Main page
▼
ዲሞክራሲን በተግባር እናውል፤ የሰላማዊ ሰልፍ መብታችን ይመለስ! ሦስተኛው የበይነ መረብ ዘመቻ ጋዜጣዊ መግለ
ዞን 9 ኢ-መደበኛ የአራማጆች እና የጦማሪያን ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ማኅበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ
የተለየ እና ወገናዊ ያልሆነ ታረክ ለመፍጠር እየሠራ የሚገኝ የወጣቶች ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ይህንን የምናደርግበት
ዋና ዓላማ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሀገሪቷ ጉዳይ ያገባኛል ብለው ውይይት የማድረግ ባሕል እንዲያሳድጉ በማድረግ
ሀገሪቷን በሁሉም መስኮች ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርሱ ሐሳቦች እንዲወለዱ ለማመቻቸት ነው፡፡
የተከበራችሁ የዞን9 ነዋሪዎች፣ በ2005 ዓ.ም ሊደረጉ ከታቀዱት አራት የበይነመረብ ዘመቻዎች ሦስተኛው የፊታችን
ረቡዕ ሚያዝያ 30 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አርብ ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል፡፡ ሦስተኛው
ዘመቻ መንግሥትን እና ሁላችንንም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 30 የሰፈረውን ‹ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር
በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት እንድናከብር›
የሚጠይቅ ነው፡፡
ሰላማዊ ሰልፍ እና ስብሰባ የማድረግ መብት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የተደረገለት
ዜጎች ድጋፋቸውን ወይንም ተቃውሟቸውን ከመሰሎቻቸው ጋር በመሆን ሐሳባቸውን መግለጽ እንዲችሉ እና ያገባናል የሚሉት
ጉዳይ ላይ ሐሳብ እዲለዋወጡ እና እንዲወያዩ ነው፡፡
የ1997 ዓ.ም ምርጫ ቅስቀሳ አካል የነበሩት
የሚያዝያ 29 እና 30 ሰልፎች በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እና መሰብሰብ መብት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጅ ለተወሰነ ጊዜ ተገድቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዛ በኋላ የተካሄዱ ጥቂት ሰላማዊ ሰልፎች የአንድ ወገን
ሐሳብ የሚንጸባረቅባቸው እና ለዚያም ሲባል ይሁኝታን ያገኙ ብቻ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ከሚያዝያ 30፣ 1997
ወዲህ ተቃውሞን አስመልክቶ የተደረገው ሰልፍ የወ/ት ብርቱካንን መታሰር አስመልክቶ የተካሄደ ሲሆን 250 ሰዎችን
ብቻ ያሳተፈ ነበር፡፡ በወቅቱ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በሰልፉ ላይ ለሚኖረው የደህንነት ችግር ኃላፊነት
እንዲወስዱ መጠየቃቸው የተሳታፊዎችን ቁጥር ለመቀነስ መገደዳቸው ይታወሳል፡፡
ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳች
ዙሪያ የሚደረጉ ስብሰባዎችም ቢሆኑ በግልጽ ተአቅቦ ባይደረግባቸውም የተለያዩ አስተዳደራዊ ጫናዎችን በመፍጠር
እንዳይካሄዱ የእጅ አዙር ክልከላ ይደረግባቸዋል፡፡ ከመንግሥት የእጅ አዙር ክልከላ ሲያልፍም የመሰብሰቢያ ቦታ
አቅራቢዎች ከሚደርስባቸው ቅድመ ማስፈራራርያ ወይንም ይደርስብኛል ብለው ከሚያስቡት አስተዳደራዊ በደል የተነሳ
መሰብሰቢያ አዳራሾችን ይከለክላሉ፡፡
የሦስተኛው ዘመቻ ዓላማ መሣሪያ ሳይዙ ሰላማዊ ሰልፍ እና ስብሰባ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ላይ የተጣሉ ቀጥተኛ እና የእጅ አዙር ገደቦች እንዲነሱ መጠየቅ ነው፡፡
ዘመቻው በዋነኛነት የሚካሄደው ‹‹ፌስቡክ›› እና ‹‹ትዊተርን›› (#Assembly4Every1 እና
#Demonstration4Every1 የሚሉ ኃይለቃሎችን) በመጠቀም ይሆናል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ እና ስብሰባ የማድረግ
ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን በተመለከተ የተለያዩ ጽሑፎች በጦማራችን የሚወጡ ሲሆን በፌስቡክ እና በትዊተርም ላይም
ይለቀቃሉ፡፡ በሁለቱ (የዞን9 እና የሕገ-መንግሥቱ ይከበር!) የማኅበረሰብ ገጾች ላይ ለዚሁ ዘመቻ ሲባል የተዘጋጁ
አጫጭር ጽሑፎች ይሰራጫሉ፡፡ ዘመቻውን የሚመለከት ‹ባነር› ተዘጋጅቶ ዘመቻው በሚቆይባቸው ቀናት የተለያዩ ፕሮፋይል
ምስሎችም ተዘጋጅተው የሽፋን ምስል እና የፕሮፋይል ፎቶ ይሆናሉ፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ለመላው የዞን9
ነዋሪዎች እና በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት ተከብሮ ማየት
ለምትፈልጉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ጉዳዩ ላይ ያላችሁን አመለካከት፣ መብቱ የተጣሰባቸውን ክስተቶች በማካፈል በጉዳዩ
ላይ በመወያየት እንዲሁም የፕሮፋይል ፎቷችሁን በመቀየር በዞን9 ጦማር እና በ‹ዞን9› እና ‹ሕገ-መንግሥቱ ይከበር›
የፌስቡክ ገጾች የዘመቻው ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑ በትህትና እንጋብዛለን፡፡
ስለሚያገባን እንጦምራለን!!!
ዞን9
No comments:
Post a Comment