Wednesday, June 12, 2013

ቅኔው ህዝብ እና ደንባራ መሪዎቻችን



 
በመሀመድ ሀሰን

አፍ ተለጉሞ ሀገራዊ ዝምታ በነገሰበት፣የኑሮ ውጣ ውረድ በህዝቡ ጫንቃ ላይ በተጠመደበት፣ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በቁጥጥር ስር በዋለበት፣ ፍርሀት ዘውዱን የደፋ በመሰለበት፣ መፈናቀሉ በበረታበት፣ የስደት እልቂት ተመራጭ በሆነበት፣ በየሰበቡ መንገዶች ሁሉ ወደ ቃሊቲ በሚወስዱበት፣ ፕሬስ በሌለበት፣ ፖለቲከኞች በተዳከሙበት፣ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነ እድር፣ ሀይማኖት፣ እቁብ፣ ንግድ፣ ፍ/ቤት፣ ት/ቤት….. በሌለበት፤ ህገመንግስታዊ መብቶች በተነፈጉበት፣…. ወቅት ቅኔ የሆነው ህዝብ ሚስጥር የሆነው ማንነቱን ባለፈው እሁድ ግንቦት 25 ቀን2005ዓ.ም ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰምቷል፡፡ ይህን ህዝብ ቶሎ ማኮሰስም ሆነ ቸኩሎ ማወደስ አስቸጋሪ መሆኑን በተደጋጋሚ ማስተዋል ችለናል፡፡ ከ9 ወር በፊት የአውራው ፓርቲ ጠ/ሚንስትር ለነበሩት አቶ መለስ ያለቀሰው ህዝብ ነው ባለፈው እሁድ ‹‹ሆሆ..!!›› ብሎ ወጥቶ የስርዓታቸውን አስከፊነት የገለፀው፡፡ ለዚህ ነው አንዳንድ ሰዎች ገና መጠናትና መመርመር፣ ያለበት ቅኔ ህዝብ ሲሉ መደመጥ የጀመሩት፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ቅኔነት ደግሞ ይበልጥ ሲያስበረግጋቸው የተስተዋለው ባለስልጣናቱን ነው፡፡ቅኔነቱን ለመፍጠር የነሱ አስተዋፅኦ ምን እንደነበር ከመመርመር ይልቅ ሲደነብሩ ተስተውሏል፡፡ በደንባራ መሪዎቻችን ላይ የነበረው ቃጭልም ወዲያው ነበር ቂል-ቂል የተሰማነው፡፡ መደንበራቸው ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳም ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ፣ ከበርካታ መብቶቹ ውስት አንዷን ብቻ መዞ የተጠቀመው ህዝብ ላይ እንደደነበሩ መረማመድን መርጠጠዋል፡፡
ባለፈው ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ተጠራውን ሰልፍ አስመልክቶ፡ ሰልፉ ከተፈቀፈቀደ ቦሃላም ሆነ ከመፈቀዱ በፊት በርካታ ትችቶች ሰምተናል፤ ሙግቶች አስተውለናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የኔን ትኩረት ሰቅዞ የያዘው ሰልፉን ከጠራው ሰማያዊ ፓርቲ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው፡፡ ሰልፉ ከመካሄዱ ቀደም ብሎና ሰልፉ ከተካሄደ በኋላ ፓርቲው ለከፍተኛ ሀሜት ተጋልጧል፡፡ ሰልፉን እያስፈቀዱ በነበረበት ወቅት እነዚህ ሰዎች የማይመስል ነገር ለምን ይሞክራሉ ሚል አስተያየት ነበር የበረከተው፡፡ ሲፈቀድላቸው ደግሞ ማን አደባባይ ሊወጣላቸው ነው … ያለ አንዳች ምስጢርማ ይህ ሰልፍ አልተፈቀደላቸውም…. የሚለውን ጥርጣሬ የተጫነው አስተያየት አስከተልን፡፡ የሰልፉን ስኬታማነት ተከትሎ ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ቀዳማዊ ጠርጣሪዎች ሙቀቱን ለመጋራት ሲራኮቱ፣ የተቀሩት ደግሞ ለቀደመው ሀሜታቸው ማጠናከሪያ በመፈለግና አዳዲስ ተለጣፊ ታርጋዎችን ማዘጋጀታቸውን ቀጠሉ፡፡

እነዚህ ከላይ ያነሳኋቸው ሰሞነኛ ነጥቦች ተራና የአንድ ሰሞን ጫጫታ መስለው ቢታዩም ረጋ ብሎ ለመረመራቸው ግን፣ ለዘመናት ተጠናውተውን የቆዩትን የፖለቲካ ባህላችንን ወለል አድርገው የማሳየት አቅም አላቸው፡፡ በሽኩቻ አዙሪት የጦዘው፤የሰከረው፤የደቀቀው፤የተንኮታኮተው፤የተመናመነው፣… ፖለቲካችን ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከሚነሱት ሀሳቦች ጠቃሚነት ይልቅ ሀሳቡን ያነሳው ግለሰብ ላይ መንጠልጠል፤ፊትለፊት የቀረበልንን ትተን ሌለው ያልተነገረንን መፈለግና በመሰለን መንገድ ነገር መሰንጠቅ ፖለቲካዊ ባህላችን ከሆነ ቆየ፡፡ አዙሪቱ ዛሬም ተጠናክሮና መልኩን ቀይሮ ቀጥሏል፡፡
ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም የተጠራው ሰልፍ በዋነኛነት አራት ነጥቦችን ያነሳ ሲሆን ሌሎች ተያያዥ የመብት ጥያቄዎችም ተካተውበታል፡፡ነጥቦቹም፡-
1.  የህሊና እስረኛ የሆኑት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ጋዜጠኞች ይፈቱ!
2.  ሰዎችን በዘራቸው እየለዩ ከመኖሪያቸው ማፈናቀሉ ይገታ!
3.  መንግስት በሀይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባቱን ያቁም!
4.  በሙሰኞች ላይ እርምጃ ይወሰድ! የሚሉ ናቸው፡፡
አሁን እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሰከን ብለን ማሰብ ያለብን የተነሱት ነጥቦች ምን ያህል                                                                       አንገብጋቢናቸው፣ ጠቀሜታቸው ምን ያህል ነው፣ አስፈላጊነታቸውስ ወዘተ… የሚሉትን ነጥቦች እንጂ፡ ማን አነሳው የሚለው ከነጥቦቹ ቀድሞ ሊመጣ አይችልም፡፡ በተነሳው ሀሳብ ቅዱስነት ከተስማማን፡ እንኳን አይደለም አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ፣ ኢህአዴግና ሰይጣንም ቢያነሱት ክፋት የለውም፡፡
በግለሰቦች ላይ ከተንጠለጠለ ተራ አሉባልታ ይልቅ ሌሎች እውነትነት ያላቸውን ለእውነት የቀረቡ ጥያቄዎች ቢነሱ፣ ትግሉን ከመጉዳት ይልቅ ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ጥያቄዎችን መሰንዘር ይቻላል፡፡ የግለሰቦች ሽኩቻና አምልኮ አሁን ሰልፉን ባስተባበረው ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ላለመንገሱ ዋስትናው ምንድነው?፣ በዕለቱ የተንጸባረቀውን የህዝብ ስሜት የእውነት ተቀብሎ የማስቀጠል አቅምና ችሎታቸው እንዴት ነው?፣ ኮታ ከመሙላት በዘለለ ይህንን ህዝብ ከነትግሉ ይዞ ማቆየት እንዴት ይቻላቸዋል?፣ ህዝቡ ያስተላለፈውን መልዕክት ምን ያህል ተረድተውታል?፣…የሚሉትን ጥያቄዎች ለአብነት ያህል መጠየቅ ይቻላል፡፡
የግንቦት 25ቱ ሰልፍ መንግስት ላይ ከፍተኛ ሽብር ከመፍጠሩ በበለጠ፣ ለተቃዋሚዎችም ጭምር ከፍተኛ መልዕክት እንዳስተላለፈ ይሰማኛል፡፡ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን በመጥራቱና ህዝቡ እንዲሰባሰብ ላደረገው አስተዋጽዎ የሚገባውን ዋጋ ልንነፍገው አይቻለንም፡፡ ነገርግን ያ ሁሉ ህዝብ ሰማያዊን አውቆት፡ደግፎትና አምኖት ወጣ ማለት አይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ህዝቡ የተመቻቸለትን መድረክ ተጠቅሞ፡ ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ፣ ቤተመንግስት ድረስ የተዘረጋ ቀይ ምንጣፍ እንዲጠብቃቸው ለሚሹ ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጭምር ትልቅ የቤት ስራ ሰጥቷል፤፡ የሚሰማ ከተገኘ፡፡
ሲደናበር የተሰማው የመንግስት ቃጭል
ቀደም ብሎ በአንድ ግለሰብ ሲዘወር የነበረው የኢህአዴግ መንግስት፣ አሁን ላይ ደግሞ የሙት መንፈሱን ጨምሮ፣ በጥቂት ‹‹ሼም›› የለሾች እየተዘወረ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ፓርቲና ጥቂት ዘዋሪዎቹ በ 22 ዓመታት ውስጥ እንኳን እንመራዋለን ከሚሉት ህዝብ ጋር መተዋወቅ አልቻሉም፡፡ ፈላጭ ቆራጮቹና ህዝቡ በብዙ ነገር እየተላለፉ ተቸግረዋል፡፡ ባለስልጣናቱ ታገልንለት የሚሉትን የህዝብ ጥያቄ ከመደላድላቸው ቦሃላ ከጫማቸው ስር አውለው ጨፍልቀውታል፡፡ ከህዝቡ ጋር እንደ ህዝብ ስለማይኖሩም በራሳቸው ግዚያዊ ድሎት ውስጥ ሆነው ረግጠው የያዙት ህዝብ መኖሩን ይዘነታል፡፡ ሁሉንም ጠፍጥፎ በመስራት በአምሳላቸው እንደቀረጹት ያስባሉ፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ተጨፍልቆ ሸክማቸው የከበደው ህዝብ የስቃይ ህይወት ይገፋል፤ ያቃስታል፣ ያጣጥራል፤ አንዳንድ ግዜ ጫናው እጅግ በጣም ሲበዛና መፈናፈኛ ሲገኝ ደግሞ ከፍ ባለ ድምጽ የስቃዩን መጠን ይገልጻል፡፡ ከመሪዎቹ ጆሮ ደርሶ ከምቾታቸው የሚቀሰቅሳቸውም ይሄው ድምጽ ነው፡፡ መኖሩን የዘነጉት ድምጽ እንዲህ ባለው ግዜ እንደሚያስበረግጋቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ከግንቦት 25ቱ ሰልፍ ጋር በተያያዘ የሆነውና የተፈጠረውም ይሄው ነው፡፡ መደንበራቸውን የነገረን ቃጭላቸውም ከስልት ውጭ ሆኖ በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡
እንደ ግንቦት 25 ያሉና ሌሎች መሰል የመብት ጥያቄዎችን ያዘሉ ድምጾች በሚሰሙበት ግዜ፣ የገዢው ፓርቲ መለያ ሆነው የሚመጡ ተለምዷዊ ባህሪያት አሉ፡፡ ቀዳሚው ግን በመደንበር የሚሰጠውና እርስ በርሱ የሚጣረሰው ምክንያት አልባው የባለስልጣናቱ መግለጫ እና አቋም ነው፡፡ በተለመደው መገለጫቸው ላይ ግዜ አባክነን ሰፋ አድርገን እንዳንነጋገርበት፣ እነደነሱ የብዙ መገናኛ ብዙሀን ባለቤት አይደለንምና ገጽ ቆጥበን የተወሰኑትን ብቻ ለሀሳብ ማጫሪያነት እናንሳቸው፡፡
ሰልፉ በተካሄደበት ዕለት የነጻነትን መንገድ ጀምሬዋለሁኝ ሊለን ሞክሮ ያልተሳካለት ኢቴቪ፡ የኢኮኖሚ እድገታችንን ከአሸባሪነት መስፋፋት ጋር በማነጻጻጸር እውቀት አጠር አስተያየት የሰጡት አቶ ሽመልስን ቀርጾ አቅርቦልንልን ነበር፤ ፍሬ ሀሳብ አልነበረውም እንጂ፡፡ ከተቀረጸው ውስጥም ‹‹…ሰልፍ አልተከለከለም…መከልከልም አይችልም፡፡…›› አይነት ንግግር አቅርቦልናል፡፡ አቶ ሽመልስ ምናልባት እየነገሩን ያሉት ቀበሌ ስለሚጠራው ሰልፍ ይሆን እንዴ?፣ በሀገሩ ላይ ሆኖ የውጭ ሀገር መሪን ያውም እንደ ግራዚያኒ ያለውን ጨካኝ ወንጀለኛ ለመቃወም ሰልፍ የወጡ ሰዎችን የምታስር ሌላ ሀገር ትኖር ይሆን?፣ ፓርቲያቸው እንደ ታክሲ፡ዳቦ፡…ላሉ ችግሮች እንጂ ለመፍትሄ መሰለፍን የሚቃወም ስለመሆኑ ከእሳቸው ውጪ እማኝ መጥራቱ አይከብድም?... ቀጠሉና ደግሞ እራሳቸው በጠቀለሏቸው መገናኛ ብዙሀን እንኳን ማቆሚያ ለማይኖረው ጥያቄ የሚዳርጋቸውን ምላሽ ሰጡ፡፡
በተቃውሞው ላይ የተነሳው ነጥብ መንግስት እርምት የወሰደበትና እሱን አስታኮ ለማምጣት የታሰበው ፖለቲካዊ ትርፍም እነደማይሳካ በመንገር ግራ አጋቡን፡፡ በእርግጥ እዚህ ጋር በታማኝ ፓርቲያቸው ላይም ሳይቀር ፋውል ሰርተዋል፡፡ ቢያንስ ችግሩ ነበር በሚለው ይስማማሉ፡፡እንደው ለእሳቸው ብቻ በሚመች መንገድ እንኳን ጥያቄ እንሰንዝር ቢባል፣ እርምት የወሰዱባቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? እርምት ተወሰደ እንኳን ብንል፣ ያልተስማሙ ወገኖች አለመስማማታቸውን በህብረት ሆነው መግለጻቸው ምንድነው ክፋቱ? ከሰልፉ ጋር በተያያዘ ሌሎች ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ትርፍ ስላለማግኘታቸው እርግጠኛ ከሆኑ ለም እርሳቸውና ባልደረቦቻቸው የከሰረ ዛቻና ፉከራ መሰንዘር አስፈለጋቸው? የእነርሱ መክሰር ለሌሎ ትረፋማነት አስተዋጽኦ አይኖረው ይሆን?
ሌላው በጣም የገረመኝ ንግግር ደግሞ ‹‹ኃይማኖት በፖለቲካ፡ ፖለቲካ በኃይማኖት ውስጥ ጣልቃ አይገባም …›› የሚለው ነው፡፡ አቶ ሽመልስ ይህንን ዓረፍተ ነገር የነገሩን ትርጉሙ ባልገባን ቋንቋ ካልሆነ በስተቀር፡ በሚገባን አማርኛ ሲነገር የሰማነውና እያየን ያለነው ግን ‹‹ፓርቲያቸው በሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በትዳር ላይም ጭምር ጣልቃ ይገባል..›› ሲባል ነው፡፡ ትግራይ ላይ የአረና ፓርቲ አባላት የገጠማቸውን ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን አንድ አይነት ቋንቋ እያወራን መግባባት አልቻልንም፡፡
ከህግ ጋር በተያያዘ አቶ ሽመልስና ሌላኛው የፓርቲ ወዳጃቸው ያነሷት ነጥብ ለምርጥ ኮሜዲያንነት ሳታሳጫቸው አትቀርም፡፡ ‹‹...በህግ የተያዘን ጉዳይ… ፍርድ ቤት ላይ ጫና ለማሳደር …›› ምናምን  የምትለዋ ማጨናበሪያ በጣም አስቂኝ ናት፡፡ በህግ የተያዘ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ ፍርድ  የመስጠት ልማድ የማን እንደሆነ ለማወቅ፡ ከጎናቸው ተቀምጦ የነበረውን ልማታዊ ጋዜጠኛ ወደ ኢ.ቴ.ቪ የምስል ክምችት ክፍል ቢልኩት፡ እነርሱ ደግሞ ትንሽ ወደ አራ ኪሎ አጥሩን አለፍ ብለው ቢያማትሩ፡ ያገጠጠውን እውነት ለኛም ሹክ ይሉን ነበር፡፡
ለማንኛውም መሪውና ተመሪው መተያየት አልቻሉም፡፡ህዝቡ ምንም አያመጣም ፤ማንም ወደ ሰልፉ አወጣም፤ በሚል ንቀት ውስጥ ያልጠበቁት ጩሕት አባነናቸው፡፡ ጩሕቱን ከማድመጥ ይልቅ ግን እንደለመዱት ድምጹን የጥቂቶች ሲሉ ፈርጀውታል፡፡ ጥያቄውንም ሊሰሙት የማይፈልጉት በመሆኑ ሁከት የሚል ስያሜ ሰጡት፡፡

ለምን ሙስሊሙን?
ከሁሉም በላይ ግን የባለስልጣናቱን ቃጭል ድምጽ የጨመረውና እኛም እንድንሰማው ያደረገው፡ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ አስገራሚ በሆነ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ውስጥ የሚገኘው የሙስሊሙ ማህበረሰብ፡ ለባለፈው እሁድ ሰልፍ ከፍተኛ ድምቀት ሰጥቶት ተስተውሏል፡፡ይህ ማለት ግን መሪዎቹ እንደሚሉት ሰልፉ ሙስሊሞች ብቻ የተሳተፉበትና የሙስሊሞች ጥያቄ ብቻ የተነሳበት ነው ብሎ ማለት፡ ከሌላ ያአደባባይ ላይ ቅጥፈት ይጥላል፡፡ በእርግጥ ሰልፉን ከሙስሊሞች ጋር ብቻ አያይዘው ለማውራት መፈለጋቸው በራሱ የሚነግረን እውነታ ይኖራል፡፡ እንደ ጭራቅ፡አደገኛ፡አሸባሪ….እንዲታይ ይፈልጉት የነበረው የሙስሊሙ ማህበረሰብ፡አደባባይ ወጥቶ ከክርስቲያን አጋሮቹ ጋር ያሳየው አንድነት ፍጹም ያልጠበቁትና ያስደነገጣቸው ትእይንት ነበር፡፡ የሙሰስሊሙ ጥያቄ ተገቢነት በሰልፉ ላይ ያለልዩነት ተስተጋብቶ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ አጋርነታቸውን በይፋ አሳይተዋል፡፡  አጅበዋቸውም ስግደት ፈጽመዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ሁሉንም ነገር ከሙስሊሞች ጋር ለማያያዝ መሞከሩ በሌላ በኩል በትግላቸው የወሰዱበትን ብልጫም ጭምር ማሳያ ነው፡፡ የሙስሊሙ ጥያቄ የእያንዳንዱ ሙሰሊም ጥያቄ በመሆኑና የጸና አቋምም ስላላቸው፡ ጥያቄያቸውን ከመመለስ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ባለፈው ሳምንት በድረ ገጽ ላይ ያነበብኳት የ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› ጽሁፍም፡ አስረግጣ የምትናገረው ይህንኑ እውነታ ነው፡፡‹‹…የሚሊዮኖችን የመብት ጥያቄ በሃይል ለመፍታት ማሰብ የሚታሰብ መንገድ አይደለም፡፡ጥያቄዎችን ኃይማኖታዊ፡ ትግላችንም ሰላማዊ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል ተገቢውን ትኩረትና መፍትሄ መስጠት ከተደጋጋሚ የፖለቲካ ክስረትና ህዝባዊ መቃቃር ያድናል፡፡ ትግላችን መብታችን እስኪከበር ድረስ ሰላዊ ሆኖ ይቀጥላል !ለዚህም አንዳች ጥርጥር የለንም!››ከጽሁፉ የተቀነጨበ፤  

No comments:

Post a Comment