አባይ ሰሞኑ ሀይሉን ጨምሯል፡፡ ሁሉንም አግበስብሶ እወሰደ ነው፡፡ ጥግ ቆሞ ክፉና ደጉን የሚያስተውል
የጠፋ እስኪመስል አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ ከወንዙ ውስጥ ሰጥመዋል፡፡ መድረሻቸውን ቢጠየቁ ግን አንዳቸውም በእርግጠኝነት
አይናገሩም፡፡ ገዢው ፓርቲ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ወጣቱ፣ ሽማግሌው፣ አሮጊቷ፣ ተማሪው፣ ሰራተኛው፣ ተማረው፣ ያልተማረው፣….አብዛኞቹ
ያልተተኮሰው ባሩድ እየሸተታቸው ጦርነትን እያበሰሩን ነው፡፡ ከተቃዋሚው ወገን ያየን እንደሆነ የሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ ቀዳሚው ነው፡፡
በአንድ በኩል ኢህአዴግን በሌላ በኩል ደግሞ ግብጽን ተንኮስ የሚያደርገው የሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ፣ ተንኳሽነቱ የሚጀምረው ከርዕሱ
ነው፡፡ ርዕሱ ‹‹እነሱ ከአባቶቻቸው አይበልጡም እኛም ከአባቶቻችን አናንስም!!!›› ይላል፡፡ ይህ ርዕስ ምናልባትም የበርካታ ሰሞነኞችን
ስሜት ይገልጽ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው መግለጫ ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የሚሰጥ እንደመሆኑ በርካታ ትችቶችን ማስከተሉ አይቀርም፡፡
የተሻሉ አማራጮችን መጠቆም ያልቻለው ይህ መግለጫ፣ በዘመናት ውስጥ የመጡ ተለዋዋጮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ባለመቻሉ ሩቅና የመጨረሻ
አማራጭ የሆነውን ጦርነት በመናፈቅ ሙቀቱን ለመቀላቀል የቸኮለ ይመስላል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ቀደም ብለው ስለ አባይና ወቅታዊው
ጉዳይ ባተቱበት ጽሁፋቸው ላይ ያሰቀመጧት ሀሳብ፣ ለሰማያዊ ፓርቲ መግለጫና በዛ ስሜት ውስጥ ላለን ኢትዮጵያውያን ጥሩ ምላሽ ሳትሆን
አትቀርም፡፡ ፕሮ በጽሁፋቸው ላይ ‹‹…ለፍቅር መተዋወቅ እንደሚያስፈልግ
ሁሉ ለጠብም መተዋወቅ ያስፈልጋል፤ የተሟላ መረጃ ቢኖረን የጥንት ታሪክ እየጠቀስን ሰዎችን ለጦርነት አንቀሰቅስም ብዬ አምናለሁ፤…››
ይሉና ከግብጽ የጦር ሀይል አቅም ጋር የተያያዙ እውነታዎችን ማስቀመጣቸውን ይቀጥላሉ፡፡
የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የመገናኛ ብዙሀንንም መረጃዎች የተመለከትን እንደሆነ ከጥቂቶቹ
በስተቀር አብዛኞቹ ጦርነትን የናፈቁ ዘገባዎችን ይዘው በመውጣት ጦርነቱን ለማብሰር የቸኮሉ ይመስላሉ፡፡ በእርግጥ ጥቂቶች በተቃራኒው
ሌሎች ጥርጣሬዎችን በማንሳት ሌላኛውን ጎን መመልከታቸው አልቀረም፡፡ በዚህኛው ምድብ ውስጥ ያሉት ሰዎች የሰሞኑን ሽኩቻ ለፖለቲካዊ
ትርፍ ሲባል ሆን ተብሎ የታቀደ ነው ሲሉ ይጠረጥራሉ፡፡ የግብጽ ፖለቲከኞችም ሆኑ ኢትዮጵያውያኑ ፖለቲከኞች የውስጥ ውጥረታቸውን
ለማርገብ የሰሞኑን ሙቀት አልተጠቀሙበትም ማለት እንደማይቻል ነው በዚህኛው ምድብ ውስጥ ያሉት ጠርጣሪዎች ስጋታቸውን የሚገልጹት፡፡
ገና በጽንስ ላይ ላለው አባይ ነጋሪት መጎሰማችን እና በአደባባይ ወንዙን አስቀየስን ብሎ መደንፋቱ ግብጾችን በቶሎ እንዲበሳጩ አድርጓቸዋል
የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ከነዚህኞቹ ውስጥ እጅግ በጣም ጠርጣራዎቹ ደግሞ ‹‹የተሰበሰበው ገንዘብ ከ10 በመቶ የማይበልጥ መሆኑና
ቀረውን ገንዘብ መሰብሰብ ስለሚያዳግት፣ ባለስልታናቱ ሆን ብለው ወደ ጦርነት እንድንገባ ፈልገዋል፡፡›› ይላሉ፡፡ አሁን ላይ ቆመን
የትኛው ሀሳብ ትክክል እንደሆነ ለመናገር ቢከብድም በሀገር ጉዳይ ላይ የተለያየ ሀሳብ ተነስቶ መንሸራሸሩ፣ የተሻለውን አማራጭ ለማየት
ሚረዳ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡
የምን ጦርነት? ማንስ ሊያተርፍ?
የጦርነቱ መዓዛ ባየለበት በዚህ ወቅት ሰከን ያለ ጽሁፍ ካቀረቡት ውስጥ አንዱ የዞን ዘጠኙ
ዘላለም ክብረት ነው፡፡ ዘላለም ክብረት ‹‹ኢትዮጵያ-አባይ-ግብጽ›› በሚለው ጽሁፉ ላይ ካነሳቸው በርካታ ነጥቦች ውስጥ አንዱ የተፋሰሱ
ሀገራት ከወንዙ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በዘላቂነት ችግሮቻቸውን ሊፈቱባቸው የሚችሉት አራት አማራጮች ይዘረዝራሉ፡፡ የመጀመሪያው
አማራጭ ተባብሮ መስራት ሲሆን፣ ሁለተኛው አማራጭ ተበደልኩ የሚለው አካል ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ወስዶ ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት ነው፡፡
በሶስተኛነት የተቀመጠው ሌላው አማራጭ ከዚህ በፊት ተሞክሮ ያልተሳካው የላይኞቹን ተፋሰስ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ማሳመጽ እና ኢትዮጵያን
አሁን ያለው አጠቃቀም ሳይሳካ አስገዳጅ ውል ውስጥ መክተት ነው፡፡
በአቶ ዘላለም ጽሁፍ ላይ እንደተገለጸው፣ ጦርነት አራተኛውና የመጨረሻው አማራጭ ነው፡፡ በዘሂሁ አማራጭ ውስጥ ቃል በቃል
‹‹… በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ጦርነት ማስነሳት ለህልም የቀረበ አማራጭ ነው፤…›› ይለናል፡፡
ግብጽ በአሁን ወቅት በውሀው የመጠቀም መብታችንን መገደብ ባትችልም፣ ወደ ጦርነት መግቢያ እድሉ ጠባብ በሆነበት ጦርነትን መናፈቅ ምን ይሉታል? መሪዎቻችንም በህዝቡ ስሜት
ተነሳስተው ከጦርነቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ጥቅምን ለመሻት አይነሳሱም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ገና ባልጠነከረውና ጽንስ በሆነው ኢኮኖሚያችን
ላይ ጦርነትን መመኘትም ጽንሱን ለማጨናገፍ መሯሯጥም ጭምር ነው፡፡ ህዝቡ በልቶ በማደር ችግር ውስጥ ባለበት ሰዓት የዳቦና የዘይትን
በጀት ወደ ጦርነቱ ስለማዞር ማሰብ እብደትም ጭምር ነው፡፡ በጦርነቱ ኢትዮጵያ ክፉኛ እንደምትጎዳ ለማሰብ ጠንቋይም፣ ወልይም መሆን
አያስፈልግም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ከላይ በተጠቀሰው ጽሁፋቸው መግቢያ ላይ ‹‹ ጦርነት እንኳን በልቶ ላልጠገበ ህዝባና ለጥጋበኞችም
አይመችም፤ የተራበ ህዝብ በጠገቡ መሪዎች ሲነዳ ግን ጦርነት ለአጉል ጀብደኛነት ዝና የሚጠቅም መስሎ ይታያቸዋል፡፡›› ይላሉ፡፡
እንደ ሰሞኑ ያለ እሰጥ አገባ ከዚህ ቀደም በፍጹም ተስተውሎ የማያውቅ አይደለም፡፡ በደርግ
ግዜ ኢትዮጵያ እና ግብጽ፣ እንዲሁም ሱዳንና ግብጽ (በአልቱራቢ እና በሆስኒ ሙባረክ ግዜ) ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ፣ ከአሁኑ
በባሰ ከፍተኛ የሆነ የቃላት ጦርነት ይለዋወጡ ነበር፡፡ ስለዚህ ትላንትን በመርሳት በቃላት ጦርነቱ ብቻ ተሸብሮ ለሀገራዊ ሽብር
መቻኮሉ ቀውሱን ያፋጥነዋል፡፡
ሱዳን በግብጽ ላይ ፊቷን አዙራለች የሚለው ዜና ለኢትዮጵያውያን ጦርነት ናፋቂዎች የልብልብ
ሳትሰጠን አልቀረችም፡፡ በሱዳን ላይ ተስፋ መቁረጥ ባይገባም ሙሉ በሙሉ እምነት መጣሉ ግን ስህተት ውስጥ ሊጥለን ይችላል፡፡ ፕሮ
እነዳሉት ሱዳንን ጨምሮ አብዛኞቹ ጎረቤቶቻችን ከግብጽ ጋር አብረው የአረብ ማህበርተኞች ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ከእኛና ከግብጽ ማን
ያዋጣታል ብሎ መጠየቁ ፌዝ ሊሆን ይችላል፡፡ ሱዳኖች ከኢጥዮጵያ ጋር ባላቸው የሀይል አቅርቦት ንግድ የተነሳ ወደኛ ያደላሉ የሚሉ
ትንታኔዎችም ብቅብቅ ሲሉ ይስተዋላል፡፡ ሆኖም ግን እኛ አብዛኛው የነዳጅ ፍጆታችን ከሱዳኖች መሆኑና በተሻለ ዋጋም እያገኘን እንደሆነ
ይዘነጋል፡፡ በዚህ በኩል ካየነው ሱዳን ለኛ በኢኮኖሚው በኩል በጣም አስፈላጊዋ ሀገር እንደሆነች ይገለጥልናል፡፡
በሱዳን ላይ ሙሉ እምነት የማያስጥል የቅርብ ግዜ ክስተትም አለ፡፡ ‹‹የናይል ተፋሰስ ሀገራት
የጋራ ስምምነት›› ውል በግንቦት ወር 2002 ዓ.ም ሲፈረም፣ ‹‹አሁን ያለውን የአጠቃቀም ኮታ በማይነካ መልኩ›› የሚል ሀረግ
ካልገባበት አንፈርምም ያሉት ግብጽና ሱዳን ነበሩ፡፡ በዚህ የተነሳም ለተፋሰሱ ሀገራት የተሻለ እልባት ያመጣል የተባለው ህግ ሳይጸድቅ ቆይቷል፡፡ባለፈው ሀምስ ግን
ኢጥዮጵያ የቅኝ ግዛት ውሉን ውድቅ በማድረግ የናይል ትብብር መዕቀፍን አጽድቃለች፡፡
ፎርብስ መጽሄት የግብጽ ጦር በኢትዮጵያ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አማራጮች ለማሳየት ሞክሯል፡፡
ከፎርብስ ትንታኔ ብንነሳም ጦርነቱ ተመራጭ የሆነው አማራጭ ሆኖ አናገኘውም፡፡ የግብጾች እቅድ ግድቡን ማውደም እንደሆነ የሚያትተው
ፎርብስ ይህንን ለማድረግ ግን መሰናክሎች እንዳሉ ይዘረዝራል፡፡ ለግብጽ ሀይል ዋነኛው ፈተና የሚሆንበት ከግብጽ እስከ ኢትዮጵያ
ያለው ርቀት ነው፡፡ አሁን ካለችበት ርቀት አንጻር ለአየር ላይ ጥቃት እንኳን አመቺ አይደለም፡፡ ግብጽ ሊኖራት የሚችለው ብቸኛው
አማራጭ ለግድቡ ቅርብ የሆነችው የሱዳንን የአየር ክልል መጠቀም ነው፡፡ እንደ ፎርብስ ትንተና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ካላት ቅርበት
አንጻር ቀጥተኛ የጦር ፍጥጫ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡
በፎርብስ የተቀመጠው ሌላኛው አማራጭ ግብጽ ልዩ ሀይልና ታጣቂዎችን በመላክ ኦፕሬሽን ማካሄድ
ነው፡፡ በዚህ አካሄድ የግድቡን ፕሮጀክት ማዘግየት ወይም ማስተጓጎል ትችላለች፡፡ ሱዳን በዚህ ግዜ ልዩ ሀይሉ ሰርጎ ስለመግባቱ
ምንም አይነት ግንዛቤ እንደሌላት ትናገራለች፡፡ በዚህ ሁኔታ ታጣቂዎችን መላኳ ግድቡን ለማውደም ዋስትና ሊሆን አይችልም ላል ፎርብስ፡፡
ምክንያቱ ደግሞ እነዲህ ያሉ ግድቦች በልዩ ወታደራዊ ሀይል የሚጠበቁ መሆናቸው ነው፡፡ የግብጽ ወታደሮች የፈለገ የሰለጠኑ ቢሆንም
ቁጥራቸው አነስተኛ ሆኖ መግባታቸው እቅዳቸውን እንዳያሳኩ ያደርጋቸዋል ይላል የፎርብስ ትንታኔ፡፡ በማጠቃለያው ላይም ግብጽ የፈለገው
ሀይል ቢኖራት ርቀት ስለሚገድባት ሙሉ የቶር ሀይሏን መጠቀም አትችልም፡፡ የትኛውንም አማራጭ መጠቀም ለግብጽ ዋጋ ያስከፍላታል፤
ይለናልፎርብስ መጽሄት፡፡
ስለዚህ፡ በየትኛውም መንገድ ብንሄድ ጦርነቱ ሩቅ ያለ፡ ብዙ አማራጮች ያልተሟጠጡበትና እንደ
መጨረሻ አማራጭ ልናየው የሚገባ እንጂ፡ እንዲሁ ዝም ብሎ ሳያመዛዝኑ ዘው ብለው የሚገቡበት አይደለም፡፡ ጽሁፌን አንድ በላይ ከተባለ
ወዳጄ በሰማኋት ተረት ልቋጫት፡፡
ባልና ሚስት ናቸው አሉ፤ አንድ ቀን ይጣሉና ሚስት ረዘም ያለ መንገድ አቆራርጣ ከአባቷ ዘንድ
ትሄዳለች፡፡ አባትም የልጃቸው ያለወትሮ መምጣት ስገርማቸውና ‹‹ልጄ ምን ሆነሽ መጣሽ?›› ይሏታል፤ ልጅትም ‹‹ከባሌ ጋር ተጣልቼ››
ትላቸዋለች፡፡ አባት ‹‹በምን ምክንያት ተጣላችሁ?›› ብለው ጥያቄ አከሉ፤ ልጃቸውም ‹‹እየበላን ሳለ አጉርሺኝ አለኝ አላጎርስም
አልኩት፡ተጣላንና መጣሁ፡›› ብላ መለሰች፡፡ አባት ይሄኔ ‹‹ከባልሽ አፍና ከአባትሽ ቤት የቱ ይቀርብሻል?›› ሲሉ ጥያቄ አከል
ምላሽ ሰጧት፡፡

No comments:
Post a Comment