Wednesday, June 5, 2013

ድሬን ምን አቃጠላት?


ፍቅር ወይስ የትራንስፖርት ችግር?



    በ መሀመድ ሀሰን


 
 
ድሬዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት እጅግ በጣም ላቅ ያለ ነው፡፡ ለራሳቸው የሚገባቸውን ክብር ለመስጠት ሌላ እማኝ ፍለጋ የሚኳትኑ አይመስሉም፡፡ ከተማቸውን ‹‹ፍቅር ያጥለቀለቃት፡ ፍቅር ያቃጠላት፡…›› ሲሉ ያወድሷታል፡፡ ለማንኛውም ይህንን ጉዳይ ለሌላ ሰፊ ገጾች እያመቻቸን እናቆየውና ድሬዎች ዛሬ ላይ እያሉት ያለውን አባባል እንመርምረው፡፡ በርከት ያሉ ድሬደዋውያን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ‹‹ ፍቅር ያቃጠላት ›› የሚለውን አባባላቸውን ‹‹የትራንስፖርት ችግር ያቃጠላት›› በሚል የተኩት ሲሆን፡ ነዋሪውም በከፍተኛ ጉርምርምታ ውስጥ ይገኛል፡፡ ለዚህ መነሻ የሆነው ደግሞ ከሰሞኑ የወጣውና ማንኛውም የህዝብ ማጓጓዣ መኪና ከ12፡00 ሰዓት ቦሃላ እንዳይንቀሳቀስ የሚለው ህግ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ይህ ህግ ተሳፋሪውን ወደፈለገበት ያዘዋውሩ የነበሩ ሚኒባስ መኪኖችን ከስራ ውጭ ያደረገ በመሆኑ የአነጋጋሪነቱን ዙር አክሮታል፡፡
የዛሬው የትራንስፖርት ህግና ችግሩ መነሻ ይሆነን እንደሆነ እንጂ ድሬዎችና በአከባቢዋ ያሉ የጎረቤት ከተሞችና ገጠሮች ነዋሪዎች ከመጓጓዣ ችግር ጋር በተያያዘ የሚተርኳቸው በርካታ ትዝታዎችና ቁጭቶች አሏቸው፡፡ እራሱን የሁሉም ነገር አድራጊና ፈጣሪ አድርጎ የማቅረብ ልክፍት የተጠናወተው የኢህአዴግ መንግስት፡ ከአዲሱ የባቡር መስመር ግንባታ ጅማሮው ጋር በተያያዘ የሚነዛው ዲስኩርም ከመገለጫ ባህሪው የተለየ አይደለም፡፡ ዲስኩሩ የባቡር አገልግሎት ግናባታን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይም ቢሆን ቀድሞ ያስጀመረው እሱ መሆኑን ሊነግረን ምንም አይቀረውም፡፡ በነጋ በጠባ ቁጥር ሀገር አቋራጭ እና የከተማ ባቡር መስመር ግንባታ እንዳስጀመረ በፉከራና በሽለላ ታጅቦ ይተርክልናል፡፡ ነገር ግን ከድሬ ከተማ ጋር በታህሳስ ወር 1902 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) አብሮ ተገንብቶ ህዝቦቿ ከማንም ቀድመው በትራንስፖርቱ ዘርፍ እንዲሰለጥኑ ያስቻላቸው የባቡር አገልግሎት የተቋረጠው በሱው ዘመን መሆኑን ሊነግረን አይሻም፡፡ ኢትዮጵያ ባቡር አልባ የሆነችው በኢህአዴግ ዘመን ነው ከማለት ይልቅ መቃብር ፈንቅለው ከእምዬ ምኒሊክ ጋር የታሪክ ሽሚያ ግብግብ ይገጥማሉ፡፡
በድሬደዋ ውስጥ የባቡር አገልግሎት መቋረጡ
 በርካታ ነዋሪዎችን ሌላ ነገር እንዲያስቡና ሁኔታው ሆን ተብሎ ድሬን ለማጥፋት የታቀደ ሴራ እንደሆነ አጥብቀው እንዲያስቡ አስገድዷቸዋል፡፡ አሁን ያለው የከተማዋ እንቅስቃሴም ከባቡሩ ጋር አብሮ የተገታ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም ትዝታውን ብቻ ታቅፎ ማመንዠክ ትርፉ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ባቡሩ የቆረቆራት ከተማ ከባቡሩ ውጪ እንዴት ኑሮን ልትገፋ ይቻላታል? ዛሬ ላይ የድሬና የባቡር ግንኙነት በቀደምት የታሪክ መጽሀፍትና በሙዚቃዎቻችን ላይ ብቻ ተገድቦ ቀርቷል፡፡ በተለይ ዘፈኖቻችን 2005 ዓ.ም ላይም ቆመው ድሬን ካለባቡሯ ማሰብ የፈለጉ አይመስሉም፡፡ ባቡሩ ከቆመ ከስንት ዓመት ቦሃላ ዘንድሮም ሀይልዬ ታደሰ፡ ጋሪውም በባጃጅ ባቡሩም በትዝታ መተካቱን ዘንግቶ ፡
‹‹…ባለጋሪው አንተ        ባለባቡሩ                                                                                            ድሬ ናፈቀኝ ሲመሽ መዞሩ…››
ይለናል፡፡  እንደውም ሳስበው እነዚህ ዘፈኖች ለድሬ ህዝብ ብሶት ቆስቋሽ መስለው ይሰሙኛል፡፡
ከሀዲዱ የተገፋው ባቡር ከአስፓልቱም ሲገፋ
ከዘመናት የባቡርና አገልግሎቱ እጦት ቦሃላ ለድሬዎችና አከባቢዋ ነዋሪዎች እንደ አማራጭ የአስፓልት ላይ ባቡር ሆኖ ሚኒባስ መኪና መጣላቸው፡፡ ይህኛውም ባቡር ከ 9 እና10 ዓመታት አገልግሎት ቦሃላ አገልግሎቱን እንዲያቋርጥ ተገዷል፡፡ የሰሞኑን ጉርምርምታም የፈጠረው ከዚሁ የለሊት ተጓዥ ሚኒባሶች መታገድ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አዲሱ አሰራር ጋር በተያያዘ በከልካዩ አካል፡ በተገልጋዩ እና አገልግሎት ሰጪው መካከል የሚነሱት ሀሳቦች ፍጹም በተለያየ ጽንፍ ላይ የቆሙ ናቸው፡፡
የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሃን በመቆጣጠር ተረኛ የሆኑት የመንገደኞችና ትራንስፖርት ባለስልጣናት ያወጡት ህግ ቅቡልነት እንዲኖረው በሰፊው እየወተወቱ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዴም እርስ በርሱ የሚጣረስ አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል፡፡ ህጉ እንዲወጣ ያስፈለገው ለተሳፋሪው ጥቅም ሲባል እንደሆነ የሚናገሩት ሀላፊዎቹ፡ በዋነኝነትም አደጋን፡ የተሳፋሪውን ምቾት እና ደህንነት እንዲሁም እንደ ኮንትሮባንድ ያሉ ከህገ ወጥነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ሲሉ እርምጃውን መውሰድ እንዳስፈለጋቸው ነው የሚተርኩልን፡፡
የለሊት ትራንስፖርት ተጠቃሚ የሆኑ ተጓዦች ደግሞ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ተወካዮች በሚሉት ፈጽሞ አይስማሙም፡፡ እርምጃው እኛ ምስኪኖችን ከማሰብ ይልቅ የህዝብ ማመላለሻ ባለንብረት የሆኑ ሀብታሞችንና በስራቸው የተደራጁ ጥቂት ቡድኖችን ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ ይከሳሉ፡፡
ባለፈው 15 ቀን በውል በማላስታውሳት አንዲት ማለዳ (አርብ ይመስለኛል) የኢትዮጵያ ሬድዮ ይህንኑ የለሊት ጉዞና እርምጃውን አስመልክቶ ዘለግ ያለ ፕሮግራም እያስደመጠ ነው፡፡ የስራ ሀላፊዎቹ የሚደረድሯቸው ምክንያቶች በካፌው ውስጥ የነበረውን ሰው ለስላቅ ፈገግታና ለክርክር ጋብዞታል፡፡         ‹‹…ይህ የለሊት ጉዞ እጅግ በጣም አደገኛና ተሳፋሪውንም ምቾት የሚነሳ በመሆኑ በጉዞ  ላይ የነበሩና ተጨናንቀው ይሄዱ የነበሩ ሰዎች ስንደርስላቸው በጣም ነው ደስ የሚላቸውና የሚያመሰግኑን፡፡…›› አይነት ይዘት ያለው ንግግር በማድረግ ላይ ሳለ ሬድዮኑ የማያስተናግዳቸው ድምጾች በካፌው ውስጥ መሰንዘር ያዙ፡፡ የሰውዬውን ንግግር በመተው የራሳችን እውነት ያሉትን መደርደር ጀመሩ፡፡
‹‹…እነኚህ ሰዎች ማንን ነው የሚዋሹት?: ተሳፋሪው ተገዶ ነበር እንዴ የሟዘው?፡ በፍላጎቱ ወደ ጉዳዩ ለመድረስ የጓጓን ተሳፋሪ በማጉላላት እንዴት ነው ማስደሰት የሚቻለው?፡ በሚኒባሶቹ ደርሶብን የማያውቀው የመጉላላትና ብሎም የመታሰር ችግር ገጥሞን ከጉዟችን የተሰናከልነውማ በናንተው አዲሱ አሰራር ነው፤…›› ሁሉም ማቆሚያ የሌለውን ተሞክሮ መደርደሩን ቀጠለ፡፡
ሌላኛው የስራ ሀላፊ ተከተሉና ‹‹…ተሳፋሪውም ዘና ብዬ እየተኛሁ እሄዳለው፤ እዛም ዘና ብዬ ማታ እመለሳለሁ፤ የሚል ትምክህት አዳብሯል፡፡…›› አሉ፡፡ እንደገና ሌላ ምላሾች በካፌው ውስጥ ካሉ ተጠቃሚዎች ተሰነዘሩ፡፡ ብዙዎቹ የተጋሩት ሀሳብ፡ ‹‹የማታ ጉዞ ዘና ተብሎና በምቾት ተተኝቶ የሚኬድበት ነው እንዴ?፡ በምሽት ተክለፍልፎ የተጓዘና ድካም የተጫጫነው ሰው ቀኑን ዘና ብሎ የሚውልበት መንፈስና ግዜ ይኖረዋልን?፡ እውነት ቢዝናኑ እንኳን ምኑ ትምክህት ያሰኘዋል?›› የሚሉ ነበሩ፡፡
ህጉን ባወጣው አካል የሚነሳው ሌላኛው ነጥብ ከአደጋ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ከዚሁ የአደጋ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከድሬደዋ አዲስ አበባ አገልግሎት ከሚሰጠው በረከት(ስሙን ቀይሬው ነው) ጋር መደበኛ ያልሆነ ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡ በረከት የለሊት ጉዞ አደጋው ከቀኖቹ የባሰ እንዳልሆነና የሀላፊዎቹ ንግግር ግነት እንዳለበት  ነው የሚናገረው፡፡ በረከት በሚሰራበት የድሬደዋ አከባቢ ሚኒባሶች ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው በሚል በተደጋጋሚ እንደማሳያ በቴሌቪዥን የሚቀርበው ምስል በጣም እንዳስገረመው አጫውቶኛል፤ ምንንያቱ ደግሞ ዘጠኝ ሰዎች የሞቱበት ይህ የመኪና አደጋ የተፈጠረው አዴሌ በተባለችው አከባቢ ሲሆን፡ ሀላፊዎቹ እንደሚሉት መኪናው ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ ሳይሆን ከአወዳይ ጫት ጭኖ ወደ ድሬደዋ እየሄደ የነበረ ነው የሚል ነው፡፡ አክሎም ከአወዳይ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ መኪና በጭራሽ እንደሌለ ይናገራል፡፡ ስራ ከጀመረ ከ አራት ዓመት በላይ እንደሆነው የሚናገረው በረከት፡ በ አራት ዓመት ውስጥ በራሱ ላይ ምንም አይነት አደጋ ያልደረሰበት ሲሆን፤ በሌሎች ላይ ግን አራት ያህል አደጋዎች ሲደርሱ መታዘብ ችሏል፡፡          
ከኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ ለሚነሳባቸው ቅሬታ በረከትና ሌሎችም የስራ ባልደረቦቹ ‹‹አህያውን ፈርቶ ዳውላውን›› በሚል ስላቅ ያልፉታል፡፡ የሚባለው እንኳን እውነት ሆኖ ቢገኝ ኮንትሮባንድን የሚቆጣጠረው አካል ስራው ምንድነው ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
ከለሊት ጉዞ የደህንነት ችግር ጋር በተያያዘ ለሚነሳው ቅሬታ አገልግሎት ሰጪዎች ብቻ ሳይሆኑ ተጠቃሚዎችም ጭምር ምላሽ አለን ይላሉ፡፡ ቤዛዊት (ስሟ የተቀየረ) ለሰባት አመታት ያህል ባስፈለጋት ግዜ አገልግሎቱን ስትጠቀም ቆይታለች፡፡ ሚኒባሶቹን ለመጠቀም ከመረጠችባቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው አገልግሎቱን ከሚሰጧት ሰዎች ጋር የፈጠረችው ቤተሰባዊ ግንኙነት ነው፡፡፡ ቤዛዊት በፈለገችው ሰዓት ደውላ ቦታ ታስይዛለች፡ መኪናው እቤቷ ድረስ መጥቶ ይወስዳታል፡ አዲስ አበባም በውድቅት ለሊት ከደረሱ መንገድ ላይ ጥለዋት ሳይሆን የሚሄዱት እስኪነጋ መኪና ውስጥ ያለ አንዳች ስጋት ጋደም እንድትል ይመቻችላታል፡፡ ጉዳይዋንም በቶሎ ጨርሳ ለተጨማሪ ወጪዎች ሳትዳረግ በዛኑ እለት ወደ ድሬደዋ ትመለሳለች፡፡ ድሬደዋ በየትኛውም ሰዓት ብትገባ መኪኖቹ እራሳቸው እቤቷ ድረስ ያደርሷታል፡፡ ከፈለገችም ሆቴል በማፈላለግ አልጋ ያስይዟታል፡፡ ይህ ከድሬደዋ አዲስ አበባ የሚመላለሱ ተጓዦች ሁሉ የሚያገኙት አገልግሎት እንደሆነ የምትናገረው ቤዛዊት ‹‹ ከዚህ የበለጠ ደህንነት ከየት ይገኛል?›› ስትል በአግራሞት ትጠይቃለች፡፡ ቤዛዊት ‹‹ በልቶ ማደር ለሚያሳስበን ህዝቦች ለነፍሳችንም ብቻ ሳይሆን ለኪሳችንም ጭምር የሚመጥነው ደህንነት ያለው ከሚኒባሶቹ ላይ ነው፡፡›› በሚል አስረግጣ ትናገራለች፡፡
ከቤዛዊት በተጨማሪ ያነጋገርኳቸው የለሊት ጉዞ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን የሚመርጡበት በርካታ ምክንያቶች እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በፈለጉበት ሰዓት ስራቸው ሳይስተጓጎል በአዲስ አበባና ሌሎችም አከባቢዎች ያላቸውን ጉዳይ ጨርሰው መምጣት የሚያስችላቸው በመሆኑ፡ አዲስ አበባ ላይ አለ ከሚባለው ከአቅም በላይ ከሆነው የኢኮኖሚ ብዝበዛ እንደሚታደጋቸው፡ የቀኑ ሙቀት ከጤናቸው ጋር በተያያዘ እንደሚከብዳቸው፡ በቀን የሚወጡ መኪኖች ውስን በመሆናቸው፡ ከአዲስ አበባ ቦሃላም ቢሆን የሚኖረውን ቀጣይ ጉዞ ስለሚያሳጥርላቸው፡ ወዘተ አማራጭ እንደሆናቸው ይዘረዝራሉ፡፡ አክለውም ‹‹ጥቅማችንንና የተመቸንን የምናውቀው እኛ ተሳፋሪዎቹ እስከሆንን ድረስ ምርጫውን መተው የነበረባቸው ለእኛ ለተጠቃሚዎች እንጂ፤ ችግራችን የማይመለከታቸውና ምንም ያልጎደለባቸው ባለስልጣናት በዘመቻ የሚወስኑት መሆን አልነበረበትም፡፡›› ሲሉ ተሳፋሪዎቹ ተጨማሪ ከስ ይሰነዝራሉ፡፡
በዚህ ሰሞነኛው ህግ ድሬደዋ፡ሀረር እና ጅጅጋን ብቻ መሰረት አድርገን እንኳን ብናየው ከሀምሳ እስከ ስልሳ የሚሆኑ መኪኖች ከስራቸው ውጪ እንዲሆኑ ተገደዋል፡፡ በባለንብረቶቹና ህጉን ባወጡት አካላት መካከል ዛሬም መግባባት የለም፡፡ ሀላፊዎቹ ህገ ወጥ ናችሁ ይላሉ፤ ባለንብረቶቹ ደግሞ ህጋዊ ነን፡ ደረጃ አቅርበን የሚቀበለን አጥተን ነው፡ መኪኖቻችንም ቢሆኑ ከቀኖቹ የተሻለ ብቃት ያላቸው ናቸው ይላሉ፡፡ ህጉ ከመውጣቱ በፊትም ቢሆን ከኛ ጋር የተደረገ ምንም አይነት ውይይት አልነበረም ሲሉ እርምጃው በግብዝነት መወሰዱን ይናገራሉ፡፡ የመገኛኛ ብዙሀኑም ህጉን ያወጣውን አካል ብቻ በመከተል አገልግሎቱን መቃወምን ብቻ የተያያዙት ይመስላሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን ጉዳዩ ብዙሀኑን የሚመለከት እነደመሆኑ ሁሉንም ሊያግባባ በሚችል መልኩ የሰከነ ውይይትና አካሄድ የሚፈልግ ነው፡፡ አሁን የተወሰደው እርምጃም ግብዝነት የተጫነውና የተጠቃሚውን ፍላጎትና መብት ከግምት ያስገባ አይደለም የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ከሁሉም በላይ ግን በባለንብረቶቹም ዘንድ ሆነ በተጠቃሚው በኩል ከፍ ባለ ጉርምርምታ ከድማዳሜ ላይ የተደረሰበት የሚመስለው ነጥብ ‹‹ህጉ የወጣው የተወሰኑ አክስዮን ማህበራትንና በስራቸው የተደራጁ ወገኖችን ለመጥቀም ሲባል ነው፡፡›› የሚለው ነው፡፡ ስለዚህም ይህንኑ ጉዳይ በደንብ በማጤን አሳማኝ ምላሽ መስጠቱ ጉርምርምታውን ሳይፈታው አይቀርም፡፡              



No comments:

Post a Comment