ቃሊቲ ግቢ ብቻ ሳይሆን ሀገር ነው፤ የአንድ ሀገር እውነታዎችና ሰዎቿ ሁሉ በዚህ ይገኛሉ፤
ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ብቻ አይደለም ቃሊቲ ማሰቃያ፣ ማመናጨቂያ፣ ማጉላያ፣ ማዋከቢያ፣ መበቀያ፣ … ጭምር ነው፤ ግቢው በጣም ሰፊ ነው፤
በስፋቱ ልክ ብዙ እውነታዎችን ታጭቋል፡፡ በአንድ ወቅት ርዕዮት ዓለሙንና ፈትያ መሀመድን ጠይቀን ስንወጣ፣ አንድ ሰው (የፈትያ
ጠያቂ ይመስለኛል) ‹‹አንተ ይህ ግቢ እኮ በጣም ሰፊ ነው፤ ከእስር ቤትም በላይ ነው፤ ለምን ሌላ ነገር አይሰሩበትም? ወይ ደግሞ
በተካኑበት የመሬት ችብቸባ በሊዝ ይሽጡት፤›› አለኝ፤ እኔም ‹‹ምን ይሰሩበታል! የሚሰራን ሰው እያመጡ ያኮላሹበት እንጂ!›› ስል
መለስኩለት፡፡ ቃሊቲ እርግጥ ነው ሰፊ ነው፤ በስፋቱ ልክ ከክፋት ባሻገር አንዳንድ ደግነቶችንም በዙሪያው አቅፏል፡፡ በክፋቶቹ ውስጥ
ደግሞ ኢህአዴግ ከፍሎ የማይጨርሳቸው እዳዎች እዚህም እዛም አፍጠው
ይታያሉ፡፡ እኔ እውነታዎቹን ባየሁና በሰማሁ ቁጥር ‹‹ኢህአዴግ እዳ አለበት!›› እንድል የሚያስገድዱኝ ናቸው፡፡ ርዕሱ እንዳይንዛዛብኝ
ብዬ እንጂ ‹‹ ኢህአዴግ እዳ! ፣ፍዳ!፣ ግፍ!፣ ጡር!፣… አለበት!!›› ብል ምንኛ ሀሳቤን በገለጸልኝ! ለማኝኛውም እነዚህን የኢህአዴግ ግፎች፣ ፍዳዎች፣ እዳዎች፣ጡሮች፣… ከዛሬ
ጀምሮ፣ ‹‹ኢህአዴግ እዳ አለበት!›› በሚል አብይ ርዕስ ስር የተለያዩ ንዑስ ርዕሶችን እየሰጠን የቃሊቲውን እውነት እንጨዋወተዋለን፡፡
ዛሬ ግን ላስቀድመው የነበረውን ክፍል በአግባቡ ማስኬድ ተስኖኛል፡፡ ከሰሞኑ በቃሊቲ እነ ርዕዮት
ዓለሙ፣ ፈትያ መሀመድ፣እማዋይሽ፣… ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍና እነሱም እየወሰዱት ያለው እርምጃ፣ እጅግ በጣም ቀደም ብዬ ልጽፍበት
ያሰብኩትን ‹‹ርዕዮታዊ መንፈስ…›› በተረጋጋ ሁኔታ እንዳሰፍረው የሚያደርግ አይደለም፡፡ ሰሞነኛው ቃሊቲ ከርዕዮታዊው መንፈስ ጽሁፌ
አናጥቦኛል፡፡ በዛሬው ጽሁፌ ትንሽ (ኽረ በጣም!) ልዘባርቅ እችላለው፤ ሲፈጸም የከረመው ጉዳይ ያልተለመደ ባይሆንም፣ መረን ለቀቀ!
በዛ! ከአንድ መንግስት አይደለም መንግስት ባለበት ሀገር ላይ እንኳን ሊፈጽሙት የሚከብድ ውንብድና ነው!
መቼም እኔ ዛሬ ስዘባርቅ የምንደው የጽሁፍ ህግ እንደነሱ ሁሉን ገዥ የሆነውን የሀገር ህግ
ከመናድ አይከፋም፤ ግፋ ቢል ጽሁፌ ስነ ጽሁፋዊ ውበቱን ቢያጣ ነው፤ ግፋ ቢል በቋንቋ ምሁራኑ ቢተች ነው፤… ምንም ቢሆን ለዛሬ
ግድ የለኝም፤ ዛሬ የምዘባርቀው ብዙ እውነት በመኖሩ፣ እሱኑ ማስተላለፉ ላይ አተኩራለው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ወቅቱ እኮ በደምፍላት
ጭምር የሚያጽፍ ነው!›› ሲሉኝ፣ አይገባኝም ነበር፤ አሁን ግን እኔ እራሱ ደምፍላት ውስጥ እንዳለው ይሰማኛል፤ ታዲያ ምክንያታዊነት
ገደል ገብቶ ወገቤን ይዤ እሞጣሞጣለው ማለት አይደለም፤ እንዲያማ ከሆነ፣ ከነሱ በምኑ ተሻልኩት? ለማንኛውም ቀጠልኩኝ፡፡
የነ ርዕዮትን የእስር ቤት አያያዝ ሳስብ አሜሪካዊው ሻለቃ ናዲል ሀሰን ድንገት ትዝ አለኝ፡፡
ይህ አሜሪካዊ ወታደር የሰራው ወንጀል እጅግ በጣም ሰቅጣጭ የሚባል ነው፤ አይደለም ሲፈጽሙት ሲሰሙትም ያማል፡፡ ይህ ወታደር በፈረንጆቹ
ህዳር ወር 2009 ዓ.ም ላይ አብረውት የሚሰሩ 13 ወታደሮችን ተኩሶ ይገላል፤ በተቀሩት 32 ወታደሮች ላይ ደግሞ የግድያ ሙከራ
ይፈጽማል፡፡ ታዲያ በእስር ላይ የሚገኘው ናዲል፣ ከተያዘበት 2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም ያለፈው ወር ድረስ፣ ከ
300.000 የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚጠጋ ደሞዙ ሲከፈለው ነበር፤ ህክምናን ጨምሮ በእስር ቤት ውስጥ ያሉ መብቶቹን በሙሉ ይጠቀማል፡፡
እንዲህ ያለው እውነት ለኛ ኢትዮጵያውያኑ አጃኢብ ነው!
መቼም ‹‹እኛ ጋርስ እንዴት ይሆን?›› ብሎ መጠየቅ በራሱ በብዙሀኑ ስነ ልቦና ላይ እንደመጫወት
ይቆጠራል፡፡ አስታውሳለው ርዕዮት አይደለም ከታሰረች ቦሃላ ሊከፈላት፣ መታሰሯ እንደተሰማ ነው ቀድማ የሰራችበትን ደሞዝ እንኳን
የከለከሏት፡፡ አስታውሳለው ‹‹ፍርድ ቤት›› ጉዳይዋን ከሰዓት ልንከታተል፣ ጠዋት ላይ ሟቹ ጠቅላያችን ፓርላማ ተገኝተው ‹‹አሸባሪ››
እያሉ ሲጠሯቸው ነበር፡፡ አስታውሳለው ርዕዮት በህመም በምትሰቃይበት ወቅት ወደ ህክምና እንኳን ሊወስዷት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ርዕዮት
ትምህርቷን እንዳትማር ሰበብ ሲያመርቱና እርስ በርሱ የሚጋጭ አስተያየት ሲሰጡባት ነበር፤ ቀደም ብሎም እዛው ማረሚያ ቤቱ ውስጥ
እራሳቸው ከሳሽ እራሳቸው መስካሪ በነበሩበት ሁኔታ ከሰዋት ነበር፤
ሌላም ሌላም…፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ ይኽው እንደሰማነው መብቱን ብቻ በአግባቡ ከሚጠቀመው አሜሪካዊው ሻለቃ በተቃራኒ፣
የኛዋ ኮ/ል በከባድ ወንጀል ተይዘውም ስልጣናቸውን እንደተሸከሙት ከአጥሩ ውስጥ ሆነው የነ ርዕዮትንም መብት በመንጠቅ ጭምር ተጨማሪ
ግዙፍ ወንጀሎችን ይሰራሉ፤ ወይስ እነዚህ ሰዎች ወደ ወህኒ የሚወርዱት በተቀያሪነት ለማሰቃየት ነው? ያደለው ከነ ስልጣኑ ይታሰራል!
ለነገሩ እዚህች ሀገር ላይ ሞት እንኳን መች ከስልጣን ይለያል?!
እኔ የምለው? እነዚህ ባለስልጣኖች መቼ ነው ቆይ መፈራራታቸውን የሚያቆሙት? ከውጪ እሰከ እስር
ቤት ድረስ በጉያቸው እንደሸሸጓቸው ነው፡፡ ታሳሪ ባለስልጣናቱም የፓርቲያቸውን ስስ ብልት ስለሚያውቁ ይመስላል ዛሬም በማሽቃበጥ
ምህረትን ይሻሉ፤ ፍርድ ቤት በቆሙበት አጋጣሚ ለፓርቲያቸው ከንቱ ውዳሴ በማቅረብ አፈጻጸምን ያማርራሉ፤ ደግሞ እኮ ኮሎኔሏ ‹‹አንቺን
ብሎ ጋዜጠኛ!...›› አሏት አሉ፤ የፓርቲያቸው ልሳኖች ‹‹ወንጀለኛ›› ብለው ሲሏቸው ያጠየቁትና ጉዳዩን በሚገባ የዘገቡላቸው የርዕዮች
የስራ አጋሮች መሆናቸውን ማን በነገራቸው!
እነ ርዕዮት በሴትየዋ፣ በእስር ቤቱ ጠባቂዎች፣ በታሳሪ ሰላዮች፣ በእስር ቤቱ ቢሮክራሲ፣…
መብታቸው ተነፍጎ መሰቃየታቸው ሳይበቃ፣ ርዕዮት ጭራሽ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ እንዳይጠይቃት ተከለከለች፡፡ ይሄኔ ነው እንግዲህ የተከማቹት
ስቃዮች ጫፍ የደረሱትና እሷንም ለረሀብ አድማ እርምጃው ያበቃት፡፡ ታዲያ ስቃዩ ከርዕዮት ባሻገር በሌሎችም ላይ ይፈጸም ነበርና
ርዕዮታዊውን መንፈስ በመከተል፣ ሌሎች የተወሰኑ ሴቶችም የረሀብ አድማውን ከአዲሱ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ ይህን ጽሁፍ እስካስገባሁበት
መስከረም 4 ምሽት ድረስ ተቀላቅለው ምግብ አልበሉም ነበር፡፡
ከነዚህ ውስጥ አንዷ የአወሊያዋ ተማሪ ፈትያ መሀመድ ናት፡፡ በሴቶች ዞን ብዙ አስገራሚ ህይወት
ያላቸው ጠንካራ ሴቶች ቢኖሩም፣ ርዕዮታዊውን መንፈስ በመጋራት በኩል የምትጀግንብኝ ሌላኛዋ እስረኛ ብዙም ያልተወራላት ፈትያ መሀመድ
ናት፡፡ የታናናሾቿ ሀላፊነት ያለባት የ22 ዓመቷ ፈትያ ለእስር የተዳረገችው የእናቷን ሀዘን እንኳን በወጉ ሳትጨርስ ነበር፡፡ ከሙስሊሙ
ማህበረሰብ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከበርካታ ሴቶች ጋር በማዕከላዊ ከ ሶስት ወር በላይ የታሰረችው ፈትያ፣ ወደ ቃሊቲ ያመራችው ግን
ብቸኛዋን ነበር፤ አሳሪዎቿ ሌሎችን በሚፈልጉት መንገድ ሲፈቱ ፈትያ ግን የራሷን መንገድ በመምረጧና የአይበገሬነት መንፈሷ አብሯት
በመኖሩ ሳትፈታ ቀርታለች፤ እስከ አሁንም የፍርድ ሂደቱን በመከታተል ላይ ናት፡፡
ፈትያ በመጠየቂያ ሰዓቷ ላይ የሚታይባት በራስ የመተማመን መንፈስ የሚገርም ነው፤ ‹‹በልኬ
ጉድጓድ ቆፍረው እንኳን ቢቀብሩኝ ከአላማዬ ንቅንቅ አልልም፤ የማደርገው ነገር ሁሉ የማምንበትን ነው፤›› ትላለች፡፡ ጠያቂዎቿ በመጡ
ግዜም ሀዲስ በማውራት የምታበረታቸውና የምታጠነክራቸው ከሽቦው ውስጥ ያለችዋ ፈትያ ናት፡፡ እንደ ርዕዮት ሁሉ የንባብ ማዕቀብ የተጣለባት
በመሆኑና በሁኔታው እጅግ ከመቆጨቷ የተነሳ፣ ‹‹እዚህ ያለ ንባብ ከምታሰር፣ንባብ ተፈቅዶልኝ ማዕከላዊ እንደፈለጉ ቢያሰቃዩኝ ይሻላል፤››
ስትል አድምጫለሁኝ፡፡ ታዲያ ፈትያ የምታደርገውን ነገር ሁሉ አምናበት የምታደርገው እንጂ ማንም እንዲያወራላት እንደማትፈልግ የሰሞኑ
የረሀብ አድማዋ አንዱ ማሳያ ነው፤ በፍጹም እንዲወራ እንዳልፈለገች አውቃለሁኝ፤ ሆኖም ግን ‹‹መወራት ያለበት ሁሉ መወራት አለበት››
በሚለው ስለማምን ለማውራት ተገድጃለው፡፡
ታዲያ እንደ ርዕዮት፣ፈትያ፣እማዋይሽ፣ሂሩት፣ጫልቱ፣… ያሉት ሴት እስረኞች፣ ከሌላው እስረኛ
ሁሉ በተለየ ሁኔታ ልዩ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን፣ የሚጠየቁበት ሰዓትም እንዲሁ በጣም አስቀያሚ የሚባል አጭርና አድልዎው ያፈጠጠበት
ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች (በተለይ ርዕዮትና ፈትያ) እያንዳንዳቸው በሁለት ጠባቂዎች ግራና ቀኝ የሚጠበቁ ሲሆን፣ ከጠያቂዎቻቸው ጋር
በሚጨዋወቱበት ግዜም የጠባቂዎቹ ጆሮ አፋቸው ስር ይለጠፍና አንዳንድ ግዜ እስረኞቹ አፋቸው ስር ተጨማሪ ሁለት ጆሮ ያላቸው ሊመስለን
ይችላል፡፡ ፖሊሶቹ ምን ማውራት እንዳለብህ እንኳን ሊወስኑልህ ይሞክራሉ፤ ያልጣማቸውን ወሬ ሁሉ ‹‹አይቻልም!›› በማለት ያስቆማሉ፤
ሳቅ ጨዋታችን ያበግናቸዋል፤ በራሳቸው የማይተማመኑ ስለሆኑም እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ከራሳቸው ጋር ያያይዙታል፤ ስለዚህ ሁሉ ነገራቸው
ነቅቶ አፋችን ላይ ያርፋል፤ እንግዲህ የአፍ ትራፊክ መሆናቸው ነው፡፡
እንዲህ ባለው ሁኔታ ብዙ ግዜ በጠባቂዎቹና በጠያቂዎቹ መካከል ግጭቶች ሲፈጠሩ አስተውያለው፡፡ ከነ ርዕዮት ጋር በተመሳሳይ ክስ የታሰሩት ወንወዶች እንኳን ያለጠባቂዎች
አጀብ በየትኛውም ሰዓት ሰፋ ላለ ግዜ እንዲጠየቁ ሲፈቀድላቸው፣ እነ ርዕዮት ግን ዛሬም ከሰኞ እስከ አርብ ከ6 ሰዓት ጀምሮ ለ
አስር ደቂቃ፣ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድን በተመሳሳይ ሰዓት ለ30 ደቂቃ ይጠየቃሉ፡፡ በዚህች ደቂቃ ውስጥም ‹‹ፖለቲካ ታወራላችሁ››
በሚል ይፈርጃሉ፤ ቃሊቲ ውስጥ ፖለቲካ ማውራትም እንግዲህ ወንጀል ነው፡፡
‹‹የአስር ደቂቃ ፖለቲካ›› ነው ያለችው እህቷ እስከዳር? ታዲያ ይህቺው ሰዓት በር ላይ ባሉ ቢሮክራሲዎችና ትንኮሳዎች
መሽራረፏንም ጭምር ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
በነገራችን ላይ በቃሊቲ ያሉ የነ ርዕዮት ጠባቂዎች (ሁሉንም አይመለከትም) ትዕዛዝ ፈጻሚዎች
ስለሆኑ፣ እንደ አለቆቻቸው በእስረኞቻቸው መካከል ያለው አንድነትና የሚያሳዩት ጥንካሬ ያርዳቸዋል፡፡ የጠያቂዎቻቸው ማንነትና ብርታት
ያበሳጫቸዋል፤ እንደ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም፣ ዶ/ር ሽመልስ ተ/ጻድቅ፣ ዶ/ር ያዕቆብ ሀ/ማሪያም፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣… ላሉ
ታላላቅ ጠያቂዎች እንኳን ክብር የላቸውም፡፡ ለታሳሪ ቤተሰቦችም ቢሆን ትንሽ ትልቅ ሳይሉ፣ ከሰው እንዳልተፈጠሩ ሁሉ ምግባራቸው
የሚያስቀይም ነው፡፡ ታዲያ አንዳንድ የተባረኩ ፖሊሶች ቢኖሩም፣ መልካምነታቸው ስለማይፈለግ ለቅጣት ይዳርጋቸዋል፤ አልያም በቅርቡ
እንዳደረጉት ከቦታ ቦታ ያዘዋውሯቸዋል፡፡ በቃሊቲ ያሉ የስርዓቱ አገልጋይ ፖሊሶች ዘወትር በማበሳጨትና በማሰላቸት ጠያቂ እንዳይኖር
ለማድረግ ብዙ ይጥራሉ፤ የሚሸነፍላቸው አጥተው ሲብስባቸው፣ በፖሊስ ልብስ የተሸፈነው ትክክለኛው ማንነታቸው ይወጣና መተናኮስ ይጀምራሉ፡፡
መቼም እንዲህ ያለውን አስቀያሚ ሁኔታ ወደ ቃሊቲ ጎራ ያለ (በተለይ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችን እና ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቆ ጋር
በተያያዘ የታሰሩትን ጠያቂ) ሁሉ ያውቀዋል፡፡
ትንኮሳው ገና ከመግቢያው በር ላይ ነው የሚጀምረው፤ ስድስት ሰዓት ሆኖ ‹‹ልዩ›› ጠያቂዎች
በር ላይ ተኮልኩለን በምንጠብቅበት ሰዓት የዕለቱ ተረኛ ይመጣና ጮክ ብሎ! ‹‹እ! ግንቦት ሰባቶች ናችሁ?!...እናንተ ሁሉ ግንቦት
ሰባት ናችሁ?...›› ይልና እያጉረመረመ ወደ ውስጥ ይዞን ይዘልቃል፡፡ መቼም አንባቢዎቼ ‹‹እና የናንተ ምላሽ ምንድነው?›› የሚል
በሰላማዊ ሀገር ላይ የሚጠየቅ የዋህ ጥያቄ ትሰነዝሩ ይሆናል፤ በቃ ቃሊቲ እነሱ ከሚፈልጉት ውጪ ያንተ ምላሽ ቦታ የለውም፤ እዚህ
የፈለጉትን ነህም አይደለህምም፤ እንደፍላጎታቸው ይወሰናል፤ ገና በር ላይ ሲጠራ ‹‹አይደለሁም!›› ብለህ ሙግትህን ልትጀምር ስታስብ
እንዳትገባ ይከለክልሀል፡፡ እነሱ እንዲህ ያለውን ስያሜ የሚለጥፉብንና ጮክ ብለውም የሚጠሩን እንድንሸማቀቅና የአከባቢው ሰውም ጭምር
እንዲፈርጀን ነው፤ እውነታው ግን ከዚህ በተቃራኒ ቃሉ ለቀልድ ጭምር ውሎ፣ በስድስት ሰዓት የምንሄድ ጠያቂዎችን፣ ‹‹ እ!..አንቺ
ደግሞ ስንት ቁጥር ነሽ? መቼም ዘንድሮ ጨዋታው በቁጥር ሆኗል፤…›› በሚል ያስፈግጉናል፡፡
አንድ ግዜ እንዲህ ባለው ሁኔታ ወደ ውስጥ ከዘለቅን ቦሃላ እየተጨዋወትን እና እየተሳሳቅን
እነ ርዕዮት ጋር ከደረስን ቦሃላ፣ ‹‹እሺ እንዴት ነሽ ግንቦት ሰባት?…›› እየተባባልን ሰላምታ ተለዋወጥን፤ ይሄኔ በዕለቱ የርዕዮት
ጠባቂ የነበረችው እሳት ጎርሳ እሳት ልሳ ‹‹ለምንድነው ስርዓት የማትይዙት?...›› በሚል ያልሰማናቸውን እና ልገልጻቸው የሚከብዱኝን
አስቀያሚ ቃላት ደረደረች፤ እኛም ጥፋታችን ምን እንደሆነ ጠየቅናት፤ ‹‹ በቃ! ምንድነው ግንቦት ሰባት ነን ምናምን እያላችሁ የምትሉት?...››
አለችን፡፡ ‹‹የኔ እህት አትበሳጪ ይህንን ስያሜ የሰጡን በር ላይ የቆሙት ያንቺው ጓደኞች ናቸው፤›› አልኋት፡፡ መግባባት ግን
አልቻልንም፤ እሷም ይበልጥ ተበሳጭታ ተጨማሪ ነገሮችን ቀባጠረች፡፡ በሌላኛው ቀን ስንመጣ በዚህ ጉዳይ ርዕዮትም እኛም ላይ በማረሚያ
ቤቱ ክስ እንደመሰረተችብን ሰማሁ፡፡
በሌላኛው ቀን እንዲሁ አባት አቶ ዓለሙ፣እስከዳር፣ስለሺና እኔ ሆነን ርዕዮትን ልንጠይቃት ሄድን፡፡
ያለችውን አጭር የመጠየቂያ ሰዓት መሻማት ስላለብን እኔና ስለሺ ቀድመን ትንሽ አወራናትና ቦታውን ለሁለቱ ለቀቅን፤ ከዛም እነሱ
እስኪያወሯት እኔና ስለሺ አጠገባችን ባገኘነው እንጨት ላይ ቁጭ አልን፤ ወዲያውም አንዲት ፖሊስ ከውስጥ ወጥታ ወደ አጠገባችን መጣችና
ስለሺን ‹‹አሁን እዚህ ተዘፍዝፈህ ሰዓትህን ግደልና ቦሃላ ሰዓት አለቀ ብለህ አፍህን ትከፍታለህ!›› ብላ እሷው አፏን ከፈተችው፡፡
ለካ ይህቺው ሴት ሌላ ግዜም ታስቸግረው ኖሯል፣ ‹‹አንቺ ሴትዮ ለምንድነው የማትተዪኝ?›› ሲል አጭር ምላሽ በጥያቄ አቀረበላት፤
ከዚህ ቦሃላ እስክንወጣ ድረስ ያለማቋረጥ ትለፈልፍ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ተናዳፊዎች ያሉበት ነው ቃሊቲ፡፡ ቃሊቲ ከዚህም በላይ
ነው፡፡
ስለሺ ሀጎስ (የርዕዮት እጮኛ) የቃሊቲውን ግፍ በመቅመሱ በኩል ግንባር ቀደሙ ነው፤ የትንኮሳ
ሰለባ ከሆነባቸው ይልቅ ያልሆነባቸውን ግዚያቶች መቁጠሩ ይቀላል፤ ከ አራት ኪሎ እስከ ቃሊቲ ያለውን አስቀያሚ መንገድ ያለማቋረጥ
ለሁለት ዓመታት ያህል መመላለስ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ የሚያውቀው፣ ለአንድም ቀን ቢሆን ቃሊቲ ደርሶ የተመለሰ ሰው ነው፡፡
በአጭሩ ለመግለጽ፣ የአንድ ቀን የቃሊቲ ደርሶ መልስ አንድን ሙሉ ቀን ያበላሻል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ስለሺ ርዕዮት ቃሊቲ ከገባችበት
ግዜ አንስቶ፣ ለሁለት ዓመታት ያህል በየቀኑ ቀኑን ሲያጣ ነበር ማለት ነው፡፡አባት እና እናትም ቢሆኑ በማረፊያ ግዚያቸው የዚሁ
ስቃይ ሌሎቹ ሰለባዎች ናቸው፤ እህቷ እስከዳር ዓለሙም በተለይ ስራዋን ካጣችበት ግዜ አንስቶ ቀኖቿን እየገበረች ትገኛለች፡፡ በጥቅሉ
እሷ ከታሰረችበት ግዜ አንስቶ ያለውን እድሜውንና ህይወቱን ለቃሊቲው መንግስት ገብሯል፡፡ ግን ታዲያ ሁኔታዎች እንዲህ ሆነው ለዘላለም
አይቀጥሉም፡፡
ስቃያቸው በመመላለስ ብቻ ቢያበቃ ጥሩ ነው፤ ግን እውነታው እንደዛ አይደለም፤ በየግዜው ለሰው
ልጅ ከመቻል አቅም በላይ የሆኑ ትንኮሳዎች፣ ግልምጫዎች፣ጉንተላዎችና ስቃዮች አሉ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ጓንታናሞ በሆነው
ማዕከላዊም ለሁለት ወራት ያህል አሰቃዩት፡፡ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ
ግን ለፍቅሩ ያለውን የመቻል ጥግ ማንም ሊደርስበት አልቻለም፤ ወደፊትም እንደማይሳካ በልበ ሙሉነት ለመናገር እደፍራለው፡፡ እንዲህም
ሆኖ ስለሌሎች ስቃይና መብት መቆርቆሩን ያልተወ ቅን አሳቢነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ልጅ ነው ስለሺ ሀጎስ ማለት፡፡ አሳሪዎቻቸውም
የርዕዮትና የስለሺ ነፍስ ምን ያህል እንደተቆራኘች ስለሚያውቁም ነው ብዙ ግዜ በፍቅሯ ስቃይ የሚመጡባት፤ አሰሩት፣ገረፉት፣አጎሳቆሉት፣…
ለመናገር የሚከብዱ ብዙ ነገሮችን ፈጸሙበት፤ ግን ታዲያ የጋራ እምነታቸውን በማስቀየር ሊያንበረክኳት አልቻሉም፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ ዋነኛ መነጋገሪያ የነበረው የርዕዮት የረሀብ አድማ ማድረግ ነው፤ አድማው ሌሎች
በርካታ ስቃዮች ከጀርባው ቢኖሩትም፣ ለመጨረሻው ውሳኔ ያበቃት ግን እንደቀደመው ግዜ እንዳትጠየቅ መደረጉ ነበር፤ የረሀብ አድማዋን
አጠናክራ ከገፋችበትና ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን ሲበቃ ግን፣ ሌላ ሰበብ ተፈጠረ፤ ‹‹እኛ እንዳትጠየቅ ያልነው በእህቷ
እስከዳርና በእጮኛዋ ስለሺ ነው›› ሲሉ ሌላ የለመዱትን የውሸት አክሮባት ሰሩ፡፡ እኔ ግን ይህቺም ሰበብ ብትሆን በመበለጣቸው ለሌላ
ተጨማሪ በቀል ሲሉ እንደፈጠሯት አስባለው፤ የማይሆን ክስ በመፍጠር የሚዋደዱ ነፍሶችን ነጥለው ለተጨማሪ ሰቀቀን መዳረግ፡፡ ለስለሺም
ሆነ ለእስከዳር አሁን ባለው ሁኔታ ርዕዮትን ጨርሶ አለማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ለአንድም ቀን ቢሆን አለመተያየታቸው ከባድ ሰቀቀን
ነው፤ ለርዕዮትም እንዲሁ፤ ነገር ግን ይሄ እስከ አሁን ካለፉት መከራ የማይብስ በመሆኑ፣ እምነታቸውን አይቀይረውም፤ የበላይነታቸውንም
አይነጥቀውም፡፡
በዚህ ጨካኝ ውሳኔያቸው ባለመርካታቸውም፣ አርብ መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም ህግ ያውቃሉ፣የህግ
ሰዎች ናቸው በሚል ወደ ቃሊቲ ጥያቄ ሊያቀርብ የሄደውን ስለሺ ከ ስምንት ሰዓት እስከ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ድረስ በእስር አቆይተው
የተለመደውን ህገ ወጥ ተግባራቸውን ሲፈጽሙበት ውለዋል፡፡ እንዲህ ያለው እገታ በስለሺ ላይ ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤
ለምዶታል፤ ቃሊቲ የሚስቱ ብቻ ሳይሆን የስቃዩም ጭምር መኖሪያ ከሆነ ከራረመ፡፡
ለኔ ግን የሰሞኑ እርምጃቸው ስርዓቱ ምን ያህል እንደዘቀጠና የግፋቸው ጉዞ ምን ያህ ተጠናክሮ
እንደቀጠለ ነው የሚነግረኝ፡፡ የቃሊቲ አዛዥ ናዛዦችም ከህግ በላይ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ባስተውልም፣ አሁን ግን የራሳቸውን አምባገነናዊ
ስርአት በቃሊቲ እንዳቋቋሙ ይሰማኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች እራሳቸውን ከህግ በላይ አድርገው በሚቆጥሩበት ሀገር ላይ እንዴት የታሳሪዎችን
ህግ ሊጠብቁ ይቻላቸዋል? አንድ ማሳያ ልጥቀስ፤
በአንድ ወቅት የርዕዮትን ችሎት ልንከታተል በልደታ ‹‹ፍርድ ቤት›› ተገኝተናል፤ ችሎቱ እንዳለቀም
እነ ርዕዮትን የሚወስዳቸው መኪና እሰኪመጣ እንዲሁም ሌሎች እስረኞች እስኪሟሉ በግቢው ውስጥ ወዳለ ማረፊያ ቦታ ይወሰዳሉ፤ ይሄኔ
እንደ ሁልግዜውና እንደ ግቢው ልማድ፣ ቤተሰቦቿ ራቅ ብለው ቆመው ይሰናበቷታል፤ ሁኔታውን ያስተዋለው አንድ የፖሊሶቹ ሀላፊ (ቃሊቲም
ቢሆን ቤተሰቡን በደንብ ያውቀዋል፤ጥላቻውንም በተደጋጋሚ ይገልጻል፤) ፊቱን አጨማዶና ድምጹን ጠንከር አድርጎ ‹‹ዞር በሉ ከዚህ!...
እናንተንም ሰብስቤ ነው የማስገባችሁ!›› ይላቸዋል፤ እነሱም ያሉበትን ግቢ ስም አምነው በነጻነት ፈታ ብለው እየሳቁ ‹‹አረ ባክህ?!››
ይሉታል፤ እሱም በእርግጠኝነት ኮራ ብሎ ‹‹ማሪያምን አስገባቹሀለው!›› ብሏቸው አረፈው፡፡ በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ሆኖ እንዲህ
የሚል አንድ የፖሊሶች ሀላፊ ሀላፊ፣ ቃሊቲ ውስጥ ደግሞ ከበታቹ የሚያዛቸውን ጨምሮ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመቱ አይከብድም፡፡
ያም ሆነ ይህ፣ ርዕዮትን ከያዘችው የበላይነት መንገድ ማንም ሊመልሳት አይችልም፤ ምክንያቱ
ደግሞ ርዕዮታዊው መንፈስ ማንም እንደፈለገ ሊጠመዝዘው በማይችለው ደረጃ ጠንካራ መሰረት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ርዕዮት የስርዓቱ
ጭካኔ፣ ኢ ፍትሀዊነት፣ ኢ ዴሞክራሲያዊነት፣ኢ ሰብዓዊነት፣… በጥቅሉ ርዕዮት የስርዓቱ ሚዛን ማሳያ ናት፤ ሳምንት ርዕዮታዊው መንፈስ
እንዴት ያለ ነው?፣ ጥንካሬው ምን ይመስላል?፣ከየት መጣ?፣ እንዴት?፣… የሚሉ ሌሎችም በርካታ መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ርዕዮታዊ
ወጋችንን ‹‹ ርዕዮታዊው መንፈስ እንደ ቻይኒዝ ባምቡ›› በሚል ርዕስ ስር
እንቀጥለዋለን፡፡ እስከዛው ግን በቃሊቲው መንግስት ስቃይ ስር ላሉ ወገኖቼ ብርታቱን እመኛለው፤ በመጨረሻም ከሰው ልጅ፣
ከህግ፣ ከፍትህ፣ ከዴሞክራሲ… ይልቅ ህንጻና መንገድ የተሻለ ዋጋ በሚሰጣቸው ኢህአዴጋዊ አገዛዝ ውስጥ እንዳለን ሳስበው፣ በበዓሉ
ግርማ ‹‹ኦሮማይ›› ውስጥ ያለ አንድ ግጥም መሰነባበቻችን እንዲሆን ተመኘው፡፡
‹‹ከጎራው ዘልቄ እስኪ ልነጋገር
ካለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር?
የኔ ውብ ከተማ-
ህንጻ መች ሆነና የድንጋይ ክምር፤
የኔ ውብ ከተማ-
መንገድ መች ሆነና የድንጋይ አጥር፤
የኔ ውብ ከተማ የኔ ውብ አገር
የሰው ልጅ ልብ ነው
የሌለው ዳርቻ የሌለው ድንበር፡፡
ሕንጻው ምን ቢረዝም፡ ምን ቢጸዳ ቤቱ
መንገዱ ቢሰፋ ቢንጣለል አስፋልቱ
ሰው ሰው ካልሸተተ ምንድነው ውበቱ?
እኔ ውብ የምለው
የሰውን ልብ ነው፡፡
ምን ቢነድ ከተማው ተንቦግቡጎ ቢጦፍ
ቢሞላ መንገዱ በሺ ብርሀን ኩሬ
በሺ ብርሃን ጎርፍ
ምን ያደርጋል?
ምን ያሳያል?
ካለሰው ልብ ብርሃን
ያ ዘላለማዊ ነበልባል ያ ተስፋ ሻማ
ጨለማ ነው
ሁሉም ጨለማ፡፡..›› (ገጽ 250-251)
ህንጻዎቹም የጨቋኞቹ መኖሪያና ገንዘብ ማግበስበሻ፣ መንገዱም የነሱው መመላለሻ ከመሆን ያለፈ
ፋይዳ የለውም!

ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡
ReplyDelete