በመሐመድ
ሐሰን


አዲስ አበባን ለኑሮ የማትመች ሲኦል
ካደረጓት ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ቤት የማግኘት ችግር ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ገንዘብ ከፍሎ እንኳን ቤት ማግኘት በጣም
አታካች ከመሆኑም ባሻገር: ከቤቶቹ ጥራትና ዋጋ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ቅሬታም ቢሆን ከኢትዮጵያዊነት ስብዕና የራቀ ግፍ የሚፈጸምበት
ነው፡፡ እንዲህ ያለው ቀዳሚና ግዙፍ ችግር መፍትሄ ሊበጅለት ነው ሲባል ደግሞ የህዝቡ በተስፋ መሞላት እና መፈንጠዝ የሚጠበቅ ነው፡፡
ከሰሞኑ የንግድ ባንኮችን እና ቀበሌዎችን አጨናንቆ የተመለከትነው ሰልፍም የዚሁ ተስፋ ማሳያ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን የከተማዋን
ዋነኛ ችግር ለመቅረፍ የተወጠነው እቅድ በጎ ስለመሆኑ ማንኛውም ሰው ይስማማል፡፡ ነገር ግን በተስፋ ከተጨናነቁት ሰልፎች ውስጥም
ቢሆን የሚነሱት ስጋቶችና ጥያቄዎች፡ ውሃ የማይቋጥሩ ናቸው በሚል እንደ ቀልድ የሚታለፉ አይደሉም፤ ለተጨማሪ እይታ በር የሚከፍቱ
እንጂ፡፡
በፖለቲካ የተጠለፈ ተስፋ?
በ1997 ዓ.ም የኮንዶሚኒየም (የጋራ
መኖሪያ ቤት) ምዝገባ ሲካሄድ፡ ጉዳዩን ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ ሳይመዘገቡ
የቀሩ በርካቶች ነበሩ፡፡ አሁን የተጀመረውን አዲሱ ምዝገባም ቢሆን ከፖለቲካው ጋር ያያዙት ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ጉዳዩን በበላይነት
ይዘነዋል የሚሉ የስራ ሃላፊዎችም፡ በሰሞነኛው የቤት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ የተለያየ ሀሳብ የሚሰነዝሩ መገናኛ ብዙሀንን፡ የፖለቲከኛ
አለቆቻቸውን አፍ በመዋስ ‹‹ተላላኪ›› ሲሉ አድምጠናል፡፡
ጉዳዩን ከፖለቲካው ጋር የሚያያይዙት
ሰዎች በቀዳሚነት የሚያነሱት ከምርጫ ጋር የተያያዘውን ነጥብ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፡ ‹‹የዚህች ሀገር ብቸኛው ልማት አብሳሪ
እኔ ነኝ፡ እኔ ከሌለው ሀገሪቱ ትበታተናለች፡…›› ከሚለው ልማዳዊ ዲስኩሩ በመነሳት፡ አሁን የሚጀመረውን የቤት ግንባታ ፕሮግራምም
ከሱ ውጪ ሌሎች እንደማይጨርሱት ማሳመን ይፈልጋል ሲሉ ይወቅሱታል፡፡ ባለስልጣናቱም ከዚሁ ስጋት ጋር በተያያዘ ለህብረተሰቡ ግልጽ
ያለ መረጃ በማቀበል ዋስትና መስጠት የሚፈልጉ አይመስሉም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ግንባታው ከተያዘለት የግዜ ገደብ በመነሳት፡ ሂደቱን
ለቀጣይ ሁለት ምርጫዎች የተከፈለ ቀብድ ነው የሚለውን ሀሳብ አጠንክሮታል፡፡ እንዲህ ያለው የፖለቲካ ጨዋታ ደግሞ ህዝቡን ለተጨማሪ
የባርነት እና እስረኛነት ህይወት መዳረጉ እሙን ነው፡፡ ከዚህ ስትራቴጂ በመነሳትም ‹‹ቁሳዊ ሀብትን ብቻ በማብሰር እስከመቼ እያበሉ
መግዛት ይቻላል?›› የሚለው ጥያቄ ተያይዞ ይነሳል፡፡
ፓርቲውና ባለስልጣናቱ
መሬት ሲቸበችቡ እና ቤት ሲሰሩ በመኖራቸው፡ ህዝቡ ውስጥ ያለውን ብሶት ለማስተንፈስ በሚል የሰሞኑ ተስፋ ሆን ተብሎ እንደተፈጠረ
የሚጠረጥሩም አሉ፡፡ ምሁራን እና ተቃዋሚዎችም በጉዳዩ ላይ አማራጮችን በመጠቆም ዋስትና ከመስጠት በመቆጠባቸው ከህዝቡ ትችት አላመለጡም፡፡
ጉዳዩን በበላይነት
የሚቆጣጠሩት ሰዎች ከፖለቲካው ነጻ ናቸው ተብሎ ስለማይታመን፡ የፓርቲው አባላት በተለያየ መንገድ ከግናባታው ሂደት ብቸኛ ተጠቃሚ
እንዲሆኑ ሊደረግ የሚችልበት እድልም ሰፊና ብዙዎች የሚጋሩት ስጋት ነው፡፡ ከቀደሙ ተሞክሮዎች በመነሳት መናገር እንደሚቻለው፡ ለስራው
የሚያስፈልጉ ግብአቶች በሙሉ በፓርቲው ስር የተደራጁ አባላት እንዲያቀርቡ ይደረጋል፤ ከጥቃቅን የመንገድ ስራዎች ጀምሮ እስከ ቤቶቹ
ግንባታ ድረስ ያለው ስራም ለአባላቱ ተመርጦ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ጉዳዩን ከሀገራዊነት ወደ ፓርቲያዊነት ያወርደዋል፡፡
ያልተመለሱ ጥያቄዎች
ከፖለቲካዊ አንድምታው
በበለጠ አዲሱ የቤቶች ልማት ፕሮግራም በርካታ ያልመለሳቸው ውስብስብ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ ከሁሉም በላይ ከምዝገባው ሂደት እንኳን
ቀድሞ የሚነሳው ጥያቄ፡ በልማት ስም ከተሰሩት እና ወደፊትም ከሚሰሩት ግፎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጥቂት ኮሚቴዎችን ብቻ በጥቅም
አስሮና አሳምኖ የአንድን መንደር ነዋሪ በሙሉ ለከፋ ችግር ከመዳረግ፡ ከአሁኑ ተጠያቂነት ያለበት አሳማኝ ስራ ለመስራት ማሰቡ የተሻለ
ነው፡፡ ነዋሪዎችን በልማት ስም አፈናቅሎ መልሶ ነገ ወደሚፈርስ ቦታ እያዘዋወሩ እንደተከራይ ማንከራተት ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊም ሆነ
ማህበራዊ ቀውስ እንደሚዳርጋቸው የምር መታሰብ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ‹‹ለልማት›› ተፈናቃዮች የኮንዶሚኒየም (የጋራ መኖሪያ)
ቤት ያለ እጣ ቀድሞ እንዲሰጣቸው የሚደረግበት አሰራር ነበር፡፡ ወደፊትስ ተመዝግበው ቤት
የሚጠብቁ ሰዎችን እጣ ከማራዘም፡ በልማት ስም ለሚነሱ ነዋሪዎች እራሱን የቻለ ተጠባባቂ መኖሪያ በመገንባቱ በኩል ምን አይነት እቅድ
ተይዞ ይሆን የሚለው ጥያቄ መልስ የሚሻ ነው፡፡
ከቀድሞው የጋራ
መኖሪያ ቤት ምዝገባ ጋር በተያያዘ እንደ ዋዛ ሊታለፉ የማይገባቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ ወደ አራት መቶ ሺህ (400.000) ሰው ተመዝግቦበታል
የሚባለው የቀድሞው የጋራ መኖሪያ ቤት አንድ መቶ ሺህ (100.000) ለሚሞሉ ነዋሪዎች እንኳን አልተዳረሰም፡፡ በነዚህ ሁሉ ዓመታት
ይህቺን ብቻ ከሆነ ማሳካት የተቻለው፡ በቀጣይ እየታሰበ ያለው ፕሮግራምስ በተባለው ግዜ ለመድረሱ ምን ዋስትና አለው? የቀድሞ
ተመዝጋቢዎች ፋይል ጠፋ መባሉ ምንድነው የሚነግረን? በቀጣይ የተመዘገቡ ሰዎችስ ዋስትናቸው ምንድነው? እስኪጣራ እንደ አዲስ መመዝገባቸውስ
ቦሃላ የሚጣራበት መንገድ ስለመኖሩ ዋስትና ይሰጣል? ቀድሞ የመመዝገብ እድሉን አግኝተው የነበሩ ነገር ግን አሁን የተባለውን ገንዘብ
መቆጠብ የማይችሉ ነዋሪዎች እየገጠሙን ነው፤ የነሱስ ተስፋ ምንድነው?
ከቤት ልማት ጋር በተያያዘ የሚሰሩ
መስሪያ ቤቶች ለሙስና የተጋለጡና በተለያየ ግዜም እንደሚቀያየሩ ይታወቃል፤ ታዲያ ህዝቡ አዲሱን ፕሮግራም እንደሚያስፈጽሙ እንዴት
እምነት ሊጥልባቸው ይችላል? ከግል ተቋራጮች ጋር ያለው የዋጋ ልዩነትና ቤቱን መረከቢያ የግዜ ምጣኔ መንግስት ካቀረበው ጋር ያለው
ልዩነት ተመዛዝኖ ይሆን? ህብረተሰቡ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር
ባለፈው ቅዳሜ ለአዲስ ጉዳይ መጽሄት (ቅጽ7 ቁጥር 169 ሰኔ 005) በላከው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው ‹‹…ዋናው ጉዳይ ለሁሉም
የህብረተሰብ ክፍል የሚሆን የቤት አቅርቦት አማራጭ ወይም ስልት ተነድፏል ወይ? የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ማረጋገጡ ነው፡፡…›› ይላል፡፡ እኔ
ግን ይህንኑ ጥያቄ መልሼ ለራሱ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መጠየቅ እወዳለው፡፡ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚሆን የቤት አቅርቦት
አማራጭ ወይም ስልት ስለመነደፉ ምን ያህል እርግጠኞች ናችሁ? ዋስትናስ መስተት ይቻላቹሀል? መልሱን ተጨባጭ በሆነ መረጃ ብታሳዩን
መልካም ነው፡፡
ይሕው ከላይ የተጠቀሰው ደብዳቤ
‹‹ዓላማችን ከተሞቻችንን የልማት የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ማዕከላት ማድረግ ነው!!›› የሚል መልዕክት በመዝጊያው ላይ
አስፍሯል፡፡ እውነት በከተማችን ውስጥ የምናያቸው ከቤት ግንባታና መልሶ ማልማት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከላይ የተጠቀሱትን የሚኒስቴር
መስሪያ ቤቱን ዓላማዎች (ልማት፡ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር) የሚያሟሉ
ናቸው? በልማት ሰበብ የተፈናቀሉትን በአግባቡ አለማስፈር፡ በከተማዋ ውስጥ ያለው የቤት ችግር በአግባቡ ካልተቀረፈ፡ በመስሪያ ቤቱና
በነዋሪው ዘንድ መግባባትና መተማመን ካልተፈጠረ፡… ከተዘረዘሩት ውስጥ የትኛውን አላማ ለማሳካት እንደምትጥሩ ማወቁ ያጓጓል፡፡
አንድ ወዳጄ የሰሞኑን የቤት ባለቤትነት
ምዝገባ ይፋ መደረግ ተከትሎ ‹‹ቆጥ ላይ ከማደራችን በፊት ደረሱልን››
ነበር ያለው፡፡ በእርግጥ አሁንም ህብረተሰቡ እንደደረሳችሁለት እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል፡፡ እንደኔ እምነት አዲስ አበባ ላይ ማደሪያ
ቆጥ እንኳን በአማራጭነት ስለመገኘቱ በእርግጠኝነት መናገር ይከብደኛል፡፡ወዳጄ ግን ከ‹‹ደረሱልን›› ወደ ‹‹ደረሱብን›› ከመሸጋገሩ
በፊት ችግሩን የምር መረዳትና ተጨባጭ መፍትሄ መፈለጉ ለሁላችንም
ሳይበጀን አይቀርም፡፡
No comments:
Post a Comment