በ መሀመድ ሀሰን
እርግጥ ነው፡የተሻለ ግዜና እውቀት ያለው
ሰው በኢህአዴግ የአልባነት ጉዞ ላይ ከጥራዝም በላይ መጻፍ እንደሚችል ይሰማኛል፡፡ እኔ ግን የዘመነ ኢህአዴግ ፍጥረት እንደመሆኔ፡አሁን
ስላለው ስርዓት የራሴ የሆነ መረዳት አለኝ፡፡ ይኽውም ምንድነው? ካላችሁኝ፡ የኢህአዴግ የመጨረሻው ህልም በዚህች ምድር
ላይ ሰው አልባ የሆነችን ሀገር መፍጠር ይመስለኛል፡፡ እንደ ዜጋ ስናስበው መቼም ከዚህ የከፋ እርግማን የለም፡፡ኢትዮጵያ በምትባል
ምድር ላይ ተፈጥረን፡የተፈጠርንባትንም ምድር ተነፍገን፡ምድሪቱም ሰው አልባ ሆና፡…ከዛስ?…..ይህንን ህልም ማሰብ ቅዠት
የሚሆንባችሁ ጥቂቶች እንደማትሆኑ እገምታለው፡፡ነገር ግን የገዢዎቻችን ህልምና ፍላጎት ወደዛው እያመራ ስለመሆኑ በርከት ያሉ ማሳያዎችን
ማንሳት ይቻላል፡፡
የምን ሰው አልባነት?
ሀገራችን ኢትየጵያ
ሰው አልባ ወደመሆን እተሸጋገረች ነው ስል ደግሞ የምን ሰው አልባነት ነው?እንዴት ሀገር ሰው አልባ ትሆናለች?ቀባጣሪ፤ሟርተኛ፤አልያም
ደግሞ የ‹‹አውራውን›› ፓርቲ አፍ ተውሳችሁ መርዶ ነጋሪ ትሉኝ ይሆናል፡፡ግዴለም እኔ ይህንን የማሰብ ብቻ ሳይሆን የማለት መብታችሁንም
አልጋፋም፡፡ ይልቅስ እኔ ሰው አልባ ስላልኳት ሀገር የሚሰማኝን ላካፍላችሁ፡፡
ባለፈው ሳምንት ካነበባችሁት
ከፕሬሱ ብንነሳ፡በአሁን ሰዓት ሀገሪቱ መሰረታዊ ከሚባሉ ለሰው ልጆች ከተሰጡ ነጻነቶች ውስጥ ዋነኛ የሆነው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ
መብቷን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስደፍር መልኩ ተነጥቃለች፡፡ አሁን ላይም ቢሆን የተወሰነ ጭላንጭል አለ የሚል መከራከሪያ ይነሳ ይሆናል፡፡
ነገር ግን መከራከሪያው በበርካታ ምክንያቶች ውድቅ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ጭላንጭሉን(አለ ከተባለ) የሚታገሰው አንድም
ብርሀን አይፈነጥቅም፤ቢፈነጥቅም በኔ ላይ የሚያደርሰው ፖለቲካዊ ኪሳራ የለም ብሎ እስካመነ ድረስ ሲሆን፤በሌላ በኩል ደገሞ ጨለማው ሲያስፈራው፡ ጭርታው ሲደብረው እራሱ
በተን ያደረጋቸው ናቸው፡፡እነዚህ ግን በሀገሪቱ ላይ የፕሬስ ውጤቶች አሉ ለማለት የሚያስደፍሩ አይደሉም፡፡ በተለይም በሁለተኝነት
የጠቀስኳቸው፡ጭላንጭልነታቸውን አምኖ የሚቀበለው የጨለማው ባለቤት የሆነው ኢህአዴግ ካልሆነ በስተቀር፡ የነጻው ፕሬስ ናፋቂ የሆነ
ሰው ከድቅድቁ ጨለማ ውጪ የሌለው ጭላንጭል ፈጽሞ ሊታየው አይችልም፡፡ እነዚህ ተቋማት በገዢው ፓርቲ ፍላጎት፡ይሁንታ፡የገንዘብ ድጋፍ፡…የተቋቋሙ
ሲሆን፤በስራቸው ያሉ ‹‹ጋዜጠኞችም›› ጋዜጠኝነትን(አብዛኞቹ) ለሆዳቸው፡ለኑሯቸው፡ለፍርፋሪ ጥቅማጥቅሞች፡…ሲሉ የሚሰሩ ናቸው፡፡
ስለዚህ በሀገራችን ፕሬሱም ሆነ ባለሙያው እንደሌሉ የሚቆጠሩበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ ይህንን መሰረታዊ የሆነውን ሀሳብን
በነጻነት የመግለጽ፡የመጻፍ፡የተጻፈውን የማንበብ፡…መብቱን ተነፍጎ አፉ፡አይኑ፡እጁ፡ የታሰረ ህዝብ ምኑ የዛች ሀገር ዜጋ ነኝ ያሰኘዋል?
ከፕሬስ ጋር የተያያዘውን ጉዳይ እንደው ለአብነት ያህል አነሳነው እንጂ፡ በዚህች ሀገር ላይ በመሰረታዊነት የተነፈግናቸው
ነጻነቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡የመሰብሰብ፡የመንቀሳቀስ፡ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፡የመደራጀት፡ የመነገድ፡የመስራት፡የመማር፡…ነጻነቶች
እንደዜጋ ሊኖሩን የሚገቡ፤ነገር ግን በዛሬዋ ኢትዮጽያ ላይ የሌሉ ነጻነቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር ይሁንታን የሚያገኘው በገዢዎቻችን
ፍላጎትና አምሳል እስከተረተጸ ድረስ ብቻ ነው፡፡ሁሉም ዜጋ በአንድ
የገዢው ፓርቲ ጭንቅላት ርዕዮት ብቻ እንዲያስብ ይፈለጋል፡፡ ይህ ደግሞ የተለያየ ፍላጎትና ተፈጥሮ ላለው የሰው ልጅ የሚቻልም፡የሚሆንም
አይደለም፡፡ይህ ህልማቸው እውን የሚሆን ከሆነና መሰረቱንም እያጸና ከሄደ መጨረሻው የሚሆነው ሀገሪቱ ላይ ሰው አልባነትን መፍጠር
ነው፡፡እንደ ፋብሪካ እቃ በገዢዎቻቸው ጭንቅላት ብቻ የሚያስቡ ፍጥረታትን መቼም ሰው ብሎ መጥራት ይከብዳል፡፡
ዛሬ ላይ ግን እንደምናየው በተገላቢጦሹ ዜጎች ደረጃ ወጥቶላቸው፡አእምሮ አልባዎቹ የሀገሪቱ ምርጥ ዘሮች በመባል የአንደኛ
ዜጋነት ደረጃ ሲሰጣቸው፡የራሳቸውን ህሊና ለመጠቀም የሚሞክሩትን ደግሞ ሀገራቸውን በመንጠቅ፡ በከሀዲነት ሊፈርጇቸው ይሞክራሉ፡፡ታዲያ
የነዚህ ሰዎች ህልም ምን አይነቷን ኢትዮጵያ መፍጠር ይመስላቹሀል?
ሌላው ቢቀር ዛሬ ውሏችን፡አዳራችን፡አመጋገባችን፡ሀይማኖታችን/አምልኳችን/፡የመሬት/የቤት/ባለቤትነታችን፡ምርጫችን፡
...ሁሉ በነሱው ቁጥጥር ስር የወደቀ ነው፡፡ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የሀገር አልባነት አደገኛ ህልማቸው አይሳካም በሚል፡ህልመኞችን
ከጥፋታቸው፡ሀገሪቱን ደግሞ ከጥፋት የመታደጊያ መንገዱ በኛው በዜጎቿ እጅ ላይ ያለ ነው፡፡ይህም የሚሆነው በማንም መልካም ፈቃድ
ሳይሆን፤ በኢትዮጽያውያኑ የያገባኛል ስሜት መነሳትና መስራት ነው፡፡ እምቢኝ! ሀገሬ ሰው አልባ አትሆንም፤ቢያንስ እኔ አለሁላት፤
የሚል ስሜትና ቁጭት በያንዳንዳችን ውስጥ ሊፈጠር ይገባል፡፡በእርግጥ እኛ ይህንን ስናደርግ፡ሽብርተኛ፡አድሀሪ፡የደርግ ርዝራዥ(ለምሳሌ
የኔ እኩዮችየኢህአዴግ ፍጥረት መሆናችንን ይረሱታል)፡ሟርተኛ፡…ይሉናል፡፡ችግር የለውም፤እነሱ ህልማቸውን ጨምሮ ጉዟቸውም ንግግራቸውም
ምክንያት አልባ ነውና ልንሰማቸው አይገባም፡፡የኛ ህልም እያፈረሷት ያለችውን ኢትዮጽያ መታደግ ነውና፡፡ ለማንኛውም ዛሬን እንደመሰነባበቻ
በሀዲስ አለማሁ የልምዣት መጽሀፍ ውስጥ ባለችው ግጥም እንሰነባበት፡፡ (ነገር ግን የዚህን ገፀባህሪ ተስፋ የቆረጠ ፍልስፍና መከተል
ወይስ ለለውጥ መነሳሳት? ይህ ነው ጥያቄው፤መሆን ወይስ አለመሆን? እኔም እላለሁኝ ሰው መሆን ወይም አለመሆን!)
ይህ
የወንበዴ አለም፣የወንበዴዎችን ሥራት ተከትሎ
ደካሞችን ረግጦ፣ሀይለኞችን አዝሎ
ያም ቢጮህ፣ያም ቢጮህ ይቀጥል ወደፊት፣ይጓዝ ዝም ብሎ
ይህ ነው ያለም ሥራት ብንወድም ብንጠላ
ይህን ለመቀበል፣ልቡ የሚኮራ ደሙ የሚፈላ
ታግሎ መለወጥ ነው መንገድ የለም ሌላ፡፡
ነገር ግን እንደኛ፣ደሙ የማይፈላ ፣የረጋ ቀዝቅዞ
አለሙን እንዳለ፣እስከጉስቁልናው፣እስከግፉ ይዞ
ጥቃት እንዳያስቆጭ፣ምክንያት በመፍጠር፣መንፈስን አቡዞ
ግፍ እንዳያሰቃይ፣በጌሹዋማ ጠላ፣ራስን አፍዝዞ
ቀን እየሰከሩ፣ሌሊት እየተኙ፣መቀጠል ነው ጉዞ፡፡
ሀሀሀሀሀሀ እንዲያ ነው መጠጣት፣መተኛት፣ማለምና መስከር
ስካር መልካም ነገር፣እልም መልካም ነገር፣
እግዜር የነሳኝን፣ያደርጉኛል ጌታ፣ያስገዙኛል አገር፡፡
ባልገዛ፣ባልነዳ፣ባላዝዝ ባልናዝዝ፣ስሰክር ተሹሜ
ወዳጆቼን ባልሾም፣ጠላቶቼን ባልሽር፣ስተኛ በህልሜ
የዚችን አለም ጣም፣ሳልቀምስ እሞት ነበር፣በድሜየ ፍጻሜ፡፡
ጨምሩኝ ከጠጁ፣ልስከርና ልንገስ
ዙፋን ይዘርጋልኝ፣ልብሰ መንግስት ልልበስ
ድሆችን ላበልጽግ፣ሀብታሞችን ላደህይ፣የልባችን ይድረስ፡፡
አምጡ! ስጡ! ጠጡ! ስጡ! አምጡ! አምጡ፡፡
ደካሞችን ረግጦ፣ሀይለኞችን አዝሎ
ያም ቢጮህ፣ያም ቢጮህ ይቀጥል ወደፊት፣ይጓዝ ዝም ብሎ
ይህ ነው ያለም ሥራት ብንወድም ብንጠላ
ይህን ለመቀበል፣ልቡ የሚኮራ ደሙ የሚፈላ
ታግሎ መለወጥ ነው መንገድ የለም ሌላ፡፡
ነገር ግን እንደኛ፣ደሙ የማይፈላ ፣የረጋ ቀዝቅዞ
አለሙን እንዳለ፣እስከጉስቁልናው፣እስከግፉ ይዞ
ጥቃት እንዳያስቆጭ፣ምክንያት በመፍጠር፣መንፈስን አቡዞ
ግፍ እንዳያሰቃይ፣በጌሹዋማ ጠላ፣ራስን አፍዝዞ
ቀን እየሰከሩ፣ሌሊት እየተኙ፣መቀጠል ነው ጉዞ፡፡
ሀሀሀሀሀሀ እንዲያ ነው መጠጣት፣መተኛት፣ማለምና መስከር
ስካር መልካም ነገር፣እልም መልካም ነገር፣
እግዜር የነሳኝን፣ያደርጉኛል ጌታ፣ያስገዙኛል አገር፡፡
ባልገዛ፣ባልነዳ፣ባላዝዝ ባልናዝዝ፣ስሰክር ተሹሜ
ወዳጆቼን ባልሾም፣ጠላቶቼን ባልሽር፣ስተኛ በህልሜ
የዚችን አለም ጣም፣ሳልቀምስ እሞት ነበር፣በድሜየ ፍጻሜ፡፡
ጨምሩኝ ከጠጁ፣ልስከርና ልንገስ
ዙፋን ይዘርጋልኝ፣ልብሰ መንግስት ልልበስ
ድሆችን ላበልጽግ፣ሀብታሞችን ላደህይ፣የልባችን ይድረስ፡፡
አምጡ! ስጡ! ጠጡ! ስጡ! አምጡ! አምጡ፡፡
ሀዲስ
አለማየሁ፣የልምዣት፣ ገጽ 156
No comments:
Post a Comment