Friday, October 25, 2013

ኢህአዴጋዊ ጠብሽ


በመሐመድ ሐሰን         (ላይፍ መጽሄት ላይ የወጣ)

አንድ ጎረምሳ ሲጠብሸው ፍሪዙን (አናቱን) ያካል፤ ከዛም ቤተሰቡን አልያም ወዳጆቹን ቀፍሎ ይሔዳል፡፡ ችግሩ መንግስት ሲጠብሸው ነው፤ መንግስት ሲጠብሸው ምኑን የሚያክ ይመስልሀል? ሀገርን፣ ዜጎቿን፣ እና ሀብቷን ካልክ አልተሳሳትክም፡፡ ግን ታዲያ ለመንግስት ከአንድ ጎረምሳ እኩል ‹‹ያካል›› አይባልም፤ ይቧጥጣል እንጂ፡፡ በአሁን ሰዓት የመንግስትን ስልጣን በመያዝ፣ በመንግስት እና በፓርቲ መካከል ያለውን ድልድይ ያፈራረሰው ኢህአዴግ፣ በከፍተኛ ጠብሽ ውስጥ ለመውደቁ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ እውነታውን ለመረዳት አከባቢያችንን ማስተዋል ነው፡፡ ፓርቲው የመታው ጠብሽ ኢኮኖሚያዊ ብቻ አይደለም፤ ይልቅ ፓርቲው የተመታው በሀሳብ፣ በምክንያት፣ በህግ፣ በፍትህ፣ በፖለቲካ፣ በፖለቲከኛ፣ በጋዜጠኛ፣….ጠብሽም ጭምር እንጂ፡፡ እናም ሀገር ምድሪቱን እየቧጠጣት ነው፡፡
ኢኮኖሚያዊ ጠብሽ
አንድ ከመንግስታዊ ተቋም ክስ ተመሰርቶበት የነበረ ወዳጅ አለኝ፡፡ በወቅቱ ተቋሙ እንደከሰሰው ቀረበና በጉዳዩ ላይ ከሀላፊዎቹ ጋር ብዙ ከተነጋገረ ቦሃላ፣ እሱን በማሰልጠን ‹‹አጣን›› ያሉትን ወደ ሀያ ሺህ ብር እንዲከፍላቸው ተስማሙ፡፡ እሱም በውላቸው መሰረት ከወር ደሞዙ ያስቆርጥ ጀመር፡፡ ከበርካታ ወራት ቦሃላ ባለፈው ደወለልኝና ‹‹ባክህ እነዛ ሰዎች እኮ በድጋሚ ከሰሱኝ!›› አለኝ፡፡ ‹‹ደሞ ምን እንሁን ነው የሚሉት?›› አልኩት፤ ‹‹ በድጋሚ አሁን ሌላ ሀላፊ ሲመጣ የቀድሞ ውላችን ተሸሮ ሀምሳ ሺህ ብር እንድከፍል በፍርድ ቤት አስወስነው ውሳኔው ተላከልኝ፡፡›› በማለት ድርጀቱን አማሮ እርግማን የተቀላቀለበት ብሶቱን አካፈለኝ፡፡
በነገራችን ላይ ይህ ጓደኛዬ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ከነገረኝ ቦሃላ ፣ በብዥታ ቀደም ብሎ እሰማቸው የነበሩና አሁንም ከየሰው የምሰማቸው አንዳንድ መሰል ጉዳዮች፣ ኢህአዴግ ኢኮኖሚያዊ ጠብሽ ውስጥ መሆኑን እንድገምት አድርጎኛል፡፡ ግምቱ ግን ግምት ብቻ ሆኖ አልቀረም፤ በቅርቡ ስሜቴን የሚጋሩ በርካታ ተጠቂዎች ገጥመውኛል፡፡ መንግስት ገንዘብ ፍለጋ የሰነዶችን አዋራ በማራገፍ ገንዘብ እያሰሰ ነው፡፡ የኢኮኖሚያዊ ጠብሹ ማሳያ ይህ ብቻ አይደለም፡፡
በተለይ ከወቅታዊው የሙስሊሞች ጥያቄ ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ እየወሰደ ያለው የእስር እርምጃ የጠብሹን መጠን ለማሳየት እንደ ጥሩ ምሳሌ ሊነሳ ይችላል፡፡ ምዕመናኑን ሰበብ እየፈለገ በየእስር ቤቱ ካጎራቸው ቦሃላ የዋስ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ያደርጋል፡፡ ታዲያ ዋሱ በገንዘብ ነው፡፡ ከ አንድ ሺህ ብር እስከ ሀያ አምስት ሺህ ብር ለዋስ በሚል እንዲያስይዙ ይጠየቃሉ፡፡ ታዲያ አንዳቸውም ብሩን ካስያዙና ከተፈቱ ቦሃላ ፍርድ ቤት አይቀርቡም፣ ብሩም አይመለስም፡፡ ጸጉርህን እና ኪስህን እያከክ በከንቱ መመላለስ ብቻ ነው መፍትሄው፡፡
ሌላኛው በንግድ ማህበረሰቡ ላይ የተያዘው ተገቢ ያልሆነ ግብር የማግበስበስ ዘመቻ ዋነኛው የኢኮኖሚ ጠብሹ ማሳያና መፍትሄውም ተደርጎ የተወሰደው ነው፡፡ ነጋዴው በሱቁ ካለው (በድርጅቱ) ካለው የእቃ ዋጋ በላይ የሚጠየቅበትን ገራሚ አሰራር እያየን ነው፡፡ ይህ የገንዘብ ጥማቸውን የሀራራ መጠንም ጭምር የሚያሳብቅ ስግብግብነት ሆኖ ተወስዶባቸዋል፡፡ ከደሞዝተኛው ላይ የማይቆረጥ የግብር አይነት የለም፡፡ ሰራተኛው እና መንግስት እኩል ሲካፈሉም እያየን ነው፡፡  
አረ ጉዱ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በመለስ ሙት ዓመት (ወር) ስም፣ በመለስ ፋውንዴሽን ምክንያት፣ በአርፋጅ ተማሪ ሰበብ፣ በመንገድ ስራና ጥገና ተሳቦ፣… አዋጡ! አዋጡ! ነው፤ እንደውም እኮ ግዴታም ጭምር ተቀላቅሎበት ነው፡፡ ህዝብ እና ሀገር በፓርቲው ይቧጠጣሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ፣ እንዲህ ባለው ሁኔታ የተገኘው ገንዘብ (በተለይ ከግብር) እየዋለ ያለው ፣ፓርቲው ለፖለቲካ መጠቀሚያነት በሚፈልጋቸው እንደ ኮንዶሚኒየም ባሉ የቤት ፕሮጀክቶች ላይ መሆኑ ነው፡፡ ከብዙሀኑ ሰብስቦ ለጥቂቶች የማዋል አይነት አሰራር፡፡ ዓባይም የኢህአዴግን ኢኮኖሚያዊ ጠብሽ በማናሩ በኩል በከፍተኛ ሁኔታ ይጠረጠራል፡፡
ሲጀመር በራሱ የኢህአዴጋዊነት መገለጫ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ጠብሽ ይመስለኛል፡፡ እስኪ ኢህአዴግ አሉኝ ከሚላቸው ምናምን ሚሊየን አባላቶች ውስጥ አንተ እንኳን የምታውቃቸውን አስብ፤ ከፈለግክ ቀበሌ ወይም ክፍለ ከተማ ሂድ! አብዛኞቹ (ሁሉም በለው ከፈለክ) አባል የመሆናቸው መነሻ ኢኮኖሚያዊ ጠብሽ ሲሆን፣ በሀሳብ በኩልም ቢሆን እልም ያሉ ጠብሻናሞች ናቸው፡፡

የሀሳብ ጠብሽ
ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በኢህአዴግ ጉያ ስር የተሰባሰቡ ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ጠብሻቸውን ለማስታመም ስለሚመጡ፣ የተወሰነ ግዜ ያላቸውን ቀለሃ ይተኩሱና ከዛ ቦሃላ ወደ ትክክለኛው መነሻቸው ይመለሳሉ፡፡ እንደግፍህ ያሉትን ፓርቲ ይደገፉታል፡፡ እንዲህ ያሉት ሰዎች እጣ ፈንታቸው ሁለት ሊሆን ይችላል፡፡ አንድም ምንም ያልገባቸውን ሀሳብ ዝም ብለው ይዘባርቃሉ፡፡ ሚናገሩት ነገር ምንም ደርዝ ላይኖረው ይችላል፡፡ ብቻ ዝም ብሎ ማውራት! እንደ እንትና ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደገደል ማሚቱ ከላይ አለቃ ያለውን ብቻ ማስተጋባት ሁለተኛው እጣ ፈንታቸው ይሆናል፡፡ ማን ነበር ስሙ? አዎ! እንደሱ ማለት ነው፡፡
እንዲህ ያለውን ኢህአዴጋዊ የሀሳብ ጠብሽ ለማስተዋል ብዙም ርቆ መሄድ አያስፈልግህም፡፡ ለምሳሌ ቴሌቪዥን ክፈት፡፡ ጋዜጠኛው ፖለቲከኞቹን ተክቶ የባጥ የቆጡን ሲፖተልክ ትሰማዋለህ፡፡ የሀሳብ ጠብሽ በነገሰበት ማን ስህተቱን ነግሮ ‹‹ሀይ!›› ይለዋል? ዝም ብሎ መሸክሸክ ነው እንጂ! ከሆነ ቢሮ ተጋብዞ የመጣ እንግዳ ካለም ከቻለ የተሰጠውን ያነባል፤ ካልሆነም ባልገባው እና በማያውቀው ሀሳብ ላይ አለማወቅ የቸረውን ድፍረት ተጠቅሞ ይዘባርቃል፡፡
አሁን ደግሞ የመሪ ጠብሹም ክፉኛ ስለጎዳቸው፣ ጠባቂ እንደሌለው መንጋ ፓርቲውን ወደ አደጋ ውስጥ እየከተቱት ይገኛሉ፡፡ የጣሉትን እና የተበለጡበትን አጀንዳ መልሰው አፈሩን አራግፈው ያነሱታል፤ በድጋሚም ግን ይሸነፉበታል፡፡ አሁን ለምሳሌ ሰሞኑን የተከበረውን የባንዲራ ቀን እንደ ምሳሌ ብናነሳ፣ አባባላችንን በደንብ ያስደግፍልናል፡፡ የማይደፈረውን ደፍረው ‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው›› አሉ፡፡ ከዛ ደግሞ ባለፈው ግዜ ከሙስሊሞቹ ጠንካራ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ክፉኛ የሀሳብ ጠብሽ ሲመታቸው፣ ‹‹ባንዲራውን አክራሪዎች አቃጠሉት…›› በሚል ከኔ በላይ ስለባንዲራ ተቆርቋሪ ላሳር አለና ፍረጃውን አጠንክሮ ቀጠለበት፡፡ ግን ብዙ መጓዝ አልቻለም፡፡ በኢዱ ተቃውሞ ላይ ላይ ‹‹ባንዲራችንንማ እንዴት እንደምንወደው እናሳያቹሃለን!›› በሚል ከልጅ እስከ አዋቂው ድረስ በገፍ ይዞ ወጣ፡፡ ድጋሚ እንዳያንሰራራ ሆኖ ተበለጠ፡፡ ይሄኔ ሌላ ስህተት ሰሩ ባንዲራ መቀማት ጀመሩ፡፡… የዘንድሮውን አከባበር ደግሞ እንዳያችሁት ምንም በማይገናኝ መልኩ ባንዲራንና አክራሪነትን አያይዘው በጠብሻናሞቻቸው አማካይነት ሲያደነቁሩን ዋሉ፡፡
የጅል (የሞኝ) ዘፈን ሁሉም አንድ ነው እንዲሉ፣ ዓመቱን ሙሉ ‹‹አክራሪነት፣ሽብርተኝነት፣ መለስ፣…›› በሚሉ ድግግሞሾች ሲያላዝኑብን ውለው ከረሙ፤ በቅርቡም ሚተውት አይመስሉም፤ ይሄን ትተው ምን ሌይዙ ይችላሉ ለነገሩ? ጠብሽ ይሉሀል ሄ ነው! የተገዢ መሳለቂያ እስከመሆን የሚያደርስ ባዶነት!
መብራት ሲጠፋ፣ ጋዜጠኛ ሲታሰር፣ ኔትወርክ ሲቋረጥ፣ ዶላር ስናጣ፣ ውሃ ሲሄድ፣ ስደት ሲበረክት፣ ኑሮ ሲወደድ፣ ሙስና ሰበረክት፣ ሰልፍ ሲከለከል፣ ወዘተ ወዘተ ሁሌ የልብ የማያደርስ ጠብሻናም ምላሽ መስጠት እስከመቼ? ጠብሽ በበረታ ቁጥር ሀገሪቱን እና ህዝቧን እየቧጠጡስ የት ይደረሳል? ኽረ ሼም ነው! መንግስታዊ ጠብሽማ ይደብራል! ሀገርንም ጭምር  ያጠብሻልና ይሰውረን፡፡                   
                            

No comments:

Post a Comment