Main page

Friday, October 18, 2013

ማንኩሴዎች ሲበረክቱልን! ከበእውቀቱ ወደ ሀብታሙ



በመሐመድ ሐሰን

‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› በተሰኘው ተዓምራዊ ልብወለድ መጽሀፍ ነው ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በዛብህ ቦጋለ የተባለ ማንኩሴ ገፀ- ባህሪ ያስዋወቁን፤ የሀዲስ ዓለማየሁ በዛብህ የተሰኘው ስም ለአንድ ኢትዮጲያዊ አዲስ ባይሆንም፣ የበዛብህ የትውልድ አካባቢ ተደርጋ የተሳለችው ማንኩሳ ግን ለብዙዎቻችን አዲስ ነበረች፤ ከዚህ ግዜ ጀምሮ እንግዲህ እኔን ጨምሮ በርካቶች በምናብ ከምንናፍቃቸው አከባቢዎች አንዷ ለመሆን በቅታለች ማንኩሳ፡፡
ከዘመናት  ቆይታ በኃላ ደግሞ  በዕቀቱ ስዩም የተባለ ፀሀፊ ወደ ድርሰቱ ዓለም ገባና፣ ‹‹ክንፋም ህልሞች›› በተሰኘ ስራው ላይ ማንኩሳን ‹‹ ቀበሮ ጀምሮ የተወው ጉድÕድ ትመስላለች›› ሲል ገለፃት፡፡ ያም ሆኖ ግን በምናብ ከምንነጉድባቸውና በአካልም ለመሔድ ከምንuምጥባቸው ቦታዎች አንዷ ከመሆን አላገዳትም፡፡ ምናልባት ብዙዎቻችሁ ወደ ማንኩሳ እንድትነጉዱ የሚያደርጋቸሁ፣ ከበዛብህ ቦጋለ ቀጥሎ በዕውቀቱ ስዩም ይሆናል፤ እሱም በአንድ ወቅት መዓዛ ብሩ የጨዋታ እንግዳ አድርጋ ባቀረበችው ወቅት፣‹‹ከበዛብህ ቦጋለ ቀጥሎ በቅኔ  መንፈስ የሚታወቅ ማንኩሴ  ቢኖር እኔ ነኝ፤›› በሚል ፌዝ አከል ንግግር ማድረጉን አውቃለሁ፤ በእርግጥም ይህንን ንግግር እኔ ከፌዝ ባለፈ እውነታነትን እንዳዘለ ከሚያምኑት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ነገር ግን፣ በተለይ በአሁን ሰዓት ማንኩሳ ስትነሳ ከበዛብህ ቀጥሎ ቶሎ ወደ ህሊናዬ የሚመጣው በዕውቀቱ አይደለም፤ ‹‹እና ታዲያ ማንን ልትጠራ ፈለግክ? አንተ ደፋር!›› ካላችሁኝ፣ ምላሼ ስዩም የሚል ነው፤ መምህር ስዩም መሰለ!
ዛሬ በጡረታ ተገልለው ማንኩሳ ላይ የከተሙትና በማርቆስ የእንጊሊዘኛ መምህር የነበሩት የአቶ ስዩም መሰለን ቤተሰብ ስንከተል የምናገኛቸው ወጎች፣ታሪኮች፣ ልማዶች፣ህይወቶች ፣ሰዎች ፣…. ተነግረው የማያልቁ አስደማሚዎች ናቸው፡፡ ‹‹ኤርትራዊ ናችሁ›› ተብለው የተባረሩትና የሰፈሩን ልጆች በጣፋጭ አንባሻቸው ያሳደጉት የአቶ አስፋው ሚስት እማማ ሀለፎም፣ በሱዳን ገዳማት ለረዥም ዘመናት የቆዩትና በወጋቸው መሐል ‹‹የአላህ!.....›› እያሉ ወሬያቸውን የሚቀጥሉት መነኩሴዋ አያታቸው ፣በአካባቢው የነበሩ ጠንካራ ወጎችና ልማዶች፣ በቤታቸው ውስጥ በእሳት ዙሪያ የሚካሔደው የተረትና የግጥም ውድድር እንዲሁም ጨዋታ፣ የአባትና ልጆች ግንኙነት፣ የባልና ሚስት ግንኙነት፣ … ብቻ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ብዙ ጣፋጭ ወጎች የሚወጡት ስብስብ ነው በዙሪያቸው ያለው ማህበረሰብ፡፡
ማንኩሴዎችና ማርቆሴዎች ከጥበብ ጋር ያላቸው የመንፈስ ቅርርቦሽ ጥብቅ ሊባል የሚችል ነው፤ ከማንኩሳ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘውና የስዩም ቤተሰብ ሌላኛዋ መኖሪያ በሆነችው ማርቆስና አከባቢዋ ያሉ ሰዎች፣ የጥበብ ፍቅራቸውን ለመግለፅ በሰፈሩ ጉብላሊቶች (የስጡም ልጆችን ጨምሮ) የተደረሱ ድራማዎችና ቲያትሮችን ለማየት ወንበር ከየቤታቸው ተሸክመው ነበር የሚታደሙት፡፡ ታዲያ የማይረባ ስራ ለመለየት ግዜና የጋዜጣ ገፅ አይጠብቁም፤ እዛው መድረክ ላይ ያልጣማቸውን ስራ ያጥረገርጉታል፡፡ ጀማሪዎቹም እንዲህ ያለውን ትችት በመልመዳቸው፣ የተሻለ ነገር ለማምጣት ዘወትር በሚያደርጉት ጥረት ወደ ብስለት ይሸጋገራሉ፤ ሒሳቸውንም እጅ በመንሳት ጭምር ሰጥ ለጥ ብለው ይውÚታል፡፡
ይህ ባህል በአካባቢዋ ሁሉ ተዛምቶ ሳይሆን አይቀርም፣ በባህር ዳርና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከሎች ይቀርቡ ለነበሩ የማይረቡ ስራዎች፣ የአካባቢው ተወላጆች ወደ አቅራቢዎቹ ጫማቸውን ጭምር በመወርወር ነበር ምላሽ የሚሰጡት፡፡ በተለይ ዛሬ በኢትዮጲያ  ቴሌቪዥን ላይ ከኔ በላይ ለኢህዴግ ተቆርuሪ ፣ ለመሪዬ ተቆርuሪ፣ …ላሳር እያለች በሬሳዎች አካባቢ ጭምር በመንጎማለል የምትሳለቀው አንዲት ‹‹ጋዜጠኛ?›› ተብዬ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግጥም ስራዎን ታቀርብ በነበረበት ወቅት ምላl ጫማና ጩኸት እንደነበር ፣አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ በእርግጥ ኢቴቪን ካነሳን አይቀር በዚህ ጣቢያ ውስጥ ከዛ ጥበበኛ ህዝብ መሀል (ማርቆስና አከባቢዋ) ወጥተው ለሆዳቸው ያደሩ ብዙ ሆድ አደሮች እንዳሉ ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡
ቀደም ብዬ በጠቀስኩት መንገድ ጠንከር ያለ የጥበብና የንባብ ባህል ተጠናክሮ ከሚካሔድባቸው ቤቶች አንዱ ነው የመምህር ስዩም ቤት፡፡ እስከ ጥግ ድረስ ነፃነት በሚሰጡ አባትና ወግ አጥባቂ በሆኑት እናት ወ/ሮ ሀገሬ ከበደ መካከል ያደጉት ልጆቻቸው  በእሳት ዙሪያ በሚጋሩት ጥበባዊ ስራ የተለያዩ የአድናቆትና የተግሳፅ አስተያየት እየሰሙ ነው ያደጉት፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ ለጥበብ ስራ ማጣፈጫነት ገጸ በሀሪ ፍለጋ ብዙም ርቀው አይማስኑም፤ አካባቢያቸውንና የቤተሰቡን አካል ጭምር ለዚህ የማዋል ትልቅ አስተውሎት አላቸው፤በተለይ አሁን የጎረመሰውና ያኔ በልጅነቱ ኮልታፋ የነበረው ዱኒ አሁንም ድረስ የቤተሰቡ ወግ ማጣፋጫ ነው፡፡ይህ ቤተሰብ የማያባራ የሳቅ ምንጭ ነው፤ ፖለቲከኛው፣ ዘፋኙ፣ ጋዜጠኛው፣…ሁሉም በዚህ ቤት ውስጥ ያለገደብ ወደጨዋታው መድረክ ይዶላሉ፡፡ ከንባብ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው የመምህር ስዩም ቤተሰብ ውስጥ ሁሉም አንድ አይነት ተሰጥኦ አላቸው የሚባሉ አይደሉም፤ ለምሳሌ ዱኒ በአባቱ የግጥም ችሎታ ይስቃል፤ ይዝናናል፡፡
በንባብ በኩል ሁሉም የየራሳቸው ጣዕም ያላቸው ናቸው፡፡ እናት ወ/ሮ ሀገሬ ከበደ የስለላ መፅሁፍትን አጥብቀው የሚወዱ ሲሆን፣ ከስለላ ጋር በተያያዘ ያላነበቡት ስራ እንደሌለ ከቅርብ ሰው ሰምቻለው፤ በዚህ መነሻነትም አንደኛው ልጃቸው ‹‹ እናታችን የስለላ ስራዎችን አብዝታ ከማንበቧ የተነሳ ልጆን በከፍተኛ ንቃት ውስጥ እየሰለለች ያሳደገች ሰላይ እናት ነው ያለችን፤›› ሲል እውነትን ከፌዝ ጋር ቀልቀል አድርጎ ያስፈግጋል፡፡ ይኸው ልጃቸው በአንድ ወቅት የስለላ ስራዎችን በብዛት በማሳተም የሚታወቁት አንጋፋው ደራሲ ማሞ ውድነህ ሞተው በነበረበት ወቅት፣ የሆነ ሰው መፅሀፋቸውን እንዲዘረዝርለት አጥበቆ ሲጨቀጭቀው፣ ‹‹ ለምን ሀገሬ ከበደ ጋር አትደውልም!›› የሚል ምላሽ ይሰጠዋል፡፡
የመምህር ስዩምን የንባብ ባህል ደግሞ ጤና በራቀው uu ከገለጽነው እብድ ያሉ የመፅሀፍ ቀበኛ ናቸው፤ በዓለማችን ላይ የገዘፈ ስም ያላቸውን የራሽያ ደራሲዎች ስራ አንድ በአንድ እንዳነበቡ ልጆቻቸው ጭምር የሚመሰክሩላቸው መምህር ስዩም፣ በተለይ በመምህርነት ዘመናቸው ትጉህ አንባቢ የነበሩ ሲሆን በወቅቱ የወጡና አሉ የተባሉ ማንኛውንም መፅሀፍት ለማግኘት የማይከፍሉት መዋትነት አልነበረም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ በፍፁም እንደማይረሳው ልጃቸው በአንድ ወቅት አጫውቶኛል፡፡ መምህር ስዩም በወቅቱ ይከፈልቸው የነበረው ደሞዝ ብዙም የሚያወላዳ አልነበረም፤ ቀልባቸው ግን አንድ መፅሀፍ ላይ አርፏል፤ የመፅሀፉ ጥማት የበረታባቸው መምህር ስዩም ደሞዝ የተቀበሉ እለት፣ ወደ መፅሀፍት መሸጫው ቦታ ያመሩና የደሞዛቸውን ግማሽ ይሰዋሉ፤ አስቡት የመፅሀፉ ብር ተቀንሶ የቀረው ገንዘብ  ከ6 በላይ የነበረውን ቤተሰብ ለአንድ ወር የማስተዳደር  ግዴታ አለበት፡፡
መምህር ስዩም በዚህ መንገድ የሚገዟቸውን ፣የሚዋሷቸውን፣ከቤተመጽሀፍት የሚያገኙዋቸውን ውድ መፅሀፍቶች ልጆቻቸው እንዲያነቡ ያደርጋሉ፤በእርግም አንብበዋል፤ለልጆቻቸውን ከመፅሀፍ ጋር የማቆራኘት ጉጉታቸው ከልጆቹ እድሜም የቀደመም ነበር፡፡ ለዚህ ማሳያ ከሚሆነው እውነታ አንዱ፣ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ልጃቸው ሀብታሙን ወደ ላይብረሪ (ቤተ-መፅሀፍት) ይዘውት ይሔዱና ከመደርደሪያው ላይ አንድ መፅሀፍ መርጠው ካነሱ በኃላ ‹‹ይኸውልህ ሀብቴ ! ዘ ኦልድ ማን ኤንድ ዘ ሲ! እንዴት ያለ ድንቅ መፅሀፍ መሰለህ!›› ብለው ወኔ በተሞላበት ንግግር መፅሀፉን ይሰጡታል፤ልጅም መፅሀፉን እነደተቀበለ ‹‹እነዴ ! አባዬ እንግሊዘኛ እኮ ነው!›› የሚል ምላሽ ሲሰነዝር፤እሳቸውም  ጠንከር ባለ ድምጸት ‹‹ሀብቴ ! ምን ነካህ ?ፈረንጆቹ ባንተ እድሜ ይፅፋሉ፣ አንተ እንዴት ላንብበው ትላለህ!…›› ብለው ቁጭት ይጭሩበታል፤እሱም ከዛን ግዜ ጀምሮ እየተንገዳገደ የቻለውን ያህል መግለጥ ይጀምራል፡፡ በዚህ መንገድ የተገነባ ጠንካራ የንባብ ባህል ነው መምህር ስዩም ለልጆቻቸው ያወረሱት፡፡ልጆቻቸውን የምናውቅ ብዙዎቻችን ባላቸው የንባብ ጉጉትና አቅም እንገረም ይሆናል፤መሰረቱ ግን ከልጆቹ በላይ ያነበቡት አባት ናቸው፡፡
ከላይ ስለገለፅነው ጠንካራው የጥበብ ፣የሳቅ(የቀልድ)፣ የንባብ፣ የእውቀት፣…ምንጭ ስለሆነው የስዩም ቤተሰብ ካለምኩኝና ካሰላሰልኩኝ እንዲሁም እውቀታቸውን ከተጋራው በኃላ ነው፣ ከዚህ ጠንካራ ቤተሰብ የተገኘውን ማንኩሴ (በዕውቀቱ ስዩም )የማስታውሰው፡፡ በዕውቀቱ እንዲህ ካለው ከፍታ ላይ ከመውጣቱ በፊት ከቤተሰቦቹ ብሎም ከማንኩሳ ባለፈ ማርቆስ ድረስ ባሉ ጥበብ ወዳጆች ተፈትኖና ተሸልሞ ነው ብቃቱን ያሳየው፡፡ የአንባቢው እና የመንፈስ ጠንካራው ስዩም ልጅ በመሆኑ ነው ዛሬ በዕውቀቱ ሀገሪቱ ላይ ካሉ ፀሀፊዎች ሁሉ ውዱና የምንሳሳለት ፀሀፊ ለመሆን የበቃው፤ ለዚህም ነው በዕውቀቱ ከኢትዮጵያ አልፎ አሜሪካና አውሮፓ ጭምር ያሉ ጥበብ አፍቃሪዎች እንዲናፍቁት ያደረገው፤ ለዚህ ነው እኔም ማንኩሴዎችን አብዝቼ የምናፍቃቸውና እንዲበዙልን የምመኘው፤ለዚህምነው ዛሬ የማንኩሳ፣ ያውም የስዩም ፍሬዎች ሲበረክቱልን በደስታ እየቦረቅኩ ብዕሬን ያነሳሁት፤አዎ ማነኩሴዎቹ የስዩም ፍሬዎች በርክተውልናል፤ የበዕውቀቱ ስዩም የሁለት ግዜ ታናሽ የሆነው ሀብታሙ ስዩም ‹‹17 መድሬና ሀያ ምናምን ቁምጣ ›› በሚለው መፅሀፉ አንባቢው ጋር ደርሷል፤ መፅሀፉን ላነበበና ሀብታሙን በግል ለሚያውቀው፣ ከበዕውቀቱ ስዩምና ከአባቱ ጋር ከፍተኛ የመንፈስ ቁርኝት አላቸው፡፡ ሁለቱም የጠንካራ አባታቸው የመንፈስ ውርሶች ናቸው፤ እንዴት የሚለውን በስፋት የመተንተን ጉዳይ ለሌላ ሰፊ ገፅ የምናመቻቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የማውቀውን ያህል ግን በጥቂቱ አወራችኋለው፤ በቅድሚያ ጠንካራው አባታቸውን በቅርቡ በእውቀቱ ስዩም በጉልበታም ብዕሩ እንዴት ስንኝ እንደቋጠረላቸው እንመልከት፡-
           ለአባቴ
ሰው ብቻ አይደለህም፣ካፈር ወጥተህ ላፈር
መላክ ነህ፣ሉሲፈር
ክብርህ ማንነትህ፣ባመጽ የሚታፈር፤
የማትንበረከክ
የማትርመጠመጥ
ከባለጌ ዙፋን
በርጩማ የምትመርጥ
ያለብህር ሰርጎጅ
…ያለሙሴ በትር
በመታገስ ብቻ፣ባህር የምትመትር፡፡
ካዘልከኝ ጀምሮ፣እንኮኮ ጫንቃህ ላይ
ከፍታውን እንጂ፣ ዝቅታውን ሳላይ
እንደንስር መጠቅሁ፣እንደ ምስራቅ በራሁ
የገዛ ክንፎቼን፣እንደ ዳንቴል ሰራሁ፡፡
በርግጥ ደሀ ነበርክ
ከሰላምታ በቀር የማታበረክት
ነጠላህ መናኛ፣ ሰውነትህ የክት፣
በርግጥ ደሀ ነበርክ
የነጣህ የጠራህ
ከጦር ሜዳ ይልቅ ገበያ የሚያስፈራህ፡፡
ቤሳ ባታወርሰኝ አወረስከኝ ትግል
የትም እንዳይጥለኝ ፣ ሕይወት እንደ ፈንግል፡፡
አባየ ብርሃን
ኣባ የምስራቅ በር
ገመና ሸሻጊ፣እንደ ካባ ገበር
አባቴ ባትሆን ይጸጽተኝ ነበር፡፡
በእውቀቱ ስዩም በግጥሙ ላይ የስጋ ብቻ ሳይሆን የመንፈስም ውርሱ የሆነውን የአባቱን ጥንካሬ፣እውነተኝነት፣ትዕግስት፣ጀግንነት፣ውለታ፣ያወረሰውንእውነት፣የአባቱን ብርሀንነት፣…በጥቅሉ የአባቱን ታላቅነት በኩራት ይገልፃል፡፡ ሀብታሙ ስዩምም የአዲሱ መፅሀፍ ማስታወሻነት ደመቅ ጎላ ብሎ  እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹ሃገሬ ከበደና መምህር ስዩም መስለ ለሚባሉ የመጀመሪያየም ሆነ የመጨረሻ የኔ ናሙና ለነበሩ ሰዎች፡፡ታውቃላችሁ አልወዳችሁም፤ አመልካቹሀለሁ እንጂ!››
በተመሳሳይ ሁኔታ በመፅሀፉ የምስጋና ገፅ ላይ አንድ ቦታ ላይ’’…. ልጓም የማልወድ ፈረስ ነኝ፤…››ይላል፡፡ ከዚህም ባሻገር በእውቀቱ ግጥም ውስጥ የተገለፀው አባታቸው ማንነት በሁለቱም ላይ ይንፀባረቃል፡፡ የምርም በዕውቀቱ ከአባቱ፣ሀብታሙ ደግሞ ከበዕውቀቱ ያለምንም አካላዊ ጫና የመንፈስ ውርርሳቸው በግልፅ ይታያል፡፡
ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ይህ ፅሁፍ የሁለቱንም ስራ ሆነ የቤተሰቡን ህይወት ሙሉ ለሙሉ አይዳስስም፤ በዕውቀቱን እና ሀብታሙንም በአንድ ሚዛን ላይ እኩል የማሰፈር ተልዕኮ የለውም፡፡ ሀብታሙን በአካል፤ በእውቀቱን ደግሞ በስራው ደንብ አውቃቸዋለሁኝ፤ሁለቱ ከእድሜም ከተጓዙበት የህይወት ጎዳናም አንፃር አሁን ላይ የማይነጻጸሩባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡  አንዱና ዋነኛው፣ በእውቀቱ በሂደት ያካበተው የንባብ ልምድና ሀብት አይደለም ከሁለት ግዜ ታናሹ ከእኩዮቹ ጋርም የሚነፃፀር አይደለም፡፡ በእውቀቱ በእውነትም በንባብ በኩል ከመምጠቅ አልፎ ለተለያዩ የእውቀት ዘርፎች ያለው ተጋላጭነትም የሚያስደምም ነው፡፡
በነገራችን ላይ ይህንን የንባብ ጉዳይ ጨምሮ ከየትኛውም ስራዎቹ ጋር በተያያዘ፣ የበዕውቀቱ ቁጥር አንድ አድናቂ ከሆኑ ሰዎች ውስጥ አንዱ ሀብታሙ ነው፤ በዕውቀቱን በደንብ ስለሚያውቀውም ይመስለኛል፣የሱን ስራዎች በማንበብ በሳቅ እንባ እየዘራ ሆዱን ይዞ ሲንፈራፈር ያየሁት ሰው ሀብታሙ ነው፡፡ ታዲያ በወንድማዊ መንፈስ እንዳይመስላችሁ፣ ሀብታሙ አንድም ቀን የበዕውቀቱ ወንድም መሆኑን አውርቶ አለማወቁ ብቻ ሳይሆን፣ መሆኑም ጭምር በፍፁም እንዲታወቅበት አይፈልግም፡፡ እሱ እራሱን ችሎ በራሱ መንገድ ተገምግሞ አቅሙን ማሳየት የሚፈልግ ትጉህ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከአባታቸው በወረሱት ጥንካሬ፣ በዕውቀቱ በራሱ ጥረት እዚህ እንደደረሰ ሁሉ፣ ሀብታሙም ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ከነበረው ሂደት ጀምሮ መጽሀፉ እስከታተመበት ባሉት ሶስት አመታት ድረስ በፍፁም በእውቀቱን ተደግፎት አያውቅም፡፡ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የተለያዩ ቦታዎች ስራ ሲጀምር፣ በዕውቀቱ እንደማንም ስራውን ካየ ቦሃላ ነው እውነቱን የሚረዳው፤ ለማመን ቢከብድም የሀብታሙ መፅሀፍ ማተሚያ ቤት እስገባበት ድረስ በዕውቀቱ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ከባህሪያቸው፣ ካለባቸው ውጥረት እንዲሁም ከሌሎች በግልጽ ከማይገቡኝ ምክንያቶች ጋር ተያይዞ ወንድማማቾቹ በአካል የሚገናኙት አልፎ አልፎ ነው፡፡ ያም ሆኖ ታዲያ ነፍሶቻቸው አንድ እስኪመስሉ ድረስ አጥብቀው ከመቆራኘታቸው የተነሳ መንገዳቸውና የሚመሳሰሉባቸው ነገሮች ይበዛሉ፡፡
ሁለቱም አሁን ላለው የየራስቸው ከፍታ ከመድረሳቸው በፊት በተመሳሳይ መንገድ ጥበብን ባገኙት ክፍተት ሁሉ በመስራት እየተሸለሙ ነው የመጡት፡፡ በዕውቀቱ ማርቆስ ውስጥ ፅሁፎች እያሸነፉለት ይሸለም የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ወቅት በቦታው በእንግድነት የተገኙት ሰአሊ እሸቱ ጥሩነህ ይመስሉኝል የለበሱትን ጃኬት አውልቀው ሸልመውታል፡፡ ሀብታሙም ጎንደር ዩንቨርስቲ ውስጥ መድረክን ከመምራት አንስቶ በሚያቀርባቸው ጥበባዊ ስራዎቹ ተደጋጋሚ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡
ወደ አዲስ አበባ እንደመጣም አንድ አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ታላቅየው በዕውቀቱ በተደጋጋሚ ስራዎቹ ወዳሸነፋለት ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር በማምራት ተወዳድሮ ስራው ለህትመት በቅቶለታል፣ ሽልማትም አግኝቷል፡፡ በትምህርቱም በኩል ሁለቱም በተመረቁበት  መስክ አልተሰማሩም፤ በእውቀቱ በሳይኮሎጂ፣ ሀብታሙ ደግሞ በህግ ነው የተመረቁት፡፡ ሀብታሙ እንደውም ወደ ስልጠናው  ማእከል ገብቶ ብዙ ከገፋበት በኋላ ነበር ነፃነትን ፍለጋ ጥሎ በመፈርጠጥ አሁንም ድረስ ላልቆሙ ተደጋጋሚ ክሾችና ተጨማሪ እዳዎች ጭምር የተዳረገው፡፡
ሁለቱም በተመሳሳይ መልኩ ጥበብን በተለያየ ቅርፅ ይከውኗታል፤ በእውቀቱን ከልጅነቱ ጀምሮ ለህትመት እስካበቃችው ስራዎች ድረስ ብንከተለው ተዋናይነት ፣ ተውኔት ፀሀፊነት፣ አጭርና ረዥም ልብ-ወለድ ደራሲነት፣ ወግ፣ኮሜዲ፣ ግጥምና ስዕል ውስጥ የምናገኘው ሲሆን፣ ጅማሮውም ጋዜጠኝነትን መሞካከር ነበር፡፡ በእውቀት ለመጀመሪያ  ጊዜ ወደ ለንባቢዎቹ ያደረሰው በ1995 ዓ.ም “ኗሪ አልባ ጎጆዎች”  የተሰኘውን  የግጥም ስብስብ ሲሆን፣ “የበረሀ ጠኔን” የመሰሉ ድንቅ ፍልስፍናን ያዘሉ ግጥሞቹ የተፃፉት ገና  የዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ በነበረበት ወቅት ነው፡፡
ሀብታሙም ወደ አዲስ አበባ የመጣው በመጀመሪያ ደረጃ ጋዜጠኛ ሆኖ ለመቀጠር ሲሆን፣ እስከ አሁንም ድረስ ይህንኑ ስራውን እየሰራ ጎን ለጎንም ቢሆን እንደወንድሙ ሁሉ ውስጡ ያሉትን ቅርጾች እያሳየን ይገኛል፡፡ ከጎደር ዩቨርሲቲ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የተለያዩ የፊልም ጽሁፎችን እየሰራ ያለው ሀብታሙ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ  ከስራው በተረፈው ግዜ ወደ “ብሉ ናይል” የፊልምና የቴሌቪዥን አካዳሚ ተወዳድሮና በሱ አቅም ከፍተኛ የሚባለውን ክፍያ (በወር 800 ብር) እየፈጸመ የፊልም ጥበብ ትምህርቱን አጠናቆ ተመርቋል፡፡  ሀብታሙ ነፃነቱን ማንም እንዲነካበት የማይፈልግ ሰው በመሆኑ አንዳንዴ ነውጥ ቢጤም ያምረዋል፤ ከፍ ሲል ደግሞ ብስጭቱን በስእል ጭምር  ይገልጻል፡፡  አንድ የማስታውሰውን እውነት እዚህች ጋር ላወጋችሁ ወድጃለው፤ግዜው እኔና ሀብታሙ በአንድ የሬድዮ ጣቢያ ውስጥ በጋራ የምንሰራበት ወቅት ነበር፤ ታዲያ ቤቱ ዘወትር ስብሰባ የሚበዛበትና ነፃነቱንም የሚጋፋው ስለነበር፣ ረዘም ያለው ስብሰባ እየተካሄደ ባለበት ሰዓት ሀብትሽ አቀርቅሮ የሆነ ነገር ይሞነጫጭራል፤ በኋላ ስብሰባው ተጠናቆ የተቀመጠበት ቦታ ላይ ጥሎት የተነሳው ወረቀት ላይ ያየሁት ስዕል የሚገርም ነበር፤ በአንድ የማይክራፎን ሀውልት ላይ ጋዜጠኛው በገመድ ተሰቅሎ የሚያሳይ ስዕል ነበር የሳለው፡፡ ከዚህ በኋላ ተደጋጋሚ የስዕል ሰራዎችን ሲሰራ ማስተዋል ችያለው፡፡ በሌላ በኩል ሀብታሙ አጭርና ረዥም የሬዲዮ ድራማዎችን፣ ጭውውቶችን፣ ወግ፣ የዘፈን ግጥም እና ግጥሞችን የሚፅፍ ሲሆን፣ እንደ በእወቀቱ ሁሉ ቀድሞ ለማሳተም አዘጋጅቶት የነበረው የግጥም ስራውን ነው፤ ነገር ግን ሁል ግዜም “አብዝቼ ማዳመጥ የምፈልገው ስሜቴን ነው” የሚለው ሀብታሙ፣ በቅድሚያ 17ቱን መድፌና ሀያ ምናምኑን ቁምጣ ሊያቀብለን ወዷል፡፡ 
በአሁን ሰዓትም ከሬድዮ ጋዜጠኝነቱ ጎን ለጎን ቀድም ብሎ ወንድሙ ይሰራበት በነበረው የቀድሞው “ሮዝ”  የአሁኑ “አዲስ ጉዳይ” መጽሄት ላይ ፌዝ (ሳቅ) ያዘሉ ቁም ነገራም ወጎቹን እያስኮመኮመን ይገኛል፤ ይህ ቦታም የተገኘው ያለ ወንድሙ እገዛ ሲሆን፣ በእውቀቱ ጽሁፉን ያየው ከአንባቢዎች እኩል መጽሄቱ ገበያ ላይ ከዋለ በኋላ ነበር፡፡ 
ነፃነታቸው ትልቅ ስንቅ የሆናቸው ሁለቱ የስይቲ (በሀብትሽ አገላለፅ) ፍሬዎች፣ በፁሁፋቸው ውስጥ የራሳቸው የሆኑ ጣእሞችና መልኮች ያሏቸው ልባም ፀሀፊዎች ናቸው፡፡ ሳቅ እንደጎርፍ ከሚፈስበት ቤት የተገኙት ማንኩሴዎች (ማርቆሴዎች) በሀገራችን ላይ ሳቅ ያንሳል ብለው ያምናሉ፤  ለዚህም ይመስላል የሁለቱም ጾሁፎች ውስጥ የፌዝ ፍጆታ ከፍ ባለ መጠን ጥቅም ላይ የሚውለው፤ ታዲያ ፌዞቹ ጥርስን ብቻ ሳይሆን አእምሮንም ከፈት (ነቅነቅ) የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በተለይ ከፍ ያሉ የፍልስፍናም ሆነ ሌሎች ሀሳቦችን በብቃት በማንሳት ደረጃ በእውቀቱ ዳገቱ ላይ ብቻውን የተቀመጠ ቢሆንም፣ “አማረኛን (ቃላትን) በተለየ ገጽ” በማየቱ በኩል ሁለቱም የተሳካላቸው ፌዘኞች ናቸው፤ በተለይ ደግሞ ሀብታሙ ይህንን ዘመን ይበልጥ ሰለሚቀርበው እንዲህ ያለችውን ፍተላ ተክኖባታል፡፡
እነዚህ የስዩም ፍሬዎች ጥበብን ተጠምተዋታል፣ አጣጥመዋታል፣አድገውባታል፣ ፈትሸዋታል…በመሆኑም አሁን ላይ ለጥበብ ያላቸው ክብርና በራስ መተማመናቸው ብቃታቸውን በደንብ ይገልጸዋል፡፡  በይበልጥ በእውቀቱ ሀገራችን ውስጥ ብዘም በጽሁፍ ብቻ መኖር ባልተለመደበት ሁኔታ እሱ የሙሉ ጊዜ ፀሀፊ ከመሆኑም ባሻገር፣ፈተናውን እንደሚያልፍም ጭምር ቀደም ብሎ በልበ ሙሉነት ይናገር ነበር፡፡ “የተለያዩ ስራዎችን በመሞከር አዲስ ደሴት (ህዋ) ለማሳየት እፈልጋለሁ…አንባቢው ትንሽ ነው ግን እንፈጥረዋለን!”  በሚል እርግጠኝነት ሁኔታውን ሲገልጥ የተደመጠው በእውቀቱ፣የእውነትም ትንቢቱ የሰመረለት ይመስላል፤  በአሁን ሰዓት ማንም የሱንም ሆነ የወንድሙን ስራዎች ይናፍቃል፡፡ ባህልን፣ ፖለቲካን፣ ሀይማትን፣ ታሪክን… ሁሉንም ናጥ አድርገው በእውቀትና በፌዝ ይመረምሩታል፤ እኛንም ወደነሱ ምናብ አስጥመው ያመራምሩናል፡፡
ለማንኛውም የገባሁበት የቤተሰብ ማዕበል በቀላሉ የሚወጣበት ባለመሆኑ፣ እንደምንም ብዬ ባልተገባ አጨራረስ ጥጌን ካልያዝኩ የጋዜጣዋ ሙሉ ገፆች ላይበቁኝ ነው፡፡ እንዲህ ያለው  ተናፋቂ ቤተሰብ ደግሞ በተለይ እንደባለቤቶቹ የተባ ብእር ባላቸው ልጆች ቢገለፅ ይበልጥ ይጣፍጣል፤  እንዲያም እንዲሆን እንጠብቃለን፡፡ እኔ ግን ጉዳዩን እዚህች ጋር ልቋጨውና፣ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የሀብታሙ ስዩም “17 መድፌና ሀያ ምናምን ቁምጣ”  የተሰኘውን መጽሀፍ በሌላ ቀን እንደምመለስበት ቃል በመግባት ብንሰነባበት እመርጣለሁ፡፡ ታዲያ ክረምትን ጠብቀው በጭን ብቻ ሊያሞቁን የተመኙ ቀሽም ፀሀፊዎችና መጽሀፎች ገበያውን በሞሉበት ሰዓት የደረሰልንን “17 መድፌና ሀያ ምናምን ቁምጣ”ን እንድታነቡት ስጋብዛችሁ በልበ ሙሉነት ነው፤ እኔ ሀብትሽ ገላግሌ ብየዋለሁኝ፤ ዘመናችንን በደንብ አድርጎ ከሽኖታል፡፡ የቻላችሁ የአንድ ቀን የግማሽ ኪሎ ስጋ ዋጋችሁን ለመጽሀፉ ብትሰዉ፣  እንደማትቆጩ አሁንም በእርግጠኝነት ደግሜ አረጋግጥላችኋለሁ:: 

No comments:

Post a Comment