Main page

Wednesday, September 18, 2013

2006- በክረምቱ የተበላሸውን ሀገርና ትውልድ የተቀበልንበት ዓመት?



በቀደሙት ግዚያት ክረምት መጣ ሲባል ተማሪዎች፣መምህራን፣ገበሬውና ሌሎችም ሰራተኞች በየፊናቸው ሊከውኗቸው የሚጓጉላቸው ተግባራት ነበሩ፡፡ መምህራኑና ተማሪዎች እንደልብወለድ ያሉና ሌሎችም ትምህርታዊ ያልሆኑ ስራዎችን በማንበብ እራሳቸውን ዘና አድርገው ተጨማሪ እውቀት የሚገበዩበት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለቀጣዩ ዓመት ትምህርትም ጭምር የሚዘጋጁበት ግዜ ነበር፤ ከወዳጅ ዘመድና ቤተሰብ ጋር በተሻለ መገናኛ ግዜም ጭምር ነበር የክረምቱ ወቅት፡፡ በበጎ ተግባራት ላይ ይሰማሩ የነበሩ በጎ ፈቃደኛ መምህራንና ተማሪዎች ቁጥርም ቢሆን ጥቂት የሚባል አልነበረም፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የትምህርት ግዜ መዘጋቱን ተከትሎ ያለው የመጽሀፍት ግዢና መዋዋስ አብዮት በፍጹም ከህሊና ሊጠፋ የሚችል አይደለም፡፡… እነዚህ ሁሉ ተናፋቂ ነገሮች የሚከወኑበት ያ ጣፋጭ ክረምት፣ እንዲሁም ሀገርን በመለወጡ በኩል ትልቅ ሚና የሚጫወቱት መምህራንና ተማሪዎቹ  አሁን ላይ በርካታ ጋሬጣዎች ተደቅነውባቸዋል፤ እኔ ግን ሁለት ነገሮች ይበልጥ ጎልተውብኛል፤ ክረምቱ በሁለት ጎራዎች ተጠልፏል፤ አንዱ የገዢው ፓርቲ ስልጠና ሲሆን፣ ሌላኛው ክረምትን አስታከው የሚወጡ ከመንፈስ ይልቅ ለስጋ የቀረቡ ‹‹መጽሀፍት?›› ናቸው፡፡
፩ ስልጠና
የኢህአዴግን መንግስት ከተጠናወተው ከፉ ደዌ አንዱና ዋነኛው ስልጠና ነው፤ ለሁሉም ነገር መፍትሄው ስልጠና ነው ብሎ ያምናል፡፡ በአሁን ሰዓት ሀገሪቱ ውስጥ ነገሮችን በመጠቀ እይታ የሚተነትነው ፊታውራሪው ምሁር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በስልጠና አባዜያቸው ላይ ድንቅ እይታ አለው፡፡ ከዶክተሩ ትንታኔ ውስጥ የተወሰኑትን ዓብይ ነጥቦች ላስቀምጥ፡-
 ‹‹ልክ ኦሪት ተሸሮ ወንጌል የሚሰበክበት ዘመን እንደሚባለው፣ በልማታ ማህበረሰብ (ኢህአዴግንና ስርዓቱን በምናባዊ መንገድ የሚገልጹበት ቋንቋ ነው) ትምህርት ተሸሮ ስልጠና የሚሰበክበት ዓለም ነው፤…ትምህርት ማለት ወደ እውቀት ለመድረስ የአንድን ሰው አእምሮ ማበልጸጊያ (መኮትኮቻ) ነው፤…ስልጠና በሌላ በኩል የተወሰነ ግብ ተይዞ፣ የተወሰነ ሙያ (scale) ለማግኘት የምንከተለው ዘርፍ ነው፤…›› ካሉ ቦሃላ በስልጠና ና በትምህርት መካከል አሉ የሚሏቸውን ነጥቦች በስፋት ይዘረዝራሉ፡፡ ትምህርት ብዙ ግዜ፣ገንዘብ፣…እንደሚፈጅና በርካታ ውጣ ውረዶች እንዳሉት ግቡም እውቀት እነደሆነና በተቃራኒው ደግሞ ስልጠና በተወሰነ ግብና በጀት የሚከናወንና የተወሰነ ግንዛቤ፣ሙያ፣ክህሎት…የሚጨበጥበት እንደሆነ  ዶክተሩ በማሳያ ጭምር በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡ በሌላ በኩል ዶክተር ያስቀመጡት ነጥብ ‹‹…ስልጠና የአንድ ትምህርት ዘርፍ እንጂ ስልጠና የበላይ ትምህርት የበታች መሆን አይቻለውም!...የትምህርት ጎዳና አዝጋሚ በመሆኑ በትምህርት የሚገኘውን ነገር ሁሉ በአቋራጭ ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ነው፤…ስልጠና ጫንቃው የማይችለው ነገር ሁሉ ተሰጥቶታል፤›› የሚል ነው፡፡ ስልጠና አንዳንዴ እንደ ዶክትሬሽን የሚወሰድ በመሆኑም አሰልጣኝ ያለውን ብቻ አራግፎ የሚሄድበት፣ ተማሪዎቹ (ሰልጣኞቹ) ደግሞ ዝም ብለው የሚቀበሉበት አደገኛ አካሄድ መኖሩን፣ እንዲሁም በስልጠና የተፈጠረውን ችግርም ጭምር በስልጠና ለመፍታት የሚደረገው ሩጫ አደገኝነትም በዶክተሩ ከተነሱት ነጥቦች ውስጥ ናቸው፡፡
የኢህአዴግን የስልጠና አካሄድ ዶክተሩ ደህና አድርጎ ስላስቀመጠው ብዙም ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም፤ ይልቅ አሁን በስልጠና ይገኛል ከተባለው የተወሰነ ክህሎት ዝቅ ባለ ሁኔታ በአሁን ሰዓት በስልጠና ሰበብ የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች በሙሉ አላማቸው አንድና አንድ ይመስላል፤ ይህም የፓርቲውን ህልውና በማስጠበቅ ላይ ብቻ ያተኮረና አካሄዱም ፍጹም ሀላፊነት የጎደለው ይመስላል፤ ስልጠናዎቹ የሚሰጡት በሰልጣኙ ፍቃደኝነት ላይ ያልተመሰረተ ከመሆኑም በተጨማሪ የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል እንኳን ማሰልጠን እንዳለባቸው በአግባቡ የተረዱት አይመስልም፡፡ ሰራተኛው፣ገበሬው፣ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣አስተማሪው፣ተማሪው፣ ታዳጊው፣…ማንም ከሞት ከኢህአዴግ ስልጠና አያመልጥም፡፡  በዛ ላይ አሰልጣኝ ተብዬዎቹ በወጉ እንኳን ትምህርታቸውን ያልተማሩ ተራ ካድሬዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ በእርግጥም እንዲህ ያለውን እውነታ መታዘብ ቀላል ነው፡፡
እንግዲህ በክረምቱ በዚህ ስልጠና ከተጠለፉት ውስጥ መምህራንና ተማሪዎች ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ በተለይ መምህራኑ (የዩኒቨርሲቲ መምህራን ዋነኞቹ ናቸው) የኢህአዴግ ስልጠና ዋነኛ ዒላማዎች ናቸው፡፡ በየትምህርት ተቋማቱ ያሉ ጥቃቅንና ከፍተኛ ሀላፊዎች ክረምቱን ሙሉ የገዢውን ስልጠና (ፕሮፖጋንዳ ቢባል ይበልጥ ይገልጸዋል) ሲጠጡ ነው የከረሙት፡፡ አስቡት እንግዲህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትውልድ ይቀርጻሉ በሚል ተስፋ የተጣለባቸው ‹‹ምሁራን›› (በእርግጥ አብዛኞቹ ሹመኞች ናቸው) ከላይ በገለጽናቸው ካድሬዎች በኩል ስልጠና እየወሰዱ ነው፤እነዚህ የየትምርት ክፍሉ ሀላፊዎች ነገ ወደየ ግቢያቸው ሲመለሱ ለበታቾቻቸው የሚያስተላልፉትን ትዕዛዝና የሚሰጡትን አመራር መገመት ብዙም አይከብድም፤ የበታቾቻቸው ደግሞ በተማሪዎቻቸው ላይ…በቃ! ተያይዞ ገደል መግባት ነው፡፡
ክረምትን ማንም ከኢህአዴግ ውጪ እንዳያስብ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱት አመራሮቹ፣ በየቦታው ህዝቡን በተመሳሳይ ስልጠናዎች የጠመዱት ሲሆን፣ መምህራኑ ጥለዋቸው በሄዱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ደግሞ ታዳጊ ተማሪዎች (ከ9 እከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች) ለስምንት ሳምንታት እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡ ተማሪዎቹ በጉብዝናቸው የተመረጡ ሲሆን፣ ለማበረታቻ በሚመስል መልኩም ከየክፍሉ ከሴቶች ጋር ብቻ በመወዳደር አንደኛ የወጡ ሴት ተማሪዎች ተካተዋል፡፡ እርግጥ የዚህ ስልጠና ዓላማ ባልከፋ ነበር፤ ነገር ግን የስልጠናው አወጣጠን ፍጹም ጥናት ያልተካሄደበት የግብዞች ስራ ከመሆኑ በተጨማሪ ቤኒቨርሲቲዎች ውስጥ ቆይተው ስልጠናውን እንዲወስዱ መደረጉ በራሱ ብዙ ትችቶችን የሚጋብዝና ስርዓቱም ለትምህርት ያለው ንቀት የት ድረስ እንደወረደ ማሳያ አድርገው የሚያቀርቡት ብዎች ናቸው፡፡
በፖለቲካ የማጥመድ ስራውን በየትምህርት ቤቱ በለስላሳና በኬክ በማታለል የሚተጋው ኢህአዴግ፣ከሰሞኑ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለ8 ሳምንታት ‹‹ላሰለጠናቸው›› ተማሪዎች ይበልጥ ትኩረት የሰጠው በመጨረሻዎቹ ሶስት ቀናት ነበር፤ ‹‹ለምን በነዚህ ቀናት?›› የሚል ጥያቄ ከተነሳ መልሱ በነዚህ ቀናት የተሰጠው ስልጠና ከፌዴራሊዝም እና ከህገ መንግስቱ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፤ ስለዚህም በነዚህ የመጨረሻ ቀናቶ ውስጥ ከየቀበሌው የተሰባሰቡ ካድሬዎች እየተረባረቡ አጠመቋቸው፤ ‹‹ዋነኛ አላማቸውም ይህ ይመስል ነበር፤›› ብሎኛል ከተካፋዮች መካከል አንድ ስሙ የማይጠቀስ ሰው፡፡ እንግዲህ በዚህ አሰራር ሀገሪቱ ላይ አሉ የሚባሉ ቁልፍ ሰዎች በሙሉ አንድ አይነት ጥምቀት ተጠመቁ ብሎ አምኗል ፓርቲው፡፡
፪ መጽሀፍት
በእርግጥ አሁን ላይ ከመጽሀፍት ጋር ያለውን ነገር ማንሳት በራሱ የራስምታት አለው፤ የወረቀት ዋጋው መናርና መንግስትም ከአእምሮ ልማት ጋር በገጠመው ጸብ የተነሳ ለዚህ ምንም መፍትሄ ባለማበጀቱ፣ አይደለም መጽሀፍትን የተመናመኑትን የህትመት ውጤቶች እንኳን ገዝቶ ማንበብ ከማይደፈርበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ አእምሯችን ገና ሳይበለጽግ፣ የሚነበቡ ነገሮችን መግዛት ቅንጦት የሆነባት ሀገር ለመሆን በቅታለች-ኢጥዮጵያ፡፡ ከመጽሀፍቱ ጀርባ የሚያርፈው ዋጋ መጽሀፍቱን ከመግዛት ይልቅ ‹‹መግዛት ነበር!›› እያልን እንድናልፋቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉ መጽሀፍት ሻጮችም መጽሀፍት ቤታቸውን ወደ ስጋ ቤት መቀየራቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ሩሯቸውን ለመደጎም ሲሉም መደርደሪያቸውን በደብተር እየሞሉት ነው፤ አቤት የደብተሩ ዋጋ! የዘንድሮ ወላጅ ግን እንዴት ነው የሚችለው?! በጣም የሚያስደነግጥ ዋጋ ነው የሚጠራው፡፡
የኔ ዋናው ጉዳይ ግን ከጥቂት መጽሀፍትና ከብዙ ደብተሮች ጎን ለጎን ተደርድረው ያየኋቸው ‹‹መጽሀፍት?›› ናቸው፡፡ ‹‹ጥበበ ፍቅር››፣‹‹የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገመና››፣‹‹ካማሱትራ››፣‹‹ጣፋጭ በቀል››፣ ‹‹ፍትህን በራሴ››፣‹‹የማይረካ ጥማት››፣ ‹‹የፍቅር ኬሚስትሪ››፣‹‹የስኬት መንገዶች››፣‹‹የዓለማችን ምርጥ የፍቅር ታሪኮች››፣አሜኬላ ያደማው ፍቅር››፣‹‹ራስን መፈለግ››፣‹‹የሀብት መንገድ››፣‹‹ፍርሀትን አትፍራው››፣‹‹FM 66.6››፣… ኡ ፍ! ልብ ያደክማሉ፤ የአብዛኞቹ መልዕክት ጭንነ ሀብት ተኮር ሲሆን፣ ሽፋናቸውም በእርቃን ጭምር ያጌጠ፣ እራሳቸውንም ፈልገው ያላገኙ መንገድም ስኬትም አልባ ጸሀፍት ትውልዱን ለማኮላሸት ክረምቱን ጠብቀው የበተኗቸው ‹‹መጽሀፍት›› ናቸው፡፡ በክረምቱ የወጡ ጥሩ መጽሀፍት ግን መደርደሪያው ላይ ብዙም ጎልተው እንዳይታዩ ተደርገዋል፡፡
እኔ በበዓሉ ጸለምተኛ መሆን ፈልጌ አይደለም እንዲህ ያለው ብሶት የምዘባርቀው፤ ነገር ግን ክረምትን ጠብቆ የሀገሪቱን ቁልፍ ትውልድ ለማጥፋት በሁለት ጎራዎች የሚደረገው ርብርብ ቢያበግነኝ ነው፤…እነዚህን ይዞ አዲሱን ዓመት መጀመር ለኔ ምንም ፋይዳው ስለማይታየኝ ነው፤ ሂደታችንን መመርመር፣መፈተሸ፣ውጤቱንም መመዘን ይኖርብናል፡፡ ቀጥዬ ለሁላችንም አዲሱን አመት መመርመሪያ የምትሆነውን የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያምን ‹‹ተጠየቅ መስከረም!›› የተሰኘች ግጥም ነው በገጸ በረከትነት የማቀብላችሁ፡፡
ተጠየቅ መስከረም፤                                                              
ዛሬስ ዋዛ የለም!                                                             

 አንተን ለመቀበል እንቁጣጣሽ እያልን፤                                               

 ከርስ እንሞላለን፤እንሳከራለን፤እንጨፍራለን፡፡                                     

 አልገባኝም እኔን አንተ መወደድህ፤                                                 

 ስትገባ ስትወጣ ድግስ መቀበልህ፤                                             

 ዶሮው፤በጉ፤ ሰንጋው ይታረድልሀል፤                                                

 ርጥብ ቄጠማና ደም መውደድህ ታውቋል፡፡                                         

እንስማው ተናገር፤                                                        

 የያዝከውን ነገር፤                                                             

 ስጦታህ ምንድነው? ለኛ ያመጣኽው?                                             

 ክፈተው ሣጥንህን፤ እስቲ እንመልከተው፤                                         

 ለምለሙን ሳር እንደሁ ይጋጡት ከብቶቹ፤                                               

ለኛ ምን ይዘሃል? ለኛ ለሰዎቹ?                                                     

ሞት ሊጠፋ ነው ወይ ባዲስ ፍልስፍና?                                          

 መድኃኒት አመጣህ? ለህመም? ደሀነት? ለኛ ድንቁርና?                                 

ተጠየቅ መስከረም፤ ያመት መጀመሪያ፤                                              

መነሻ፤ መድረሻ የሰው ልጅ የታሪክ መቁጠሪያ፤                                     

 ተጠየቅ መስከረም ማን አዲስ ይለብሳል? ቡትቶውን ጥሎ፤                                

 ፎቅ ቤት ማን ይሰራል? ጎጆውን አቃጥሎ፤                                          

 ተጠየቅ መስከረም፤ ያለፈው መስከረም ምን ታሪክ ነገረህ?                                

 ምን ሰማሁ፤ ምን አየሁ፤ ምን ተሰማኝ አለህ?                                        

መዝገቡ ምን ይላል? አንብበው፤ እንስማው፤                                             

የቱ ያመዝናል? ስራ ነው? ምኞት ነው?                                          

 መስከረም ተጠየቅ!                                                            

ተናገር! አትሳቅ!                                                             

 ጎተራው ተሟጦ በዕዳ ለታሰረው፤                                                   

 ለዚያ ለገበሬ ሳያርፍ ለሚሰራው፤                                                 

 ሚስቱና ልጆቹ እየተላቀሱ ለሚፈጽም ተግባር፤                                         

 በጦር ግንባር ላለው ለዚያ ለወታደር፤                                                 

ካልጋ ተቆራኝቶ ታሞ ለሚያጥረው፤                                                  

 ወይ አይሞት፣ ወይ አይድን ስቃይ ለታደለው፤                                        

ለወላድዋ ድሃ ባልዋ ለሞተባት፤                                                  

የልጆችዋ ረሀብ ሰቀቀን ለበላት፤                                                    

 ምን ይዘህ መጥተሀል?                                                           

ተናገር፤ እስቲ በል!                                                          

 በፍርሀት፤ በስጋት፤ ስቃይ ለሚበሉት፤                                               

 ፍትህ ይዘህ መጣህ ወይ? ህግና እኩልነት?                                           

 ሰላም አመጣህ ወይ? ነጻነትና ሀብት?                                               

 ሰውን ልታድስ ነው? ወይስ ልታሻግት?                                            

የዘንድሮው አክሊል ትጋት ነው ስንፍና?                                              

 ችግር ደባል ነው ወይ ዘንድሮም እንዳምና?                                          

ተናገር! ላዳምጥህ!                                                             

ትዝብት አይሰለችህ!                                                              

 ለኔ ያመጣኽው በሳቅህ ገብቶኛል፤                                                  

አንዲት ጥያቄ ናት ምን ሠራህ የምትል፡፡                                           

ይጭነቅህ ይጥበብህ ግራ ይግባህ አንተም!                                           

አንተም አልነገርከኝ፤ እኔም አልነግርህም፡፡

No comments:

Post a Comment