Main page

Sunday, June 2, 2013

ከሕዝባዊ ታጋይነት ወደ ግለሰባዊ ሙሰኝነት፡ ስለ ሽግግሩ ሒደት ጥቂት ዘገባ

በዳኛቸው አሰፋ (ዶክተር)
 
 Addis Guday
ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የታየውን የሥልጣን ሽግሽግ ተከትሎ በዋናነት ተቀዳሚ ርዕሰ ጉዳይ የሆነው በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የቆየው የሙስና እና የአገር ንብረት ምዝበራ ጥያቄ ነው፡፡ የጉዳዩም አሳሳቢነት እነሆ ሰሞኑን በአንዳንድ የከፍተኛ የጉምሩክ ባለሥልጣናት ወሕኒ ቤት መውረድ ተስተጋብቷል፡፡
የዚህ መጣጥፍ ፍሬ ነገር የሚያተኩረው በአገሪቱ ውስጥ በተነሳው የሙስና ጉዳይ አንዳንድ ይጠቅማሉ የምንላቸውን ጥያቄዎች ለማንሳትና ከራሳችን አተያይ ባሻገር አንባብያንም የራሳቸውን ምልከታ እንዲያንፀባርቁ ለመጋበዝ ነው፡፡
 
ከዚህ በታች የምናቀርበው የፖለቲካ ትንተናም በሚከተሉት ወሳኝ ጥያቄዎች ላይ የተመረኮዘ ይሆናል፡፡
 
1- አገሪቱ ላይ የሚስተዋለው ሙስና ሥርዐታዊ ነው ወይስ ከግለሰቦች የሞራል ግድፈት የመነጨ?
2- አንዳንድ ሰዎች እንደጠየቁት ሙስና መኖሩ ቀደም ብሎ እየታወቀ በአሁኑ ሰዓት የተወሰነ እርምጃ ለመውሰድ ለምን አስፈለገ?
3- ሥልጣን ላይ ያለው ሥርዐት በውስጡ አቅፎ የያዘውን የሙስና ህዋስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ራሱን ማጽዳት ይችላል ወይስ አይችልም? የሚሉት ይሆናሉ፡፡
 
እነዚህን ከላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ከመነሳታችን በፊት እንደ መንደርደሪያ እንዲሆነን ሰሞኑን ከአንድ ወጣት ጋር በአ.አ.ዩ አካባቢ በሚገኝ የፎቶ ኮፒ መደብር በተገናኘሁ ጊዜ ያካፈለኝን የአንድ ገበሬና የአንድ ዝንጀሮ ተረት ላነሳሁት ጉዳይ ብጠቀምበት ይበጃል ብዬ አቅርቤዋለሁ፡፡ አንድ ገበሬ ማሳው ላይ ቀኑን ሙሉ ሲደክም ውሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ ጉብታ ላይ ተቀምጦ ሲያየው የዋለው ዝንጀሮ “አያ ገበሬ እንደም ዋልክ?” ብሎ ሰላምታ ያቀርብለትና “ዛሬ እርሻህ ላይ በጣም ስትለፋ አይቼሀለሁ፡፡ ለመሆኑ ምንድን ነው የዘራኸው?” ብሎ ይጠቀዋል፡፡ ገበሬውም ሲዘራ የዋለው ባቄላ ቢሆንም ይህ ለዝንጀሮ የሚነገር አይደለም በማለት “አያ ዝንጀሮ የዘራሁትማ ተልባ ነው” ብሎ ይመልስለታል፡፡ ዝንጀሮውም ፈገግ ብሎ “እሱንማ እዛው ስንዘልቅ እናየዋለን” ብሎ መለሰለት ይባላል፡፡
ይህንን የዝንጀሮውንና የገበሬውን ምልልስ በምናጤንበት ጊዜ ተምሳሌቱ ከአገራችን የፖለቲካ ሥርዐት ጋር የሚያገናኘው ነገር አለ ብለን እናምናለን፡፡ ገበሬውን እንደ መንግሥት ወይም እንደ ሪፖርት አቅራቢ የመንግሥት አካል፤ ዝንጀሮውን ደግሞ እንደ አንድ ነጻነት ያለው አካል እንውሰደው፡፡
በመንግሥት በኩል ያለው ለሕዝብ ማድረስ የሚፈልገውን በጎ በጎ ነገሮች (ሪፖርቶች) ብቻ ያቀርባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለሕዝብ መድረስ የለበትም የሚለውን ይሸሽጋል፡፡ ዝንጀሮው እንዳለው የቀረበውን ሪፖርት ዘልቆ የሚያይና የሚፈትሽ አካል ከሌለ እውነታው ላይ ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ዝንጀሮው በርግጠኝነት “ዘልቀን እናየዋለን” ማለቱ የመመርመርና የመንቀሳቀስ መብቱ በእጁ እንዳለ በመረዳቱ ነው፡፡ የአገራችን ሕዝብም እንደ ዝንጀሮው የመፈተሽና የማረጋገጥ ነጻነት በእጁ ቢኖር ኖሮ ከእውነት የራቀ ሪፖርት ሲቀርብለት ዝም ብሎ አይቀበልም ነበር፡፡
በመሆኑም በአገራችን የፖለቲካ ሥርዐት ሕዝቡ በራሱም ሆነ በወኪሎቹ አማካኝነት ዘልቆ የማየትና የማጣራት መብቱ የተገደበ ስለሆነ የተዘራውና የበቀለው “ተልባ” ወይም “ባቄላ”፤ “እንክርዳድ” ወይም “ስንዴ” መሆንና አለመሆኑን እንዳይለይ ተደርጓል፡፡ ሰሞኑን የፀረ- ሙስና ኮሚሽን ትንሽ ዘለቅ ብሎ እንዲያይ ቢደረግ ይኸው አንዳንድ ጉዶችን ለማየት በቅተናል፡፡
 
1- አገሪቱ ላይ የሚስተዋለው ሙስና የሥርዐት ወይስ የግለሰቦች የሞራል ግድፈት?
 
ሙስናን ወይም ምዝበራን በሚመለከት የፖለቲካ ትንተና በሚቀርብበት ጊዜ ተቀዳሚ ሆኖ መነሣት ያለበት ጥያቄ በሥርዐትና በግለሰብ ሥነ ምግባር መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ነው፡፡ መጽሐፉ “በመጀመሪያ ቃል ነበር” እንደሚለው በፖለቲካ ትንተናም “በመጀመሪያ ሥርዐት ነበር” ስለሆነም በዚህ ጸሐፊ አመለካከት ሙስና የግለሰብ የሞራል ድክመትንም የሚያሳይ ቢሆንም መነሻው ከሥርዐት ጋር በጣም የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ኢህአዴግ “እኩልነትን ለማስፈን የታገልኩና አሁንም በትጋት እኩልነትን የሚያንጸባርቅ ሥርዐት መሥርቼ እየተጓዝኩ ነው” ይላል፡፡ ኢህአዴግ “የእኩልነት አባት” መሆን መከጀሉ የሚያስወቅሰው ባይሆንም ስለ “እኩልነት” ያለው ዕይታና ግንዛቤ በጣም የጠበበና አንድ ወጥ በመሆኑ ሥርዐቱ ሕዝቡ ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡
ዴሞክራሲን በተጎናጸፉ አገራት በትንሹ የሚከተሉት የእኩልነት ዘይቤዎች ይኖራሉ፡፡
ሀ. የሕግና የፖለቲካ እኩልነት
ለ. ማኅበራዊ እኩልነት/የብሔር እኩልነት
ሐ. ለሁሉም በውድድርና በችሎታ ለማደግ የመሳተፍ እኩልነት
የኢህአዴግን የ22 ዓመታት ሥርዐት በምናይበት ጊዜ የብሔር እኩልነት ላይ የተወሰነ መደላደል ቢሠራም በሕግና በፖለቲካ እኩልነት እንዲሁም ለሁሉም በውድድርና በችሎታ ለማደግ የመሳተፍ እኩልነት ላይ ትልቅ ክፍተት ያለበት ሥርዐት ነው፡፡ እነኚህ እኩልነቶች ደግሞ ከፍትሕ መፋለስ ጋር የተያያዙ ስለሆነ ሌላ ገጽታቸው የሙስና ባሕርያትን ይዞ ይጓዛል፡፡ ከዚህ በፊት ጥንታዊ ግሪኮች “አይሶኖሚያ” ወይም በሕግ ፊት የሰው ልጅ እኩል መሆን እንዳለበት ያሳሰቡትን ለማተት ስለሞከርን ከዚህ መጣጥፍ የአገሪቱ ሀብትና ቢሮ ለሁሉም በእኩልነት ክፍት አለመሆኑ ከሙስና ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
የኢህአዴግ ተቀዳሚ የፖለቲካ ኃጢአት (Original Sin) ፍትሐዊ የሆነ የንዋይ ክፍፍል ላይ ለመድረስ የሚያስችሉትን ጤናማ ውድድር፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ በችሎታ ሥራ ላይ የመሰማራት፣ በብቃት የከፍተኛ ትምህርት ዕድል የማግኘት፣ የመንግሥት ኮንትራትና ጨረታ ለሁሉም እኩል ክፍት መሆን ወዘተ. አለመሟላቱ ነው፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ ንብረት በዕድልዎና ውድድር በጎደለው መንገድ ለሁሉም ዜጎች ክፍት አለመሆኑ ነው፡፡
ንብረትን በሚመለከት የምናየው ሁለተኛው ተቀዳሚ ኃጢአት ደግሞ ኢህአዴግ በትግል ላይ ጀምሮ የያዘውን የአመለካከት አሻራ የመንግሥትን ሥልጣን ከጨበጠም በኋላ እንደያዘ መቀጠሉ ነው፡፡ በትግል ዘመናቸው አሸንፈው ያገኙትን በሙሉ በምርኮነት የራሳቸው ንብረት ያደርጉ ነበር፡፡ በኋላ ይሄም ማለት ለእነርሱ በ “ንብረት” እና በምርኮ መሐል የፅንሰ ሐሳብ ልዩነት አይታያቸውም ነበር፡፡ አሁንም እንደቀድሞ የትግል ዘመናቸው ማንኛውንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለ ነገር ሁሉ የ“እኛ ነው” የሚል አስተሳሰብ አላቸው፡፡ በሌላው ዓለም ዴሞክራሲያዊ የሆኑ አገሮች አንደኛው ዋና መለያቸው የመንግሥት እና የመንግሥት ያልሆነ ንብረት ማለትም መንግሥት የሚገባበት እና መንግሥት የማይገባበት ቦታ በግልጽ ያስቀመጡ መሆናቸው ነው፡፡
ይህንን ለማብራራት ሌሎቹን ነገሮች ወደ ጎን ትተን የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍን በምናይበት ጊዜ ከላይ የተነሡትን አድልኦዎች በማንኛውም የአካዳሚና መሥፈርት ሊተገበር የማይገባውን ተተግብሮ እናያለን፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ከእውነት የራቀም ቢሆን “ትምህርት እንዲማሩ የሚፈቀድላቸው የመሳፍንትና የደጅ አዝማቾች ልጆች ናቸው” ይሉ ነበር፡፡ አሁን ግን በስፋት ክፍት ቦታ ተይዞላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ፈትነውና አወዳድረው ማስገባት ሲገባቸው በቀጥታ ትእዛዝ “እነኚህን ተቀበሉ” በማለት በተለያየ ክልል የፓርቲ “መሣፍንት” የመማር ዕድል ያገኙት ተወዳድረውና ብቁ ሆነው ሳይሆን የገዢው ፓርቲ አባል በመሆናቸው “ገዢዎች መማር አለባቸው” በሚል ሌሎች ተወዳዳሪ ዜጎችን ወደ ውጭ በመገፍተር ነው፡፡
ፍትሕን ያገናዘበ የፖለቲካ ሥርዐት የሌለበት ቦታ ላይ ሙስና በስፋት መስተዋሉ አይቀሬ ነው፡፡ እንዲህ ዓይቱን ሁኔታ ሊዮን ትሮትስኪ አንድ መጽሐፍ ላይ ሲያስረዳ ከጥንት ጀምሮ የመጡ ቅዱሳን መጻሕፍት “ሠርተህ ብላ” የሚል አስተምህሮ የያዙ ሲሆን፣ በስታሊን ዘመን ግን አስተምህሮው “ታዘህ ብላ” መሆኑን ገልጿል፡፡ የዚህን አነጋገር መንፈስ እኛም ወስደን አሁን በአገራችን ያለውን ሁኔታ ስናይ “ሠርተህ ብላ” ሳይሆን “ተደራጅተህ ብላ” መሆኑን እንረዳለን፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ሥርዐቱንና ሙስናን በአገራችን ውስጥ የሚያገናኛቸው ሁኔታ የሚከተለው ነው፡፡ በማንኛውም የዴሞክራሲ አገራት ዜጎች በሕግ የተደነገገላቸውን የሥራ ድርሻ ለማከናወን ይጥራሉ፡፡ ወደ መንግሥት ሥራ አብዛኛውን ጊዜ የሚመጡ ሰዎች ለሙያቸው ፍቅር ያላቸውና በተወሰነ መልኩ “አገራችን ማገልገል አለብን” የሚል የሞራል አቋም ያላቸው ናቸው፡፡
ተገቢ በሆነ መንገድ ሀብት እያፈሩ፣ ባለሀብት ሆነው አገራቸውን ለመጥቀም ቅን ሐሳብ ያላቸው ደግሞ ወደ ንግድ ዓለም ይገባሉ፡፡ ወደ እኛ ሀገር በምንመጣበት ጊዜ ግን ሀብት ለማፍራት ወደ ንግድ ዓለም መግባት አስፈላጊ መሆኑ ይቀርና ሰፊ የሀገር ሀብት ወደ ሚያስተዳድረው የመንግሥት መዋቅር መግባት አትራፊና የሀብት መንገድ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ መንግሥት የመሬት አስተዳዳሪ ስለሆነ ብቻ በዚህ ዙሪያ ትልቅ የምዝበራ በር ከፋች መሆኑን እንደምሳሌ ማንሣት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንጻር መንግሥት እንደ ፊውዳል ሥርዐቱ የመሬት ባለቤትነቱን ካልተገፈፈ ሙስና ይጸዳል ብሎ መገመት ትልቅ የዋሕነት ይመስለናል፡፡
ይህን ነጥብ ለማጠቃለል በየትኛውም ዓለም እንደታየው ከፍ ያለ ንብረት አስተዳዳሪ የሆነ መንግሥት ከፍ ወዳለ ሙስና መውደቁ አይቀሬ መሆኑን እናስታውሳለን፡፡
 
2- እርምጃውን አሁን መውሰድ ለምን አስፈለገ?
 
የጉምሩክ ባለሥልጣናት ከታሠሩ በኋላ በተወካዮች ም/ቤት ውስጥም ሆነ ከውጭ ዜጎች “የሙስና መኖር ቀድሞ እየታወቀ ይህ እርምጃ ለምን አሁን ተወሰደ?” የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው ተገቢ ሆኖ ይታየናል፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመረዳት የሚከተሉት ሁለት ነጥቦች መታየት ይኖርባቸዋል፡፡
አንደኛ፡- የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ በአገሪቱ የፖለቲካ ሥራ ላይ ቁንጮና የተጠናከረ ክንድ የነበራቸው በመሆኑ ሕይወታቸው ባለፈበት ጊዜ የመተካካት እንቅስቃሴ ብናይም የሰውየው አለመኖር አመራሩ አካባቢ የፖለቲካ ክፍተት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በመሆኑም በአመራሩ ላይ ፍጹማዊ የበላይነት ያለው ሰው ከቦታው ሲነሳ ከጀርባ የመተካካት ሽኩቻ ስለሚነሣ አንዱ አንደኛውን በመጣል የበላይነት ለመቀዳጀት ሕዝባዊና የሞራል ጡሐራት ለማሳየት ይሞክራል፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ዜጎች ከዚህ በፊት ያላገኙትን አንዳንድ በተዘጋው “የሥልጣን አዳራሽ” ውስጥ ብቻ ያሉ ሰዎች ሊያዩ የሚችሉትን በጭላንጭል እንዲያዩ ጊዜያዊ ቀዳዳ ይበጅላቸዋል፡፡ ስለሆነም አሁን ከሽኩቻው ጀርባ ምንም እየተካሔደ እንደሆነ በጭላንጭል ለማየት ችለናል፡፡
እንደ ፓርላማ እና የፀረ- ሙስና ኮሚሽን ያሉ ተቋማትም ከዚህ ቀደም የተሰጣቸውን የሥራ ድርሻ የሕዝብን ቀልብ በሳበ መልኩ ሲያከናውኑ አይታዩም ነበር፡፡ አሁን ግን የተገኘውን ክፍተት በመጠቀም በተለይ ፓርላማው እየተዘዋወረ የአስፈጻሚውን አካል በተለያዩ ኮሚቴዎቹ አማካኝነት እየመረመረ በርካታ ድክመቶችንና ጉድለቶችን ማየቱና ለሕዝብ ማሳወቁ የሚያስመሰግነው ሲሆን፣ እዚህም ላይ ቢሆን ከላይ የሚካሔደው የሥልጣን ሽኩቻ አልቆ በበላይነት አንድ ኃይል በወጣ ጊዜ የእነርሱንም እንቅስቃሴ እንደ ቀድሞው የተቀዛቀዘና የተዳፈነ ይሆናል ብለን እንሰጋለን፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ እንደ ታሪክ ማጣቀሻነት ለመጠቀም ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ገሸሽ ተደርገው ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑባቸው ወራት የነጻነት ጮራ በመፈንጠቁ አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የኅትመት ውጤቶች፣ ውይይቶች፣ ሰላማዊ ሰልፎች… በአጠቃላይ ታይቶ የማይታወቅ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ሲከናወኑ ነበር፡፡ ወዲያው ግን በተከታታይ የመጡት ሁለት ሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተወግደው ሠራዊቱ የሥልጣን ክፍተቱን ሞልቶ ከተጠናከረ በኋላ ያቺ በየቦታው የፈነጠቀችው ጮራ ጨለማ እንዲወርሳት መደረጉን እናስታውሳለን፡፡
ሁለተኛ፡- ማንኛውም ሥርዐት ሙስና ተንሰራፍቶበት ረዘም ላለ ጊዜ እያደገ በሚሔድበት ጊዜ ሥርዐቱ ፍጹማዊ እክልና ውድቀት እንዳይገጥመው አንዳንድ የእርማት እርምጃዎችን መውሰዱ አይቀሬ ነው፡፡ እዚህ ላይ የመኪና ሞተርን በምሳሌነት ብንወስድ መኪናው ተነድቶ ሞተሩ በጣም ሲግል መኪናውን ወደ ጎን ቆም አድርጎ ራዲያተሩን በመክፈት የሚፈላውን ውኃ በማስተንፈስ… ለተወሰነ ጊዜ ዘለቄታዊ መፍትሔም ባይሆን መኪናውን ማቀዝቀዝ ይችላል፡፡ አሁን የምናየው የተወሰኑ ሙሰኞችን የማሠርና የመክሰስ ሁኔታ ዘለቄታዊ መፍትሔ ባያመጣም የሥርዐቱ ሞተር ለጊዜውም ቢሆን ከግለቱ የተነሣ እንዳይፈነዳ ከማቀዝቀዝ ሂደት ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌደራሉ ዋና ኦዲተር ያቀረበው ሪፖርት ለሕዝቡ በአስቸኳይ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ያሳሰበ ሆኗል፡፡ ከፍተኛ ለሆነ የሀብት ብክነትና ምዝበራ በር የሚከፍት የሒሳብ አያያዝ ግድፈት በበርካታ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ መኖሩ ለሕዝብ ይፋ በወጣበት ጊዜ ሥርዐቱ አደጋ ላይ እንደሆነ በመረዳት ጊዜያዊና አጣዳፊ እርምጃ በተወሰኑ ሰዎች ላይ እንዲያሂድ አስገድዷል፡፡
ሆኖም ግን ስማቸው በሪፖርቱ ላይ በአሉታ የተነሣው ተቋማት ሪፖርቱን የማጣጣል፤ ጭብጥና ይዘቱን ለማምከን በቴሌቪዥን ገለጻ እየተሰጠ ነው፡፡ “ሕዝብና ወረቀት የያዘውን አይለቅም” እንዲሉ ይህ የማጣጣል ሙከራ ይሳካል የሚል እምነት የለንም፡፡

3- ሥርዐቱ በውስጡ ያለውን የሙስና ሕዋስ ተቆጣጥሮ ራሱን ማጽዳት ይችላል ወይስ አይችልም ?
 
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው ሙስና በአገራችን የፖለቲካ ሕይወት በራሱ የቆመ ነገር ሳይሆን ከሥርዐቱ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው፡፡ የኢህአዴግ አሁን የተጀመረው የ“ፀረ-ሙስና” እንቅስቃሴ መሠረታዊ ከሆነ የሥርዐት ለውጥ ውጪ የሚካሔድ ስለሆነ የምዝበራ ሂደቱን ትንሽ ሊያስታግሰው ይችል እንደሆነ ነው እንጂ በምንም መልኩ ሊቆጣጠረው አይችልም፡፡
ሙስና እንዳለና በዚህ ዙሪያ ችግር እንደተፈጠረ ሕዝቡ ቀደም ብሎ ቢያውቀውም መንግሥት አሁን የሙስናን መኖር አምኖ ተቀብሎ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ የጀመረ ሲሆን፣ ሙስናን በማጽዳት ሥርዐቱ ራሱን በራሱ አስተካክሎ ሊቀጥል ይችላል ወይ? ተብሎ የሚነሣው ጥያቄ የግድ ወደ ሥርዐቱ እንድንሔድ ያስገድደናል፡፡
ከዚህ አኳያ ስንነሣ የኢህአዴግ የፖለቲካል እና የመንግሥት አመሠራረት የሚከተሉትን ሦስት መሠረታዊ ችግሮች የያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ሀ/ የተለጠጠ መዋቅርና የኢኮኖሚ ዘርፉ የሰፋ ትልቅ መንግሥት መሆኑ፣
ለ/ ፒራሚዳዊና ከላይ ወደ ታች የተዘረጋ የሥልጣን አወቃቀር፣
ሐ/ የአገሪቱን ሥልተ ምርት (Mode of Production) ጥንታዊ በሆነው ግብርና ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ወደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪያዊነትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማለትም ዘመናዊነትን በብቸኝነትና በጉልበት ለማምጣት በኃይል ለመጫወት የሚሞክር (“Civilizing Mission አለኝ” የሚል) መሆኑ፣
እነኚህ ሦስት ሁኔታዎች የኢህአዴግን መንግሥት ኢ-ዴሞክራሲያዊ አድርገውታል ብለን ስለምናምን ነጥቦቹን አንድ በአንድ እያነሣን ለማብራራት እንሞክራለን፡፡
ሀ/ ትልቅ መንግሥት
አሁን ባለንበት ዘመን ያሉት ዕውቅ የፖለቲካል ፈላስፎች በጣም የተንሰራፋና በቅርጹም ሆነ በይዘቱ ትልቅ የሆነ መንግሥት ያቀዳቸውን ሥራዎች ለማከናወን ሆነ የግለሰቦችን መብት ለማክበር በእጅጉ ይቸገራል የሚል አስተሳሰብ አላቸው፡፡ በአንጻሩ እንደ በጎና የተሻለ መንግሥት አድርገው የሚያቀርቡት መዋቅሩ የተወሰነ (Minimal State) እንዲሁም በቅርጹም ሆነ በይዘቱ አነስ ያለ ሥርዐተ መንግሥትን ነው፡፡
የኢህአዴግን የፖለቲካል ሥርዐት በምንመለከትበት ጊዜ በይዘቱ በጣም ሰፊና በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ መካከል ልዩነትና ወሰን አለ ብሎ የማይቀበል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሕዝብና በግለሰብ (Public እና Private) መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት የሚንድ አንድ ወጥ የሆነ ጠቅላይ ኮሚኒቲ (Total Community) እና ጠቅላይ መንግሥት(Total State) ነው፡፡ ወደአገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ስንመለስ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በየክፍለ ግዛቱ የነበሩትን ራሶችና ደጅ አዝማቾች ድል አድርገው በበላይነት ማዕከላዊ ሥርዐቱን አጠናክረው በወጡበት ጊዜ እንደፈረሳቸው ስም “ጠቅል” የሚለው ስያሜ የሥርዐታቸውን ባሕሪይ ያንፀባረቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አሁን ደግሞ የኢሕአዴግ የፖለቲካው ሥርዐት ሁሉንም በአንድ ረድፍ (በማኅበራዊው፣ በኢኮኖሚውና በፖለቲካ) ያካተተና ብዝኃነትን በስም እንጂ በግብር የማይቀበል በመሆኑ ሁለተኛው የ “ጠቅል ዘመን” ብለን ልንሰይመው እንችላለን፡፡
በሁሉም የአገሪቱ ንብረት ላይ በበላይነት እጁን የከተተ መንግሥት የአስተዳደር እክል፣ የብክነት ችግር፣ የትግበራ እንከን ብሎም የሙስና መናኸሪያ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህም በመነሣት እነኚህን ድክመቶች ለመሻገር መሠረታዊ የሆነ የሥርዐት ለውጥ መካሔድ አለበት እንጂ ግለሰቦችን ብቻ መከታተሉ ተገቢም ቢሆን ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊሰጥ አይችልም፡፡
ከመብት ጥሰት አኳያ ይሄን ሥርዐት በምንመለከትበት ጊዜ አጠቃላይና ለግለሰቦች ሕልምና መሻቶች ቦታ የማይሰጥ፤ እንዲሁም በሕዝብ ስም ወይም አስፈላጊ ነው ብሎ በሚያምነው የፖለቲካ ፕሮግራም ስም የግለሰቦችን ውጥንና ግብ ያጨናግፋል፡፡ ነገር ግን በማንኛውም የፖለቲካል እና የሞራል መመዘኛ ገና ለገና “ይጠቅማል” ተብሎ ለታሰበ የፖለቲካ ግብና “ብዙኃኑን ይጠቅማል” በሚል ፈሊጥ የግለሰብን ደኅንነት መሸርሸር ትክክል አይሆንም፡፡
እዚህ ጋ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ስለ ፍትሕ ትልቅ ተቀባይነት ያገኘውን ድርሳን የጻፉት የሀርቫርዱ ፕሮፌሰር ጆን ሮውልስ (John Rowls) “ለማኅበራዊ ጥቅም ሲባል የግለሰብን መብት እንዳንጥስ የፍትሕ እሳቤ ያቅበናል፡፡” ብለዋል፡፡
ለማጠቃለል ኢህአዴግ በብዙኃኑ ስም ከመሬት ነጠቃ፣ ከቤት ማፍረስ፣ ከደመወዝ መቁረጥ፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ በፖሊስነት እንዲያገለግል በማድረግ፣ በቂ ካርታ የሌላቸው ወጣቶች ወደ ንግድ ዓለም ለመግባት ሲያስቡ በድርጅቱ እንዲታቀፉ ማስገደድ፣ ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው የሚወጡ ሥራ እንዲያገኙ የፓርቲ አባልነትን በመስፈርትነት ማስቀመጡ ከላይ ለጠቀስነው የግለሰብ መብት ረገጣ እንደማሳያ የሚቀርብ ሲሆን፣ በሌላም ሥርዐቱ በመንግሥትና በፓርቲ መሐል ልዩነት የማያውቅ ጠቅላይና አካታች (Totalize የሚያደርግ) መሆኑን ያሳየናል፡፡

ለ/ የማዘመን ሚና
እንደሚታወቀው አገራችን የዘመናዊነት ጉዞ ከጀመረች ውላ አድራለች፡፡ ከዚህም አኳያ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ኃይለ ሥላሴ ድረስ በየጊዜው ሥልጣን ላይ የወጡት መሪዎች አገሪቱን “ከኋላ ቀርነት” ወደ “ዘመናዊነት” ለማሸጋገር ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን እንዳለፉት መንግሥታት ይህንኑ “የማዘመን” ፕሮግራም እየተከተለ ነው፡፡
አገሪቱ ገና የኢንዱስትሪያዊነት ደረጃ ላይ ስላልደረሰች አብዛኛው ሕዝቧ በግብርና ላይ የተሰማራ በመሆኑ የግድ ከዚህ ሥልተ ምርት (Mode of Production) መሸጋገር ቢኖርባትም አካሔዱ ኃይልና ጉልበት ላይ ተመሥርቶ ሽግግሩን ለመከወን የሚደረግ በመሆኑ የሕዝቦች አኗኗር እና መብት ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠረ ነው፡፡ ኢህአዴግ “እኔ ወደ ዘመናዊነት የሚወስድ የሕዳሴ ጉዞ ላይ ስለሆንኩ ለዚህ ግብ ይበጃል ያልኩትን ነገር በሙሉ እፈጽማለሁ” ብሎ ተነሥቷል፡፡ እዚህ ላይ ችግሩ የሕዳሴው ራእይ ከአንድ ፓርቲ የፈለቀ እንጂ በውይይት የተቀረጸ ባለመሆኑ የዚህ ራእይ ተጋሪ ያልሆኑ ዜጎች በጠቅላላ በጉልበት እንዲቀበሉት ተደርገዋል፡፡ ይህንንም ስንል “ሕዳሴ” የሚለው ሐሳብ በጎ ቢሆንም ይዘቱ ግን ከግለሰብ ግለሰብ ወይም ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ ሊለያይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለአንዳንድ ሰዎች የቦሌን መንገድ በስድሳ ሚሊዮን ዶላር ከማደስ ሁለት ወይም ሦስት የኦፔራና የቴአትር አዳራሾችን እንዲሁም የሥነ ጥበብና የሙዚቃ ት/ቤቶችን መገንባት የሕዳሴ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በሌላ በኩል በሕዳሴና በልማት ጥሪ ስም በአንዳንድ ክልሎች ዜጎች ከመኖሪያቸው ሲፈናቀሉና የአኗኗር ዘይቤያቸውም ሲናጋ እያስተዋልን ነው፡፡ ይህ ችግር የሚመነጨው “ማኅበረሰቡ ባይገነዘበው ነው እንጂ እኔ ያመጣሁት ፕሮግራም ወይም የማዘመን ሚና (Civilizing Role) ጠቃሚ ነው” ከሚለው ዕሳቤ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህን ፕሮግራም ለማስፈን በሚደረገው የመንግሥት ሙከራ ላይ ተቃውሞ እየተነሳ መሆኑን እያየን ነው፡፡
ሐ/ ፒራሚዳዊ የሥልጠና አወቃቀር
በአንዳንድ የፖለቲካ ፈላስፎች አስተምህሮ አንጻር ሆነን የኢህአዴግን የፖለቲካል ሥርአት ስንመለከተው የአግድም (Horizontal) ሳይሆን አንድ ወጥና ከላይ ወደ ታች የወረደ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ የሥልጣን አዘረጋግ ሕዝቦችን በራሳቸው ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ የሚያደርግና በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ዓይነት ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ወይም ኃይሎች እንዲኖሩ የማይፈቀድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አንድወጥ የፓርቲ ሥርዓት ከላይ ወደ ታች ባለ የጠበቀ የሥልጣን ተዋረድ የተዋቀረ በመሆኑ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቋማት በጠቅላላ ተጠሪነታቸው ለዚሁ ኃይል ብቻ ይሆናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥርዐት ዴሞክራሲን ጠርጎ የሚያስወግድ በመሆኑ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ እንዲሁም የመቃወም ነጻነቶች በአጠቃላይ የፖለቲካ ነጻነቶች ስለማይኖሩ የመንግሥት ተቋማት ለፓርቲው ከማገልገል ውጪ ሕይወት አልባ ይሆናሉ፡፡
በመሆኑም አንዳንድ የፖለቲካ ፈላስፎች እንዳሳሰቡት “ሥልጣን ያማስናል፤ ፍጹማዊ ሥልጣን ደግሞ ፍጹም ያማስናል” (Power Corrupts, Absolute power corrupts absolutely) ይህም የሥልጣን ብልግና በሙስና፣ በአድልዎ፣ በሞራል ዝቅጠት፣ በምዝበራ፣ በንዝህላልነትና በማንአለብኝነት ይገለፃል፡፡
መደምደሚያ
ወደ ጽሑፉ መደምደሚያ ከመግባታችን በፊት በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩ ዳኛ የመንግሥት ገንዘብ አጉድሎ የተከሰሰና በእርሳቸው ችሎት ቀርቦ ጥፋተኛነቱ ለተረጋገጠ ሰው የሠጡትን ተግሣጽ ልናጋራ እንወዳለን፡፡
ዳኛው ለተከሳሹ— “ሰማህ ወይ? የመንግሥት ገንዘብ ሲያዝ ልክ ለቡጢ እንደተዘጋጀ ሰው እጅህን ጭብጥ አድርገህ ትይዘዋለህ፡፡ ከዚያም እጅን ‘ጠበቅ ጠበቅ’ ስታደርገው ጨብጠህ ከያዝከው ነገር ‘ፊጪጭ ፊጪጭ’ እያለ የሚወጣውን ላስ ላስ ታደርጋለህ እንጂ እንደው በመንግሥት አገር እጅህን ከፍተህ ትገምጠዋለህ?” አሉት፡፡
አሁን የሚካሔደውን ምዝበራ በምናይበት ጊዜ የዳኛው ምክር ሕጋዊ ጥያቄ ሊያስነሣ ቢችልም ሲሆን የምየው ግን እርሳቸው እንዳሉት “በጠብታ የሚላስ” ሳይሆን “እጅ ተከፍቶ” የአገሪቱ ንብረት እየተገመጠ መሆኑን ነው፡፡
እስካሁን የቀረበውን ትንተና በሦስት ነጥቦች ለማጠቃለል እንወዳለን፡፡
አንድ፡- ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው ዞሮ ዞሮ ከተዘረጋው ሥርዐት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በመሆኑም ሥርዐቱ በቅርጹም ሆነ በይዘቱ ዐቢይ የሆነ ለውጥ ካልተካሔደበት አሁን ያለው ሥርዐት በራሱ አቅም ራሱን አድሶ ወደ ፊት ለመቀጠል ያስቸግረዋል የሚል አመለካከት አለን፡፡
ወደ ግለሰቦች በምሔድበት ጊዜ ሁሉም የሥርዐቱ አመራሮች በሙስና የተዘፈቁ ናቸው ለማለት ሳይሆን፤ ሙስና ባልነካቸውና በሙሰኞቹ መካከል በሚካሔደው ትግል ሙሰኞቹ ሥርዐቱ ስለሚደግፋቸው ድል ማድረጋቸው የማይቀር ነው፡፡
ሁለተኛ፡- ሥርዐቱ ለሙስና የተመቸ ነው በምልበት ጊዜ ያለው መንግሥት በእጅጉ ትልቅና ሰፊ እንዲሁም በሥሩ ሰፊውን የአገሪቱን ሀብት አስተዳዳሪ በመሆኑ ከሙስናና ከአስተዳደር ግድፈት የዳነ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የተንሰራፋ መንግሥት አንድ የምሥራቅ አውሮፓ የፖለቲካ ፈላስፋ “ከሚችሉት በላይ ይጎርሱና ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የጎረሱትን ያኝኩታል” ሲል ይገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካ ኃይል እና የኢኮኖሚ ኃይል አንድ ቦታ ወይም ሁነት በሚያጋጥምበት ጊዜ የዜጎች ነጻነትና መብት ትልቅ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡
ሦስተኛ፡- ኢህአዴግ ሥልጣን በብቸኝነት ጠቅልሎ መያዙ፣ ራሱን ከሌላ ፓርቲ ጋር ለማወዳደር አለመፈለጉና ለትችትና ለሒስ ቦታ አለመፍቀዱ “የምናለማም እኛ የምናጠፋም እኛ” ማለትም ዜጎች አይመለከታቸውም በሚል ዕሳቤ በፓርቲ ውስጥ የሚካሔደውን ሙሰኝነት ያለዜጎች ተሳትፎ ለመቋቋም መነሣቱ ውጤታማ እንደማያደርገው ከወዲሁ መናገር ይቻላል፡፡ ምናልባት ዜጎች በዚህ ዙሪያ ጥያቄ ባነሡ ቁጥር የሚሰጠው መልስ “ተባብረን መፍትሔ መፈለግ አለብን” ሳይሆን የሚሉት በአጠቃላይ ዜጎችን ወደ ጥቆማ አቅራቢና ወደ “ጆሮ ጠቢነት” ሚና የሚያወርድ ነው፡፡ ይኸውም የሚሆንበት ምክንያት ለኢህአዴግ የሕዝብ ትብብር ማለት መረጃ ማቅረብ ብቻ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑ ነው፡፡ በእኛ አስተሳሰብ ግን የሕዝብ ተሳትፎ ስንል ዜጎች በነጻነት የሚሳተፉባቸውን ሕዝባዊ ስብሰባዎች፣ ነጻ የምክክር መድረኮች፣ ተቃውሞና ትችት የማሰማት መብት ወዘተ. በተፈቀደ ጊዜ በጉዳዩ ላይ የሕዝብ ተሳትፎ አለ ለማለት እንችላለን፡፡
የዚህ ግጥም ጸሐፊ ጸገየወይን ገ/መድህን ከኢህአፓ መስራቾችና መሪዎች አንዱ የነበረ ዕውቅ ታጋይ ሲሆን ለህዝብ መብት ሲታገል መስዋዕት ሆኗል፡፡ ይህ ግጥም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲን ጽ/ቤት ከተዘጋጀው “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች ከ1943-1993” ከሚል መድብል በከፊል የተወሰደ ነው፡፡
ናስተማስለኪ
…ሰማሽ ወይ እናቴ ሰማሽ ወይ ቅድስት
የመልክሽ ዓይነቱ የምስልሽ ብዛቱ ኁልቈ መሣፍርት፣
አንዳንዱ ይልሻል መሶበ ወርቅ ንጽሕት
የሥርጋዌ ትርጉም የተገለጸባት
ሸልሞ ሸላልሞ የሠራት መለኮት፣
የሚያነሆልለው መቼ ሆነ ጌጧ
እንጀራ አይገኝም መና ነው ተውስጧ፣
በወርቅ የተለበጥሽ ታቦት ነሽ ለሌላው
መቅደስ ለሚገባው ቅባት ለተቀባው፣
እኔ ግን መሃይምን አላየሁ ምስጢር
መልክሽን ጠባይሽን እንዳልመረምር፣
ተውስጥ ሲያስተጋባ የወንጀሉ ትእዛዝ ሥርዐትና ሕጉ
አሜን ብቻ ሆነ የመሃይምን ወጉ፣
የታደለውማ ጠምጥሞ ጠማጥሞ፣ ደርቦ ደራርቦ፣
ሲደልቅ ሲጸፋ ሳብ ረገብ ሲል በማኅሌተ ገንቦ፣
ጥቂት ቀረበ ብዬ ለማዳመጥ ብሻ
መች መቆሚያ አለና መች መተንፈሻ?
ትንፋሽ እያጠረኝ መማለል ታልቻልኩኝ አቤት አቤት ብዬ
እንዲያው መገተሩ መቆም ምን ጉዳዬ፣
ከቶ እንዴት ይበለኝ ዝም ብለህ ሥገድ
ጉልበቴ መቁሰሉን፣ አጥንቴ ማግጠጡን ያላየልኝ ዘመድ፣
ባፍንጫዬ ይውጣ በታቦት ማመኔ
ነቀዝ ሲጨርሰው እያየሁት ባይኔ፣
ገራሕት የሚልሽም አልጠፋም ነበረ
ማገጥ እያበቀልሽ ሐሳቡ ተሻረ፣
ያየሽም ይገኛል በአምሳለ ማዕጠንት
የተጠወረብሽ ነበልባለ እሳት
ወላፈኑ ሚገርፍ ፍሕሙ የሚገላምጥ የሚያበግን አንጀት፣
ጢሱ አፍ የሚያፍን የሚያስቀሳፍት፣
ልብ የሚያስለመልም የሚያፈስ ሐሞት፣
የተራራ መቅረዝ ይልሻል ዕውር
ያለቦታው ገብቶ፣ በማያውቀው ነበር ሲሆን ምስክር፣
ብርሃንማ ቢኖር እንተያይ ነበር እንነጣጠር፣
ብርሃን ቢኖር ነው ወይ የተመሰግሁ ዱር፣
ተአጋም መካከል ተጥቅጥቅ ቆንጥር፣
በዚህ ወጣ እንዳልል በዚያ እንዳላገድም
ቀን ጠፋ ቀን ጠፋ በየትም በየትም፣
ደሜንም ጨለጠው፣ ገላዬን ጨረሰው ቆንጥሮ ቆንጥሮ
ወጣት ሽማግሌው ባልቴቱ ወይዘሮ
በጅጌ በወንፈል ተነሥ ለምንጣሮ፣
ጨለማን ጋሻ አርጎ፣ አዕጹቁን አድርቶ ሥሩንም አዛምቶ
ዋርካ እየመሰለ፣
አምባ የሚሹትን መጠጊያ ያጡትን ግራር አታለለ፣
ከየትም፣ አረፈድን፣ ከየት ባጀነ በሾሁ አንክሰን
የምነቅልበቱ ወረንጦ አጥተን
ቀኝ ኋላ ዙር ሁኖ ቀረ ዘያንች፣
ጉድ አትፈራ መሬት ጉዳንጉድ አብቅላ
አስጠቀጠቀችን በሾክ ባሜከላ….
ጸገየወይን ገብረመድህን
የኮሌጅ ቀን ግጥሞች (በከፊል የተወሰደ)
ከ1943-1993

No comments:

Post a Comment