Monday, February 25, 2013

መሰረት ደፋር የግማሽ ማራቶን፣ አበሩ ከበደ የማራቶን አሸናፊዎች ሆኑ


የሳምንቱ መጨረሻ ቀን ባለድል አትሌቶች መሰረት እና አበሩ
የሳምንቱ መጨረሻ ቀን ባለድል አትሌቶች መሰረት እና አበሩ
የሁለት ጊዜ የ5 ሺህ ሜትር ኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ኢትዮጵያዊቷ ድንቅ መሰረት ደፋር አሜሪካ ኒው ኦርሊንስ ውስጥ እሁድ የካቲት 17 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር አንደኛ በመውጣት የስፍራውን ክብረወሰን ሰብራ በአሸናፊነት አጠናቃለች። መሰረት በታሪኳ ሁለተኛዋ የሆነውን የግማሽ ማራቶን ውድድር ለማጠናቀቅ 67 ደቂቃ ከ26 ሰከንዶች ወስዶባታል።
በተመሳሳይ ቦታ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች አንጋፋው እና የቀድሞው የአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮን ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም ሁለተኛ ደረጃን አግኝቶ አጠናቋል። ብሪታኒያዊው ሞ ፋራህ በኬኒያዊ ማርቲን ሌል ተይዞ የነበረው የስፍራውን ክብረወሰን በመስበር አሸንፏል።
ጃፓን ቶኪዮ ውስጥ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አበሩ ከበደ የሴቶቹን ውድድር በአሸናፊነት አጠናቃለች። አበሩ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2 ሰአት ከ25.34 ደቂቃ ሲወስድባት ሁለተኛ የወጣችው ሌላዋ ኢትዮጵያዊት የሺ ኢሳያስ ርቀቱን በ2፡26፡01 አጠናቃለች። አበሩ እና የሺ ከ25ኛው ኪሎ ሜትር ጀምሮ ተነጥለው በመውጣት አብረው ከሮጡ በኋላ ርቀቱ ሊጠናቀቅ 10 ኪ.ሜ ያህል ሲቀረው አበሩ ለብቻዋ ተነጥላ በመውጣት በመሮጥ ነው በአሸናፊነት ያጠናቀቀችው።
አበሩ ውድድሩን በድል ካጠናቀቀች በኋላ በሰጠችው አስተያየት “የስፍራውን ክብረወሰን ለመስበር ሀሳብ የነበረኝ ቢሆንም ነፋሻማው የአየር ሁኔታ እና በተለይ ከ37ኛው እስከ 41ኛው ኪ.ሜ ድረስ ያለው ዳገት ነገሮችን አስቸጋሪ አድርጓቸዋል” ብላለች።
በወንዶች የቶኪዮ ማራቶን ውድድር ኬኒያዊያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች በማግኘት ሲያጠናቅቁ አሸናፊው ዴኒስ ኪሜቶ በ2፡06፡50 ጊዜ የስፍራውን ክብረወሰን ሰብሯል።
በተያያዘ ዜና በ30ኛው የጃን ሜዳ አለም አቀፍ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ፈይሳ ሊሊሳ እና ሂዎት አያሌው በአዋቂ ወንዶች እና ሴቶች አሸናፊ ሆነዋል።
በአዋቂ ወንዶች የ12 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ፥ የመከላከያው ፈይሳ ሊሊሳ በበላይነት ሲያጠናቅቅ ፤ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶቹ ይገረም ደመላሽ ሁለተኛ ፣ መወስነት ገረመው ከአማራ ሶስተኛ እና አበራ ጫኔ እና ተስፋዬ አበራ አራተኛ እና አምስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
በስምንት ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች ሂዎት አያሌው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንደኛ ፣ ገነት ያለው እና የብርጓል መለሰ ከመከላከያ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ሲያጠናቅቁ መሰለች መልካሙ እና በላይነሽ ኦልጅራ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃን አግኝተዋል።
በውድድሩ ላይ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ በመሆን ውድድራቸውን ያጠናቀቁ አትሌቶች የፊታችን መጋቢት ወር አጋማሽ በፖላንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአለም ሃገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ይሳተፋሉ።

No comments:

Post a Comment