ስራ
አስኪያጁ እና ዋና አዘጋጁ አሁንም በእስር ላይ ናቸው
ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 11ቀን 2006 ዓ.ም የ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ አዘጋጆች እና ባለቤቶች
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባቀረበባቸው ክስ የተነሳ ሐዋሳ ድረስ በመሄድ ሊጉላሉና ስራቸው ሊስተጓጎል ችሏል፤ አዘጋጆቹ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
በተከፈተባቸው ክስ የተነሳ፣ ሐዋሳ ድረስ በመመላለስ ለተጨማሪ ስቃይ እና እንግልት መዳረጋቸው ቀጥሎ፣ ጋዜጣዋ ለገበያ በቀረበች
ማግስት እለተ እሮብ ጥቅምት 20 ቀን 2006 ዓ.ም፣ የ‹‹የኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ አባላት (ስራ አስኪያጁ ሚሊዮን ደግነው፣ ዋና
አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ እና ከፍተኛ አዘጋጁ ኤፍሬም በየነ) በቀጠሯቸው መሰረት ሀዋሳ ቢገኙም፣ የተሰማው ዜና ግን የፍርድ ቤት ውሏቸውን
ብቻ የሚያትት አልነበረም፤ ከወደ ሐዋሳ የተሰማው አሳዛኝ ወሬ ሶስቱ የ‹‹የኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ ባልበረቦችን ይዛ ትጓዝ የነበረችው
ባጃጅ (ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሊሆን ይችላል በተባለው) የመገልበጥ አደጋ እንደደረሰባት የሚገልጽ ነበር፡፡
በወቅቱ የደረሰው አደጋ እና ከክሱ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ብዙዎችን ያነጋገረ ከመሆኑ ባለፈ፣
በኤፍሬም ላይ የደረሰው ከፍተኛ የጉዳት መጠን ግን ይበልጥ ልብን የሚሰብር ነበር፤ ሁለቱም እግሮቹ ምንም እንደማይንቀሳቀሱ ሰማን፤
በተጨማሪም የሳንባ ችግር ገጥሞት ወደ ማገገሚያ ክፍል መግባቱ ተወራ፤ እራሱን ችሎ በእግሩ መቆም ለተሳነው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ
ደግሞ እንዲህ ያለው ጉዳት ተጨማሪ የራስ ምታት ነው፤… ከትርፍ ይልቅ የቀጣዩን ህትምት የማተሚያ ቤት ክፍያ ለማሟላት ለሚፍጨረጨሩ
የግል ፕሬሶች፣ በኤፍሬም ላይ የደረሰው አይነት ጉዳት እና ለውስብስብ ህክምናው የሚያስፈልገው ወጪ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ››
የሚሉትን ብሂል የሚያስታውስ ነው፡፡ እንዲህ ያለው እውነት የ ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች በርካታ የሀገሪቱ ነጻ ፕሬሶችም
የሚጋሩት ነው፡፡
ጉዳዩ አሁንም በተለዋጭ ቀጠሮ ምክንያት መፍትሄ አላገኘም፤ ከአዲስ አበባ እስከ ሐዋሳ የተዘረጋው
የ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ የክስ ሂደት እና መከራም አሁን ባለበት ሁኔታ የተቋጨ አይደለም፤ ክሱ በሀዋሳ መታየቱን እንዲቀጥል
ፍርድ ቤቱ ወስኖ ለህዳር 10 ቀጥሯቸዋል፤ ያኔ የሚመጣው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እና በሌሎች ባልደረቦቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለው ተጨማሪ
ስቃይ እና እንግልትም ለፈጣሪ የሚተው ይመስላል፡፡
ከዚህ ሁሉ ስቃይ ቦሃላ፣ ቅዳሜ እለት (ጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ.ም) ለቀጣዩ ስራቸው ወደ
ቢሯቸው ጎራ ያሉት የጋዜጣዋ አዘጋጆች፣ ከወደ ለገጣፉ በመጣባቸው ሌላ ክስ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በእለቱ ሰድስት ኪሎ ስብሰባ ማዕከል
አከባቢ ወደሚገኘው የጋዜጣዋ ዝግጅት ክፍል ዘው ብለው የገቡት ከለገጣፉ የመጡ ፖሊሶች እና ሌሎች ተባባሪዎቻቸው ጸሀፊዋን እና ሚሊዮንን
ይዘው ሄደዋል፤ በወቅቱ ለስራ ጉዳይ ወጣ በማለቱ ከእስር የተረፈው
ዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ ለቀጣዩ እትም መሯሯጥ ጀመረ፤ የጋዜጣውን ስራ ከጨረሰ ቦሃላም ሰኞ እለት ቃሉን ለመስጠት ባልደረባው
ሚሊዮን ደግነው ወደታሰረበት ለገጣፉ ቢያመራም ለእስር ተዳርጓል፤ እስከ ቀጣዩ አርብም (ምናልባትም ከዛ በላይ) በእስር እንደሚቆይ
ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ሰኞ ቃሉን ሳይቀበሉ እንዳሳደሩት፣ እንዲሁም ማክሰኞ ቃሉን ሳይቀበሉት እንደዋለ የነገረኝ ጌታቸው፣
ማክሰኞ ቃሉን ሳይሰጥ በእስር ቤቱ በተሰየመው ግዚያዊ ችሎት ቀርቦ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀበት ቢሆንም፣ቦሃላ ላይ ግን
አርብ (ጥቅምት 29) በሰንዳፋ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ታዟል፡፡ የጌታቸውን ጉዳይ የያዙት ፖሊስም ሳጅን ተፈሪ ሲሳይ ይባላሉ፡፡
No comments:
Post a Comment