Tuesday, February 4, 2014

ምሁራኑ ሠልጣኝ፣ ሹመኞች አሰልጣኝ የሆኑበት ዩኒቨርሲቲ ሆኗል

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ




(ዕንቁ መጽሄት)

መጽሔታችን የአገራችን የትምህርት ሁኔታበከፍተኛ ደረጃ ችግር ላይ የወደቀ መሆኑን በመገንዘብ፣ የችግሩን ጥልቀት ለማወቅና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማስቀመጥ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ካደረጉ ምሁራን ጋር ተከታታይ ውይይቶችንስታደርግ ቆይታለች፡፡ በዚህ ዕትማችንም ውይይቱን በመቀጠል ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋርስለትምህርት ፍልስፍና፣ ስለዩኒቨርሲቲ ተልዕኮና ስለሌሎቸ ተያያዥ ጉዳዮች ቆይታ አድርገናል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ለአብዛኛው የመገናኛ ብዙኃን ተከታታይ እንግዳ ስላልሆኑ ማስተዋወቅ ያለብን አይመስለንም፡፡ ውይይቱን እነሆ፡-
ዕንቁ፡-ውይይታችን በዩኒቨርሲቲባህሪና ትርጉም እንጀምር፡፡ ለመሆኑ ዩኒቨርሲቲ ምን ማለት ነው?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ከሁሉ አስቀድሞ ይኼ ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ መልስ የሚሰጠው ሳይሆን በተለያየ ጊዜና በተለያየ የባህልና የአመለካከት አውድ ውስጥ ተፈትሾ ለመግለጽ የሚሞከር ጉዳይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ በባህሪው የሕዝብ (‘ፐብሊክ’) እና የግል (‘ፕራይቬት’) የሆነ ልዩ ተቋም መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡እንደሕዝብ ተቋምነቱ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ተሰማርቶ ለማኅበረሰቡ ይውላሉ ወይም አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ነገሮች በማበርከት አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ እንደግል ተቋምነቱ ደግሞ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ የራሱ የሆነ ግብና ዕቅድ አንግቦ ለሰው ልጅ መንፈሳዊና አዕምሯዊ ብልጽግናንናበአጠቃላይ ዕውቀትን ለማጎናጸፍ የተቋቋመማዕከል ነው፡፡
አሁን የበላይነት ወደያዘው የአገራችን የትምህርት ፍልስፍና ስንገባ፣የዩኒቨርሲቲዎች ሕልውና የተመሰረተበትን የግል ጥሪና ፍላጎት ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ተቋማቱን የሕዝብ አገልግሎት አቅራቢ ብቻ ለማድረግመንግሥትና የዩኒቨርሲቲዎቹ የበላይ አስተዳዳሪዎች ቆርጠው ተነስተዋል፡፡በመሆኑም ለማኅበረሰቡ “ቀጥተኛ ጥቅም” አይሰጡም ያሏቸውን እንደፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ሥነ-ጽሁፍ፣ ቋንቋና ሌሎች የሥነ-ሰብዕ ትምህርቶች እንዲቀጭጩ መደረግ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች አልመረጡም በሚል ፈሊጥ የቅድመ-ምረቃ ፕሮግራሙ ወደመዘጋት እየደረሰ ነው፡፡
ዕንቁ፡-የዩኒቨርሲቲን ተፈጥሮና ጠባይ ከሞላ ጎደል ለመመልከት ትንሽ ወደታሪክ መመለስ ይኖርብናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለመሆኑዩኒቨርሲቲ እንደ ተቋም እንዴት ተጀመረ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ይኼ ጥያቄ ማንም ሰው እንደሚረዳው ሰፋ ያለ ትንታኔና ገለጻ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሆኖም ግን ጥቂት ነገሮች ለመግለጽ ያህል፣ በዚህ መስክጥናት ያደረጉትምሁራንእንደሚነግሩን ዩኒቨርሲቲ አውሮፓበ13ኛው እና በ14ኛው ክፍለ ዘመን ከደረሰችበት የመንፈስ፣ የባህል፣ የፍልስፍና…ወዘተ ሥልጣኔ የመነጨ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ታሪክ ዙሪያ ከጻፉት ምሁራን መካከል እውቅናን ያገኙትና በሰፊው የሚጠቀሱት‘ቻርልስ ሆሜር ሀስኪንስ’ (Charles Homer Haskins) ናቸው፡፡እንደሳቸው አቀራረብ ዩኒቨርሲቲ ከጥንታዊ ግሪኮችና ከሮማውያን ሥልጣኔ ጋር ግንኙነት ቢኖረውም በይዘቱናበጠባዩ የመካከለኛው ዘመን ውጤት ነው፡፡
ከአዕምሯዊ ይዘቱ አካላዊ ወደሆነው ቅርጹናአደረጃጀቱስንመጣ፣ ‘ሀስኪንስ’ በታሪክ ድርሳናቸው ላይእንዳብራሩትለዩኒቨርሲቲ (ግቢ) መፈጠር ምክንያት ከሆኑት ውጫዊ ሁኔታዎች መካከልበወቅቱ ተማሪዎችን የገጠማቸውየቤት ኪራይ ዋጋ መናር አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜብዙ ተማሪዎች ትምህርት ለመቅሰም ወደከተማ ይጎርፉ ነበር፡፡ የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የቤት ኪራይ ዋጋም በጣም እየናረ ሄዶ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ተማሪዎች የሚከፍሉትን የቤት ኪራይ ወጪ ለመቀነስ በአንድ ላይ መሰባሰብና በጋራ በመሆንተደራድረው የቤት ኪራይ ማስቀነስ ጀመሩ፡፡ ይሄ አንዱ ምክንያት ነው፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ ከአስተማሪዎች የሚመጣው ችግር ነበር፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል ገንዘብ እየተቀበሉ ከማስተማር ሥራቸው የሚጠፉ መምህራን ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይኼ ነው የሚባል የትምህርት ዝግጅት ወይም የማስተማር ችሎታ ሳይኖራቸው “መምህራን ነን” የሚሉም ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት ተማሪዎች ተሰብስበውና ተቋም ፈጥረው አስተማሪዎችንሕጋዊ ግዴታ ያስገቧቸው ጀመር፡፡የትምህርት ዝግጅታቸውን የሚያሳይ ሰርተፊኬት መጠየቅምተጀመረ፡፡ ይህ ሰርትፊኬት ቀስ በቀስ ለዲፕሎማና ለዲግሪ መፈጠር አስኳል ሆነ፡፡
ዕንቁ፡- አንደኛው የዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ ዕውቀት ማመንጨት ነው ካልን፣ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የዕውቀት ድርሻ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-የዩኒቨርሲቲን ተልዕኮና የእውቀትን ድርሻ በሚመለከት ሁለት አበይት የሆኑ ክርክሮችና አመለካከቶችአሉ፡፡አንደኛው፣ ከ300 ዓመት በፊት በአጠቃላይ ስለትምህርትና ስለዕውቀት ጠቃሚነት የጻፉት (የሳይንስ አብዮት ጀማሪዎች ከሚባሉት አንዱ)እንግሊዛዊው ሮጀር ቤከን እንዳስተማሩትዕውቀት ከተግባር ተለይቶ ሊታይ የማይችል፣ ለሰው ልጅ የኑሮ ደረጃ (በጤና፣በእርሻ …ወዘተ)አስተዋጽኦ ማድረግ ያለበት ነገር ነው፡፡በቤከን እምነት ዕውቀት የዕድገት ወይምየኑሮ ማሻሻያ መሳሪያ ነው፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ የሚጠቀስላቸው አባባል እንደሚነግረን ለእርሳቸው‹‹ዕውቀት ማለት ሀይል ነው››፡፡
ወደ ሁለተኛው አመለካከት ስንመጣ ደግሞ ከመቶ ዓመታት በፊት “The idea of the University” በሚል ርዕስ ወሳኝ ድርሳን የጻፉትን ካርዲናል ኒውማንን እናገኛለን፡፡ እንደ እርሳቸው አመለካከት ዕውቀት የራሱ ተልዕኮ አለው፡፡ እንደ መገልገያ መሳሪያ ብቻ ሊታይ አይገባውም፡፡ ዕውቀት የሰውን ልጅ አዕምሮ የሚኮተኩትና ሰውን የተሟላ ፍጡር የሚያደርግ ነው፡፡
እነኝህንሁለትየአመለካከት ዘይቤዎች መሰረት አድርጎ አሁንም አልፎ አልፎ ክርክሩ ቢቀሰቀስም፣ባለንበት ዘመንአንድ ዩኒቨርሲቲ የተሟላ ነው የሚባለው ቢያንስ ቢያንስ የሚከተሉትን ሦስትዕቅዶች አንግቦ ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ ይኸውምየመማር ማስተማር ሂደት የሚከናወንበት፣ ዕውነት ላይ ለመድረስ ጥናትና ምርምር የሚደረግበትና በልዩ ልዩ መስክለማኅበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጥበትተቋም ነው፡፡በመሆኑም ምርጫው የሮጀር ቤከን“ጥቅማዊ” መንገድ ብቻ ወይም የካርዲናል ኒውማን“አዕምሮን ማበልጸግ”የተናጠል አስተሳሰብ አይደለም፡፡
አሁን በአገራችንመንግሥት እየተከተለ ያለውንየትምህርት ፍልስፍና ስንመለከት፣መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችችግር-ፈቺና ቁሳዊ ጥቅምን ማምጣት የሚችሉመሆን አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ ይኼም ማለት፣ትምህርት ራሱ በራሱ በጎና አስፈላጊ ነገር ሳይሆን መንግሥት ላቀደው የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት አጋርና አካል መሆን አለበት ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ዩኒቨርሲቲውን በሚመለከት አንድ ትልቅ እንደ ደንቀራ ሆኖ የገጠመን ችግር ይኼ ነው፡፡በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ወደፊት በሚቀጥለውዕትም በሰፊው እንመጣበታለን፡፡ ከወዲሁ ግን ከችግሩ አኳያ አንድ ሁለት ነገሮች ብቻተናግሬ ልለፍ፡፡ በሌላ ጉዳይም ላይ ተደጋግሞ እንደሚታየው ሁልጊዜም በባህላችን መካከለኛ መንገድ ከመምረጥ ይልቅ ነገሮችን ከአንድ ወይም ከሌላ ጥግ ብቻ የማየት ግድፈት አለብን፡፡
ሁለተኛ፣ገዥው ግንባር በሌሎች ጥያቄዎችም ላይ እንደሚያደርገውችግር ብሎ ለሚያነሳቸው ጉዳዮች በሙሉ አንድ ብቸኛ መፍትሄ እንዳለ አድርጎ የማቅረብ አባዜ አለበት፡፡እስከሚገባኝ ድረስ ‹‹ከቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ ውጪ የተለየ አቀራረብ ሊኖር አይችልም›› የሚለው ወይም ደግሞ ‹‹አማራጭ የለም››የሚለው አመለካከት ምርጫ የሚያሳጣ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ነጻነትን በእጅጉየሚጋፋም ነው፡፡ እንዲያውም በሕግ የሰው ልጆችን አስተሳሰብ ከመገደብ የበለጠ ጫና የሚፈጥረውና ነጻነት ገፋፊ የሚሆነው በተወሰነ ጥያቄ ዙሪያ አማራጮችን ዘግቶ ልክ አንድ ብቸኛ መፍትሄ እንዳለ አድርጎ የማቅረብ አካሄድ ነው፡፡ ይኼ ‹‹እኔ ካቀረብኩት የመፍትሄ አማራጭ ውጪ ሌላ መንገድ ሊኖር አይችልም›› የሚለው አካሄድ ዩኒቨርሲቲዎችንአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲከተሉእያደረጋቸው ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲ የሰው ልጅ በረዥም ታሪኩ ያከማቻቸውየአዕምሮ ውጤቶች ተጠብቀው የሚቀመጡበት፣ ለአዲሱ ትውልድ የሚተላለፉበትና በታሪክ ውስጥ የተነሱ ጥያቄዎች የሚፈተሹበት፣ የሚመለሱበት…ወዘተ ማዕከል ነው እንጂ የፖለቲካ አስተዳደሩ ወሳኝ ናቸው የሚላቸውን ጉዳዮች ብቻ እንግቦ የሚንቀሳቀስ ተቋም አይደለም፡፡ አንድ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ተልዕኮዬ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት ብቻ ነው›› የሚል ከሆነ ሕልውናውን እንደዩኒቨርሲቲ ያጣል፡፡ዩኒቨርሲቲ ዕውቀት ፈልገው የሚመጡት ተማሪዎች ማኅበረሰቡ ሊያቀርብላቸው ወይም ሊያስተምራቸው የማይችለውን ትምህርትና ተሞክሮ የሚቀስሙበት አምባም ነው፡፡
ዕንቁ፡-በዘመናችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ወይም የበላይነት የያዘው ትምህርት ፍልስፍና ምንድን ነው?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ወደ አሁኑ ዘመን የትምህርት ፍልስፍና በምንገባበት ጊዜ ብዙ ጸሐፍትአራት ዋና ዋና ንድፈ-ሃሳቦችን ያቀርባሉ፡፡የመጀመሪያው መሠረታዊነት ወይም ‘ፐረኒያሊዝም’ የሚባለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይኼን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ምሁራን እንደሚሉት የሰው ልጅ ተፈጥሮ (በየትኛውም ቦታ ቢኖር) ተመሳሳይ ነው፤ ዕውቀት የትም ቦታ አንድ አይነት ነው፡፡ስለሆነም የሚሰጠው ትምህርትም አንደ አይነት ወይም ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡የሰው ልጅ ምክንያታዊ እንስሳት ነው፤ ይህ ምክንያታዊነቱ ግን መኮትኮት አለበት፡፡የአስተማሪው ተቀዳሚ ሥራ ደግሞየሰውን ልጅ ምክንያታዊነት መኮትኮት ነው፡፡ትምህርት ዘለዓለማዊ የሆነ ዕውነትን የሚያስተምር ነው፤ ለኑሮ የሚያዘጋጀ መሳሪያምነው፤የሰው ልጅ ወሳኝ ወይም መሠረታዊ የሆኑ እንደሥነ-ጽሁፍ፣ ታሪክ፣ ሒሳብ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ-ጥበብ …ወዘ ትምህርቶችን መማር አለበት፡፡እንዲሁምተማሪዎች ያለፈውን (ሊቃውንትትተውት ያለፉትን) ዕውቀት መማርና መመርመር አለባቸው፡፡
ሁለተኛው፣አመለካከት ደግሞ ‘ፕሮግረሲቪዝም’ የሚባለው ነው፡፡ይኼን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ምሁራን እንደሚገልጹት፣ ትምህርት በየጊዜው እየጎለበተ የሚሄድ ነገር በመሆኑ መምህራን ራሳቸውን በዕውቀትና በማስተማር ዘዴ በየጊዜው ማሻሻልአለባቸው፤ትምህርት ራሱ ሕይወት ነው እንጂ ለሕይወት የሚደረግ ዝግጅት አይደለም፤ማወቅ ማለት መተንተንና የሕይወት ተሞክሯችንን መረዳት ማለት ነው፤ ትምህርት ከተማሪው ፍላጎት ጋር መዛመድ አለበት፤ ተማሪው ሌላ ሰው “ይህን ተማር” ስላለው ሳይሆን የሚፈልገውንና ለእርሱ አስፈላጊ የሆነውን ትምህርት ነው መማር ያለበት፤ዕውቀት ተፈላጊ የሚሆነውአንድ ነገር ልናደርግበት ስንችል ብቻ ነው፤የመምህሩ ሚና ማማከር እንጂ አቅጣጫ ማስያዝ አይደለም፤ ትምህርት ቤት ውድድርሳይሆን ትብብርና መደጋገፍየሚፈጠርበት ቦታ ነው፤ ነጻ የሆነ የሃሳብ ልውውጥ ሊፈጠር የሚችለው በዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡
ሦስተኛው፣ አመለካከት ‘ኢሴንሻሊዝም’ የሚባለው ሲሆን፣ አመለካከቱንየሚያራምዱ ምሁራን እንደሚሉት የሰው ልጅ ተምሯልየሚባለውመሠረታዊ የሆኑ ትምህርቶችን ሲያውቅ ነው፡፡ መማር ከፍተኛ ጥንካሬ የሚጠይቅ ነገር ነው፤መማር የማንፈልገውን የትምህርት ዓይነት መማርን ጭምር የሚያካትት ሲሆን ለመማር ደግሞ ‘ዲሲፕሊን’ በጣም አስፈላጊ ነው፤ትምህርት የሚሰጠው “ተማሪው ምን ይፈልጋል?” የሚለውን መሠረት አድርጎ ሳይሆን “ለተማሪው ምን ያስፈልገዋል?” የሚለውን ተከትሎ መሆን አለበት፡፡ ተማሪውየሚማረው የማይፈልገውን ትምህርት እንኳን ቢሆን በሂደት እየተማረ ሲሄድ ይወደዋል ብለው ያምናሉ፡፡የመማር ማስተማሩ ሂደት የሚያርፈውበአስተማሪው ላይ ነው፤ስለዚህ አስተማሪው ወሳኝ ነው፡፡ ትምህርት ሰዎችየውስጥ አቅማቸውን እንዲያወጡ የሚረዳ መሳሪያነው፡፡
አራተኛው፣ አመለካከት‘ሪኮንስትራክሽኒዝም’ይሰኛል፡፡ ትምህርት አዲስ የኅብረተሰብ ሥርዓት (social order) ለመፍጠር ማገልገል አለበት፤ ትምህርት ማኅበረሰቡን ለመለወጥና ለመሻሻልመዋል አለበት፤ ትምህርት የተሻለ የኑሮ ግብ የምንመታበት መሳሪያ ነው፤…ወዘተ የሚሉትን ሃሳቦች የሚያራምድ አመለካከት ነው፡፡
ዕንቁ፡-ከላይየተመለከትናቸውየትምህርትንድፈ-ሃሳቦች ከጥንታዊው እና ከአሁኑ ዘመን የኢትዮጵያ የትምህርትፍልስፍና ጋር እንዴት ይዛመዳሉ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ከሁሉ አስቀድሞ ይኼ ጥያቄ በጣም ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ለጥያቄውመልስ ለመስጠት ሦስት በዚሁ ጉዳይ ላይ የተጻፉ ድርሳናትንመመልከቱ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንደኛ የዛሬ 45 ዓመትገደማ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ በ“ውይይት” መጽሔት ላይ“የኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና” በሚል ርዕስ የጻፉት ጽሑፍ፣ ሁለተኛ፣የዶ/ር ሀይሉ ፉላስ “knowledge and Its Attainment in the Ethiopian context”(The Ethiopian Journal of Education June 1974 vol.7 no.1) የሚለው ጽሑፍና ሦስተኛ፣ዶ/ር ተሾመ ዋጋው የጻፉት“The Development of Higher Education and Social Change an Ethiopian Experience” (1990) የሚለው መጽሐፍበጣም ጠቃሚ ድርሳናት ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
እነኝህን ሦስቱን ድርሳናት በምናይበት ጊዜ፣ጥንታዊው የኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና ከላይ ‘ፐረኒያሊዝም’ ብለን ከጠቀስነው የትምህርት ፍልስፍና ጋር በእጅጉ የተዛመደመሆኑንእንረዳለን፡፡የጥንታዊ ኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና በመሠረታዊነትበክርስትና ወይም በእስልምና አስተምህሮት ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ስለእግዚአብሔር ጠባይ፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋራ ስላለው ግንኙነት፣ ስለዓለም አፈጣጠር ….ወዘተያለቀለት ወይም ዳግመኛ ምርምር የማይጠይቅና በቅዱሳን መጽሐፍት ላይ ተመርኩዞ የሚጠና ነው፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ከሃይማኖት አበው ጠቅሰው እንደጻፉት ‹‹ነአምን ዘእንበለ ተኅሥሦ››(ሳንመረምር ሚስጥራቸውን እንቀበላለን) የሚለው አባባል ይኼንን ነጥብ በሚገባ ያብራራዋል፡፡ይኼ አንደኛው አስተምህሮት ነው፡፡
ሁለተኛው፣ አስተምህሮት ዓለም በሁለት ነገሮች እንደተከፈለችው ሁሉሰውም በሁለት ነገሮች የተከፈለ ነው የሚለው ነው፡፡ የዓለም አከፋፈል ሰማያዊና ምድራዊ ሲሆን የሰው ልጅ አከፋፈል ደግሞ ነብስና ሥጋ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ሰማያዊ ዓለሙ ምድራዊ ዓለሙን እንደሚመራ ነብስ ደግሞ ሥጋን እንድትመራ ይጠበቃል፡፡የቀለም ትምህርት ዓላማው ቅዱሳት መጽሐፍትን እያስተማረ ለሚመጣው ዘለዓለማዊ ዓለም ማዘጋጀት ነው፡፡
ሦስተኛ፣ አስተምህሮት ደግሞ ይህች ዓለም አላፊና ጠፊ በመሆኗ ከንቱ ናት፤ ሰማያዊው ዓለም ግን ዘለዓለማዊ ደስታን ይሰጣል የሚለው ነው፡፡ይኼ እንግዲህ ቁሳዊ ብልጽግናንና ዕድገትንአያበረታታም፡፡ዶ/ር ኃይለገብርኤል ይኼን አስተሳሰብ በሚመለከትሲጽፉ ‹‹ባህላችን ቀለም ለተማረ ሰው ከእጅ ሠራተኛና ከገበሬ የበለጠ ደረጃ ሰጥቶታል›› ይላሉ፡፡
በኔ እምነት በአክሱም ዘመነ መንግሥት ትልቅ ቦታ የነበራቸው በቴክኒክ፣ በግንባታ/ምህንድስና፣ በልዩ ልዩየእደ-ጥበብ ሥራዎች …ወዘተ የተሰማሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ይሁን እንጂ ክርስትናና እስልምና ከሙጡ በኋላ ቀደም ሲል ትልቅ ቦታ ይሰጣቸው የነበሩት ተሽረው ካህናትና ኡለማዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ እንዲይዙ ተደርጓል፡፡ ምናልባት የአገሪቱ የቁሳዊ ሥልጣኔና ብልጽግናከአክሱም በኋላ ወደታች እየወረደ የመጣውከዚህ የዕሴት ለውጥ ጋር የተያያዘሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡
ለማጠቃለል፣የአገራችንም ሆነ የምዕራቡንዓለም የ‘ፐረኒያል’ አመለካከት ስንመለከትአንደኛ፣ሁለቱም ማለትም የኢትዮጵያው ቁዱሳን መጽሐፍትን፣ የምዕራቡ ዓለም ደግሞጥንታዊ የግሪክና የሮማውያን ድርሳናትን አይሻሩም፣ አይለወጡም፣ አይጠየቁም የሚሉ ናቸው፡፡ሁለቱም በመማር ማስተማሩሂደት ላይየአስተማሪው ድርሻ ትልቅ እንደሆነናአካላዊ ቅጣት ዋና የማስተማሪያ መሳሪያ እንደሆነም ይቀበላሉ፡፡በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ትምህርት ማለት መንፈሳዊና አዕምሯዊ ብቃትን ማዳበርነው፤ከሃይማኖትና ከባህል የተረከብነውን እውቀት እናጠናዋለን እንጂ ወደፊት ሌላ የዕውቀት ግኝት እናመጣለን በሚል ተስፋ ምርምር የምናካሄድበት ዘርፍ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡
አሁን ወዳለንበት የትምህርት ፍልስፍና በምንሄድበት ጊዜ ደግሞ፣ከ‘ኮንስታረክሽኒዝም’ና ከ‘ፕሮግረሲቪዝም’አስተሳሰቦች ጋራ የተዛመደ አመለካከት አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ትምህርት በይዘቱ ማኅበራዊ የኑሮ ደረጃን የሚለውጥ መሳሪያ ነው፤ማኅበረሰብን ከመለወጥ ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም፤በተጨማሪም የትምህርት ተቀዳሚ ትኩረት መሆን ያለበት በትምህርቱ ይዘት ላይ ሳይሆን ችግር ፈቺ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ጥያቄ ላይ ነው፤በመሆኑም የሚመረጠው የትምህርት ዓይነት የሚወሰነው የማኅበረሰቡን ችግር ይፈታል ወይስ አይፈታም ከሚል አስተሳሰብ በመነሳት ነው፡፡ ትምህርት ተማሪውን ያማከለና የተማሪውን አጠቃላይ ፍላጎት የሚያሟላ መሆን አለበት፤ የትምህርት ሥርዓቱ በየጊዜው እንዳስፈላጊነቱ መሻሻልና መለወጥ አለበት…ወዘተ የሚሉት አመለካከቶች ከወቅቱ የአገራችን የትምህርት ፍልስፍና ጋር በእጅጉ ይዛመዳሉ፡፡ወደአገራችንሁኔታ በምንመጣበት ጊዜ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ትምህርት የልማት አጋር በመሆን መንግሥት ያቀደውን የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ አስፈጻሚ መሆን አለበት የሚል አቋም ተይዟል፡፡
ዕንቁ፡-እስካሁን የተነጋገርንበትን ጉዳይ ማለትም ስለ ትምህርት ፍልስፍና ስለጥንታዊውና አሁን ስላለው የትምህርት ይዞታ በሚቀጥሉት ዕትሞቻችን ላይ በሰፊው እንቀጥላለን፡፡ ለአሁኑ የዛሬ ስድስት ወር ገደማ ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ዩኒቨርሲቲ መጥተው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ስለደሞዝ ጭማሪ የተናገሩት አስካሁን ድረስ በማነጋገር ላይ ያለ ጉዳይ ስለሆነየእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?የሚለውን ይግለጹልን፡፡
ዶ/ርዳኛቸው፡-ዩኒቨርሲቲ ከሕዝብም ሆነ ከፖለቲካ አመራሩ ክፍል የሚመጣ ሃሳብ የሚፈትሽበት፤ለማኅበረሰቡም ሆነለአስተዳደርክፍሉገንቢ አስተያየቶችንና አመለካከቶችን የሚቀርቡበት ተቋም ነው፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በተገላቢጦሹሃሳብና ምክር ይፈልቅበታል በሚባለው ተቋም ሹመኞች በተለያየ ምክንያት እየመጡ አስተማሪዎችን እየሰበሰቡ የሃሳብና የምክር አቅራቢነትሚናመጫወታቸው በጣም ያስገርማል፡፡በተለያየ ጊዜየዩኒቨርሲቲውን መምህራን እየሰበሰቡ ከኃይማኖት እስከልማት፣ከዕድገት እስከ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ …ወዘተ“አሰልጣኞች” ተመድበው “ሥልጠና” ሲሰጡቆይተዋል፡፡ ይህን ጉዳይ ይበልጥ ለማብራራት በቅርቡ አቶ ብርሃኑ አስረስ ከጻፉት መጽሐፍ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ከታህሳሱ ግርግር በኋላጀኔራል መንግሥቱ ነዋይተይዘው ፍርድቤት በቀረበቡበት ወቅት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠየቁ “የተናቀ መንደር ‘በምንትስ’ ይወረራል”ብለው የተረቱት ተረት ሁኔታውን በሚገባ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ሠልጣኝ የመንግሥት ሹመኞች አሰልጣኝ የሆኑበት ግቢ ሆኗል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን የደሞዝ አንሶናል ጥያቄውንሲመልሱ ‹‹እናንተ እውቀትና ክህሎት ያላችሁ በመሆናችሁ ከዩኒቨርሲቲው ውጪ ተንቀሳቅሳችሁ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ትላላችሁ››ብለው ነበር፡፡ መምህራንን ከተመደቡበት የማስተማር ውጪ ሌላ ተፎካካሪ ሥራ “ሥሩ”ብለውመምከራቸውና በመማር ማስተማርሂደቱ ላይ ጫና እንደሚፈጥር አለመገንዘባቸው አስገሞኛል፡፡መቼም ይኼ “ምክር” ለአብዛኞቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች አዲስ ነገር ሆኖ እንደማይገኝ ጥርጥርየለኝም፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን “ከማስተማር ውጪ በኮንሰልታንሲም ሆነ በልዩ ልዩ መንገድ ገንዘብ ይገኛል” ብሎ መንገር ለነብር “ሚዳቋ ወይምጥንቸል ትበላላች” ብሎ እንደመምከር ይሆናል፡፡
ደሞዝን በሚመለከት ከመምህራኑ ይበልጥ በጣም እየተጎዱ ያሉት የጥበቃ፣ የጽዳት፣ የካፍቴሪያና የአትክልተኛነት ሥራዎችን የሚሰሩት ሠራተኞች ናቸው፡፡እነኚህ ሠራተኞች የሚሰሩት ሥራ ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ ሆነ ሳለ የሚከፈላቸው ደሞዝ ግን እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ ሰባት እና ስምንትዓመታት ያህል ያገለገሉ ሠራተኞች ደሞዝ ይጨመርልናል ብለው ሲጠብቁ “ቋሚ አድርገናችኋል” በሚል ፈሊጥ የደሞዝ ቅነሳ ተደርጎባቸዋል፡፡ይኼ በእጅጉ የሚያሳዝንና ፍትሃዊነት የጎደለው እርምጃ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡በበኩሌ ዩኒቨርሲቲው አንጋፋና ትልቅ ተቋም እንደመሆኑ መጠንስሙንና ክብሩን በጠበቀ መልኩ ለእነኝህ ሰዎች ደህንነት አስቦ የደሞዝ ማስተካከያ ማድረግ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደጽዳት ሠራተኞች በምንሄድበት ጊዜ ደግሞ ያለው ችግር ተገቢ ደሞዝ ያለማግኘት ብቻ ሳይሆን ከጤንነትምጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ስለማቀርብ ለጊዜው በዚሁ ይብቃን፡፡

Tuesday, November 12, 2013

"ሙሰኞቹን አትንኳቸው! መንግስቴ የፀናችው በነሱ ነውና!"


በመሐመድ ሐሰን

(ኢትዮ-ምህዳር ላይ የወጣ)


ግዴላችሁም እመኑኝ ይህ ህዝብ የተዋጣለት ቀልደኛ ሆኗል፤ "አያውቅም" በሚል ጥቅል ፍረጃ ስናጣጥለው የከረምነው የኢትዮጵያ ህዝብ በብዙ ርቀት ጥሎን ሄዷል፤… ቀልደኛ በማድረጉ በኩልም አንድ ለሀገሪቱ የሆነው ብቸኛው እና ዝነኛው ቴሌቪዥን ጣቢያችን ቀዳሚውን ስፍራ ይወስዳል፡፡
የኢ.ቴ.ቪ "ጋዜጠኞች" እና በነሱ አማካኝነት ወደ ቴሌቪዥን መስኮቱ የሚመጡ ባለስልጣናት ያልተሳካ ፖለቲካዊ ተውኔት አልጥም (አልዋጥ) ያላቸው የጣቢያው ተመልካች የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ከሚተላለፍ አንድ ፕሮግራም ጀርባ የራሳቸውን ተውኔት፣ትንታኔ፣ቀልድ፣ፍተላ፣… ማቅረብ ከጀመሩ ሰነበተ፡፡… ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2006 ዓ፣ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሙስና ጋር በተያያዘ "የነቀዙ ህሊናዎች" በሚል "ዶክመንተሪ"ውን ያቀረበ እለትም ያስተዋልኩት ይህንኑ እውነት ነበር፤ እኔም ዛሬ ያስተዋልኩትን እውነት ላካፍላችሁ መርጫለው፡፡
ሐሙስ ምሽት እኔ የሙያ ነገር ሆኖብኝ፣ ወዳጆቼና ቤተሰቦቼ ደግሞ የኔ ፍላጎት ተጭኖባቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደ ልማዱ በከፍተኛ ትጋት ሲያስተዋውቀው የከረመውን "ዶክመንተሪ" ለመታደም ቁጭ ብለናል፤ ዛሬ እንዳጋጣሚ በቤቱ ውስጥ ያለው ሰው ብዛት ቤታችንን ዲሽ (ቪዲዮ) ቤት እስመስሎታል፤ ከወዳጆቼ አንዱ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በጣቢያው እና በርዕሱ ላይ ትችቱን መሰንዘር ጀመረ፡-
"እኔ የምለው? አንድ የነቀዘ ጣቢያ እንዴት ስለ ንቅዘት ማውራት ይቻለዋል?... አረ በናታችሁ እኛንም በፕሮፖጋንዳቸው ከማንቀዛቸው በፊት ጣቢያ ቀይሩልን!…" ሲል ምሬት ያየለበት አስተያየቱን ሰነዘረ፤ ሌላው ተከተለ፤
"ጋዜጠኞቹ እራሱ እኮ ይሄኔ ይህንን ፕሮግራም ለመስራት በቅድሚያ ሙስና በልተው ይሆናል፤… "… የውይይት አቅጣጫው መልኩን ቀይሮ ከፕሮግራሙ ይልቅ ፕሮግራሙን በትዕዛዝ የሰሩት የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰራተኞች ናዳ ይወርድባቸው ጀመር፤… ለተወሰነ ጊዜ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅቶች ውስጥ ይሰራ የነበረው ወዳጃችን እውነተኛ ያለውን ገጠመኝ ያካፍለን ጀመር፡-
"ጋዜጠኖቹ ሙሰኛ መሆናቸውን ትጠራጠራለህ እንዴ?... ህዝብ ከፍሎ በሚያስተዳድረው ጣቢያ ውስጥ ደሞዝ ተከፍሏቸው እየሰሩ፣ የህዝብን ጉዳይ እንዲዘግቡ ስንጠራቸው በስንት ልምምጥ መሰላቹ የምናሰራቸው?... ከካሜራ ማኑ ጀምሮ እስከ ሪፖርተሮቹ ድረስ ከሌላው ሚዲያ የተለየ ተጨማሪ አበል እንዲከፈላቸው ይፈልጋሉ፣ የተለየ እንክብካቤ ለምን አልተደረገልንም ብለው ይንጫነጫሉ፣ አበል እንደሌለው ካወቁ አይመጡልህም፣…ስንቱን ዘርዝሬ ልንገራችሁ? በቃ ባለስልጣን በሏቸው!"
የወዳጄ ንግግር እኔም በግል የታዘብኳቸውን እውነቶች አስታወሰኝ፤ እውነት ለመናገር የጣቢያው ሰራተኞች ካለባቸው ችግር ጥቂት ትዝብቱን ብቻ ነው ያጋራን፤… ኢ.ቴ.ቪ ካልተገኘ በሚል የተሰረዙ ስብሰባዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፤… በጣቢያው ውስጥ ቁጭ ብለው ፓርቲው  በሚሰፍርላቸው ቀለብ ታግዘው፣ የፓርቲውን ውዳሴ እና ጥቅማጥቅም ለማግኘት ምስል እየቆራረጡ "ዶክመንተሪ?" ብለው የሚያቀርቡ ሰዎችንም ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡… በዩፕሮግራሞች ላይ ግንባር እንዲያስመቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸውም በገዢው ፓርቲ ጸበል የተጠመቁት ናቸው፡፡…ከጣቢያው ጋር የተያያዙ ጉዶች ድርሳን ሊወጣቸው የሚችል ቢሆንም ወዳጆቼ አሁንም ውይይታቸውን ስላላቆሙ ላስቀድማቸው፤
"በደንብ ይግረማቹና ጋዜጠኞቹ ለፕሮግራሙ የሚሆናቸውን ሰው የመረጡት በምንም መመዘኛ ሳይሆን፣ በተለያየ የሙስና መንገድ ነው፤…" አለ ብዙ ጊዜ ከኢ.ቴ.ቪ ጋዜጠኞች ጋር እንደሚዝናና የሚያወራው ሌላኛው የቤታችን ታዳሚ፡፡
አሁን ፕሮግራሙ ሊጀመር ነው፤… የፈረንጅ ፊልም ለማየት መጥቶ፣ ክርክራችን ፕሮግራሙን የማየት መጠነኛ ጉጉት የፈጠረበት ቀልደኛው ጎረቤታችን፣ ፀጥታ ለማስፈን ሲል፡-
"እባካችሁ ዝም በሉ፤ ፕሮግራሙ ከጀመረ ቦሃላ፣ አይደለም እንደናንተ አይነት ፀረ-ልማት አስተያየት፣ ተራ ወሬ እንኳን ከሙሰኞቹ ተርታ ሊያሰልፈን ይችላል፤…አልያም የኢ.ቴ.ቪን ፕሮግራም ለማሰናከል የሞከሩ አሸባሪዎች የሚል ክስ ሊያስቀርብብን ይችላልና ፀጥ በሉ! ፌዴራል ፖሊስ በቆመጡ ፀጥ ከሚያሰኛቹ እኔ በምክሬ ብገስፃቹ ይሻላል፤" ብሎ ፕሮግራሙን ለማየት ወደ ቲቪው ከመዞሩ ማስታወቂያ ሲለቀቅ ተመለከተ፤ "ዶክመንተሪው" በስፖንሰር መታገዙ ነው እንግዲህ፤… ጎረቤታችን ተግሳፁን ሳይጨርስ ለሌላ ውይይት የሚጋብዝ አግራሞቱን ሰነዘረ፡-
"በለው! ላንቺም ‘ስፖንሰር?! ይህ ነው እንጂ የተዓማኒነት እመርታ!"… አንዱ አንዱን እየተከተለ ቀጠሉ፡፡                                                               
"አንተ ደግሞ፣ የሚከታተለው ቢጠፋ እንኳን እንደነ "ገመና" ምናምን በማስታወቂያ ሞቅ ደመቅ! ይበል እንጂ፤" አለ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ይሰራ የነበረው ጓዴ፤ 
"ግን ድርጅቶቹ ምን ለማትረፍ ነው እንዲህ ያለውን ደረቅ ፕሮግራም የሚያስተዋዉቁት?" ጎረቤቴ ጠየቀ፡፡
"እንዴ ምን ነካህ ጣቢያው እራሱ እኮ መንግስት ሆኗል፤ በመጀመሪያ በትህትና አጋርነትህን እንድታሳይ ይጠይቅሀል፤ ካንገራገርክ በሙስና ክስ ማስፈራራት ነው፤… ለነገሩ ያን ያህል መድከም አስፈላጊም ላይሆን ይችላል፤ የየተቋማት ሀላፊዎች እራሳቸው እንዲህ ያለውን የእጅ መንሻ ትብበር በማድረግ ከተጠያቂነት ማፈግፈግን እንደ አማራጭ ይጠቀሙበትም ይሆናል" በመጀመሪያ ትችት መሰንዘር የጀመረው ወዳጄ ነበር፡፡
አሁን ከ‘ስፖንሰሮቹ ማስታወቂያ ተመልሰናል! ፕሮግራሙም የምር ጀምሯል፤… በየፕሮግራሙ መሀል ማስታወቂያ እየገባ ባይረብሸኝም፣ በዙሪያዬ ያሉ ወዳጆቼ ግን በሰሙት እና ነገር ላይ ሁሉ ትንታኔ በመስጠት ከተመስጦዬ እያናጠቡኝ ነው፡፡…
በፕሮግራሙ የሆነ ደቂቃ ላይ ህይወት በአድሎዋ ሙስና የሰራችባቸው ጎልማሳ ብቅ ብለው ሙሰኞችን "...ጸረ-ልማት ናቸው፤…እኔ በልቼ የቀረው ይሙት የሚሉ… የውጪ ጠላት ይሻላል!..." ዓይነት አስተያየታቸውን ሲሰነዝሩ፣ የፍልስፍና መምህር የሆነው ወዳጄ አድናቆቱን መሰንዘር ጀመረ፤
"እውነትም እኮ ይህ ህዝብ ቅኔ ነው! አያችሁልኝ ባገኘው አጋጣሚ ባለስልጣናቱን ልክልካቸውን ሲነግራቸው?..." ጎረቤቴ በአስተያየቱ ግራ ተጋብቶ፡-
"የታሰረን ባለስልጣን ልክ ልኩን መንገር ምን ያስገርማል?" ሲል ጠየቀ፤ ለተናጋሪው አድናቆት የቸረው መምህሩ ወዳጄም፡
"ምን የታሰሩትን ብቻ አሁን ስልጣን ላይ ያሉትንም ሰዎች ልክ ልካቸውን እየነገራቸው ነው እንጂ!... ሙስና እኮ የስርዓቱ መገለጫ ነው፤ የደም ስር! ልትለው ትችላለህ፤ አሁን የሚያወሩትን ድራማ እንዳትሰማ፤ ሙስናን እንደሚሉት አከሰሙት ማለት አብረው ስርዓቱን ወደ መቃብር አወረዱት ማለት ነው፤… እንደውም አንድ ነገር ልንገርህ፤ እኔ እንደሚመስለኝ እንደውም፣ ከገዢው ፓርቲ ይፋ ያልሆኑ አስርቱ ትዕዛዛት አንዱ፣ ‹ሙሰኞቹን አትንኳቸው! መንግስቴ የፀናችው በነሱ ነውና!› የሚል ይመስለኛል፡፡"
ፕሮግራሙን በትጋት ለመከታተል የማደርገው ጥረት በሁለት መንገድ እየተሳካ አይደለም፤ አንድም ጓደኞቼ እያናጠቡ ሲያስቸግሩኝ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከፕሮግራሙ ይልቅ ጆሮዬ ወደ ወዳጆቼ ትንተና እየተሳበ አስቸግሮኛል፤ ህግ በመማር ላይ ያለው ወዳጄ የበኩሉን ማለት ቀጠለ፡-
"የፕሮግራሙ አዘጋጆችም ሆኑ ተሳታፊዎቹ ለመንግስት በመወገን በህጉም ላይ ጭምር ሙስና እየሰሩ ነው፤ እንዲህ ያለውን ያለፍርድ ቤት ውሳኔ የፍርድ ቤትን ስራ መስራት ለኢ.ቴ.ቪ ከተሰጠው ቆየ፤ ይህ ሁኔታ ከዚህ ቀደም በጋዜጠኞች፣ በፖለቲከኞች፣ በሙስሊሞች፣ እና ሌሎች  ክሶችም ላይ የታየ ነው፤…"
አማርኛ እና ትያትርን አጥንቶ የተመረቀው ወዳጄም፣ የህግ ተማሪው ወዳጄን ትንተና ተከትሎ ያስተዋለውን አከለ፡
"በነገራችን ላይ እኚህ ለምስክርነት የቀረቡት ሰዎች እራሱ የሙስና ክስ ያለባቸው ነው የሚመስሉት፤ በድንጋጤ ውስጥ ከመሆናቸው የተነሳ ቋንቋቸው የተሰናሰለ አይደለም፤ ሙስና የሚለውን ቃል በጥራት ለመጥራት የቸገራቸውን አስተውያለው፤ ንግግራቸው ሁሉ ባልተሳካ ቃለ ተውኔት የታጀበ ነው፤ ስለዚህ በቋንቋችን እና በተውኔት ላይ ጭምር ሙስና እየሰሩ ነው፡፡…"
ሟቹ ጠ/ሚኒስትር በ‘ስክሪኑ ላይ ገጭ ሲሉ፣ ውይይታችንን ይሰሙ ይመስል ሁሉም ፀጥ አለ፤ እሳቸውም አሉ፡ "...መንግስት አንድ እጁን ታስሮ ነው የሚታገለው፤ እጁም እግሩም ያልታሰረው ተራው ህዝብ ነው፤…" የሳቸውን ንግግር ተከትሎ ዳግም ፀጥታውን ጎረቤቴ አደፈረሰው፡
"የትኛውን ህዝብ ነው የሚሉት? ህዝቡ ነው እንጂ ካለሙስና አላሰራ ባሉት የስራ ሀላፊዎች እግር ከወርች የታሰረው እና በግድ የሙስና ተሳታፊ እንዲሆን የተገደደው፤… እዩት ደግሞ ይሄኛው መተባበር አለብን ይላል፤ ገዢዎቻችንን ለማጋለጥ መተባበር መጨረሻው ቃሊቲ ገብቶ መሰባበር መሆኑ አልገባውመ፤…"
ቲቪውንም ወዳጆቼንም ለመከታተል የማደርገው ጥረት እንደቀጠለ ነው፤…የጠ/ሚኒስትሩን አዳኝነት ሲመሰክሩ የነበሩ ሰዎች በአንድ ዶክመንተሪ ላይ አብረው በመሳተፍ ህልማቸውን አሳክተዋል፤ በጠ/ሚኒስትሩ ምጡቅነት ለናወዙ ልጆቻቸውም ይህ አጋጣሚ እንደ ጥሩ የምስራች የሚቆጠር ሳይሆን አይቀርም፤…
በዙሪያዬ የከበቡኝ ተንተኞች እየተዳከሙ ነው፤ የኢ.ቴ.ቪ ማጫወቻም ፕሮግራሙ ቋቅ ብሎት ይሁን ወይም ደግሞ መሀይም ነው ምንም አያውቅም ብለው የሚንቁት የኢትዮጵያ ህዝብ እርግማን ደርሶ ይሁን አላውቅም ፕሮግራሙ መቆራረጥ ጀመረ፤ ታዲያ በዚህ መሀል ተዳከሙ ካልኳቸው ጓደኞቼ አንደኛው "ደግሞ ከሰሞኑ ማን ላይ እርምጃ ሊወስዱ ይሆን?... እኔ ግን ሳስበው ሳስበው ከመብራት ሀይል ሰዎች ጋር ሳይቃቃሩ የቀሩ አይመስለኝም፤…" አለ፤ እሱን ተከትሎም ከመጠን በላይ የተለቀቀ ሀይል ቴሌቪዥኑን አቃጥሎበት፣በኛ ቤት ቴሌቪዥን ላይ ጥገኛ የሆነው ጎረቤታችን የረሳው ንዴቱ ብልጭ ብሎበት፡ "እነሱንማ ይበሏቸው! እነሱ በሙስና ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ በማሳቀቅ የሽብር!፣ የጥፋት!፣ የውድመት!...!! ወንጀል ነው መጠየቅ ያለባቸው፤ የሀገሪቱን ህዝብ ጨለማ ውስጥ እንዳኖሩት ሁሉ ጨለማ ክፍል ውስጥ ማሰር ነው!..." እያለ ብሶቱን አሰማ፡፡ ሁሉም እሱን ተከትለው ብሶታቸውን ሲግተለትሉ መብራት ሀይል እርግማኑን ለማብረድ በማሰብ ይመስላል መብራቱን አጠፋው፤ እኛም በያዝነው ወሬ ተመስጠን ፕሮግራሙ ይለቅ አይለቅ ሳናውቅ የመብራቱ መጥፋት ከትንታኔያችን ገታን፤ አንደኛውም እንዲህ ሲል አከለ፡ "አረ እናንተ ሰዎች ግዴላችሁም እኚ ሰዎች ሁሉ ነገራችንን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው እየሰሙን ሳይሆን አይቀርም፤"… በጨለማው ላይ የወዳጃችን የመጨረሻ ንግግር ስጋትን አክሎበት ተለያየን፡፡
እኔ ግን ፕሮግራሙንም፣ መብራቱንም፣ ወዳጆቼንም ሸኝቼ የፍልስፍና መምህሩ ወዳጄ "ሙሰኞቹን አትንኳቸው! መንግስቴ የፀናችው በነሱ ነውና!" ሲል ከሰነዘረው ሐሳብ ጋር ቀርቼ ሰሞኘኛውን የ "ኢትዮ-ምህዳር" ጉዳይ ከኢህአዴግ የሙስና እርምጃ ጋር ማሰላሰል ጀመርኩኝ፡፡
የ"ኢትዮ-ምህዳር" ጋዜጠኞች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ የደረሱባቸውን ክሶች፣ አደጋዎች፣ መጉላላቶች፣ እስር፣… ስንመለከት ምንጩ ይኽው የስርዓቱ ሙሰኞችን አይነኬነት ማሳያ ነው፤ በሙስና ላይ የምር ዘመቻ ማካሄድ አደጋ እንዳለው እና ሙሰኞችም ሀይ ባይ እንደሌላቸው፣ ከህግ በላይ እንደሆኑ እና እርስ  በርሳቸውም እንደሚፈራሩም ጭምር በግልጽ የታየበት ነው፡፡
በጋዜጣዋ ላይ ክስ ሊቀርብ ይችላል- ግድ የለም፤ ከህግ አግባብ ውጪ ከከተማ ከተማ እያዟዟሩ ማጉላላትን ምን ይሉታል?.. ይህንንም ይሁን ብለን እንለፍ፤ የአንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና ስራ አስኪያጅ ያለምንም ክስ በባለስልጣን ትዕዛዝ ጆሯቸው ተይዞ እንደ በግ ተወስደው ሁለትና ሶስት ቀናት እስር ቤት የሚታጎሩበት አካሄድ ምን ይነግረናል? ሀይ ባይ እንዴት አጡ? ማንስ ነው የሚናገራቸው? ከህግ ውጪ ያለውን እርምጃቸውንስ ማነው ያወገዘው? የማውገዝ ሞራል ያለው አካልስ ይኖር ይሆን? በሙስና ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃስ ምን ያህል እውነተኛ ነው?... የሚሉ በርካታ መሰል ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፤ ዞሮ ዞሮ ግን ሁኔታዎች ሁሉ የመምህሩን አባባል የሚያስረግጡ ይመስላሉ፤ "ሙሰኞቹን አትንኳቸው! መንግስቴ የፀናችው በነሱ ነውና!" … ከተነኩ እንግዲህ ከሰሞኑ እንዳስተዋልነው እንደ በግ በማንኛውም ተቆጣጣሪ በሌለው ባለስልጣን ትዕዛዝ እንደ በግ ተጎትቶ ከከተማ ከተማ መንከራተት፣ አልያም ያለጥያቄ መታጎር ነው፡፡
"ሙሰኞቹን አትንኳቸው! መንግስቴ የፀናችው በነሱ ነውና!"
ሀገሪቱ ላይ የተንሰራፋው የሙስና ስርዓት ህጋዊነትን የተላበሰ ይመስላል፤ ስርዓቱም ከላይ እስከ ታች በጉዳዬ ስለተዘፈቀ፣ "ዙፋኔን እስካልነቀነቅክ ድረስ ደሀ ሀብታም ሳትል ዝም ብለህ ጋጥ!" የሚል ውስጠ ደንብ እንዳለው ያስጠረጥራል፡፡…
ሀገሪቱ ላይ ከሙስና የጸዳ ሀብታም ማግኘት ህልም እየሆነ ነው፤ ከስርዓቱ ጋር እስከተስማሙ ድረስ ህጋዊነታቸው ይታወጅላቸዋል፤ የተኳረፉ ቀን ደግሞ የወንጀል መዝገባቸው ገለጥና ወደ ወህኒ ይወርዳሉ፤ ሁሉም እንዲህ ያለውን ማኖ እንዲነካ ይበረታታል፤ በስርዓቱ ላይ ፋውል የሰራ ቀን ወይም ሊሰራ ያሰበ ቀን ብዥሙ አንገቱ ላይ የገባው ገመድ ይጎተታል፡፡…
በቀደመው ስርዓት የሀብት መጠን ከፍ ባለ ቁጥር ስጋቱ የመወረስ ነበር፤ አሁን ግን ከታች እስከ ላይ ባሉ የስራ ሀላፊዎች የመጋጥ ስጋት ተቀይሯል፡፡…
አንድ ምርር ያለው ነጋዴ ከሰሞኑ እንዳለኝ ብዙ ሀላፊዎች ወንበር ላይ በተቀመጡ በወር እና በሁለት ወራቸው ከአናታቸው ላይ ቂቤ ይፈሳል፤ በአባዛኛው ዜጋ አናት ላይ ደግሞ እሳት ይንበለበላል፡፡
የኢህአዴግ መንግስት በሙስና ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ከመቀረፍ አቅም በላይ እንደሆነና ችግሩም ከግለሰቦች ይልቅ ስርዓታዊ እንደሆነ የሚያምኑ ምሁራን ቁጥር በርካታ ነው፤ ባለፈው አዋራ ያስነሳው የጉምሩክ ከፍተኛ ሀላፊዎች እስር ወቅት ከተጻፉ ድንቅ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ የዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ፅሁፍ ነው፤ ዶክተር "ከሕዝባዊ ታጋይነት ወደ ግለሰባዊ ሙሰኝነት" በሚል በ"አዲስ ጉዳይ" ላይ ባቀረበው ትንታኔ ላይ ይህንኑ እውነት የሚያረጋግጥ ነው፤ ዶክተር ዳኛቸው "አገሪቱ ላይ የሚስተዋለው ሙስና ሥርዐታዊ ነው ወይስ ከግለሰቦች የሞራል ግድፈት የመነጨ?" በሚል በሚሰነዝረው የመጀመሪያ ጥያቄው ላይ፡ "…ሙስና የግለሰብ የሞራል ድክመትንም የሚያሳይ ቢሆንም መነሻው ከሥርዐት ጋር በጣም የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡" ይላል፡፡ ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎችን አንስቶ ሰፋ ያለ ትንታኔ በሚሰጠው የዳኛቸው ጽሁፍ ውስጥ በርካታ እውነቶችን ግልጽ ብለው እናገኛል፤ እስኪ እኔ ለተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ማጠናከሪያ የሚሆኑኝን ነጥቦች ከጽሁፉ ውስጥ አለፍ አለፍ እያልኩ ልጥቀስ፡-
 …አሁን በአገራችን ያለውን ሁኔታ ስናይ “ሠርተህ ብላ” ሳይሆን “ተደራጅተህ ብላ” መሆኑን እንረዳለን፡፡
…ሀብት ለማፍራት ወደ ንግድ ዓለም መግባት አስፈላጊ መሆኑ ይቀርና ሰፊ የሀገር ሀብት ወደ ሚያስተዳድረው የመንግሥት መዋቅር መግባት አትራፊና የሀብት መንገድ ይሆናል፡፡
…መንግሥት እንደ ፊውዳል ሥርዐቱ የመሬት ባለቤትነቱን ካልተገፈፈ ሙስና ይጸዳል ብሎ መገመት ትልቅ የዋሕነት ይመስለናል፡፡
…በየትኛውም ዓለም እንደታየው ከፍ ያለ ንብረት አስተዳዳሪ የሆነ መንግሥት ከፍ ወዳለ ሙስና መውደቁ አይቀሬ መሆኑን እናስታውሳለን፡፡
…ማንኛውም ሥርዐት ሙስና ተንሰራፍቶበት ረዘም ላለ ጊዜ እያደገ በሚሔድበት ጊዜ ሥርዐቱ ፍጹማዊ እክልና ውድቀት እንዳይገጥመው አንዳንድ የእርማት እርምጃዎችን መውሰዱ አይቀሬ ነው፡፡
…ሙስና በአገራችን የፖለቲካ ሕይወት በራሱ የቆመ ነገር ሳይሆን ከሥርዐቱ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው፡፡ የኢህአዴግ አሁን የተጀመረው የ“ፀረ-ሙስና” እንቅስቃሴ መሠረታዊ ከሆነ የሥርዐት ለውጥ ውጪ የሚካሔድ ስለሆነ የምዝበራ ሂደቱን ትንሽ ሊያስታግሰው ይችል እንደሆነ ነው እንጂ በምንም መልኩ ሊቆጣጠረው አይችልም፡፡
…ኢህአዴግ በብዙኃኑ ስም ከመሬት ነጠቃ፣ ከቤት ማፍረስ፣ ከደመወዝ መቁረጥ፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ በፖሊስነት እንዲያገለግል በማድረግ፣ በቂ ካርታ የሌላቸው ወጣቶች ወደ ንግድ ዓለም ለመግባት ሲያስቡ በድርጅቱ እንዲታቀፉ ማስገደድ፣ ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው የሚወጡ ሥራ እንዲያገኙ የፓርቲ አባልነትን በመስፈርትነት ማስቀመጡ ከላይ ለጠቀስነው የግለሰብ መብት ረገጣ እንደማሳያ የሚቀርብ ሲሆን፣ በሌላም ሥርዐቱ በመንግሥትና በፓርቲ መሐል ልዩነት የማያውቅ ጠቅላይና አካታች (Totalize የሚያደርግ) መሆኑን ያሳየናል፡፡
…አንዳንድ የፖለቲካ ፈላስፎች እንዳሳሰቡት “ሥልጣን ያማስናል፤ ፍጹማዊ ሥልጣን ደግሞ ፍጹም ያማስናል” (Power Corrupts, Absolute power corrupts absolutely) ይህም የሥልጣን ብልግና በሙስና፣ በአድልዎ፣ በሞራል ዝቅጠት፣ በምዝበራ፣ በንዝህላልነትና በማንአለብኝነት ይገለፃል፡፡
ዳኛቸው ያነሳትን አንድ ምሳሌ እኔም የዘመኑን ሙሰኞች በደንብ የምትገልጽ ስለመሰለኝ፣ አስፍሪያት እንሰነባበት፤
….በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩ ዳኛ የመንግሥት ገንዘብ አጉድሎ የተከሰሰና በእርሳቸው ችሎት ቀርቦ ጥፋተኛነቱ ለተረጋገጠ ሰው የሠጡትን ተግሣጽ ልናጋራ እንወዳለን፡፡
ዳኛው ለተከሳሹ— “ሰማህ ወይ? የመንግሥት ገንዘብ ሲያዝ ልክ ለቡጢ እንደተዘጋጀ ሰው እጅህን ጭብጥ አድርገህ ትይዘዋለህ፡፡ ከዚያም እጅን ‘ጠበቅ ጠበቅ’ ስታደርገው ጨብጠህ ከያዝከው ነገር ‘ፊጪጭ ፊጪጭ’ እያለ የሚወጣውን ላስ ላስ ታደርጋለህ እንጂ እንደው በመንግሥት አገር እጅህን ከፍተህ ትገምጠዋለህ?” አሉት፡፡
አሁን የሚካሔደውን ምዝበራ በምናይበት ጊዜ የዳኛው ምክር ሕጋዊ ጥያቄ ሊያስነሣ ቢችልም ሲሆን የምየው ግን እርሳቸው እንዳሉት “በጠብታ የሚላስ” ሳይሆን “እጅ ተከፍቶ” የአገሪቱ ንብረት እየተገመጠ መሆኑን ነው፡፡

ኀሰሳ ስጋ
እልፍ ከሲታዎች ቀጥነው የሞገጉ
"ስጋችን የት ሄደ?" ብለው ሲፈልጉ
በየሸንተረሩ፣ በየጥጋጥጉ
አሥሠው አሥሠው በምድር በሰማይ
አገኙት ቦርጭ ሆኖ ባ‘ንድ ሰው ገላ ላይ፡፡
(በዕውቀቱ ስዩም- ኗሪ አልባ ጎጆዎች)

Wednesday, November 6, 2013

"ኢትዮ- ምህዳር" ጋዜጣ ቀጣዩ የኢህአዴግ ኢላማ?



ስራ አስኪያጁ እና ዋና አዘጋጁ አሁንም በእስር ላይ ናቸው


ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 11ቀን 2006 ዓ.ም የ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ አዘጋጆች እና ባለቤቶች የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባቀረበባቸው ክስ የተነሳ ሐዋሳ ድረስ በመሄድ ሊጉላሉና ስራቸው ሊስተጓጎል ችሏል፤ አዘጋጆቹ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተከፈተባቸው ክስ የተነሳ፣ ሐዋሳ ድረስ በመመላለስ ለተጨማሪ ስቃይ እና እንግልት መዳረጋቸው ቀጥሎ፣ ጋዜጣዋ ለገበያ በቀረበች ማግስት እለተ እሮብ ጥቅምት 20 ቀን 2006 ዓ.ም፣ የ‹‹የኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ አባላት (ስራ አስኪያጁ ሚሊዮን ደግነው፣ ዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ እና ከፍተኛ አዘጋጁ ኤፍሬም በየነ) በቀጠሯቸው መሰረት ሀዋሳ ቢገኙም፣ የተሰማው ዜና ግን የፍርድ ቤት ውሏቸውን ብቻ የሚያትት አልነበረም፤ ከወደ ሐዋሳ የተሰማው አሳዛኝ ወሬ ሶስቱ የ‹‹የኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ ባልበረቦችን ይዛ ትጓዝ የነበረችው ባጃጅ (ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሊሆን ይችላል በተባለው) የመገልበጥ አደጋ እንደደረሰባት የሚገልጽ ነበር፡፡
በወቅቱ የደረሰው አደጋ እና ከክሱ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ብዙዎችን ያነጋገረ ከመሆኑ ባለፈ፣ በኤፍሬም ላይ የደረሰው ከፍተኛ የጉዳት መጠን ግን ይበልጥ ልብን የሚሰብር ነበር፤ ሁለቱም እግሮቹ ምንም እንደማይንቀሳቀሱ ሰማን፤ በተጨማሪም የሳንባ ችግር ገጥሞት ወደ ማገገሚያ ክፍል መግባቱ ተወራ፤ እራሱን ችሎ በእግሩ መቆም ለተሳነው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ደግሞ እንዲህ ያለው ጉዳት ተጨማሪ የራስ ምታት ነው፤… ከትርፍ ይልቅ የቀጣዩን ህትምት የማተሚያ ቤት ክፍያ ለማሟላት ለሚፍጨረጨሩ የግል ፕሬሶች፣ በኤፍሬም ላይ የደረሰው አይነት ጉዳት እና ለውስብስብ ህክምናው የሚያስፈልገው ወጪ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› የሚሉትን ብሂል የሚያስታውስ ነው፡፡ እንዲህ ያለው እውነት የ ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች በርካታ የሀገሪቱ ነጻ ፕሬሶችም የሚጋሩት ነው፡፡
ጉዳዩ አሁንም በተለዋጭ ቀጠሮ ምክንያት መፍትሄ አላገኘም፤ ከአዲስ አበባ እስከ ሐዋሳ የተዘረጋው የ‹‹ኢትዮ-ምህዳር›› ጋዜጣ የክስ ሂደት እና መከራም አሁን ባለበት ሁኔታ የተቋጨ አይደለም፤ ክሱ በሀዋሳ መታየቱን እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱ ወስኖ ለህዳር 10 ቀጥሯቸዋል፤ ያኔ የሚመጣው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እና በሌሎች ባልደረቦቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለው ተጨማሪ ስቃይ እና እንግልትም ለፈጣሪ የሚተው ይመስላል፡፡  
ከዚህ ሁሉ ስቃይ ቦሃላ፣ ቅዳሜ እለት (ጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ.ም) ለቀጣዩ ስራቸው ወደ ቢሯቸው ጎራ ያሉት የጋዜጣዋ አዘጋጆች፣ ከወደ ለገጣፉ በመጣባቸው ሌላ ክስ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በእለቱ ሰድስት ኪሎ ስብሰባ ማዕከል አከባቢ ወደሚገኘው የጋዜጣዋ ዝግጅት ክፍል ዘው ብለው የገቡት ከለገጣፉ የመጡ ፖሊሶች እና ሌሎች ተባባሪዎቻቸው ጸሀፊዋን እና ሚሊዮንን ይዘው ሄደዋል፤  በወቅቱ ለስራ ጉዳይ ወጣ በማለቱ ከእስር የተረፈው ዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ ለቀጣዩ እትም መሯሯጥ ጀመረ፤ የጋዜጣውን ስራ ከጨረሰ ቦሃላም ሰኞ እለት ቃሉን ለመስጠት ባልደረባው ሚሊዮን ደግነው ወደታሰረበት ለገጣፉ ቢያመራም ለእስር ተዳርጓል፤ እስከ ቀጣዩ አርብም (ምናልባትም ከዛ በላይ) በእስር እንደሚቆይ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ሰኞ ቃሉን ሳይቀበሉ እንዳሳደሩት፣ እንዲሁም ማክሰኞ ቃሉን ሳይቀበሉት እንደዋለ የነገረኝ ጌታቸው፣ ማክሰኞ ቃሉን ሳይሰጥ በእስር ቤቱ በተሰየመው ግዚያዊ ችሎት ቀርቦ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀበት ቢሆንም፣ቦሃላ ላይ ግን አርብ (ጥቅምት 29) በሰንዳፋ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ታዟል፡፡ የጌታቸውን ጉዳይ የያዙት ፖሊስም ሳጅን ተፈሪ ሲሳይ ይባላሉ፡፡