Main page

Saturday, August 17, 2013

የኦሮሞን ጥያቄ መመለስ ወይስ ማዳፈን?



በመሐመድ ሐሰን
ሰሞነኛውን የፖለቲካ አየር የተቆጣጠረው ርዕሰ ጉዳይ እንደ ሌሎቹ ጉዳዮች በወረት ነካክተን የምናልፈው አይደለም፡፡ ዛሬ ላነሳው የወደድኩት የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በተለያየ ግዜ የሚነሳ ቢሆንም የብዙዎች መነጋገሪያ ሳይሆን የሚከስምበት ግዜ ይበዛል፡፡ የብሄረሰቡ ተወላጆች እና ልሂቃኑ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ጉዳዩ ያነሳሉ፤ ሌሎች የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ያልሆኑ ኤትዮጵያውያን ግን፣ በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ ማየት ተለምዷዊ አይደለም፡፡ ከሰሞኑ ግን በኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አጋጣሚውን ያገኘ ሰው ሁሉ፣ ያመነበትን እና የመሰለውን ሀሳብ እየሰነዘረ ነው፤ ፍጭቱም ከረር ያለ ይመስላል፤ ይህ እጅግ በጣም ጥሩ የሚመስል ጅምር ነው፡፡ በፍጭቶቹ መሀል በርካታ ቁም ነገሮችን እየተጋራን ከመሆኑም ባሻገር፣ ጉዳዩ ወሳኝ የሆነ ሀገራዊ ምላሽ የሚሻ በመሆኑ፣ የውይይቶቹ መጀመር ወደ መፍትሄ የሚወስዱንን መንገዶችም ጭምር ሊያመላክቱን የሚችሉም ናቸው፡፡ ለአብነት ያህልም ከሰሞኑ ያነበብኩት ‹‹የዘመኑ መንፈስ›› የተሰኘው የበዕውቀቱ ስዩም ጽሁፍ ብዙ ብዥታዎችን የማጥራት አቅም እንዳለው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ አንግበናል በሚል በተሳሳተ መንገድ እየተጓዙ ላሉትም ጥሩ የቤት ስራ የሰጠ ድንቅ! ጽሁፍ ነበር፡፡  
የዛሬውን ጽሁፍ ለማንሳት አስብ የበነረው እና በማስታወሻዬም ላይ ያሰፈርኩት ከዓመት በፊት ነበር፡፡ በወቅቱ እስረኛ ወዳጆቼን ለመጠየቅ ወደ ማዕከላዊ እና ቃሊቲ እስር ቤቶች እመላለስ በነበረበት ወቅት፣ ከማስተውላቸው እስረኞች ውስጥ አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጆች ነበሩ፡፡ ገበሬ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ የሀይስኩል ተማሪ፣ አስተማሪ፣ የቤት እመቤት፣ ነጋዴ፣ የቤት ሰራተኛ፣ የፓርኪንግ ሰራተኛ፣ የጎዳና ተዳዳሪ፣ የቀን ሰራተኛ፣ ሊስትሮ፣ ዳያስፖራ፣ ጋዜጠኛ፣ ሾፌር፣ ፖሊስ፣ ወታደር፣ ባለስልጣን፣ ፖለቲከኛ፣ ወጣት፣ አሮጊት፣ ሽማግሌ፣ ወዘተ ወዘተ በእስር ቤቶቹ ውስጥ ያየኋቸው የኦሮሞ ልጆች ናቸው፡፡ ጥቂት የማይባሉትም ከፍተኛ የሚባል ድብደባ ተፈጽሞባቸው፣ እንደልባቸው ለመራመድ ሲቸገሩ አስተውያለው፤ ጠያቂዎቻቸውም አስቀያሚ ሊባል የሚችል እንግልት እና ውክቢያ ሲፈጸምባቸው በአይኔ አይቻለው፤ እናም በወቅቱ በውስጤ ብልጭ ያለው ጥያቄ ‹‹ኦሮሞነት ሀጢያት ነው እንዴ?›› የሚል ነበር፡፡ ምናልባትም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት፣ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን ‹‹ጽንፈኛ›› እንዲሆኑ ያደረጋቸውም እንዲህ ያለው ጭካኔ ሳይሆን አይቀርም ስል አሰብኩኝ፡፡ እኔም ዛሬ የማነሳቸው ጉዳዮች አዲስ ናቸው ብዬ ባላስብም፣ ለተጀመረው የአደባባይ ሙግት ግን ሐሳብ ማጫሪያ ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተጨማሪም ደግሞ ከዓመት በፊት ሳሰላስለው የቆየው ጉዳይ አሁን ላይ ማንሳቱ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል፡፡
ለመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ምንድነው? የልሂቃኖቹ እና የፖለቲከኞቹ ጥያቄስ? እውነት ለህዝቡ የቆሙ ጠያቂዎች አሉ? ህዝቡ እየተበደለ ያለው በማን ነው? ተጠያቂውስ ማን ነው? መፍትሄው ምንድነው? …እነዚህ እና ሌሎች በርካታ መሰል ጥያቄዎች የምር መመርመርና መልስ ማግኘት ይኖርባቸዋል፤ ካልሆነ ግን እንደ ሀገር ለመቀጠል ያለን ህልም አጠያያቂ እንደሆነ መቀጠሉ አይቀሬ ነው የሚሆነው፡፡      
የጥያቄዎቹ ጉዞ ትናንት እና ዛሬ
ይህንን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ወቅት ካገላበጥኳቸው ጋዜጦች አንዷ ‹‹አዲስ ነገር›› ነች፡፡ ‹‹አዲስ ነገር›› በሀምሌ 5 ቀን 2000 ዓ.ም እትም ላይ፣ ዐብይ ተ/ማሪያም እና ታምራት ነገራ  ‹‹የኦሮሞ ጥያቄ ምንድነው?›› በሚል ያለፉትን 50 ዓመታት ጥያቄዎች ሰፋ አድርገው አቅርበዋል፡፡ በዚሁ ጽሁፍ ላይ እንቅስቃሴው ያለፈባቸው መንገዶች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
በመጀመሪያ በ1940ዎቹ እና 50ዎቹ የነበረው ጥያቄ በኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግና፡በታሪክ፡ባህል እና ቋንቋ መዳበር ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ሜጫና ቱለማ መጥቶ ትግሉን ወደ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ከመለወጡ በፊት፡ የአመጹ የመጀመሪያ ጠባይ ፖለኪካዊ ሳይሆን ማህበራዊ ንቅናቄ (social movement) ነበር፡፡ ቀጥሎ ‹‹በራሳችን መሬት ባሪያ አንሆንም›› የሚል መነሻ ይዞ የባሌ አመጽ ይመጣል፡፡ የተማሪዎች የአይዲዮሎጂ ትንታኔ ልዩነት (የአብዮቱ ቅርጽ ላይ) መከፋፈል ተፈጠረና የተማሪዎች እንቅስቃሴ መከፋፈል ሶስተኛውን መንገድ ያዘ፡፡ ይህንን ልዩነት ተከትሎ የተፈጠሩት የኦ.ነ.ግ እና የመ.ኢ.ሶ.ን መንገዶች ሌላኛውን አራተኛ ደረጃ ፈጠሩት፡፡ የኦሮሞን ጥያቄ ከቅኝ ግዛት ጋር በማያያዝ ‹‹የኦሮሞ ጥያቄ የሚፈታው ነጻ የኦሮሚያ ሪፐብሊክን በማቋቋም ነው›› ለዚህም ሰላማዊው መንገድ ብቻ በቂ አይደለም ያለው ኦነግ ከመንገደኞቹ ውስጥ የራሱን ድርሻ ሲዘግን፡ ‹‹የለም የኦሮሞ ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ በመሆን ይፈታል›› ያሉት ኦሮሞዎች መ.ኢ.ሶ.ንን ተቀላቀሉ፡፡ እናም የኦሮሞ ጥያቄ በመ.ኢ.ሶ.ን እና በኦ.ነ.ግ መካከል ተከፈለ፡፡ ይሄኔ ለኦሮሞ ጥያቄ አማራጭ መፍትሄ ይዘው የተነሱት መኢሶኖች በደርግ ተኮርኩመው ሲወድሙ ኦነግ ብቸኛውን መንገድ በመያዝ ጉልበት ያገኘ መሰለ፡፡ በመቀጠል አምስተኛው መንገድ የመጣው ኦነግ የሽግግር መንግስቱ አባል ከሆነ ቦሃላ ነበር፡፡ ጥያቆውም ‹‹በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መኖር ይቻላል፤ እና የኦሮሚያ ሪፐብሊክ መመስረት አለበት›› በሚሉ ሁለት አማራጮች መካከል መዋለል ጀመረ፡፡ ይህም መንገድ ከሽፎ ህ.ወ.ሐ.ት እና ህ.ግ.ሐ.ኤ ኦ.ነ.ግን ‹‹አታለው›› ወደ ካምፕ አስገብተው ትጥቅ ያስፈቱታል፡፡ ይሄኔ ኦነግ ‹‹ከአቢሲኒያውያን ጋር መስራት አንችልም›› ከሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ስድስተኛው መንገድ ተፈጠረ፡፡ እንደገና ወደ ኋላ ሄደው ከቅኝ ግዛት ጥያቄ ጋር አያያዙት፡፡
ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ቦሃላ አሁን ላይ (ሰባተኛው መንገድ ልንለው እንችላለን) ጥያቄዎቹ ሰብሰብ ብለው ወደ ሶስት ተጠቃለሉ፡፡ አንደኛው ‹‹አሁንም የኦሮሚያ መገንጠል ለኦሮሞ ጥያቄ መፍትሄ ያመጣል›› የሚል ሲሆን፡ ሁለተኛው መንገድ ‹‹በዴሞክራሲያዊ አንድነት ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮች ጋር መኖር ይቻላል፡፡›› የሚል ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የሚቀመጠው ደግሞ ከስልጣን ባለቤትነት ጋር ተያይዞ ‹‹ኦሮሞ የኢትዮጵያ ትልቁ ብሄር በመሆኑ፡ በአገሪቱ የስልጣን የበላይ መሆን አለበት፡፡›› የሚለው ነው፡፡
የቱ ጥያቄ ሚዛን ይደፋል?
እንግዲህ እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች መሰረት አድርገን አሁን ያለውን ሁኔታ ስናስተውል አብዛኞቹ አጀንዳቸውን በዋናነት ሁለተኛውና ሶስተኛው ላይ ማድረግ የፈለጉ ይመስላሉ፤ ቀጣይነቱ ላይ ምንም ዋስትና ባይኖረውም፡ ከቅርብ ግዚያት ወዲህ፡ የኦሮሞን ጥያቄ እናቀነቅናለን የሚሉ ድርጅቶች (ሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪ ያሉትም) አላማቸውን በነዚሁ ጥያቄዎች ዙሪያ በማድረግ መሰባሰብ ጀምረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የመጀመሪያውን የሚያቀነቅኑ የሉም ማለት አይደለም፤ ከሰሞኑ ብዙዎቻችን እንድንነጋገርበት ያደረገውም በዚህ ረድፍ ላይ የተሰለፉት ‹‹ልሂቃን›› የሰነዘሩት አተያይ ነው፡፡ እርግጥ  የቱ ሀሳብ የበለጠ ሚዛን ይደፋል የሚለው ጥያቄ ለሰፊ ክርክር የሚጋብዝ ቢሆንም፣ እንደየግል አመለካከት እና እምነታችን፣ እንዲሁም ሁሉንም ሀሳብ ካቀነቀኑት ቀደምት የጥያቄው ተዋንያን አሁናዊ እምነት በመነሳት የሆነ ነጥብ ላይ መድረስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ቀደም ብዬ በጠቀስኩት ‹‹የአዲስ ነገር›› ፊቸር ጽሁፍ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት የኦሮሞ ምሁራን አንዱ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ናቸው፡፡ ዶክተር ነጋሶ በኦሮሞ ጥያቄ አቀንቃኝነታቸው ለረጅም ግዜ ከመቆየታቸው ባለፈ፣ ‹‹ነጻ የኦሮሚያ ሪፐብሊክ›› የሚለውን ሀሳብ ከወጠኑት እና ካቀነቀኑት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነበሩ፤ በወቅቱ ለጽሁፉ አስተያየታቸውን በሰነዘሩበት ወቅት ግን ‹‹የኦሮሚያ ነጻ ሪፐብሊክ ሀሳብ ዘመኑ እያበቃ ይመስላል›› ከማለታቸውም ባለፈ በአሁን ሰዓት የአንድነት ፓርቲን ተቀላቅለዋል፡፡ አሁንም ነገሶ እንቁላሉን ሰብረው ስለመውጣታቸው የሚጠራጠሩ ጥቂት ባይሆኑም፡፡ ከነጋሶ ውጪም ቢሆን እንደ ኦ.ነ.ግ ያሉ ድርጅቶች በጀመሯቸው አዳዲስ መንገዶች ‹‹መገንጠል›› በሚለው አማራጭ ላይ መለዘብን ሲመርጡ፣ ጉዳዩን ለህዝቡ ክፍት አድርገው መተው የፈለጉም አሉ፡፡
ከመገንጠል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ማቆሚያ የሌላቸው በርካታ ጥያቄዎች፣ተቃውሞዎች እና ስጋቶች ይነሳሉ፡፡ በመጀመሪያ መንገዱ ለህዝቡ ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝ እና የህዝቡ እውተኛ ጥያቄ ስለመሆኑ ብዙዎች ጥያቄ አላቸው፤ ከዚህ በተጨማሪ ግን ሌሎች በጥያቄው ላይ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች፣ አሁን በሀገራችንም ሆነ በዓለም ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ፡ አከባቢውን (ቀጠናውን) መሰረት ያደረገ መፍትሄ ስለመሆኑ፣ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ፣ በዙሪያቸውም ሆነ በውስጣቸው ስላሉ ሌሎች ህዝቦች፣ መገንጠልን የመረጡ ህዝቦች (ኤርትራ ጥሩ ምሳሌ ናት) የፈለጉትን ውጤት አግኝተዋል ወይ? የሚሉና ሌሎችም ጉዮች የምር መጤን እንዳለባቸው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
እነዚህ መንደርደሪያዎች የኦሮሞን ጥያቄ በሚያቀነቅኑት እና በኦሮሞ ህዝብ ውስጥ ስላለው ትክክለኛው ጥያቄ ሀሳብ እንዲሰነዘር የሚጋብዙ ናቸው፡፡
ጭቆናን ማስወገድ ወይስ ጭቆናን በሌላ ጭቆና መተካት?
ጋዜጠኛ ስለሺ ሀጎስ ‹‹መለስ እንደ ኤዲፐስ›› የምትል አንድ ድንቅ ያልታተመች ጽሁፍ ነበረችው፤ መቼም የንጉስ ኤዲፐስን ታሪክ ብዙዎቻችሁ የምታውቁት ይመስለኛል፤ ንጉስ ኤዲፐስ ይሸሽ የነበረው አባቱን ላለመግደል እንጂ፣ መግደልን እራሱ በመርህ ደረጃ በመቃወሙ አልነበረም፤ ስለሆነም ከመግደል አልተመለሰም፡፡
ብዙ ግዜ የኦሮሞ ልሂቃን እና ፖለቲከኞች ስለ ኦሮሞ ህዝብ ሲናገሩ ከአፋቸው የማትጠፋ አንድ ቃል አለች፤ ‹‹የብሄር ጭቆና›› የምትል፤ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በሌላ ግዜ ለብቻው የምመለስበት ቢሆንም፣ እኔ በበኩሌ ጨቋኝ ብሄር በሌለበት፡ ‹‹የብሄር ጭቆና›› ነበረ በሚለው አልስማማም፡፡ እርግጥ ነው ጭቆና ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ጭቆናው ግን የገዢዎች ነው፡፡ ልሂቃን ነን የሚሉ ሰዎች ሁሌ የሚያነሱት ሂሳብ ስለማወራረድ ነው፤ ምን አይነት ሂሳብ እንደሚያወራርዱ ግልጽ ባይሆንም፤ እዚህች ጋር ነው እንግዲህ የኤዲፐስ ምሳሌ የሚመጣው፤ ኤዲፐስ አባቱን መግደልን እንጂ መግደልን በራሱ በመርህ ደረጃ አልተጠየፈም፤ ስለዚህ ከመግደል አልተመለሰም፣ ገደለ፤ አሁንም የኦሮሞ ልሂቃን ነን የምትሉ ሰዎች ስለ ጭቆና ስታወሩ መጠየፍ ያለባችሁ ጭቆናን እራሱኑ ነው፡፡ ሌሎችን ስለመጨቆን የምታስቡ ከሆነ፣ በገዢዎቻችን ላይ ብቻ ሳይሆን በናንተ ላይም የጨቋኝነት መንፈስ ሰፍሯልና፣ ነገ እናንተም የገዢዎቻችንን ምግባር ላለመድገማችሁ ምንም ዋስትና የለም፤ ለዚህም ነው እኛ ተጨቁነናልና በተራችን ሌሎችን መጨቆን አለብን፡ በሜጫ (እንዲህ ያለውን ዘግናኝ ቃል መድገም በራሱ ያማል!) መቆራረጥ… የሚሉ ‹‹ልሂቃኖችን?›› ከሰሞኑ ማድመጥ የቻልነው፤ ታዲያ እነዲህ ያሉ ‹‹ሰዎች›› ስለጭቆና የማውራት  የሞራል ብቃት አላቸው? እውነት የኦሮሞ ህዝብንስ ይወክላሉ? እኔ ግን አይመስለኝም፤ ይሄኔ ነው የስለሺን አፍ ተወርሶ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ‹‹አንተም እንደ ኤዲፐስ!›› ማለት፡፡
እነዚህ የጨቋኝነት መንፈስ የተጠናወታቸው እና ለኦሮሞ ህዝብ ነው የምንታገለው የሚሉ ልሂቃኖች፣ የኦሮሞዎችን ጥያቄ እንኳን ማክበር የሚከብዳቸውና የኦሮሞዎችን ኦሮሞነት እንኳን ሊክዱ የሚቃጣቸው ናቸው፡፡ ያኔ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የኦሮሞ ልጆች ወደ መ.ኢ.ሶ.ን እና ኦ.ነ.ግ ተከፋፍለው በነበረበት ወቅት፣ ወደ መ.ኢ.ሶ.ን የሄዱት ‹‹ችግራችንን በኢትዮጵያ ውስጥ ሆነን እነፈታዋለን፤›› በማለታቸው፣ በሌላኛው ጎራ የተሰለፉት ‹‹የቅኝ ግዛት ትንታኔን የማያቀነቅን፡ኦሮሞ አይደለም፤›› በሚል ነበር ኦሮሞነታቸውን ሊክዱ የሞከሩት፡፡ በሸዋ፣ በየጁ፣ በአርሲ፣ በአምቦ፣ በወለጋ፣… ኦሮሞዎች መካከል በራሱ መግባባት፣ መተማመን እና መከባበር ካልተፈጠረ፣ ነገ እንገንጠል የሚሉ ሀይሎች አንዱን ከአንዱ እየለዩ ስላለመጨቆናቸው ምን ዋስትና አለ? እንነጋገር ከተባለ እኮ አንዱ እራሱን የበላይ አድርጎ በመቁጥር የሌላውን ኦሮሞነት የሚክድበት ሁኔታ እኮ ነው ያለው፤ ስለዚህ ዓላማችን ጭቆናን ማስወገድ ወይስ መልኩን ቀይሮ መጨቆን በሚለው ላይ መግባባት ይኖርብናል፡፡ ፖለቲከኞቹም ሆኑ ልሂቃኖቹ ስለ አንድ የኦሮሞ ህዝብ እንደሚታገሉ ቢነግሩንም የኦሮሞ ህዝብ መሰረታዊ በሆኑ ጥያቄዎች ላይ እንኳን ሲግባቡ አናይም፤ እና ታዲያ እየታገሉ ያሉት ለማን ነው? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱም ናቸው፡፡
ጠቅላይ ኢትዮጵያዊነት-ሌላኛው ደንቃራ?
አብዛኞቹ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከኦሮሞነት ተነስተው ኦሮሞነት ላይ መቆም ይፈልጋሉ፤ ወደ ኋላም ወደ ፊትም አይሰፉም፡፡ እኔ እከሌ ነኝ፣ የእከሌ ልጅ፣ የእከሌ ወንድምና እህት፣ የዚህ ሰፈር፣ ቀበሌ፣ ወረዳ፣  ከተማ፣ ጎሳ፣ ሀገር…ልጅ ነኝ በማለት ወደ ፊት እና ወደ ኋላ ከመስፋት ይልቅ፣ ከኦሮሞነት ላይ ይነሳሉ ኦሮሞነት ላይ ይቆማሉ፡፡ እዚህ ጋር አጽንኦት ሰጥቼ የኦሮሞ ብሄርተኞችን ልጠይቃቸው የምፈልገው፣ ተጨቆንን፣ ተገፋን በሚል እንዴት ኢትዮጵያዊነታችሁን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ? የሚል ነው፡፡
 በተቃራኒው ደግሞ ጠቅላይ ኢትዮጵያዊነትን (ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን?) የሚያቀነቅኑ ጥቂት የማይባሉ ፖለቲከኞችና ልሂቃን ከኢትጵያዊነት ይነሱና ለሌሎች አመለካከቶች በራቸውን ይዘጋሉ፡፡ ብሄር የሚባል ነገር ለም ይላሉ፤ ጭቆና ለሚለው ቃል ጆሮ መስጠት ይቀፋቸዋል፤…ባሉበት ጠበው ይቆማሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ካወራኋቸውና ሀሳብ ከሰጡኝ ሰዎች አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ስለሺ ‹‹ከኢትዮጵያ ፈቀቅ ብለው ለምን ስለ አፍሪካ እና ስለተቀረው ዓለም አያስቡም?›› ሲል ይጠይቃል፡፡
ከኦሮሞ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ሌላኛውን ፈተና የምናነሳው እዚህች ጋር ነው፡፡ ‹‹የኦሮሞ ብሄርተኞቹ ልይነቶችን ለማጥበብ መንገዱን ቢጀምሩትም፡ በተቃራኒው የቆሙት ፖለቲከኞች ካላገዟቸው ዳግም ወደ ብሄርተኝነቱ መመለሳቸው አይቀሬ ነው፡፡›› የሚል፡፡ አዲስ ነገሮች እንዳሉት ‹‹ለብቻ ታንጎ መደነስ አይቻልምና››፡፡ ስለዚህ ችግሩን ተቀብሎ ወደ መፍትሄ መሄዱ በተቃራኒው የቆሙት ፖለቲከኞች እና ልሂቃኖችም ጭምር ሀላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡   
ጥያቄውን መመለስ ወይስ ማዳፈን?
መጋቢት 1985 ዓ.ም የወጣችው ‹‹ማህሌት›› መጽሄት በወቅቱ የኦህዴድ ምክትል ጸሀፊ ከነበሩት አቶ ኢብራሂም መልካ ጋር ቆይታ አድርጋ ነበር፤ አ.ህ.ዴ.ድ ህ.ወ.ሐ.ት ሰራሽ ድርጅት ነው በሚለው ጉዳይ ላይ የተወሰነ ቆይታ ካደረጉ ቦሃላ ጋዜጠኛው ‹‹ እንግዲህ እርሶ የሚሉት ኦህዴድ ነጻ ድርጅት ነው ማለት ነው?›› የሚል ጥያቄ ይሰነዝርላቸዋል፡፡ ይሄኔ እሳቸው ‹‹…ድርጅታችን ኦህዴድ ነጻ ድርጅት ነው፡፡… በጋራ የሚያስተሳስረን ነገር ዓላማ ነው፡፡…በመታገላችን ደርግ በመሰበሩ ሰላምና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ሰፍኗል፡፡ እኛ የምናውቀው ይህን ነው፡፡›› የሚል ምላሽ ይሰጡታል፤ አጽንኦቱ የራሴ ነው፡፡
አሁን ላይ ያሉ የኦህዴድ ባለስልጣናትም ከዚህ የተለየ መልስ የላቸውም፡፡ ለሀያ ዓመታት በሙሉ አሰልቺና በውሸት የተሞሉ ተመሳሳይ ምላሾች፡፡ እነዚህ ከራሱ ከኦሮሞ ህዝብ ማህጸን የወጡ ልጆች ናቸው እንግዲህ የግል ጥያቄዎቻቸው ሲሟሉላቸው የስርዓቱ ዱላ በመሆን ህዝቡን ለዘመናት ሲያሰቃት የኖሩት፡፡ አሁንም ኦህዴድ ነጻ ድርጅት ነው ይሉናል፤ በጋራ የሚያስተሳስረን ነገር ዓላማ ነው ይሉናል፤ በመታገላችን ሰላምና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ሰፍኗል ይሉናል፤ አረ ከሰማናቸው የማይሉት ነገር የለም፤ በመጨረሻ ግን እኛ የምናውቀው ይህን ነው ብለዋል፤ እውነታቸውን ነው፤ የሚሉትን ነገር በሙሉ የሚያውቁት እነሱ ብቻ ናቸው፤ እውነታው ግን መራር እና በተቃራኒው ያለው ነው፤ እነሱ ዓላማቸውም ስላልሆነ ከዚህ በላይ ማወቅ አይጠበቅባቸውም፤ ማወቅም አይችሉም፡፡ እውነታውን በዚሁ በጠቀስኩት መጽሄት ላይ የቀድሞው የኢ.ህ.ዴ.ን ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ያሬድ ጥበቡ  ‹‹ኦህዴድ ህወሐት ሰራሽ የምርኮኛ ሰራዊት ድርጅት ነው›› በሚለው ጽሁፋቸው ላይ እነደሚከተለው አስፍረውታል፤
‹‹በታህሳስ 1976 ዓ.ም የኢህዴን ሊቀመንበር ስለነበርኩ የመጀመሪያውን ድርጅታዊ ግንኙነት ለማድረግ ወደ ኤርትራ (ሳህል) ሄጄ በነበረበት ግዜ ነው በ EPLF ውስት በቁም እስር ላይ ከሚገኙ የወታደር ምርኮኞች መሀል ለኢህዴን አባል እንዲሆኑ ከመለመልናቸው ውስጥ ፣ ከኦሮሞ ብሄረሰብ የሆኑት ተመርጠው OPDOን እንዲመሰርቱ የተደረገው፡፡›› ካሉ ቦሃላ አንደበት እና ልሳን የሌላቸው ድርጅቶች ችግሩን ያባብሱት እንደሆነ እንጂ፣ መፍትሄ እንደማያመጡ ጽፈዋል፡፡
የኦህዴድ ሰዎች ግን ህወሐት የበላይ እንዳልሆነ፡ ምርጫዎች ፍትሀዊ እንደሆኑ፡ ማንንም ሰው እንዳላስገደሉ፡ ምርኮኛ የነበረው የኦሮሞ ህዝብ ነጻ የወጣው እኛ ከመጣን ቦሃላ ነው በሚል ለጨቋኞች ጥብቅና ይቆማሉ፣ አምላካቸው ለሆነው ሆዳቸው ተገዝተው ይምላሉ፤ ይህ ግን ለጉዳዩ እልባት ከመስጠት ይልቅ፣ በግዚያዊነት አፍኖ ነገ የሚፈነዳ ፈንጅ እንደመቅበር ይቆጠራል፡፡
 ቀደም ብለን በጠቀስነው ‹‹ማህሌት›› መጽሄት ላይ የወቅቱ የአህዴድ ምክትል ጸሀፊ የነበሩት ሰው ያሏትን ነገር እዚህች ጋር ልጠቅሳትና የየራሳችንን ጥያቄ እናንሸራሽርባት፤ ‹‹..እኔ ኩሩ ኢተዮጵያዊ ነኝ ከማለቴ በፊት ኦሮሞነቴ መረጋገጥ አለበት፡፡ ኦሮሞነቴን ያላረጋገጠች ኢትዮጵያ ሺ ቦታ ትበጣጠስ፡፡ እያንዳንዱ ብሄር ብሄራዊ ኩራት ይሰማው፡፡ ጥሩ ኦሮሞ የመሆን እድሉን ካገኘሁ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ኢትዮጵያዊ እሆናለሁ፡፡..››   
አሁን ያለው ስርዓት ከኦሮሞ ጥያቄ ጋር በተያያዘ፣ ከንጉሱ (ዐጼ ሀይለስላሴ) አገዛዝ በባሰ ጨካኝ እና ትዕግስት አልባ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለዚህም ዶክተር ነጋሶ ‹‹አዲስ ነገር›› ላይ የሰጧት አስተያየት ጥሩ ማሳያ ናት፤ ‹‹ሁሌ ሰልፍ መውጣት ነው፤ሁሌ መታሰር ነው፡፡ ያኔ እንደ አሁኑ ጭካኔ አልነበረም፤ ግፋ ቢል የሚያስለቅስ ጋዝ ይለቀቅብናል፤ አልያም አንድ ሳምንት እንታሰራለን፡፡›› ነበር ያሉት፡፡ ዛሬስ ብሎ መጠየቅ በራሱ ለቆመጥ፣ ለእስር፣ ለከፍተኛ ስቃይ፣ ከፍ ሲልም ለጥይት ይዳርጋል፡፡     
ምንም ጥያቄ የለውም በዚህች ሀገር ላይ ምላሽ ማግኘት ካለባቸው ዋነኛ ጥያቄዎች ውስጥ የኦሮሞ ጥያቄ አንዱ እና ዋነኛውና ነው፤ ጥያቄዎቹን በየእስር ቤቱ በማጎር መመለስ አይቻልም፤ መንግስትም ሆነ እያንዳንዳችን በጥያቄው ከመበርገግ ይልቅ መወያየት፣ መደማመጥ፣ መከራከር፣ በመጨረሻም ወደ መፍትሄው ለመሄድ ፍቃደኞች መሆን ይጠበቅብናል፤ ኦሮሞነት ሀጢያት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፤ እንዲሁም የኦሮሞ ጥያቄ፤ ጥያቄያቸውን ላለመስማት በመፈለጋችን እያሰርናቸውና እየገፋናቸው ለምን ወደ ‹‹ጽንፈኝነቱ›› ገቡ ብሎ መጠየቅ አይቻልም፤ የተገፋ፣ የተሰቃየ፣ የተገረፈ፣… ሰው ምንም ሊያስብ ይችላል፤ እንደ ጄኔራል ታደሰ ብሩ ያሉ ታላቅ ሀገራዊ ጀግኖች ትግሉን የተቀላቀሉት የኦሮሞን ህዝብ ለምን እረዳችሁ በሚል እንደሆነ፣ እነ ነጋሶም ቋንቋውን በመናገራቸው ብቻ እንደተገረፉ፣ እንደ ሲሜሱ ዲንጋ ያሉ ኦሮሞዎች ምርጫን በማሸነፋቸው ብቻ እንደታሰሩ፣… ቢመርም እውነታውን አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡   
እንደ እኔ አመለካከት ችግሩን መፍታት የሚቻለው እና የተሻለው መፍትሄ፣ አማራጮችን በጋራ መመልከቱ ነው፤ ለችግሩ የዘውዳዊውን አገዛዝ ተጠያቂ የሚያደርጉ በርካቶች ቢሆኑም፣ እራሳችንን መመልከት እና የያናዳንዳችን ድርሻ ምን ያህል እንደሆነም መመርመር አለብን፤ ጥያቄው ላይ ብዙ መነጋገር ይኖርብናል፤ እንዲሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ግን የትኛውም ሀገራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄ ከህዝቡ እና ከሀገራዊ ጥቅም አኳያ መመዘን አለበት የሚለው ላይ ነው፡፡ ሁላችንም ትልቁን ሀገራዊ ስዕል ማሰብ ይኖርብናል፤ በመጨረሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ሳይንስ ትምህርት ክፍል የሚያስተምሩ አንድ ምሁር ‹‹ለአዲስ ነገር›› በሰጧት አስተያየት እንሰነባበት፡፡
‹‹…ትልቁ ችግር ግን በኦሮሞ ምሁራን እና ፖለቲከኞች መካከል የሚደረገውን ክርክር ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች አያውቁትም፡፡ የማንኛውም ንቅናቄ ትልቁ ምኞት ደግሞ ከንቅናቄው ውጭ ያሉ ሀይሎች ጥያቄውን እንዲረዱ ማድረግ ነው››፡፡      

No comments:

Post a Comment