለመጥቀስ ያህል፡ ዞን9፤ተስፋዬ ገ/አብ፤አብርሀ ደስታ፤መስፍን ነጋሽ/አንዳንዶቹ ብቅ ብቅ እያሉ ቢሆንም የተናፋቂ ባልደረቦቹ መጥፋት ግን እንቆቅልሽ ሆኖብኛል/፤ውብሸት ታደለ፤አቤ ቶኪቻው፤ህይወት እምሻው፤…ጥቂቶቹ ናቸው፡፡አነኚህ ፌስቡከሮች ሀሳባቸው ተስማማንም አልተስማማንም፤ መድረኩን በአግባቡ እየተጠቀሙበት ነውና ሊመሰገኑ ይገባል ብዬ አምናለው፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ይህንን በማድረጋችን፤በበርካቶች ውስጥ የያገባኛል ስሜትን ማስረጽ ይቻላል፤የማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎችንም ከተራ አሉባልተኝነት መከላከል ይቻላል፡፡አማራጭ የሚዲያ ባህልን ይፈጥራሉ፤የአንባቢውን የሚዲያ ረሀብ ያስታግሳሉ፤ሀላፊነታችንንም እንወጣባቸዋለን፡፡
ስለዚህ፡ ‹‹አሸባሪ›› የሚለው የክብር ካባ ተደርቦልን ወደ ቃሊቲ ከማምራታችን በፊት/አዳዲሶቹ እስር ቤቶች ይለቁ እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመታሰር ተስፋ አለው/ ከመታሰሬ ይህን ያህል ቀን በፊት እያልን በመጻፍ፤የሙያ ሀላፊነታችንን ለመወጣት የየራሳችንን አሻራ ብናኖር ይበጃል እላለው፡፡አለበለዚያ ግን ገቢ እስካገኘንበትና እስከተከፈለን ብቻ  የምንቆይበት ጋዜጠኝነት ለነጋዴነት የተሻለ ቅርብ ነው፡፡
እኔ ከዛሬ ጀምሮ፡ እንደ ኢትዮ-ምህዳር ያሉት እንጥፍጣፊዎች እስኪደርቁም ሆነ  የፌስቡክ ገጼን ጨምሮ የሞሀ ገጽ /www.yemohagets.blogspot.com/ በተሰኘው የጡመራ ገጼ ላይ የተሰማኝን ለማስፈር ስንፍናዬን እንደተገፈፈ ስነግራቹ እነ ዙከንበርግን እንጂ የብሮድካስት ባለስልጣንን ተማምኜ እንዳይመስላቹ፡፡  


No comments:

Post a Comment