Tuesday, July 16, 2013

የቤተ-መንግስት ደጃፍ ግፎች 1


በመሐመድ ሐሰን
አቤት ጋዜጠኛ የመሆን እዳ! በተለይ የዚህ ዘመን ጋዜጠኝነት ፈተናው ለጉድ ነው፡፡ በአንድ በኩል እችላለሁ ያለ፡ የስራ አማራጭ ያጣ ሁሉ እየተነሳ የሚከትፍበት ሲሆን፡ በሌላ በኩል ደግሞ  ባለሙያው ከፍቃድ ሰጪው አካል እና ከመንግስት የሚደርስበት ጫና ጋዜጠኝነቱን አቀጭጮታል፡፡ በተለይ ደግሞ ማህበረሰቡ በጋዜጠኞች ላይ የሚጥለውን ተስፋ ስንመለከት፡ የቁጭታችን ልክ ጣራ ይነካል፡፡ ማህበረሰቡ ‹‹ጋዜጠኛ›› የሚለውን መጠሪያችንን እንጂ፡ የአቅማችንን፡ የሸራችንን፡ የወገንተኝነታችንን፡ የአሸርጋጅነታችንን፡… ልክ በውል አያውቀውም፡፡ ስለዚህም በደል በደረሰባቸው ፡ፍትህ በተነፈጉ ፤…ግዜ እሮሯቸውን ይዘው ወደ ጋዜጠኛ ይገሰግሳሉ፡፡ ይሄኔ በሙያው ላይ የሚወሰልቱ ‹‹ጋዜጠኞች›› የህብረተሰቡን ችግር ከሆዳቸው እና ከአለቃቸው ደስታ አንጻር በመመዘን ገሸሽ በማድረግ ተስፋ የጣለባቸውን ህብረተሰብ ሲያሳዝኑ፡ የተቀሩት ጥቂት ታማኝ ጋዜጠኞች ደግሞ አቅማቸው በፈቀደው መጠን የቻሉትን ለማድረግ ይፍጨረጨራሉ፡፡ ነገር ግን የሰፊው ማህበረሰብ ችግር በዛው ልክ ሰፊ እንደመሆኑ የየአከባቢውን ችግር በታማኝነት የሚያካፍሉን ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሀን የሉንም፡፡ ማህበረሰቡ በኢትዮጵያ ጋዜጠንነት ውስጥ ካለው አስቸጋሪ ፈተና ይልቅ ጋዜጠንነቱ ገዝፎ ስለሚታያቸው፡ አቤት ማለታቸውን አያቋርጡም፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2005 ዓ.ም የገጠመኝ ጉዳይ የማህበረሰቡ ተስፋ ማሳያ እንዲሁም የዚህ ጽሁፍም ጭምር መነሻ ነው፡፡
በዚሁ እለት ጠዋት ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ፡ አራት ኪሎ ከቤተመንግስቱ ፊት ለፊት፡ ከመኖሪያ መንደርነት ወደ ፍርስራሽ ጉራንጉርነት ወደተቀየረው ሰፈር እየዘለቅሁ ነው፡፡ የአንድ መጠነኛ የሩቅ-ለሩቅ ትውውቅ ያለን ሰው ሰላምታ ከጉዞዬ ገታኝ፡፡ ሰላምታውን ተከትሎም፡
‹‹ ለ ሀምሳ ሁለት ዓመታት ከኖርኩበት ቤቴ እኮ በግፍ ልፈናቀል ነው…›› ሲል ለወዳጅ እንኳን ረጋ ብለው ሊነግሩት የሚችሉትን ብሶት፡ ለኔ ለባዳው ምሬት በተቀላቀለበት ድምጸት ጮክ ብሎ ነገረኝ፡፡ ለምን ሊነግረኝ እንደፈለገ ግራ ገብቶኛል፡፡
‹‹እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል?›› አልሁት፡፡
‹‹እኔ ምን አውቃለው? የኢህአዴግ አባል ለሆነችውና አሜሪካን ሀገር ተንፈላሳ ለምትኖረው እህቴ ብር እና ቦታ ሊሰጧት እየተስማሙ ነው፡፡…›› ሲለኝ፡ ‹‹የአባልነት ጥቅማ ጥቅም ቀበሌ ተሻግራ አሜሪካን ገባች?›› ስል በውስጤ አጉረመረምኩኝ፡፡ ቀጠል አደረግኩኝና፡
 ‹‹እንዴት ለሷ ሊሰጧት ይችላሉ?›› የሚል ጥያቄዬን አስከተልኩለት፡፡
 ‹‹እኔው በራሴ እጅ የሰጠኋት ሰነድ በእጇ ስለሚገኝ ብቻ እሷን የቤት ባለቤት አድርገው፡ እኔን ሜዳ ላይ ሊበትኑኝ ነው፡፡›. ብሶት የተጫነው ምላሹን ሰጠኝ፡፡
‹‹ለመሆኑ ቤቱ የማንና በማን ስም ነው የሚገኘው?›› የኔ ጥያቄ ነበር፡፡
‹‹ቤቱ የእናታችን ነው፤ ካርታውም በእናታችን ስም ነው፡፡›› እስረግጦ በፍጥነት መለሰልኝ፡፡
ይህ ሰው በቆይታችን ወቅት እንደነገረኝ ከሆነ፡ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያላቸውን ቢሮዎች ሁሉ አንኳኩቶ፡ አንድም አካል ምላሽ ሊሰጠው  አልቻለም፡፡ ዛሬም ተስፋ ባለመቁረጥ በእጁ ላይ ለማስረጃነት ይሆኑኛል ያላቸውን ሰነዶች እንደያዘ እግሩ እስኪቀጥን መኳተኑን ቀጥሏል፡፡ ይህም ሰው የህብረተሰቡ አንድ አካል ነውና ይህንን ሁሉ ብሶት ለምን እንደሚነግረኝ የገባኝ ቀጣዩን ተማጽኖ ሲያቀርብልኝ ነው፡፡
‹‹እባክህ ተባበረኝ፤ አንተ ጋዜጠኛ ነህ፤…ብዙ ተበድያለው፡ ተገፍቻለው፤ ችግሬን ተካፈለኝ፡፡›› ሲል፡ እኔ ለውስጤ ‹‹በጋዜጠኛ ላይ የተጣሉ የተጋነኑ ተስፋዎች!›› የሚል ምላሽ ሰጠሁት፡፡ ተማጽኖውን እና ተስፋውን በማሰላሰል ላይ ሳለሁ፡
‹‹የአልጀዚራ ስልክ የለህም?›› አለኝ፡፡
‹‹እናፈላልጋለን አይጠፋም፡፡›› አልሁት፡፡
‹‹እባክህ ፈልግልኝ፤ ቢያንስ ቤቱን በላዬ ላይ በግፍ ሲያፈርሱት ይቅረጹኝ፤›› ሲል ተስፋ በተሟጠጠበት ስሜት ውስጥ ሆኖ ተማጸነኝ፡፡   
ከዚህ ቦሃላ ደግሞ እንደሚያገኘኝና ችግሩን ይበልጥ እንደምጋራው በማሰቡ ይመስላል፡ ከሀሳቤ ጋር ትቶኝ በቅርብ ርቀት ላይ ከነበረው የጓደኛው ቤት ዘለቀ፡፡ ዳግም ብንገናኝ ምን ልረዳው እንደምችል ባይገባኝም፡ ውስጤ ግን ጥያቄዎችን ማንሳት እና መብሰልሰሉን አላቆመም፡፡
በ አራት ኪሎ አከባቢ በአይን ብቻ እንኳን የሚታዩት ችግሮችና ግፎች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ተገቢው ቤትና ግምት አይሰጣችሁም ተብለው እጅግ በጣም አደገኛ በሚባል ሁኔታ ውስጥ ከሚኖሩት ጀምሮ፡ እንዲሁ በዘፈቀደ ያለመጠለያ ሜዳ ላይ የመበተን አደጋ እስከተጋረጠባቸውና ሜዳ ላይ እስከወደቁት ድረስ፡ በርካታ ዘግናኝ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡
በከተማዋ ውስጥ ከሚፈጸሙ መሰል አስከፊ ችግሮች ጋር ሲነጻጸር፡ የዛሬው ባለጉዳይ ያሰማን እሮሮ አንዱ ማሳያ ብቻ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤ ምናልባትም በአንጻራዊነት ካየነው፡ አነስተኛ ሊባል የሚችል ጉዳት ነው፡፡ ነገር ግን መቼ ነው በልማት ስም የሚፈጸሙ ግፎችና ጥፋቶች እልባት የሚያገኙት? እነዚህን ዜጎች ያላካተተ ልማት በሌላ ጎኑ ጥፋት አይሆንምን? የዜጎችን አቤቱታ ሰምቶ አሳማኝ የሆነ ምላሽ የሚሰጥ አካል መቼ ይሆን የሚኖረን? ይህን ጉዳይ የአንድ ተራ ግለሰብ ታሪክ ብቻ አድርጎ መውሰድ ፍጹም ስህተት ላይ ይጥላል፡፡ ይህ ዛሬ ታሪካቸውን ልናወራላቸው ያልተቻለን በርካታ ኢትዮጵያውያን እውነታ ነው፡፡ በየመንደሩ፡ በየሰፈሩ፡ በየቀበሌው፡ በየወረዳው፡… ጥፋቱ አድማሱን እያሰፋ ለመምጣቱ በርካታ አስረጂዎችን መደርደሩ ከባድ አይደለም፡፡ በመጨረሻም ትልቁ እና አስከፊው ሀገራዊ ውድቀት መከተሉ አይቀሬ ይሆናል፡፡
ታዲያ የሀገሪቱ ‹‹አስተዳዳሪዎች›› ከዚህ በእጅጉ የከፉ ታሪኮችን አስተውለው አያውቁ ይሆን? ዝምታቸውስ ለምና እና እስከመቼ ይቀጥላል? ጋዜጠኞችስ እንዲህ ያሉ ችግሮች ከባለስልጣናቱ መልስ (ሰበብ ብንለው ሳይሻል አይቀርም) እስካልተገኘላቸው ድረስ አፍነን የምናቆየው እስከመቼ ነው? ከአለቆቻችን ከንቱ ውዳሴ ይልቅ በመከራ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ድምጽ መቼ ይሆን የምንሰማው? ህብረተሰቡ በጋዜጠኞች ላይ ያነገበው ተስፋ ከመክሰሙ በፊት መታደግ ይቻል ይሆን? ምላሹን ለየራሳችን እንተወው፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ ባለታሪካችንን ጨምሮ፡ ሌሎች ዘልቀን የማንጨርሳቸው ግፎች እና በደሎች የሚፈጸሙት፡ ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መቀመጫ (በቤተ-መንግስቱ) አፍንጫ ስር መሆኑ ነው፡፡ አፍንጫቸው ግን ይህንን እንኳን ማሽተት የቻለ አይመስልም፡፡ እና ይህንን ካላሸተተ ሌላውን ስስለማሽተቱ በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ምናልባት በመካከላቸው ላይ ያለው ብቸኛው የአስፓልት መንገድ፡ ኑሯቸውንና ህይወታቸውን የየቅል አድርጎ ከፍሎት፡ የድሆቹ ድምጽ አልሰማ ብሏቸውም ይሆናል፡፡ አስፓልት እና ወታደር በለየው አንድ ግቢ ውስጥ እየኖሩ ላለመተያየት፡ ላለመሰማማት፡ ላለመረዳዳት፡ ላለመተዛዘን፡ ላለመግባባት፡ላለመደማመጥ፡ ላለመነጋገር፡  … መወሰን መቻል መጨረሻችንን የት ያደርሰው ይሆን?


No comments:

Post a Comment