Main page

Wednesday, June 5, 2013

የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ከፍተኛ አመራሩ ችግር እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቆሙ



05 June 2013 ተጻፈ በ   
-    በዩኒቨርሲቲዎች የአስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች አሉ ተብሏል
-    የዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ተጓቷል
-    የትምህርት መሣሪያዎች አቅርቦት ችግር መኖሩ ተገልጿል
-    ለዘርፉ ከተመደበው ከፍተኛ በጀት አንድ ቢሊዮን ብር ያህሉ ተመልሷል

መንግሥት በቀረፀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የትምህርት ሥርዓቱን ለማሻሻልና በተደጋጋሚ የሚተችበትን የጥራት ችግር ለመቅረፍ ትልቅ ትኩረት ቢሰጥም፣ የተጠቀሱትን ግቦች በማሳካት ረገድ በዕቅድ ዘመኑ አጋማሽ የተገኙ ውጤቶች አጥጋቢ አለመሆናቸው ተገለጸ፡፡
ዘርፉን የሚመሩት የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ለችግሩ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ያሉ አመራሮችን ወቅሰዋል፡፡

የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት የዘርፉ ተዋናዮችን አመለካከት መቀየር በዋነኝነት የተያዘ ፕሮግራም መኖሩን፣ ይህም “የለውጥ ሠራዊት ግንባታ” በሚል ስያሜ ትግበራ ውስጥ መገባቱን ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የ11 ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርት ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ፕሮግራም መሠረት የለውጥ ምክር ቤት፣ የልማት ቡድንና የአንድ ለአምስት አደረጃጀቶችን በመፍጠር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት በአጠቃላይ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና፣ በከፍተኛ ትምህርትና በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በመክፈል የለውጥ ሠራዊትን የማደራጀት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ ከእነዚህ አደረጃጀቶች ጋር ተጣምረው መሥራት የሚችሉ የሕዝብ ክንፍ አደረጃጀቶችን የመፍጠር የተግባር እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ የለውጥ አደረጃጀቶች የታቀደውን ውጤት ለማምጣት የሚያስችሉ ጅምር ሁኔታዎች መኖራቸውን፣ ከእነዚህም መካከል የለውጥ አደረጃጀቶቹ ስለለውጥ በለውጥ ቋንቋ መነጋገርና መግባባት መጀመራቸው፣ በፕሮግራሙ መሠረት በየስድስት ወራት የአፈጻጸም ምዘና እየተካሄደ መሆኑ በጥንካሬ ሊታዩ የሚችሉ ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ነገር ግን የለውጥ ፕሮግራሙ ዓበይት ዕቅዶችን በመፈጸም ረገድ ችግሮች ይስተዋላሉ ችግሮቹም ቁልፍ ናቸው ብለዋል፡፡ ከሚኒስትር ጀምሮ ከፍተኛ አመራሮች መንጠባጠብ ይታይባቸዋል፡፡ የድጋፍና የክትትል ሥራው መቆራረጥ ይታይበታል፤ የልማት ቡድኖችን ማስፋትና ማመጣጠን እንዲሁም ሁሉንም ሥራዎች በሚጠበቀው ደረጃ አቀናጅተው እየመሩ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ “መካከለኛ አመራሩ ደግሞ የለውጡን ሥራ መመርያና ትዕዛዝ ሰጥቶ ሪፖርት የመቀበል አሠራር አድርጎ የመቁጠር መሠረታዊ የአመለካከት ችግር አለበት፤” ብለዋል፡፡ እንዲሁም ሥራውን በሚፈለገው ብቃት፣ መጠንና ጥራት ለመፈጸም የሚያስችል የአቅምና የክህሎት ችግሮች በመካከለኛ አመራሩ የሚስተዋል መሆኑን ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በሠራተኛው በኩል ደግሞ አዳዲስ አሠራሮችን ለመቀበል መጠራጠር፣ የጠባቂነት ስሜትና ከተለመደው አሠራር ያለመውጣት በዋናነት የተስተዋለ ችግር ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ችግሮቹ የተለዩ በመሆኑ በቀጣይ የተጠቀሱትን ማነቆዎች ለመፍታት መንቀሳቀስ የሚኒስቴሩ ተልዕኮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተማሪዎችን ውጤት በሁሉም የትምህርት ዓይነት ለማሻሻል በተያዘው ዕቅድ መሠረት የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ከዕቅድ በታች መሆኑን፣ ይሁንና ከቀደሙት ዓመታት መሻሻል ይታይበታል ብለዋል፡፡ “ነገር ግን በእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ በሒሳብና ሳይንስ ትምህርቶች የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ ነው፤” ብለዋል፡፡

በአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ 70 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች በሳይንስ ዘርፍ የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ወስኗል፡፡ ነገር ግን በታችኛው የትምህርት ክፍል በሳይንስ ዘርፍ የታየው ዝቅተኛ ውጤት ከተቀመጠው ፖሊሲ ጋር አይጣጣምም፡፡ በመሆኑም ጉዳት አለው የሚል ጥያቄ ከምክር ቤቱ አባላት ቀርቦላቸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ችግሩን ለመቅረፍና ለማጣጣም ሥራው መጀመሩን፣ የታየው ዝቅተኛ ውጤት አጠቃላይ የአገሪቱን ሁኔታ ቢገልጽም የለውጥ ሠራዊት በጥሩ ሁኔታ በተገነባባቸው ሞዴል ትምህርት ቤቶች በተጠቀሱት የትምህርት ዓይነቶች በግብ ከተያዘው በላይ ውጤት ማስመዝገቡንና ስለዚህ ይህንን በአገር አቀፍ ደረጃ በማስፋት ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል፡፡ በሒሳብና በሳይንስ ትምህርቶች ላይ የታየውን ዝቅተኛ ውጤት ለማሻሻል የሥልጠና ማቴሪያሎች መዘጋጀታቸውን፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርትን ለማሻሻል ለመምህራን ሥልጠና የሚያገለግሉ አሥር ሞጁሎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አስረድተዋል፡፡

ይህ የሚኒስትሩ ንግግር የመምህራን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃትን ጥያቄ ውስጥ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ አንድ የምክር ቤቱ አባልም በዚህ የቋንቋ ችግር የተነሳ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የመመረቂያ ጥናታቸውን የአገር ችግር ለመቅረፍ በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ከመጨነቅ ይልቅ ለቋንቋው የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ተመራቂ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መመረቂያ ጥናታቸውን እንዲሠሩ ቢደረግ ጥቅሙ የጐላ አይሆንም ወይ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ሚኒስትሩ በቀረበው አማራጭ ላይ ያልተስማሙ ሲሆን፣ የተስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ የበለጠ መሥራቱ የተሻለ መፍትሔ ነው ብለዋል፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት የተጀመሩት አዳዲሶቹ 13 ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቅ ባመቻላቸው፣ በተማሪዎች ኑሮና በአስተዳደር ሥራ ላይ ተፅዕኖ መፈጠሩንና ከዓመት በፊት የተጀመሩት ሌሎች ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታም ተጓቷል ብለዋል፡፡ ይህ ችግር የተፈጠረው በተቋራጮችና በአመራሮች ችግር የተነሳ ነው በመሆኑም ጠንካራ ክትትልና የማስተካከል ሥራ ይጠይቃል የሚል መፍትሔ አስቀምጠዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የመማሪያ መጻሕፍትንና ጆርናሎችን በአንድ ቋት በማደራጀት በጋራ በኢንተርኔት እንዲጠቀሙ እየተሠራ ቢሆንም፣ በ13 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የተዘረጋው ኔትወርክ በኢትዮ ቴሌኮም መሠረት ልማት አለመሟላት አለመጀመሩ ይህም በመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ እንቅፋት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት መሣሪያዎች አቅርቦት ላይም ችግር መኖሩን የሚናገሩት ሚኒስትሩ፣ በኢንጂነሪንግ የሥልጠና ዘርፍ የታቀደው የመጻሕፍት አቅርቦት ብቻ አፈጻጸሙ 92 በመቶ በመሆኑ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ባደረገው የ2004 ዓ.ም. የበጀት አፈጻጸም ኦዲት ከፍተኛ ምዝበራዎችና ብልሹ አሠራሮች መኖራቸውን ለምክር ቤቱ በቅርቡ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ሚኒስትሩ የተጠቀሰው ችግር ውስብስብ መሆኑን በመጥቀስ ችግሩን ለመቅረፍ አግባብነት ያላቸው የዩኒቨርሲቲ አመራሮች የሚሳተፉበት አገራዊ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክር ቤት መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ ችግሮቹን ለመዋጋት ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመሆን ከዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ማኅበረሰቦች ጋር በተደራጀ ሁኔታ ትግል ተጀምሯል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የሀብት አስተዳደርና በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደረጉ ትንኮሳዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ንቅናቄ ውስጥ ተገብቷል ብለዋል፡፡

የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ዘንድሮ 3.38 ቢሊዮን ብር ከመንግሥት እንደተመደበለት፣ ከ2004 ዓ.ም. ለአዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ወደ 2005 ዓ.ም. በመተላለፉ አጠቃላይ በጀቱ 4.361 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አጠቃላይ በጀት ውስጥ ባለፉት አሥር ወራት 3.25 ቢሊዮን ብር ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ የተቀረው የበጀቱ አካል ከዚህ በኋላ ሥራ ላይ የማይውል መሆኑን በመገንዘብ ለመንግሥት ተመላሽ ሆኗል ብለዋል፡፡

ከቀረቡት ሪፖርት ላይ በርካታ የአፈጻጸም ችግሮች መኖራቸውን ያስተዋሉ አንድ የምክር ቤቱ አባል፣ “ገንዘብ እያለ ሥራዎች እንዴት ይጓተታሉ? እንዴትስ በማስፈጸም ችግር ገንዘብ ይመለሳል?” በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የተወሰኑ ግዥዎች በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሳቢያ በመጓተታቸው፣ እንዲሁም አንዳንድ ፕሮግራሞች ተሻሽለው በሌሎች የመንግሥት ተቋማት በመከናወናቸው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

reporter

No comments:

Post a Comment